የቀንበጥ የአንድ ዓመት ጉዞ እንደዋዛ?


እንኳን ደህና መጡልኝ
የቀንበጥ የአንድ
ዓመት ጉዞ እንደዋዛ?

„የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ
 ወራት ፈጠሪህን አስብ።“
መጽሐፈ መክብብ ፲፪ ቁጥር ፩

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
 01.05.2019
ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ


እንዴት ናችሁ የኔዎቹ ደህና ናችሁ ወይ?

ዛሬ ቀንበጥ ብሎግ ሥራ የጀመረችበት አንደኛ አመቷ ነው። ቀንበጥ ብሎግ በ2015 መጋቢት ላይ አደራጅቸው በዝምታ 3 ዓመት በሱባኤ ከቆዬች በኋዋላ ተስፋን ተከትሎ በትጋት የበኩልን ለማድረግ ቀለል ባለ መንፈስ ተግባሩን አህዱ ያለችው ልክ የዛሬ ዓመት ግንቦት 1.2018 ነበር።

ከቀደሙ ጹሑፎቼ ወደዚህ አርኬቡ ያሻገርኳቸው ጥቂት ጹሁፎች፤ ለህትምት ከበቁት ግጥሞቼ እና የወግ ገበታዎች ያከልኳቸው፤ እንዲሁም የጸሐፊ እና የተርጓሚ የአቶ መስፍን ማሞ ጹሑፍ አክሎ፤ በዋናነት አገራዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን አዳዲስ ጹሑፎችን ጨምሮ በዓመቱ ውስጥ ፖስት የተደረጉት ከግንቦት 1. 2018 እስከ ታህሳስ 2018 ድረስ 537 የህሊና ውጤቶች፤ ከጥር አንድ እስከ ሚዚያ 30 ቀን 2019 ድረስ ደግሞ 144 ጹሑፎች ፖስት ተደርገዋል። በድምሩ ከግንቦት አንድ 2018 እስከ ግንቦት አንድ 2019 ድረስ 681 ጹሑፎች ለንባብ በቅተዋል።

በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በአመዛኙ ድጋፋዊ አመክንዮዎችን፤ ከድጋፍም ወጣ ያሉ ወቀሳዎችን ያዘሉ ጹሑፎች ሲሰተናገዱ እኔ ባስበኩት ልክ ግን የአብይ ሌጋሲ ዝንባሌው አዎንታዊ መሆን በለመቻሉ አዝኛለሁኝ።

እኔ አብሶ በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ እኩል፤ ፍትሃዊ እና ተጠያቂነት ያለበት አያያዝ እጠብቅ ነበር። አብሶ ከመሰከረም 2018 ወር ጀምሮ ያሉ ነገሮች ግን ተስፋን የሚፈታተኑ ነበሩ ማለት ያስችለኛል። የአብይወለማ ሌጋሲ ከበቀልም፤ ከሴራም፤ ከ66ቱ አሉታዊ የፖለቲካ ትሩፋት ንክኪ ይኖረዋል ብዬም አላሰብኩም ነበር።

የተለዬ ሃሳብን፤ የተለዬ ዝንባሌን፤ አማራጭ ዕይታዎችን ለማስተናገድ የአብይወለማ ሌጋሲ ያሳዬው ቁርጠኝነት ከጠበቅኩት በታች ነው የሆነብኝ። ርህርህና፤ ደግነት፤ ሰብዕዊነትም እንዲሁ በጠበቅኩት ልክ አላገኘሁትም የአብይወለማ ሌጋሲ።

ቀንበጥ ተግባሯን እሀዱ ያለችው ጠብቃው የነበረችውን ሰብዕዊነት፤ ተፈጥሯዊነት ሙሉ መርሁ አድርጎ ይጓዛል ብዬ ያመንኩበትን ለማወአብይ ወይንም አብይወለማ መንፈስ ለመደገፍ፤ ለማገዝ፤ ክፍተቱን ለመሙለት፤ በትርጉም ለማቃናት፤ ግድፈቶችን፤ ስህተቶችን ደግሞ አይማረኝ ላልምርህ ብሎ ለመሞገት ነበር።

እንደ ዕድል ሆኖ ግን አብሶ እኩልነት ላይ ባለው ፍልስፍና አስደንጋጭ ነገሮች መከሰታቸው በትርጉም አቃንቶ ሙሉ አቅምን ለማፈሰስ ህሊናን የፈተነ ብቻ ሳይሆን የፈተለ ጊዜ ነበር ማለት እችላለሁኝ። ከሀምሌው ዝምታ በኋዋላ የማያቸው ነገሮች ሁሉ ተስፋን በተስፋው ልክ የማቆም አቅም ስስ ነበር።

የጠ/ሚር አብይ አህመድ ሆነ የዶር ለማ መገርሳ በተስፋ ውስጥ ጸንቶ እና ዘልቆ ለመቀጠል ያላቸው ቁርጠኝነት እና ሚዛናዊነት በተገባው ልክ አለመሆኑ አብሶ እንደ እኔ ላለ ቅን መንፈስ ውስጥን ክፉኛ የሚጎዳ ነበር። ባለመታደል ሐሤታችን በቅንቅን በመወረሩ እንደ ለመደብን ዛሬም ተስፋን ፍለጋ መመሳን ሆኗል ዕጣ ፈንታችን።

አብሶ የአቶ ለማ መገርሳ የዴሞግራፊ ፍልስፍና እጅግ የሚሰቀጥጥ ነገር በአገሬ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ታቅዶ መከወኑ ነገ ዳምኖ መምጣቱ ነጋሪ የማያስፈልገው ሀቅ ነው። ከመስከረም እስከ ግንቦት ያለው የአዲስ አበባ እና  የአካባቢው ነዋሪ የስጋት፤ የፍርሃት፤ የመኖር ዋስትና ማጣትም ለተስፋ ተስፈኛ ደንቀራ ሆኗል።

አንዲት አገር ርግጥ የሚያደርጋት ርዕሰ መዲና የአንድ አገር መንግሥት ተቀምጦ በቅጡ የት እና መቼ፤ እንዴት እና በምን ሁኔታ ህጋዊ እውቅና በሌለው አዬር ላይ ባለ ዝንቅ መንፈስ ኤሉሄ ኤሊሄ ማለቱ ዘመኑን ምጥ አድርጎታል። በዚህ ላይ በተጨማሪነት ደግሞ ከድጥ ወደ ማጡ እንዲሉ የ ኦፌኮን ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር እና የመድረኩም አባል የሆኑት የአቶ በቀለ ገርባ ሳጥናኤላዊ ኢ-  ሰብዐዊ፤ ኢ - ተፈጥሯዊ፤ ኢ - ወንጌላዊ፤ ኢ - ቁራናዊ ፍልስፍና ሲታከል በጠቃጠቆ ተስፋ አንዲዥጎረጎር አድርጎታል ዘመኑን።

በዚህም ላይ የኦሮሞ የፖለቲካ በኢትዮጵያ አሁን ባለው የሥልጣን አቅም የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ መቀጠሉ ሌላው የመከራ ዋይታ ሆኗል። ዛሬም ስለሞት ቀጣይነት፤ ከሞትም አሟሟቱ የከፋ፤ የሚዘገንን፤ የሚሰቀጥጥ የጭካኔ ነገር ሲታሰብ የትኛው ዘመን ይሆን እኛ ያለነው ያሰኛል።

ጠ/ሚር አብይ ሥልጣን ከተረከቡ ጊዜ በኋዋላ እንኳን ሚሊዮኖች መፈናቀላቸው ሺዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸው፤ ለተጎዱ ርዳታ ያለው ፍጥነት እና ቅንነት ሲታሰብ ተባደግ ሆነ እና ተስፋ አምሮ አለቀሰ።

እርግጥ ነው በቋሚነት የሚታዩ የ100 ቀናት ድንቅ ክንውኖች ዘለግ ባሉ ዓመታት የማይታሰቡ ግን ባጭር ጊዜ የተከወኑ፤ ባዶ ካዝና ተረከብው ይሄው ዓመቱንም እንደምንም ጥርስን ነክሶ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ፤ በማህበራዊ ኑሮ የቤተሰብ ለቤተሰብ ግንኙነት አብሶ ስደት ላይ የነበሩ ወገኖች ወደ አገር መግባታቸው የማይታዩ ረቂቅ ዎህታዎች ነበሩ። 

የዴፕሎማሲው ግኙነት ጥንካሬ እና ግብዕቱ በመልካም የሚታዩ ቢሆንም ይህን መልካም ጎን የሚጫኑ መታበዮች፤ መገለሎች፤ መጫኖች፤ ደግሞ ታይተዋል። ከሁሉ ደግሞ ኢትዮ ኤርትራ በመልካም ሁኔታ የመቆዬቱ እና የትግራይ ጉዳይ ሲታሰብ፤ የደቡብ ነገር ሲሰላ አትራፍባይ አጉዳይ የሆኑ ሁኔታዎችም አለበት።

የመደመሩ ማንፌስቶ ልበለው ፍልስፍና አላውቅም ሞቶ ልበለው ይሆን መሪ ቃል ደስታችን ሙሉ አላደረገውም። ወጋ ጠቀም ሆነ። የሲቃ ጊዜ ወይንም ግራጫማ ወቅት ብለው የሚሻል ይሆናል። በዚህ ሳቅ፤ በዛ ዕንባ።

እኔ እንደ ሌላው አይደለሁም ጥገናዊ ለውጥ ስለመሆኑ አሳምሬ አውቃለሁኝ። ጥገናዊ በመሆኑም ሥር ነቀል ለውጦች ስለምን አልመጡም አልልም። ለሥርነቀል ለውጥ ታግሎ የሚያሸንፍ አቅም ያለው የፖለቲካ ድርጅት ስላልነበረን የነፃነት ተጋድሏችን በቀጥታ ጥገኛ የሆነው በኢህዴግ የጥገናዊ ለውጥ ተስፋ ላይ ነው … ስለዚህ ራሱን አጥፍቶ የእኛን ፍላጎት መጠዬቁ ራሱ የሚያስኬድ አይሁንም።

አሳዛኙ ነገር አሁን እንዲያውም እኔ እንደማስተውለው የጥገናዊ ለውጡ ተስፋ ከኢህአዴግ ማዕቀፍ እዬወጣ ወደ ጃዋራዊው ወደ ዳውዳዊ ሚዛኑ እዬደፋ እንዳለ ነው እኔ የሚሰማኝ።

የቀደመውን የኦህዴድ መንፈስ እንኳን ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ያለነው። ሽግግር ሊባል የሚችለው ለእኔ እንደሚገባኝ ኦህዴድ እነዚያን ጣምራ የኦነጋውያን ፍላጎትን ቀስ እያደረገ እዬመዘዘ እያወጣ የሄደበትን የማለማመድ መንገድ ነው እያዬሁ ያለሁት … ያ ደግሞ ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም አደገኛ መንገድ ነው። ቀጣዩም ያለመሰከን አደጋ ተከታይ ነው ብዬ ነው እማስበው …

በዚህ ውስጥ የቀዳማዊት እመቤት ቢሮ ሰሞኑን ጭጭ ረጭ ቢልም መልካምነትን፤ ደግነት፤ ርህርህናን፤ እናትነትን ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ አይቸበታለሁኝ። ተስፋዬ ከዛ ላይ ሙሉዑ ነው። ኢትዮጵያም የምትድነው በዛ መንገድ ነው። እኩል የሆነ፤ ፍትሃዊ የሆነ፤ ሃይል እና ተግሳጽ የሌለበት፤ እልህ እና በቀል ያለዘለ፤ ተስፋን እርጋታ የተዋደደበት ርጉ መንፈስ አያለሁኝ። ይህ በመንግሥትም፤ በሃይማኖት ተቋማትም፤ በሲብክስ ድርጅቶችም ቢሰፍን የተሻለ ተስፋ ማድረግ ይቻል ነበር።

በሌላ በኩል መጋቢት አንድ ቀን የተከሰተው ሉላዊ የአውሮፕላን አደጋም ሌላው አስደንጋጭ ግን ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ጎልታ የወጣችበት አጋጣሚ ሲሆን በ150 ዓመቱ የአጤ ቴወድሮስ ቁንዳላ ወደ ቅደስት አገሩ መመለስም የነገን ባናውቅም መልካም ነገር ነበር።

ሌላው ስለመዝለቁ ብዙም እርግጠኛ ባያደርገንም ሴቶችን ወደ ፖለቲካው ወሳኝ ዘርፍ ለማምጣት የተሄደበት ሥር ነቀል እርምጃም ማለፊያ እና ወሸኔ የነበረ አመክንዮ ነበር።
የተፎካካሪ/ የተቀናቃኝ/ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ኢህዴግ ካለፈው በተሻለ ሁኔታ ለመቀራረብ የነበራቸው መሰተጋብር ከዘለቀ መልካም ነበር ማለት ልቻል። ነገር ግን የራስን ሚና ትቶ የገዢውን መንፈስ ማንቆለባበስ ሚዛን የለሽ፤ ራዕይ አልቦሽ፤ ግብየለሽ ተንሳፈፊ አድርጎታል ተስፋችነን።

በሌላ በኩል የአዲስ አባባን የባለቤትነት ጥያቄ ህምም የተሰማው የባልደረስ ንቅናቄ እንደ ቤታዊ ልጅ አለመታየቱ ደግሞ የሚያም ብቻ ሳይሆን ተስፋ በርቀት የተወረወረበት ጉዳይ ሆኖ እኔ በግሌ አግኝቸዋለሁኝ። አብሶ ከነፃነት ፈላጊው ወገን የተሰነዘረበት ትችት እና መገለል ጨለማን ፈቅዶ መቀበል ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ።

ሌላው ስጋት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ በተፈጥረው ልክ መንቀሰቃሰ፤ መከናወን ካለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ሰከን ብሎ ታይቷል። ይህም ስፖርታዊ ጨዋነት ከቀጠል ለዚህ በትንሹም በትልቁም ለሚበሳጨው አዬር ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይቻለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሚናው ያለዬው የሥነ ጥበብ አምክንዮ ግን በረጭታ ተውጦ ማዬቴ ነገን ተስፋ ለማድረግ አሉታዊ ጫና ፈጥሮበታል።

በግል ሚዲያ በኩል የሚታዬው ተሳትፎ እና ያለው አንፃራዊ ነፃነት አሁን ባለው ሁኔታ  ለእኔ ፍጽምና ስለማልጠብቅ ማለፊያ ነው፤ ከቀጠለ …

በሌላ በኩል በተያያዥ ግን የሰላም ሚ/ር ተልዕኮ እና ውጤቱ ሲለካ ደግሞ ዕንባ ለጠ/ሚር አብይ ሌጋሲ ዕንባ ከማዋጣት በዘለለ የተገባውን ያህል ድርሻውን አለመወጣቱን አስተውያለሁኝ። ራሱ ከሥም ባሻገር የተሻገረው የተግባር ልክ በተቀነስ ላይ ያለ ነው። ሌላው ቀርቶ አዋሳ ዛሬ የጥንቷ የለችም። መልሰን እንገኛታለን ለማለትም ዘግይቷል፤ በዛ ላይ ታቅዶ እዬተሠራ ያለ አሉታዊ ጉዳይም አለ ... 

አቅም በፈቀደ ሁኔታ ከሁለት ሳምንት ከየካቲት መጀመሪያ እስከ እኩሌታው ካለነበርኩበት ውጪ ያሉትን ጊዜያት ሁሉ ብሄራዊ፤ አልፎ አልፎ አለም አቀፍ ሁነቶችን በትትርና በባለቤትነት ስሜት ለመከወን ሞክሬያለሁኝ። አብዛኛው ለዋቢነት ዘሃበሻን እና ሳተናውን በድህረ ገጽ ደረጃ፤ በሚዲያ ሁሉንም የመንግሥትንም የግልንም ሚዲያ ተጠቀሚያለሁኝ። ፎቶ ጉጉል ሳተናው እና ዘሃበሻንም ተጠቀሚያለሁኝ። ዓመቱ እንዲህ ተከውኗል። 

ከሰነበትኵኝ መልካም ነገሮችን በመልካምነታቸው፤ ስጋቶቼን እንደመጠናቸው በመከታተል ለናንተ ለውዶቼ ለአክባሪዎቼ፤ ለቅኖቹ ታማኝ ታዳሚዎቼ አቀርባለሁኝ እውነትን ካለምንም ጥርጥር እና ይልዩኝታ እንደ ተፈጥሮው በመወገን። 

የኔ ውዶች፤ የእኔ ክብረቶች እንደ ወትሯችሁ ሁሉ ወደፊትም በሃሳብ ጦርነት ተስፋን በተስፋነቱ ይዘልቅ ዘንድ ሙሉ ትብብራችሁን ትሰጡኝ ዘንድ በታላቅ ትህትና በአክብሮትም እጠይቃለሁኝ። ኑሩልኝ።

ሉዑል አግዚአብሄር ጦርነት የሚባል ነገር አያሰማን።
የጦርነት ዘመን ያብቃልን! አሜን።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።