እንኳን ወደ ከበቡሽ
ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
በከበቡሽ
ቁራሽ
እንጀራ
በቢሆነኝ
ብራ
በሰብለ
ህይወት
አዝመራ
ለራህብ
የሚራራ።
„የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ
እንዳልጠግብ፣ እንዳልከዳህም“
(ምሳሌ 30 ቁጥር 8)
• ዕፍታ።
ዕለተ ማዕዶተ ተናኜ ፈንገጥ ያሉ ዕይታዎቼ የሚቀርቡበት ነው። የሃሳብ ቀን።
• የመኖሬ ፍልስፍና። ፍኖተ ካርታ ልንለው እንችላለን።
ህይወቴን እምመራበት በርካታ መርሆዎች አሉኝ። ዝርግነት አልወድም። ዝርግ ሰውም ክፍሌ አይደለም። ልሙጥነትም ተጠግቶኝ አያውቅም። ጠፍጣፋነትንም እጠዬፋለሁኝ። ውራጅ ሰብዕና የለኝም። ራሴን ተውሼም አልኖርኩም።
ልብ እንዲገጠምልኝ አልፈቅድም፤ ምን እንዳለኝ፤ ምን እንደምችል፤ ምን እንደሚፈቀደልኝ፤ ምን ደግሞ እንደማይፈቀደልኝ ጠንቅቄ አውቃለሁኝ። በሚገባ። እራሴ ተቋም ነኝ። ዝንቅ ያልሆነ ወጥ አሻረም አለኝ።
(1) መኖር ነፃነት ሊኖረው ይገባል ብዬ አምናለሁኝ።
(2) ለነፃነቱ ደግሞ መታመን።
(3) ለመታመኑ ተፈጥሯዊነት።
(4) ለተፈጥሯዊነቱ ጥሩ አስተዳዳሪነት።
(5) ለጥሩ አስተዳዳሪነቱ ጥሩ አድማጭነት።
(6) ለጥሩ አድማጭነት ጥሩ ዕውቅና።
(7) ለዕውቅናው ውስጥን ሳይሰስቱ ወይንም ሳይነፍጉ መስጠትን።
(8) መስጠትን በተሰጠው ልክ ሚዛኑን አስጠብቆ እራሰን ሳይሸሹ
ወይንም ከራስ ጋር ድብብቆሽ ሳይጫወቱ።
1)
በቅድሚያ ስለ ነፃነት።
ነፃነት ነፃነትን ይፈልጋል። ለነፃነት ነፃነት መስጠት የባለቤቱ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ አድዋ ግሎባል የነፃነት ክስተት ነው። አድዋ የነፃነት ክስተት ሆኖ ግን ነፃነቱን ተቀምቶ በኦዳ ሥርዕዎ መንግሥት ዘንድሮ አስተውለናል።
ስለዚህ የዓድዋ ነፃነት ለራሱ ነፃነት አልበቃም ማለት ነው።
ስለምን? አድዋ ክስተት እንጂ ሰው ስላልሆነ። ስለዚህም አድዋ ነፃነቴ ያለ ሰብዕና የዓድዋን ነፃነት በራሱ ውስጥ ማስከን ይጠይቀዋል። ምሳሌ አንድ ሰው ሌላውን ሊያፍቅር ይችላል። ማፍቀሩን ለአፍቃሪው ካልተናገረ የዓድዋ ነፃነት ተኗል ማለት ነው።
ወይንም ፈጣሪ ሲፈጠር የሰጠው ነፃነት ታግቷል ማለት ነው። ዓድዋ የሙሉ ጊዜ የህይወት፤ የመኖር፤ የሂደት፤ እራስን የማወቅ የነፃነት ዩንቨርስቲ ነውና።
በዚህ ሂደት ሃዲድ ሰርተን ለመኖር ነፃነቱን መሰጠት ይገባል።
መኖር ነፃነቱን ሲቀማ መኖር መቃብር ይወርዳል። ያለ እሱም እናንተም አብራችሁ ያላችሁ ሊመስላችሁ ይችላል። ግን ተላልፋችኋል። ለራሱ ነፃነት መሰጠት የተሳነው ሰብዕና ቤተሰቡን፤ አገሩን፤ ማህበራዊ ህይወቱን መምራት አይቻለውም።
መኖር በሰው ልጆች ቀመራዊ መዋቅሩ የሚደራጀው በነፃነት ልክ መሆን አለበት። መኖር ነፃነትን የሚፈለገው ከራሱ ለራሱ ነው። ለራሱ መኖር ነፃነት መስጠት የተሳነው ሰብዕና አልተፈጠረም።
·
የመኖር ነፃነት በተለያዬ መንገድ ይገለጣል።
·
መኖሬ ማልቀስ ካስፈለገው ማልቀስ ይኖርበታል። መሳቅን ከፈለገ ነፃነቱ ሊሰጠው ይገባል። መታገስ ካስፈለገውም እንደዛው። ማፍቀር ከተፈቀደለትም ያ ነፍስ ታድሏልና እና ሊገደብ አይገባም። መሳቅ፤
ማዘን፤ መታገስን፤ ማፍቀርን ብንውስድ የራሳቸው ማንነቶች አሏቸው።
የሚገርማችሁ በሃዘን ወቅት ለምሳሌ የማይካድራው ጭፍጨፋ ሊሆን ይችላል አዘንኩ ብሎ ነግሯችሁ ካሜራው ከእሱ ርቆ ሲመለስ ሲስቅ ታገኙታለችሁ፤ ወይንም ሲያሾፍ። ይህ ሰው ነጻነቱን እራሱ ቀምቶታል።
ያ አጀንዳ የእሱ ስላለሁነ እንደ ድንጋይ መጎለት አልነበረበትም።
ውስጡ አላዘነም እና። ማዘን ውስጥን ይጠይቃል ከደስታ በላይ። በሃዘን አጀንዳ መክለፍለፍ ለሃዘን የተሰጠውን ነፃነት መግፈፍም ማንነቱን መጫን ነው። ማዘን ማዘን ነው። ውስጥን በተመስጦ በሃዘን ውስጥ ማመሳጠር። በራስ ውስጥ መኖርን መፍቀድ።
ለዚህም ነው በሃዘን ጊዜ ሳቅ ሊመጣ የማይችለው። ሳቅ ቢመጣም ሃራም የሚባለው። ሃራም የምንለው እኛ ሳይሆን የተፈጠረበት የራሱ የማንነቱ የነፃነት ልክ ነው ለዛ ሃራም ፍትህ የሚበይንለት። ሌላ አንድ ምሳሌ ላንሳ። አንድ ሰው ለወዳጅነት ሊመጣ ይችላል። ሲመጣ እንኳን ደህና መጣህ አቀባበሉ እራሱ የነፃነት ቃና ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እሱ በመጣበት እግሩ ቢመለስ ነፃነቱ ነው።
እኔ ነፃነቱን ተጠቅሞ ለሚሄድ ሰው መልካም ጉዞ ነው ማለት ያለብኝ። ይህ „የመሄድ“ ነፃነት የእሱ የራሱ አንጡራ መብቱ ነው። መሄድ። እኔ መሄዱ ከጎዳኝ ግን እኔ ነፃነትን የእሱንም የእኔም ተጭኘዋለሁ ማለት ነው።
መምጣቱም መሄዱም በመኖሬ ውስጥ እኩል የተመጣጠነ አቅርቦት እንዲኖረው ማድረግ የማልችል ከሆነ እኔ ለ ራሴም ነፃነት አልሰጠሁትም፤ ለሌላም ለመስጠት ንፉግ ነኝ ማለት ነው። መኖሬም እራሴ በካቴና አስሬዋለሁኝ ማለት ነው።
3)
ለነፃነቱ መታመን።
እኔ ነፃነቴ ከእኔ ጋር ስለመሆኑ እማረጋግጠው፤ ነፃነቴም ከእኔ ጋር ስለመሆኑ ማህተሙ እኔ ለነፃነቴ ታማኝ ስሆን ብቻ ነው። ቀደም ብዬ ያነሳሁትን ምሳሌ ልድገመው። አንድ ወዳጄ ወደ እኔ መጣ። እኔም እንኳን ደህና መጣህ ብዬ ተቀበልኩት።
ስቀበለው ከተቀበልኩት ቅጽበት ጀምሮ መታመንን ተቀብዬ ነው እንኳን ደህና መጣህ እምለው። እንኳን ደህና መጣህ ለማለት ያበቃኝ ለመታመን የገባሁት የራሴ ፈቃዳዊ የህልና ውለ - ቀለበት ነው።
ለዬትኛውም ግንኙነት ይሁን ለአጭርም ለረጅምም ጊዜ ይሆን ያ ወዳጄ ከእኔ ጋር እስከቆዬበት ድረስ እኔ ለእሱ መታመንን መስጠት ግዴታ ነው። መታመኔን ካጓደልኩኝ ለመኖር የተሰጠኝን ነፃነት አጎሳቁለዋለሁኝ።
እኔም መለዬት ብፈልግ እራሴው መሄድን እወሰናለሁ ማለት ነው። እሱም ሊከፋ አይገባም። ነፃነቱን ፕራክቲስ ሊያደርገው ይገባልና። እኔ አሱ መጥቶ ሲሄድ ወይንም እኔ እሱን ሳሰናብተው ከተከፋሁኝ ለራሴም መኖር ታማኙ አይደለሁም ማለት ነው። ነፃነቴን ተጭኜዋለሁም ማለት ነው። ስለዚህ የ ዓድዋ ልጅም፤ የልዑል እግዚአብሔርም ልጅ አይደለሁም ማለት ነው። መተላለፍ።
ይህም ብቻ አይደለም ወዳጄ በአንድ ወቅት ትቶኝ ሊሄድ ይችል ይሆናል። ሲመጣም አንድ ቀን ጥሎኝ እንደሚሄድ አስቤ ነው እምቀበለው። ሲሄድ መልካም ጉዞ መመኜት ብቻ ሳይሆን አብረን በቆዬንባቸው ወቅታት አብረን የከወናቸው ማናቸውም የህይወት ሚስጢሮች፤ ጉዳዮች ሁሉ በመታመን ስለታመኑ እብድ የዘራው አዝመራ መሆን አይገባቸውም። የፈለገ ሁነት ይፈጠር።
እሱ እንኳን የህሊና ውሏችን ተላልፎ ቢዘረግፈው እኔ የዛ ሰለባ መሆን የለብኝም። ማዘንም የለብኝ። ካዘንኩኝ እኔ ለራሴ የሰጠሁት መታመንም፤ ነጻነትም ዝቅተኛ ነው ማለት ነው። እራስን መሸሸትም ነው።
ምክንያቱም እኔ የእኔ እንጂ የትውስት አይደለሁም እና። እኔ ውራጅ ሆኜ አልተፈጠርኩኝም። እኔ ሙሉ ሰብዕና ያለኝ፤ በተፈጥሮ ሙላት በፈጣሪዬ ፈቃድ የተፈጠርኩኝ ሰብዕ ነኝ። እኔ በእኔ ውስጥ መኖሩ የሚረጋገጠው መታመኔን እስከ ፍጻሜ ማረጋገጥ ስችል ብቻ ነው። ለራሴ ታማኝ መሆን።
ብዙ አብረው የቆዩ ሰብዕናወች ሲለያዩ ስንጥቅ የሚፈጥሩት በመኖር ፍልስፍና ውስጥ የራሳቸው የግዴታ ሰንጠረዥ ሊስት ስሌላቸው ነው።
አንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ላንሳ … በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ የኢንሳ ሠራተኝነት ተያይዘው የተፈጠሩ ሙሉ ግብግቦች ይህንን መርኽ ከመጣስ የመነጩ ናቸው።
ጊዜ ተጠብቆ ያ የበሰለ፤ ያ ያፈራ፤ የውስጥነት ሃዲድነት መናድ አይገባውም ነበር። የሰው ልጅ የራሱን መኖር የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ሳይኖረው ነው መንግሥት አገር የሚመራበት ፍኖተ ካርታ የለውም እዬተባለ የሚተቸው።
የሰው ልጅ ለመኖሩ እራሱ መርኽዊነትን አደራጅቶ መምራት አለበት። በነገራችን ላይ መታመን ለሰው ብቻ አይደለም፤ ለእንሰሳም፤ ለተፈጥሮም፤ ለአምክንዮም እኩል ነው ሊሰጥ የሚገባው። እኔ ለማምንበት አምክንዮ እስከ መጨረሻው መታመንን መመገብ ይኖርብኛል።
በስተቀር በመኖሬ ውስጥ ነፃነት፤ በነፃነት ውስጥ መታመን ውህዳዊነቱ ይከስላል። ጠቃጠቆ ወይንም በለቃም ይሆናል። ትልቁ የእኔ የህይወት መርህ መታመን ነው። መታመን ሲሶ፤ እርቦ፤ ንጥል፤ ቅርንጫፍ፤ ጭፍጫፊ አይደለም።
ሌላው ኩነት ፍጹም ላይሆን ይችላል እንደ ሰው አፈጣጠራችን። በመታመን ግን ፍጹም መታምን ግድ ነው። ብኩን መታመን ግጥሜ አይደለም። ሞተር ነው ለእኔ መታመን። ለመታመኑ ተፈጥሯዊነት። ተፈጥሯዊነት ቅብ ያልሆነ መቻል ማለት ነው።
ተፈጥሯዊነት ንጹህ ነው። አርቲፊሻል ሰዎች ለእኔ ሬሳ ናቸው። ቁመው ሲሄዱ ባያቸውም ለእኔ እሬሳ ቆሞ ሲሄድ ማዬት ማለት ነው። መታመኑ ንጹህ፤ የጸዳ፤ በጥቅማ ጥቅም ያልተበከለ፤ የወረት ያልሆነ፤ ቅጽበታዊ ያልሆነ፤ ቅምጥ ፍላጎት አሽኮኮ ያላደረገ፤ እንደ ተፈጥሮ መሆን የሚችል ባለመክሊቱ ርጉው ሙሉዑ መታመን ነው በዬትኛውም ሁኔታ ላዬውም፤ ላገኘውም፤ ልሆንበትም እምፈቅደው።
3. ለተፈጥሯዊነቱ ጥሩ አስተዳዳሪነት።
መኖር ካለ አስተዳዳሪ እረኛ አልበሾ መኖር ከብትነት ነው። ተፈጥሯዊነት እራስን ማስተዳደር ይጠይቃል። ማስተዳደር ማለት መደራጀት ነው። ሃሳብን - መኖርን - ፍላጎትን - ጉዞን - ዕለታትን በሚገባ ማደራጀት። ማደራጀት ያልተቻለ ነገር ማስተዳደር አይችልም።
ለማስተዳደር ሁሉም የመኖር ዓይነት ዶሴ ወይንም ፋይል ሊኖረው ይገባል። ተፈጥሮ እራሱ እኮ የተደራጀ ነው። እዩት የቀን እና የሌሊት መፈራራቅ፤ የበጋ፤ የክረምት፤ የሃገይ እና የበልግ የወቅታት ቅደመተከተል፤ ተፈጥሮ ፈጣሪ በሰራው ልክ ሂደቱን ጠብቆ እራሱን አደራጅቶ እራሱን በራሱ ያስተዳድራል።
የምንበጠብጠው እኛው ነን። ስለምን? እኛው እራሳችን ዝብርቅርቆች ስለሆን እንጂ ተፈጥሮ እራሱን በራሱ ለማስተዳደር በራሱ ማንነት ውስጥ ተደራጅቶ፤ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ይጓዛል። ደን ስንመነጥር ወይንም ስናቃጥል እኛው እንጂ እሱ እራሱን አያነድም።
እንዲያውም ከተቃጠለው ቦታ የተረፉት እንደገና አጨብጭበው ተነስተው እናያለን። ስለዚህ የሰው ልጅ እራሱን ለማስተዳደር የራሱ አስተዳደሪነትን አደራጅቶ መምራት ግድ ይለዋል። በስተቀር ውሎ ጉዞ የለሽ ድካም ነው የሚሆነው።
4. ለጥሩ አስተዳዳሪነት ጥሩ አድማጭነት።
አድማጭነት ጸጋ ነው። ከንግግር ጥብብ ሦስት መክሊቶች አንዱ አድማጭነት ነው። ጥሩ አድማጭ ብቁ አስተዳዳሪ እና ተናጋሪነት ይወጣዋል። በንግግር ጥበብ ውስጥ ሁለት ፒላሮች እንዳሉ ነው የሚነገረው። እኔ ነኝ ሦስት ያደረግኩት።
ተናጋሪ እና አድማጭ ሲሉ የንግግር ጥበብ መምህራን ይገልጣሉ። የንግግር ጥበብ መምህሬ መምህር አብንትም ያሰተማረኝ ሁለት ብቻ ብሎ ነው። እኔ ደግሞ በለመደብኝ ፈንጋጣ ባህሬዬ ሦስተኛውን አክላለሁኝ። እሱም ፊድባክ ወይንም ግብረ ምላሽን ነው።
ልክ በተውኔት ዓለም ሁለት ብቻ ናቸው ነው የምትለው ፕላኔታችን ትራጀዲ እና ኮሜዲ። እኔ ደግሞ በትራጀዲ እና በኮመዲ ማህል ሲቃ የሚባል አለ ባይ ነኝ። ዝንቅ የሆነ ስሜት የሚሰተናገድብት ሳቅ እና ዕንባ።
በጨለማ እና በብርሃን ማህልም ግራጫ የሚባል አለ ሊመሽ እና ሊነጋ ሲል ብዬ ፕላኔታችንንም በተጫማሪ የትበብ ሊቀ - ሊቃውንትን እሞግታለሁኝ።
ልክ እንደዛ በንግግር ጥበብ ውስጥም ተናጋሪ እና አድማጭ ብቻ ሳይሆን የሁለቱ ሊንክ ፈጣሪ ፊድባክ አለ። ስለዚህ ንግግር ጥበቡ በሦስት ይከፈላል ብዬ አምናለሁኝ። ይህ የራሴ ፍልስፍና ነው። በነገራችን ላይ ንግግር መክሊት ነው፤ ክህሎቱን በስልጠና ማምጣት ይቻላል።
ለአንድ ብቁ የተዋጣለት አስተዳዳሪ መሰረታዊው የስኬት ቁልፉ አድማጭነት ነው። መኖርን ማድመጥ ይገባል። ለማድመጥ መፍቅድ፤ ለፈቀዱት ብቁ አስተዳዳሪነትም አምጦ መወልድ ግድ ይላል።
ወደ ህይወቴ የሚመጣ ማንኛውም የመኖር አመክንዮ ሰብዕም ሊሆን ይችላል ለእኔ የሰጠኝን ዕድል በቅጡ ላስተዳድረው- አክብሬ ልመራው - ላደምጠው ይገባል።
ይህን ማድረግ ከተሳነኝ መኖርን ለማኖር የጎደለኝ ጥበብ አለ ማለት ይሆናል። የጠቅላይ ሚነሰትር አብይ አህመድ ያን የመሰለ በ ኢትዮጵያ ታሪክ የተገኜ ተቀባይነት ቤንዚን አርከፍክፈው አመድ ነው ያደረጉት። ለምን ብትሉ የማስተዳደር አቅመ ደሃ በመሆናቸው። ፍግፍግም።
5. ለጥሩ አድማጭነት ዕውቅና። መኖር እራሱ ዕውቅና ይሻል።
ዕውቅናው ምንጩ አቅምን መጥኖ ይነሳል። ነገርን ነገር ያነሳዋል ይላሉ እና ባለ ቅኔዎቹ ጎንደሬዎች አቅም በኢትዮጵያ ፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ የማያወቅ ነው። አስተዳዳሪም አግኝቶ አያውቅም።
ዕውቅና አድማጭ ካለገኜ፤ አድማጭም ዕውቅና ካለገኝ ፈሶ ይቀራል። ከላይ የምታንጠለጥሉት የፍቅር ዓይነት አድማጭነቱ ዕውቅና ካልተሰጠው ተራ ሆኖ አልባሌ ሆኖ መኖርን ሳያስጌጥ ባክኖ ሊቀር ይችላል።
የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪወች በሏቸው፤ መሪዎች የህዝብ ፍቅርን ከአቅም ቆጥረውት አያውቁም። ዕውቅና ሰጥቶ ያከበራቸውን በመቅጣት፤ በመበተን፤ ወይንም በመግደል ነው የሚታወቁት። ዕውቅና ለመስጠት ንፉግ ያልሆኑት ጀርመኖች ካላቸው ላይ ሲጨመር እንጂ ሲቀነስ አላዬሁም። ለዬትኛውም የህይወት ገጠመኝ ሉላዊ አድመጭም፤ ዕውቅና ሰጪም ናቸው ብልሆቹ ጀርመኖች።
.. እናም ተከብረው ያስከብራሉ፤ አስከብረው ይከበራሉ። አንድ ሰው አክብራችሁ ዕውቅና ስትሰጡት ከወንዝ ዳር የተገኜ አሽዋ ሊመስለው ይችላል። እኔ በሕይወቴ የገጠመኝ በኽረ ጉዳይ ይህ ነው። እኔም መገበሬን አላቆምም፤ እነሱም መሳታቸው አይቀርም።
ለምን ብትሉ ለህይወታቸው ፍልስፍናዊ መርህ አልነደፉለትም እና። ለዚህ ነው አልተግባብቶም የሆነው። አንዲት ሰዓት እዚህ ብዙ መዋዕለ ንዋይ ይፈስበታል። በነፃ የሚሰጠው ድጋፍ፤ ምስክርነት፤ ተጋድሎ ከዋጋ ቆጥሮት የሚያውቅ ነፍስ ገጥሞኝ አያውቅም። ሲያፈስው እንጂ። ቅጣትም አለበት። ግለትም አለበት።
6. ለዕውቅናው ውስጥን ሳይሰስቱ ወይንም ሳይሸሹ
ወይንም ሳያፈሱ ድርጊት ላይ መገኜት።
አሁን እኔን አክብረው ለሚያግዙኝ ወገኖቼ ሁሉ አመሰግናለሁኝ መደበኛ ተግባሬ የሆነው የመኖሬ ፍልስፍና ስለሆነ ነው። ላከበሩኝ ዕውቅና መስጠት። ሌላው ደክሜለት ይዝለለው እኔ ግን ውስጤ የፈጠረብኝን ስሜት ነፃነቱን - መታመኑን - ተፈጥሯዊነቱን - አድማጭነቱን - ዕውቅናውን ሳልነፍግ እከውናዋለሁኝ።
ሼር አድርጎልኝ ኖትፌኬሽኑ ከመጣልኝ ተከታትዬ አመሰግናለሁኝ አይቀርም። ሼር እራሴ አድርጌ ምስጋናም ወቀሳም ከመጣም መልስም ምስጋናም እልካለሁኝ። ለምን እራሴን ያሾለኩኝ፤ ወይንም ያፈሰስኩኝ ስላልሆንኩኝ።
7. መስጠትን በተሰጠው ልክ ሚዛኑን ማስጠበቅ።
እግዚአብሔር አምላክ የሰጠኝ ትልቁ ጸጋ ከሙሉ አካል ጋር ሰው አድርጎ ፈጥሮኛል። እኔን ስለሰጠኝም አምላኬ እጅግ አድርጌም አመሰግነዋለሁኝ። ይህም ብቻ ሳይሆን በልቤ ያተመልኝ ልዩ የዕውቀት ማህተም አለ። ስለዚህ በሰጠኝ ልክ ሳልሰስት፤ ሳልቆጥብ መልካም ነው ያልኩትን አጋራለሁኝ።
ደከመኝ፤ ሰለችኝ፤ ጉቦ፤ ጉርሻ፤ ክብር፤ ውዳሴ ከንቱ አልሻም። ሰው ሆኜ ስፈጠር ፈጣሪ ለሰጠኝ ስጦታ በልኩ መገኜት ግዴታዬ ነው። ሚዛኑን ሳያዛቡ የሰጠውን መሰጠት የህይወት ፍኖተ ካርታ ሊሆን ይገባል። ሚዛኑን አስጠብቆ መከወን የተሰጠኝን መተግበር የመኖሬ ፍልስፍና ነው።
ሌላም ምሳሌ ላንሳ ከእኔ ቤት እንግዳ ንጉሦም // ንግሥትም ናቸው። እንግድነቱን ከተቀበልኩኝ በተሰጠኝ ልክ አክብሬ በዛች የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ሙሉ አትኩሮት በተፈጥሯዊነት፤ ሙሉ መታመን በአድማጭነት ተከውኖ እንግዳዬ ደስታው// ደስታዋ ሳይሸራረፍ እንዲፈጠር አቅም በፈቀደው ልክ ይከወናል።
የተሰናዳው ምግብ ስለመስማማቱ፤ በጉዞ ደርሶ መልስ በገጠሙ ሁነቶች እኔ በመንፈስም በአካልም አብሬ እሆናለሁኝ። ስልክ መደወልም፤ ማንሳትም አልወድም። ከደወልኩ ወይንም ካነሳሁ ግን ከሌላ ደባል ሥራ ጋር ተከወኑ አያውቅም የስልክ ግንኙነቴ። ፈጽሞ! በተሰጠኝ ልክ በሚዛናዊነት በሙሉ አትኩሮት ሃሳቤ ሳይባክን የስልክ ግንኙነቴ ይሰተናገዳል። መሪዬን የማነጋጋኢር ያህል ነው የሚሰማኝ።
ብዙ ሰው ሌላ ሥራ እዬሠራ፤ ቲቪ እያዬ፤ ወይንም እያላመጠ ይሆናል ሰውን የሚያነጋግረው። እኔ ግን በሙሉ አድማጭነት፤ በሙሉ አትኩሮት፤ በሰከነ እና በረጋ ሁኔታ አዳምጣለሁኝ። ፍሬ ነገር ሳገኝ እጽፋለሁኝ። የተሰጠኝ አድማጭነት በልኩ በራሴ ላይ ገቢር እንዲሆን እፈቅዳለሁኝ።
8. መስጠትን በተሰጠው ልክ ሚዛኑን አስጠብቆ እራሰን
ሳይሸሹ ወይንም ከራስ ጋር ድብብቆሽ ሳይጫወቱ።
በመኖር ውስጥ የሚሰጥ ጸጋ አለ። ሰማያዊ ወይንም ገኃዳዊ። ሰማያዊ ሰው ሆኖ መፈጠር፤
መክሊት ሊሆን ይችላል። በገኃዳዊ ዓለም በትምህርት ቤት የሚገኝ የ ዕውቀት ዘርፍ ሊሆን ይችላል። ሰማያዊውም ምድራዊውም ስጦታ ማንነት
አላቸው። በማንነታቸው ውስጥ ዲስፕሊን አለ።
ያን ሳይተላለፉ መኖር ማለት ነው በተሰጠው ልክ ሚሳኑን አስጠብቆ እራስን ሳይሸሹ
ወይንም ከራስ ጋር ድብብቆሽ ሳይጫወቱ መኖር ማለት። አሁን ወ/ት ብርቱካን ሚዲቅሳ የህግ ሊቀ ሊቃውንት ናቸው። ሥልጣን ከያዙበት
ዕለት ጀምሮ የሚያሳዩት ድርጊት ግን በዕውቀት ያገኙትን ማንነት፤ ዲስፕሊን በጥሰት ቼ እያሉበት ነው።
ወ/ሮ ማዕዛ አሸናፊ የሰባዕዊ መብት ተቆርቋሪነታቸው ጉልህ ነበር ይባላል። ዛሬ ደግሞ
የአማራ ሊቃናት በኮሮናም፤ በልብ ህመም እንዲሞቱ ፈቅደዋል። በኦዳ የቀውስ ባጀት የታሰሩት፤ የተረሸኑት ላሳቸው ትክክል ነው። እኒህ
እህት በምድራዊውም በሰማያዊውም ዕውቅት ጸጋ ነበራቸው።
በተሰጣቸው መሆን ተስኗቸው ቀዝቅዘዋል። በርደዋል። ስለ ሚሊዮን የ የኢትዮጵያ ሴቶች
ስደት፤ እግዳ፤ መገደል፤ ስቃይ ማዬት፤ በጫካ፤ በድንኳን መውለድ፤ መታረድ ግድ አይላቸውም። እሳቸው ግድ የሚሰጣቸው የአለቃቸው ሰብዕና ግንባታ ብቻ ነው። ከተፈጥሯቸው ጋር ተረሳስተው ነው መኖራቸውን
እያኖሩት የሚገኙት ሁለቱም የዘመና ዖዳ ልዕልታን።
• መከወኛ።
ሲያዝን ማዘን፤ ሲስቅ መሳቅ፤ ሲራብ መራብ፤ ሲጠግብ መጥገብ፤
ማረፍ ሲፈለግ ማረፍ፤ ወዘተ ሁሉም ነፃነት መታመን፤ ተፈጥሯዊነት፤ አድማጭነት፤ አስተዳዳሪነት ዕውቅና፤ መስጠት ይጠይቃል። ይህን ማድረግ ነፃነትን ጥቅም ላይ ማዋል ነው። ነፃነቱን ሳያውቅ ኑሮ የሚያረጅ የሚያልፍም ይኖራል። ነፃነት ነው መኖርን ለያኖረው ሊያስጠብበው፤ ውብ፤ ማራኪ እና አጓጊ ሊያደርገው የሚችለውም።
አንድ ምሳሌ ላንሳ … ሰው ፍቅር ሲይዘው ባህሬው ሊለዋወጥ ይችላል። ህመምም፤ መቀበጥበጥም ሊመጣ ይችላል። ያን ቢያፍነው፤ ሊያደምጠው ባይፈቅድ የራሱንም የፍቅር ተፈጥሮን ነፃነት ዲስክርምኔት አድርጎበታል ማለት ነው።
ሌላ ገጠመኝ ላንሳ … በህይወቴ ያየሁት ዕውነተኛ ነፃነት ዳንስ ላይ ያለው ነፃነት ነው። ዳንስ ላይ ሙሉ አካል ነፃ ነው። በጣም ነፃ። ሙሉ መንፈስ ነፃ ነው። በጣም ነፃ። ስለዚህ እኔ ዳንስ የነፃነት ቅኔ ነው ማለት እችላለሁኝ። ከዮጋም ይበልጣል የዳንስ አርት ላይ ገቢር የሚሆነው ነፃነት።
በተለመደው ሁኔታ የምትሳቅቁበት ሁነት ሁሉ ዳንስ ስልጠና ላይ የለም ትረሱታለችሁ። ውስጣችሁ ፍርኃት፤ ስጋት አይኖርም። አዲስ ማንነት ነው ለዛች ሰዓት የሚኖራችሁ። መሬት ላይ ስትንከባለሉ የሚፈጠረው ሁነት ሁሉ አታስታውሱትም። የበለጠ የበዛ ቁጥብነት ይኑራችሁ በሃይማኖት ሆነ በአስተዳደግ።
አትኩሮታችሁ ዳንሱን ጥበቡን ከመቀበል፤ ከመቻል የተሸለ ሠርቶ ለመገኜት መታተር ብቻ ነው የሚታዬው። ካሜራ ቢኖር እንኳን ጉዳያችሁ አይሆንም። ነፃነቱ ልክ የለውም። ለዳንሰ አርት ታማኝነቱ፤ ለጥበቡ ዲስፕሊን አድማጭነት፤ ለዲስፕሊኑ የሚሰጠው ዕውቅና እራስን የመስጠት ጥልፋዊ ማንነት ብጡል ነው። መኖርን በዳንስ ህይወት እጅግ የበራ የፈካ ያደርገዋል።
ነፃነትም ትርጉም ላይ ይወላል። በዳንስ አርት ውስጥ ነፃነት መጸሐፉ ነው። ወይንም ካሪክለሙ። አይባቃም? በመኖሬ ውስጥ ሰዓት ማክብር፤ የበዛ ቁጥብነት፤ ሽሽግ ክድን ብሎ መኖር፤ ካለ ዕቅድ ምንም ነገር አለመቀበል፤ የሃሳብ ጊዜ መኖር፤ ወዘተ …
• ፎቶው አንድ የመጋዚን መደበኛ ስልጠና ላይ መምህሬ ያነሱኝ ነው።
ለህትምትም የበቃ ከጹሑፌ ጋርም የወጣ ፎቶ ነው።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergut©Selassie
17.03.2021
ጎዳናዬ የሃሳብ ልቅና ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ