#ቀናሁኝ! ኢትዮጵያ ትሰብበት! 2) እማ ሆይ! የአንችስ ቀንሽ መቼ ይሆን? የህሊና ስልጣኔ ያላስቀና ምን ያስቀናል?
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ከማግኔቱ የአሜሪካ 2024 የምርጫ ፋክክር እና ክወና አቮላዊ ሙቀት ሳንወጣ ሌላም መልካም ሂደት ለማዬት በቃን። እንዲህም ሆነ …… ከጉንፋኔ ጋር እዬታገልኩኝ #የሱማሌላንድን አጓጊ እና ሳቢ የምርጫ ፋክክር በተለያዩ ሚዲያወች ስከታተል ሰነበትኩኝ። ግን ማህበረ - ቅንነት እንዴት ሰነበታችሁልኝ???
60 ዓመት የባከነውን ጊዜ፤ ጉልበት፤ መንፈስ አሰብኩት። በፋይዳ የለሽ ብክነትም እያንዳንዳችን በግል ሁላችንም በጋራ #ብትለታችን ለዚህ መሰል ህዝበ ጠቀም አቅም አለመብቃቱ #አሳፈረኝ። ያቺ ትንሽ በቅኝ ግዛት የማቀቀች፤ እንደኛው ድሃ በሚባሉት ተርታ የምትገኝ የአህጉራችን ቤተኛ ሱማሌላንድ ለዚህ ክብር፤ ለዚህ ልዕልና፤ ለዚህ ልቅና መብቃቷ እጅግ ደነቀኝ። እጅግም አስቀናኝ። #ቅን የፖለቲካ #ሊቃውንት እና #ሊሂቃን ያላት መሆኗንም በጥልቀት አስተዋልኩ። ከዚህ ጋር ለሰባዕዊነት ያላቸውን አትኩሮትም ተማርኩበት። ለሰው ልጅ ሰውነቱን ከማክበር፤ ለዛም ከመጠንቀቅ በላይ ምን የመሪነት ዊዝደም አለና።
እንሆ ስልጡኖቹ የሱማሌላንድ ልጆች ተሳፋቸውን ሰንቀው፤ ተስፋቸውንም አሰልጥነው ጉዟቸውን በአብነት አስከበሩት። #ብርቱካኖች አሸነፋ። ብርቱካኖች ሲያሸንፋ በሰፋ ልዩነትም ነው። ገዢው ተሸናፊው ፓርቲም ሽንፈቱን ገና ሳያውቅ እኩል የፋክክር ሜዳ ፈቀደ። ይህ ልዕልና ስልጣኔ #የውሃ ልክም ነው። ሚዲያወች እኩል አገለገሉ። በመከባበር ላይ የታደመው ተፎካካሪ ህዝብ ግራ ቀኙን በጥሞና አዳመጠ። ቀኑ በጉጉት ተጠበቀ። ታዛቢወችም የደከሙበት ሂደት አፈራ። ማጭበርበር የለበትም።
ብልጠት አልታዬበትም። አቅም አቅሙን አስመሰከረ፤ አመሳጠረም። ይጨርስላቸው፤ አሜን። ከውስጡ ስልጣኔ የገባው ህዝብ ምርጫውን ለልዕልና አበቃ። ኮሽ ሳይል፤ ያለጉርምርምታ፤ ያለደምመፋሰስ፤ በፀጥታ፤ በንቃት፤ በትጋት ሥልጣኔ በዓቱን አገኜ።
ይህ ለአፍሪካ ቀንድ፤ ለምስራቅ አፍሪካ፤ ለአህጉራችን የተግባር #ዩንቨርስቲ ነው። እርግጥ ነው ይህን የተገበሩ የአፍሪካ አገራት ቢኖሩም የሱማሌላንዱ ግን ይለያል። የአገር ዕውቅና ያላገኜች ባተሌ።
ግን ተስፋን ሰንቃ ተስፋ ቆራጭነትን አንከባላ ትልቁን የሥልጣን ፋክክር በባዕቷ ዕውን ስታደርግ ካለ ፊት መዟዟር፤ ካለ የቀውስ ምርታማነት በአይናችን፤ በብሌናችን ተመለከትን። ይህን መሰል ባህል እና ብቃት ያሳዬው የሱማሌላንድ ሊሂቅ፤ ሊቃናት ምስጉን ናቸው። በተለይ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለው የተደሞ መጠን፤ የጥሞና ልክ፤ የአደቡ ሚዛን፤ የአቅሉ ልዕልና ወደርዬለሽ ነው።
ኢትዮጵያዊ ሊቅ ያው እንደሚታወቀው ዲግሪ ከሌለ አዋቂ የማይባልበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሊሂቁ ቦታም ስለለው፤ በለመብቱ ሊቃውንቱ ይህን እያዩ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? መኖራቸው፤ መማራቸው ( ማስተርሱ - ባችለሩ- ዶክተሬቱ- ፕሮፌሰርነቱ) የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው ዘመናቸውን ሁሉ መታከታቸው ሚዛን ላይ አስቀምጠው ምን ምላሽ እንዳገኙ ቢገመግሙት ጥሩ ይመስለኛል። ነገ የኢትዮጵያ ምርጫ እና እርግጫ ሲመጣም በእልቀት የለሹ ስያሜ አዳዲስ ፓርቲወች ባጉም ባጉም ይሉ ይሆናል። ያው የተለመደው ትዕይንት።
ከአንዱ ለቆ ወደ ሌላው፤ ከሌላው ለቆ ወደ አንዱ ሽርሽሩም የውሃ ጎዳና ነው። በዛ ውስጥ የተሰዋው፤ የተንገላታው ነፍስ ግን አስታዋሽ አልቦሽ ነው። ጠያቂ ተጠያቂም የለበትም። ይህም ብቻ አይደለም ውህደት፤ ጥምረት፤ ህብረት የሚሉም አዲስ ማህበር አይቀሬ ነው። አድሮ ጥጃነቴ ------ የጉም ሽንት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት ምስረታ እና የትውልድ እጨዳ።
መታሰሩ፤ መታፈኑ፤ መታገቱ፤ መገደሉ፤ ቀድመው የሚከወኑ ታቅዶ የሚፈፀም የገዢወች ትልም ነው። በጭንቀት፤ በውጥረት፤ በፍርሃት ይዋጥ ዘንድ ህዝብ ቀውስ ተደራጅቶ ይመራል። ቀውሱ -----:ቀውስን እያራባ ውድመት እና አመድነትም የዘመኑ የምርጫ ፖሊሲ ዓይነተኛ መገለጫወች ናቸው። የዚህ የአብይዝም መገለጫወች እነኝህ ናቸው። አፍ ባለው መቀባር ዕድሜ ዘመኑን ሱባኤ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ብክነቱ ለከንቱነት ነው።
ጊዜ ይሄዳል ይነጉዳል። ጊዜ ጥሎን መጪ ይላል። ኢትዮጵያ ግን በነፃነት ተፈጥራ ነፃነቷን ከአገሯ አልፋ ለሌሎችም መግባ ግን ህዝቧ #በትውስት ርዕዮት# በውራጅ ማኒፌስቶ፤ #በሴራ #ድራግ አሳሯን ዘመን ተዘመን ታያለች። ለብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች መተዳደሪያ ነው የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ። ዓላማውም - ተግባሩም፤ መብቱም ግዴታውም ሳይታወቅ ተወጥኖ ዓመታቱን ሳያከብር በሁለት ፍሬ ሰብዕናወች ተንጠልጥሎ ዘመኑን ሁሉ እንደ #ቆዘመ ገበርዲን እና ከረባቱን እንዳመለከ ይኖራል ወይ ይከስማል። ወይንም ይተናል።
ለዚህም ነው እኔ የፖለቲካ ድርጅት ለኢትዮጵያ ከተፈጥሯዋ ጋር ሊመጣጠን ስላልቻለ፤ መሥራቾችም በውጥን ስለሚጠናቀቁ፤ ወይንም የመድረክ ተንታኝነት ብቻ መደበኛ ተግባራቸው ሆኖ ለሥልጣን እና ለኃላፊነት በቅተው ሳይመዘኑ ዕድሜ ዘመናቸው በብክነት እና በእንግልትም የሚጠናቀቀው። ማን ከማን ይሻላል እንዳይባል ጉልበት፤ ጠበንጃ፤ ብልጥነት ጊዜ እያገኙ እንዲህ ዘመን ከዘመን ተስፋ ሰማይ ደጅ ብቻ የሚገኘው።
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሱማሌላንድ ሄደው ቢማሩ ጥሩ ይመስለኛል። ከመልካም ነገር ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኞች እያቀረቡ የሚያወያዩትም በሱማሌላንድ የምርጫ ተመክሮ #ወርክሾፕ፤ #ፓናል ዲስከሽን፤ #ሰሚናር ሊያዘጋጁ ይገባል ባይም ነኝ። ውጭ የሚኖሩትም በግልም በጋራም ወደ ሱማሌላንድ ሄደው ይህን ሥልጡን የህሊና ፀጋ #ቢቀስሙ ምኞቴ ነው።
አይዋ ብልጽግና እስቲ ጎራ በል እና ለመማር ሞካክር። ለምርጫ ቅስቀሳውን በተለዬ ስልት መጀመርህን፤ ጦርነቱም፤ የኮሪደር ፕሮጀክቱም፤ እሚሸኝም ከኖረ በድንገቴ፤ ቃጠሎም፦ መፈናቀል እና የህሊና ነቀላ እና ተከላው፤ ነባር ትውፊቶችን መገናኛቸውን መበጣጠሱንም፤ ጭንቀት አምራችነታቸው ታቅዶ ነው እዬተከወኑ የሚገኙት። ሰው ከቀዬው ሲነቀል፤ በድሮን ሲያልቅ #ምርጫ ምኑ ሆኖ ያስበው? መኖሩ እና ትንፋሹ ሰርክ ፍጥጫ ላይ ሆነው።
አለመታፈሩ የሚገርመኝ ምርጫ ይህን ጊዜ ቀርቶታል ሲባል ነው። መኖር በጨርቅ ተሿጥራ። ያ ምርጫ ሲካሄድ የነበረው የቀጠለው የቱ ነው? ትርምስምሱ፤ ሺግሽጉ፤ ስልጠናው፤ ዴሞግራፊው #አና ብሎ እዬተሰራበት። መርካቶ እንኳን ነዶ እስኪያልቅ ድረስ ሲኦል ሆኋል። ይህ ለቀጣዩ ምርጫ እዬተከወነ የሚገኝ ቅድመ መንገድ ጠረጋ ነው። አብይዝም ቀድሞ ትርምሱን ያጠናቅቅ እና ሰሞናተ ምርጫው በሰላም ተጠናቀቀ ይባላል። የሚገርመው በሳል የሚባሉ ፖለቲከኞች መሸነፋቸው ምንጩ ምን እንደ ሆን አይመረምሩትም። በሰላም ማለፋ አግራሞት እንደ ፈጠረባቸው ያወጉናል። ያው ወደ ለመዱት መደበኛ ሥራቸው ይመለሳሉ። ሚዲያ ላይ የፖለቲካ ትንታኔ።
በነገራችን ላይ "ብልጽግና" ቃሉ ጣፋጭ ነው። ሙሉ ተስፋን ይመግባል። እኔ ግን ከአብይዝም ወዲህ ተጠቅሜበት አላውቅም። በእሱ ትክ መለምለም፤ ማሰበል፤ መፋፋት፤ "መደመር" ይህም ቀመራዊ ቃል ውስጥ የወጣ ቢሆንም ለኢንተግሬሽን ውል ያለው ቁምነገር ነው። እኔ ግን አልጠቀምበትም። በዚህ ፈንታ ህብራዊነት፤ አብሮነት፤ መታከል ወዘተ እለዋለሁኝ። አማርኛ ቋንቋ ዲታ ነውና ብዙ አማራጮች አሉት። የሚቀናበትም ለዚህው ነው።
ሃሳብ ከቃል ይመነጫል። ቃሉ ለህዝብ ጠቀም ካልዋለ በአዘቦቱ ለመጠቀም #ይሰቀጥጣል። በድሮን ህዝብ እዬተጨፈጨፈ፤ እንሰሳት የዱር እና የቤት እዬነደዱ - እዬተሰደዱም፤ ዓውድማ ከእነ ቡቃያው አመድ ስንቁ እዬሆነ፤ በጥበብ፤ በፀሎት፤ በድዋ አንቱ ሆና የተፈጠረችን የአፍሪካ ህሊና አገር ኢትዮጵያ አፍርሶ የራሱን የስም ኢንፓየር ለመገንባት ጥድፊያ ላይ የሚገኝ የአብይዝም አገዛዝ "ብልጽግና፤ መደመር" እያለ ቧልቱን ሲተውን ቃሎቹ እራሳቸው #ግዞት ላይ እንዳሉ ይሰማኛል።
የሰለጠነው የሱማሌ ላንድ የምርጫ ዘመኑን ጠብቆ ያልተመቸውን ሲያሰናብት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያኖች ግን ይህን አንጋጦ ከማዬት በስተቀር ሌላ መንገድ የላቸውም። በሰላም መከወን የሚገባው በኽረ ጉዳይ ባሩድ፤ ቦንብ፤ ፈንጅ፤ ድሮን፦ ቃጠሎ፤ ነዲድ፤ ካቴና፤ እገታ ያነጋግርህ #ኮረጆህ ይህ ነው መባሉ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አፍርበታለሁኝ። እንደ ትጋቴም ለዚህ መሰል ጭካኔያዊ ዘመን ናፍቆት አልነበረም ቤተሰቤም እኔም የተገበርነው። እናም ሃዘኔ ጥልቅ ነው።
ሱልጡኑ ሱማሌላንድ ግን ብቀናባቸውም ግን አስደስተውኛል። ከውስጤ ነው የተደሰትኩት። ሰው መትረፍ አለበት። ታሪክ መቁሰል የለበትም። አደራም መታመም አይኖርበትም። የሰለጠነ ህሊና ከቅንጣቱ እስከ ገዘፈው ክስተት ድረስ ጥንቃቄ ያደርጋል። ይህ የሱማሌላንድ ቅን ፖለቲከኞች፤ እነሱ #ሊሂቃንንም ስለማይንቁ ባህላቸውን፤ አላሃቸውን ያከበሩ ለህጉ ለመገዛት የቆረጡ፤ የወሰኑ፤ በህይወቱ እዬኖሩ ያሉ ስለሆኑ ተምሳሌነታቸው ግዙፍ ነው። አርያነታቸውም ጉልላት ነው። የፖለቲካ ህይወታቸው ተቋም ነው።
ይህን የመሰለ ስልጡን ሊሂቅ// እና ሊቅ ያለው የሱማሌላንድ ህዝብ ለምን ሙሉ ነፃነቱ ለማግኜት አድማጭ አላገኜም??? ሱማሌ ራሱ ይህን ሂደት ቢያሟላ እኮ መለዬቱ ሳይሆን አንድነቱ ነው የበለጠ ለአቅም፤ ለጉልበት ብቁ የሚሆነው። እኔ በአዬሁት የምርጫ ነፃዊ ፋክክር እግዚአብሄር// አላህ ተስፋቸውን ያሳካ ዘንድ ምኞቴ ነው።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ሁሉን ሰጥቶን መሪ #ብልህ አጥቶ በነፃነት ራህብ ለሚገኘው ወገናችን ሱማሌላንድን አይተን፤ ቅንነታቸው በሥልጣኔ ውህደት ለስኬት መብቃታቸውን ስናስተውል መቅናት አወንታዊ ነው። ከህብራዊነት፤ ከውህዳዊነት፦ ከመተማመን፤ ከመፈቃቀድ፤ ከመተቃቀፍ በላይ ምን እንመኝ????
#ክወና።
1)ኢትዮጵያ ትሰብበት!
2) እማ ሆይ! የአንችስ ቀንሽ መቼ ይሆን?
ለአዲሱ የሱማሌላንድ መሪ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው እንደ አንድ ግሎባል ዜጋ እመኛለሁኝ። ሥላጣኑን ለሚያስረኩብት እጅግ ሥልጡን፤ ብልህ፤ ባለአደብ፤ ባለአቅል ለቀደሙት የሱማሌላንድ መሪም ያለኝን አክብሮት እያገለጽኩኝ ይህን አደባቸው ለግሎባሉ የሚያበረክቱበት ዕድል ቢመቻችም ምኞቴ ነው። አፍሪካም ብትሸልማቸው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergure©Selassie
21/11/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
የምርጫው ዘገባ ቢቢሲ አማርኛው ስለዘገበው ይህን ማንበቡ ይሻላል። እንዳልደጋግመው ብቻ ሳይሆን ውስጣችን መገምገም ስለሚያስፈልግ ነው በዛ ላይ ያተኮርኩት።
"የተመራጩ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ጋር ስለተፈረመው ስምምነት ምን ይላል? ተመራጩ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ)"
"በሶማሊላንድ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ አሸነፉ"
የፎቶው ባለመብት, Cabdiraxmaan Cirro
20 ህዳር 2024
ከሶማሊያ ተነጥላ ነፃ ሀገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ፤ ለአራተኛ ጊዜ ባደረገችው ምርጫ አዲስ ፕሬዝዳንት መርጣለች። በዚህ ምርጫ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሶማሊላንድን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሙሴ ቢሂ በተቃዋሚው ዋዳኒ ፓርቲ መሪ አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) ተሸንፈዋል።
የሶማሊላንድ ምርጫ ኮሚሽን ማክሰኞ፣ ኅዳር 10/2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ውጤት እንደሚያመለክተው ፕሬዝዳንት ቢሂ ከመራጮች ድምፅ ውስጥ ያገኙት 35 በመቶው ገደማውን ነው። የሶማሊላንድ ፓርላማ አፈ ጉባኤ የሆኑት ተቃዋሚው አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ደግሞ 64 በመቶው ገደማውን ድምፅ አግኝተዋል።
ከቢቢሲ ኒውስ ዴይ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የተመራጩ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ቃል አቀባይ ማህሙድ አደም ጃማ ጋላል፤ ምርጫው “ከፍተኛ ፉክክር” የታየበት ቢሆንም ሂደቱ “በተቃና ሁኔታ” መከናወኑን ተናግረዋል።
“በቀጣናው ከሚገኙ ብዙ ሀገራት” ከሚታየው የምርጫ ሂደት አንጻር የሶማሊላንዱ ምርጫ “እጅግ ነፃ እና ፍትሐዊ” እንደነበረም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
በቀጣናው ላይ ተፅዕኖ ያላቸው አሜሪካ እና ኢትዮጵያም የሶማሊላንድን ምርጫ አሞግሰዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 6/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ምርጫውን “ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ” ሲል አሞካሽቷል።
ሚኒስቴሩ ትናንት ማክሰኞ ከምርጫው ውጤት ይፋ መሆን በኋላ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ እና ተመራጩ ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) ላሳዩት “ምሳሌ የሚሆን ዲሞክራሲያዊ መሪነት” አድናቆቱን ችሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሞሐመድ አብዱላሂ በፕሬዝዳንትነት ለመመረጣቸውም “የእንኳን ደስ አለዎት” መልዕክቱን አስተላልፏል።
በሶማሊላንድ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይል እና ለንግድ የሚውል 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ከሶማሊላንድ በሊዝ እንድታገኝ የሚያደርግ ነው።
በምላሹ ደግሞ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ እንደ ሀገር እውቅና ላላገኘችው ሶማሊላንድ እውቅና ልትሰጥ እንደተስማማች የሐርጌሳ ባለሥልጣናት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የተስማማው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻን ለሶማሊላንድ ለመስጠት እና እንደ ሀገር እውቅና የመስጠቱን ጉዳይ “አጢኖ አቋም ለመያዝ” እንደሆነ አስታውቋል።
ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙበት ወቅት የመግባቢያ ሰነዱ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ወደሚሆን ስምምነት እንደሚቀየር ቢገለጽም፤ አንድ ዓመት ሊሞላው ቢቃረብም እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። በአንጻሩ የስምምነቱ መፈረም የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድን እንደ ግዛቷ አካል የምትቆጥረው ሶማሊያን ግንኙት አሻክሮታል።
መንገደኞችን በማጓጓዝ ቀዳሚዎቹ ግዙፍ አውሮፕላኖች የትኞቹ ናቸው?
20 ህዳር 2024
የንጽህና አጠባበቅን የቀየሩ አምስት አፍሪካዊ ፈጠራዎች
20 ህዳር 2024
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል “ሥራውን ለመሥራት” የተወካዮች ምክር ቤትን እገዛ ጠየቀ
19 ህዳር 2024
ተመራጩ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ)
የፎቶው ባለመብት, AFP
ተመራጩ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት፤ ፓርቲያቸው ስምምነቱን እንደሚገመግመው ተናግረው ነበር። ተመራጩ ፕሬዝዳንት የመግባቢያ ስምምነቱን ውድቅ አድርገው ባያውቁም ስለጉዳዩ ሲያወሩ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋን ይጠቀማሉ።
የተመራጩ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ስምምነቱን እንዴት እንደሚመለከተው ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ማህሙድ አደም፤ “ከቀድሞም ቢሆን አቋማችን አንድ ነው፤ ተመሳሳይ ሆኖ ይቆያል” ሲሉ ስምምነቱን የመገምገም ሀሳብ እንዳልተቀየረ አስረድተዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ፓርቲያቸው በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ጋር ስለተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት አስተያየት መስጠት እና መወያየት እንደማይችል አስታውቀዋል። ማህሙድ፤ አስተያየት ላለመስጠት በምክንያትነት የጠቀሱት “በሂደቱ ወቅት ስምምነቱ ለፓርቲው ያልተገለጸ” መሆኑን እና “ከዚያም በኋላ ፓርቲው ስምምነቱን አለመመልከቱን” ነው።
ቃል አቀባዩ፤ “በአጠቃላይ ግን ከጎረቤቶቻችን ጋር የሚደረግ ማንኛውም ፍትሐዊ እና የጋራ ተጠቃሚነት ትብብርን እንቀበላለን። በተለይ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ታላቅ አጋር እና ወዳጅ ነበረች። ወደ ሥራ ስንገባ ደግሞ ያለፈው መንግሥት የሠራውን እንገመግማለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
እስካሁን ድረስ እየተሸኘ ካለው የሶማሊላንድ መንግሥት ጋር ውይይት አለመደረጉን የገለጹት ማህሙድ፤ “እስከሚያውቁት ድረስ” ፓርቲያቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ንግግር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ይሁንና ፓርቲው እንደ ገዢው ፓርቲ ሁሉ የሶማሊላንድን እንደ ሀገር እውቅና የማግኘት ጥረት እንደሚያስቀድም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል። ፓርቲያቸው ሶማሊላንድ እንደ ሀገር እውቅና የሚያስገኝላት “አሳማኝ ምክንያት” አላት ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ፤ “እንደ ዋዳኒ ፓርቲ፤ ተመራጩ ፕሬዝዳንት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚመሠርቱት መንግሥት ይህንን ህልም እውን ለማድረግ፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ለመሳካት የምንችለውን ሁሉን እናደርጋለን” ብለዋል።
ተመራጩ ፕሬዝደንት በአውሮፓውያኑ በመጪው ታኅሣሥ አጋማሽ መንበረ ሥልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ