«በአማራ ክልል አራት ካምፖች “ለጅምላ ማሰሪያነት” መዋላቸውን አምነስቲ አስታወቀ
https://www.bbc.com/amharic/articles/ce9gxlvyyzro
«በአማራ ክልል አራት ካምፖች “ለጅምላ ማሰሪያነት” መዋላቸውን አምነስቲ አስታወቀ
በአማራ ክልል ለአንድ ወር በዘለቀው “የዘፈቀደ እስር” የተያዙ “በሺዎች የሚቆጠሩ” ነዋሪዎች በዳንግላ፣ ኮምቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች እንዲሁም በጭልጋ ወረዳ በሚገኙ ጊዜያዊ የእስር ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
አምነስቲ፤ “ኢትዮጵያ ለአገራዊ፣ ለአህጉራዊና ለዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ግዴታዎች ግድ የለሽ ወደመሆን አዲስ ምዕራፍ ገብታለች” ሲል ወቅሷል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህንን ያለው ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለውን “የዘፈቀደ እስር” በተመለከተ ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 27፤ 2017 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ባወጣው መግለጫው ነው።
ተቋሙ፤ በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን እስር እና የእስረኞች አያያዝ በተመለከተ ከእስር ካምፖች የወጡ ሰዎችን ጨምሮ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አካላት እንዳነጋገረ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
አምነስቲ፤ እስሩን አስመልክቶ ባደረገው ጥናት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ አራት የእስር ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ እንደደረሰበት አስታውቋል።
“አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባደረገው ጥናት፤ ግብረ ኃይሉ በመላው አማራ ክልል የሚገኙ አራት ጊዜያዊ የእስር ካምፖችን በሺዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መሙላቱን አረጋግጧል” ሲል በጥናቱ ደረሰበትን ገልጿል።
ከመስከረም ወር ጀምሮ በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለው “የዘፈቀደ እስር”፤ “በፖለቲካዊ” የፍርድ ቤት ጉዳዮች ላይ “የአስፈጻሚውን አካል ጣልቃ ገብነት የተቃወሙ” ዳኞች፣ አቃብያነ ህግንም ኢላማ ያደረገ እንደሆነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ምሁራንም ለእስር ከተዳረጉት መካከል ናቸው ተብሏል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም መግለጫ እንደሚያስረዳው “የጅምላ እስር” ከተፈጸመባቸው የእስር ካምፖች መካከል አንዱ የሚገኘው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ስር በምትገኘው ዳንግላ ከተማ ነው።
አምነስቲ ያነጋገራቸው ከዳንግላ የእስር ካምፕ የተለቀቁ አንድ ግለሰብ በካምፑ ውስጥ “ከ1,600 በላይ ታሳሪዎች” ይገኙ እንደነበር እና ተጨማሪ ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን እንደተናገሩ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
በዳንግላ ካምፕ የሚገኙ ቦታዎች በታሳሪዎች “በመጨናነቃቸው” ምክንያት ባለስልጣናቱ “ተጨማሪ የእስር ክፍሎችን በቆርቆሮ” እየገነቡ መሆኑንም ግለሰቡ ተናግረዋል ተብሏል።
አምነስቲ፤ ጥቅምት ላይ በካምፑ ውስጥ አዲስ ግንባታዎች መከናወኑን እንዳረጋገጠ በመግለጫው አስታውቋል።
የተቋሙ መግለጫ እንደሚያስረዳው በክልሉ ውስጥ እስር እየተፈጸመበት የሚገኘው ሌላኛው ቦታ በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ የሚገኘው “ጮሪሳ ወታደራዊ ካምፕ” ነው።
- በአማራ ክልል አዊ ዞን ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ6 ህዳር 2024
- መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች በግዳጅ ተሰውረው በእስር ላይ ከቆዩ ሰዎች መካከል ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ መኖራቸውን ኢሰመኮ ገለጸ23 ጥቅምት 2024
- በሁለት ሳምንት ውስጥ በአማራ ክልል 11 ዳኞች መታሰራቸው ተነገረ18 ጥቅምት 2024
በዚህ ካምፕ የሚገኙ ታሳሪዎችን የጎበኙ አንድ ግለሰብ በወታደራዊ ካምፑ ውስጥ “ቢያንስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረው” እንደተመለከቱ ተገልጿል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጭልጋ ወረዳ ሰራባ ከተማ ሌላ የእስር ካምፕ እንደሚገኝ የጠቀሰው የአምነስቲ መግለጫ፤ የአራተኛው ካምፕ መገኛ በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ እንደሆነም አስረድቷል።
እነዚህ ካምፖች “በአቅራቢያ ካሉ የተለዩ ዞኖች የሚመጡ ሰዎችን ለማሰር” እንደሚውሉ በመግለጫው ላይ ስፍሯል።
ባለስልጣናት በእነዚህ የካምፖች ውስጥ “የተሃድሶ ስልጠና” እየሰጡ መሆኑን ከምንጮቹ መስማቱን አምነስቲ ገልጿል።
አንድ የአይን እማኝ “የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ካምፑ ውስጥ ስልጠና ለመስጠት ሲዘጋጁ ተመልክቻለሁ” እንዳሉ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ሌላ የታሳሪ ቤተሰብ ደግሞ በእስር ላይ ያሉት ግለሰቦች “የተሃድሶ ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ እንደሚለቀቁ” እንደተገለጸላቸው መስማቱን ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ “ኢትዮጵያ ለአገራዊ፣ ለአህጉራዊና ለዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ግዴታዎች ግድ የለሽ ወደመሆን አዲስ ምዕራፍ ገብታለች” ሲል ወቅሷል።” ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ “የዘፈቀደ የጀምላ እስር ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን እንደ ፖለቲካዊ መሳሪያ” መዋሉን የተናገሩት የተቋሙ ቀጣናዊ ዳይሬክተር፤ ይህ ድርጊት አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጸመው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሽፋን በማድረግ” እንደሆነ ገልጸዋል።
ቲጌሬ፤ “አሁን በአማራ ክልል የታየ የያለው [ድርጊት] የጅምላ እና ዘፈደቀ እስር የዘወትር ስልት እየሆነ መምጣቱን ያሳያል” እንዳሉ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ