«የበሻር አል አሳድ እና ቤተሰባቸው ቀጣይ ሕይወት ምን ሊሆን ይችላል?» BBC.
https://www.bbc.com/amharic/articles/cjr2nl2p18go
«የበሻር አል አሳድ እና ቤተሰባቸው ቀጣይ ሕይወት ምን ሊሆን ይችላል?»
15 ታህሳስ 2024, 07:27 EAT
«ባለፈው ሳምንት እሁድ በሻር አል አሳድ ለ24 ዓመት የሙጢኝ ብለው ከያዙት ሥልጣን ሲወገዱ፣ የእርሳቸው የፕሬዝዳንትነት ዘመን ዶሴ ብቻ ሳይሆን፣ ቤተሰባቸው ከ50 ዓመታት በላይ ሶሪያን ሲገዛ የነበረው መዝገብ አቧራው ተራግፎ መነበብ ጀምሯል።
አሳድ በአውሮፓውያኑ 2000 መንበረ ሥልጣኑን ከመረከባቸው በፊት አባታቸው ሐፊዝ አል አሳድ አገሪቷን ለሦስት አስርታት መርተዋታል።
አሁን፣ በእስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሃያት ታህሪር-አል ሻም (ኤችቲኤስ) የሚመሩት አማፂያን የሽግግር መንግሥት የመሠረቱ ሲሆን፤ ከሥልጣን የተነሱት ፕሬዝዳንት፣ ባለቤታቸው እና የሦስት ልጆቻቸው የወደፊት መጻዒ ዕጣ ፈንታ አይታወቅም።
አሁን ከነቤተሰቦቻቸው በሩሲያ ጥገኝነት ጠይቀው የሚገኙት የቀድሞው የሶሪያ ፕሬዝዳንት ምን ይጠብቃቸዋል?
አሳድ ለምን ወደ ሩሲያ ሸሹ?
ሩሲያ በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ለአሳድ ጠንካራ አጋር የነበረች ሲሆን፣ በመካከለኛዋ ምሥራቅ አገር ሶሪያ ሁለት ቁልፍ የጦር ሰፈሮች አሏት።
በአውሮፓውያኑ 2015 ሩሲያ አሳድን በመደገፍ የአየር ጥቃት ዘመቻ የጀመረች ሲሆን፣ ይህም በጦር ሜዳ ያለው ድል ወደ መንግሥት እንዲያዘነብል አድርጎ ነበር።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ ሶሪያን በቅርበት የሚከታተል አንድ ቡድን እንደዘገበው በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ ብቻ 8,700 ሲቪሎችን ጨምሮ ከ21,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ነገር ግን፣ በዩክሬን እያካሄደችው ባለው ጦርነት ትኩረቷ የተከፋፈለው ሩሲያ የአሳድ መንግሥት በኅዳር ወር መገባደጃ ላይ በአማፂያኑ የተፈጸመበት መብረቃዊ ጥቃት እንዲቀለበስ ወይም እንዲቆም ለመርዳት ፈቃደኛ አልነበረችም ወይም አልቻለችም።
አማፂ ኃይሎች ደማስቆን ከተቆጣጠሩ ከሰዓታት በኋላ አሳድ እና ቤተሰባቸው ሞስኮ መግባታቸውን እና ጥገኝነት የሚሰጣቸው "በሰብዓዊነት" እንደሆነ የሩስያ መንግሥት ሚዲያ ዘግቧል።
ነገር ግን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት ጋዜጠኞች አሳድ የት እንዳሉ እና የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በተመለከተ ተጠይቀው "አሁን የምናገረው የለኝም. . . እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለ ውሳኔ [ጥገኝነት ስለመስጠት] ያለ ርዕሰ ብሔሩ ሊደረግ አይችልም። የርዕሰ ብሔሩ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
የአሳድ ቤተሰቦች ከሩሲያ በተለይም ከሞስኮ ጋር ያላቸው ግንኙነት በደንብ የተሰነደ ነው።
በ2019 ፋይናንሺያል ታይምስ ባደረገው ምርመራ የአሳድ ቤተሰብ በእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከሶሪያ እንዲወጣ ለማድረግ በሩሲያ ዋና ከተማ ቢያንስ 18 ቅንጡ አፓርታማዎችን ገዝተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የ22 ዓመቱ የአሳድ የበኩር ልጅ ሀፌዝ በሞስኮ የፒኤችዲ ተማሪ ነው።
በሳምንቱ መገባደጃ ላይ በተፈጠረው ትርምስ መካከል በሞስኮ የሚገኙ ባለሥልጣናት የሩሲያን የጦር ሰፈር እና የዲፕሎማቲክ ሚሲዮን ለመጠበቅ "ከሶሪያ ታጣቂ ተቃዋሚዎች" ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ 5 ታህሳስ 2024
- 'ቅብብሎሽ' ትላንት እና ዛሬን ማያያዣ ድልድይ . . .14 ታህሳስ 2024
- 'አልፀፀትም' በሚል ርዕስ መጽሐፍ የሚያስመርቀው ጃዋር መሐመድ የሚጸጽተው ነገር የለም?13 ታህሳስ 2024
የአሳድ ባለቤት እና ልጆች እነማን ናቸው?
አሳድ በምዕራብ ለንደን ከሶሪያ ቤተሰቦች የተወለደችውን እና የብሪታኒያ እና የሶሪያ ዜግነት ያላትን አስማን ነው ያገቡት።
የኢንቨስትመንት ባንክ ውስጥ ከመሥራቷ አስቀድሞ በለንደን ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲ ተምራለች።
አስማ በ2000 ወደ ሶርያ ሙሉ በሙሉ ጠቅልላ የመጣች ሲሆን፣ በሻር አል አሳድ ጋር የአባታቸውን መንበር በተረከቡበት ወቅት ጋብቻቸውን ፈጽመዋል።
በለንደን የኢኮኖሚክስ እና የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ነስሪን አልሬፋኢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አስማ "የብሪታኒያ ፓስፖርት ስላላት ወደዚያ ልትመለስ ትችላለች" ብለዋል።
"ይኹን እንጂ አሜሪካ በአባቷ በዶ/ር ፋዋዝ አል-አክራስ ላይ ማዕቀብ ጥላለች" ስለዚህም አስማ ሞስኮ መቆየት ትፈልግ ይሆናል ሲሉ አክለዋል።
ሜይል ኦንላይን ጎረቤቶቻቸውን ጠቅሶ ባሠራጨው ዘገባ የልብ ሐኪም የሆኑት የአስማ አባት እና እና የቀድሞ ዲፕሎማት እናቷ ሳሃር፣ ልጃቸውን እና ባለቤቷን "ለማጽናናት" ሞስኮ መቆየት ይፈልጋሉ ብሏል።
በሻረ አለ አሳድ እና ባለቤቱ አስማ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የሶርያው ፕሬዝዳንት ሀፌዝ አል አሳድ እና ባለቤታቸው አኒሳ በ1990 አካባቢ ከልጆቻቸው (ከግራ ወደ ቀኝ) ማሄር፣ባሽር፣ባሴል፣ ማጂድ፣ ቡሽራ ጋር
እኤአ በ2022 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለኮንግረስ ባቀረበው ሪፖርት በሥልጣን ላይ ለረዥም ዓመታት የቆየው የአሳድ ቤተሰብ፣ ምንም እንኳን ከአገር ውጪ በተለያዩ ዘርፎች እና ስያሜዎች የተሰወሩ ቢሆኑም፣ አጠቃላይ ሀብታቸው በ1 እና በ2 ቢሊዮን ዶላር መካከል ይሆናል ሲል ገምቷል።
በሪፖርቱ መሠረት በሻር እና አስማ "ከሶሪያ ታላላቅ የምጣኔ ሀብት ተዋናዮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት" የነበራቸው ሲሆን፣ ይህም "ድርጅቶቻቸውን በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ወደ ሕጋዊው መስመር ለማስገባት፣ በሥልጣን ላይ ለነበረው መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ" ይገለገሉበታል ብሎ ነበር።
በተጨማሪም አስማ "በሶሪያ የነበረውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ የሚከታተለው የኢኮኖሚ ኮሚቴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የነበራት ሲሆን በሶሪያ "የምግብ እና የነዳጅ ድጎማዎች፣ የንግድ እና የመገበያያ ገንዘብ ጉዳዮች" ላይ ቁልፍ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈች ተገልጿል።
አስማ 'የሶሪያ ትረስት ፎር ዴቨሎፕመንት' ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍ አብዛኛው ከባሕር ማዶ የሚገኝ ሰብዓዊ ዕርዳታ በመንግሥት በተያዙ አካባቢዎች መልሶ ግንባታ እንዲውሉ አድርጋለች ተብሏል።
በ2020 የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፣ አስማ በባለቤቷ እና በቤተሰቧ እገዛ "በሶሪያ ከጦርነት አትራፊዎች መካከል አንዷ እና ታዋቂዋ ሆናለች" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ሌላ ከፍተኛ የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣን ደግሞ እሷን "የቤተሰቡ የንግድ ሥራ ኃላፊ" ካሉ በኋላ፣ ከበሻር የአጎት ልጅ ራሚ ማክሉፍ ጋር የምትፎካከር "ቱጃር" ሲሉ ገልፀዋታል።
ራሚ ማክሉፍ ከሶሪያ ሀብታሞች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከአሳድ ቤተሰብ ጋር ያለው መቆራቆዝ፣ በተደጋጋሚ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚያጋራቸው መረጃዎች የተነሳ ከማንም የተሰወረ አልነበረም።
አሳድ ሕግ ፊት ሊቀርቡ ይችሉ ይሆን?
የአሳድ ሥርወ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ ሶሪያውያን "ተነግሮ የማያልቅ የሰው ልጅ ስቃይ ያስከተለ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ረገጣ" አሳልፈዋል ብለዋል።
ይህም "በኬሚካል የጦር መሳሪያዎች፣ በቦምቦች እና በሌሎች የጦር ወንጀሎች ጥቃቶችን እንዲሁም ግድያ፣ ማሰቃየት፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ አስገድዶ መሰወርን እና ማጥፋትን" ያጠቃልላል።
የዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመጣስ እና በከባድ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የተጠረጠሩ ሰዎች ለሕግ እንዲቀርቡ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጠይቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት የሶሪያ እስላማዊ አማፂ ቡድን ከሥልጣን የተወገደው አገዛዝ ባለሥልጣናት የሆኑ እና የፖለቲካ እስረኞችን በማሰቃየት ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦችን ስም ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የ'ሶሪያ ሳልቬሽን' መንግሥት መሪ የሆኑት አቡ መሐመድ አል ጆላኒ፣ ወደ ሌላ አገር የሸሹ ባለሥልጣናት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
በፈረንሳይ የሕግ ባለሙያዎች፣ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በሶሪያ ከደረሰው የኬሚካል ጥቃት ጋር በተያያዘ፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች ውስጥ ተባባሪ በመሆን አሳድ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሩሲያ አንድ ሰው በተጠረጠረበት ወንጀል ለፍርድ እንዲቀርብ ወደ ሌላ አገር ወይም ግዛት ተላልፎ እንዲሰጥ አታደርግም።
በተጨማሪም በሻር አል አሳድ ሩሲያን ወጥተው ለሶሪያ ተላልፈው ሊሰጡበት ወደሚችሉበት ወይም ሌላ በወንጀል ሊከሰሱበተ ወደሚችሉበት አገር ይሄዳል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው።»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ