እንዲህ እንደ ጨው ዘር መበተናችን እኮ ጥቃት ነው። እዛም መከራ ተሰዶም መከራ። ግን የተሻለ ዜና ነው። "በምያንማር የወንጀል ካምፖች ተይዘው የነበሩ 138 ኢትዮጵያውያን ተለቀቁ" BBC
"በምያንማር የወንጀል ካምፖች ተይዘው የነበሩ 138 ኢትዮጵያውያን ተለቀቁ"
https://www.bbc.com/amharic/articles/c805zvpjnlgo
"በምያንማር በሚገኙ የሳይበር ወንጀል ካምፖች በግዳጅ ሠራተኝነት ተይዘው የነበሩ 138 ኢትዮጵያውያን ተለቅቀው ወደ ታይላንድ መግባታቸውን በሀገሪቱ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ አማርኛ ተናገሩ።
የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ብዛት 138 እንደሆነ ለቢቢሲ ያረጋገጠው በሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ አስፈላጊው ሰነድ ተሟልቶላቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደሚደረግ ገልጿል።
በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ምያንማር ብዛት ያላቸው የሳይበር (የበይነ መረብ) ማጭበርበር የሚከናወንባቸው ካምፖች የሚገኙባት ሀገር ነች።
በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቢያንስ 154 ግቢዎች ውስጥ የሚፈጸሙት የማጭበርበር ወንጀሎች በአብዛኛው የሚከናወኑት "የሥራ ዕድል ታገኛላችሁ" በሚል ተታልለው በግዳጅ ለዚህ ድርጊት በተዳረጉ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ነው።
ከእነዚህ ዜጎች መካከልም ታይላንድ ውስጥ ሥራ ታገኛታችሁ በሚል ተታልለው ወደ ምያንማር የተወሰዱ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል።
የኢትዮጵያውያኑ ተጎጂዎች ወላጆች ኮሚቴ 300 ገደማ ኢትዮጵያውያንን ስም የመዘገበ ሲሆን፣ አጠቃላይ በተለያዩ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር "ሦስት ሺህ ይደርሳል" ተብሎ እንደሚገመት ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያውያኑ መደብደብ እና በኤሌክትሪክ ሾክ መደረግን ጨምሮ የተለያዩ የማሰቃየት ቅጣቶች ይፈጸሙባቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን ከእነዚህ ካምፖች ለማስወጣት ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን ከምያንማር መንግሥት ጋር ንግግር እያደረገ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር።
ምያንማር በሚገኙ እነዚህ ካምፖች ውስጥ የነበሩ 260 የውጭ ሀገር ዜጎች ትናንት ረቡዕ የካቲት 5/2017 ዓ.ም. ከሰዓት ተለቅቀው አጎራባች ወደ ሆነችው ታይላንድ ገብተዋል።
ከ19 ሀገራት ከተወጣጡት ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ከግማሽ በላዩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በታይላንድ የሚገኙ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከምንጮች የተገኘው የታይላንድ መንግሥት የውጭ ሀገራት ዜጎች ዝርዝር መረጃ እንደሚያሳየው፤ ከ260ዎቹ ተመላሾች መካከል "138 ያህሉ ኢትዮጵያውያን" ናቸው።
አንድ ምንጭ፤ "በዚህ ቡድን ውስጥ ብቻ 138 ኢትዮጵያውያን አሉ። ነገር ግን ማንነታቸው ላይ የፓስፖርት እና ሌሎች መረጃዎች አልተሰበሰቡም" ብለዋል።
በታይላንድ የኢትዮጵያ መንግሥትን ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን የሚያከናውነው በሕንድ ኒው ዴልሂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ከካምፖቹ የተለቀቁ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር 138 መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጧል።
ቢቢሲ ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከኢትዮጵያውያን ቀጥሎ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የጎረቤት ሀገር ኬንያ ዜጎች ሲሆኑ፣ 24 ኬንያውያን ተለቅቀዋል ተብሏል።
የፊሊፒንስ ዜጎች በ16፤የማሌዥያ ዜጎች ደግሞ በ15 ተከታዮቹን ደረጃዎች እንደያዙ ከምንጮች የተገኘው የታይላንድ መንግሥት መረጃ ያመለክታል።
ከተለቀቁት ሰዎች መካከል የኡጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የናይጄሪያ እና የቡሩንዲ ዜጎች እንደሚገኙበት የቢቢሲ የደቡብ ምሥራቅ እስያ ቢሮ ዘግቧል።
ከተለቀቁት ዜጎች መካከል 221 ያህሉ ወንዶች፤ 39 የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች እንደሆኑም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ከተለቀቁት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መካከል "የተወሰኑት ታይ ቻንግ" ከተባለው የማጭበርበሪያ ካምፕ እንደሆነ ቀሪዎቹ ደግሞ "ኬኬ ፓርክ" እና "ሽዌ ኮኮ" ከተባሉት ብዛት ያላቸው ካምፖች ከሚገኙባቸው አካባቢዎች ነው።
በካምፖቹ ውስጥ የነበሩት 260 ሰዎች እንዲለቀቁ ያደረገው አካባቢውን የሚቆጣጠረው "ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" የተባለው ታጣቂ ቡድን ነው።
ቡድኑ፤ በካምፑ የነበሩ ሰዎችን ያስለቀቀው አጎራባቿ ታይላንድ ካምፖቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ በሚል ወደ አካባቢው የሚሄደውን የኤሌክትሪክ ኃይል እና የነዳጅ አቅርቦት ካቋረጠች በኋላ ነው።
ካረን በተባለው የምያንማር ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድኑ ያስለቀቃቸውን ሰዎች ወደ ታይላንድ የላከ ሲሆን ሲደርሱም የሀገሪቱ ሠራዊት ተረክቧቸዋል።
ኢትዮጵያውያኑን ጨምሮ የተለቀቁት ዜጎች በአሁኑ ሰዓት በቀይ መስቀል ስር እንደሚገኙ ቢቢሲ በህንድ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የተለቀቁት ሰዎች፤ የታይላንድ መንግሥት ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝርዝር ሰለባዎች በዘረጋው "national referral mechanism" በተባለው ሂደት የማጣሪያ ውስጥ ያልፋሉ።
ይህ ሂደት የመጡት ሰዎች በትክክልም የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚከናወን ነው።
ሰዎቹ ተጎጂ መሆናቸው ሲረጋገጥ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ዜግነታቸውን የማጣራት እና ሌሎች ሂደቶች ይከናወናሉ።
ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ከካምፖቹ ወጥተው ወደ ታይላንድ የገቡ ኢትዮጵያውንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሂደት ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅ ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ መንግሥት በታይላንድ ኤምባሲ የሌለው መሆኑ የዚህ መጓተት አንዱ ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመላክ የሚሠሩ ድርጅቶች በታይላንድ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ሥራዎች ደርቦ የያዘውን በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲን የሚያገኙት ታይላንድ በሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ በኩል ነው።
ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ የሕንድ ኤምባሲ ለሚቀርቡለት የዜግነት ማረጋገጥ ጥያቄዎች "በቶሎ ምላሽ የማይሰጥ መሆኑ" የተለቀቁት ኢትዮጵያውያን በፍጥነት መመለስ ላይ ስጋት እንደሚፈጥር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምንጭ ተናግረዋል።
ባለፉት ሳምንታት ከካምፖቹ ወጥተው ወደ ታይላንድ የገቡ 10 ገደማ ኢትዮጵያውያንም በማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ አክለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምንጭ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያደራጀው ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተወጣጣ "ብሔራዊ ኮሚቴ" ከዚህ ቀደም በታይላንድ መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ንግግር ማድረጉን ገልጸዋል።
ኮሚቴው፤ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ከ30 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውሰዋል።
አሁን የተለቀቁት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስም ብሔራዊው ኮሚቴው፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት እንዲሁም ኤምባሲው በጋር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
"[ኢትዮጵያውያኑ ከታይላንድ] ለመውጣት ትራንስፖርት እና የጉዞ ሰነድ ያስፈልጋቸዋል። ብሔራዊ ኮሚቴው እና ኤምባሲው ከኢሚግሬሽን ጋር የሚሠሩት ይሆናል" ብለዋል።
የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከምያንማር ወደ ታይላንድ ከገቡት ሰዎች ሀገራት ኤምባሲዎች ጋር በመተባባር ሰነድ የማረጋገጥ እና በፍጥነት ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ እንደሚያከናውን የሀገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።
የምያንማር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፉተም ዊቼያቻይ፤ ሀገራቸው በታጣቂዎች ተለቅቀው ወደ ታይላንድ የሚገቡ ሰዎችን በሙሉ እንደማይቀበሉ መናገራቸውንም ዘገባዎች ጠቅሰዋል።
"የመጡበት ሀገር የማይቀበላቸው ከሆነ አንቀበላቸውም" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከምያንማር ማጭበርበሪያ ካምፖች ወጥተው ወደ ታይላንድ ለሚገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች መጠለያ እንደማይዘጋጅ ገልጸዋል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ