50በ60 ያረጠ ፖለቲካ።
እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
„ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን
በፊታቸው እንዳታደረጉ ተጠንቀቁ።“
(የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ ፮ ቁጥር ፩)
50በ60 ያረጠ ፖለቲካ።
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ
·
እፍታ።
ወይ ጉድ ሦስት ዜሮ እኛን ቁጭ አደርገው ወደ
20 ተሸጋገሩ። ግርም ይላል። ከመቼው 2020 እንደ ተደረሰ። ግን ቅኔዎቹ የአገሬ ልጆች እንዴት ናችሁ? የትውልድ የሃሳብ ብከነት
አጀንዳችን ቢሆን ምን ትላላችሁ?
ትህትናዊ አክብሮት፤ ትህትናዊ አድማጭነት፤ ትህትናዊ
ህዝባዊ ፍቅር፤ ትህትናዊ አስተዳደር ቤተ - መንግሥት ላይ ይተጋጋጠ እዬሆነ ነው። ይትብኃል ሱባኤ ላይ ነው። ቀኑ ይመለስለት ዘንድ
አቤት እያለ ነው ወደ እዮር።
ትህትና ግዞት ላይ ሆኖ በዚህ ፈንታ ፉከራ፤ መታበይ፤ ማን አለብኝነት፤ ደንታ ቢስነት፤ ግዴለሽነትን፤
ጉድለተ - ኃላፊነት የሚያውጁ ሥንኛት፤ ቃላት ቁሙ ተሰቀሉ እያሉን ነው። „ቃል ይተክላል ይነቅላል“ የተባለው ከተከላው ነቀላው
ማዘንበሉን እያስተዋልኩ ነው። ሁሉን ነገር ሳልጠራጠር እንደሚቀበል ቅን አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በማደምጣቸው ነቃይ ቃላት፤ ነቃይ
ሥንኛት የትውልዱን ማግሥታዊ ተስፋ ሳስበው ያምጥብኛል። ይቀጭጭብኛል።
ዛሬ ለዕርእሴ ተያያዥ እና ተወራራሽ የሆኑ ጉዳዮችን
አነሳለሁኝ። ከቅኖች የጹሑፌ ታዳሚዎችም ትዕግስታችሁ እንደማይለዬኝም
አስባለሁኝ። ወቀሳዬን እምልክላቸውም ቢሆኑም ያተርፉበታል እንጂ አይከስሩበትም። ለእነሱ የማይታያቸው ለእሷ ታይቷት ይሆናል ብለው
በቅንነት ቢያስቡ ትወልድን ከብክነት መታደግ ይቻላል። ገደል አፋፍ ያለን ጎሽ! እያሉ ከማበረታታት፤ እእ የያዝከው መስመር ዝበት
አለበት ብሎ መድፈር ያድናል። ከአመስጋኝ ሸንጋይ ይልቅ ቅናዊ ተቺ በስንት ጣዕሙ።
·
መተላለፍ።
„ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ ይላል“ ንጉሥ ዳዊት።
„የቤትህ ቅናትም በላኝ“ ይላል ልብ አምላክ ዳዊት። እንዲህ ሲል የህግ ጥሰትን ከመጠዬፍ ነው ብዬ አስባለሁኝ። ምድር የተሰጠችው
ለሰው ልጅ በህግ ትተዳደር ዘንድ ነው። ኢትዮጵያ የፕላኔታችን ቤተሰብ ናት። አገረ - ኢትዮጵያ በአምላክ በአላህ ቃልም ነው የተፈጠረችው
ብዬ አምናለሁኝ። ህግ በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያለቅሳል። ህግ በኢትዮጵያ ሲያለቅስ እግዚአብሄርም ያለቅሳል። ህግ ከሌለ ሃይማኖት
እራሱ እንደማይኖር ያውቃል እና። ፈርኃ እግዚአብሄር፤ ፈርኃ አላህ ምንጩ ለህግ ከመገዛት ይመነጫል እና። ግን በዚህ ውስጥ እያንዳንዳችን
እንኖርበት ይሆን?! እንፈታተሽ።
ምድራዊ ህግን ያላከበረ ሰማያዊ ህግን ያከብራል
ተብሎ አይታሰብም። ፈጽሞ። ይህን ከቤተ - መንግሥት ስንነሳ ለቤተ - መንግሥቱ ከተመቼው ሰማያዊውም ምድራዊውም ህግ ይጣሳል። አቶ
ታከለ ኡማን ከሌላ ከተማ አምጥቶ “የታከለ ህግ„ ረቆላቸው ሲሾሙ ምድራዊ ህግ መጣሱን ያመለክታል። ኢትዮጵያ የፌድራሉ የሥራ ቋንቋ
አማርኛ የሚለውን፤ በጓዳ ገብቶ የብልጽግናው የሥራ ቋንቋዎች በጉልበትም ጸድቆም እያዳመጥን ነው።
ቋንቋ ተጨማሪ በብልጽግናው ሲበይን
ኢትዮጵያዊ መንግሥትን የሚመራው በዚህው ድርጅት ነውና ህገ - መንግሥቱ በቁሙ ተጥሷል። በሌላ በኩል ደግሞ ህገ - መንግሥቱ አይነካም
ፉከራ ይደመጣል። በሁለቱም አቅጣጫ መተላለፍ ጎልቶ ያገሳል።
እንዲሁም ደግነት ከስሞ ለቡራዩ ተጎጅዎች እርዳታ
የሚያደርጉ ንዑዳን ሲታገቱ፤ የኢትዮጵያን ሰንድቅ ዓላማ ይዛችሁ እኛ የፈቀድልናቸውን እንግዶቻችን ተቀበላችሁ ተብለው የአዲስ አበባ
ኗሪዎች በጠራራ ጸኃይ ሲረሸኑ „አትገደልን“ ሰማያዊ የእግዚአብሄር ህግ ተጥሶ ነው።
የጌዴኦ ሰቆቃ ሳይደረሰለት
ቀርቶ ዜጎች በራህብ ሲቆሉ፤ ያ አልበቃ ብሎ ዕንባ የተስተናገደበት መንገድ „እኔ ስሾም ከሆነ ችግሩ የተጀመረው ስወርድ ይቀራል“
መስቃዊ ንግግር „የሚያዝኑ
ብጹዕን ናቸው“ ተጥሶ ነው። እንግዲህ እነዛ ምንዱባን
በ50በ60 ዘመነ ፍዳን ይጋታሉ ማለትም ጭምር ነው። ሃሳቡ ከሥልጣን የመውረጃው ዘመን በርቀት ታስቧልና።
·
የፓርቲ ህገ - ደንብ የገብያ ውሎ አይደለም።
ከሰሞኑ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የፓርቲን ህገ -
ደንብ የገብያ ውሎ አድርገውታል። በቃ! የሚሸጥ፤ የሚለወጥ ሸቀጥ። በሚሊዬነም አዳራሽ ለሰበሰቧቸው
ምርጥ ወጣቶች ህገ - ደንቡን ሲያብራሩ የፓርቲ ህገ ደንብ ህግ ተጥሶ የተከወነ ነው። ለዛውም በብሄራዊ ጉባኤ ያልጸደቀ። ህገወጥ ደንብ በህገ - ወጥ መንገድ። ይህም ሆኖ
የፓርቲ ህገ - ደንብ ሥርዓት ባለው፤ ወግ ባላው ድርጅቱን ለተቀበሉ ወይንም በእጩነት ለተመለመሉ ብቻ የሚነገር፤ ገለጣ የሚደረግበት፤
አባል ሲሆኑም በነፍስ ወከፍ የሚሰጥ ለአባላቱ የፖለቲካ ህይወታቸው መመሪያ ህጋቸው ነው። የፓርቲ ህገ - ደንብ በመንግሥት ዓዋጅ የሚጸደቅ ሰነድ አይደለም።
እንዲዚህ ዓይነት መግለጫ በህዝብ አደባባይ የሚያስፈልገው
የህጎች ሁሉ እጬጌ የሆነው ህግ መንግሥቱ ብቻ ነው፤ ወይንም መሪ ዕቅዱ እንጂ የፓርቲ አባልነት የገብያ ውሎ አይደለም። የአንድ
ፓርቲ ህገ - ደንብ የልዋጭ ማዋዕለ ንዋይም አይደለም። በውነቱ ስለ ጠቅላይ ሚኒስተሩ እኔ አፈርኩኝ። ከጠቅላይ ሚኒስተራንታቸው በፊት
ከነበረው በቀደመው አቅማቸው ልክ ብፈልግ ባፈላልግ አጣኋቸው። ጠፉብኝ ወይንም ተሰወሩብኝ።
የፓርቲ ህገ - ደንብ እንዲህ የዓዋጅ አዳራሽ
ፈጽሞ አይደለም። የፓርቲ ህገ - ደንብ የአደባባይ ነጭ ለባሽ አይደለም። አባላት ብቻ በሴል ወይንም በህዋስ፤ በመሰረታዊ ድርጅት፤
በወረዳ ጉባኤ፤ በዞን ጉባኤ፤ በክልል ጉባኤ፤ በብሄራዊ ጉባኤ ነው ውይይት የሚያካሄዱበት። የፓርቲውን ዲስፕሊን እራሱ የብልጽግናው ብቸኛ መሰራች
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ አላወቁበትም።
በነገራችን ላይ „የዴሞክራሲ ጽንሰት ውርጃ“ ጹሑፌ ላይ የተረሳ አንጎል ሦስተኛ ሰነድ አለ፤ መርኃ ግብር ወይንም ዕቅድ
ብዬ ነበር። የአጭር የረጅም ጊዜ ዕቅድ እና እነሱን የሚያይዝ
ሊንኩ የመካከለኛው ስለመሆኑ፤ ዕቅዱ ከሁለቱ መሰረታዊ ሰነዶች ከደንቡ እና ከፕሮግራሙ እንደሚመነጭም፤ ሦስቱም ሰነዶች የሚጸድቁት፤
የሚሻሻሉት፤ የሚሰረዙት በብሄራዊ ጉባኤ መሆኑንም አበክሬ ገልጬ ነበር። የሰሞኑ የኢህዴግ ይባል የብልጽግና ሥ/አስ/ ስብሳበቸው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ
እንደሚወያዩ አዳማጫለሁኝ። ይህም ጥሩ ነው ማድመጥ እና
በፍጥነት ለማረም ተፍ ተፍ ማለት።
ሚዲያዎች በተለይ ወሳኝ በሁኑ ግድፈቶች ላይ ይሉኝታ ሊኖራቸው አይገባም። ትውልድም ሆነ አገር
በዬዘመኑ እንደ ጥንቸል የመሞከሪያ ጣቢያ የሚሆኑትም ለዚህ ነው። ዝምታ፤ ይሉኝታ በመርኽዊ ጉዳዮች ላይ የተገባ አይደለም። የትወልድን
ህሊናዊ አቅምም ገዳይ ነው።
የሆነ ሆኖ እንደ አዲስ ፓርቲ መስራችነት ጠሚር
አብይ አህመድ በፓርቲ አመሰራረት ዕውቅትም ዲስፕሊንም አልቦሽ መሆናቸውን
አስተውያለሁኝ። ሂደቱ በሙሉ የተዛነፈ ነው። ዕቅድ አልባ ፓርቲ መሰረትኩኝ ጎደሎ ቁጥር ነበር ለእኔ። አሁን ተወያዩበት በተባለው
መስመርም በዚህም ሂደት ትክክል ነው እያልኩ ግን አይደለም። ቢያንስ ከተኙበት ከእንቅልፋቸው ተነስተዋል። ካቢኔ አቋቁመህ፤ አዲስ ፓርቲ መሰረትኩ
ብለህ፤ መንግሥት እዬመራሁ ነው እያልክ ግን ዕቅድ የለውም። ዕቅድ ሳይኖር የምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሰጠ። ማፈሪያ!
እራሱ የምርጫ ቦርድ የወደፊቱ በጀቱ፤
የሥራው ቅደም ተከተል የአወጣበት መርህ ግብር ለወደፊቱ የሚወሰነው በዚህው ዕቅድ ምንጭነት ነው ሊሆን የሚችለው። እኔ እምመራበት
ሰነድ ዕቅድ የት ሄደ ብሎ አልጠዬቀም አቬቶ ኢትዮጵያዊው የምርጫ ቦርድ። የምርጫ
ቦርድ ሹመኞች አማካሪን ጨምሮ የሥራ መሰረታቸውን እረስተው ነበር ዕውቅና የሰጡት። ብሄራዊ ዕቅድ አልባ አዲስ ወጥ የፖለቲካ ፓርቲ
ዕውቅና መስጠት? ብሄራዊ ዕቅድ አልባ መንግሥትን እመራለሁ ማለት? አላዛሯ ኢትዮጵያ መርኽ አልባ ጉዞ ላይ ነው ያለችው። ያስፈራል።
መርኽ ባለቤት ያገኜም አይመስልም።
·
መገራት።
በዚህ በአሁኑ የሚሊዬነም አዳራሽ ንግግር ያልተቆነጠጠ፤ ያልተገራ፤ ጨዋነት ያጣ ንግግር ነው
እኔ ያዳመጥኩት። ግን የሰው ልጅ ስንት ጊዜ ፈርሶ ይሰራል? ፖለቲከኞች የትዳር አጋር ሲኖራቸው የትዳር አጋሮቻቸውን መስመር የማያስያዝ
ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። እያባበሉ መስመር የማስያዝ። እያቆላመጡ የማስተካከል ግዴታ አለባቸው። እንዲህ ትህትናን ያህል
የሁለመና የመልካምነት ምንጭ እዬተላጠ ሲሄድ በሊሂቃኑ ሁሉ ነው እኔ እማዳመጥው፤ ትዳር ያላቸውን ማለቴ ነው። ሚስቶች ሆይ! የት
ነው ያላችሁት ማለቴም አልቀረም።
ጥሩ ሚስት ህግም ናት፤ ህግ አስከባሪ ናት። ችሎትም ናት። ባህልም ናት። መታመንም ናት። ሰው
ሲጠላህ፤ ሰው ሲያቃልህ፤ ሰው ክብሩን ሲቀንስብህ፤ ሰው ሲያሳንስህ ከማንም በላይ ለዚህ ዓይነት የቁልቁለት ፈተና ሚስት ጉዳዩን
ቀረብ አድርጋ መርምራ፤ ቀዳዳውን ሁሉ ወደ በጎነት፤ ወደ ቸርነት በመግራት ማረቅ ይገባታል። ይህን ማድረግ ከተሳናት ምኑን ሚስት
ሆነችው? ሚስት የህሊና
ችሎትም እንጂ የጓዳ አደባባይ ብቻ አይደለችም።
ወደ እናትነት ልሁቅ ጸጋ በረከቷ ሲመጣም ደግሞ ጥልቅ የሆነ ገኃዱ ዓለም እና መንፈሳዊው ዓለም
የሚገናኝ የሚስጢር ማዕዶት ሆና እናገኛታለን ልዕልት ሚስትዬ። ወለደችም መሃን ሆነችም ከደሟ ጋር የተፈጠረ እናትነት አለ። ሰማያዊ
ቡራኬ። ይህ ሁሉ ጸጋ የተሰጣት ሚስትዬ አንድን ባተሌ የትዳር አጋር ለመግራት ሙሉ አቅሙ አላት። በሽንገላ ሳይሆን በድንግልና ጌታዬ!
አባቴ! ሆድዬ! እያለች። እሱነቱን የሰጣት ስለሆነ በጸሎት ታግዛ ብትጀምረው ብዙ ምስቅልቅሎችን ማሳተገስ ይሳካላታል።
ሴት ልጠቀምበት ካለች ከጸሐይ
ያላነሰ ሁለገብ ጉልበት አላት። በአገራችንም ቢሆን የእቴጌ ጣይቱ፤ የእቴጌ ተዋቡ፤ የእቴጌ ምንትዋብ፤ የእቴጌ ሰብለወንጌል
ድርሻ ቀላል አልነበረም። ተምሳሌት ያጣ ህዝብ እንኳን በፈጣሪው በአላህ የተሰጠውን ለመከወን አይሳነውም። እንኳንስ እያለን። ወደ
እራሳችን መመለስ ከተቻለ።
·
ተዝች ላይ።
… ግን ኢትዮጵያ በዬትኛው ሊሂቅ ህሊና ይሆን ተጽንሳ ይሁን ጽላት ሆና ያለችው? በዬትኛዋ የሊሂቅ
የትዳር አጋርስ አላዛሯ ኢትዮጵያ እና የትውልዱ ብክነት ጉልላት ሆነው ይሆን? ቅኖች ትመረምሩት ዘንድ የቤት ሥራውን ልስጥ፤ ግን
ከስሜታዊነት እና ከጥላቻ እንዲሁም ከቂመኝነት እና ከበቀለኝነት ወጥታችሁ። ምቀኝነቱ፤ ቂሙ፤ ስሜታዊነቱ ካለ በዛ ውስጥ ፍትኃዊ
ሆኖ ግድፈትን ለመለዬት አይታያችሁም፤ አይቻላችሁም።
ሊሆን የሚችለው እራሳችሁን ብቻ ይሆናል እምታደምጡት። ወይንም ይሆነኛል ያላችሁትን
ብቻ ይሆናል ወግናችሁ አቅል የምትሰጡት። ያ ደግሞ ፍትኃዊ ዕይታን ያቆስለዋል እንጂ አይፈውሰውም። ያጣነውን ነገር እንወቅ። ብዙ
ነገር አጥተናል በአውሎው ፈረሰኛ ሙላት ተማርከን። እራሳችንም ስክነት አጥተናል። ስሜታችን ስስ ሆን። ቤንዚን እና ክብሪት ሁሉም
አሰናድቶ ይጠበቃል።
·
ህም!
ተወራራሽ ጉዳዮችን ከውኜ ወደ ተነሰሁበት አንባር ጉዳይ
ስገባ ሁለት በትረ
ነገሮችን አነሳለሁኝ። ቅኑ¡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ
አህመድ በአዲስ አባባ ሚሊዬነም አዳራሽ ካድሬዎቻቸውን ሰብስበው ስለተናገሯቸው ተስፋን ቀሳፊ
ንግግሮች በማስተዋል፤ አደብ ገዝቶ ማዬት የሚገባ ይመስለኛል። የነገ ግራጫማነት የትውልድ ብክነት ጠንቅ ስለሆነ። የሃሳብ
አንከሊስ የሚያጠቃው ትውልድ ካልናፈቀን ውስጣችን የሚጎበኙ አመክንዮችን የራስነገር ልንላቸው ይገባል።
የሚሊዬንም ንግግሩ ፖለቲካዊ ውሳኔም ነው። ዕድምታው፣ እንዳትሞቱ መብት አልባ ነን ብላችሁ
ህሊናችሁን ሸልሙን። ሰው ሁነን ተፈጥረን በመብታችን ያሻንን
እንመርጣለን ካላችሁ ግን ገዳይ አይጠዬቅም ተገዳይነታችሁን ግን አስልታችሁ፤ አቅዳችሁና ተልማችሁ ይሁን። የቻላችሁ ኑዛዜም አስገቡ።
ንስኃ መግባት ካለባችሁ ተሎ ከውኑ እዬተባለ ነው።
ሞት ያቀደ ምርጫ የ2012 ዓ.ም ተደሞ። እንዳይረሳ „ጦርነት እንገባለን፤
100ሺህ ሰው በአንድ ቀን ለመሰዋት እንገደዳልን፤ ወደ አንባገነንነት ጫፍ አትውሰዱን“ እነኝህ ኃይለ ስንኛት እንዴት እቅፍቅፍ
ተደረገው መሰላችሁ የሚሊዬንሙ ንግግር ያስተናገዳቸው። የዕለቱ ምህዳን በአስፈሪ ግርማ ሞገስ ታጅቦ የስጋት፤ የሰቀቀን ነጋሪት እዬጎሰሙ
ክፉ ፈቃዶች አሻጋሪ ሆነው እንደ መጡ ማስተዋል ይቻላል።
ግን ይህ እንደ ስክንዳንብያ አገሮች የሚቃጣው ኢትዮጵያዊው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ አካል ነፍሱ
ምን አለ ይሆን ያን ሲያደምጥ? ጣመው ወይንስ መረረው? ተመቸው ወይንስ ጎረበጠው ይሆን? አቃራው ወይንስ ሽቅብታ አሰኘው ይሆን?
ወይንስ እኔ መርኽ አስከባሪ ነኝ ብሎ በድፍረታዊ ትህትና ተነሳ? የዓለም የሰላም አባት፤ የኖቤል ተሸላሚ ጠሚር አብይ አህመድ ወዮላችሁ
እያሉ ነው። በድህነት፤ በጉስቁልና ለመኖርም እኛን ምረጡ ነው የሚሉት በአደባባይ። በስተቀር የሞት ስንቅ ይጠብቃል ነው። ያው ፋና ጥራቱን እወደዋለሁኝ።
እዛ ላይ ገብቶ ማዳመጥ ነው ራዲዮ አብይዝምን።
ጠ/ሚ ዶክተር ዐብይ በብልጽግና ፓርቲ ዙሪያ የአዲስ አበባ ወጣቶች ውይይት ላይ ያደረጉት ንግግር
ተስፋን አስቀድሞ የሚገድል፤ ጠሐይ ሆይ! በኢትዮጵያ ምድር ብቅ ብትይ አናትሽን ባባሩድ ነው
እምበረቅዝው የሚል አዋጅ ነው የተደመጠው። ፉክክር የሚባል
የለም ነው እዬተባለ ያለው። ያው የአቶ ጃዋር መሃመድ „ምርጫ ኮንስኮዬንስ አለው“ ያለው ነው በቃላት ተሞሽሮ ብቅ ያለው።
·
ምን ልበል?
መጥኔ ለዚህ ዘመን ትውልድ አባልተኞች ልብል። እንዲሁም አገር ቤት ለሚገኙ መብት አልባ ሆናችሁ
ደግማችሁ ተወለዱ ለታወጀባቸው ወገኖቼም መጥኔ ብያለሁኝ። ወዮልሽ አገሬ! በዓይነት ነው መከራው። የአሳር ቡፌ። እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ
በአደባባይ „አጥፍተናል ይቅርታ አድርጉልን ብለው“ይቅርታ በጠዬቁበት አንደበት አሁን ደግሞ አጥፊ አይደለነም፤ አልነበርነም ሰማዕታት
በጥፋት እንዲሰዉ ያደረጉት የፖለቲካ ተፎከካሪዎች ጋፋፍተው እነሱ ነበሩ ያን ያስደረጉት።
ፖለቲከኞች ወንድሞቻቸውን፤ ቤተሰበቻቸውን
ጠብቅው፤ ሌላውን ለማገዶ ላኩ፤ የድሃ እናት አልቅሳ ቀረች ይሉናል። ካሳ ተጠያቂዎች እንሱም ናቸው ዓይነት ነው ገለጣው። እንዲህ
መሰል ነገር ሲገጥማቸው ጎንደሬዎች „አዛኝ ቅቤ አንጓች“ ይሉታል። ኢህዴግ ለድምጽ አልባዎቹ እናቶች ጥብቅና ሲቆም¡ ምነው አሁንስ
የታሰሩ ልጆች ያሏቸው እናቶችም አሉ፤ ቢሯቸው ተቀምጠው የተረነሹትም
እንዲሁ እናት አላቸው። አዘኔታው የአንጀት ከሆነ፤ የአንገት ካልሆነ። ዛሬም የኢትዮጵያ እናት ታለቅሳለች። ዕንባ አባሽ፤ አይዞሽ
የሚል አላገኘችም። ጥሬው ሃቅ ይኸው ነው።
ለነገሩ ለእነ አሻጋሪዎቻችን፤ ከእሱ በላይ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ባዩች ይህ አሽሙር ደህና አድርጎ
አናታቸውን ያለ ርህራሄ በጥርቆታል ብዬ አስባለሁኝ። ቁጭ አድርገው ይወቋቸዋል። አንድ ጊዜ በተፈጥሮ ሂደት እስኪወስዳችሁ፤ ሌላ
ጊዜ ደግሞ እናንተ አክተሮች አትሞቱም በዬዘመኑ ጃኬታችሁን እዬቀዬራችሁ ብቅ ትላላችሁ፤ ሌላ ጊዜ „አንቺ የፖለቲካ ነጋዴ አለመሆንሽን
አውቃለሁኝ፤ ለክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም በአንድ ውይይት ከጓዶቻቸው ጋር ባደረጉት አንተ የፖለቲካ ነጋዴ
አይደለህም ብሎኛል አብይ“ ሲሉ ሁሉ አዳምጫለሁኝ።
እና ማነው ትውልድን ማጋጁ ነው ፍሬው ነገር? ማን ነውስ የፖለቲካ ነጋዴው? ማነውስ በዬዘመኑ እናቶችን
ያለ ጠዋሪ የሚያስቀረው? ሌሎች የኦሮሞ ሊሂቃን ቢሆኑ ጉዳያቸው አልነበረም ገልጥለጥ አድርገው እንቅጩን ይነግሩን ነበር። የኦሮሞ ሊሂቃን ግድ አይስጣቸውም
ልባቸው የሚላቸውን መሸፈኛ ቅርፊት ሳያስፈልጋቸው ፍርጥ አድርገው ይናገሩ ነበር። ጠቅላዩ ግን አለመደባቸውም። ማህል ላይ ገትረው
ቁጭ ነው። ወጣሪ ሲመጣ እንዲህ ለማለት ነበር ብለው ያዳድጣሉ እንደ ሐረሩ ጉባኤ የመኪና ምንትሶ፤ ወይንም እንደ ጎንደሩ የአፍ
ወለምታ።
ሌላው ተቃዋሚ አይባሉም ከዛሬ ጀምሮ „ተፎካካሪ ወንድሞቻችን ናቸው፤ አብርኃም ደስታ ካሸነፍከኝ
እቅፍ አድርጌ ሥልጣኔን በክብር አስረክብኃለሁ“ የተባለለት ቃለ ምህዳን ያው በርድ ተቸልሶበታል። ይህም ብቻ አይደለም „አሸባሪዎቹ
እኛ ነን“ የተባለው እነሱ ናቸውም ገፋፊዎች አስገዳዮች እነሱም አይሞቱም ተብሎለታል። ፐ¡ ከወረዱ ላይቀር እንዲህ ነው። አክሮባቲስትነት።
ሌላው ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተደማሪ/ ተቃዋሚ እኔ ሁልጊዜ እንዲህ ነው በአራት እረድፍ የምጽፈው።
በቀንበጥ ብሎጌ ላይ ማብራሪያ ስጥቼበታለሁኝ። ብቻ እንደ ዜጋ ሳስበው ይገርመኛል። ለነገሩ ይበላቸው። እኛ ምን አገባን? እነሱ
ግጥግጥ፤ ቅልቅል ላይ ነበር ቤተ - መንግሥት የባጁት። አሁንም ፍቅሩ አላለቀም። ይመስለኛል። እሰተ ሚያዚያ ይቀጥል ይሆን? ወፊቱ
ትጠዬቅ። እኔ በምን አቅሜ። ብቻ ግን ዳርዳሩ እዬተከረከመ መሆኑን እያስተዋልኩ ነው። ለኳቸው በሁሉም መስክ አቅማቸውን። አክብረህ ተቀብልህ ማነኮት።
የሆነ ሆኖ አሁን ባስተዋልኩት ነገር ያው ዘረ ቅንጅቶች የጥፋተኝነትን ስሜት ተሰምቷቸው ከማናቸውም የፉክክር ሃሳብ እንዲታቀቡ ብቻ ሳይሆን መጡብን ብሎ መራጩ ህዝብ እንዲሰጋም በስልት ተቀናብሮ የተሰናዳ ባለ ሦስት ስለት ሳንጃዊ ንግግር ነው። በዛን ጊዜ በደጉ ዘመን ልበለው የ100 ቀኑን ትጋት፤ ለሄሰኑም ሆነ ለኖቤሉ የሰላም ሽልማትም
ያበቃቸውን ዕንቁ ትጋት የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የተስፋ ምድር ትትርና መንፈስ ስታስቡት፤ አንተ ኃጢያተኛ ብለው እግር
እና እጁን አስረው እራሳቸው በፈቃደኝነት እንደ አናንያ፤ እንደ ሚሳዬል፤ እንደ አዛርያ እሳት ውስጥ ማግደውታል ብዬ አስባለሁኝ።
እግዚኦ!
መድረክ ስትደፍር፤ ከመደርክ አልለይም ብልህ ሰርከኛ ስትሆን መናፈቅህ ትንታ ይገጥመውና የተላመጠ አገዳ እዬሆኑ መምጣትም አለ። አሁን የቀረው እኔ በግሌ የምጠብቀው ጠቅላይ
ሚኒስተር አብይ አህመድ አገር ውስጥ ለነበሩ ጋዜጠኞች „ተቃለቢነትን“ ሸልመው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛን ውጭ አገር የሚኖር አንድ ቀንጣ ነፍስን ነጥለው „ኃላፊነት የሚሰማው“ ሲሉ በተደጋጋሚ አዳምጠን ስለነበር ይህ ደግሞ የሚዳጥበትን ቀን ነው የሚናፈቀኝ።
ብዙ ቃለኪዳኖች ምነና ላይ ነው ያሉት።
·
እም። ለማወራረሻ
ለላይኛው የውስጥ ቁስለቴ። ከቶ ፋሻ ማምረቻ ቤቴ ውስጥ ላምርት ይሆን?
1) „ እስከዛሬ
በኢትዮጵያ ባለን ልምድ በእናንተ ዕድሜ እንኳን የምታውቁትን ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን
ጦስ ብታዩ፣ ፖለቲከኞች ወንድሞቻቸው፣ ልጆቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው ምንም አልሁኑም አዲስ አባባ ውስጥ። የድሃ ልጅ ተቀጠፈ። ያን የድሃ ልጅ ማንም አያስታውሰውም። እናት ናት ያለ ጧሪ የቀረች። በቅርቡም ሁልጊዜ እንደምታዩት ወጣቱን ጋፋፍቶ ወደ መገዳደል የሚወስድ ኃይሎች ሲሞቱ አይታይም ሲያገዳድሉ
እንጂ።“ (ዶር አብይ አህመድ)። የድምጹ ቅላጼው
ልዩ ነው። ምቱ አንጀት ውስጥ ገብቶ የአዲስ አበባ እናቶችን ሆ! ብሎ እንዲወጡም የሚያነሳሳ ነው።
አዋሳ ላይ በምልሰት … „አይምሰላችሁ የአቤል ዕንባ ይጮኃል“ (ዶር አብይ
አህመድ) አዋሳ ላይ በግፍ ያላፉትን ነፍሳት እንዲህ እንደ አንድ የኃይማኖት አባት ያበለጸገ መሳጭ ስብከት አሰምተው ነበር። አሁን
ደግሞ አስገዳዩ ሌላ ነው፤ አስገዳዩም አለ በህይወት በቅርቡም አይታችኋል። ሁሁሁሁሁሁሁሁ! ይደክማል። ፖለቲካ ውስጥ የገባሁበትን
ቀን እረገምኩት። ቤተሰቦቼም የታደሉ ስለመሆናቸው የገባኝ ዛሬ ነው። ክውን ብለው መቀመጣቸው ስንቱን ነገራቸውን እንዳተረፉ አስተዋለኩኝ።
·
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ የትውልድ
ብክነት „የድምጽ አልባዎቹ እናቶች“ ዕንባ አጀንዳዬ ሆኖ የኖረው አሁን እኔ ነኝ አያሉን ነው ጠሚሩ። የት ነበሩ እስከዛሬ ድረስ?
በዚህ አገላለጽ የቀደሞውን የቅንጅትን ሹመኞች የአሁን ተደማሪዎችን የእነ ሰማዕቷ ሺብሬ ደስአለኝ ደም
ያፈስሳችሁ፤ ወደ አገር ሲገባም ግንቦት 7 ጳጉሜ 4 ቀን 2010 አቀባበሉ እና ዘግዬት ብሎ ከመስከረም 5 ከኦነግ አቀባበል ጋር ተያይዞ በተቋጠረው ቂም በጠራራ ጸሐይ 5 ወጣቶች ተረሽነዋል
አዲስ አባባ ላይ። „ለለውጡ እንደ ተከፈለ መስዋዕትነት ይቆጠር“ ብለወት ነበር።
አሁን ደግሞ ተጠያቂው ሌላ ነው ሲሉ ገፍተውታል።
ሰማዕትነቱንም ንቀውታል። በዛን ጊዜ 1300 ወጣቶችም ወደ ጦላይ ተወርውረዋል። እና አሽሙሩ ለእነሱው ይመስላል ለዛው ለተደማሪዎች።
በሌላ በኩል የአዲስ አባባ እናቶች ሆይ! ሞኝ አትሁኑ ነገም ልጆቻችሁን እንዳያስገድሉባችሁ እሰቡበት ነው። ወይ ጎንደሬዎች ባለ ቅኔዎች እኮ ናቸው እንዲህ ዓይነት በኸረ ጉዳይ ሲገጥማቸው።
„ልብ ያለው ሸብ ይሉታል“ ምርጫ 2012 ካቴና ይታዘዝለት ይሆን ወይንስ ባሩድ? ምን ቆርጦት! ካቴና እና ባለሃብት ሁልጊዜ ከባለዘመኖች
ጋር እንደ ተሰለሰ ነው ልስን። የሞት ዓዋጅ በቄንጥኛ ንግግር። ለመሆኑ የዛን ጊዜው 1997 ዓ.ም ይሁን የቅርብ ጊዜው የ2011 ዓ.ም የመስከረሙ
ገዳዩስ ማን ነበር?
·
በትኛው ሥርዓት? „መ“ መልስ የለም።
·
መረጃ አቀባዩስ ማን ነበር? በዬትኛው ሥርዓት? „መ“ መልስ የለም።
2) „የብልጽግናን ሃሳብ፤ የብልጽግና የአሰራር
ሥርዓት በፍጹም
ለሚቀጥሉት 50/60 ዓመታት
ማሸነፍ አይችልም“
ጠሚር አብይ አህመድ በሚሊኒዬም አዳራሽ ለሰበሰቧቸው
የአዲስ አባባ ወጣቶች የተናገሩት ቃለ ምህዳን ነው። ይህ ዕድምታ ወጣትነትህ ገደብ ተጥሎበታል፤ ሃሳብ አፍላቂ ሆነህ አልተፈጠረክም፤
ለወደፊትም ከሁለት ትውልድ በላይ ለሚዘልቅ ዘመን አዲስ ሃሳብ አፍላቂ ትውልድ አይፈጠረም ከእኔ ሃሳብ በስተቀር። ምንድ ነው ይሄ?
እርግማን ይሆን? ይህን እኛ ብንለው ነበር የሚያምረው። እኛው ብንመሰክርላቸው።
የተፈጥሮ ሂደት
በአብይዝም ዘመን አይተዋወቁም። ዕውቅናም ለመስጠትም አይፈቅድም። አብይዝም ንፉግ ነው። እሚገርመው ስለተፈጥሮ ሳይንስ እና ስለ ማህበራዊ
ሳይንስ ደግሞ በቀደመው ንግግራቸው ጥልቀት ያለው ዕሳቤ በተመስጦ አዳምጥ ነበር። የትኛው አብይ ይሆን አሁን ያለው? ስንተኛውስ
አብይ ይሆን አሁን ያለው? የበፊቱ ምርጫዬ የነበረው ጥልቅ እሳቤ አሁን ደግሞ ያን የጣሰው ዕይታ እሰከ 60 ዓመት ይዘልቃል እዬተበለ
ነው።
ሳስተውለው። እሳቸው ስለራሳቸው ባስቡት ልክ
ጽናት ያለው ዕውቅና በማጣታቸው ይመስለኛል፤ ዛሬ ዛሬ ከንግግራቸው እማዳምጠውን ስመዝነው፤ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጭንቀት
በዛባቸው። ጭንቀት ተጫናቸው። ጭንቅት ነሰታቸው። የጭንቀት በሽታ እንዳያማቸው እስገለሁኝ። ስለዚህም ነው ሚስቶች ሆይ! የምለው።
እንትን ይናገራል? 50በ60ን። ምን እያለው ይሆን አዲሱን ሞደኛ?
እንዲህም እያለ …
·
ጠሐይም ባለችበት
ተገትራ ኤሉሄ! ኤሉሄ! ለ60 ዓመት ትላለች።
·
ጨለማም ባለበት
ቁሞ ኤሉሄ! ኤሉሄ! ለ60 ዓመት ይላል።
·
በጋም አንቃሮ እያዬ ኤሉሄ! ኤሉሄ! ለ60 ዓመት ይላል።
·
ጸደይም አንጋጦ
እዬተመለከተ ኤሉሄ! ኤሉሄ! ለ60 ዓመት ይላል።
·
በልግም አተኩሮ
እያሰበ ኤልሄ! አሉሄ! ለ60 ዓመት ይላል።
·
ክረምትም እያነባ ኤሉሄ! ኤሉሄ! ለ60 ዓመት ይላል።
·
እስከ 60 ዓመት ድረስ በአላዛሯ ኢትዮጵያ የሚመጣ የሚሄድ ዓመት የለም፤
ወርም የለም፤ ሳምንትም የለም፤ ደቂቃም የለም፤ ሰከንድም የለም። ኢትዮጵያዊ ትውልድን እያለፈ ይሄዳል። እናስተውል። ፉከራ አይደለም
እናስተውል ስለ ውስጣችን ሰጥተን እንመርምረው ለማለት ነው። ይህ ተፈጠሯዊ የማያቋርጥ ሂደት የሚታገተው ለኢትዮጵያዊው ለተወለደውም
ብቻ ሳይሆን ገና ለሚወለደውም
ጭንቅላት፤ ህሊና ወይንም አዕምሮ ጭምር ነው። ጨልምተኛ ዕሳቤ፤ ተስፋንም የተዋጋ ወልደ ግራ። ግን ለምን 60
ላይ ተገተረ የትንቢታቸው ወሰኑ፤ እሰተ ሺህ ዓመት ለምን አላሉትም? ምኞት አይከለከል። ለዚህ ነው እኔ ላልተፈጠሩትም ነው እምታገለው
እምለው።
·
እኔ ግን እላለሁኝ … እንዲህ
አንድ ጠንካራ ጉልበታም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ቢነሳ
በህይወት እሳቸው እያሉም ሊቦዳድሰው ይችላል 50በ60ን። ከዚህም በላይ እናት በድባብ ትሂድ እንጂ ብሩህ ህሊና በማናቸውም ጊዜ
እና ሁኔታ ይፈጠራል። መላ የኢትዮጵያ እናቶች እንዲመክኑ ካልተደረገ እንደ ዘመነ ህወሃት አማራ ብቻ ተነጥሎ እንዲመክን እንደተደረገው። የበለጡ፤ የመጠቁ ህሊናዎች አሁንም ኢትዮጵያ አላት ወደፊትም ይኖራታል።
ብቻ ብቻ ለቀጣዩ ትውልድ መሃንነት በስልት ሊከወን ይችላል። ይህም አይሆንም ብሎ ማሰብ አይቻልም። „አያያዙን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል“
ይላሉ ጎንደሬወች።
ኢትዮጵያዊው ተፈጥሮ ለጠሚር አብይ አህመድ ሲባል
እንደ ኩሬ ውሃ ታቁሮ stagnant water ሆኖ ይቀመጣል
ማለት ነው። ጥሬ! ለላርባ እንኳን ያልደረሰ ሃሳብ ነው። ያረጠ!
የመኖርን ሆነ የተፈጥሮ ሂደትን ያላገነዛበ ብቻ ሳይሆን የልዑል እግዚአብሄርንም ቅብዕ የተዳፈረ። ወላጆች ብቁ ሃሳብ አፍላቂ መሪ
ልጆች አትወልዱም የሚል ተሰፋ አስቆራጭ ንግግር ነው።
እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ከዬትኛው
ፕላኔት ነው የመጡት? ከኢትዮጵያዊው ሴት ማህጸን አይደለም ወይ የተወለዱት? ከኢትዮጵያዊው አብራክ አይደለም የተገኙት? ይህ ሥልጣን
በሳቸው ክህሎት ተመዝኖ፤ ተለክቶ፤ ተበጥሮ፤ ተንተርትሮ፤ ነጥሮ ነው የተገኜውን? ፈቃደ እግዚአብሄር ባይታከልበት ይገኝ ነበርን?
በሰውኛውም ቢሆን ያ የጎንደር ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ሞገዳዊ አብዮት ባይነሳ ያገኙት ነበርን?
በአረጠው የአብይዝም ፍልስፍና 50በ60 ዘመኑ
ይቆጥራል ግን ትውልድ በኢትዮጵያ አይበቅልም ቢበለቅልም አያበቅልም፤ ዘመኑ
ይጓዛል የሃሳብ ፍሰት አይጸንስም ቢጸነስም ያስወርደዋል፤ አብይዝም ብቻ ቀጥ ብሎ እንደ ስልክ እንጨት ተገትሮ
ይገዛል፣ ይነዳል ለ50ለ60 ዓመት ቋሚ፤ ዘላቂ፤ አልመውቲ ሆኖ ይዘልቃል።
እርጅና አይነካውም፤ መሻገት ትውር አይልበትም፤ አይወይብም፤ አይዝግም፤ አይነቅዝም በቃ እንዳሸተ የሚኖር የሰማይ ጠጋ¡ ነፍስ እኔ እና የእኔ ሃሳብ
ህይወት እና መንገድ ነን ይልኃል አብይዝም፤ ይልሻል አብይዝም። ሙተኃል እዬተባለ ተረስቶ አንድ ቀን አስታውሰውት የማያውቁት የአዲስ አበቤ ወጣት ካድሬ ያጨበጭባል። ያሽካካል፤ ያውካካል። ለውርዴቱ ስጦታ ይፍለቀለቃል። ማህከነ!
ለዛውም እኮ በአንዲት ብናኝ ሥርዓታዊ ሂደት ባልታዬበት
የብልጽግና (ፓርቲ? ) ነው ይህ የሚነገረን። ሥርዓታዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመሰራረት ፈጽሞ አልተከተለም። ለዚህም ነው እኔ የጨረቃ
ቤት፤ የዓዋጅ ፓርቲ፤ የቀብድ ፓርቲ፤ የመያዦ ፓርቲ፤ የዱቤ ፓርቲ እያልኩኝ የዳቦ ሥም በዓይነት እማወጣለት። የሚገርመው ሥርዓት
ተከትሎ እንደ ተፈጠረ ሁሉ „የብልጽግና ሃሳብ የብልጽግና የአሰራር ሥርዓት በፍጹም ለሚቀጥሉት 50/60 ዓመታት
ማሸነፍ አይችልም“ የብልጽግናን የአሰራር ሥርዓት ይሏችኋል በህግ ጥሰት ውስጥ መንገድ ሆኖ ይቀጥላል። ህግ ጣሽነት መሪነት ሆኖ
ይቀጥላል ነው ዕሳቤው። ተሳህለነ! እራሱ መቼ በሥርዓት ተፈጠረ እና የአሰራር ሥርዓተ የሚኖረው።
·
የትኛው የብልጽግናው ሥርዓቱ?
ተኮትኩቶ ያለበቀለ ልቅ ሂደትን የተከተለ እንደልቡ ድርጅት ነው ብልጽግና። ግን የትኛው ሥርዓት ብለን ስንጠይቅ?
·
አንድ አባል
ሳይኖረው የተመሰረተው?
·
አንድ የመሰረታዊ ድርጅት ጠቅላላ ስብሰባ ያልተካሄደበት?
·
አንድ የወረዳ ጉባኤን ያላስተናገደ?
·
አንድ የክልል ጉባኤን ያላስተናገደ?
·
የብሄራዊ ጉባኤን ያልስተናገደ?
·
መሰረታዊ ሰነዶች ፕሮግራም፤ ደንብ እና ዕቅድ በብሄራዊ ጉባኤ ያላጸደቀ፤
·
ዕቅድ ያልነበረው?
·
የፓርቲ ሰነዶችን ደንቡን፤ ፕሮግራሙን፤ ዕቅዱን ማጽደቅ የሚቻለው አይደለም
ሥ/አ/ኮሜቴ ማዕከላዊ ምክርቤት ሥልጣን የለውም። በፍጹም።
ሰነዶቹ የሚጸድቁት በብሄራዊ ጉባኤ ብቻ ነው። እሳቸው እራሳቸው መሥራቹ ዶር አብይ አህመድ፤ ሃሳብ አፍላቂው የብልጽግና ፎርም ሞልተው
አባል አልሆኑም አይደለም ሌላው። እርግጥ ነው ከዚህ ወቀሳ
በኋላ ሁሉም ፎርም ለመሙላት ይጣደፉ ይሆናል። ለዛውም ፎርሙ ከተዘጋጀ ነው። እራሱ ፎርሙ ተሰናድቷል ብዬ አላስብም። ስንት አባል
አላችሁ ብሎ ምርጫ ቦርድ አልጠዬቃቸውም።
በብልጽግናው በጉባኤ ያልተመረጠ
-
·
ማዕከላዊ ኮሜቴ
·
ቁጥጥር እና ኦዲት
ኮሚሽን፤
·
በማዕከላዊ ምክር ቤት ያልተመረጠ ሥ/አሥ/ኮሜቴ ይዘህ ይህን ያህል መፎከር።
እራሱ ኢህዴግ እኮ አልፈረሰም በብሄራዊ ጉባኤው በህጋዊነት አልከሰመም። ይህ እኮ አንጎል ጉዳይ ነው። ሽግግርም ከሆነ፤ ውርርስም
ከሆነ፤ ሽግሽግም ከሆነ ሥርዓት ሊጠበቅ ይገባል።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ
የሚሉን።
·
እኔን እራሴን
ብቻ እንደ ብልጽግና (ፓርቲ?) ቢሮ፤
·
ብሄራዊ ጉባኤ፤
·
ማዕከላዊ ምክር ቤት፤
·
ኦዲት እና
ቁጥጥር፤
·
ፖሊት ቢሮ እዩኝ እና ተቀበሉኝ ቢሉ እንኳን አንድ ነገር ነው።
ወይ በአዋጅ
ብልጽግና የሚባል ፓርቲ ተቋቋመ ተብሎ ቢነገር የተሻለ ይሆን ነበር። በስተቀር ግን በፓርቲ ህይወት ውስጥ መደበኛ ሆኖ በዘርፉ ለሰራ
እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ላለ፤ ለዛውም እንደ ጓድ ገ/መድህን በርጋ ዓይነት በ100 ዓመት የማይገኝ የፖለቲካ ሊሂቀ - ሊሂቃን ህሊናዋን
ያነፃት ነፍስ ግን ይህን አይቀበለውም። ያስፈነጥረዋል። በለብ ለብ ቅልቅሎሽ የትውልድ ህይወት ሊባክንም፤ ትውልድ አቅሙንም ሊያባክን
አይገባም። በዛ ላይ ሽንገላው። ደፍረው አይናገሩት ይህን የተፋለሰ መስመር ማዕርግ አድርገው።
ትናንትም ዛሬም
„እኛ ኢህዴጎች መለሲዝም ነን“ ይበሉን በዛ እንስማማ። አዲስ ፓርቲ ነኝ ግን አያስኬድም ያስኬድ ሲሉም „የብልጽግና ሃሳብ የብልጽግና
የአሰራር ሥርዓት በፍጹም ለሚቀጥሉት 50/60 ዓመታት ማሸነፍ አይችልም“
ይህን ስንኝ ያንሱት፤ ደፍረውም አይናገሩት። አመክንዮው ልውስ ነው። አንድ ንጥር የፖለቲካ ድርጅት ፓርቲ የመርኽ አቅም እንጂ ህልውናውን የሚያስቀጥለው የመርኽ ጥሰት ሸጎሬ አይደለም።
እውነቱ ስናገረው ጉልበት የፖለቲካ ፓርቲ አይሆንም። ለዚህም ነው እኔ ብልጽግና ተፈጥርኩ ሲል የትውልድ ፓርቲ የመሆን
አቅም የለውም፤ የጨነገፈ ነው ብዬ በፌስቡኬ ላይ ስጽፍ የሰነበትኩት። የጦር ኃይል ስላል ህግ „ህግ“ መሆኑ ፈጻሚም አስፈጻሚም ባይኖሩትም
ህግነቱ ግን ሉዑላዊነት
አለው። የፓርቲ ህግ የራሱ ማንነት ብቻ ሳይሆን ሉዐላዊነትም አለው።
አብይዝም ችግሩ ለመማርም ዝግጁ አይደለም። ለማድመጥም
ዝግጁ አይደለም። አዋሳ ላይ „ቆንጥጡኝ፤ ሥልጣን ምን እንደሚያደርግ ስለማላውቅም ላጠፋ እችላለሁኝ“ የነበረው ቅዱስ መንፈስ ለልቅነት
የመታሰቢያ ሃውልት ይሆን? በድጋሚ አዋሳ ላይ „የታመመው ንግዳችሁ ብቻ ሳይሆን እኛም ታመናል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያልተመመ አለና“
ያለው መንፈስ መታመሜን እዩልኝ እያለን ይሆን?
የሆነ ሆኖ በማንአለብኝነት መርኽ „መርኽ ነኝ“
ብሎ አይታወጅም። የልምድም የዕውቀትም ማነሰም አይቻለሁኝ በብቸኛው የብልጽግናው የዓዋጅ ድርጅት መሥራች ነኝ ባሉት በጠሚር አብይ
አህመድ። አንድ አዲስ ፓርቲ እመሰርታለሁ ያለ ነፍስ ዕቅድ አልባ ነው የነበረው። ዕቅድ
አልባ ካቢኔ ሰማይ አልባ መሬት ነው። ህሊና አልባ ሰው ማለት ነው። ቀበቶ አልባ ሱሪ ማለት ነው። ማንም ግድፈቱን እንደ አጀንዳ
አንስቶም አልተወያዬበትም ነበር። ሁሉም በፕሮግራሙ እና በደንቡ ላይ ብቻ ነበር አትኩሮቱ። እኔ ብቻ ነኝ ብልጽግና መጣሁ ካለ ጀምሮ
ፌስቡኬ ላይ ስጽፍ የቆዬሁት። በስተመጨረሻም ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ስሞገት ጠንከር አድርጌ ሄድኩበት። ዘሃበሻም ለጥፎታል ግን
ሊንኩን አክዬ ለመለጠፍ መግባት አልቻልኩም። በቴክኒክ ችግር ምክንያት።
የዴሞክራሲ ጽንሰት ውርጃ {ዘለግ ያለ ሙግት ከምርጫ ቦርድ ጋር}
·
ስንጥቅ በስርንቅ።
አብይዝም እንደ ባለ የሰማይ ጸጋው እንደ ሄኖክም
ያሰኜው ምናብ ነው። ተፈጥሯዊ የመኖር ሂደት ብሎ ነገር ኢትዮጵያ ዘው ላይል ማል፤ ተገዘት እዬተባለ ነው። በቃ ዘመንም፤ ትውልድም ታግቶ ይቀመጣል ነው ዝንፉ የአብይዝም ብያኔ። ትውልዱ
ያያል ግን አያይም፤ ትውልዱ ይሰማል ግን አይሰማም፤ ለምን? ማሰቢያው እንዳይሰራ ተቆልፏል። ከዚህም
ባለፈ መጪውም ኢትዮጵያዊው ትውልድ እንዳያስብ፤ አዲስ ሃሳብ እንዳያፈልቅም ተቆልፎ ነው የሚወለደው ይልኃል አዲሱ የተፈጥሮ ሳይንቲስቱ¡
አብይዝም፤ ይልሻል የተፈጥሮ ሳይንቲስቱ አብይዝም።
ኢትዮጵያዊው አዲስ ብጡል ሃሳብ ሆይ! ባለህበት እርጋ ተብለኃል። የፈረደብህ። እና መቼ ይሆን ይግባኝ ይገባኛል የምትለው? ንገረና!
ሲኦላዊ ዕሳቤ አመንጭው፤ የዘፍጥረት ህግጋት ጣሹ፤
በኢትዮጵያ የባቢሎን ግንብ አናጺው አቶ በቀለ ገርባ የዓለምን የገብያ ህግ በጥሰት፤ የፈጣሪን የተፈጥሮን የመኖር ህግ በመጨፍለቅ፤
የአዳም እና የህይዋንን የምርቃት ሂደት በመርጋገጥ አትጋቡ፤ አትገበያዩ፤ የሌላ ሰው ቋንቋ አትናገሩ በታጠረ አጥር ውስጥ ብቻ ተቀመጡ
ብለው ሲያውጁ ዘመን የሰጠውን ግሎባላይዜሽን ሲገድቡ፤ አብይዝም ደግሞ አትሰቡ፤ ለማስብ እንዳትፈጠሩ እኔ ከፈጠሪ ከአላህ ጋር እንጋገርበታለሁ የማያስብ ትውልድ እስከ 60 ዓመታት ድረስ ይፈጠር ዘንድ እዬተባልን ነው። ምንድን ነው ይህ ኦሮሙማ
የሚባል ጉድ? የኩሬ ውኃ። ማሰብን አይፈቅድም። አብሮነትን አይፈቅድም።
ግሎባላይዜሽን ስልጣኔን አይፈቅድም። አዲስ ሃሳብ የማመንጨት ነፃነት አስቀድሞ ስቅላት ይበይንበታል። ማሰቢያህ የእኔ ጭንቅላት ብቻ
ነው ይልኃል። ማረጥ!
ኢትዮጵያዊው ሰው ሆይ የት ነው ያለኽው?! በሃሳብ
ሞግተው። ዝም ብለህ እንደ ወረደ አትሰልቅጠው። ፈትሸው። እንደ አንድ ኦብጀክትም ቁጭ አድርገህ እያንዳንዷን የህይወትህ ሂደት እንቅፋት
ምርምራውን በጨዋ ደንብ ሥራበት። በልተው። ዝም ብለህ አትዬው። በኢትዮጵያ ምድር አዲስ ሃሳብ አይበቅልም አያሰብልምም መባል መኖር
አይተነፍስም የማለት ያህል ነው። አዲስ ትውልድ ሲፈጠር ተኝቶ ነው የሚፈጠረው ነው የሚልህ አብይዝም። የአሁንም ያለውም ቢሆን እንደ እኔ የሚያስብ የለም ሬሳ ነው ነገርዬው። ድፍረት ይባል? ጥጋብ ይባል? መታበይ ይባል? መካሪ ማጣት ይባል? ንቀት ይባል?
ገርነት ይባል ምን እንበለው? ማን እንበለው? መቼ እንበለው? ወይንስ ወደዬት ነህ እንበለው? የዛሬውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን፤ የቀጣይ
የሁለት ትወልዱንም ተስፋ ምሶ የሚቀብር። ያረጠ።
„መደመር“ መጽሐፍን ስላለነበብኩት ውስጡ ምን
እንደያዘ አላውቅም። ነገር ግን በዚህ በሥልጣን ዘመን ባዬሁት አቅም ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ልክነት ምን ያህሉን ዶር
አብይ አህመድ እንዳጡ፤ ቀደም ብዬ ከ2016 ጀምሮ ለራሴ የፍቅራዊነት ሚጢጢ ፕሮጀክቴ ሳጠናቸው ስለነበረ እሳቸው አይታያቸውም እኔ
ግን ምን ያህል ቁልቁለት ላይ እንዳሉ ይታዬኛል። አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ይሄ ከራስ አምልኮ በመጣ የሴራ ድር ላይ በሰሩት ኃጢያት
ምርቃታቸው ተነስቶ ይሆን
እላለሁኝ። ትህትናቸው፤ አዛኝነታቸው እንኳን የለም አይደለም
ያነ ሳቢ እና አጓጊ የአንደበት ለዛቸው። ስልችት ይላችኋል።
አሁን በዚህ ክው ብሎ ተፈጥሯዊነት እና ሰባዕዊነት
በደረቀበት፤ የህግ የበላይነት በተመጠጠበት፤ እኩልነት በተጋጋጠበት፤ የህሊና ነፃነት በተቀረጣጠፈበት፤ ስጋት ግጥግጥ ላይ ባለበት ዘመን ጌጥ ሆኖ እስከ 50/60 ዓመትን
ማለም ይቻል ይሆን? እኔ ግን እላለሁኝ አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ አይቻልም ማለት መታመም እንጂ የጤና አይመስለኝም። ምን አለ ንግግር
ከማድረጋቸው በፊት ሪህርሳል ቢሰሩ። ቢጋርም ቢኖራቸው። ለነገሩ ቅን እና ደግ አማካሪም ያላቸው አይመስለኝም። አማካሪ ስል ውድቀታቸውን የማይመኝ፤ መኮሰሳቸው የማይናፍቀው ድንግል አማካሪ። ውድቀታቸው በዬዕለቱ እዬሰላ፤ እዬሰለጠነ
ነው እማዬው። ሞረድ ተአገር ጠፋ። ሞረድ ሆይ - ሆይ! የት ነው ያለኽው?! ሽርክትክት የሆነ ነገር ነው እማዬው። ንጥርነት ሰጠመ።
·
የኢትዮጵያ ዓይነተኛ የፖለቲካ ችግር እንደ ሥርጉትሻ ዕይታ።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ማህበራዊ ንቃተ ህሊናን ምን
ማለት እንደሆን አይታወቅም። ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ስለመኖሩም በቂ ግንዛቤ ያለ አይመሰለኝም። ማህበራዊ ንቃተ ህሊና መኖሩ ቢታወቅ
እንኳን ዕውቅና ለመስጠት አይፈቅዱም የፖለቲካ ሊሂቃኑ። ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አነሳሳቸው የማይቀጥሉት በዚህ የዕውቅት ድህነት
ነው። መጣጣም አይችሉም።
አሁን በአማራ ማህበረሰብ የአማራ የማንነት እና
የህልውና ተጋድሎ እንዲህ ይመጣል ብሎ ያሰበው አልነበረም። የአማራ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና የመሰልጠን አቅም ደረጃ ላቂያነት
ነው የወለደው። ስለዚህም የትኛውም ድርጅት ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ይመጣል ብሎ ስለማያስብ ሲፈነዳ በቀጥታ ፊት ለፊት ግብግብ ይገጥማል።
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ብሎ መጥራት የቻለ ፖለቲከኛ አታገኙም። ለምን? ማህበራዊ ንቃተ ህሊና የተፈጥሮ ሂደት ውጤት
ስለመሆኑ አያውቁትም። ቢያውቁትም እነሱ ከሚያስቡት በላይ የሰለጠነ፤ የበቃ፤ የበሰለ፣ ያሰበለ ወላዊ ማህበራዊ ንቅናቄ የሚፈጥር ስለመሆኑ አይቀበሉትም። የተበለጡ ይመስላቸዋል። ለነገሩ ቀድሞ መተንበይ ብሎ
ነገር የለም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን።
ማህበራዊ ንቃተ ህሊና የሚያቀርባቸው አመክንዮዎች
ያልተሰቡ ድንገቴ ስለመሆኑ ቀደምው በዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ፕሮግራም ላይ አይካተቱም። ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ሲመጣ ግን ከፕሮግራሙ
የሌለው ድርጅት ሁሉ የባለቤትነት
መብት ይጠይቃል። ካልቻለ ዘረፋ ይገባል። በዚህ ማህል
በሚፈጠረው ስብት - ስብቃ ግጭት ይወለዳል። አንዳንዱ ደግሞ ያነን የሚያስተናግድ አዲስ ድርጅት ይፈጥራል።
ለመሸከም ግን ግዙፉነቱን
የሚችል የዲስፕሊን አቅም ላይኖረው ይችላል። አሁን እንደ ጠቅላይ ሚነስተር አብይ ገለጣ እስከ 50/60 ዓመት ድረስ ማህበራዊ ንቃተ
ህሊናም ትውር አይልም፤ አይፈጠረም ኢትዮጵያ ምድር ነው የሚሉት። መሃን ዕሳቤ። ግን ከዬትኛው ዩንቨርስቲ ይሆን ይህን ፍልስፍና
የተማሩት? ስታስቡት እራሱ ብናኝ የሚስብ ቡቃያ ነገር ታጡበታላችሁ።
የማያውቁት ነገር ሊያውቁትም የማይሹት ነገር ማህበራዊ ንቃተ ህሊና የሚያፍለቀው
ሃሳብ ወላዊ ስለሚሆን ጉልበታም እና አንድን ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ ምዕራፍ ከፋች መሆኑን ነው። ለመስዋትም ፈቀደኛ ነው።
ቆርጦ ስለሚገባበት። በዚህ ውስጥ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ዕውቅና ለመስጠት የተሳነው ኢህዴግን
አውራው ፓርቲ ህወሃትን መቀሌ እንዲመሽግ የተገደደበት ምክንያት፤ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና የፈጠረው አብዮትን ዕውቅና የመንፈግ መከራ
ነው። ዓለም ቁሞ የሚጠበቅ እንደ ኩሬ ውሃ stagnant
water የሆነ አምክንዮ አስተናግዳ አታውቅም ብዬ ጽፌ ደጉ ሳተናው አውጥቶት ነበር ያው ተጋድሎው እንደ ተነሳ።
ያው ምክሩ ለግራ ቀኙ ነበር። ለዲያስፖራዊው አውራ
ድርጅት ለግንቦት 7 እና ለአገር ቤት አውራ ድርጅት ለህወሃት። ሁለቱም ስክነትት ነሳቸው ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ንቃተ ህሊናን እንዳለ
አልቆጠሩትም፤ ሊፈጠር ይችላል ብለው አላሰቡም። ስለሆነም ዕውቅና ነፈጉት። ህወሃት „የአሸባሪዎች“ ሲለው ግንቦት 7 „የነፃነት
ኃይሉ ንቅናቄ“ አለው። „የነፃነት ኃይል“ የሚባሉት ያን ጊዜ ከሲዳማ፤ ከአፋር፤ ከኦዴግ ጋር ግንቦት 7 የደረገው ጋብቻ ነበር።
አገራዊ ንቅናቄ። እነሱ ስለ አማራ ማንነት የህልውና ጥያቄ ግድ ብሏቸው ንቅናቄውን አስነሱት በማለት ዘረፋ እና ኮፒ ራይት ውስጥ
ተገባ። ስለሆነም ገዢው ፓርቲም፤ አገር እረከባለሁ ብሎ የሽግግር ሰነድም ያዘጋጀው የዲያስፖራው አውራ አገራዊ ንቅናቄም ሁለቱም ወለቁ።
ሰፊው ድጋፍ ግንቦት 7 አማራ ስለነበር ልብ ሸፈተ።
አሁንም የባልደራስ ንቅናቄ በቂ አትኩሮት፤ በቂ
አክብሮት፤ በቂ አያያዝ፤ በቂ ዕውቅና ካልተደረገለት የኢህዴግ አዲሱ የጨረቃ ቤት ብልጽግና ያበቃለታል። ተደማሪዎችም በአማራ ተጋድሎ
የገጠማቸው ውደቀትን አብረው ይጎነጫሉ። ቲካ ቲካ ሲሉት ስለማስተውል። አሁንም ካለፈው ግድፈት ሳይማሩ ተጻረው ተሰልፈው ነውና የማያቸው።
ከውደቀት እንዴት መማር አይቻልም? ግን ናቂዎች ስለሆኑ ያ ገናና እውቅናቸው ምን ላይ እንዳለ ያውቁታል። ምን ያህልም ዋጋ እንዳስከፈላቸው
ያውቁታል።
ከዚህ ለውጥ ከተባለው ሁለት ዓመት ቢቆዩ ያልቅላቸው
ነበር። ለዚህም ነው አገር ሲገቡ ዕድሉን በጥንቃቄ ይዘው መጓዝን የመረጡት። ችግሩ ግን አሁንም ማህበራዊ ንቅናቄ የፈጠረውን ባልደራስን
ድጠን እንወጣለን ዘመቻቸው ተጨማሪ ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው። ዲያስፖራውን አይተውታል። ብዙ መንፈስ እነሱን
ተስፋ ያደረገ አገረ ቤት የሚኖረውም ሸሽቷቸዋል። ሸኝቷቸዋልም። አለን ያሉት የተጠጉበት ቤተ - መንግሥትም ቢሆን ነጋ ጠባ ልክ
ልካቸውን እያኮመኮማቸው ነው።
ምንም አቅም አይኑረው አንድ ድርጅት። ግን ማድመጥ
ይቻል። ከማንም ይሆን ማደመጥ ጥሩ ነገር ነው። አሁን አብይዝም ማህበራዊ ንቃተ ህሊናን እራሱን ይፈጠራል ብሎ አላሰበም እስከ
60 ዓመት ድረስ። መሃን ትውልድ እንኳን ተፈጠረ ቢባል ማህበራዊ ንቃተ ህሊና በዬትኛውም ሁኔታ ላይ ይነሳል። ተጨባጩ ህሊናዊ ሁኔታ ለም ሆኖ ከተሟላ ይፈጠራል። አብይዝም 50በ60ን ሲነድፍ
ተፈጥሮን የካደ፤ ተፈጥሮን ሃራም ያለ አስተሳሰብ ነው። ያረጠ።
ድፍረታቸው ነው እኔ የሚገርመኝ። በጣም ይገርሙኛል።
መድፈር አቅም ያለውን አምክንዮዊ መንፈስ ነው። እሱን ሸሽትህ ገድለህም፤ አስረህም የተፈጥሮ ሂደትን እገድላለሁኝ፤ አስራለሁ ብትል
አንተ ማነህ ብሎ እራሱ የተፈጥሮ ሂደት ቅጣቱን ያሸክምኃል። ሲወድቁ እንኳን ለዘር የሚሆን ነገር ለማትረፍ ቢታሰብ መልካም ነው።
„አሟሟቴን አሳምረው“ ይላል ቅኔኛው የጎንደር ሰው።
ለዛውም እኮ ፍሬ ያለው ዕሳቤ ቢሆን እንኳን በሆነ።
የምናዬው ጭካኔ ነው። እርህራሄ የነጠፈበት ዘመን። ይህ የምናዬው ብትክት ነገር። የሥርዓት ምስቅልቅል ነው እኔ እማዬው በሁሉም
ዘርፍ። ዛሬ ሰዋዊነት አና ተፈጥሯዊነት የነገሰበት ሉላዊ ዘመን ነው ያለነው። ዕውቀቱም ግሎባል ነው። ሥልጣኔውም የዛኑ ያህል የመጠቀ
ነው። በዚህ በ10 ዓመት ውስጥ እንኳን ስንት ግሎባል ለውጥ አለ። እንኳንስ የዛሬ 50 እና 60 ዓመት። ዛሬ ኢትዮጵያዊው ዜጋ
ሉላዊ ዜጋም ነው። የዲጅታል ዘመን ነው። ከጉግል የመጠቁ ሥልጣኔዎች በላይም አዲስ በጣም አዲስ ፈጠራዎች ገና ይፈልቃሉ። ዓለም አብይዝምን ቁጭ ብላ
አትጠብቅም እና። መራራው ዕውነት ይኽው ነው።
በዚህ ምክንያት ህወሃት ያቀደው 40/50 መለሲዝም
አከተም። እሳቸው ኮርጀውም ለቃቅመውም „መደመር“ ብለው ከመለሲዝም 40/50 አፍንግጠው 50በ60 ብለው ከች አሉ። ያው የአማራ
የማንነት እና የህልውና ተጋድሎም በፍልስፍናቸው ስለማያካትቱት ያን ለመስበር ቀድመው እርምጃ የወሰዱበት መስሎ ቢታያቸውም ቀኑን
ቆጥሮ ከች ይላል፤ ዘመኑን በሚፈቅድለት ስልት እና ዘዴ።
አይደለም አዲስ ይመጣል ብለው ሊያስቡ እሳቸውን
ለሹመት ያበቀዋው ህዝባዊ ንቃተ ህሊና ዕውቅና ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ አልታዩም። አዳፍነው መቅበር አሰኝቷቸዋል።
ግን ሂደት በራሱ ጊዜ
ያቀርበዋል። ስለምን? ማንኛውም ነገር በእንቅስቃሴ በእድገት ላይ የሚገኝ ነውና። ከዚህ ጋር የዩንቨርስቲዎች፤ የትምህርት ተቋማት
መስተጓጎልም አብሮ ሊመረመር ይገባል። ሃሳብ አፍላቂ ትውልድን ከመፍራት የመነጬ ሊሆንም ይችላል። ትምህርት የሂደት ውጤት ነው።
በቅርብ አይታይም።
·
መኃን።
ጠ/ሚር አብይ አህመድ እሳቸውን የሚተካ ትውልድ
አይደለም የሚናፍቃቸው። በአስተሳሰቡ ማህን የሆነ ትውልድ ነው ምኞታቸው። ለዚህም ነው አቶ ኤርምያስ አመልጋ እና አቶ ክርስትያን
ታደለ የታሰሩት። ወደፊትም ብቅ የሚሉ አቅሞች ይጠላፋሉ ማለት ነው በዚህ ቀጫጫ ዕሳቤ መሰረትነት።
ይህን ንግግር እያዳመጥኩኝ እሳቸው ከተሾሙ በኋላ
እዬሰፋ የመጣውን የዩንቨርስቲዎችን ህውከት ሳስብ መሃን ትውልድን ከመናፈቅ የመጣ ስትራቴጃዊ አመክንዮ መሰለብኝ።
በአንድ ዓመት
ከ30 እስከ 40 ሺህ የሚገመት የዩንቨርስቲ ተማሪ ከትምህርት አገልግሎት መስተጓጎል ለዚህ አንድ የመነሻ ግብዕት ይሆናል። አሁን
በፖለቲካ ልምድ እና ተመክሮ ሙሉ የአማራ ሊሂቃን እና ኢታማጆር ሹሙ ህልፈት ከዚህ ጋር እኔ አዬዋለሁኝ። ለቀጣዩም በዚህ 18 ወራት
ያዬነው የመደበኛ ትምህርት መስተጓጎል እጅግ አሳሳቢ ነው ከ50በ60 ያረጠ ፍልስፍና ጋር በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል። ትምህርት
ውጤቱ ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩት በረጅም ጊዜ ነው እና የሚታዬው።
·
እርገት።
አዲስ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የሚያመነጭ ዛሬም የለም፤
ነገም እስከ 60 ዓመትም አይኖርም ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ። ይህ አጓጉል የጓጎለ ዕሳቤ ነው። የጎልማሳን፤
የወጣትን፤ የቡቃያን ብቻ ሳይሆን ገና የሚወለዱት ልጆችም ሃሳብ ሳይኖራችሁ ትፈጠራላችሁ ነው እዬተባሉ ያሉት። ምን ዓይነት ዲስክርምኔሽን እንደሆን አልገባኝም። በሽታ እንበለው? እንኩሮ ትልም
ነው። በግልም በወልም ሃሳብ ይፈልቃል። በዬትኛውም ጊዜ፤ በዬትኛውም ሁኔታ። በዬትኛውም ሥፍራ። ይህን የተፈጥሮ ሂደት የሚገድብ
አንዳችም ኃይል አይኖርም።
ብልጽግና ተመሰረትኩ ካለ ጀምሮ የሞግትኩባቸውን
ተጨማሪ አጫጭር ጹሑፎች ለማግኜት ከፈለጋችሁ ሊንኩ ይህ ነው። ፌስቡኬ ላይ የቀደመው ጹሑፌ በርከት ያለ ሲሆን ሁሎችም አጫጫር ናቸው። አንድ ብቻ እንዳይመስላችሁ በርከት ያሉ ናቸው። ወደ ቀደሙ ጹሁፎቼ ሄዳችሁ መመልከት ትችላላችሁ - በትህትና። አመሰግናለሁኝ።
ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ፍቅርም ሲያልቅ ትዕግስት ይሰደዳል።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ