የዴሞክራሲ ጽንሰት ውርጃ {ዘለግ ያለ ሙግት ከምርጫ ቦርድ ጋር}


 እንኳን ወደ ቀንበጠ ብሎግ በሰላም መጡ።

„ድሆች ግን ዳግመኛ በመኝታቸው ያስባሉ፣ ባለ ጠጎች ባይቀበሏቸው ግን ልምላሜ
እንደሌለው እንደ ደረቅ እንጨት ይሆናሉ፤ ርጥበትም ከሌለ ዘንድ ሥር አይለመልምም፤
ሥርም ከሌለ ቅጠሉ አይለመልምም።“(መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ ምዕራፍ 26 ቁጥር 1)

ዴሞክራሲ ንሰት ርጃ።

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Seregute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
29.12.2019



·         ቅድም።

አምላክ አለቀሰ
መርኽ አለቀሰ
የቃልኪዳን ሰነድ ሰለተቦደሰ
የህሊና ልኩ ስለተቀደደ።


·         ፍታ።

በዚህ ጹሑፍ የፖለቲካ ድርጅት አፈጣጠርን የሥርዓት ግሽበትን እንመለከታለን። መግቢያ ላይ ያለው ቃለ ወንጌልም ያመሳጥረዋል። ጉዳዬ ሥር ከሌለው ፍሬ ሰብል ጥበቃ ተስፋው ሩቅ ስለመሆኑ ያስተረጉማል። ተስፋ መውደቅ ሲያምረው እንዲህም ይፈተናል። የምርጫ ቦርድ አዲሱን የብልጽግና (ፓርቲ?) ህጋዊ ዕውቅና እንደ ሰጠ፤ በቱማታ እንደ መዘገበው ከሰሞናቱ ጠቅሷል። በዚህ አያያዝ የዴሞክራሲ ችግኝ ማብቀያ ተብሎ የታሰበው  የመጀመሪያ የጽንስ ውርጃውን አሳይቶናል። በአብን ላይ ያለው እምቅ ጫናን ቆዬን ብለን ማለት ነው። እሱ እራሱን የቻለ የታመለ የአምክንዮ ሽፍጥ ስላለበት። 

ግን የአገሬ ቅኔዎች እንዴት ናችሁ?

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ይህን የብልጽግና(ፓርቲ?) አመሰራረት የግድፈት አካሄድ በሚመለከት በፌስቡኬ ላይ አጫጭር ጹሑፎችን ሳቀርብ ሰነባብቻለሁኝ። አሁን ጫን ያለ የመርኽ ይፋዊ የክብረ ድንግልናና ጥሰት ተስፋ በተጣለበት የምርጫ ቦርድ፤ ለዛውም ፖለቲከኛ እና የህግ ባለሙያ በሆነችው በክብርት ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ በሊቀመንበርነት በምትመራው ቦርድ ስለመጣ ለቀንበጥ ብሎጌ ታዳሚዎች ጠንከር ባለ ትንተና ከእግዚኦታ ጋር ልሞግተው ፈለግሁኝ። ሙያውን የሰራሁበትም ስለሆነ።

በዚህ ውስጥ ያለው አሳሳቢ ጉዳይ የትውልድ ብክነት ነው። ትውልዱ ባልሰከኑ፤ አርቀው በማያስቡ፤ በግል ስሜት እና በግልብ ፍላጎት በታጨቁ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ሲናውዝ ይሄው ሁለት ትውልድ አልፎ ሦስተኛው ቀጥሏል። ዘለቀ፤ ጸና የሚባል አንድስ እንኳን የለንም። ህብረት፤ ግንባር፤ ጥምረት፤ ቅንጅት፤ ውህደት ሁሉም ይሞከራል ይተናል። ትውልድም ይባክናል ላም ጣም በሌለው ኑሮ። ለሥርጉትሻ ደግሞ ይህ የህሊናዋ መቅደመ ጉዳይ ነው። አንኳር በኽረ አጀንዳ። 

ምክንያቱም ሁልጊዜ እመኜው የነበረ ዘላቂ የሆነ፣ የሰከነ የትውልድ ጽኑ ፓርቲ ነበር። ልክ እንደ አሜሪካኖች ዴሞክራት እና ሪፓብሊካን ፓርቲ። የመጣ ቢመጣ፤ የሄደ ቢሄድ የማይናወጽ፣ ትውልድም የማይባክንበት። ያ የምኞቴ የትውልድ ፓርቲ ደግሞ እንዲህ በድንገቴ ተሞልቶ የሚመሰረት አልነበረም። የተጠና፤ የታሰበበት፤ ሰብዕዊነትን እና ተፈጥሯዊነትን የሰነቀ፤ እርጋታዊ ማስተዋልን የተላበስ ትውልዱን አጀንዳው ያደረገ ነበር ህልሜ። ተኖ - በኖ - መንኖ ቀረ።

ስለሆነም ብልጽግናን ከመፈጠሩ የጨነገፈ ብዬ ጽፌም ነበር በፌስቡኬ። የአመሰራረት ላይ ታች ዝብጠት፤ ውሽልሽልነት የናኜበት ስለነበረ። አሁን ምርጫ ቦርድም ማስተካከል፤ ማረቅ፤ ሥርዓት ማስያዝ ሲገባው ወሸኔ ብሎ ከእነ ግዙን ግድፈቶቹ እና የሥርዓት ጥሰት እድፉ ጋር ህጋዊ ዕውቅና ሰጥቶታል። ፐ¡¡¡ የትውልድ ታላቅ መርዶ።

የጨነገፈ ያልኩት ግን የትውልድ የመሆን አቅሙን እንጂ የዴሞክራሲ ቡቃያነቱን አልነበረም። እሱን እጠብቅ የነበረው ከምርጫ ቦርድ የአሰራር እና የአፈጻጸም ፍትኃዊ የማስተዋል መርኃዊ የፊደል ገበታ ነበር። እንዲህ ወርኃዊ ሆኖ ቁርጣችሁን እወቁ እስኪለን ድረስ። ብልጽግናው ሥራ ሳይጀምር ዴሞክራሲን አሳዬ ተብሎ ብዙም አይጠዬቅም። እንደ ጀማሪ ፓርቲ እንዬው ከተባለ። ለነገሩ ተዋህጃለሁ ነው መሰል የሚለው?!

እርግጥ ነው ከታች ወደላይ ስላልመጣም ዴሞክራሲን መዳጡን ማስተዋል ይቻላል። ይህም ብቻ ሳይሆን አባላቱ ባልተወያዩበት ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተቀበሉት ዓይነትም ነው እንግዲህ ነበሩን የኢህዴግ የግንባር አባላት በሽግግር ለብልጽግና በትውስት ወይንም እንደ ዕቃ እና መሬት በውርስ ከተላለፉ ማለቴ እንጂ ብልጽግና አንድም የፓርቲ አባል እስከዚህ ቀን ድረስ የለውም። ይህም በራሱ ሌላ የግድፈት ጠቀራማ ማሳ ነው። በፖለቲካ ፓርቲነት ለመጥራትም ጋዳ ይሆናል። ይህን እሞግትሻለሁ ያለ ይምጣና ይሞክረኝ። መርህ የቁሮ እንጨት አይደለምና። 

ማጠቃለያ ላይ ስለ አባልነት የምለው ይኖረኛል። ብቻ ዴሞክራሲ ማዕከላዊነትን ብልጽግና ያስቀራል ወይንም አሰቀርቷል ለሚሉ ተስፈኞች እንቆቆውን የጋተ ይመስላል አጀማመሩ በራሱ። ከሶሻሊዝም መርኽዊ መንፈስ ለመውጣት የቤተ መንግሥቱ የነገረ ሌንጮን የመጸሃፍ ገላጭነትን ወይንም ኮከብ ቆጣሪነት ስንታዘብ። ሌሎችም አሉ በረድፍ በረድፍ ትውልዱን እያመሱ ያሉ የ60ዎቹ አማካሪዎች። ገደል። ወጣቶች ዘመናቸውን በግፍ ተነጥቀው ይታሰራሉ የቅንድብ ጸጉሮች የጠሚር የክት አማካሪ ይሆናሉ። ግርንቢጥ።
    
·         ፓርቲ መሰረታዊ ሰነዶች የማጽደቅ ሥርዓታዊ ሂደቶች።

የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሰረታዊ ሰነዶች የሚባሉት ደንቡፕሮግራሙ እና መርኃ ግብሩ ናቸው። ማናቸውም የፓርቲው የአፈጻጻም መመሪያዎች ውስጥ መመሪያውን ጨምሮ  ከእነኝሁ ሦስቱ ሥላሴ ሰነዶች ይመነጫሉ። መርኃ ግብሩ ከሁለቱ ከፕሮግራሙ እና ከደንቡ ውስጠት የሚመንጭ ይሆናል። ሦስቱም ሰነዶች በአባላት ብሄራዊ ጠቅላላ ጉባኤ ብቻ ነው የሚጸድቁት። ብሄራዊ ጉባኤ በውክልና ነው የሚመሰረተው።

መሰረታዊው ሰነዶቹ የሚሻሻሉት፤ የሚሰረዙትም፤ የሚለወጡትም በአባላት ጠቅላላ ብሄራዊ አገራዊ ጉባኤ ብቻ ይሆናል። ስለደንቡ እና ስለፕሮግራሙ መሰረታዊ ይዘት ለዚህ ጹሑፍ የጭብጥ መነሻ ብዙም ስላማይጠቅም አላነሳውም። የጹሑፌ ጭብጡ የመርኽ ጥያቄ መፋለስ ስለሆነ የማጽደቅ ሂደቶቹን (The approval Processes) ብቻ መመልከቱ በቂ ይመስለኛል። ለዚህም ነው የፖለቲካ ፓርቲ ንድፈ ኃሳባዊ ትንተና ጊዜን የነፈግሁት።

·         ውሳኔ ሃሳብ ፈሰስ።

የሦስቱን የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረታዊ ሰነዶች የውሳኔ ሃሳብ ፈሰስ ከመሰረታዊ ድርጅት ጀምሮ ረቂቁን አባላቱ ይወያዩበታል። የማሻሻያ ሃሳብም ያቀርቡበታል። መሰረታዊ ድርጅት የአባላት ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለበት የፖለቲካ ድርጅቱ መሰረታዊ አካል ነው። የፓርቲው ከፍተኛ አካላት ሁሉ በውክልና ሳይሆን በቀጥታ እጅ በማውጣት የሚመረጡት በዚኽው መሰረታዊ ድርጅት የአባላቱ ጠቅላላ ስብሰባ ነው። የፓርቲው አስኳል መነሻ ማለት ይቻላል። የቀይ የደም ሴል። 

ከመሰረታዊ ድርጅት ቀጥሎ ያለው አካል የወረዳው ጉባኤ ነው። ከመሰረታዊ ድርጅቱ ቀጥሎ ያሉ አካላት ሁሉም የውክልና ሥልጣን ብቻ ይኖራቸዋል። የፓርቲው አገራዊ ሊቀመንበር የሚመረጠው መጀመሪያ ከመሰረታዊው ድርጅቱ ነው። እያንዳንዱ የበላይ አካል ከታች ወርዶ አብሮ ከአባላት ጋር ተሰብስቦ፤ መርጦም ተመርጦም ሥርዓቱን ፈጽሞ ነው ውክልናውን የሚያገኜው። 

በስማ በለው ፓርቲ አይመሰረትም። ሥርዓት ህግ እና የፈጻጸም መርሆ አለው። እንደዛ ቢሆን አቶ ለማ መገርሳ የጠሚር እጩነቱን ለዶር አብይ አህመድ አይሰጡም ነበር። ሥርዓት አስገድዷቸው ነው የሰጡት። የሳቸው ፓለቲካዊ ምደባ ስለሆነ። ልክ ሳጅን ተመሰገን ጥሩነህ እንደ መጡበት ሁኔታ።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ከመሰረታዊ ድርጅት ቀጥሎ ያሉ አካላት ወረዳው፤ ዞኑ፤ ክልሉ እና ብሄራዊው ይሆናሉ። የውክልና የምርጫ ሂደቱም በዬአካላቱ ጉባኤ ይከወናል። ልክ መሰረታዊ ድርጅቱ በረቂቅ ሰነዶቹ ላይ እንደተወያዬበት ሁሉ የወረዳው ጉባኤም በተመሳሳይ ሁኔታ አዲሱን የፓርታውን ሰነዶች ተወያይቶ የውሳኔ ሃሳቡን ለዞን ይልከዋል። ዞኑም መሰሉን ተግባር ፈጽሞ ለክልሉ ይልከዋል። ክልሉም ለብሄራዊ ጉባኤ።

አሁን በኢህዴግ የግንባር ህይወት 4ቱ የክልል ድርጅቶች እራሳቸውን የቻሉ ተናጠል የፖለቲካ ዞጋዊ / መልክዕምድራዊም ደቡብ / ድርጅቶ ስለነበሩ የዬራሳቸውን ደንብ፤ ፕሮግራም እና መርኃ ግብራቸውን በክልል ጉባኤ ላይ አጽድቀው፤ የኢህዴግ የግንባሩን ግን በብሄራዊ ጉባኤ ያጸድቃሉ፤ ያሻሽላሉ፤ ይሰርዛሉ። የአካላቱ ምርጫ እና ስንብትም እንዲሁ በብሄራዊ ደራጃ ይከወናል። (መርኃ ግብር ወይንም ዕቅድ ባህላቸው ምን እንደነበር አላውቅም እኔ ንጹህ ሥርዓቱን ነው እምጽፈው)

·         ድፈት።

በብልጽግና (ፓርቲ?) የተከናወነው ስንመለከት መጀመሪያ በኢህዴግ ሥ/አ/ኮ ቀጥሎ በማዕከላዊ ምክር ቤት ፕሮግራም እና ደንብ ጸደቀ ከተባለ በኋላ ማህል ላይ በኦሮምያ ክልል የብልጽግናው ፓርቲ ሹመቱ ተሰጠ። ኮሚክ ተውኔት። የልግጫ - ዋንጫ። ነጮቹ ቢሰሙ ምን ሊሉ እንደሚችሉ አላውቅም። ምክንያቱም የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ዕውቅና ከኢህዴግ ህጋዊ ሥልጣን ጋር የተጣመረ ስለሆነ። ሲፈርስም ሲተካም ፕሮሲጀራሊ መሆን እንዳለበት ብሄራዊ ሳይሆን ሉላዊ መርኃዊ ስምምነትም ስላለ። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ታሪክ ኢህዴግ ነው ኢትዮጵያን ሲገዛ የኖረ በአውራው ፓርቲ በህወሃት አማካኝነት፤ አሁን ኦዴፓ።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ፌድራል ላይ በተዛነፍ አጸዳደቅ ሂደት ከተከናወነ በኋላ የዬክልል ጉባኤዎች ተካሂደው የብልጽግናውን ደንብና ፕሮግራም ጸደቀ ተባለ። ይህን ያደነቁ ሰዎች አዳምጫለሁኝ ትክክልም እንደሆነ ሲናገሩ ሰምቻለሁኝ። መደነቅ ሳይሆን ሊወቀስ እና መንገዱን እንዲስተካከል መርኽዊ ሙግት ሊቀርብበት ይገባል። የኢህዴግ ሥ / አስፈጻሚ ይሁን ማዕከላዊ ምክር ቤቱ የፓርቲ ፕሮግራም እና ደንብን የማጽደቅም የማሻሻልም ምንም ሥልጣን የላቸውም። ህገወጥ ተግባር ነው የተከወነው።

እራሱ የክልሎቹ ድርጅቶች /ብአዴን፣ ደህዴን፣ ኦዴፓ/ የብልጽግናውን ደንብ ፕሮግራም ረቂቅ መርምረው ማሻሻያ ለብልጽግናው ብሄራዊ ጉባኤ ማቅረብ እንጂ የማጽደቅ ቅንጣት ታህል መብት የላቸውም። ማድረግ የሚችሉት የራሳቸውን ቀደምት ሰነዶች ዋጋ እንደማይኖራቸው ወስነው፤ እራሳቸውን ማክሰም ብቻ ነው ይጠበቅባቸው የነበረው እንጂ ብልጽግናውን ተካን ማለት ፈጽሞ አይችሉም። ኢህዴግንም አፈረስን ማለት አይችሉም። ብልጽግናው ሃሳብ ላይ ያለ የተንሳፈፈ፤ አድራሻው ያልታወቀ ቋጠሮ ምናብ ነው የሆነው የአፈጻጻም ሂደቱ በጥሞና ሲጠና። የጨረቃ ቤት እንደሚባለው።

 ምክንያቱም ተፈጠርኩ ሲል አንድም ሥርዓት አልተከተለም። የተፋለሰ አካሄድ ነበር። ዝብርቅርቅና ውጥንቅጥ። ይህን ደግሞ ማስተካከል፤ ማረም የሚገባው ብሄራዊው የምርጫ ቦርድ ነበር። ህግ ጥሰትን ህጋዊ አደርጎ እንደ ተቀበለ ነው እያዬን ያለው።  የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የህዝብ እና የመንግሥትን ኃላፊነት የቤተዘመድ ውሎ አድርጎት አረፈው። በቀኝም ይምጣ በግራ የአንድ ማህበረሰብ ፍላጎት ብቻ ይፈጸም ተብሎ ተደምድሟል። ጉዳዩ ይኸው ነው ዴሞግራፊ የህሊና ነቀላና ተከላው ተመስጥሮ በዚህ ሂደትም ይታያል። በዴሞግራፊ እና በጠንቅነቱ የበሰለ ተግባር ሊሰራ ይገባል የምለውም እኔ ለዚህ ነው። ቀንበጥ ብሎጌ ላይም ብዙ ሰርቼበታለሁኝ። 

ሂደቱ ሲስተዋል … የብልጽግናው ምሰረታ ሆነ የሰነዶቹ የማጽደቅ ሂደት ውስጡ ሱሪ ከሱሪ በላይ ወይንም ሸሚዝ ከጃኬት በላይ የመልበስ ያህል ነው ሂደቱን በጥሞና ስትከታተሉት። የቅደም ተከተል ብቻ ሳይሆን ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት በድፍረት በሥርአት አልባ ሂደት ተገርስሰዋል። 

በዚህ ሂደት ምርጫ ቦርዱ ምንም ማረሚያ አልሰጠም። የማንን ጎፈሬ እንደሚያበጥር አይታወቅም። የምርጫ ቦርድ ሥልጣኑ የመንግሥት ጥገኛ ወይንም አሽከር ሆኖ ነው የምታዩት። አሁን ላይ የየትኛው መንግሥት እንዳትሉኝ፤ እኔም አላውቀውም።
አሁን ያለው የብልጽግና ይሁን የኢህዴግ መንግሥት የሚታወቅ ነገር የለም። የቄሮን ኢንፓዬር ቆዬን ብለን። የጉለሌውን አጤ እስቲ ታገሰን ብለን። የአጤ ደጺን ምናብም እስቲ በእርጋታ ተግ በል ተብሎ።

ያው አለሁኝ በሚለው የአብይ ካቢኔ ምንም ዓይነት ሥርዐታዊ ክንውኖች በስክነት አልተከወነም። ሂደቱ ቦጅቧጃ ነው። አሁን እራሱ እዬገዛ ያለው ማን እንደሆን አይታወቅም። ከህወሃት ጋርም በጥምረት ይሁን በተፎካካሪነት ወይንም በተቃዋሚነት ብልጽግናው የሚቀጥልበት ሁኔታ የሚታወቅ ነገር የለም። 

በዚህም ዘርፍ የንብረት ክፍፍሉን ሂደት አሁንም ተግ እባክህ በልልን ብለን ተለማምጠን ማለት ነው። ብዙ መርኽዊ ጉዳዮች አዬር ላይ እንደ ተንጠለጠሉ ተንሳፈው እግዚኦታ ላይ ነው ያሉት። የፖለቲካ ድርጅት ፓርቲ ምስረታ የቅደም ተከተል ሥርዓታት ሱባኤ ገብተዋል። በዚህ ውስጥ አገር የሚመራው ነው እንዲህ ባለ የፖለቲካ ግሸበት ላይ የሚገኜው።  እንደ ዜጋ የሁላችንም ኃፍረት ነው። 
 
ነባሩ የግንባር አባል ድርጅቶች ብአዴን፤ ኦዴፓ፤ እና ደህዴን ነባር የመሰረታዊ ድርጅቶቻቸው አሳኮሎቻቸው አዲሱን የብልጽግና ሰነድ አልተወያዩበትም፤ የማሻሻያ ሃሳብ እንዲያቀርቡበትም አባላት መብት አልተሰጣቸውም፤ ነባሩንም ሰነድ የመሰረዝ መብት አላገኙም። የብልጽግና ወኪሎቻቸውንም አልመረጡም። ድፍን ቅል የሆነ መከራ።
ዴሞክራሲ ይሉኃል ይሄ ነው። በድፍጠጣ። በእርግጫ በዘመነ ዬሜጫ ሱናሜ። 

ለዛውም የብልጹግ (ፓርቲ?) የምስራች ደወል ዴሞክራሲ እንዲህ በጫና ሰንጎ ከቸች ብሏል። በአንድ ነፍስ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ተስፋ። የዚህ ነፍስ ተስፋ በተፈጥሮ ሂደት የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና የሆነ አደጋ ነገር ቢሆን የመንፈስ ጥሪት የለም። የመርኽ ጥሪት የለም። የሥርዓት ጥሪት የለም። የተማከለ የአቅም እርሾ የለም። ኦ! አምላኬ።
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ፤ … ለምሳሌ የብአዴን የመሰረታዊ ድርጅቶች፤ የብአዴን የወረዳዎች፤ የብአዴን የዞናት አካላት ነባሩን የብአዴንን ሰነድ ተወያይተው እንዲከስሙ የውሳኔ ሃሳብ አላቀረበም፤ የአዲሱን የብልጽግናንም መሰረታዊ ሰነዶችም አያውቃቸውም፤ አልተወያዩበትም፤ አካላቱንም እራሱ አያውቋቸውም በማን እዬተመሩ እንደሆነ የሚያውቁት ነገር የለም። 

ምክንያቱም እነሱ አልመረጧቸውም እና። የጤፍ ጠላ የሆነ ነገር ነው። የሚገረመው የክልሉ ብአዴን ግን እራሱን አክስሞ ብልጽግና ነኝ ብሎ አውጇል። ፍሬ ሳይዘራ የሰብል ጥበቃ። መሰረታዊ ድርጅት ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዘር እና ማሳ ነው። የመሠረት ድንጋይ።   

በንፋስ ኃይል እዬተገፋ የሚሰራ ወፍጮ አለ እንደዛ ነገር ነው የሆነው። መሰረቱም ላዩም እንደተንሳፈፈ ነው። መሰረቱ መሰረታዊ ድርጅት ሲሆን ቁንጮው ወይንም መዳረሻው ብሄራዊ ጉባኤ ነው። የታዬው ግን ጅዋጅዊት ነው። 

ለማታውቀው ሰነድ ተገዢ ሁን በፓርቲ ታሪክ ውስጥ ሆነ የማያውቅ ገማና ነው። ነባሩን የኢህዴግን አመራር ላይፈልግ ይችላል አባላቱ፤ ይህም ዕድል አልተሰጠውም። አዲሱን ብልጽግናንም ላይቀበል ይችላል አባላቱ።

ዝም ብሎ ስታስቡት የፌስቡክ የአዬር ላይ ጎጆ ወይንም ትዳር ዓይነት ይሆንባችኋል። ማያያዣ ቀርቶ እናስታምመው ቢባል የመርኽ ቅርጥምጣሚ ታጣላችሁ። ተደማሪ ሚዲያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ሚዲያ ደግሞ ሥርዓት መጣሱ ስንቅ ሆኗቸው በዕልልታ እና በኩልልታ ያጅቡታል። ማፈር ይገባቸዋል። 

አንድ ቤት ሲሰራ መሰረት ይሰራለታል፤ ከዛ ጣሪያው አለ። አሁን ሁሉም የለም ሥሙ ብቻ ነው ነው ያለው። ግድግዳው መርኽ ነው እሱም የለም። መሰረት ላይ አልተነሳም ጣሪያውም አልተከደነም። ነባሩም ኢህዴግ የለም እያሉን አዲሱም ጉባኤ ሳያካሂድ፤ አማራሩ ሳይታወቅ አለን እያሉ ነው። በአለንየለም ይመዝገብላቸው። አለን የሚባለው በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ነው። 

ጠሚር አብይ አህመድ ስልጣን ስላላቸው ብቻ በአንዳዊ አመራር ነው እንዲህ እና አንዲያ እዬተሆነ ያለው፤ አራጊም ፈጣሪም እሳቸው ብቻ ናቸው። ይህ ነገ ወደዬት ሊያመራ እንደሚችል ፈጣሪ ይወቀው። እሳቸው የጋራ አመራር ብሎ አያውቁም። ማድመጥ አልተሰጣቸውም። ጠረኑ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን መንገድ የተከተለ ይመስላል።
የምርጫ ቦርዱ መርኽን እንዲያስፈጽም ተቀምጦ መርኽ አፈጻጸም ላይም የክት እና የዘወትር እንደ አበጀ ነው እኔ እማስበው። 

የታሪክም፤ የቱሩፋትም ግድፈት ለፖለቲካ ባህልም ግርፋት ነው መንገዱ። አንድ ፓርቲ የራሱ ማንነት አለው። ማንነቱ የሚመነጨው ደግሞ ከአመሰራረቱ ጀምሮ ባለው ሂደቱ ጨዋነት ነው። ለዚህ ለራሱ ጥንቃቄ የተደረገ አይመስልም። አገራዊ ታሪክ ጨምሮ ነው እየነደደ የሚገኜው። ብክነት - በፍቀት።

አዲሱን ብልጽግና ወረዳዎች አያውቁቱም፤ የወረዳ ጉባኤ አልተካሄደምና። ነባሩንም አልሰረዙም በወረዳ ጉባኤ አልከሰሙም እና። ዞኖች በአዲሱ ላይ አልተሳተፉበትም። ነባሩንም አላከሰሙም።

ከሁሉ ደግሞ የሚከፋው ሦስተኛው ሰነድ ጭራሽ ሲነሳ አልሰማሁም። ደንብ እና ፕሮግራም ብቻ ነው የሚባለው። ዋናው መርኃ ግብርስ? መርኃ ግብር የአጭር፤ የረጅም ጊዜ ተብሎ ይሰናዳል። የሁለቱን ሊንክ ሆኖ የሚያገናኝ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ነው። ይህም ተሰናዳም ረቂቅም ቀረበም ጸደቀም ሲባል አልሰማነም። የብልጽግናው ምጥቀት¡ የፖሊሲው ሁሉ መተግበሪያ ነው መርኃ ግብሩ። ውሽልሽል የሆነ ነገር ነው እያስተዋልን ያለነው። ንቃቃታ

የግድፈቱን ዓይነት የሚገልጽልኝ ቃል ማግኜት አልቻልኩም። አናርኪዝም ልበለውን? ከላይ እንደጠቀስኩት የፖለቲካ ግሸብት ልበለውን? ወይንስ የጨረቃ ቤት? ሂደቱን ስታዩት ዲፕሬሽን ውስጥ የሚማቅቅ ነው የሚመስለው። ጉዞውን ውጋት የሚንጠው። ወይንም ስቅዛት የሚያጣድፈው። መርኃ ግብር ወይንም ዕቅድ የሌለው ፓርቲ ምን ሊባል ይሆን? ሥምየለሽ እንበለውን?! በምኑ ይሆን ብልጽግና ከሰማዬ ሰማዬት ወርጄ ከመደመር ተወልጄ ተከሰትኩኝ ካለ ካቢኔውን እዬመራ የሚገኜው በዬትኛው መርኽ ዕቅድ? ተዕብ!

·         ብልጽግና (ፓርቲ?) የዕውቅና ሂደት።

ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ተቀብልኩት ያለው የብልጽግና (ፓርቲ?) በዬትኛው የብልጽግናው ብሄራዊ ጉባኤ የጸደቀውን መሰረታዊ ሰነድ (ደንብ፤ ፕሮግራም፤ ዕቅድ ወይንም መርኽ ግብር )? በዬትኛው የብልጽግናው አገራዊ ጉባኤ የተመረጠውን ማዕከላዊ ኮሜቴ? በየትኛው የብልጽግናው ብሄራዊ ጉባኤ የተመረጠውን የኦዲት እና ቁጥጥር ኮሚሽን አውቆ፤ በዬትኛው አገራዊ የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሜት የተመረጠውን ሥራ አስፈፃሚ ወይንም ፖሊት ቢሮ አይቶ፤ አረጋግጦና መርምሮ ነው ህጋዊ እውቅና የሚሰጠው? ለመሆኑ ብልጽግናው ዕቅድ መርኽ ግብርስ አይደለም የጸደቀ ረቂቅ አለውን? „ላም አለኝ በሰማይ“ የሆነ ነገር።

ኢትዮጵያዊው የምርጫ ቦርድ እውር ድንብሱን ዕውቅና ይሰጣልን ለአንድ ኢትዮጵያን ለሚያህል ገናና አገር ለሚመራ አውራ ነኝ ለሚል ድርጅት? ከቶ ሳያነቡ ፊርማ አለን? አገር እኮ ነው። አገር እንዲህ ባለ ቀልድ እና ቧልት ይመራልን?! ኃላፊነትም ተጠያቂነትም ክው ብሎ የደረቀበት ረጭራጫ ራጫማ መንገድ። አዬ ኦሮሙማ! በዬቦታው ዱቅ እያለ መላ ቅጥ አሳጣው ሁሉመናውን መቅኖ ነሰቶ በመርኽ ጥሰት በድገቴ ተውኔት አሽቆጥቁጦ።
 
አገር ለሚመራ ፓርቲ በዚህ መሰል ግዙፍ ጥንቃቄ ጎደል ሁኔታ ዕውቅና ይሰጣልን? ማንም ምንም ከህግ በላይ የለም፧ ሁሉም በህግ ፊት እኩል መሆን አለበት። ይኖርበታልም። ለህግ የማይገዛ ነፍስ የአገር መሪ ድርጅትን ሊመራ አይችልም። ለዚህ ሚዛን የተሰጠው ደግሞ አገር መምራትን እንደ አሻቦ ወይንም እንደ አሽዋ ሜዳ ላይ የሚታፈስ የመስክ ውሎ አድርጓታል። ጥበብ የነጠፈበት፤ ማስተዋል የገረጣበት።

ሌላ አዲሱ ህጋቸው 10ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ የሚልም አለበት፤ ይህስ? በቃ ተፎካካሪ/ ተደማሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ ለሚባሉት የደጅ ልጆች ወይንም የማሟያ መላሾኞች ብቻ ይሆን የሚሰራውን በዬቀኑ ውሃ በቀጠነ የሚሰናዳው የዘመነ አብይዝም ህግ ማምረቻ ካንፓኒ? 

·         ዴታ መሆን የነበረበት።

የኢህዴግ ማዕከላዊ ኮሜቴው አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ነባሩን የኢህዴግ ሥ/አ/ኮ በቅድሚያ ማሰናበት ነበረበት። አስቸኳይ ጉባኤ እንዲጠራ መወሰን ነበረበት።

·         ኢህዴግ ጉባኤ ተግባር እና ኃላፊነት። መሆን የነበረበት። 

1)      ነባሩ የኢህዴግ ማዕከላዊ ኮሜቴው፤ ቁጥጥር እና ኦዲት ኮሚሽኖች ስላከናወናቸው ተግባራት ሪፖርት ያዳምጣል፤ የመረጠው አካል ጉባኤው ነውና።
2)      ነባሩ የግንባሩን ሰነድ የመሰረዘ ውይይት ያካሄዳል። ይፈጽማልም።
3)      ነባሩን የማዕከላዊ ኮሜቴ አካላት የማሰናበት ሂደት ይፈጸማል፤
4)      ነባሩን የኦዲት እና የቁጥጥር አካላት የማሰናበት ግዴታ ይከውናል። ምክንያቱም የኢህዴግ ሥ/አ/ ወይንም ፖሊት ቢሮ አባላት በማዕከላዊ ኮሜቴ ሲመረጥ የኢህዴግ ማዕከላዊ ኮሜቴ፤ ኦዲትና ቁጥጥሩ ሁለቱ ከፍተኛ አካላት በቀጥታ የሚመረጡት በብሄራዊ  የኢህዴግ ጉባኤ ስለሆነ የመረጣቸው አካል ብቻ ነው ማሰናበት የሚችለው። ተጠሪነታቸውም ለብሄራዊ ጉባኤ ብቻ ነውና። ይህ ሂደት አልተፈጸመም። ለድርድርም የሚቀርብ አይደለም። የህግ ጥሰቱ ልክም መጠንም አልተሰራለትም። ኢህዴግ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ ግንባር ነው እንዲህ የውሻ ሞት የተፈረደበት።
 
·         የብልጽግናው (ፓርቲ?) ጉባኤ ተግባርና ሃላፊነት። መሆን የነበረበት።

ብልጽግና የግንባሩን አባል ድርጅቶች እያከሰመ ሲመጣ ከመሰረታዊ ድርጅት ጀምሮ እራሱን በውህድነት እዬፈጠረ መምጣት ነበረበት። በስክነት። እርግጥ ዕድሉ አልፎታል። ዘግይቷልም። አሁን በጭብርቅ አንባርጭቃ ሆኗል። ነገር ግን የሆነው ከላይ ወደታች ነበር። እሱም ሙሉ ለሙሉ አልተከናወነም። ክልል ላይ ተንሳፎ ነው የቀረው። ይህም ወደል ግድፈት ነው። 

ቀድሞ ነገር እንኳን የኢህዴግ ሥ/አሰ/ኮ ቀርቶ የኢህዴግ ማዕከላዊ ምክርቤት፤ ቁጥጥር እና ኦዲት ኮሚሽንን መሪ አካላትን አስወግዶ ኢህዴግን የማፈረስ፤ ነባር ሰነዶችን የመደምሰስ ሥልጣን በፍጹም የለውም። ይህ የጉባኤ ተግባር ነውና። ብሄራዊው ጉባኤ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የመጨረሻው የሥልጣን አካል ነው።

እርግጥ ነው ጉባኤ እስኪሰበሰብ ማዕከላዊ ምክር ቤት የጉባኤውን ኃላፊነት እና ተግባር ተክቶ ይሰራል፤ ማዕከላዊ ኮሜቴ እስኪሰበሰበሰብ ሥ/አስፈጻሚ ኮሜቴ የማዕከላዊ ኮሜቴውን ተግባርና ኃላፊነት ተክቶ ይሰራል ሲባል ለሌሎች ሩትን ዕለታዊ ዝርዝር ተግባራት እንጂ የመሰረታዊ ሰነድ ደንብ፤ ፕሮግራም፤ ዕቅድ የማጽደቅ፤ አገራዊ ግንባር ሆነ ፓርቲውን የማክስም፤ የማዕክላዊ ኮሜቴ፤ ኦዲት እና ቁጥጥር የመመረጥ እና የማሰናበት ወዘተ ሥልጣን የለውም የትኛውም አካል ከአገራዊው ጉባኤው በስተቀር። የአንድ ፓርቲ ብሄራዊ ጉባኤ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት ህልውና ህገ መንግሥቱ ነው። የሂደቶች ሁሉ መከወኛ እጬጌ ነው።

·         ሆነ ሆኖ ብልጽግናው ፈቃደኛ የሆኑትን የግንባሩ አባል ድርጅቶች ብቻ እና በአጋርነት ወደ አካልነት ሽግግር ላይ የሚገኙትን የጋንቤላ፤ የሱማሌ፤ የቤንሻንጉል ጉምዝ፤ የአፋር ተወካዮችን ጨምሮ የብልጽግናው ጉባኤ ተሰብስቦ መጀመሪያ የጉባኤውን ሂደቱን የሚመሩ ጊዜያዊ አካላት ወይንም ፕሬዚዲዬም ይመርጣል። ምክንያቱም ዕውቅና ያለው በምርጫ የመጣ ተመራጭ ሰሌለው ብልጽግናው። ከመሰረታዊ ድርጅትም አልተነሳም። ክልል ላይ የተንጠለጠለ ነው።  
  
·         የሆነ ሆኖ በጊዜያዊ የፕሬዚዲዬሙ ሰብሳቢነት አጀንዳዎች ቀርበው ይጸድቃሉ።
·         በፕሬዚዲዬሙ ሰብሳቢነት የብልጽግናው መሰረታዊ ሰነዶችን ረቂቅ ደንቡን፤ ረቂቅ ፕርግራሙን የዘለሉትን ረቂቅ መርኃ ግብሩን ወይንም ዕቅዱን መርምሮ የማጽደቅ ግዴታ ነበረበት። ግን አልተከናወነም።

·         አዲሱ የብልጽግና አርማ የሚጸድቀውም በዚሕው ጉባኤ ነው። ያው ደንቡ ላይ አብሮ የመጽደቅ ዕድል ቢኖርም ግን ይፋዊ የሆነ ሂደቱ በጉባኤውም እንደ አጀንዳ ተይዞለት ቢከወን የበለጠ ዕውቅናውን ያደምቀዋል። ምኞቱ ብልጽግና አይደል? ተስፋ አይከለከልም፤ አይገደብምምና። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ዓርማ ህይወት የሚሰጠለት ታምረኛ ምልክት ነው። ይህ ታዲያ በድንግልና ለሚቀበሉት እንጂ በዬዘመኑ ጃኬታቸውን እዬቃያዬሩ ለሚቀላወጡት አይደለም ይህን የምለው። 

·         ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን የብልጽግናው ጉባኤ አስመራጭ ኮሜቴ በፕሬዚዲዬም ካስመረጠ በኋላ አዲሱን የማዕከላዊ ኮሜቴ አካላትን እና ኦዲት ቁጠጥር ኮሚሽኖችን ይመርጣል። ከህወሃት ውክልና የተሰጣቸውን በምርጫ አያሳትፍም። በጉባኤም አያሳትፍም። ህውሃት አልደመርም ብሎ እራሱን በግብር አግልሏል። ሁለት ወዶ የለምን እና። ስለዚህ በህወሃት የሚታወቁት ባለሥልጣናት የኢህዴግ የሥ/አ/ ኮሜቴ፤ የማዕከላዊ ምክር ቤት፣ የኦዲት እና ቁጥጥር ኮሚሽን አካላት በሙሉ በዚህ ጉባኤ አይሳተፉም፤ የሥልጣን ውክልናም አይሰጣቸውም። ቤት የለቀቀ ሰው አዲስ በገባው ሰው ላይ የመዳበል መብት የለውም።

ይህን የማስፈጸም አቅም ሊኖረው የሚገባ ደግሞ የምርጫ ቦርድ ነበር። ይህን ዋሳኝ መርኽዊ ተግዳሮት ችሎ ይፈጽማዋል ወይ ስል ጋዳ ነው። እሱ እራሱ የመንግሥት አሽከር ሆኖ ነው እያዬሁት ያለው። እራሱ በዚህ ውስጥ የአቶ ለማ መገርሳም ጉዳይ በዚህ ዳኝነት ጉዳይ የሚታይ ይሆናል። ይህን የሚያደርገው የመርኽ ሰው ኢትዮጵያ ቢኖራት ነው። አሁን አቶ ለማ መገርሳ የብልጽግናውም ጉባኤ ተሳታፊ የመሆን አቅም የላቸውም። ታረቁን ሰምተናል። ነገር ግን ዝርዝሩን ማወቅ አለብን። መብት አለን። ይህ የቀልድ ተርቲማቸውን ማውለቅ ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም ህወሃት ይዞት የነበረው ሥልጣንና ሃላፊነት በቀጥታ በብልጽግናው ከማዕከላዊ ኮሚቴ ለሚመጥኑት አዲሶቹ ይይዙታል። አሁን እንደማዬው አዝማሚያ ግን አዲስ ሌላ ድርብ ዕድል እዬተሰጠ እና በሁለት ፓርቲ የመታቀፍ ዝንባሌ እያዬሁ ነው። እራሱ ህወሃት ነባር የወከላቸውን አባላት ይሁን አካላት በራሱ ጉባኤ፤ በራሱ ማዕከላዊ ምክር ቤት ማሰናበት ይኖርበታል ይቀጥሉ ቢባሉ እንኳን።

 ለነገሩ አሁን የሁለቱም አካላት ናቸው በህግ ጥሰት ፍዳዋን በምታዬው አላዛሯ ኢትዮጵያ። ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን እንደ ምሳሌ ባነሳ የብልጽግናውም የህውሃትም አባል ናቸው። አንድ ሰው የሁለት ፓርቲ ውክልናን በዓለም ታሪክ ተስተናግዶ አይታወቅም። ንፍዘት! ዜጋው እንዲህ ነው ዕድሉ እዬታጠፈ የሚገኜው። በተለይ ወጣቱ። የሚችሉት ቀድመው የተሰናበቱት አቶ ዛዲግ አብርሃም ብቻ ይሆናሉ አባልም፤ አካልም የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው የሳቸው በብልጽግናው። 

በዚህ ውስጥ የሌሎች ተተኪ ወጣቶች ዕድል እዬተቃጠለም ነው። ነባሮቹ ከሥልጣናቸው ካለቀቁ የጋንቤላው፤ የቤንሻንጉሉ፤ የአፋሩ፤ የሱማሌው ሊሂቃን የቦታ ሽግሽግ ዕድል አይገጥመውም። አቶ አስመላሽ ወ/ሥላሴ የኢህዴግ ጽ/ቤት አማካሪ ናቸው። አሳቸው ተሸኝተው በአዲሱ የብልጽግና ውስጥ ያለ ሰው መተካት ግድ ይላል። መርኽ አስፈጻሚ ቆራጥ ልጅ ኢትዮጵያ ቢኖራት። ግን ሁል ጊዜ ክህደት ነው የሚፈጸምባት።
·                 የብልጽግናው ጉባኤ አዲስ የኦዲት እና የቁጥጥር አካላትን ይመርጣል። በተመሳሳይ          ከህወሃት ውክልና ነጻ በሆነ ሁኔታ ይህም ይከወናል።

በሌላ በኩል አዲስ የተመረጠው የብልጽግና (ፓርቲ) ማዕከላዊ ምክር ቤቱ የራሱን ስብሰባ አድርጎ የብልጽግናውን ሥ/አ/ኮሜቴ ይመርጣል። ሊቀመንበሩን፤ ምክትሉን፤ ጸሐፊውን ለጉባኤው ያሳውቃል፤ የህወሃት ውክልና በዚህም አይኖርም። ይህ በብሄራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተዋረድ የሚከውን ተግባር መሆን ነበረበት። አዲስ አበባን ጨምሮ ግን አልተከናወነም። ማህል ላይ ተንሳፎ ነው የቀረው። 

መቋጠሪያም አልተበጀለትም። ፓርቲ ለማለት እኔ አልችልም። ለዚህ ነው ቅንፍ ውስጥ የማስገባው። ጥሰት የበዛበት ኩነት ስላለ በብልጽግናው። ኢትዮጵያ በዬዘመኑ እንደ ጥንቸል የሙከራ ጣብያ ነው የምትሆነው። በግለሰብ አምልኮ በሚናጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ። በዚህ ውስጥ የሚደቀው ተመክሮ በአገር ሃብት ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። ታስቦበትም አይውቅም። ንቅዘት። 

ወደ ቀደመው ጉዳይ ስንመለስ እንጨት ተለቅሞ ማሰሪያ ልጥ ከሌለው ከጫካው ይቀራል። ልክ እንደዛ ማለት ነው። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት መነሻው መሰረታዊ ድርጅት ሲሆን መዳረሻው ብሄራዊ ጉባኤ ነበር። ሁለቱም አብሰንት ናቸው። ግንጥል ጌጥ። ወይንም ግማሽ ራስ ሹሩባ።

 የሚገርመው አብረው የሚሠሩት እራሱ ይህን ሥርዓት አልበኝነት ጉዞ መቅጣት፤ መግራት፤ ማረቅ አልቻሉም። ግርባው ብአዴን በተለዬ። አብሮ እንደለመደበት በደመነፍስ ይጋልባል። ዘመን የማያስተምረው የጉድ ቁልል። የአገርም ጠንቅ። እንቅፋት።

በፓርቲ ህይወት ወስጥ አደገኛው የውስጥ ደዌ ሥርዓት አልበኝነት ነው። ይህ በይፋ በብልጽግናው (ፓርቲ?) ሰፍኖ ታዩታላችሁ። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት ወጣት ወደ ሥርዓት አልበኝነት ጉዞ ላይ ነው። ከማን ይማር? ቢያንስ ምርጫ ቦርድ ይህን መልክ ለማስያዝ እንዴት ይሳነዋል? እንብኝ ካለ መንግሥት ምርጫ ቦርድ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ቢሮውን መዝጋት ነበረበት። በቃ። መርኽ ከሌለው አንድ ድርጅት ምን ሊሆን ይቀመጣል። ለሥርዓተ አልበኝነት ንግሥና? ማህከነ!

·         ርጫ ቦርድ ልፍስፍስነት እና የመርኽ ትልልፍ።

„ህግ ተላላፊዎችን ጠላሁ“ ይላል ልብ አምላክ ንጉሥ ዳዊት። የህግ ባሙያ ሊሂቅ ህግ ሲተለላፍ ደግሞ ምን ይል ይሆን ይህ ምስባህክ? እኔ እንደማስበው ብልጽግና የቀብድ የፖለቲካ ድርጅት ወይንም የመያዦ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ለማያልቀው የሰብዕና ግንባታ ልዩ ዳረንጎት።

1)      ህዴግ መፍረሱን ምርጫ ቦርድ በምን አረጋገጠ እና ህጋዊ ዕውቅና ሰጠ?
2)      አሁን ምርጫ ቦርድ ኢህዴግ መፍረሱን ተቀብሎ ለብልጽግናን ዕውቅና
       ከሰጠ ማነው የብልጽግናው (ፓርቲ) ሊቀመንበር፤ ማነው የኦዲት እና
       የቁጠጥር ኮሚሽን ሰብሳቢ? እነማን ናቸው የብልጽግናው ሥ/አሰ/
       አካላት/ወይንም የፖለቲ ቢሮ አባላት?
       እናማንስ ናቸው የብልጽግናው የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላትስ? እነማንስ
       ናቸው የብልጽግናው የጉባኤ ውክል አካላት? በጓዳ ድርድር የቀብድ ብልጽግና
       ተመሰረተ? ስንት ዓይነት ቀልድ ነው ያለው?
3)      ብልጽግናው ፕሮግራም እና ደንቡም እንዲሁም የተረሳው መርኃ ግብሩ
         በጉባኤ ካልጸደቀ  ዕውቅና አንድ ፓርቲ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ
         ደንብ እና ፕሮግራም በጉባኤ ያላጸደቀ ፓርቲ፤ ዕቅድም የሌለው እንዴት
         ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅና ሊሰጠው ይችላል? በምን ቀመር?! በዝምድና፤
          በአምቻ በጋብቻ? ወይንስ በችሮታ? ወይንስ በርህርህና?! ልግጫ።
4)           ሌላው ወሳኙ ጉዳይ አሁን እኮ ማዕከላዊ ኮሜቴ፤ ኦዲት እና ቁጥጥር
            ላይ፤ ሥ/ አ/ ኮሜቴ ላይ የሱማሌ፤ የአፋር፤ የጋንቤላ፤ የቤንሻንጉል፤
            የአፋር አካላት የፖለቲካ ሊሂቃን መኖር ግድ ይላል። ቀልዱ ይቁም!
            27 ዓመት ሙሉ ገባሪ ወንዝ ሆነው በትርፍ ዜግነት ተገለው ኖረዋል።
            በተጨማሪ የህወሃቶች ኮታ ደግሞ መወገድ ግድ ይሆል። ይህ መርሓዊ
            ጉዳይ ነው። መርኽ እና ኦሮሙማ ባይተዋወቁም በይቀራረቡም፤ ስድ
            እና ልቅ  ገጠመኝ ነው በ17 ወራት የታዘብኩት። የፓርቲ አካልነት
            በማስተዛዘኛም፤ በገጸ በረከትነትም አይሆንም። ፓርቲ በህግ እና
            በሥርዓት የሚመራ የነቁ ዜጎች የልቅና ልዕልና ማህደር ነውና። ፓርቲ
             የቶንቦላ ሎተሪ አይደለም።
5)               ስለሆነም አዲስ የሥልጣን ክፍፍል ድልድል እንዲኖር ግድ ይላል። ይህ
            ሳይሟላ፤ ይህን ሳያረጋግጥ ነው የምርጫ ቦርድ ዕውቅና የሰጠው
            ለአዲሱ የብልጽግና ድርጅት ለዛውም ፓርቲ ብሎ። ድንቄም!
            ኢትዮጵያዊው ምርጫ ቦርድ  የመርኽ ጥሰት ብቻ ሳይሆን ወንጀል ነው
            የፈጸመው። ህግ ቢኖር ራሱ የምርጫ ቦርድ ሊከሰስ የሚችልበት
            ጉዳይ ነው። በተፋለሰ መንገድ የተሰጠ ዕውቅና ነገን ክው አድርጎ
             ያደርቀዋል። ዴሞክራሲንም በቁሙ ይቀብረዋል። ተስፋም ይንቃቃል።
            ዴሞክራሲ እኮ ለፓርቲ አሰራር መድህኑ ነው፤ ቢገኝ ማለት ነው።
            ጭላጭ የዴሞክራሲ ፍርፋሬ በብልጽግና ምስረታ በሂደቱ የለም፤
            የሚገርመው ምርጫ ቦርድ ደግሞ ተደርቦ አዳፈነው። መራቆት!

ብልጽግና (ፓርቲ?) ከአጀማመሩ ጀምሮ ሂደቱ ሥርዓትን ያልጠበቀ፤ የፓርቲ መርህን የጣሰ አጤ በጉልበቱ የሆነ ድርጅት ነው። ፓርቲ ከሚባልም የምኞት ዝክረ ማህበር ወይንም የጨረቃ ቤት ቢባል ይሻለዋል። ወደ ጽዋ ማህበርም ያሰኘዋል። ሙሴ ስላለው። ዶር አብይ አህመድ ናቸው ሙሴው።  ምክንያቱም በተፋለሰ መንገድ ነው ህልው ሆኛለሁ  የሚለን። ለዚህ ነው እኔ የትውልድ ፓርቲ የመሆን አቅም በጭራሽ የለውም፤ የጨነገፈ ነውም የምለው። አንጃም ያሰጋዋል። አንድ ፓርቲ እንዲዘልቅ አመሰራረቱ ወሳኝ ነውና።

ይህ ሁሉ የአንድ አገርም ህግጋት፤ የፓርቲ አደረጃጃት መርሆዎችም ተጥሶ፤ ምርጫ ቦርድ ይሁንታውን ሰጥቷል። ለአንድ ሰው ሰብዕና ግንባታ ሲባል ነው። ለጠሚር አብይ አህመድ ሥልጣን ዘላቂነት። 

የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እና በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር እንኳን የለም። ምክንያቱም ዛሬም ነገም ቀናቱ የፈጣሪ / የአላህ ሥልጣን ብቻ ነው።
ብልጠት እና ብልህነት ልዩነት አላቸው። ብልህነት ጥበብ ነው። ብልጠት ግን ማጨበርበር ነው። ምርጫ ቦርድ በዚህ ውስጥ መዳከሩ ዜጋው የከፈለውን መስዋዕትን የመርገጥ ያህል ይሰማኛል። ብዙ ዋጋ ከፍለንበታል ሁላችንም። ወጣትነታችን ገብረንበታል። ለዴሞክራሲ ሥርዓት ምሰረታ። 

አንድ ፓርቲ በአስገዳጅ ሁኔታ ብቻ መሆን የለበትም የሚፈጠረው። ከ25 ዓመት በላይ በክፉም በደጉም በሉላዊ ደረጃ የሚታወቅ የኢህዴግ ግንባር መፍረሱም፤ መሰናበቱም እንዲህ መርህ ተጥሶ፤ ተልፈስፍሶ ሞቱ ሲታወጅ፤ አዲሱም„የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት“ አይነት ሲሆን ደራጃችን ሆነ በፓርቲ አደረጃጃት የተመክሮ ክህሎታዊ አቅማችን ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነ ያሳያል። እውነትም ኋላቀሮች መሆናችን በይፋ ታውጇል።

·         ታመን ቁልቁልት ተስፋ ለተጣለበት የምርጫ ቦርድ።

መታመን አቅም ነው። መታመን ስኬት ነው። መታመን ግብ ነው። መታመን ተቀባይነት ነው። መታመን ዕውቅና ነው። መታመን ዕውነት ነው። መታመን ፋክትም ነው። መታመን ድልም ነው። ከዚህ አንጻር ለምርጫ ቦርድ ታማኝነትም ቁልቁለት ነው ይህ የአፈጻጸም ድርብርብ፤ ንብርብር ድንብስ ግድፈት። ተራ ግድፈትም አይደለም። በአገር ታሪክ የተቀለደ ወንጀል። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ስንት ነገር ተገብሮበት እንዲህ ሆኖ ፈሶ ቀረ ተሰፋ አንንቃሮ።

በሌላ በኩል የታሪክ ዝበትን ሊያሰከትል የሚችል ነውም። ክብርት ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ ከፍተኛ የህግ ባለሙያ ናት፤ በሙያ ምስጉንም እንደ ነበረች ነው ቀደምት ታሪኳ የሚገልጸው፤ የፖለቲካ ድርጅት ሊቀመንበር ነበረች፤ በዛም ለቃሏ ማደሯ ነው ሁላችንም እንድናከብራት የሆነው። ፈተናም በገፍ በግል እንደ እኔ ያሉ ቅኖች የተቀበልነበት ጉዳይ ነው።

አቅሜ የታደፈነበት፤ ተሳትፎዬ የታገደበት፤ ትውልድ ከአኔ ሊያገኝ የሚገባው ተመክሮ የመከነበት ለእሷ እና ለቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ባለኝ የተለዬ ቁርጠኛ ጽኑ አከብሮት ነበር። የጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራሜም ተከሶበታል። ሰበቡ ለእኔም የፖለቲካ ህይወት ተዝርዝሮ የማያልቅ የፈተና ቁልል አሸክሞኝ ኖሯል። ህይወቴን አመሰቃቅሎታል። ቤተሰቦቼም ዋጋ ከፍለውበታል።

እና ዛሬ እሷን በመታመኗ ውስጥ ሳጣት፤ የከፈልኩት መስዕዋትነት ከንቱ የከንቱ ከንቱ መሆኑን አዬሁት። እሷ የቀረባት የለም። እድሜ ለምንትሶ? እርግጥ ተምሬበታለሁኝ። ከእንግዲህ ስለማንም የፖለቲካ ስብዕና ፊት ለፊት ወጥቼ አልሞግትም፤ አልማገድምም። ዳርቻ ነው። ለካስ የመርኽ ሰብዕና የጊዜ ጉዳይ ነው። ሰውን ጊዜ ነው መርኃዊም ሆነ መርኽ የለሽም የሚያደርገው። ይቀዘቅዛል። ይበርዳል። ይጨንቃልም። ያስፈራልም። እንዲህ ሮል ሞዴል ሲመክን።

ከዚህ አንጻር ለህሊናዋ፤ ለሙያዋ፤ ለሃይማኖቷም በታማኝነትን ለማዝለቅ የወሰደችው እርምጃ ለሰብዕናውም ሆነ ለታሪኳም ጉስቁልና መንገድ ጠራጊ ነው። ከእሷ የሚጠበቅ አይደለም። ስለ ክብሯ ስስታም ልትሆን ይገባት ነበር። የህዝብ ፍቅር መንገድ ላይ አይቀናም። በመርኽ አፈጻጻም፤ እና ላመነችበት አቋም ጽናት ህግ ናት ብለን ስለምናስብ በዚህ መልክ ሳገኛት እኔ እራሴ ደንግጫለሁኝ።

አማካሪያዋም በመርኽ ደረጃ ህወሃትን ስትሞግት የነበረች ብርቱ ወጣት ወ/ት ሶልያና ሽመልስም ቢሆን ስለ እሷም መስከሬያለሁ ተስፋ ያላት ወጣት ብዬ። ብቻ „ከበሮ በሰው እጅ ሲይዙሽ“ ዓይነት ነው ነገር ዓለሙ የሆነው። ወጣቷ ጦማሪ ስትተቸው ከነበረው ስህተት ውስጥ ነው እሷም የተዘፈቀችው። ዕድሏን አባከነችው። ዕውነትን ወግኖ በመቆም እረገድ የሚገኜው ጽናት እና ሐሤት የምድር ገነት ነውና። ለህሊና ማደርን የመሰል የህሊና ለምለም ስንቅ የለም።

·         ነገረ የተወካዮች ምክር ቤት።

የተወካዮች ምክር ቤት በኢህዴግ ግንባር ሥር የነበረ ነው። ብዙዎቹ ካድሬ እንደሆኑ አሰባለሁኝ። አሁን ይህ የተወካዮች ምክር ቤት እንደ ቤት ኪራይ ወደ ብልጽግና ሊዛወር ሊንቆረቆር ነውን? ወይንስ ሊበተን? ይህም ሌላው የቀውስ ዓውድ ይሆናል።

·         ባልነት በፈቃደኝነት።

ለዬትኛውም ፓርቲ አባልነት በፈቃደኝነት ስለመሆኑ ደንቡ ይደነግጋል። ይህ አባልነት በፈቀደኝነት ደግሞ መብት እና ግዴታን አጣምሮ የሚከወን ነው። እንደማስበው የዬድርጅቱ አባል የነበሩ አባልተኞች ግዴታቸውን እዬተወጡ መብታቸውን በአንጻራዊነት በቀደመው ጊዜ ያገኙ ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ። የመምረጥ የመመረጥ ወዘተ።

አሁን ተመሰርትኩ ያለው ብልጽግና (ፓርቲ?) የትኞችን አባል ይዞ እንደሆነ አልገባኝም። የነባር አራት ድርጅቶች ነው እንዳይባል አልተሰበሰቡም፤ ደንቡን ፕሮግራሙን የብልጽግናቸውን አያውቁትም፤ ምን አልባትም ኢህዴግ መፍረሱንም ያልሰሙ ሊኖሩ ይችላሉ። አቶ የኋንስ ቧያለው መቼም ነገረ ሥራቸው ሁሉ ልቅ እና ያለ ነው አውቶማቲካሊ የብልጽግና ሆኛለሁ ሲሉ ተረብ ቢጤ ጣል አድርገዋል። ህግ እና ሥርዓት በተጣሰ ሁኔታ እንዲህ መፎከር አለን?! ዝገት።

እሳቸው ሲሆኑ አቶ ለማ መገርሳ፤ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂሚስ? አቶ ለማ በግላቸው አልተደመርኵኝም ሲሉ ወ/ሮ ኬርያ ኢብርሂም የዞግ ድርጅታቸው ህዋህት አልተደመረም። ከዚህ አንጻር የአቶ ዮኋንስ ቧያለው መርኽ አልቦሽነት ፍንተው ብሎ ይታያችኋል። ፍልሰት።
 
እንዴት ነው አባልነት በገልባጭ መኪና እንደተጫነ ድንጋይ ከአንዱ መኪና ወደ ሌላው ይገለባበጣልን? ወይንስ የፓርቲ አባልነት የገብያ ውሎ ነውን? ወይንም የፓርቲ አባልነት የአክስዮን ማህበርተኝነት ይሆን? ወይንስ የአንድ ወቅት የፈንድ ራይዚንግ ፋንታዚ ኢቤንት?

በዛ ሰሞን ለነገሩ መሳቂያው ብአዴን በድህረ ገጹ ግጥም አድርጎ አባል ለመሆን የምትፈልጉ ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን፤ ከዚህ ሰዓት እስከዚህ ሰዓት መጥታችሁ አመልክቱ ሲል የፖለቲካ ድርጅት አባልነትን የድንጋይ ድርደራ ውሎ አድርጎታል። እም። እንዴት አይነት የላሸቀ ዘመን ተደረሰ? የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ክፍት የሥራ ቦታ? ? ? ህም!

በዚህ መሰል ውልቅ የፖለቲካ አደረጃጀት፤ ድቀት በሰፈነበት ወለምታ በነገሰበት አሰተሳሰብ የአገር ህልውና ይወሰናል። የህዝብ እጣ ፈንታ ይበዬናል። መኖርም ይቀማል። ለዚህም መስዕዋት ይኮናል። ይህን የተቃወመ ይታሰራል፤ ይገደላልም። 

አንድ የፓርቲ አባል በሥነ - ምግባሩ፤ በታታሪነቱ፤ በክህሎቱ፤ በማህበረሰቡ ባለው ተቀባይነቱ፤ በተግባር ትጋቱ፤ ከደባል ባህሪያት ነጻ ስለመሆኑ፤ ሌብነትን ስለመጠዬፉ፤ በንቃተ ህሊናው ብሰለቱ፤ በማስተዋል አቅሙ አብነት ያለው ለዛውም እጩ ጊዜ ተሰጥቶት፤ በሚገባ ተጠንቶ ነው የሚወሰነለት። እራሱ በኢህዴግ አንድ የሚደመጥ ሞጋች መርኽዊ አቅም ያለው ሰው አላዬሁም። ዕንባ ማዋጣት አቅም ነው እንዳትሉኝ።

ብልጽግና ቃሏን „እደመራለሁ“ ያለ በቃ ምን ይሁን ምን በአንድ ጆንያ ይሰበሳባል ልክ እንደ እህል። በኋላ ደግሞ ለአገር ንቅዘት፤ ለህዝብ እንግልት ሸክም ይሆናል። የትውልድ ብክነት። ይህን ሁሉ የማጣራት ግዴታ ነበረበት የምርጫ ቦርድ። እንዲህ በግዴለሽነት የ100 ሚሊዮንን ህዝብ የመኖርን ተስፋ ቃሬዛ ላይ ከሚያውል። የአገርንም የመከራ ጊዜ ከሚያራዝም። አደራ በል ቦርድ!

ለመሆኑ አዲሱ ብልጽግና (ፓርቲ?) ምን ያህል አባላት አሉት? መቼ አባልነታቸው ተወሰነላቸው? ፎርም ሞልተዋልን? በዬደራጃው ያሉ አካላት አጽድቀውላቸዋልን? ምን ያህል አካላት አሉትስ? በምን ያህል መሰረታዊ ድርጅት ተቋቁሟል? በምን ያህል ወረዳስ ጽህፈት/ቤት ከፍቷል? በምን ያህል ዞን ጽ/ቤት አለው? እኔ እንደማስበው የግንባር አባላቱ ፈረስን ስላሉ ባዶ እጃቸውን ወና ቤት ውስጥ ነው ቁልጭ ቁልጭ እያሉ ነው ያሉት። እነሱንም የመረጠ አንድ የብልጽግና የመሰረታዊ ድርጅት የለም። ለናሙና። ድርቀት። መጨንገፍ እንዲህ ነው። ማስወረድም እንዲህ። ዴሞክራሲ ተስፋው ቀራንዮ ላይ እያቃሰተ ይታዬኛል።  
  
·         ጠቃለያ።

ወይ ኢህዴግ ሆነው ይቀጥሉ፤ ብልጽግና እንሆናለን ካሉ ግን ሥርዓትን እና መርኽን መጠበቅ ግድ ይላል። የሥልጣን ስብጥሩም በአዲስ መልኩ መዋቀር ይኖርበታል። አፋርን፤ ጋንቤላን፤ ቤንሻንጉልን፤ ሱማሌያን ያከተተ መሆን አለበት። የሱማሌ፤ የጋንቤላ፤ የአፋር፤ የቤንሻንጉል የፖለቲካ ሊሂቃን በሁሉም የፓርቲ አካላት በብቃታቸው ቦታ ሊኖራቸው ይገባል። ሊቀመንበር የመሆንም። ምክትል የመሆንም።

ከዚህ ውጭ በዚህ የመርኽ ጥሰት እቀጥላለሁ ካለ ግን በማቆያ፤ በቀጠሮ ፓርቲነት፤ በቀብድ ድርጅትነት ለአንድ አውራ ድርጅት የማይመጥነው ብቻ ሳይሆን በህግም ሊያስጠይቀው የሚገባ ጉዳይ ነው። ምርጫ ላይ እኮ እራሱ መሳተፍ አይገባውም ብልጽግናው። ምክንያቱም ህጋዊ ሂደቶችን ሥርአቶችን አልከወነም እና።  

በሌላ በኩል ሂደቱ ሳስተውለው ሰኞ ተረገዝኩ፤ ማክሰኞ ተወለድኩኝ፤ እሮብ ወደ ት/ቤት ሄድኩኝ፤ ሃሙስ ዩንቨርስቲ ገባሁኝ፤ አርብ ልብስ ግዢ የመመረቂያ ገብያ ሄድኩኝ፤ ቅዳሜ ተመረቅሁኝ እና እሁድ ፌስታ አደረኩኝ፤ ሰኞ ስራ ጀምርኩኝ ነው የሆነው። መቼም ጠሚር አብይ አህመድ ፌስታ ነፍሳቸው ነው። ድግስ ለሳቸው ኦክስጅናቸው ነው። 

ሌሎች ተፎካካሪ/ ተቃዋሚ/ ተቀናቃኝ አዲስ ፓርቲዎች እንዴት ዕውቅና ለማግኘት እንደሚታሹ፤ እንዴት እንሚሰለቁ፤ እንዴት እንደሚሰቃዩ አስተውለን ሥልጣን ላይ ላሉ እነ እንደልቡን ዶር አብይ አህመድን ስናስብ ደግሞ ዕውቅና ለማግኜት የእጅ ሥራ ዳንቴል ያህል ሲቀል አፈጻጻሙ የአገር ዜጋ የክት እና የዘወትር፤ የልጅ እና የእንጀራ ልጅ፤ የቤተኛ እና የገለልተኛ ተዛነፍ አያያዝን እናያለን። ይህ ደግሞ ወልጋዳ መንገድ ነው። ለትውልድ ቡቃያም አረማዊ *አረማሞ ስልት ነው። መሃን! የትውልዱን ተስፋም ጠፍ እያደረገው ነው ቦርዱ እራሱ።

ፓርቲ ማለት የሰው ህይወት የሚወሰንበት፤ መኖር በቅጥ የሚቀመርበት፤ ህይወት የተሻለ ተስፋ የሚታይበት፤ አቅም በተደራጀ ሁኔታ ሃይል የሚፈጥርበት፤ ክህሎት የሚቀናበት፤ በነቃ ህሊና የሚመራ፤ በፉክክር ነጥሮ የሚወጣ፤ በሳልነትን ያሰበለ መሪ ተቋም ነው። እንዲህ በመሰለ ለብ ለብ እና ግልቦሽ እንኳንስ ፓርቲ ኢትዮጵያ እድርም አስተናግዳ አታውቅም። ኢትዮጵያ ሰፊ ተመክሮ አላት በተለያዩ ማህበራዊ፤ ባህላዊ ይሁን ሃይማኖታዊ የድርጅት አፈጣጠር እና አመራር ታሪኳ።

የሆነ ሆኖ ስለተመኙት ብልጽግና አይገኝም። ሥምም ብልጽግና አይሆንም። ለመበልጸግ መርኽን ተከትሎ መነሳት ያስፈልጋል። መጀመሪያ መርኽን አብልጽጎ ይነሳ ብልጽግናው። በመርኽ ክብረ ድንግልና ጥሰት የተጀመረ ድርጅት ዕድገቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መነሻው ይናገራል። የጥናትም፤ የስክነትም፤ የክህሎትም ድቀት ግሸበት ታይቶበታል ገና ከውጥኑ። ስብከት ጠንካራ ድርጅት አይሆንም። ጠንካራ ድርጅት መርህ መር ሲሆን ብቻ ነው ጉልበት የሚኖረው።(ብልጽግና የሚለው ሥያሜ ከዬት እንደፈለቀ የትውስት፤ ቀሰማ ስለመሆኗ አንድ ቀን በሌላ ጹሁፍ እገልጸዋለሁኝ)

ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን „አያያዙን አይቶ ሸክሙን ይቀሙታል“ ይላል የጎንደር ሰው። ሥርዓት ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት የህልውናው ፒላሩ ነው። ሥርአት አልበኝነት ገና በውጥኑ ከመጣ ውርጃም፤ አንጃም፤ አናርኪዝምም ዕጣ ክፍሉ ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ የ50 ዓመት የፓርቲ ምስረታ ታሪክ ይህ አይጠበቅም ነበር። „አድሮ ጥጃ።“ ሳስበው እኔ በግሌ ባልቦካ ጭቃ እንደሚሰራ ቤት ምርጊት ፍርክርክር ማለቱ አይቀሬ መሆኑን ነው የሚታዬኝ። ሟርት አይደለም። አያያዙ ዝርክርክ ነውና። 

የሚገርመው የሚያደነቁረን ፕሮፓጋንዳው ነው። የሚዲያው ውሎ አጀብ ነው። እኔ እዚህ ጭምቷ አገር ሆኜ ያው የፕሮፖጋንዳ ልሳን የሆኑ ዘመን የማያስተምራቸው ቧንቧዎች ሳስብ ባታት ላይ ስለመሆናቸው ነው እሚገባኝ። ምክንያቱም በሌለ ነገር ላይ ይህን ያህል ድልቂያ ሳይሆን ደብቁኝ የሚያሰኝ ጥሬ ሂደት ነው የተከናወነው። ጮርቃ።

አንዱም ነገር በሥርዓት አልተከናወነም። መሰንበቱንም ፈጣሪ/ አላህ ይወቀው። በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያን የመንግሥት አቅም ስታዩት ይደክማችኋል። አርቃችሁ ለማሰብ ያቅታችኋል። እርግማን። ምርቃታችን ተነስቷል።

·       „ነፃና ፍትኃዊ ምርጫ“ ህዕልም ዕልም እንዳይሆን ብቻ። 

ከሁሉ ግን የነፃ እና ፍትኃዊ ምርጫ ዕወጃ በዚህ መልኩ መቅድሙ ተስፋን ገና ከመምጣቱ በፊት ክው አድርጎ ያደርቀዋል። እኔ ክብርት ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ የምትሰጠውን መግለጫ ሳዳምጥ አገረ ሲዊዲን ኢትዮጵያ የሄደ ይመስለኛል። ወይንም ዴንማርክ፤ ወይንም ሲዊዝ እንደለ ጓዛቸውን ጠቅለልው ኢትዮጵያ ከእነ መልክዕ ምድራቸው የሄዱ ይመስሉኛል። አንዳንድ ጊዜ የትኛው ፕላኔት እንዳለች ሁሉ ግራ እስኪገባኝ ድረስ በተደሞ አሰተውላታለሁኝ። ኡራኖስ ላይ ሳተርን ላይ ወይ ሜርኩሪ ላይ ያላች እስኪመስለኝ ድረስ። ያው ውስጤ ብትሆንም ግድፈት ብዬ አማስበውን ግን ለመናገር የክት እና የዘወትር የለኝም።

የሆነ ሆኖ ምናው እንደ እሷ እንዲህ አይነት ሰላማዊ ግዴለሽ ስሜት የሚሰማኝ በሆነ። ስንት ቀን እንቅልፍ አጥቻለሁኝ እኔ? ስንት ቀንስ ሰለ ሰብዐዊነት ግድ የሚላቸውን አድማጮቼን አስቸግሬያለሁኝ። ዓለም እራሷ ስለ ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ ናት። 

እያንዳንዱን ኢ-ሰብዕዊ ድርጊት በዓይናቸው ሞልተው ለማዬት በጣም ነው የሚቸገሩ ያልተወለዱን፤ የዓለም ዜጎች። ዓመታዊ ሪፖርቱም ይኽው ተኮር ነው። የዓለምን ዕድምታ ተድሞ ማስታዋል ነው። ለክብርት ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ብቻ የተሰራች ኢትዮጵያ ያለች እስኪመስል ድርስ ቅልጣን ቢጤ የሚያጠቃው መግለጫ በዬጊዜው እስኪያቅለሸልሸኝ ድረስ ትሰጣለች። ዘመናይነት ጥሩ አይደለም። ለሰው ነፍስም ግፍ አለውና። የሰው ስቃይም ግፍ አለውና።  

ለነገሩ ብዙ ተስፋ ያደረጉ አገሮች ምርጫ አጥተው እንጂ ተስፋቸው እንደ ከሸፈም ያውቃሉ። የምርጫ ቦርድ ደግሞ ዘመናዊነትን በቅልጣን ያውጃል። ሩብ አገር የለም በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሌጋሲ በሰላም የሚመራ። 

እቴጌ ትግራይ መቼ ነው በጠሚሩ ተመርታ የምታወቅው? እራሱ ኦሮምያ መቼ ነው በህግ ተዳድሮ የሚያወቀው፤ አልፎ ተርፎ አዲስ አበባን እያመሰ አይደለምን? ይህን ዕውቅና ሰጥቶ መፍትሄ ማፈላለጉ ይበጅ ነበር። ሞት በራችን ላይ ቆሞ እኛ የምርጫ ሰነድ ለማሳታም ውጭ አገር ያሰኜናል። „ቂጥ ገሊቦ“ የሆነ ነገር። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄድ ምርጫ በዚህ ሁሉ ሺህ ዓመት ኢትዮጵያ ሰነድ ማሳተም አቅቷት የትውስት አገር ጥማት ታይቷል። ጉርሻ ይባል ጉቦ አይታወቅም። ብቻ አገራዊ ጠረኑ ድርቀት የናኘበት ዘመን ላይ ነን። ዋይታ ላይ ሆኖ ቅብጠቱ በዛ መቀናጣቱም አቃረን።

የሰው ልጅ እንደ በሬ ሰንጋ በሚመተርበት አገር ተቀምጣ ክብርት ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ እናት በድንጋይ ተቀጠቅጣ እዬተገደለች ያለችበት ዓለም ልዩ ነው። አራስ የአራስ ወግ አጥታ እዬተረሸነች፤ „ፍትኃዊ እና ነፃ ምርጫ“ ስትል ግርም ይለኛል ክብርት ወ/ት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ። 

እንደ አፏ ይሁን። „ቸር ተመኝ ቸር ታገኝ“ እንዲሉ። አለኝ የምትለው የራሷ የምርጫ ቦርድ አካላት የበታች የተደራጀ ጣጣውን የጨረሰ፤ ትጥቁን ያሟላ ካለም መልካም ነው። ያው ምርጫ ታች ተወርዶ ስለሚሰራ፤ ተዋረዳዊ ክንውንም ስለሆነ። ስንት ጽህፈት ቤት አደራጀት እሷ እሷ እራሷ?!

የሆነ ሆኖ ዴሞክራሲ የግድግዳ ማስጌጫ ሳይሆን ሕይወቱን በመሆን ማክብር/ ማስከበር መቻል ይጋባ ነበር። ቢያንስ በተገኜው መድረክ ዕድሉን ያገኙ ነፍሳት እሷም ሆነች አማካሪዋ ድርጊት ላይ መገኜት ነበረባቸው። ይህ እኮ ሰውንም የማዳን ተግባር ነበር። ይህም እኮ አገር የማዳን ተግባር ነው። 

ይህ እኮ ተስፋን የመታደግ ጉዳይ ነበር። ሰው የሚባለው ፍጡር ዋጋው አንሶ ነው እማዬው በዬአጋጣሚው። ስንት ጊዜ ይማጥ? በተዘጋ በር ግን ተስፋን ማግኜት ጣር ነው። ኢትዮጵያ በጨለማ አጥር ውስጥ ናት። ተሰቅዛለችም። በሌላ በኩል በሥርዓት የተደራጁትን እነ አብን እያሳደዱ፤ ቁልፍ ትንታግ ሞጋች መሪዎችን እንደ አቶ ክርስትያን ታደለን፤ እና አቶ በለጠ ካሳን ለካቴና እዬገበሩ፤ ሥርዓት ጣሹ መሪ ቃል አዛዥ ናዛዥ እናም እንደልቡ ሆነው በቀላጤ ዕውቅና ለብልጽግናው ሲሰጥ ከማዬት በላይ የሚከረፋ የሚጎፈንንም ነገር ከቶውንም የለም። ይህ ሂደት በራሱ ምርጫ ቦርድን ከጨዋታ ውጭ አድርጎ ተልዕኮውን ከርችሞታል። 

መርኽ ለመርህ ጠያቂውም ተጠያቂውም፤ አቃቢ ህጉም ዳኛውም ችሎቱም እራሱ እጬጌ መርኽ ነው። በመርኽ ጥሰት ለሚደርሰው የትውልድ፤ የጊዜ፤ የመዋለ መንፈስ ብክነት ከተጠያቂነት መዳንም አይቻልም ምርጫ ቦርድን ጨምሮ።

እኛ ቸል ብንለው ዓለም በዓራት ዓይኑ እዬተከታተለው ነው ነገረ ኢትዮጵያን። ድምጣቸውን አጥፍተው የሰብዕዊ መብት ጥሰቱን ሆነ እንደ ድርጅት በተለይ በአብን ላይ ያለውን ፍጹም የተለዬ ዲስክርምኔሽን እና አፈናን ሥራዬ ብለው የሚከታተሉትም አሉ። ለዚህ ተመስገን ነው።
ስማሚያ ለአብነት ሃድራ።
  
·         ቅኔቹ ዬፌስ ቡክ ልቦቼ ብለጌን ትከታተሉ ዘንድ ሊንኩ ይህ ነው። ወደ ብሎጌ ጎራ ስትሉ ብርቱካናማ ቦክስ ዲያሎግ ይመጣል፤ ያን ስትጫኑት በሩ ይከፈታል። ሊንኩ ይሄው ነው። ዘለግ ያለ ሙግት ሲኖረኝ በብሎጌ ከች እላለሁኝ።
·         ብሎጌ ህሊናዎች ደግሞ በዚህ የመግቢያ በር ካለምንም የእልፍኝ አስከልካይ መግባት ይቻላል። አጫጭር ጹሑፎች ሲኖሩኝ ፌስ ቡክ ላይ አዘውትራለሁኝ። ፌስ ቡክ እድሜውን ያርዝመው እንጂ ለአጭር ትጥቅ ልዩ ስጦታ ምቹ ማሳ ነው። ካለዘጉት እውነት ፈሪው ጠሚር አብይ አህመድ። ቢያዘጉትም በሌሎች ብቅ ይባላል። ዛሬ አለም ብዙ አማራጭ አላት።
·         በድምጥ ሲያሰኜን ደግሞ ይኸው እና ቁጥር አንድ ዩቱብ ቻናሌ  በአገርኛ በአውራው ሉላዊ ቋንቋ በእጬጌ አማርኛ።

·         ስለ ፍቅራዊነት ብናውቅስ ለምትሉ ቅኔዎቼ ደግሞ ይኸውና ቁጥር ሁለት ዩቱቤ።
https://www.youtube.com/channel/UCb4Maqp24liAGdbPE553WGA

መፍቻ።

·         አረማሞ። አረማሞ ማለት እህል ሆኖ ተዘርቶ ሲያፈራ ግን ጠቀራዊ አመድ የሚያመርት የእህል ዕድገት ገጠመኝ ነው። ሽፋኑ ሲገለጥ ዱቄት የሆነ ጠቀራ ይወጣዋል። በተለይ የማሽላ እህሎችን ያጠቃል።

መርኽ ያለው ትውልድ ናፈቀኝ።
ዕውነት የሆነ መርኃዊ መሪም ሽው አለኝ። 
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።

የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።






አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።