"አማርኛ ቋንቋ እና አማረኛ ፊደላት አፈዳደል" Ermias Melesse

 

"አማርኛ ቋንቋ እና አማረኛ ፊደላት አፈዳደል"

Ermias Melesse

"(ጋደም ብላችሁ አንብቡት)
አማርኛ ቋንቋ
ያው ሲጻፍ "አማኛ" ተብሎ ነው። አንዳንዶች ደግሞ "አማ'ኛ" ነው ይሉታል። 
 
"አማረኛ ራሱ ምንድን ነው?" ቢሉ ያማረ የተዋበ ልሣን እንደኾነ ቃሉ ራሱ ይናገራል። እንግሊዝ ብሎ እንግሊዝኛ ካለ አማረ ብሎ አማረኛ ይላል። አንዳንዶችም " አማረኝ ከተሰኜው ግስ የተወሰደ ነው። ትርጉሙም አሰኜኛ፣ ደስ አለኝኛ፣ ተመቸኛ... እንደ ማለት ነው" ይሉታል። 
 
እና አማርኛ ሙድ ያለው ቋንቋ ነው። ለአፍ እሚቀል፣ ለምላስ የሚጣፍጥ ደስ የሚያሰኝ ዜመኛ ቋንቋ ነው። አማረኛ የራሱን ለመስጠት እማይሰስት ከሌሎችም ለመቀበል እማይገደው ምቾት ያለው አራዳ ቋንቋ ነው። አማረኛ ብዙ ቃላትን ለሌሎች አውርሷል፣ ብዙ ቃላትን ከሌሎች ተውሷል። 
 
የአማርኛ ታሪካዊ አመጣጥ፦
 
አማርኛ የኢትዮጵያ መደበኛ ቋንቋ ነው። የቋንቋ እና ሥነ ልሣን ጥናቶች እንደሚሉት አማርኛ እንደ ዕብራይስጥ እና ዓረብኛ አይነት ሴማዊያን ቋንቋዎች ውስጥ አንዱ ነው። በአፍሪካ ውስጥ ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካው ሐውሳ ና ከምሥራቅ አፍሪካው ስዋሂሊ ቀጥሎ ፫ ኛውን ቦታ እንደሚይዝ ተጽፏል። ( ዶ.ር አንበሴ ተፈራ "የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎቻቸው አጭር ቅኝት" )
አንዳንዶች ከስዋሂሊ ቀጥሎ በ፪ኛ ደረጃ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
 
 እንዴውም በትክክል ቢጠና ከሰዋሂሊ የበዛ ተናጋሪ እንደሚኖረውም ይጠቁማሉ። በአሁኑ ሰዓት ከመቶ ሚሊዮን በላይ ተናጋሪዎች ያሉት ቋንቋ ነው። እንደ ላቲን ከግራ ወደ ቀኝ መጻፉ ከዓረብኛና ከዕብራይስጥ ልዩ ያደርገዋል። እንደዚህ መጻፉም የራሱ የኾነ ሃይማኖታዊም ባህላዊም ምክንያት አለው።
 
አማረኛ የካማራ/ አማራ ግዛት ተብሎ የሚታወቀው ቦታ በአሁኑ መካከለኛና ደቡብ ወሎ ይገኝ እንደ ነበር በታሪክ ይጠቀሳል። [ የኢትዮጵያ ካርታ 1459 በዝርዝር ] 
 
ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ200 - 130 ዓ.ዓ የነበረው አጋታርከስ ሥለ ቀይ ባህር እና አካባቢው ሲጽፍ "ትሮጎዶላይት" ያላቸው ሕዝቦች – τής Kαμάρ λέξιςα (የካማራ Camàra ቋንቋ)
ወይንም Kαμάρα λέξιςα (ካማራ Camàra ቋንቋ) ይናገሩ እንደ ነበር ዘግቧል። 
 
[James Cowles Prichard, Researches into the physical history of mankind: Researches into the physical ethnography of the African races, Volume 2 , Sherwood, Gilbert, and Piper, London,1837: 145 ] ። 
 
የተለያዩ የታሪክ አጥኝዎች ከዚህ ተነስተው የአጋታርከስ ካማራ ቋንቋ የአሁኑ አማርኛ ወላጅ እንደኾነ ያስረዳሉ። ለበለጠ መረጃ እኒህን ጥራዞች ማግኜት ከቻላችሁ ማንበብ ትችላላችሁ።
 
Amharic Language, The national encyclopedia: a dictionary of universal knowledge , London, 1879
The Encyclopedia Britannica, or, Dictionary of arts, sciences, and general literature, Volume 13 , (1855), Page 219
 
ብዙ ሊቃውንት እንደሚስማሙበት አማርኛ ልሣነ-ንጉሥ (የቤተ-መንግሥት ቋንቋ) የኾነው በ1272 ዓ.ም ከ ዛጔ ሥርወ መንግሥት በኋላ ዓፄ ይኩኖ አምላክ ሰሎሞናዊውን ሥርወ-መንግሥት መልሶ ሲያቋቁም ነበር። በበ፲፬ ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደግሞ ልሣነ ሕዝብ መኾን ችሏል። [ ዶ.ር አንበሴ ተፈራ፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች አጭር ቅኝት] 
 
እዚህ ላይ "... መልሶ ሲያቋቁም..." እሚለው ላይ አማርኛ በፊትም የመንግሥት ልሣን እንደ ነበር አማላካች ነው። ሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት ከዛጔ በፊትም ነበርና የአማርኛ ልሣነ ንጉሥነትም ከዚያ በፊት አጠያያቂ አይኾንም። 
 
ይህንንም ኹሉ ያደረገው ኹሉንም የግዕዝ ፊደላትን እንዳለ በመውሰድ እና ፮ ዐዳዲስ የላንቃ ፊደላትን ማለትም ሸ፣ ቸ፣ ኘ፣ ዠ፣ ጀ፣ ጨ እና ኸ ን በመጨመር ነበር። ነገር ግን ልሣነ ጽሑፍ መኾን የጀመረው ዶ.ር አንበሴ ተፈራ እንደሚሉት በዓፄ ቴዎድሮስ ዘመን ነው። በተለይ ደብተራ ዘነብ ኢትዮጵያዊ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገርላቸዋል። 
 
አለቃ ዘነብ የንጉሡ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ነበሩ። በተለይ "መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ" የተሰኜች ሳቅን እያጫረች ነገረ ክርስቶስን የምታስተምር ቁም ነገር አዘል ወገኛ መጽሐፋቸው ይታዎቃሉ። 
 
ይኽ በመይሣው የተጀመረው የአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በእምየ ዘመን እንደ ሰደድ እሣት ሊቀጠጠል ችሏል። 
 
አማርኛ ለብዙ ዘመናት በእጅ ሲጻፍ ቆይቶ በ1900 ዓ.ም ገደማ በማተሚያ መሣሪያ ተከትቧል። ፊደላቱም በዶ.ር አበራ ሞላ ፈጠራ ወደ ኮምፕዩተር ገብተው ከ1980 ዓ. ም ወዲህ በኮምፕዩተር መጠቀም ከመቻሉም ሌላ በዩኒኮድ እውቅና አግኝተዋል። 
 
የአማረኛ ፊደልና ቋንቋም እውቅና እያደገ ሥለመጣ በእጅ ስልኮችም በሚገባ ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል። አፕል የቋንቋ ገበታዎቹን ሌሎችም እንዲጠቀሙበት በ2007 ዓ. ም ስለከፈተ አማርኛን እንደሌሎች የዓለም ባለ ፊደል ቋንቋዎች መርጦ መጠቀም ተችሏል። 
 
እንዲሁም በ2008 ዓ. ም ግዕዝ የመጀመሪያን የአሜሪካ የባለቤትነት መታወቂያ (ፓተንት) አግኝቷል። በ የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ደግሞ አማርኛ ወደ ማናቸውም ሌላ ቋንቋ በ ኮምፒውተር በቀላሉ ወደ ሚተረጎሙት ቋንቋዎች ገብቷል። ኾኖም የትርጉሙ ጥራት ከፍ ያለ ሳይኾን ስሕተቶች የተሞላበት ኹኖ ቀርቷል።
 
አማርኛ እንዲህ እንዲህ እያለ በሺ እሚቆጠሩ ዘመናትን አልፎ እዚህ ደረጃ የደረሰ ዘምነን ያለ፣ ዜመኛ ለአንደበት እሚጠፍጥ ዘመናዊ ቋንቋ ነው። በቋንቋውም ባለ ቅኔዎች ሎሬትነትን ተሸልመውበታል። ደራሲያን እስካጽናፍ መጥቀውበታል። ሙዚቀኞችም አንቱታን አትርፈውበታል። 
 
የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ እና የሌሎችም ሊቃውንት በሥነ-ጥበብ፣ በምርምር እና በሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቻቸው ተራቅቀውበታል። ለቋንቋው እድገትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተውለታል። 
 
እና ድሮም አሁንም አማርኛ ያንድ ብሔረሰብ ቋንቋ አይደለም። የኹሉም ብሔረሰቦች ቋንቋ ነው። ፊደሎቻችንም የኹሉም ኢትዮጵያዊያን ሀብት ነው። 
 
ኧረ የአፍሪካ ኹሉ ሀብት ነው ወገን። ዛሬ አማሪካ ባንዱ ግዛት አማርኛ በሥራ ቋንቋነት ተመድቧል። በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ምርጫ ላይም አብሮ ተጠቅሷን። በእሥራኤልም እንዲሁ። ቻይና እና አውሮፓ በድግሪ መርሐ ግብር እየተሠጠ ይገኛል። 
 
የአማረኛ ሞክሼ ፊደላት፦
 
አንዳንድ ምሁራን ሞክሼ ፊደላት/ ሆሄያት በመማር ማስተማር ተግባር ላይ መሰላቸትን፣ መታከትንና መወሳሰብን አስከትለዋል፤ እንዲሁም በሥነ ጽሑፎቻችን ላይ የተዘበራረቀ የፊደላት አጠቃቀም እንዲከሰት አድርገዋልና ይቀነሱ እያሉ ሲከራከሩ ይሰማል። ግን እነዚህ ምሁር ተብየዎች ያላስተዋሉት ሊጠፋብን የሚችል ወይንም ያስተዋሉብን ሊያጠፉብን የፈለጉት ነገር አለ። እሱንም እጥር አድርገን እንደሚከተለው እናያለን።
 
ሞክሼ ፊደላት የሚባሉት በንባብና በንግግር ጊዜ ተመሣሣይ ድምፅ ያላቸው ኹነው ነገር ግን ሲጻፉ በቅርፆቻቸው የሚለያዩ ፊደላት ሲኾኑ እነዚህም ሀሌታው "ሀ" ፣ ሐመሩ "ሐ"፣ ብዙኃኑ "ኀ"፣ ንጉሡ "ሠ" ፣ እሳቱ "ሰ" ፤ እሳቱ/አሊፉ "አ" ፣ ዓይኑ " ዐ" ፣ ጸሎቱ "ጸ" እና ፀሐዩ "ፀ" ናቸው፡፡
 
አበው ሊቃውንት እያንዳንዱን ፊደል ሲቀርጡ ትርጉም ሠጥተው እና አመሳጥረው ነው። ቤተ-ክርስትያንም እያንዳንዱን ነገር ስታስተምር በምክንያታዊነት ነው። እያንዳንዱም ሆሄ የራሱ የኾነ ትርጉም ሥላለው ሞክሼ ፊደላትን አንዱን በሌላው ቦታ እየተኩ መጻፍ የትርጉምና የምሥጢር መፋለስን ያስከትላል።
 
የሚከተሉትን ሐረጋት ወይም ዓ. ነገሮች እንደ ምሣሌ እንይ እስቲ...
፩ኛ. ሰረቀ በሥጋ እምድንግል ⇒ ከድንግል በሥጋ ወሰደ ማለት ነው አሱም ሌብነትን ያመላክታል። ሲስተካከል ሠረቀ በሥጋ እምድንግል ሲኾን ትርጉሙም ከድንግል በሥጋ ተወለደ/ ተገለፀ ይኾናል።
፪ኛ. የዓለም ድህነት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ኾነ ⇒ የዓለም መደህየት ወይንም ማጣት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ኾነ፡፡ ትክክለኛው ግን ድህነት ሳይኾን "ድኅነት" ነው መኾን ያለበት። ትርጉሙም የዓለም መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ኾነ ይኾናል፡፡
፫ኛ. ሰረቀ ብርሃን ⇒ የብርሃን በሌባ መሰረቅ። ሲስተካከል ሠረቀ ይኾናል፤ ትርጉሙም መውጣት ይኾናል።
 
፬ኛ. ሥብሐት ለእግዚአብሔር ⇒ ስባት ወይንም ውፍረት ለእግዚአብሔር ይገባል ማለታችን ነው። 
 
ትክክለኛው ግን ስብሐት ለእግዚአብሔር ⇒ ምስጋና ለእግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
 
፭ኛ. የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በአል ⇒ የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ጣዖት ማለታችን ነው። ማስተካከየው በዓል ሲኾን "ዓመታዊ ክብር" የሚል ትርጉም ይሰጠናል።
 
፮ኛ. ሰብዓ ሰገል ከሩቅ ምሥራቅ መጡ ብንል ⇒ ሰባ (70) ጥበብ ከሩቅ ምሥራቅ መጡ ይኾናል፡፡ ትክክለኛው "ሰብአ" ሰገል= የጥበብ ሰዎች ይኾናል።
 
፯ኛ. የክርስቶስ ትንሳኤ ⇒ የክርስቶስ መከልከል (ነሳ/ከለከለ)፡፡ ሲስተካከል በ "ትንሣኤ" ይጻፋል፤ እሱም የክርስቶስን ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ይገልጥልናል። 
 
፰ኛ. ዛሬ አዲስ አመት ነው ⇒ ስህተቱ ያለው "አመት" እሚለው ላይ ሲኾን ትርጉሙም የሴት ባሪያ/አገልጋይ ማለት ነው። ሲስተካከል ዓመት ይኾናል፤ ርሱም ፲፪ ወራት የኾነው ማለት ነው።
 
፱ኛ. አርዮስ ምሑር ነው ⇒ አርዮስ ምሕረት የተደረገለት/ጻድቅ ነው
፲ኛ. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ምሁር ናቸው ⇒ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሊቅ ናቸው።
 
ወገን... ብዙ መጠቃቀስ ይቻላል። ለምሣሌ ያህል ግን እነዚህ በቂ ናቸው። "ለጠቢብሰ አሐቲ ቃል ትበቁአ" እንዲሉ ሊቃውንት ልብ ላለው በቂ ነው። ኹላችንም የፊደሎቻችንን አፈዳደል እና ትርጉም እንወቅ እንማማር። 
 
ከላይ በተለያየ ምክንያት ሞክሼ ፊደሎቻችንን እንዲቀነስ የሚሹ ብዙ አፈንጋጭ ሊቃውንት አሉ ብለናል። የዘርፉ ሊቃውንት እንደሚሉት ደግሞ እነዚህ ሞክሼ ፊደላት/ ሆሄያት ከተቀነሱ ደግሞ የትርጉምና የምሥጢር መፋለስ ከመከሠቱም በላይ ሌላው ዓለም ያላገኘው ትልቁ የቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ሀብትና የስብሐተ እግዚአብሔር መፍሰሻ የኾነው ያሬዳዊ ዜማ በምልክቶቹ ላይ አደጋ ይደርሳል፡፡ ይህም ማለት ወጥ የኾነው የድጓው፤ የቅዳሴው፤ የሰዓታቱ፤... የቤተ ክርስቲያናችን ዜማ ኹሉ ጎደሎ የኾነ ወይም የተወሰነው ክፍል ዜማው የማይታወቅ ይኾናል ማለት ነው፡፡
 
ለምሣሌ...
 
ሊቃውንቱ እንደሚሉት “ሆ” ተብሎ የተመለከተ ምልክት ሲገኝና "ሖ ” ተብሎ ተመልክቶ ሲገኝ ዜማው ፈጥሞ የማይገናኝ ከመኾኑም በላይ አንዱ (የመጀመሪያው) ግእዝ ዜማ ሲኾን ሌላው (፪ው) ደግሞ እዝል ዜማ ነው፡፡ “ሆ” ማለት “ኢይፈርሆ” እንደሚባለው ግእዝ ዜማ አዚም ማለት ሲሆን “ ሖ ” ማለት ደግሞ “አንጺሖ” እንደሚባለው እዝል ዜማ አዚም ማለት ነው፡፡
 
♦ የሀሌታው ሀ፣ ሐመሩ ሐ እና ብዙኃኑ ኀ ትርጉምና ያላቸው ልዩነት...
 
፨ ሀ ብሂል ሀልዎቱ ለአብ እምቅድመ ዓለም ⇒ ሀ ማለት የአብ አኗኗሩ ከዓለም በፊት ነው፡፡
 
፨ ሐ ብሂል ሐመ ወሞተ ወተቀብረ ⇒ ሐ ማለት ክርስቶስ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፡፡
 
፨ ኀ ብሂል ኃያል እግዚአብሔር ⇒ ኀ ማለት እግዚአብሔር ኃያል ነው፡፡
 
• ምሁር ⇒ የተማረ፤ ሊቅ
• ምሑር ⇒ ይቅርታ/ ምሕረት ያገኘ
• ውሑዳን ⇒ የአንድነት ደጋፊዎች (ተዋሕዶ)
• ውኁዳን ⇒ ጥቂቶች፤ አናሳዎች
• ድህነት ⇒ ማጣት፤ መቸገር (ድህነትንና ባለጠግነትን አትሥጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ሥጠኝ። (ምሳሌ ፴፥ ፰) እንዲል
•ድኅ ነት ⇒ መዳን፤ መፈወስ (እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ድኅ ነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን። (የሐዋ. ፳፰ ፤ ፳፰)
• አኅ ያ ⇒ የእግዚአብሔር ኅቡእ ስሙ ነው፡፡ (ላልቶ ይነበብ)
• አህ ያ ⇒ ለጭነት የሚያገለግል የቤት እንስሳ፡፡ (ጠብቆ ይነበብ)
• አኻ ያ ⇒ በወንዝ ዳር የሚበቅል ዛፍ፡፡ (የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል። መጠፈ ኢዮ ፵ ፤ ፳፪) እንዲል
 
♦ የንጉሡ ሠ እና እሳቱ ሰ ትርጉምና ያላቸው ልዩነት
፨ ሠ- ብሂል ሠረቀ በሥጋ ⇒ ሠ ማለት ጌታ በሥጋ ተወለደ /ተገለጠ፡፡
፨ ሰ- ብሂል ሰብአ ኮነ እግዚእነ ⇒ ሰ ማለት ጌታችን ሰው ሆነ፡፡
• ሠረቀ ⇒ ወጣ፤ ተገለፀ፤ ብቅ አለ፡፡
• ሰረቀ ⇒ ሌባ መነተፈ፤ የራሱ ያልኾነ ነገርን ወሰደ
• ሥብሐት ⇒ ውፍረት/ሥባት
• ስብሐት ⇒ ምስጋና
• ሳለ⇒ በጉሮሮው ኡህ፤ ኡህ አለ
• ሣለ ⇒ ሥዕልን/ ምስልን ሠራ
•ትንሣኤ= መነሳት
• ትን ሳ ኤ ⇒ መከልከል
♦ የእሳቱ/አሊፉ " አ " እና ዐይኑ " ዐ" ትርጉምና ያላቸው ልዩነት
፨ አ- ብሂል አአኲቶ ወእሴብሖ ለእግዚአበሔር⇒ አ – ማለት እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ አመሰግነዋለሁ፡፡
፨ ዐ– ብሂል ዐርገ ሰማያተ እግዚእነ ⇒ ዐ – ማለት ጌታችን ወደ ሰማይ ወጣ/ ዐረገ፡፡
• በዓል ⇒ የቅዱሳን መታሰቢያ የሚከበርበት ቀን
(ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። ማር. ፳፪፥፩)
• በአል ⇒ አይሁድ ያመልኩት የነበረ የጣዖት ስም
(ለበአል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ። ሮሜ ፲፩ ፥ ፬)
• ሰብአ ሰገል ⇒ የጥበብ ሰዎች (ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በሥውር ጠርቶ... ማቴ. ፪፤፯)
• ሰብዓ ሰገል ⇒ 70 ጥበብ (ከዚህ በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፡፡ (ሉቃ፲ ፥፩)
• ሰአለ ⇒ ለመነ
• ሠዐለ ⇒ ሥዕል ሣለ
• አመት⇒ አገልጋይ፤ ባሪያ (አመተ ማርያም= የማርያም አገልጋይ)
• ዓመት ⇒ ፲፪ ወራት ከ፭ ወይም ከ፮ ቀናት (፶፪ ሳምንታት )
• እሩቅ ⇒ ሩቅ ቦታ (ረ እና ዘሮቿ ራሳቸውን የቻሉ መኾናቸውን ያዙልኝ)
• ዕሩቅ ⇒ ያልተከፈነ፤ ልብስ የለሽ (ዕሩቅ ብእሲ)
• መአት ⇒ እጅግ ብዙ
• መዓት ⇒ ቁጣ፤ መቅሠፍት
(አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ በመዓትህም አትገሥጸኝ። (መዝ.፮፥ ፩)እንዲል
♦ የጸሎቱ "ጸ" እና ፀሐዩ "ፀ" ትርጉምና ያላቸው ልዩነት
 
፨ ፀ - ብሂል ፀሐይ ጸልመ በጊዜ ስቅለቱ ለእግዚእነ ⇒ ፀ ማለት – ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፡፡
በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። (ማቴ. ፲፫ ፤ ፵፫)
፨ ጸ ብሂል- ጸጋ ወክብር ተውህበ ለነ ⇒ ጸ ማለት – ጸጋ እና ክብር ለእኛ ተሠጠን፡፡
"በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በ ጸሎት ጽኑ" እንዲል፡፡ (ሮሜ ፲፪ ፤ ፲፪)
መፍትሔ
፩. ትክክለኛውን ፊደል በትክክለኛው ቦታ ለማስቀመጥ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም፡፡
ለምሣሌ የምንጽፈውን ቃል የሚከተለው ሊንክ ላይ በመጻፍ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተጻፈ ማየት፡፡ http://www.amharicbible.org/
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሄር፤ መልዓክ፤ ፃ ድቃን፤ ሠማ እ ታት፤ ዒየሡሥ ክርሥቶሥ፤ ሉቃሥ፣ ዮሀንሥ ፤ ሀዋርያት... ብሎ ፅፎ አያውቅም፡፡
፪. የምንጽፈውን ነገር የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲያርሙት ማሳየት፤
፫. ዕድሉ ከተገኘ ሕዝብ በተሰበሰበበት አጋጣሚ ኹሉ በትምህርት መልክ በተደጋጋሚ ማቅረብ
፬. በሀገር ደረጃ ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ በሥርዓተ ትምህርት መልክ አዘጋጅቶ ትውልዱን ማስተማር...
እኔም ይኽንን ጽሑፌን ለአባቶች አሳይቻለሁና።
NB፦ በ2010 ዓ.ም የተጻፈ ነው። ካሁን በፊትም ፌስቡክ ላይ አጋርቸው ነበር።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።