BBC "የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ይዘት “አሳሳቢ” መሆኑን 14 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስታወቁ"

 https://www.bbc.com/amharic/articles/cly04m7gezvo

 

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ይዘት “አሳሳቢ” መሆኑን 14 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አስታወቁ

 

"አስራ አራት የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ “አካሄድ እና የይዘት ግድፈቶች” እንደሚስተዋሉበት ገለጹ።

ድርጅቶቹ ይህን የገለጹት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅን በተመለከተ በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው።

“በአዋጁ ከለላ ተሰጥቷቸው የነበሩ የቁጥጥር እና ሚዛን መጠበቂያዎች በረቂቅ አዋጁ ሊሻሩ የሚችሉ መሆናቸው በእጅጉ ስላሳሰበን ይህንን የአቋም መግለጫ አዘጋጅተናል” ሲሉ መግለጫ ያወጡበትን ምክንያት ጠቅሰዋል።

ድርጅቶቹ አክለውም “የአዋጁ ማሻሻያ አስፈላጊነት ላይ ገለልተኛ ጥናት ባልተደረገበት፣ በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይትም ባልተካሔደበት ሁኔታ” ረቂቁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ መቅረቡን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ማሻሻያ ከተደርገባቸው ሕጎች እና አዋጆች መካከል የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ አንዱ ነበር።

የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ “ነጻና ገለልተኛ የሚዲያ ምኅዳር ለመገንባት ከፍተኛ ተስፋ” እንደ ነበር ያስታወሱት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ፤ “ለፕሬስ ነጻነትና የተሻለ የሚዲያ ሥራ መሠረት በመሆኑ አዋጁ በስፋት ተቀባይነትን አግኝቶ ቆይቷል” ብለዋል።

ተቀባይነት አግኝቶ የቆየው ይህ አዋጅ “ተለዋዋጭ በሆነው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ” ሳቢያ፤ “የሚዲያ ነፃነትን ከማረጋገጥ አንጻር የሕጉ ተፈጻሚነት በተግባር ችግሮች” እንደገጠሙት ድርጅቶቹ አውስተዋል።

በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ፤ “የገለልተኛ ጋዜጠኝነትና የመገናኛ ብዙኃን መብቶች ጥበቃ ዋነኛው መለኪያ” ይሆናል ተብሎ የታመነበትን አዋጅ “በርካታ አንቀጾች ይዘት እና መንፈስ የሚቀይር” መሆኑን 14ቱ ድርጅቶቹ ጠቁመዋል።

ድርጅቶቹ “ረቂቅ ማሻሻያው የአካሄድና የይዘት ግድፈቶች በስፋት የሚስተዋሉበት ሲሆን፣ በረቂቁ ማሻሻያ ላይ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውይይቶች ባለመከናወናቸው የሲቪል ማኅበረሰቡን፣ የሚዲያ ሙያተኞችን እንዲሁም የሌሎች መብቶች ተሟጋቾችንና የማኅበረሰብ ድምፆች እንዳይሰሙ አድርጓል” ሲሉ የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቁን ተችተዋል።

በተጨማሪም ድርጅቶቹ ማሻሻያው “በሥራ ላይ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጥበቃ የሚሰጣቸውን ነጻነቶች የሚገድብ እና የሚዲያ ተቆጣጣሪውን አካል በአስፈጻሚው አካል ተጽዕኖ ውስጥ የሚል ስጋት አለን” ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት የሚመለመሉበት እና የሚሹመበት ሂደት ላይ ጉልህ የሚባል ማሻሻያ አድርጓል።

የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ወይም ተቀጣሪዎች የቦርዱ አባል እንዳይሆኑ የሚከለክለው የአዋጁ ድንጋጌ በማሻሻያው ተሰርዟል። ከዚህ በተጨማሪም ማሻሻያው የቦርድ አባላት ምልመላ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት የሚያትተውን አንቀጽ ሰርዞታል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለስሥልጣን ዋና ዳይሬክተርን ሹመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰጥቷል።

በሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ ዋና ዳይሬክተሩ የሚሾሙት በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ቦርድ አቅራቢነት ነበር።

“በነባሩ አዋጅ ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ መሰጠታቸው ሥልጣንን ጠቅልሎ ለአንድ አካል መስጠትና በሂደትም ላልተገባ ተፅዕኖ በር [ይከፍታል]” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያዎች “በአንድነት ሲነበቡ የነባሩን አዋጅ አንቀጽ 7 ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ረቂቅ አዋጅ ያደርገዋል” ብለዋል።

በነባሩ አዋጅ አንቀጽ ሰባት የመገናኛ ብዙሃን ገለልተኝነት እና ነጻነትን ያትታል።

አንቀጹ “ባለሥልጣኑ ተግባርና ኃላፊነቱን ሲወጣ ከማንኛውም ዓይነት አግባብነት ከሌላቸውና ከተቋሙ ዓላማዎች ጋር ከማይሄዱ ፍላጎቶችና ተጽዕኖዎች ገለልተኛና ነጻ መሆን ይኖርበታል” ይላል።

 ዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ “ባለስልጣኑ በተለይም ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፥ ከሃይማኖር ተቋማት፥ ከንግድና ከሌሎችም ማኅበረሰባዊ ቡድኖችና ተቋማት ገለልተኛና ነጻ መሆን ይኖርበታል” ሲል ይደነግጋል።

በሰብዓዊ መብቶች እና በሚዲያ ነጻነት ላይ የሚሰሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፤ “ከረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ሒደት ጋር በተያያዘ በርካታ ጉዳዮች እንደሚያሳስቡንና አስቸኳይ መፍትሔም ሊፈለግላቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ለማስገንዘብ እንወዳለን” ብለዋል።

ድርጅቶቹ በመግለጫቸው፤ “የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ በጥናት የተደገፈ ማስረጃ እንዲቀርብ እና በባለድርሻ ወገኖች ሰፊ ውይይትና መግባባት እንዲደረስበት” ጠይቀዋል።

“የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በምክር ቤቱ ከመፅደቁ በፊት ትርጉም ያለውና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት እንዲከናወን” ጥያቄ አቅርበዋል።

ድርጅቶቹ አክለውም፤ “የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መንፈስ ዴሞክራሲን ከማስፈንና የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን ከማረጋገጥ አንጻር የነበረውን አስቻይ የሕግ ማዕቀፍ የሚንድና ወደኋላ የሚጎትት እንዳይሆን በአጽንኦት እንጠይቃለን” ብለዋል።

መግለጫውን በጋራ ካወጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ይገኙበታል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።