ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ100 አገራት ላይ ታሪፍ ጣሉ BBC

 

ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ100 አገራት ላይ ታሪፍ ጣሉ

https://www.bbc.com/amharic/articles/c367prpn0d3o

 

"ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያን ጨምሮ 100 ገደማ አገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ሸቀጦች ላይ ታሪፍ ጣሉ።

ትራምፕ ረቡዕ፣ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም. ይፋ ያደረጉት ታሪፍ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ የዓለም አቀፍ ንግድ ለውጥ ነው።

ትራምፕ በአገራቱ ላይ የጣሉት የመነሻ ታሪፍ ምጣኔ 10 በመቶ ነው። ይህ ታሪፍ መጠን ለምርጫ ቅስቀሳ ባደረጉ ጊዜ የእቅዳቸው አካል አድረገው ከጠቀሱት ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት ወደ አገሪቱ ምርቶችን የሚልኩ 60 አገሮች "የለየላቸው አጥፊዎች" የሚል ምድብ ውስጥ አካትቷል።

በዚህ ምድብ ውስጥ የተካተቱት የአውሮፓ ኅብረት፣ ቻይና ለተከተሉት ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲ ምክንያት ከፍተኛ የታሪፍ ምጣኔ እንደሚጣልባቸው ትራምፕ ተናግረዋል።

እንደ ዋይት ሀውስ ገለጻ 10 በመቶ የታሪፍ ምጣኔ በተጣለባቸው አገራት ላይ እርምጃው ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ከመጪው ቅዳሜ፣ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።

ከፍተኛ ታሪፍ የተጣለባቸው አንዳንድ አገራት ላይ ውሳኔው ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው ከሚቀጥለው ሳምንት ሚያዝያ 1 ጀምሮ መሆኑም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ

ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ የተወሰኑ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ እና ከታሪፍ ነጻ በመሆን ወደ አሜሪካ ገበያ እንዲያስገቡ ከሚፈቅደው የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት ውጪ የተደረገችው ኢትዮጵያ፤ በትራምፕ ታሪፍ የተጣለባቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ እንደተካተተች ፎርብስ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው የታሪፍ ምጣኔ 10 በመቶ ሲሆን በዚህ መሰረት አዲስ አበባ ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ወደ አሜሪካ የሚላኩ ምርቶች ተጨማሪ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል።

ትራምፕ ኢትዮጵያ ላይ የጣሉት 10 በመቶ ታሪፍ፤ በሁሉም ሀገራት ላይ ያስቀመጡት የታሪፍ መነሻ ምጣኔ (baseline tariff) ነው።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2024፤ 465.8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ወደ አሜሪካ መላኳን የአገሪቱ መንግሥት መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ ዋነኛዎቹ ቡና እና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ወደ አሜሪካ የላከችው ምርት ከ2023 ጋር ሲነጻጸር የ24.4 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ታይቶበታል።

ይህ አይነቱ ወደ አሜሪካ የሚላክ ምርት ቅናሽ ኢትዮጵያ ከአጎዋ እድል ተጠቃሚነት ከታገደች በኋላ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የወጪ ንግድ ላይ ታይቶ እንደነበር በገንዘብ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ የወጣ አንድ ጥናት ያሳያል።

 

ኢትዮጵያ ከአጎዋ ከመታገዷ ሦስት ዓመታት አስቀድሞ በ2011 ዓ.ም. ይህንን እድል በመጠቀም 246 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ልካለች።

ኢትዮጵያ አጎዋን በመጠቀም በአብዛኛው ትልክ የነበረው የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ነው።

የአጎዋ እግድ በኢትዮጵያ ንግድ ላይ ያስከተለውን ንዝረት እና የተገኙ ትምህርቶችን በተመለከተው ጥናት እንደሚያመለክተው በ2014 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ካመረተችው አጠቃላይ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ውስጥ 62 በመቶው የተላከው ወደ አሜሪካ ነበር።

በ2015 ዓ.ም. የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከአጎዋ መታገዷን ተከትሎ እድል ሲጠቀሙ የነበሩ 63 በመቶ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ወደ አሜሪካ የላኩት ምርት ቀንሷል።

39 በመቶው አምራቶች ደግሞ ሠራተኞቻቸውን አሰናብተዋል።

የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ መንግሥት በፈጸማቸው የሰብአዊ ጥሰቶች ምክንያት ኢትዮጵያ ከአጎዋ እድል ውጪ ከተደረገች በኋላ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ወደ እድሉ ተጠቃሚነት መመለስ አልቻለችም።

 

ጎረቤት አገራት

ኢትዮጵያን ከሚያዋስኑ ስድስት ሀገራት ውስጥ አምስቱ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ቡጢ አርፎባቸዋል። በአሜሪካ ታሪፍ ያልተጣለባት ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ነች።

ጎረቤት አገራት ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የተጠላባቸው ታሪፍ ምጣኔ ከኢትዮጵያ በጋር ተመሳሳይ 10 በመቶ ነው። ግብጽም በተመሳሳይ የ10 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባታል።

ከአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የሆነው የ50 በመቶ ታሪፍ የተጣለው በሌሴቶ ላይ ነው።

በመቀጠል ማዳጋስካር 47 በመቶ፣ ሞሪሺየስ 40 በመቶ፣ ቦትስዋና 37 በመቶ ቀረጥ ከተጣለባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል ናቸው።

አንጎላ በ32 በመቶ፣ ሊቢያ 31 በመቶ፣ ደቡብ አፍሪካ 30 በመቶ ቀረጥ የተጣለባቸው ሲሆን ናይጄርያ የ14 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባታል።

"የለየላቸው አጥፊዎች"

የነጩ ቤተ መንግሥት ባለስልጣናት "የለየላቸው አጥፊዎች" ተብለው በተለዩ 60 ገደማ አገራት ላይ ከሚያዝያ 1 ጀምሮ የሚተገበር የአጸፋ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ገልጸዋል።

እነዚህ አገራት ከአሜሪካ የሚመጡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የጣሉ፣ አሜሪካ ላይ ከታሪፍ ውጪ የሆኑ የንግድ መሰናክሎችን ያስቀመጡ ወይም የአሜሪካን ኢኮኖሚያዊ ግብ ለማሳነስ እንደተንቀሳቀሱ መንግሥት ያመነባቸው እንደሆኑ ተነግሯል።

ይህ አይነቱ ታሪፍ ከተጣለባቸው የአሜሪካ የንግድ አጋሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • አውሮፓ ኅብረት - 20 በመቶ
  • ቻይና - 54 በመቶ
  • ቪየትናም - 46 በመቶ
  • ታይላንድ - 36 በመቶ
  • ጃፓን - 24 በመቶ
  • ካምቦዲያ - 49 በመቶ
  • ደቡብ አፍሪካ - 30 በመቶ
  • ታይዋን - 32 በመቶ

 

ካናዳ እና ሜክሲኮ በአዲሱ የታሪፍ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም። የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት የሁለቱ አገራት ጉዳይ ከዚህ ቀደም በተላለፉ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዞች የተቀመጡ ማዕቀፎችን በመጠቀም እንደሚታይ ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት ፌንታሊን እና የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የ25 በመቶ ታሪፍ እንደተጣለባቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ የ25 በመቶ ቀረጥ እንደሚጣል አስታውቀዋል።

ተንታኞች ይህ እርምጃ የንግድ ጦርነቱን በማባባስ በአሜሪካውያን ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስከትል እና ይህም የአገሪቱን እድገት መጠን እንደሚያዘገይ እየተናገሩ ነው።

በዓለም ዙሪያ አንዳንድ አገራት የኢኮኖሚ ውድቀት እንዲያጋጥመው ሊያደርግ እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ ግን፤ አገራት ከፍተኛ ቀረጥ በመጣል እና ሌሎች ንግድ እንቅፋቶችን በመጠቀም በአሜሪካ ላይ ጥቅም የበላይነት እየወሰዱ በመሆኑ ይህ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑን ቀረጡን ይፋ ሲያደርጉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ይህንን ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ይፋ ሲያደርጉ ከአምስት አስርት ዓመታት ለሚልቅ ጊዜ አሜሪካ "በቅርብ እና ሩቅ ወዳጅ እና ጠላት ሀገራት ስትዘረፍ፣ ስትሰረቅ፣ ስትደፈር እና ስትመዘበር" ነበር ብለዋል።

እርምጃው "የኢኮኖሚያዊ ነጻነታችን አዋጅ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ታሪፍ ምንድን ነው? እንዴት ይሰራል?

ታሪፍ ከሌሎች አገራት በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣል ግብር ነው።ብዙውን ጊዜ ታሪፍ የሚሰላው የምርቱ ዋጋ ላይ የተጣለውን የግብር መጠን በመቶኛ በማስላት ነው።

ለምሳሌ፤ የ10 ብር ዋጋ ባለው ምርት ላይ 25 በመቶ ቀረጥ ከተጣለ፤ የሸቀጡ ዋጋ 2 ብር ከ50 ሳንቲም ጭማሪ ያደረጋል ማለት ነው።

ይህንን ታሪፍ ለመንግሥት የሚከፍሉት የውጭ አገር ምርትን አገር ውስጥ የሚያስገቡ ኩባንያዎች ናቸው።

ኩባንያዎቹ ለመንግሥት የከፈሉትን ቀረጥ ለማካካስ ሲሉ ምርቱ ለደንበኞች በሚሸጡበት ጊዜ መደበኛው ዋጋ ላይ የተወሰነ ወይም ሙሉ ጭማሪ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ዓለም አቀፍ "አጸፋዊ ቀረጥ" በአሜሪካ ምርቶች ላይ ቀረጥ የጣሉ አገራትን ዒላማ ያደረገ ነው።

ይሁንና ትራምፕ የጣሉት ቀረጥ አገራቱ አሜሪካ ምርቶች ላይ ከጣሉት ያነሰ እንደሆነ ይከራከራሉ

 ትራምፕ ትዕዛዙን ሲፈርሙ

"ትራምፕ ታሪፍን እንደ መሳሪያ የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?"

"ታሪፍ የፕሬዝደንት ትራምፕ ኢኮኖሚያዊ ራዕይ ማጠንጠኛ ነው። ፕሬዝዳንቱ፤ "ታሪፍ" የሚወዱት ቃል እንደሆነ ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ በውጭ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ አሜሪካውያን ገዢዎች የአገር ውስጥ ምርቶችን እንዲገዙ እንደሚያበረታታ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳድግ እንዲሁም የሚሰበሰበው የታክስ መጠን እንዲጨምር እንደሚያደርግ ይከራከራሉ።

ለምሳሌ፤ አሜሪካ በ2024 ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በነበራት የንግድ ልውውጥ የ213 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አጋጥሟታል።

ትራምፕ ይህንን ጉድለት "ግፍ" ሲሉ ጠርተውታል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ ከጅምሩ ዒላማ ውስጥ ባስገቧቸው ቻይና፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ ላይ ታሪፍን በመጠቀም የሦስቱ አገራት ስደተኞች እና አደንዛዥ ዕፆች ወደ አሜሪካ እንዳይደርስ የማስገደድ ፍላጎት አላቸው።

ትራምፕ በዚህ የንግድ ፖሊሲ ምክንያት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ውድቀት ሊያጋጥመው ይችላል የሚለውን ስጋትን ውድቅ ከማድረግ ተቆጥበዋል።

የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሃዋርድ ሉትኒክ፤ ታሪፍ የኢኮኖሚ ውድቀት ቢያስከትል እንኳ "ተገቢ ነው" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ትራምፕ የጣሏቸው ቀረጦች ተፈጻሚነታቸው እንዲዘገይ፣ እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሰረዙ ተደርገዋል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?