"ፊንላንድ ለስምንት ተከታታይ ዓመት የዓለማችን ደስተኛ ሀገር ሆና ተመረጠች፤ ኢትዮጵያስ?" BBC

 

 "ፊንላንድ ለስምንት ተከታታይ ዓመት የዓለማችን ደስተኛ ሀገር ሆና ተመረጠች፤ ኢትዮጵያስ?" BBC

https://www.bbc.com/amharic/articles/cdxq7yvxeq4o

 እየሳቁ ያሉ ሰዎች

 

"ፊንላንድ ለስምንት ተከታታይ ዓመት በዓለም ደስተኛ ሀገር ሆና ተመርጣለች።"

"የተፈጥሮ መዳረሻ ከመሆን እና ጠንካራ የማሕህበራዊ ዋስትና ስርዓትን መዘርጋቷ ደስተኛ አገር ሆና ለመመረጧ ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ባደረገለት የዚህ የዓለም የደስታ ሪፖርት ፊንላንድ ከሌሎች ሦስት የኖርዲክ አገራት ቀድማ መቀመጥ የቻለች ሲሆን የላቲን አሜሪካዋ ኮስታሪካ እና ሜክሲኮ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ 10ኛ ባለው ደረጃ ውስጥ ገብተዋል።

በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ 132ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ጎረቤት አገር ኬንያ 115ኛ ስትይዝ ግብጽ ደግሞ 135 ደረጃን ይዛለች።

አፍጋኒስታን በሪፖርቱ ደረጃ ግርጌ ላይ በመቀመጥ 147 ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ በዝርዝሩ ላይ ደረጃቸው ወርዶ 23ኛ እና 24ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ይህም ሁለቱ አገራት ያስመዘገቡት ዝቅተኛው ደረጃ ሆኗል።

ጥናቱ እንግዳ ሰዎች ወይም የማይተዋወቁ ሰዎች ከሚጠበቀው በእጥፍ የበለጥ ደግ ሆነው መገኘታቸውን ጥናቱ አረጋግጧል።

ሆን ተብሎ የኪስ ቦርሳ በመጣል ምን ያህል እንግዳ ሰዎች እንደመለሱ በማየት እና ሰዎች ይመልሳሉ ብለው ከሚጠብቁት ጋር በማነጻጸር ተለክቷል።

የተመለሱት የኪስ ቦርሳዎች መጠን ሰዎች ከገመቱት በእጥፍ የሚበልጥ ሆኗል።

ከዓለም ዙሪያ የተገኙ መረጃዎችን ባሰባሰበው ጥናት መሠረት የሌሎች ደግነት ቀደም ሲል ከታሰበው በላይ ከደስታ ጋር የተሳሰረ መሆኑን አስታውቋል።

የኪስ ቦርሳ ጥናቱ መረጃ እንደሚያሳየው "ሰዎች እርስ በርስ እንደሚተሳሰቡ በሚያስቡበት ቦታ መኖራቸው በጣም ደስተኛ ያደርጋቸዋል" ሲሉ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚስት እና የሪፖርቱ መሪ አርታኢ የሆኑት ጆን ኤፍ ሄሊዌል ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም አቀፍ የደስታ ቀንን ምክንያት በማድረግ ይፋ የሆነው 13ኛው የዓለም የደስታ ሪፖርት ሰዎች ህይወታቸውን እንዲገመግሙ በመጠየቅ እጅግ ደስተኛ የሆኑት የዓለም ሀገራትን በደረጃ አስቀምጧል።

 

ፊንላንድ ከ10 ነጥብ ውስጥ በአማካይ 7.736 ነጥብ በማስመዝገብ ቀዳሚ ስትሆን ዴንማርክ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።

ለኮስታሪካ እና ሜክሲኮ የደረጃዎች መጨመር የቤተሰብ ትስስር ምክንያት እንደሆነ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ዌሊንግ የምርምር ማዕከል የታተመው ጥናቱ፤ ሰዎች የራሳቸውን ህይወት ከዜሮ እስከ 10 እንዲመዘኑ ጠይቋል። ዜሮ የከፋ ህይወት ሲሆን 10 ምርጥ ህይወት ተደርጎ ቀርቧል።

የአገራት ደረጃ በእነዚህ ውጤቶች ሦስት ዓመት አማካይ ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

ቀዳሚዎቹ አስር አገራት የሚከተሉት ናቸው።

  • ፊንላንድ
  • ዴንማርክ
  • አይስላንድ
  • ስዊድን
  • ኔዘርላንድስ
  • ኮስታሪካ
  • ኖርዌይ
  • እስራኤል
  • ሉክሰምበርግ
  • ሜክሲኮ

የ2025 የዓለም ደስታ ሪፖርት ሌሎች ግኝቶችንም ይፋ አድርጓል።

  • በዩናይትድ ስቴትስ እና በአንዳንድ የአውሮፓ ክፍሎች ላይ ያለው የደስታ እና የማህበራዊ እምነት ማሽቆልቆል የፓለቲካ ጽንፈኝነት እንዲሁም ልዩነት መስፋትን ያስረዳል።
  • ምግብን ከሌሎች ጋር መጋራት በዓለም ዙሪያ ካለው ደህንነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።
  • የቤተሰብ ብዛት ከደስታ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሲሆን ከአራት እስከ አምስት ሰዎች አብረው የሚኖሩባቸው ሜክሲኮ እና አውሮፓ ከፍተኛውን የደስታ ደረጃ አግኝተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት ኔትዎርክ ፕሬዝዳንት ጄፍሪ ዲ ሳክስ በበኩላቸው ግኝቶቹ "ደስታ በመተማመን፣ በደግነትና በማህበራዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው" መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል ብለዋል።

"ይህን ጠቃሚ እውነት ወደ አዎንታዊ ተግባር መተርጎም፣ በዚህም ሰላምን፣ ጨዋነትን እና ደህንነትን በዓለም ዙሪያ ማፍራት የእኛ ፈንታ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

"በዚህ በማህበራዊ መገለል እና በፖለቲካዊ ልዩነት ዘመን ሰዎችን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ በድጋሚ ለማምጣት መንገዶችን መፈለግ አለብን። ይህንን ማድረጉ ለግል እና ለጋራ ደህንነት ወሳኝ ነው" ሲሉ የኦክስፎርድ ዌልቢንግ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ጃን-ኢማኑኤል ደ ኔቭ ተናግረዋል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?