ሚስጢረ - ባቲካን። • ዕርዕሱ የእኔ ዘገባው የBBC አማርኛው ክፍል።

 

ሚስጢረ - ባቲካን።
• ዕርዕሱ የእኔ ዘገባው የBBC አማርኛው ክፍል።
«ቀጣዩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ከአፍሪካ ሊመረጡ ይችላሉ?»
24 ሚያዚያ 2025, 07:00 EAT
 
«ቀጣዩን የሮማ ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ መስፈርቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በፍጥነት እየተስፋፋች ያለችበት አካባቢ ከሆነ በእርግጠኝነት ከአፍሪካ ሊሆን እንደሚችል መተንበይ ይችላል።
 
ከየትኛውም የዓለም ክፍል በተለየ በአፍሪካ የካቶሊክ እምነቱ ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እያደገ ነው።
እየጨመረ ያለው የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር በመላው ዓለም ካሉ አህጉራት አንጻር ሲወዳደር ከግማሽ በላይ የሚሆነው እድገት የተመዘገበው በአፍሪካ ነው።
 
ከዚህ ቀደም ከ1500 ዓመት በፊት አፍሪካዊ መሆናቸው የሚታመነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳስ ገላሲያስ ቀዳማዊ ቤተ ክርስቲያኒቱን በርዕሳነ ሊቀ ጳጳስነት አገልግለዋል። 
 
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በቀጣይነት የሚመራውን አባት የሚመርጡት ካርዲናሎች ሲገናኙ ውሳኔያቸውን ይህ እውነታ ተጽዕኖ ያሳድርበት ይሆን? 
 
ናይጄሪያዊው ካህን አባ ስታን ቹ ኢሎ አመራሩ ዓለም አቀፍ ምዕመኑን የሚያንፀባርቅ መሆን እንዳለበት በመግለጽ "አፍሪካዊ ጳጳስ ቢኖር በጣም ትልቅ ነገር ነው" ይላሉ።
 
አባ ስታን ቺ ኢሎ ካርዲናሎቹ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲሁም "ተሰሚነት ያለውን ጳጳስ" ሊመርጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
"ተግዳሮቱ በቫቲካን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሹመት ላይ ያለ አፍሪካዊ ካርዲናል የለም፤ ያ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም" ይላሉ።
"ጳጳስ ሆነው ለመሾም ብቃት ያላቸው፣ በዓለም የካቶሊክ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው አፍሪካዊ ካርዲናሎችን የምናስብ ከሆነ መልሱ ምንም የለም የሚል ነው።"
 
በአውሮፓውያኑ 2013 ለቦታው ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበሩትን ጋናዊው ካርዲናል ፒተር ተርክሰን እንዲሁም በ2005 የፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ምርጫን የመሩትን ናይጄሪያዊው ካርዲናል ፍራንሲስ አሪንዜን በመጥቀስ ሁኔታው በተቃራኒ የቆመ መሆኑን ያስረዳሉ።
ፖፕ ፍራንሲስ የሊቀ ጳጳስነት ሹመታቸውን በአውሮፓውያኑ 2013 ሲረከቡ በአፍሪካ የነበሩት ካርዲናሎች ቁጥር 8 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 12 በመቶ ከፍ እንዲል አድርገዋል።
 
"ፖፕ ፍራንሲስ ለአፍሪካ ያላቸውን ቀናነት ስንመለከት . . . እዚህ አንዴት እንደተደረሰ ብዙዎቻችንን የሚያስገርም ነገር ነው" ይላሉ አባ ቹ ኢሎ።
 
ፖፕ ፍራንሲስ በጵጵስና ዘመናቸው 10 የአፍሪካ አገራትን የጎበኙ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪም አሳይቷል። 
 
አፍሪካውያን ከዓለም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር አንጻር 20 በመቶውን ይይዛሉ። እአአ በ2022 ቁጥራቸው 272 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ በ2023 ወደ 281 ሚሊዮን ከፍ ብሏል በኢንዲያና ኖተርዳም ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አባ ፓውሊነስ ኢኬቹክዉ ኦዶዞር ጳጳሳት ከመጡበት አህጉር የሚሰጠው ትኩረት ከማይመቻቸው አፍሪካዊ ካቶሊኮች መካከል ናቸው። 
 
በናይጄሪያ ለተወለዱት የካቶሊክ ቄስ ይህ ለውክልና በሚል የሚቀርብ ውትወታ ምቾት የሚነሳ ተግባር ነው።
"ሰዎች አፍሪካውያን የእምነቱ ተከታዮች በዚህን ያህል ቁጥር እያደጉ ስለሆነ ለምን አፍሪካዊ ጳጳስ አይሾምም እያሉ ነው። ከአፍሪካ ወይንም ከአውሮፓ ስለመጣህ ቀዳሚነት ሊሰጥህ የሚገባ ዕጩ መሆን አለብህ ብለው ከሚያስቡት መካከል አይደለሁም" ይላሉ።
"ከየትኛውም አካባቢ መጣህ ልክ ስትመረጥ የሁሉም ጉዳይ ጉዳይህ ይሆናል። አንድ ሃሳብ ብቻ ነው ያለህ፤ ሰዎቹ ከየትኛውም አካባቢ ቢሆኑ፣ ቁጥራቸው ምንም ያህል ቢሆን፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ጉዳይህ በክርስቶስን አምሳል ቤተ ክርስቲያኒቱን መገንባት ነው።" 
 
አክለውም ለጳጳሱ በጣም አስፈላጊው ነገር "የቤተ ክርስቲያኒቷ ሥነ መለኮት የበላይ ጠባቂ መሆን ነው" ብለዋል።
"ጳጳሱ ባሕልን በሚገባ የሚያውቅ መሆን ይኖርበታል" ያሉት ፕሮፌሰር አባ ኦዶዞር ያንንም ተጠቅሞ ለሰዎች አቅጣጫ የሚሰጥ ይሆናል ይላሉ።
 
በፕሮፌሰሩ አመለካከት በቫቲካን በሥልጣን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በአፍሪካ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችን የሚያሳስባቸው ነገር በሚመለከት የተሻለ መሥራት ይኖርባቸዋል።
 
"ለአፍሪካውያን ግድ እንደሌላቸው ወይንም እምነታቸው ከሚጠበቀው ትንሽ ዝቅ ያለ ወይንም የተበረዘ እና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው የማይገባ" እንደሆነ ተደርጎ እንደሚቆጠር አንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
 
"አፍሪካውያን ጉዳያቸው አጀንዳ መሆን እያለበት እንዳልሆነ ከተሰማቸው፣ ያኔ ሰዎች መጠየቅ ይጀምራሉ። ምናልባት ልንሰማ የምንችለው የራሳችን ሰው እዚያ ሲኖር ነው ማለት ነው ሊሉ ይችላሉ።"
 
ፖፕ ፍራንሲስ ድሆችን እና ግፉዓንን የሚረዱ ተደርገው ስለሚቆጠሩ በአፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው።
ለምሳሌ 55 ሚሊዮን ተከታዮች በሚገኙበት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ዘረፋ በተመለከተ ተቃውመው ተናግረው ነበር።
 
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ የተፈጠረውን መከፋፈል ለማስታረቅ የሄዱበት ርቀት ከፍተኛ ሙገሳን አስገኝቶላቸዋል።
 
ይኹን እንጂ ፖፕ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ በነበራቸው አቋም የተነሳ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
 
የአፍሪካ ጳጳሳት ጳጳሱ ቀሳውስት በ2023 የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጥንዶችን ሊባርኩ ይችላሉ ብለው ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ውድቅ አድርገዋል።
 
ከዚያ በኋላ ቫቲካን መባረኩ "ግለሰቦቹ የገቡበትን ለማጽደቅ አልያም የሁኔታውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አይደለም" ስትል ማብራሪያ የሰጠች ሲሆን፣ "በበርካታ አገራት ከአጭር ጊዜ የዘለለ የመጋቢነት ስልት የሚጠይቅ ጠንካራ የሆነ የባሕል እንዲሁም ሕጋዊ ሁኔታዎች አሉ" ብላለች። 
 
በአፍሪካ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በሕግ የተከለከለ መሆኑን ተከትሎ በርካታ አፍሪካውያንን የእምነቱ ተከታዮችን በአንድነት እንዲቆሙ አድርጓል።
 
ቀጣዩን የሊቀ ጳጳስነት ምርጫ በታዛቢነት እንደሚከታተሉ የተገለፁት ሦስት አፍሪካዊ ካርዲናሎች፣ ቱርክሶን፣ የጊኒው ሮበርት ሳራ እንዲሁም የኮንጎው ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖርን ለውጥ ተቃዋሚ ናቸው። 
 
የኮንጎው ካርዲናል "የተመሳሳይ ፆታ አፍሪቃያን ጥምረት ከባሕል ያፈነገጠ እና ከመነሻው ሰይጣናዊ ነው" ይላሉ።
ካርዲናል ሳራ በ2015 ለሲኖዶሱ "ልክ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ናዚ ፋሺዝም እና ኮሙኒዝም እንደነበሩት ሁሉ አሁን ደግሞ የምዕራባዊ ሃሳብ የሆነው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጉዳይ፣ ጽንስ ማቋረጥ እንዲሁም እስላማዊ አክራሪነት ማለት ነው።"
 
ካርዲናል ቱርክሶን ጋና በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ ከበድ ያለ ቅጣት ለመጣል የወሰደችውን እርምጃ ተችተው፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት "በማያሻማ መልኩ ሃጥያት ነው" ብለዋል።
 
ኦዶዞር ምንም እንኳ አፍሪካዊ ካርዲናሎች ቁጥራቸው ቢጨምርም በቤተክርስትያኒቱ ያላቸው ሥልጣን አነስተኛ መሆኑ ላይ ይስማማሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም የእምነት አባቶች የቤተክርስትያኒቱ አመራር ወካይ እንዲሆን ፖፕ ፍራንሲስ የሠሩትን ሥራ ይስማሙበታል።
ነገር ግን "በቤተ ክርስቲያኒቱ አሁንም ብዙ የማይወራ ዘረኝነት አለ" ይላሉ ኦዶዞር።
 
"ያ ምናልባት አንድ አባት ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ተግባራት ቢያከናውን አፍሪካዊ ጳጳስ በመሆኑ ብቻ እንቅፋት ሊሆንበት ይቸላል" ይላሉ።
 
በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 252 ካርዲናሎች ያሏት ሲሆን፣ የፖፕ ፍራንሲስ ምትክን ለመምረጥ ጉባኤ ሲሰየም ከካርዲናሎቹ መካከል 138ቱ ብቻ ናቸው አዲስ ጳጳስ በመምረጡ ሂደት ድምጽ መስጠት የሚችሉት።
 
እነዚህ ካርዲናሎች ለድሆች እና ለተጎዱ ወገኖችን የሚያገለግሉ ጳጳስ የመምረጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
ቹ ኢሎ፣ ፖፕ ፍራንሲስ ሲመረጡ እንደነበረው የማይታሰብ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ይገምታሉ።
"እግዚአብሔር ፖፕ ፍራንሲስ የጀመሩትን የሚያስቀጥል መሪ እንዲሰጠን እጸልያለሁ። እንዲሁም እንዲህ ዓይነት ሰው ከአፍሪካ እንዲመጣ እጸልያለሁ።"»
 
• «ስለ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ብዙዎች የማያውቋቸው አምስት እውነታዎች» 
 
22 ሚያዚያ 2025
«ከአውሮፓ ውጪ በመመረጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመምራት የመጀመሪያው የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው አርፈዋል።
 
ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያላትን ቤተክርስቲያን ለ12 ዓመታት የመሩት ፖፕ ፍራንሲስ አርጀንቲናውያን ቤተሰቦቻቸው ያወጡላቸው ስም ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የሚል ነበር። ስለ ጳጳሱ ብዙም የማይታወቁ አንዳንድ እውነታዎችን እነሆ . . .
የምሽት ክለብ ጋርድ ነበሩ
 
ቤርጎሊዮ በአርጀንቲና ዋና ከተማ በቦነስ አይረስ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኬሚስትሪ ዲፕሎማ በማጠናቀቅ በነገረ መለኮት ዲግሪ አግኝተው ሥነ-ጽሁፍ እና ሥነ ልቦና አስተምረዋል።
 
በአውሮፓውያኑ 2010 በሰጡት ቃለ ምልልስ 13 ዓመት ሲሆናቸው ሥራ እንዲጀምሩ ያበረታቷቸው ስለነበረ በአንድ የሹራብ ፋብሪካ ውስጥ በጽዳት ሠራተኝነት እንዲቀጠሩ አደረጓቸው።
 
ከዚያም በኋላ ከጽዳት ሥራው በተጨማሪ በምሽት ክበብ ውስጥ ጋርድ (የጥበቃ ሠራተኛ) ሆነው መሥራታቸውን ሮም ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲናገሩ ብዙዎችን አስደንቀዋል።
 
በተጨማሪም በአንድ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ሠርተው ነበር።
 
የእግር ኳስ አፍቃሪ ነበሩ።
 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በልጅነቱ የሚደግፉት የአካባቢያቸው የቦነስ አይረስ ቡድን የሆነው የሳን ሎሬንዞ ደ አልማግሮ የዕድሜ ልክ ደጋፊ ነበሩ።
 
በአውሮፓውያን 2014 ሳን ሎሬንዞ የኮፓ ሊበርታዶሬስን የተባለውን የደቡብ አሜሪካ የክለቦች እግር ኳስ ውድድር ላይ እጅግ የተከበረውን ዋንጫ ሲያሸንፍ በክለቡ የ106 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛው ውጤት ነበረ።
 
ጳጳሱ ለክለቡ ያላቸው ድጋፍ ለድል አድራጊነቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ "በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ግን አይደለም፣ ይህ ተአምር አይደለም" ብለዋል።
 
ቡድኑ በዚያው ዓመት የአርጀንቲናን ከፍተኛ ዲቪዚዮን አሸናፊ በመሆን የቡድኑ አባላት ከጀርባው "ፍራንሲስኮ ካምፔዮን" ወይም ሻምፒዮኑ ፍራንሲስ የሚል ጽሁፍ የሰፈረበት የቡድኑን ማሊያን ለጳጳሱ አበርክተዋል።
 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተጨማሪም ሊዮኔል ሜሲ እና ሟቹ ዲዬጎ ማራዶናን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን እንዲሁም ስዊድናዊው ኮከብ ተቻዋች ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን ጋር ተገናኝተዋል።
 
የጳጳሱ ህልፈት ይፋ ከሆነ በኋላ ለሰኞ ዕለት የታቀደው የነበሩ አራት የጣሊያን ከፍተኛ የእግር ኳስ ሊግ ሴሪኤ ጨዋታዎች ተሰርዘው ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።
 
ከሌሎች ጋር መጓዝን ይመርጣሉ።
 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለረጅም ጊዜ አገልግሎታቸውን እና እንቅስቃሴያቸውን ቀላል ያለ በማድረግ ሥነ ምግባራቸው ይታወቃሉ። ለዚህም የመጓጓዣ ምርጫቸው ማሳያ ነው።
 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ወዲያውኑ ለጳጳስ የተዘጋጀውን ቅንጡ ሊሞዚን ከመጠቀም ይልቅ ከካርዲናሎቻቸው ጋር በአውቶብስ ነበር የሄዱት።
 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከመሆናቸው በፊት በቦነስ አይረስ በአስቸጋሪ የሕይወት ዘይቤያቸው ይታወቁ የነበሩ ሲሆን ካርዲናል እና ሊቀ ጳጳስ የሆኑትም እዚያው ናቸው።
 
ፍራንሲስ በአውቶብሶች እና በከተማ የምድር ውስጥ ባቡሮች አዘውትረው መጓዝን የሚመርጡ ሲሆን፣ ወደ ቫቲካን በአውሮፕላን ሲጓዙ በአንደኛ ማዕረግ ሳይሆን በመደበኛው የኢኮኖሚ ክፍል ውስጥ ቦታ ይዘው ነበር የሚሄዱት።
 
በጵጵስና ዘመናቸውም የቅንጦት መኪናዎችን የማይጠቀሙት ፍራንሲስ ውድ ያልሆኑትን የጣሊያን ስሪት ፎርድ ፎከስ ወይም በአውሮፓውያኑ 2015 አሜሪካን ሲጎበኙ ፊያት 500 ኤል ያሉ ሞዴሎችን በመምረጥ ይታወቃሉ።
 
ብዙ ጊዜ በጉብኝት ወቅት ሰዎችን ሰላምታ ለመስጠት "ፖፕሞባይል" የተባለውን ግልጽ መኪና ይጠቀም ነበር።
ነገር ግን በእሳቸው እና በተሰበሰቡ ምዕመናን መካከል ጥይት መከላከያ መስታወት ያላቸውን ተሸከርካሪዎች አይወዷቸውም። እንዲህ ያለውን ሁኔታ "በሰርዲን ጣሳ" ውስጥ ያሉ ያህል እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
 
ቀልድ አዋቂ ነበሩ።
 
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተገናኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ በቀልድ እና በሳቅ ይታወቃሉ።
በአውሮፓውያኑ 2024 ከ15 አገራት የተውጣጡ ጂሚ ፋሎን፣ ክሪስ ሮክ እና ሁፒ ጎልድበርግን ጨምሮ ከ100 በላይ ኮሜዲያንን በቫቲካን አስተናግደዋል።
 
ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በየቀኑ "አቤቱ፣ ጌታዬ ሆይ፣ ጥሩ ቀልድ ለዛሬ ስጠኝ" እያሉ ይጸልዩ እንደነበር ለኮሜዲያኑ ተናግረዋል።
ይህም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ በአገር ክህደት የተገደለው እና በኋላም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ተብሎ የተሰየመው የቶማስ ሞር ጸሎት አካል ነበር።
 
በወቅቱ ለኮሜዲያኑ የተነበበው ጸሎት እንዲህ ይላል፡- "ቀልድ እንዳገኝ፣ በሕይወት ውስጥ ትንሽ ደስታን እንድገነዘብ እና ከሌሎች ጋር ለመካፈል እንድችል ፀጋውን ስጠኝ" የሚል ነው።
 
በተጨማሪም "በእርግጥ በአምላክ ላይም መሳቅ ትችላላችሁ። ይህ ደግሞ ማዋረድ አይደለም" በማለት ይህንንም "የምዕመናንን ሃይማኖታዊ ስሜት ሳያስከፋ ማድረግ ይቻላል" ብለዋል።
 
ከፍተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይ አፍርተዋል።
 
በ2018 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በይነመረብን (ኢንትርኔት) "የእግዚአብሔር ስጦታ" ነው በማለት ገልጸውት፣ ነገር ግን "ታላቅ ኃላፊነትን" እንሚጠይቅም አሳስበዋል።
 
ከሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ጳጳስ ትዊተርን (አሁን ኤክስ) የሚባለውን በአውሮፓውያኑ 2012 ከፍተዋል፣ ነገር ግን የተከታዮቹ ቁጥር ፍራንሲስ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
 
የጳጳሱ ኤክስ አካውንት በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛ፣ በፖርቱጋልኛ፣ በፖላንድኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በአረብኛ እና ላቲን ዘጠኝ ቋንቋዎች መልዕክት የሚያጋራ ሲሆን በአጠቃላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።
 
የጳጳሱ ኢንስታግራም አካውንት 9.9 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሲሆን በቅርቡ "አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን" መጠቀም "የሰውን ግንኙነት እንደማይተካ፣ የሰውን ክብር የሚያስከብር እና የዘመናችንን ቀውሶች እንድንጋፈጥ የሚረዳ" በማለት ጸሎት ተጋርቶበታል።
 
ፖፕ ፍራንሲስ ለመጨረሻ ጊዜ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ከህልፈታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የፋሲካ ዕለት ነበር።
በመልዕክታቸውም "ክርስቶስ ተነሥቷል! እነዚህ ቃላት የመኖራችንን አጠቃላይ ትርጉም ይይዛሉ፣ ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው ለሕይወት እንጂ ለሞት አይደለም" ብለው ነበር።»
 
• «ኢትዮጵያዊው ካርዲናል የሚሳተፉበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ምርጫ እንዴት ይካሄዳል?»
 
«በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመረጡት በመንበር ላይ ያሉት ጳጳስ ሲሞቱ ወይም ከፖፕ ፍራንሲስ በፊት የነበሩት ቤኔዲክት 16ኛ እንዳደረጉት በፈቃዳቸው መንበራቸውን ሲለቁ ነው።
 
ተተኪው ጳጳስም በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያላት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በመሆን የመሪነቱን መንበር ይረከባሉ።
 
በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጳጳሱ በታች ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ካርዲናሎች ከመካከላቸው የቤተ ክርስቲያኗ መሪ ሊሆኑ የሚችሉትን አዲሱን ጳጳስ ይመርጣሉ።
 
በዓለም ዙሪያ 252 የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካርዲናሎች ያሉ ሲሆን፣ ከመካከላቸው በአዲሱ የጳጳስ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ከ80 ዓመት በታች የሆኑት ብቻ ናቸው።
 
የእነዚህ በጳጳስ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ካርዲናሎች ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ በ120 የተገደበ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥራቸው 135 ይደርሳል።
 
ኢትዮጵያዊው ካርዲናል ማን ናቸው?
 
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል የሆኑት ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሟቹን ፖፕ ፍራንሲስን በመተካት በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏትን ቤተክርስቲያን የሚመሩትን አዲስ ጳጳስ በመምረጥ ከሚሳተፉት መካከል ናቸው።
 
የአዲስ አበባ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ካርዲናል ብርሃነየሱስ 76 ዓመታቸው ሲሆን፣ በአገር ውስጥ እና በውጪ በከፍተኛ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርትን ተከታትለዋል።
 
በአውሮፓውያኑ 1976 በኢትዮጵያ ውስጥ የቅስና ማዕረግን ተቀብለው ከሦስት ዓመት በኋላ ለአንድ ዓመት በወታደራዊው መንግሥት ታስረው ቆይተዋል። 
 
ወደ ሮም አቅንተው በመንፈሳዊ ሥራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፤ ተጨማሪ ትምህርትም ተከታትለዋል።
ከጣሊያን ተመልሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፎች በማገልገል የቤተክርስቲያኗ መሪ እስከመሆን ደርሰዋል።
 
ከአስር ዓመት በፊት ፖፕ ፍራንሲስ ወደ ጵጵስናው መንበር ከመጡ በኋላ በርከት ያሉ ካርዲናሎችን ከአፍሪካ እና ከእስያ አገራት በሾሙበት ጊዜ ብርሃነየሱስ ሱራፌልም በአውሮፓውያኑ የካቲት 15/2015 በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ካርዲናል ሆነው ተሾመዋል።
በዚህም ምክንያት ካርዲናል ብርሃነየሱስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመላው ዓለም ካሏት 252 ካርዲናሎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ፖፕ ፍራንሲስን የሚተኩትን አዲሱን ጳጳስ ከሚመርጡት 135 ካርዲናሎች አንዱ ይሆናሉ።
 
ካርዲናሎች አዲስ ጳጳስ እንዴት ይመርጣሉ?
 
ለቤተ ክርስቲያኗ አዲስ ጳጳስ መምረጥ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉም ካርዲናሎች ሮም ውስጥ ወደምትገኘው ቫቲካን ተጠርተው ፓፓል ኮንክሌቭ በሚባለው ስፍራ ተነጥለው ስብሰባ ያካሂዳሉ። 
 
ይህ ጳጳስ የመምረጥ ሂደት ከሞላ ጎደል ለውጥ ሳይደረግበት ለ800 ዓመታት ያህል ሲተገበር የቆየ ነው።
ካርዲናሎቹ በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ (ክርስቲያናዊ የአምልኮ ሥርዓት) ያደርጋሉ። ከዚያም በቫቲካን ሲስቲን ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሰበሰባሉ።
 
በመቀጠልም አዲስ ጳጳስ የሚመረጥበት ሂደት መጀመሩ ከተገለጸ በኋላ፣ ሁሉም ካርዲናሎች አዲስ ጳጳስ እስኪመረጥ ድረስ ከቫቲካን ሳይወጡ በአንድ ስፍራ ይቆያሉ።
 
በምርጫው የሚሳተፉት ካርዲናሎች በዝግ በሚካሄደው ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ቀዳሚ ድምጽ የማግኘት አማራጭ አላቸው።
ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ለሊቃነ ጳጳሳነት የሚወዳደሩት ዕጩዎች ብዛት ወደ አንድ እስኪደርስ ድረስ በየጠዋቱ ሁለት ምርጫዎችን፣ ከሰዓት በኋላም ሁለት ድምጽ የመስጠት ሂደቶችን በቤተ መቅደስ ውስጥ ያካሂዳሉ።
 
በድምጽ መስጠት ሂደቱ እያንዳንዱ ካርዲናል መራጭ የሚመርጠውን ዕጩ ስም ስር "ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጌ መርጫለሁ" በማለት በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ይጻፋሉ። 
 
ሂደቱን ምሥጢራዊ ለማድረግም ካርዲናሎቹ በተለመደ የእጅ ጽሑፍ ስልታቸው እንዳይጠቀሙ ይደረጋል።
በሁለተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ግልጽ በሆነ ልዩነት የተመረጠ ካርዲናል ከሌለ በሦስተኛው ቀን ምንም ድምጽ ሳይሰጥ ለጸሎት እና ለማሰላሰል ይውላል።
 
ከዚያ በኋላም ድምጽ መስጠት እንደተለመደው ይቀጥላል።
 
አንድ ዕጩ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ለመመረጥ ከመራጮቹ ካርዲናሎች የሁለት ሦስተኛውን ድምጽ ማግኘት ያስፈልገዋል።
በዚህ ሂደት ከዕጩዎቹ መካከል አንዱ ከፍተኛውን ድምጽ ማግኘት ካልቻለ ድምጽ መስጠቱ ለበርካታ ቀናት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሳምንታት ሊቀጥል ይችላል።
 
ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ምን ይከናወናል?
 
ካርዲናሎቹ የሚሰበሰቡበት ስፍራ ከሁሉም የተነጠለ እና ከቀሪው ዓለም ጋር የማይገናኙበት ነው።
በዚህም ወቅት ቫቲካንን ለቅቀው አይወጡም፣ሬዲዮን አይሰሙም፤ቴሌቪዥን አይመለከቱም፤ ጋዜጦችን አያነቡም ወይም በውጭው ዓለም ከሚገኝ ከማንኛውንም ሰው ጋር በስልክ አይገናኙም።
 
በስፍራው የቤት ውስጥ ሥራን ከሚያከናውኑ ሠራተኞች፣ ከዶክተሮች እና ንሰሐ ከሚቀበሉ ቀሳውስት በስተቀር ማንም ሰው ካርዲናሎቹ ወዳሉበት እንዲገባ አይፈቀድም። 
 
እነሱም የሂደቱን ምሥጢራዊነት ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል።
 
በድምጽ መስጠቱ ሂደት መካከል፣ ካርዲናሎቹ (ድምጽ በመስጠት የሚሳተፉት እና በእርጅና ምክንያት የማይመርጡት) በቀረቡት ዕጩዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።
 
ማንም ለመመረጥም ሆነ ሌላውን ለማስመረጥ ቅስቀሳ ማድረግ አይፈቀድለትም።
ቫቲካን ካርዲናሎቹ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ናቸው ትላለች። ይህ ቢሆንም ግን ለአንድ ወይም ለሌላ ዕጩ ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደት በጣም ፖለቲካዊ ነው ተብሎ ይታሰባል።
 
በየቀኑ ሁለት ጊዜ ካርዲናሎቹ ለምርጫ ድምጽ በመስጠት የተጠቀሙባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲቃጠሉ ይደረጋል።
ካርዲናሎቹ ድምጽ ከሚሰጡበት ስፍራ ካለው የጭስ ማውጫ በኩል የተቃጠሉት ወረቀቶች ጭስ ሲወጣ በቫቲካን ተሰብስበው ውጤቱን የሚጠባበቁ ምዕመናን ይመለከታሉ።
 
ወረቀቶቹ ሲቃጠሉ ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም ስለሚደረግባቸው በጥቁር የተነከሩት የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ጥቁር ጭስ እንዲወጣ ሲያደርጉ በነጭ የተነከሩት ደግሞ ነጭ ጭስ ያወጣሉ።
ይህም ጭሱን ለሚመለከቱ ሰዎች መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው። 
 
ጭሱ ጥቁር ከሆነ በተካሄደው ድምጽ አሰጣጥ ከዕጩዎቹ መካከል ማንም የበላይነት ድምጽ ያገኘ አለመኖሩን ሲያመለክት፣ ነጭ ከሆነ ግን ካርዲናሎቹ አዲስ ጳጳስ መምረጣቸውን ያበስራል።
ጳጳሱ ሲመረጡ ምን ይሆናል?
 
በዕጩነት ከቀረቡት ካርዲናሎች መካከል አንደኛው አስፈላጊውን ድምጽ አግኝተው ከተመረጡ "ይህንን ቀኖናዊ ምርጫ ተቀብለው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቀ ጳጳስነት ይቀበላሉ?" ይጠየቃሉ።
 
ተመራጩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ተብለው ሊጠሩበት የሚፈልጉትን ስም በመምረጥ የጵጵስና ካባ እንዲለብሱ ይደረጋል።
የቀሩት ካርዲናሎችም ለአዲሱ ጳጳስ እጅ ይነሳሉ፤ ሊታዘዟቸውም ቃል ይገባሉ።
 
ይህንንም ተከትሎ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን በረንዳ ላይ በላቲን ቋንቋ "ጳጳስ አለን" ተብሎ ይታወጃል።
 
የአዲሱ ሊቃነ ጳጳሳት ስም ይፋ ይሆናል፣ ጳጳሱ ራሳቸውም በአካል ወጥተው ለሕዝቡ ይታያሉ። አዲሱ ጳጳስም አጭር ንግግር አድርገው ለከተማዋ እና ለዓለም የቡራኬ ቃል ያስተላልፋሉ።
 
በመጨረሻም በምሥጢራዊ ምርጫ ሂደት የእያንዳንዱ የምርጫ ዙር ውጤትን ጳጳሱ እንዲመለከቱ ይደረጋል።
ሰነዶቹ ታሽገው በቫቲካን ቤተ መዛግብት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገው ከዚያ በኋላ ሊከፈቱ የሚችሉት በሊቀ ጳጳሱ ትዕዛዝ ብቻ ነው።»
 
• «የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አረፉ»
 
21 ሚያዚያ 2025
«ለረጅም ጊዜ በከባድ የጤና ችግር በሕክምና ላይ የቆዩት የ88 ዓመቱ አዛውንት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፓፕ ፍራንሲስ ማረፋቸውን ቫቲካን አስታወቀች።
 
ወደ ጵጵስናው መንበር ከመምጣታቸው በፊት ካርዲናል ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ በመባል ይታወቁ የነበሩት ጳጳሱ፤ ቀዳሚያቸው ፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነበር በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2013 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ የተመረጡት።
 
ፖፕ ፍራንሲስ ለወራት በሕክምና ላይ በነበሩበት ጊዜ ከአደባባይ ርቀው ከቆዩ በኋላ እሁድ ዕለት በተከበረው የትንሳዔ በዓል በቅዱስ ጴጥሮስ ለተሰበሰበው ምዕመን በአካል ተገኝተው የትንሳዔ በዓል መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
 
ጳጳሱ ዛሬ ሰኞ ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም. በፋሲካ በዓል ማግስት ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ካዛ ሳንታ ማርታ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በ88 ዓመት ዕድሜያቸው ማረፋቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች።
 
ብጹዕነታቸው ካርዲናል ፋረል በጳጳሱ ሞት ሐዘን ውስጥ ሆነው "የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣ የቅዱስ አባታችን ፍራንሲስ ሞትን በጥልቅ ሐዘን አሳውቃለሁ" ሲሉ የጳጳሱን ሕልፈት ይፋ አድርገዋል።
 
ዛሬ ሰኞ ጠዋት 7:35 ላይ ቫቲካን ውስጥ ማረፋቸውን የጠቀሱት ካርዲናል ፋረል "ፍራንሲስ ወደ አባታቸው ቤት ተመልሰዋል። ሕይወታቸውን ለጌታ እና ለቤተክርስቲያናቸው ሰውተው ነበር" ብለዋል።
አቡነ ፍራንሲስ ከደቡብ አሜሪካ የተሾሙ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጰስ ናቸው።
 
ግሪጎሪ ሳልሳዊ በ741 ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ለሮማ ካቶሊክ ከአውሮፓ ውጪ ሊቀ ጳጳስ ሲሾም አቡነ ፍራንሲስ የመጀመሪያው ናቸው።
በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካውያን መንፈሳዊ መሪ የሆኑት ፖፕ ፍራንሲስ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ አዲስ ጳጳስ እስኪመረጡ ድረስ የቤተክርስቲያኗ መሪነት ከፍተኛ ሥልጣን ባላቸው ካሪዲናሎች በጋራ የሚካሄድ ይሆናል። 
 
በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 252 ካርዲናሎች ያሏት ሲሆን፣ የፖፕ ፍራንሲስ ምትክን ለመምረጥ ጉባኤ ሲሰየም ከካርዲናሎቹ መካከል 138ቱ ብቻ ናቸው አዲስ ጳጳስ በመምረጡ ሂደት ድምጽ መስጠት የሚችሉት።
 
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ባለፉት ወራት ጤናቸው ታውኮ አምስት ሳምንታትን በሁለት ሳምባቸው ላይ ላጋጠማቸው የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) በሆስፒታል ተኝተው ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል።
 
ፖፕ ፍራንሲስ በሕይወት ዘመናቸው በ21 ዓመታቸው አንዱ ሳምባቸው በቀዶ ሕክምና እንዲወጣ ያደረገውን ጨምሮ በርካታ የጤና እክል ገጥሟቸዋል።
 
የጳጳሱ ህልፈት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በመላው ዓለም ያሉ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንዲሁም ታላላቅ የአገራት መሪዎች ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው።
 
የሆላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲክ ስኮፍ "ፖፕ ፍራንሲስ በሁሉም መስኮች የሕዝብ ሰው ነበሩ" ያሉ ሲሆን፣ የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ ደግሞ "የሌሎችንም ገጽ የሚያፈካው ፈገግታቸው በመላው ዓለም ሚሊዮኖችን ለመማረክ ችሏል" ብለዋል።
የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይሳክ ሄርዞህ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን "ወሰን የሌለው ርህራሄ" ባለቤት ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
 
የስዊትዘርላንድ ፕሬዝዳንት ካሪል ኬለር-ሱተር ደግሞ ፖፕ ፍራንሲስን "ታላቅ መንፈሳዊ መሪ፣ የማይደክማቸው የሰላም ተከራካሪ" በማለት በህልፈታቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል።
 
የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስተር ጆን ስዊኒም በተመሳሳይ ጳጳሱን "የሰላም፣ የመቻቻል እና የዕርቅ" ድምጽ ሲሉ ገልጸዋቸዋል።»

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?