ሽብር እና ጭካኔ እስከ መቼ???! #ንጹሁ ፍጡር ገበሬ በጅምላ ለምን በባዕቱ ይፈጃልን? ለምን? #አብረን #እናምጥ!

 

ሽብር እና ጭካኔ እስከ መቼ???! #ንጹሁ ፍጡር ገበሬ በጅምላ ለምን በባዕቱ ይፈጃልን? ለምን? #አብረን #እናምጥ!
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
ዛሬ ዕለተ ሃሙስ የቀን ቅዱስ ከመሆኑም በላይ እኔም መላ ቤተሰቤም ተወልደን ባደግንበት በዓት በ፵፬ቱ እቴጌ ጎንደር #የአዳም ቀን ይባላል። በስቅለቱ ልጆች ሆሆ ምሻምሾ ብለው ያጠራቀሙት ዱቄት ዘይት እና ድልህ ተሰናድቶ በወል ይመገባሉ። ዛሬ ደግሞ ስለ #ስለአዳም ተብሎ ልጆች ለምነው በሚሰበስቡት ቅቤ፤ ቋንጣ፤ እንጀራ ተሰርቶ ወጡ በጋራ ልጆች ይበላሉ። ሁለቱም ትውፊት ጥልቅ ትርጉም ያለው መከራን እና ደስታን በጋራ ማስተናገድን ዕውቅና የሚሰጥ ክስተት ነው።
 
እኔ ዛሬ ይህን ከባድ ሃዘን ባልዘግብ በወደድኩኝ። ግን ባለመታደል ምዕራፍ ፲፮ ለመጀመር ዳርዳር ስል ያገኜሁት ውስጤን የነካ ሃዘን ማቅረብ የግድ ሆነ በዕለተ አዳም ቅዱስ ቀን።
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት ናችሁልኝ። ብኖርም ባልኖርም ተግባሬን አክብራችሁ ለምትልኩልኝ ሐዋርያዊ መልዕክቶቻችሁ እጅግ አመሰግናለሁኝ። ኑሩልኝ። አሜን። ባልነበርኩበት ወቅትም ሼር ያደረጋችሁልኝ ውዶቼ ተባረኩልኝ። አሜን።
የዓመቱ ፋሲካ፤ የሁዳዴ ፆም መፍቻ ለዛውም በንጹኃን ገበሬ ላይ የተፈፀመው ሰቅጣጭ ጭካኔ #ውረድ እና ፍረድን ያጠይቃል። ገበሬን? ጉሮሮን ለምን ይጨከንበታል???
 
ከጥቂት ደቂቃወች በፊት የሉዓላዊ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የሰጠውን ማብራሪያ አዳመጥኩኝ። በተጨማሪም ከሥር የተሰጡ አስተያዬቶችንም በተወሰነ ደረጃ አነበብኩኝ። ወጥ ዕይታ ወጥ አቀራረብ ነበረው። መቅደም የሚገባው #መደንገጥ፤ እንደሰው #መጨነቅ አብሮ ማዘን ሲገባ፦ ለድርጊቱ አፈፃፀም ፋክቱን በውስጥነት ማፈላለግ ሲገባ፦ ያዳመጥኩትም፦ ያነበብኩትም ግን ለእኔ አሳዝኖኛል። ስለሆነም ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ካቀረባቸው ውስጥ ሁለት አመክንዮወችን እንደ ገበሬ አደራጅነቴ የማውቀውን ሃሳብ ማቅረብ አስፈለገኝ።
 
1) "እንዴት ለአንድ ትምህርት ቤት አጥር ሥራ 100 ገበሬወች ለሥራ ወጡ?" የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጥያቄ ነው።
 
2) "አትማሩ ተብሎ እንዴትስ? ስለምንስ ትምህርት ቤት ማደስ አስፈለገ?" ሁለተኛው ሙግቱ ነው የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና። ቃልበቃል አልፃፍኩትም ዕድምታውን ነው። ድሮ የወጣልኝ ሞጋች በነበርኩበት ዘመን ሞግቼው የማላውቅ ጋዜጠኛ ነበር፤ ዛሬም ከማድመጥ ውጭ ምንም ብዬው አላውቅም። ትንሳኤ ማቅ ሲታዘዘ ይህን ለማቆላመጥ ያቀረበበት መንገድ ውስጤን በእጅጉ ጎዳው እና ትንሽ ልል ፈለግሁኝ። ጥሞና ላይ ስለነበርኩ እንጂ በአንድ ጉዳይም የሚያጽፍ ገጥሞኝ ነበር። አንድ ሙሉ ማህበረሰብ ሲጠራ በሙሉነቱ ሊሆን ስለሚገባው። የሆነ ሆኖ ወደ ዕለቱ ጉዳይ ………
 
1) በአማራ ገበሬ ዘንድ የተለመደ የወል የሥራ ባህል አለ። ይህም ወበራ ወይንም ደቦ ይባላል። እንደዬ አካባቢው ሥያሜው ሊለያይ ቢችልም ተልዕኮው ግን #በፈቃድ ላይ የተመሠረተ #ነፃ የህብረት የሥራ ባህል ነው። ለእርሻ፤ ለጉልጓሎ፤ ለአረም፤ ለአጨዳ፤ ጎጆ ለመስራት ወዘተ ሊሆን ይችላል። 
 
ይህ በተባዕት ገበሬወች ብቻ ሳይሆን በአማራ ክልል የከተማ ሴቶችም ሆነ በገጠርም የፈትል፤ የሥፌት፤ የሰበዝ አጨዳ፤ የአክርማ ነቀላ፤ ወዘተ የወል የሥራ ባህል አላቸው። የቡና ማህበር ባህልም አለ። በጣም ደስ ብሏቸው የሚከውኑትም ነው። ተናፋቂ ኢቬንትም ነው። ሥራውን ሲጨርሱ ሆታ አለ። የውስጥ ደስታም አለ። ማዕድ በጋራ ይመገባሉ። ልዩ የሆነ የፍቅር፦ የመተባበር ባህል ነው።
 
 ኢትዮጵያ የምትመሰጠረውም በዚህ መሰል #የተባ ባህሏ ነው። በ2013/2014 እኢአ በኢትዮጵያዊነት ላይ በፃፍኩት በስፋት አቅርቤዋለሁኝ። ጋዜጠኛ ሲሳይ ቁጥሩ 100 በዝቷል ባይ ነው። እኔ ደግሞ 100 ሲያንስ ነው ባይ ነኝ። ምክንያቱም የተቋማት ምስረታ ሰፋ ያሉ አካባቢወችን አካታች ስለሆነ። ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል። አንድ ትምህርት ቤት፤ አንድ የሃይማኖት ተቋም ሲመሰረት #ኩታ #ገጠም የገበሬ ማህበራትን ያጠቃልላል። በሞፈር ዘመትም በቤተዘመድ ምክንያትም ተጨማሪ አቅም ሊኖር ይችላል።
 
የተቋማቱ ቦታውም ማዕከላዊ ነው የሚሆነው። በደርግ ጊዜ የአገልግሎት ህብረት ሥራ ማህበራት የሚባል ነበር። ተግባሩ ኩታገጠም የገበሬ ማህበራትን በኢኮኖሚ አቅም አደራጅቶ፦ አንድ የጋራ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ይከፈትላቸዋል። ስለሆነም ትምህርት ቤቱን ለመገንባት፤ አጥሩን ለማጥበቅ፤ ወይንም የጉድጓድ ውሃ ለማውጣት ከአንድ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት በላይ የሆኑ ነዋሪወችን ያሳትፋል። ስለዚህ ለእኔ የBBC የአማርኛው ዘገባ ያቀረበው ዘገባ #ለፋክት የቀረበ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። አንድም ሰው ጋዜጠኛ ሲሳይን ፋክቴ ነው ባለው ሃሳብ ላይ ፋክት ይዞ ቀርቦ የሞገተው አላነበብኩም። ለዚህም ነው ፔጄ ላይ ማብራራት ግድ የሆነው።
 
2) "የፋኖ የትምህርት #አትማሩ" ዓዋጅ እያለ እንዴት የትምህርት ቤት አጥር አዳሽ ሊኖር ቻለ ለሚለውም የጋዜጠኛ ሲሳይ ሃሳብ፦ እኔ ከተመክሮዬ መነሳት ግድ ይለኛል። እኔ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ "#አትማሩ" የኢህአፓ በኽረ አጀንዳ ነበር። በህይወቴ እምወደው ትምህርት ነበር። የደረጃም ተማሪ ነበርኩኝ።
 
እና የኢህአፓን "አትማሩ" ዓዋጅ እኔም ቤተሰቤም አልተቀበለውም ነበር። እና እናቴ ደብተሬን ገብያ የምትሄድ መስላ በዘንቢል ትይዛለች። ከዛ ወደ ትምህርት ቤት ትወስደኛለች። እስክጨርስ ድረስ ግራሩ ሥር ቁጭ ብላ #ጥጥ ታሳሳለች፤ ቀለም ታቀልማለች። ትምህርታችን ስንጨርስ በሄድንበት ሳይሆን ሌላ መንገድ ቀይራ ወደ ቤታችን እንመለሳለን። ይህን ኢህአፓወች ያውቃሉ። 
 
"እሷ ድርብርብ ጭቆና አለባት" ይላሉ። አልፎ አልፎም ደጃፋችን ላይ ማስጠንቀቂያ ይጣላል። የሚገርመው ያን ጊዜ እኛን "አትማሩ" ያሉት እነ ፕሮፌሰር ዶር ብርሃኑ ነጋ ዛሬለትምህርት ተቆርሿሪ ከመሆናቸው በላይ የትምህርት ሚኒስተርም ናቸው። እኛ እንደ ዶከክን ቅርት ብለናል። በስጋት እና በጭንቀት ተማርን፤ እድገታችንም በፍርሃት የተዋጠ ነበር። 
 
በኢህአፓ ከአገር የወጡት በሙሉ የተማሩ ናቸው። ትምህርታችን እንቀጥላለን ብለው የወሰኑ፦ በዚህ ምክንያት የተገደሉ ወጣቶች፤ የተሳደዱ ቤተሰቦች ጎንደር ነበራት። ዛሬ "አትማሩ" የሚለውን መራር ነገር ስሰማ በጣም ነበር ያዘንኩት። ጎንደርሻም ይህን መሰል ግድፈት ደግማ መፈጸሟ ሁልጊዜ ይገርመኛል። በእኛ በቃ ልትል ይገባት ነበር። በዘመነ ኢህአፓ የታጨደው የጎንደር ወጣት ነው። ዛሬም በገፍ የሚያልቀው የጎንደር ሊቃናት ነው። ዘመቻ እከሌን ለማስቀጠል የጎንደር ብሩኃን መገደል አለባቸው። 
 
የሆነ ሆኖ ለአቶ ሲሳይ አጌና የምገልጽለት በአማራ ክልል ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች እንዳሉ አምኖ ሊቀበል ይገባዋል። የፋኖን ዓዋጅ ተቀብለው ትምህርት ቤት የማይሄዱም ይኖራሉ፤ የሚሄዱም ይኖራሉ። #ወከባ በግራ ቀኙ ሊኖር ይችላል። በአብይዝም መንግሥት ለፋኖ አትገዙ፤ እንቀጣለን፤ በፋኖ በኩል ለአብይዝም አትገዙ እንቀጣለን ይኖራል። በደርግ ጊዜም እንዲሁ ነበር። ህዝባችን #በጋመ ምጣድ አሳሩን እያዬ ነው። በእኔ የወጣትነት ዘመንም ይኽው ነበር። ስለሆነም እኔ የBBC የአማርኛው ዘገባ #ለዕውነትነት የቀረበ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። አምኜዋለሁም። ማህጸኔ እንደ ዱባ ነው የተቀረደደው። 
 
ለመሆኑ ገበሬ ተገድሎ ንጹህ እንቅልፍ እንዴት ሊወስዳቸው እንደቻለ የአብይዝም ደጋፊወች ሳስበው ይጨንቀኛል። በወጣትነት ዘመኔ ትጉህ፤ ቀልጣፋ ሁለገብ ነበርኩኝ። ብዙ እጅግ ብዙ ዕድሎች ገጥመውኝ ከተማ ተወልጄ አድጌ ነገር ግን የገበሬው ኑሮ እጅግ ይመስጠኝ ስለነበር ብዙ ዕድሎቼን አጥፌያለሁኝ። ገበሬ እኮ በቁሙ የጸደቀ ባህታዊ ነው። ቸር አስቦ ቸር አቅንቶ ቸር ተመግቦ የሚኖር ቅኔ የማህበረሰብ ክፍል ነው። ገበሬን #በቦንብ???? ኦ! አምላኬ። 
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ገበሬ ማለት #የዝናብ ውሃ ነው። በቀጥታ ከሰማይ የሚወርደውን በእጃችሁ አቁታችሁ ብትጠጡት የዝናብን ውሃ ትፈወሳላችሁ። ይህ ንጹህ ማህበረሰብ በድሮን እሳት ሲቀጠል፥ እንደ ዘመኑ የትውልዱ ቤተኝነት ውስጣችን #ሊያምጥ ይገባል። ምጡ ፆታም - ዞግም - ሃይማኖትም ሳይለይ - አብረን ልናምጥ እንጂ ለወንጀሉ መደለጃ፤ ለዕንባው አቃቂር ለማውጣት ባንጣደፍ መልካም ነው። ውስጤ አዝኋል። ለዚህም ነው ገና ከውጥኑ ጦርነት አያስፈልገንም በማለት የሞገትኩት።
 
ሰሞኑን የሻለቃ ዳዊትን ቃለ- ምልልስ አዳምጫለሁኝ። አንድ #ሜትር #ጨርቅ #የተቀደደ ያህል እንኳን አልተሰማቸውም። ሙሉ ሁለት ዓመት ያለቀው፤ የደቀቀው፤ የፈለሰው፥ የተፈናቀለው፤ አካሉ የጎደለው፤ የተደፈረው ቤተ መቅደስ፤ የነደደው መሬት፤ የጎረፈው ደም በከንቱ ነው የተወራረደው። ጎጃም ላይ የአብነት ተማሪወች፤ ህዝብ አልቋል፤ ጎንደር ላይ ሊቃናት ተመንጥረዋል። ወሎ እና ሽዋም እንዲሁ የተጎዱ ቤተሰቦች አሉን። አጀማመሩን እና አመራሩን ከልብ ሆናችሁ እሰቡት። ነገስ??? በዚህ ዙሪያ የምትተጉ ሁሉ በጥሞና መርምሩት። ዘወትር ማቅ እና ዕንባ የአማራ ህዝብን #መኖርን እዬቀጠቀጠው ነውና።
 
ፋክቱ ለእኔ የBBC ዘገባ #ቅርብ ሆኖ ሳገኜው የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ትንተና እና መሞገቻ ነጥብ ግን ለፋክት በጣም ሩቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። አዝኛለሁም። የፃፈውን መጸሐፍ አንብቤ ዲፕርትመንቱ ፋክት ሊሆን ይገባል ስል ነበር። ያን ዕውነት ያሳጣ ትንተና ነው ያዳመጥኩት። ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለውም ከዚህ አንፃር ነው። 
 
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/04/2025
ሰውነት ከዬት ይጀምር????
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው። 
 
«በምሥራቅ ጎጃም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት "ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን" የዓይን እማኞች ተናገሩ»
23 ሚያዚያ 2025
«በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሐሙስ ሚያዝያ 9/2017 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ዙሪያ በደረሰ የድሮን ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።
 
በዞኑ እናርጅ እናውጋ ወረዳ ገደብ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ የትምህርት ቤት አጥር ለማጠር እና ቤት ለመሥራት 'ለልማት ሥራ' የወጡ "ሰላማዊ ሰዎች" በጥቃቱ መገደላቸውን ገልፀዋል።
 
የአካባቢው አስተዳደር ግን ጥቃቱ በአካባቢው ተሰብስበው በነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ላይ እንጂ በንፁሃን ነዋሪዎች ላይ አለመፈጸሙን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
 
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ተሰብስበው" በከተማዋ ያለው ገደብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አጥርን እያጠሩ በነበሩ የሰዎች ላይ ነው ጥቃቱ የተፈፀመው።
 
ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ እንደነበሩ የተናገሩ ሌላ የዓይን እማኝ ወዲያው ጩኸት፣ ግርግር እና ድንጋጤ መፈጠሩን ጠቁመው "የሆነውን አናውቀውም" ሲሉ በቅፅበቱ የነበረውን ሁኔታ ገልፀዋል።
 
እሳቸውን ጨምሮ ሥራ ላይ የነበሩ ሰዎች ጥቃቱ ወደተፈፀመበት አካባቢ ሲጠጉ "ሰው የሚባል አይለይም" ሲሉ ስለ ጉዳቱ ተናግረዋል።
"እንዳለ በሙሉ ጥቁር ነገር ነው የሆነው። አካባቢው በሙሉ ሰው የሚባል ነገር የለም። ከወደቀው ውስጥ የሚጮህ አለ፤ የሚንከባለል አለ። የተፈጠረው ነገር ይዘገንናል። ሰው ለሆነ እጅግ የሚዘገንን ድርጊት ነው" ብለዋል።
 
የፈረሰውን የትምህርት ቤቱን አጥር እያጠሩ እያለ ቀኝ እጃቸውን ተመትተው መቁሰላቸውን የተናገሩ ሌላ ነዋሪ "ከባድ ፍንዳታ" መከሰቱን ጠቅሰው "ብዙ ሰው ነው የተጎዳው" ብለዋል።
 
"ባሕር ዛር የሚቆርጥ፤ ሚስማር የሚመታ አለ፤ ማገር የሚቆርጥ አለ፤ የሚይዝ አለ" ሲሉ ማኅበረሰቡ መሰባሰቡን የገለፁ ሌላ የዓይን እማኝ የሟቾቹን ቁጥር "ብዛት ይኖረዋል" በማለት ገልፀዋል።
 
አስከሬን ስለማንሳታቸው የተናገሩ ሌላ እማኝ ደግሞ አብዛኛው የጥቃቱ ተጎጂዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀው፤ ሟቾቹ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው ብለዋል።
 
ከ24 በላይ ቁስለኞችንም ወደ ሕክምና መወሰዳቸውን የገለፁት እማኞች፤ አብዛኞቹ በከተማዋ ወደሚገኘው ገደብ ጤና ጣቢያ ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
 
ከ70 በላይ አስከሬን አንስተው በባጃጅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ማመላለሳቸውን የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ፤ ታዳጊዎችን እና ሽማግሌዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 120 እንደሚደርስ ገልፀዋል።
 
"ከ115 እስከ 120 የሚሆን አስከሬን ነው የተቀበረው። ያልታወቀም ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ድንጋጤ ውስጥ ስለነበርን" ብለዋል። ሌላ የዓይን እማኝ በበኩላቸው 57 አስከሬን እስከሚነሳ ድረስ እንደነበሩ ጠቁመው የሟቾቹ ቁጥር ከ100 በላይ እንደሚሆን ገምተዋል።
 
አስከሬኖቹ ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ሟቾችን መለየት ከባድ እንደነበር የተናገሩት እማኞች በዚህ ምክንያት እና በስጋት እስከ ቀትር 08፡00 ድረስ ገደብ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በጅምላ እንደተቀበሩ ገልፀዋል።
 
"አሞራ እንዳይበላቸው ቅበሩ ሲባል ማኅበረሰቡ በፍጥነት አምስት የሚሆን መቃብር ውስጥ ነው የቀበራቸው" ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል። የመንግሥት ኃይሎች ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተከትሎ ስጋት ያደረባቸው አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መሸሸታቸውን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ተጨማሪ ጥቃቶች መፈፀማቸውንም ጠቁመዋል።
 
ማኅበረሰቡ ከተረጋጋ በኋላ ለሟቾቹ ድንኳን እንደተጣለ እና ከቀናት በኋላ በአካባቢው "ፍራጅ" የሚባለው ማስተዛዘኛ መርሃ ግብር እንደተደረገም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
 
"ሰሞኑን ሲሸበር ነበር። ሕዝቡ በሙሉ ሽብር ላይ ነው ያለው" ሲሉ ዳግም የድሮን ጥቃት ይደርሳል በሚል የፋሲካ በዓልን በስጋት ማሳለፋቸውን "በዓል የሚባል ነገር የለም" ብለዋል።
 
"ከባድ ሐዘን ውስጥ ነው ያለው። በዓል ምንም አይመስልም ነበር። ለበዓል ከከተማ የሚመጡ ልጆች አልመጡም" ሲሉ አካባቢው በሐዘን ድባብ ውስጥ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
 
የአማራ ክልል ግጭት በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከተማዋ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆነች ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ጥቃቱ ሲፈፀም ግን የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋ ውስጥ እንዳልነበሩ እና በአካባቢው ግጭት እንዳልነበረ ጠቁመዋል። ታጣቂዎቹ "አንዳንድ ሥራ ለመሥራት ካልመጡ በቀር ከተማው ውስጥ አይታዩም" ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
 
ነጋዴ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ ሟቾቹ ንፁሃን ስለመሆናቸው ሲናገሩ "በርካቶቹን በንግድ ሥራቸው" የሚያውቋቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
 
"የፋኖ አባላት ቢሆኑ [አስከሬን ሲነሳ] ታጣቂ እናገኝ ነበር። ፋኖዎችን እና ማኅበረሰቡን [ለይተን] እናውቃቸዋለን። [ፋኖዎች] በአንድ ላይ ነው የሚንቀሳቀሱት" ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።
 
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው "የተሰበሰው አጥር የሚያጥረው እና ቤት የሚሠራው ሰው በቀረፃው [የድሮን ቅኝት] የፋኖ ስብስብ ነው ተብሎ ታስቦ ይሁን ያወቅነው ነገር የለም። . . .ምንአልባት ሲሰበሰብ ፋኖ ነው ተብሎ ታስቦ [ይሆናል] እንደዚያ ነው እኛ የተረዳነው" ሲሉ ጥቃት ሊፈጸም የቻለበትን ምክንያት ግምታቸውን ገልፀዋል።
 
የእናርጅ እናውጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ጌቴ ንፁሃን ሰዎች ተገደሉ መባሉን "የጠላት ወሬ" ያሉ ሲሆን፤ እርምጃው "ፅንፈኛ" ያሏቸው የፋኖ ታጣቂዎች ላይ መወሰዱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
 
"እዚህ አካባቢ ቁጥሩ በርከት ያለ የኃይል ስብስብ አለ። ሰብስበው ሥልጠና ጭምር [እንደሚሰጡ] መረጃው አለኝ። የትምህርት ቤት አጥር፤ ቤት ሥራ የሚባለው ነገር ማሳመሪያ ነው . . ." በማለት ንፁሃን በፍንጣሪም ቢሆን አልተገደሉም ሲሉ አስተባብለዋል።
የፋኖ ታጣቂዎች በበኩላቸው በወረዳው በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው ገደብ ከተማ አካባቢ ላይ ግን በወቅቱ "ምንም ዓይነት የታጠቀ ኃይል" አልነበረም በማለት በጥቃቱ የተገደለ አባል እንደሌላቸው ተናግረዋል።
 
አካባቢውን ለሥልጠና እንደማይጠቀሙት የተናገሩት የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ "ሁሉም ግድያው የተፈፀመባቸው ሲቪሊያን ናቸው። አንድም የታጠቀ ኃይል በቦታው ላይ አልነበረም" በማለት ግድያውን ማኅበረሰቡን ከማሸበር ጋር አያይዘውታል።
 
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የድሮን ጥቃቱ ላይ ክትትል እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።»
 
Lualawi ሉዓላዊ/ “ የሕወሐት እና ሻዕቢያ ትብበር ያሳስበናል ‘’/ የጎጃሙ የድሮን ጥቃት እና የ BBC ዘገባ ሲፈተሽ/ለመንግሥት ዕውቅና አንሰጥም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?