“ሰው መሃል ሆኜ ሁሉም ጨካኝ ሆኖብኝ ነበር” - የፀጋ በላቸው ዘጠኝ የጠለፋ ቀናት» BBC
መቼ የኢትዮጵያ ሴቶች ሁነኛ መንግስት ኑሯቸው እናይ ይሆን?
“ሰው መሃል ሆኜ ሁሉም ጨካኝ ሆኖብኝ ነበር” - የፀጋ በላቸው ዘጠኝ የጠለፋ ቀናት»
•
“ሰው መሃል ሆኜ ሁሉም ጨካኝ ሆኖብኝ ነበር” - የፀጋ በላቸው ዘጠኝ የጠለፋ ቀናት»
ከ 4 ሰአት በፊት
"ግንቦት 2015 ዓ.ም. የተፈጸመው የፀጋ በላቸው ጠለፋ ብዙዎችን ያስቆጣ፣ መነጋገሪያም የሆነ የወንጀል ድርጊት ነበር። ፀጋ፤ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ተጠልፋ ያሳለፈቻቸውን ቀናት በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቢቢሲ በዝርዝር ተናግራለች። እነዚያን የስቃይ ቀናት እያስታወሰች ስትተርክ፤ ከተፈጸመባት ጥቃት ይልቅ ጎልቶ የሚታየው ጥንካሬዋ ነበር።
ከቢቢሲ ጋር በነበራት ዘለግ ያለ ቆይታ፤ ስለተጠለፈችበት መንገድ እና ስላሳለፈቻቸው ዘጠኝ ቀናት በዝርዝር ተርካለች። ከጠለፋው ነጻ የወጣችበት መንገድም አስቀድሞ በክልሉ መንግሥት ከተገለጸው የተለየ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ተናግራለች። ለምን ከኢትዮጵያ እንደተሰደደች እና ስለ ቀጣይ ዕቅዶቿም እንዲሁ አጋርታለች።
ማሳሰቢያ - ይህ ታሪክ አንባቢዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ገለፃዎችን ይዟል።
ነጻ ለመውጣት በመስኮት ስሾልክ ራሴን አገኘዋለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር።
ተጠልፌ በተቀመጥኩባት ጨለማ ክፍል ውስጥ በእኔ እና በነጻነቴ መካከል ያለችው ማምለጫ አንዲት ትንሽ መስኮት ሆና ተገኘች።
እንዲለቅቁኝ ብዬ ያደረግኩት ልመና እና ለቅሶ ሰሚ አልነበረው። ምግብ ሊያቀርቡልኝ ወደ ክፍሉ የሚመጡ ሴቶች እንኳ በእንባዬ ልባቸውን አልራራም።
አመሻሽ ላይ ዋናው ጠላፊ እና ተባባሪዎቹ ከክፍሉ ሲወጡ ጠብቄ በትንሿ መስኮት አማተርኩ። አንዲት ሴት ቁጭ ብለዋል። በስጋት እና ነጻ በመውጣት ተስፋ መሃል ልቤ እየራደ ሴትዮዋ ዘወር እስከሚሉ ጠበቅሁ።
ሴትዮዋ ወደ ጎጇቸው ሲገቡ የሞት ሞቴን በትንሿ መስኮት ሾልኬ ወጣሁ። መጀመሪያ ኮቴዬ እንዳይሰማ ቀስ ብዬ ተራመድኩ። ቀጥሎ ግን ድንጋጤ እና ፍርሃት ውስጤን ስለሞላው የደመ ነፍስ ሩጫ ጀመርኩ።
በዚህ ጊዜ ጎጆ ውስጥ ያሉት ሴት ኮቴዬን ሰምተው ጮኹ። ፍጥነት ጨምሬ ሩጫዬን ከቀጠልኩ። ጩኸቱን ሰምተው ከቤት የወጡ ወንዶች ይከተሉኝ ጀመር። ዋነኛው ጠላፊ መካከላቸው አልነበረም።
ከግቢው ወጥቼ ዋና መንገድ ላይ ደረስኩ። የአድኑኝ ጩኸቴን የሰሙ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ዘወር ስል የሚያልፍ ሞተር ሳይክል ተመለከትኩ። ነጂውን አስቁሜ ሞተሩ ላይ ልወጣ ስል ሲያሯሩጡኝ ከነበሩት መካከል አንዱ ደርሶ ሞተሩን አስቆመው። እኔ ወደቅኩ።
ተስፋ አልቆረጥኩም። ጩኸቴን ሰምተው የተሰበሰቡትን ሰዎች እግር ይዤ ልመና ገባሁ። የሥራ መታወቂያዬን ከኪሴ አውጥቼ “የባንክ ሠራተኛ ነኝ። የማላውቃቸው ሰዎች አፍነው አምጥተውኝ ነው። እባካችሁ እርዱኝ” እያልኩ ተማፀንኩ።
ትልቅ ሰዎች፣ ሴቶች፣ ሕጻናት ተሰብስበዋል። አንዳንዶቹ፤ “ማንም አይነካሽም፤ ደርሰንልሻል” ሲሉ ቃል ገቡልኝ። ከሰዎች መካከል ጎትተው አይመልሱኝም ብዬ አሰብኩ።
የእኔ እምቢታ እና የሰዎች መሰብሰብ ይበልጥ ትኩረት እየሳበ ሲመጣ ዋነኛው ጠላፊ መጣ። ሊረዱኝ ቃል የገቡልኝ ሰዎች ወደ ጎን ወስዶ የፖሊስ መታወቂያውን እያሳየ አናገራቸው።
ይህንን ጊዜ የተሰበሰቡት ሰዎች ሀሳብ ተቀረ። “ጓደኛው አይደለሽ? ለምን ታስቸግሪያለሽ?” አሉኝ። “ይረዱኛል” ያልኳቸው ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባብረው፣ ተሸክመው ወዳመለጥኩበት ቤት መለሱኝ።
በጣም ብዙ ሰው ነበር። ነገር ግን ያለሁበትን ሁኔታ፣ የለመንኩትን ልመና ከቁብ የሚቆጥር አንድም ሰው አልነበረም።
ጠልፈው ሲወስዱኝም የሆነው እንዲሁ ነው። የጠለፈኝ ሰው እና አጋሮቹም ያበሩት በእኔ ላይ ነበር። አግተው የወሰዱኝም እንዲሁ በአመሻሽ ነው።
ግንቦት 15/2015 ዓ.ም. ከምሠራበት የሐዋሳ ከተማ ዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ የወጣሁት አምሽቼ ነበር። ተከራይቼ ወደምኖርበት ቤት ለመሄድ እንደተለመደው ወደ ታክሲ ተራ ሄጄ አንዱ መኪና ውስጥ ገባሁ።
የተሳፈርኩበትን ታክሲ የሞሉት ስቃዬን የደገሱልኝ ሰዎች እንደነበሩ አልጠረጠርኩም። ታክሲ ውስጥ ገብቼ ቁጭ እንዳልኩ አንድ ሰው ተሯሩጦ ገብቶ፤ ፈቅ አድርጎኝ አጠገቤ ተቀመጠ።
ታክሲውን የሞሉት ግዙፍ ሰውነት ያላቸው ወንዶች መሆናቸውን ያስተዋልኩት አጠገቤ ለተቀመጠው ሰው ሌላ ክፍት ወንበር ለማመልከት ወደ ኋላ ስዞር ነበር።
“ወራጅ አለ” ስል ከቀኝ እና ከግራ ያሉት ሰዎች አንገት እና እጄን ይዘው እንዳልንቀሳቀስ ነገሩኝ። በዚያ ሰዓት ሳስብ የነበረው ጉዳዩ ዘረፋ እንደሆነ ስለነበር ቦርሳዬን ወስደው እንዲለቅቁኝ እጠይቃቸው ነበር።
መኪናው ትንሽ መንገድ እንደተጓዘ ከመካከላቸው አንዱ “ጓደኛችንን አላናግርም ያልሽው ለምንድነው?” አለኝ።
“ጓደኛችሁ ማነው?” ጠየቅኩ።
“የኋላመብራትን አላወራም ብለሽዋል።”
የኋላመብራት ወልደማርያም የዋና ሳጅንነት የፖሊስ ማዕረግ ያለው የቀድሞ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አጃቢ ነው። በምሠራበት የሐዋሳ ከተማ የዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ በደንበኝነት ይመጣ የነበረው የኋላመብራት፤ “ላናግርሽ፣ እንገናኝ” እያለ ያስቸግረኛል። መግቢያ መውጫዬ ላይ ይጠብቀኝ፣ ስልክ እየቀያየረ በተደጋጋሚ ይደውልም ነበር።
መሥሪያ ቤት ውስጥ ባለች ባልደረባዬ በኩል ዛቻ አዘል መልዕክት ይደርሰኝ የነበረ ቢሆንም እንደዚህ አፍኖ እስከ መውሰድ ይደርሳል ብዬ አላሰብኩም።
የተሳፈርኩበት መኪና የሐዋሳ ከተማን ለቅቆ ወደ ገጠር አከባቢ ጉዞውን ሲቀጥል ፍርሃቴ እየጨመረ መጣ። ወዴት እንደምሄድ፣ ምን ሊያደርጉኝ እንደሚወስዱኝ አላውቅም። በማላቃቸው ሰዎች ቁጥጥር ውስጥ ሆኜ ሁሉም ነገር ጭልምልም አለብኝ።
መኪናው ጫካ የሆነ አካባቢ ሲደርስ በኋላ ወንበር ተደብቆ የነበረው የኋላመብራት አጠገቤ መጥቶ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ የእኔ ልመና ብቻ ይሰማበት የነበረው መኪና፤ የሰርግ ዘፈን ተከፍቶ ይጨፈርበት ጀመር።
“ጠለፋ ይሆን እንዴ?” ብዬ አሰብኩ። ኋላ እንደተረዳውትም ጉዳዩ ይህ ነበር።
ብዙ ተጉዘን አንድ የገጠር ቤት አቅራቢያ ስንደርስ ለእሱ ጋቢ ሰጥተው፤ ፊቴን ነጠላ ሸፈኑኝ። ከመኪናው ወርደን ወደ ቤቱ ስንገባ ደጅ ላይ የቆሙት ሰዎች በእልልታ ተቀበሉት። የኋላመብራት፤ ሽጉጥ አውጥቶ ወደ ሰማይ መተኮስ ጀመረ። ሁኔታው የሰርግ ድባብ ነበረው።
ሰው ሁሉ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጨፍራል። የአሸናፊነት ስሜት ላይ ነበሩ። እኔ አለቅሳለሁ፣ እለምናለሁ. . . ሰሚ አልነበረም። ሁኔታቸው ምርኮ ይዞ እንደመጣ ጀግና ነበር።
ኩራዝ ብቻ የበራበት ጨለማ ክፍል ውስጥ አስገቡኝ። ጠባቡ ክፍል ውስጥ ሊወቅድ የደረሰ አልጋ ተቀምጧል። አሁን ላይ ክፍሉን ሳስበው መቃብር መስሎ ይታየኛል። እያለቀስኩ፣ እየጸለይኩ ሌሊቱ ነጋ።
በማግስቱ ዋነኛው ጠላፊ የኋላመብራት እና አባሪዎቹ ቤቱ ደጅ ላይ ስብሰባ መሰል ነገር አድርገው ሲጨርሱ አስጠሩኝ።
“ከዚህ በኋላ የኋላመብራት ሚስት ነሽ። ሽማግሌዎችን አዘጋጅተናል። ለቤተሰቦችሽ ትደውያለሽ። ሽማግሌዎችን ይቀበሏቸዋል” ብለው በእኔ ላይ ያጸቀዱትን ውሳኔ ነገሩኝ። ያዘዙኝን ለመፈጸም ወደ ቤተሰቦቼ ደወልኩ።
ቤተሰቦቼ መጥፋቴን አውቀው ስለነበር፤ ያወሩኝ የነበረው በድንጋጤ ነበር። የት እንዳለሁ ለማወቅ በጥያቄ እያጣደፉኝ ስልኩ ተዘጋ። እኔንም መልሰው ወደዚያች ክፍል አስገቡኝ።
በዚህ ምሽት ነበር በትንሿ መስኮት ወጥቼ ለማምለጥ የሞከርኩት። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስኩት ሌላ አማራጭ እንደሌለኝ በመረዳቴ ነው።
በራሱ ውሳኔ ሚስቱ ያደረገኝ ጠላፊ ግን ነጻ የመውጣት መፍጨርጨሬን የቆጠረው ክብሩ ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ነበር። የማምለጥ ሙከራዬ ከሽፎ፤ ተሸክመው ወደ ቤት በሚመለስሱኝ ሰዓት በእልህ እሳት የነደዱ ዓይኖቹን አያቸው ነበር።
“እንዴት ታመልጫለሽ?... ልታዋርጂኝ ነው?... ከእጁ ሴት አመለጠች ልታስብዪኝ ነው?... ማንም ከእኔ እጅ አያመልጥም” ደጋግመው ከአፉ የሚወጡ ቃላት ነበሩ።
ተሸክመው ወደ ቤት የመለሱኝ ሰዎች ሳሎን ውስጥ እንደተቀመጡ ወዳመለጥኩባት ጨለማ ክፍል ይዞኝ ገባ። እንዳይሆንብኝ የፈራሁት ከባዱ ነገር ሊሆንብኝ ሆነ።
እዚያች ክፍል ውስጥ ተደፈርኩ።
ከባድ ነበር . . . በእልህ ነበር . . . ወንድነቱን ለማሳየት በትግል ነበር። አቅሜ ተፈተነ።
ራሴን በመጠበቅ ውስጥ ነበር ያቆየሁት። ከዚህ በፊት ወንድ አላውቅም ነበር። በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ለማግባት ዝግጅት ላይ ነበርኩ።
ከዚህ ድርጊት በኋላ ሲመሽ የሚሆነው እያሰብኩ ቀኑን ሙሉ ሳለቅስ እውላለሁ። በመሸ ቁጥር ወንድነቱን ይጠቀም ነበር።
“ምግብ በልታለች ወይ? ተጨንቃለች? እያለቀሰች ነው” የሚል ርህራሄ የለውም። በተደጋጋሚ ይደፍረኝ ነበር። ራሴን እስክስት ድረስ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ይጠቀመኝ ነበር።
ለቀናት በዚህ ሁኔታ ወስጥ እያለፍኩ ምንም ማድረግ አልቻልኩም። ቤት ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ ተባብሮ ጨካኝ ሆኖብኛል። እጮሃለሁ፣ እርዳታ እጠይቃለሁ፤ ህመሜን የሚረዳ አልነበረም።
ሰው መሃል ሆኜ ሁሉም ሰው ጨካኝ ሆኖብኝ ነበር።
“ተው” የሚል ከልካይ፣ “ምን እየሆነች ነው?” የሚል ጠያቂ አልነበረም። በየቀኑ ብዙ ሰዎች ወደ ቤቱ ቢመጡም ስለ እኔ ሁኔታ ግድ አላላቸውም።
መሽቶ በነጋ ቁጥር ያስፈራል። እጠባበቅ የነበረው መውጣቴን ነው።
• በጠለፋ ዙሪያ የሚካሄድ ባሕላዊ ሽምግልና ከኢትዮጵያ ሕግ ጋር ይቃረናል?20 ሀምሌ 2023
• ሁለት ሴት ልጆች ተጠልፈውበት የተመሳቀለው የደጊቱ ቤተሰብ ሰቆቃ15 ሰኔ 2023
• በሀዋሳ የ14 ዓመት ታዳጊ 'መጠለፏ' ተነገረ13 ሰኔ 2023
በአንዱ ቀን ምግብ እንድታበላኝ የተላከችን ልጅ “ያለንበት ሰፈር ምን ያባላል” ብዬ አግባብቼ ጠየቅኳት። “ቡርሳ” ብላ ነገረችኝ።
ይህንን ከነገረችኝ ከሰዓታት በኋላ እንዴት እንደሆነ በማላውቀው ሁኔታ አጠገቤ የተረሳ ስልክ አገኘሁ። ለሰከንዶች እጄ በገባው ስልክ “ቡርሳ” የሚል መልዕክት ወደ ቤተሰቦቼ ላክሁ። መልዕክቱን ከስልኩ ላይ አጠፋሁት።
ቤተሰቦቼ መልዕክቱ የደረሳቸው ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጥ አጥተው፤ በራሳቸው ላይ ታች በሚሉበት ጊዜ ነበር። መሥሪያ ቤት ውስጥ አብራኝ የምትሠራው ልጅ ስለ እኔ መጥፋት ስትጠየቅ “የኋላመብራት እንደወሰደኝ” በመናገሯ ጠላፊው የፖሊስ አባል እንደሆነ አውቀዋል። ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያሏቸው ቢሮዎችን ደጅ እየጠኑ ነበር።
በኢትዮ ቴሌኮም ትብብር መልዕክት የተላከበት ቁጥር አድራሻው “ቡርሳ” እንደሆነ አወቁ። መልዕክቱ ያለሁበት ቦታ ስም መሆኑን ስለተረዱ ያገኙትን መረጃ ለፖሊስ አቀረቡ።
በማግስቱ ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ ፖሊሶች እና ወንድሜ ቡርሳ ፖሊስ ጣቢያ ደረሱ። እስከ አራት ሰዓት ድረስ አጋቹን በምን ዓይነት መንገድ ይዘወት ነጻ እንደሚያወጡኝ እያቀዱ ነበር። የአካባቢውን ሰዎች አጠያይቀው ወደ ነበርኩበት ቤት ሲደርሱ ግን እኔም ሆነ ጠላፊዬ አልነበርንም።
የኋላመብራት፤ ፖሊሶች አካባቢው ላይ ስለመድረሳቸው አስቀድሞ መረጃ ደርሶት ነበር። እነሱ ወደ ቤቱ ከመድረሳቸው በፊት ከአካባቢው ይዞኝ ሸሽቷል። ሰውነቴ ቁስል ሆኖብኝ ብደክምም፤ ረጅም መንገድ በእግር እና በሞተር ሳይክል እንጓዝ ነበር።
በሽሽት ያስቀመጠኝ አካባቢ ላይ ፖሊሶች በተቃረቡ ቁጥር የሚያስፈሩ መንገዶችን በሌሊት፣ በጉም እንድጓዝ ተገድጄ ነበር። ምንም እንኳ የርሃብ ስሜት ባይሰማኝም፤ እየተመገብኩ ስላልነበር ሰውነቴ ዝሏል።
በጣም በሚያሰቅቀው ደግሞ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ እንኳ ወንድነቱን ይጠቀም ነበር። እኔ ላይ ስቃዩን በማብዛት ቤተሰቦቼ ጋር ደውዬ “ሽማግሌ ተቀበሉ፤ የሚሏችሁን አድርጉ” ብዬ እንድናገር ይደረግ ነበር።
ቀናት እየገፉ፣ የእኔም ድምፅ እየጠፋ ሲመጣ ቤተሰቦቼ በተጠለፍኩ በሰባተኛው ቀን ጉዳዩን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ አወጡት። ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መውጣቱ እና መነጋገሪያ መሆኑ ፖሊሶች በጠላፊው ላይ ጫና እንዲፈጥሩ አደረጋቸው። የየኋላመብራት ቤተሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋል ጀመሩ።
እነዚህ የፖሊስ እርምጃዎች እርሱ ላይ ጫና ስለፈጠረ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ጠለፋውን እንድቀበል ሊያግባቡኝ ሞከሩ። ለማሳመን ሲያቅታቸው፤ “እንለቅሻለን፣ ወደ ቤተሰቦችሽ ትሄጃለሽ። ከዚያ ግን በእርቅ ያልቃል” አሉኝ። ጉዳዩ በእርቅ እንደሚያልቅ ለማረጋጋጥ መሃላ እንደምፈፅም አስረዱኝ።
የመሃላ ሥነ ሥርዓቱ በንጋታው ጠዋት እንዲፈጸም ተቀጥሮ እያለ ፖሊሶች ወደነበርኩበት ከተማ እንደደረሱ ለየኋላመብራት መረጃ ደረሰው። እኔን ቤት ውስጥ ትቶኝ ሸሸ።
በማግስቱ ሌሎቹ ሰዎች የትራንስፖርት ብር አስይዘው ወደ መናኸሪያ ወሰዱኝ። እንዴት የተለያዩ መኪናዎችን ተሳፍሬ ሐዋሳ ከተማ እንደምደርስ ነገሩኝ። ሐዋሳ ከተማ ስቃረብ ለቤተሰቦቼ እንድደውል ሲም ሰጥተው ለቀቁኝ።
ሰውነቴም፣ አዕምሮዬም አቅማቸውን ስጨረሱ አድርጊ የሚሉኝን አደርግ ነበር። በደመነፍስ ጽፈው በሰጡኝ መሠረት ሦስት መናኸሪያዎች ውስጥ እየወረድኩ፣ እየተሳፈርኩ ወደ ሐዋሳ ተቃረብኩ። ቤተሰቦቼ ጋር ደውዬ “ተለቅቄያለሁ እየመጣሁ ነው፤ ሐዋሳ መግቢያ ላይ ጠብቁኝ” አልኩ።
ሐዋሳ መግቢያ ላይ ስደርስ ከባድ ፍተሻ ነበር። ብዙ የፖሊስ መኪኖች ቆመው፣ የሚመጣው ሰው ሁሉ ከመኪና እየወረደ ይፈተሻል። የነበርኩበት መኪናም ቆሞ ስወርድ ፖሊሶች ጠሩኝ።
“የምንፈልገው አንቺን አይደል እንዴ” ብለው ከጎን እና ከጎን እንደ ወንጀለኛ ይዘው የፖሊስ መኪና ውስጥ ሊያስገቡኝ ሲሉ “ቤተሰቦቼን ሳላገኝ አልገባም” አልኩ። በስልክ አገናኝተውኝ፤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ።
የፎቶው ባለመብት, Alemayehu Timotewos
የምስሉ መግለጫ, ፀጋ በላቸው ከጠለፋ ነፃ ከወጣች በኋላ ከሲዳማ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ጋር
ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ባለሥልጣናት እና የፖሊስ ኃላፊዎች ተሰብስበው ከየት እንደመጣሁ፣ እንዴት እንደተለቀቅኩ ጠየቁኝ። የተነሳሁበትን ቦታ እንደማላውቅ አስረድቼ አቆራርጬ የመጣሁባቸውን ቦታዎች ነገርኳቸው።
ከዚያ በኋላ ወደ ማረፊያ ክፍል ላኩኝ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ደግሞ መልሰው ጠሩኝ።
“ያገኘንሽ እኛ ነን። ከተለቀቅሽበት ቦታ ጀምሮ እየተከታተልንሽ ነበር። ሐዋሳ እስከምትገቢ የጠበቅነው ሌላ ግርግር ላለመፍጠር ነው” አሉኝ። እኔ ወደ ሐዋሳ ስመጣ እነሱ ካሳፈሩን በተጨማሪ በራሴ ሁለት መናኸሪያዎችን አቋርጫለሁ። ጉዞ የጀመርኩት መኪና እስኪሞላ እየጠበቅኩ ነበር።
የመጀመሪያው መናኸሪያ ላይ “ግርግር ላለመፍጠር ነው” ተብሎ ከታሰበ ቀጣዮቹ ሁለቱ መናኸሪያዎች ላይ ራሳቸው ፖሊሶች ይዘውኝ ሊመጡ ይችሉ ነበር።
ኃላፊዎቹ ይህንን ብለውኝ ወደ ማረፊያ ክፍሉ ተመለስኩ። ትንሽ ቆይቶ ወንድሜ ዜና ሲሰማ “በተቀናጀ ኦፕሬሽን እሷን ይዘናት እርሱ ጫካ ገባ” ይላል። እኔ የወጣሁት ግን ተሸኝቼ ነበር።
ቆይቶ ወደ ሆስፒታል ተወስጄ ምርመራ ተደረገልኝ። ምርመራው ሲያበቃ አብረውኝ የነበሩትን የፖሊስ አባላትን ወደ ቤቴ ለመሄድ እንዲለቁኝ ብጠይቅም ምላሻቸው እንደጠበቅሁት አልነበረም። ቃል መስጠት እንዳለብኝ ነግረው ወደ ጣቢያው መለሱኝ። ፍራሽ የተነጠፈባት አንዲት ቢሮ መሰል ክፍል ውስጥ አስገቡኝ።
ደጅ ላይ ወንድ እና ሴት ጥበቃዎች በተደረገበት በዚያ ክፍል ውስጥ ለአራት ቀናት ቆየሁ። ከክፍሉ መውጣት አልችልም ነበር። መጸዳጃ ቤት የምሄደው በፖሊሶች ታጅቤ ነው። ወደ ክፍሉ የሚገቡ ሰዎችን የሚፈቅዱ እና የሚከለክሉት ፖሊሶች ናቸው።
በራሴ ፍቃድ እዚያ ክፍል ውስጥ ያደርኩት በአራተኛው ዕለት ብቻ ነበር። በዕለቱም ያደርኩት ከቀኑ አስር ሰዓት እንድወጣ ሲነገረኝ ወደ ቤተሰቦቼ ቤት የምመለስበት ትራንስፖርት ባለማግኘቴ ብቻ ነበር።
ጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር የፈጸመብኝ ዋና ሳጅን የኋላመብራት ወልደማርያም በቁጥጥር ስር የዋለው እኔ ከተለቀቅኩ ከአምስት ቀናት በኋላ ነበር። ከሰባት ወራት በኋላ ደግሞ የሐዋሳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶች እና ሕጻናት ችሎት በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወሰነ።
የፎቶው ባለመብት, Sidaama Bureau of Justice
የምስሉ መግለጫ, የሐዋሳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሴቶች እና ሕጻናት ችሎት በተከሳሽ ዋና ሳጅን የኋላመብራት ወልደማርያም ላይ የ16 ዓመት የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈው ታኅሳስ 2016 ዓ.ም. ነበር
ቅጣቱ ከተላለፈ ከሦስት ወራት በኋላ የፍርድ ቤት ሰነዶችን ለማግኘት በምጠይቅበት ጊዜ ግን በማላውቀው ሁኔታ የተሰጠው ፍርድ መሻሻሉን ሰማሁ። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው የ16 ዓመት ፍርድ፤ በይግባኝ ወደ አስር ዓመት ተቀንሷል። ይህ ውሳኔ መቼ እና እንዴት እንደተሻሻለ አላወቅኩም። ይህ ውሳኔ ሲተላለፍ ያሳወቀኝ ዐቃቤ ሕግም አልነበረም።
የመጀመሪያውን ውሳኔ የተቀበልኩት “የሕግ ባለሙያዎች መሄድ ያለባቸውን ርቀት ተጉዘዋል” ብዬ በማሰብ ነበር። በሕግ ቋንቋ “ተመጣጣኝ ቅጣት” የሚል አገላለጽ ቢኖርም፤ በየትኛውም ሁኔታ ለተጠቂዋ ተመጣጣኝ የሚሆን ቅጣት ይኖራል ብዬ አላስብም።
ብዙ ሰው የሚያስተውለው በዚያች ደቂቃ በመደፈር ውስጥ ያለውን ስቃይ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ ያለውን ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የማያስተውሉ ብዙዎች ናቸው። መደፈር የዚያች ደቂቃ ጉዳይ ብቻ የሚሆነው ምናልባት ለአጥቂው ነው። ለተጠቂዋ ግን እድሜ ልኳን የሚከተላት ህመም ነው።
በሥነ ልቦናዊ ጉዳት በጣም ተሰቃይቻለሁ። እስካሁን ድረስ ህክምና እከታተላለሁ።
የተጋፈጥኩት የእነዚያ የዘጠኝ ቀናት ስቃይ ብቻ አይደለም። እነዚያ ቀናት ምናልባትም ወደፊትም ጭምር ሕይወቴን የሚጎዳ ጠባሳ ትተውብኛል። የደረሰብኝ ጥቃት ማኅበራዊ ግንኙነቴን፣ መንፈሳዊ ሕይወቴን፣ ለራሴ ያለኝን አመለካከት ጭምር ጎድቶብኛል።
ነጻ እንደወጣሁ ቀጥታ ወደ ሥነ ልቦና ህክምና ነበር ያመራሁት። በዚያ ፍጥነት ህክምና አግኝቼ እንኳ እስከ አሁን የምሰቃይባቸው፣ በጣም ብዙ ቀኖቼን በለቅሶ እንዳሳልፍ ያስገደዱኝ ህመሞች አሉኝ።
ቤተሰቦቼ በእኔ ጉዳይ ከመጠን በላይ ተጨንቀው ስለነበር እነሱ ላይ ሌላ ጭንቀት እንዳልሆን፤ ተደብቄ ብዙ ከባድ ቀናትን አሳልፌያለሁ። ከጥቃቱ በፊት የነበረችውን ፀጋ መልሶ ማግኘት ቀርቶ፤ ትንሽ ጠንከር ያለችውን ፀጋ ለማግኘት ታግያለሁ።
ይህንን ሁሉ እያሳለፍኩ ባለሁበት ምንም ሳይነገረኝ የመጀመሪያው ውሳኔ በመቀየሩ እርዳታ ፍለጋ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ወጣሁ። ፍትህ መዛባቱን እንዲሁም ከዚያም በፊት ታስሬ እንደነበር ጠቅሼ ቲክ ቶክ ላይ ቪድዮ ለቀቅኩ። የእኔ ጉዳይ በድጋሚ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትኩረት ሳበ።
የለቀቅኩት ቪድዮ ግን በሐዋሳ ከተማ ፖሊስ ዘንድ በመልካም አልታየም። የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ “የከተማውን ስም እያጠፋሽ ነው። ከድርጊትሽ ተቆጠቢ” የሚል መግለጫ አወጣ።
የተናገርኩት የደረሰብኝን ነው። የጠየቅሁት ስለ ተዛባብኝ ፍትህ ነው። ከዚህ ንግግሬ በኋላ ተጨማሪ ነገር ብናገር . . . ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል። በመጠበቅ፣ ቃል በመቀበል ሰበብ መልሰው ወደ እስር ሊያስገቡኝ ይችላሉ ብዬ ሰጋሁ ።
ይብዛም ይነስ በተደረገልኝ ህክምና፣ እግዚአብሔርም ረድቶኝ በተወሰነ ጥንካሬ ላይ ነኝ። ከዚህ በኋላ እንደ እኔ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ድምፅ መሆን፣ ክፍተቶችን መናገር አለብኝ።
ይህንን ሳደርግ ግን የሚከተለኝ ነገር አስቀድሞ በማስጠንቀቂያ ከተነገረኝ፣ ከዚያ በላይ ሀገር ውስጥ መቆየት አልችም ነበር። ያገኘሁትን አጋጣሚ ተጠቅሜ ከሀገር ለመውጣት ተገደድኩ።
ከሀገር ከወጣሁ ግንኙነት የፈጠርኩት ከዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋር ነበር። በእነርሱም አማካኝነት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከለላ ፕሮግራም ውስጥ ታቅፌ ሥልጠናዎችን እየወሰድኩ እና ድጋፍ እያገኘሁ ነው።
ከባዱን ጊዜ አልፌያለሁ። ጉዳቴ ጨርሶ ባይሽርም በተደረገልኝ እገዛ ቢያንስ አሁን እዚህ ቆሜያለሁ። ከዚህ በኋላ ግን ለብዙ ሺህዎች ድምፅ እሆናለሁ። የመሰበር ምልክት መሆን አልፈልግም። አልፌ አሳያለሁ። እጠነክራለሁ። በጥቃት ውስጥ ላለፉ እና ለሚያልፉ ሴቶች የጥንካሬ ምሳሌ እሆናለሁ።
ሴት ልጅ ከተደፈረች በኋላ “ዋጋዋ እንደበፊቱ አይደለም” ተብሎ ይታሰባል። ተፈትኖ የወጣ ወርቅ ግን ምን ያህል ውድ እንደሆነ ማሳየት አለብን።
በሌላ አቅጣጫ ሳይሆን በራሱ በሰበረኝ ነገር ላይ እጠነክራለሁ። እኔን የሰበረኝ መደፈር ነው። እኔን የሰበረኝ ፆታዊ ጥቃት ነው። በዚሁ እኔን በመታኝ ነገር ላይ ለብዙዎች መፍትሔ እሆናለሁ።
ለየትኛውም ፆታዊ ጥቃት “እምቢ” በማለት ውስጥ ያለው ማሸነፍ የሚታይበት ሕይወት እቀጥላለሁ ብዬ አስባለሁ። የደረሰብኝን ነገር፣ ያለፉኩበትን ሁኔታ የሚያሳይም መፅሀፍ እያዘጋጀን ነው።
ከዚህ በፊት በነበሩ ጠለፋዎች፣ ፆታዊ ጥቃቶች ላይ ተገቢው ቅጣት ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ በእኔ ላይ የደረሰው አይፈጸምም ነበር። እነዚህ የሕግ ክፍተቶች ለእኔ ጥቃት ምክንያት ሆነዋል።
ከዚህ በኋላ እነዚህን ክፍተቶች ለመቅረፍ ለሴቶች መብት እሟገታለሁ። በአሁኑ ሰዓት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ለመሆን የሚያስችሉኝን ሥልጠናዎች እየወሰድኩ ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትን ለራሴ በመቆም ጀምሬያለሁ። ከዚህ በኋላ ፍላጎቴ፤ በእኔ የደረሰው ነገር በሌሎች ኢትዮጵያውያን ሴት እህቶቼ ላይ እንዳይደርስ መሟገት ነው።
* ፀጋ በላቸው ከጠለፋ የወጣችበትን መንገድ በተመለከተ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበለት የሲዳማ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል። የቢሮው ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ፤ በወቅቱ ድርጊቱ ጋር የተያያዙ መረጃዎች መስጠታቸውን አስታውሰው፤ “በድጋሚ የምንሰጠው ማብራሪያ የለም” ብለዋል።»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ