«በሕገወጥ መንገድ ኃላፊነት ላይ አካላት የሚያስተዳድሩት ሀብት አይኖርም ተብሏል» «ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ክልል ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ርቀው እንደሚገኙ በሪፖርት ተገለጸ»
https://www.ethiopianreporter.com/135505/
- «በሕገወጥ መንገድ ኃላፊነት ላይ አካላት የሚያስተዳድሩት ሀብት አይኖርም ተብሏል»
« የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ሐሙስ ኅዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ ያካሄደው ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመሩት ሕወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራዎች ከማደናቀፍ አልፎ ግልጽ በሆነ መንገድ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱን በመቀጠሉ የፀጥታ ኃይሉ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠየቀ፡፡
ቡድኑ ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት ተሸጋግሯል በማለት የገለጸው የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤቱ፣ ‹‹በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ መንግሥታዊ መዋቅሮች ላይ ሕገወጥ ምደባዎችን በማካሄድና ጫና በመፍጠር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራዎች በማደናቀፍ ላይ ተጠምዷል፤›› ብሏል፡፡
ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ መንግሥታዊ ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሕዝቡን ለማስተዳደር ወንበሩን የተቆናጠጡ አካላት፣ የሚያስተዳድሩት ሕዝብም ሆነ ሀብት እንደማይኖርም ነው ጽሕፈት ቤቱ ያስታወቀው፡፡
ሁኔታው ተባብሶ በመቀጠሉ ምክንያት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ መሰል ሥርዓቱ አልበኝነት ከአቅሙ በላይ በመሆኑ የትግራይ ፀጥታ ኃይል፣ የፍትሕ አካላትና ባንኮች እየታየ ያለውን ሕገ መንግሥቱን የጣሰ አካሄድ ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ሕወሓት ከሁለት ወራት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚደረገውን ሹም ሽር በተደጋጋሚ ሲቃወም ቆይቷል፡፡ በታችኛው መዋቅር የሚገኙ ምክር ቤቶች ስብሰባ በማካሄድ አዳዲስ ምደባዎችን እንደማይቀበልና አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በካቢኔያቸው ውስጥ ያሉት አምስት ሰዎች በድርጅቱ መባረራቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ጽሕፈት ቤት ግን ‹‹በግላጭ መፈንቅለ መንግሥት እየተካሄደብኝ ነው፤›› በማለት በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው መግለጫዎች እየገለጸ ነው፡፡
የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት በማከልም፣ በእያንዳንዱ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መዋቅር ውስጥ የሚገኙና በክልሉ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላትና ተቋማት፣ የፌደራል መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሚመራው ሕወሓት በሕገወጥ መንገድ ተመድበው እየተንቀሳቀሱ ያሉት አካላት፣ መንግሥታዊ ኃላፊነት ይዘው በየትኛውም መድረክ ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ በመገንዘብ ፈቃድ ሊሰጡ እንደማይገባ አሳስቧል፡፡
በክልሉ ባሉ የሃይማኖት አባቶች አሸማጋይነት በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እና በአቶ ጌታቸው በሚመሩት ቡድኖች መካከል ውይይት ተደርጎ ዕርቅ ይወርዳል የሚል ተስፋ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም፣ በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ኅዳር 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት እየተካሄደብኝ ነው፤›› ብሎ ነበር፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህንን ያለው ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. የድርጅቱ ሌላኛው ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተወያይቶ፣ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና በሕዝቡ ላይ የተጋረጡ በግልጽ የሚታዩ ሥጋቶች ዙሪያ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የተመለከተ አጭር መግለጫ ባወጣ ጥቂት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
ስምምነት ተደርጎበታል የተባለውን ውይይት በተመለከተ ከሕወሓት በኩል ዝርዝር መረጃ አልወጣም፡፡ የፀጥታ ኃይሉም ውይይት ስለመደረጉም ሆነ ስምምነት ላይ ተደርሶባቸዋል ስለተባሉት ጉዳዮች ያለው ነገር የለም፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በአራት ቀናት ልዩነት ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ቢያወጣም፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሚመራው ሕወሓት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
ሪፖርተርም ከድርጅቱ ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም፡፡»
https://www.ethiopianreporter.com/135464/
«ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ክልል ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ርቀው እንደሚገኙ በሪፖርት ተገለጸ»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ