‹‹የም የፈውስ ምድር›› ይሉታል፡፡ ይህን ስያሜ ያገኘውም በርካታ ባህላዊ መድኃኒቶች ስለሚገኙበት እንደሆነ ይወሳል፡፡ Reporter.
‹‹የም የፈውስ ምድር›› ይሉታል፡፡ ይህን ስያሜ ያገኘውም በርካታ ባህላዊ መድኃኒቶች ስለሚገኙበት እንደሆነ ይወሳል፡፡
https://www.ethiopianreporter.com/135050/
"በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየም ዞን ውስጥ የሚገኘው ቦር ተራራ ዋነኛው የመድኃኒት ምንጭ በመሆኑ የየም ብሔረሰብ በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን ባህላዊ የመድኃኒት ለቀማ ያካሂዳል፡፡ ‹‹ሳሜታ›› ብለው የሚጠሩትን ሥርዓት ከአዋቂ እስከ ሕፃን ይሳተፉበታል፡፡"
"ዘንድሮም ይኸው የለቀማ ሥርዓት በዕለተ ቀኑ የተከናወነው፣ በየም ልዩ ወረዳ ፎፋ ከተማ በሚገኘውና የቦር ተራራ መሆኑን ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡"
‹‹በየዓመቱ ጥቅምት 17 በየም ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ቀን ነው፡፡ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ልዩ ግምት የሚሰጥበት ምክንያት ለጤና ጠንቅ የሆነውን በሽታ ለመከላከልና ለማስወገድ ሲባል በባህላዊ መንገድ ጤንነትን የመጠበቅ ዘዴ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በመሆኑ የባህላዊ መድኃኒት ለቀማው፣ ቅመማውና ሕክምናው በስፋት በብሔረሰቡ ውስጥ ሠርፆ የቆየ አገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡››
ይህን ትውፊታዊ ሥርዓት የገለጸው ‹ቪዚት የም› የተሰኘው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው፡፡ በመጣጥፉ እንደተገለጸው፣ በዞኑ ውስጥ የባህል መድኃኒት ከዕፀዋት (ቅጠላ ቅጠሎች፣ ስራስሮች፣ ቅርፊቶችና ከመሳሰሉት) ለቀማ የሚደረግበትና የተለቀመው ወደ መኖሪያ ሰፈር (ቤት) ተወስዶ ለሰውና ለቤት እንስሳት የሚሆን መድኃኒት ተለይቶ ይቀመማል፡፡ የተቀመመው መድኃኒት በንፁህ ዕቃ ተቀምጦ እስከ መጪው ዓመት ድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ ሒደት በብሔረሰቡ ቋንቋ አጠራር ‹‹ሳሞ ኤታ›› ተብሎ ይጠራል፡፡
‹‹በዕለቱ የመድኃኒት ለቀማው ሥርዓት በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄድ ቢሆንም በዋናነት የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የዕድሜ ወዘተ…ልዩነት ሳይኖር ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቦር ተራራ በመውጣት ይለቅማሉ፡፡ በቦታው ያሉ ከ‹‹ሱሉቶ››እና ከ‹‹ቶቱ›› ከሚባሉት የዕፀዋት ዓይነቶች በስተቀር ሁሉም ይለቀማል፡፡ እነዚህ የማይለቀሙትም ቢሆኑ ለጊዜው ጥናት ስላልተደረጉ እንጂ ለመድኃኒትነት አገልግሎት ባይውሉም መርዛማነት ያላቸው በመሆኑ ለሌሎች ለፀረ ተባይ ማጥፊያና ለሌሎች አገልግሎቶች መዋል የሚችሉ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡
‹‹በየዓመቱ የሚለቀምበት ቦታ (ቦር ተራራ) የተመረጠበት ምክንያት ተራራው በዞኑ የመሬት አቀማመጥ ከፍታው ከባህር ወለል በላይ 2939 ሜትር ያለው ሲሆን የመጀመሪያውን የማለዳ የፀሐይ ብርሃን ቀድሞ የሚያገኝ በመሆኑ በዚሁ አካባቢ የሚፀድቁ ዕፀዋት በሽታን የመከላከልና የፈዋሽነት አቅም ከፍተኛ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡
‹‹በየም ዞን በቦር የፈውስ ተራራ በየዓመቱ ጥቅምት 17 የሚከናወነው ለሰውና ለእንስሳት ሕመም መድኃኒት የሚሆኑ ዕፀዋት ለቀማ – ሳሞኤታ- የአገር በቀል ዕውቀት ዕሴት ነው። አሁን በዘመናዊ ምርምር ተጠንቶና ለምቶ በየፋርማሲው የሚገኝበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤›› በማለት በመድኃኒት ለቀማው ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንደሻው ጣሰው መናገራቸውን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን መሥርያ ቤት ገልጿል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ደኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የጤና ፖሊሲው የአገር በቀል ዕውቀቶች ልዩ ትኩረት እንደሰጠ ጠቁመው፣ ስድስት የባህላዊ መድኃቶች ወደ ክሊኒካል ሊገቡ ሒደት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም በሳሜታ ሥነ ሥርዓት ላይ የታደመው ሔኖክ ሥዩም በድረ ገጹ የዓይን እማኝነቱን የገለጸው፣ የባህላዊ መድኃኒት ለቀማ ትውፊቱ ከአባቶች ወደ ልጆች መተላለፉን በክብር በማመልከት ነው፡-
‹‹የዓመት የመድኃኒት አስቤዛ ዛሬ ነው የሚሰበስበው፡፡ የም በዕፀዋት ጥበብ አስቀድሞ በሽታን ይከላከላል፡፡ ቀጥሎም ሕመምን ያስወግዳል፡፡ ፈውስን ከምድር ገጸ በረከት የሚያገኝ ጥበበኛ ሕዝብ ነው፡፡…ሕፃናት ልጆች፣ ወጣቶች ከተራራው፣ ከገደሉ ላይ ተንጠልጥለው መድኃኒት ይለቅማሉ፡፡ አዲሱ ትውልድ በአባቶቹ መንገድ እየሄደ ነው፡፡ ከዚህ ዕፅ አንዱ ምናለ ሀገሬን በፈወሳት ስል ተመኘሁ!!››
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ