"በኢትዮጵያ በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ" ሲሳይ ሳህሉ ቀን: July 7, 2024

 

 
 "በኢትዮጵያ በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ"
ሲሳይ ሳህሉ

ቀን:
July 7, 2024

"በኢትዮጵያ በሚከናወኑ የትጥቅ ግጭቶች፣ ጥቃቶች ወይም የፀጥታ መደፍረሶች ምክንያት፣ በታጣቂ ኃይሎችና በመንግሥት የፀጥታ አካት በተወሰዱ ዕርምጃዎች፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ የሞትና የአካል ጉዳት አሳሳቢነት ቀጥሏል ሲል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡ በሕይወት የመኖር መብት ማሳሰቡንም ገልጿል፡፡
 
ኮሚሽኑ ከሰኔ 2015 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም. የሚሸፍነውን 3ኛው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አያያዝ የሚያብራራ ባለ132 ገጽ ሪፖርት ዓርብ ሰኔ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለጸው በትጥቅ ግጭት ወቅት፣ በግጭት ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎች ግጭት በሌለበት ወቅት ጭምር የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎችም አሳሳቢ ሆነው ቀጥለዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) [የሥራ ጊዜያቸው አልቆ ተሰናብተዋል]፣ ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለና የዘርፉ ኮሚሽነሮች በተገኙበት ለሚዲያ ይፋ ቀርቧል፡፡
 
ዋና ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ ዓመታዊ ሪፖርቱን በመደበኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ እንዲቀርብ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ፓርላማው የተደራረቡ ጉዳዮች የገጠሙት በመሆኑ ሪፖርቱን ለማቅረብ አለመቻሉንና ነገር ግን ለሚመለከታቸው አካላት በጽሑፍ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡
 
በሪፖርቱ የመንቀሳቀስ መብት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር ወይም በሌላ ምክንያት በሚጣሉ ገደቦች፣ በተለይም በመንገድ የሚደረግን እንቅስቃሴ አዳጋች ማድረጉ ተገልጿል፡፡
 
በአማራ ክልል በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች (የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልልና የፌዴራል ፖሊስ፣ እንዲሁም የአካባቢ ሚሊሻዎች) እና በተለምዶ ‹‹ፋኖ›› ተብሎ በሚታወቁ የታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው የትጥቅ ግጭት፣ በክልሉ ሁሉም ዞኖች መስፋፋቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
 
በተኩስ ልውውጥ ወቅት የመለየትን፣ የጥብቅ አስፈላገኒነትንና የተመጣጣኝነት መርሆችን ባልጠበቁ የከባድ መሣሪያ ድብደባዎች (Heavy Artilery Shelling) እና በአየር ድብደባዎች (በአብዛኛው በሰው አልባ በራሪዎች ወይም ድሮን) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች (ሴቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ሕፃናትን ጨምሮ) በአሰቃቂ ሁኔታ መገዳላቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
 
በአማራ ክልል በየኬላው በመንግሥት የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም በፋኖ ታጣቂ ኃይሎች አስገዳጅ ፍተሻ የሚደረግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በመንገድ ላይ ድንገት የተኩስ ልውውጥ ሊያጋጥም እንደሚችል፣ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ማኅበረሰብ እጅግ አስገዳጅ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር በመንገድ የሚጓዙ የትራንስፖርት አማራጮችን እንደማይመርጥ ሪፖርቱ ያስረዳል።
 
በሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የዘፈቀደ እስር፣ የጅምላ እስር ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ባለማክበር ሰዎችን ይዞ የማቆየት፣ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ሰዎችን የመያዝ ድርጊቶች መፈጸማቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
 
በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ቀርበው የዋስትና መብታቸው የተከበረላቸው ሰዎች ‹‹በኮማንድ ፖስት ይፈለጋል፣ የበላይ ትዕዛዝ ይምጣ›› በሚል ሳይፈቱ ለረዥም ጊዜ በእስር ቆይተው እንደነበሩ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ውጪ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ‹‹በወቅታዊ ጉዳይ ነው›› በሚል ለረዥም ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቆየታቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
 
በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ ዓውድ ያለ ኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ በገላን ከተማ፣ በገላን አዋሽ ሲዳ ተብሎ በሚጠራው መደበኛ ያልሆነ ማቆያ ቦታ ተይዘው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ፣ በወቅቱ በነበረው የተጨናነቀና የንፅህና ደረጃውን ባልጠበቀ የተጠርጣሪዎች አያያዝ ምክንያት በተከሰተ ወረርሽኝ፣ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ 190 ሰዎች ለሕመም ተዳርገው ሕክምና ማግኘታቸው ተጠቅሷል፡፡
በትጥቅ ግጭቱ ሳቢያ በአማራ ክልል የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ፣ ነዳጅ በጥቁር ገበያ የሚሸጥ መሆኑንና የትራንስፖርት ክፍያ በጣም እንዲንርና በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዲፈጠር ማድረጉም ተብራርቷል፡፡
 
ከነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ወራት በአማራ ክልል እንደ አስፈላጊነቱ በሌሎች አካባቢዎች ሲተገበር በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ውጪ በጣም በርካታ ሰዎች መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ለቀናት፣ ለሳምንታትና ለወራት ያህል ታስረው እንደነበር ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
 
በኦሮሚያ ክልል ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ፣ ‹ወቅታዊ ጉዳይ› በሚል ምክንያት ሰዎችን በተለይም የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ማሰር፣ በክልሉ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ቡድንን ትረዳላችሁ በሚል ሰዎችን በጅምላ ማሰር፣ እንዲሁም የመንቀሳቀስ መብታችውን ማገድ መፈጸሙ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመንግሥታቸውን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ከዋናው ግንዱ ወጥቶ የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆነ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡
 
‹‹በመሆኑም የሰብዓዊ መብት የሚባል አዋጅ፣ ተቋም፣ አሠራር መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ደመወዝ የማንከፍለው ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያደርግ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል ለእናንተ መተው ነው፤›› ብለዋል፡፡
 
‹‹እኔ በየትም ቦታ ያሉ የሰብዓዊ መብት የሚባሉ ሐሳቦችንና ተቋማትን የማያቸው ልክ እንደ መርፌ ነው፣ መርፌ የራሱን ቀዳዳ መስፋት አይችልም፡፡ እነዚህም የራሳቸውን ድክመት ማየት አይችሉም፡፡ ይህ ጥሩ አይደለም፣ አገር ያፈርሳል፡፡ ተቋማቱን ማፅዳት አለብን፤›› ብለው ነበር፡፡
 
ይህንን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር፣ ሰብዓዊ መብት ላይ በሚሠሩ ድርጅቶችና በመንግሥት በጀት የማይተዳደሩ ተቋማት ላይ መሰል ትችት መስማት የተለመደ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ሥራ ዓለም አቀፋዊ ፀባይ ያለው በመሆኑና ከተለያዩ አገሮች ሀብት እያሰባሰቡ ሥራቸውን የሚያከናውኑ በመሆናቸው፣ ከውጭ አገሮች ሀብት በሚያሰባስቡበት ወቅት ከመንግሥታት ትችት መስማት አዲስ አለመሆኑንና የተለመደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
 
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ኢሰመኮም ከመንግሥት የሚመደብለት በጀት ሥራውን ለማከናወን በቂ ባለመሆኑ፣ እንደ ማንኛውም የመንግሥት ተቋምና ድርጅቶች ከአጋር አካላት ሀብት ማሰባሰብ በአዋጅ ተፈቅዶለታል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ ከማንም አካል ተፅዕኖ ደርሶበት እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡
 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመተግበሪያ ጊዜ ያበቃ ቢሆንም፣ ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ እስርና በነፃነት የመዘዋወር መብትን የሚገድቡ ድርጊቶች አሁንም መኖራቸውንና አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸውን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል ገልጸው፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ የዘፈቀደና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የሚከናወኑ እስሮች ላይ አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
 
አገሪቱ በጦርነት ዓውድ ውስጥ በመሆኗ ምክንያት የሲቪክ፣ የሚዲያ ምኅዳርና የፖለቲካ ተቃውሞ አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙ ቢሆንም፣ እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁሞ መሄድ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን ማረጋገጥና መብቶች መከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ መብት ጥሰት ላይ ተጠያቂነት እየተወሰደ ቢሆንም ተጠያቂነቱ በቂ ባለመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂነት ያለባቸው ሰዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
 
ኢሰመኮን በዋና ኮሚሽነርነት ከሰኔ 2011 ጀምሮ ሲመሩት የቆዩት ዳንኤል (ዶ/ር) የአምስት ዓመታት ሥራ ጊዘያቸው ተጠናቆ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ መሰናበታቸው ተገልጿል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ የመጨረሻ የስንብት ቃላቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡ ለሁለተኛ ዙር ኮሚሽነርነት የመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ የአዲስ ዋና ኮሚሽነር ዕጩ ምልመላ ተካሂዶ በምክር ቤቱ እስኪሾም ድረስ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ ተተክተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡"
 
 
በኢትዮጵያ በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ - ሪፖርተር - Ethiopian Reporter - #1 Best And Reliable News Source In Ethiopiaበኢትዮጵያ በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ - ሪፖርተር - Ethiopian Reporter - #1 Best And Reliable News Source In Ethiopia

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።