ፕ/ ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ።
ብሩክ ቀን – ሥርጉተ ሥላሴ
„ … እኔ ግን እግዚአብሄርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሄር አቀርብ ነበር።
ዬማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቋረጠውን ተአምራት ያደርጋል። …“
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፭ ከቁጥር ፰ እስከ ፱)
(መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፭ ከቁጥር ፰ እስከ ፱)
ይድረስ ለኢትዮጲያኒዝም አባት እና የአብሮነት ሐዋርያ ለሆኑት ሊቀ – ሊቃውንት ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶለሳ – ባሉበት።
ሊቀ – ሊቃውንት ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶለሳ እንደምን ሰነበቱልን፤ እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። „የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ“ በዚህ በአዲሱ መጸሐፍዎት ዙሪያ ከኢትዮዽያ ኃብታት ከሆኑት ሁለት ሊቀ – ሊቃናት ጋር ያደረጉትን ክርክር ግራ ቀኙን – ታደሜበታለሁ። ከሥር ዬሚታከሉ ዬአንባብያንን አስተያዬትንም በማከል ነበር – ዕድምታዬ። መጸሐፋን ባነበው ዬበለጠ ሊረዳኝ ይችል ዬነበረው በመጽሐፋ ውስጠት ዬግሌን ዕይታ በመንፈስ ሊያጎለብትልኝ ቢችልም፤ አደባባይ ወጥቼ ዬሃያሳን ሊቃናትን ዬሙያ ድርሻ መጋፋት ተገቢ አለመሆኑን ስለማምንበት፤እምለው አይኖረኝም ነበር። ስለዚህም ዛሬ ልጽፍ ላነሳሳኝ ጭብጥ „የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ“ መጸሐፍ አለማንበቤ ዬሚያጎድለውም ሆነ ዬሚሞላው ምንም አይነት አመክንዮ አይኖረውም።
- ጠብታ።
ውስጤን ለውስጤ ሳላውሰው፦
ውስጤን ለውስጤ ስሸልመው፦
ህሊናው ገራኝ በጽናት፦
ዬምቱ ልብ፥ ርትኃዊ ባዕት።
ውስጤን ለውስጤ ሳላበድረው፦
ውስጤን ለውስጤ ሳስረከብው፦
ዬችሎቱ ፍትኃዊነት፥ ጉልተ – ሥህናት፤
ስለ-የእኔነት ህትምተ – ሆኼያት።
ውስጤን ለውስጤ ሳልነፍገው፦
ውስጤን ለውስጤ ሳቀናው፦
ማህጸነ – ተቃና፤ ኆኽተ ብርኃናት፤
ዬቅኔ ዓይን መስታውት፥
ዬእንቢልታ አንጎል ህብረታት፤
ህላዊነት- „ለአብረንታት“!
- እፍታ።
ዬዕለቱ ዬምልከታዬ ሟተት ውድ ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ ክፍል አንድና ሁለት መልስ ከሰጡበት መሰረታዊ ዬሃሳብ ቋት፤ ሁለገብ መንፈስ፤ አጠቃላይ ዕይታ ይነሳል። ውድ ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ ዬመልሰዎት አንኳራት ኢትዮዽያዊነት በውስጠዎት ያለውን ዬክብር ልቅና በሚገባ አስገነዘበኝ፤ በተመስጦው አብራራልኝ። ኢትዮዽያዊነት ማለት ለክቡርነቶዎት ምን ማለት እንደሆነ አሳምሮ – ተረጎመልኝ። እርስዎ ለትናንት፣ ለዛሬ፣ ለነገም ዬወርቅ ድልድይ መሆነዎትን – አዬሁበት። እርስዎ ዬብሩክ ቀን ስጦታችን ነዎት። እርስዎ ራስወት በአውንታዊነት ናሙናነት – ብሩክ ቀናችንም ነዎት። በኢትዮዽያዊነት ፍልቅ ማንነት ውስጥ ቅንነተዎትን፣ ቀናነትዎትን፣ ግልጽነትዎትን፣ ቀጥተኛነትዎትን፣ ታማኝነትዎት፣ ለብሩክ ቀናት መሃንዲስነትዎትን አገናዝቤበታለሁ። ስለሆነም እርስዎ ዬእኛ በመሆነዎት ትምክህት ባይገባም፤ እግዚአብሄርን አመስግኘበታለሁ። ለትውልዱ በመሆን ዬከበረ፤ በውስጥነት ዬጸደቀ፤ በቃል ኪዳን ዬቆረበ ዬዜግነት ምሳሌ መሆነዎት ዝክረ መጸሐፍ ነው። ማለፊያ!
ጥገኛ ዬሆነ መንፈስን በመጸዬፍ፤ ዬራስ መተማመንን በጸና ዬማንነት ትንፋሽ ማጽናት፤ ራስነት በዕንቁነት ማማከል ሲታደሉት ብቻ ዬሚገኝ ሰማያዊ መክሊት ነው። በተባረከ ማዕልት አዳኝ መንፈስ ይፈጠራል። ባልተባረከው ቀን ደግሞ በታኝና ገዳይ መንፈስ ይፈጠራል። ዬፍቅራዊነት አባት አቦ በቀለ ገርባ „ዓለም በጎውን አትናገርም። ዬዓለም ዜና ሁልጊዜም ክፋውን ነው። ባልና ሚስት ተስማምተው በማደራቸው ዬዓለም ማህበረሰብ በትውልድ ተገነባ፤ ታነጸ፣ ትውልድም ቀጠለ ይህን በጎ ዕሴት ዓለም አትዘገብም። ዓለም ዜና አድርጋ ዬምትነግረን ትዳሩ ሲፈርስ ነው።“ እንዳሉት ነው። ከዚህ ፍልሥፍና በላይ ዬሚገልጥ በውነቱ ዬለኝም። „ሥምን መላዕክ ያወጣዋል“እንዲሉ ሰብዕናዎት – ይመስጣል። ወሸኔ!
- ማዕዶት።
ኢትዮዽያዊነት ሲኖሩበት ዕውነትነቱ – ይታያል፤ በኢትዮጲያዊነት ውስጥ ጋር በአልፎ ሄጅነት ሳይሆን፤ ሲበቅሉበት ኢትዮዽያዊነት በርካታ ትሩፋትን – ያላብሳል። ኢትዮዽያዊነት „ገና ያልተሰራ¡“ ሳይሆን ሌላውንም ዬሠራ ስለመሆኑ ሚስጢር – ይገልጣል። ኢትዮዽያዊነት ጌጥነቱ ሲፈቅዱት ብቻ ውበቱ – ያፈካል። ኢትዮዽያዊነት ሲቀበሉት ብቻ ውስጥን – ያበራል። ኢትዮዽያዊነት ሲያደምጡት ብቻ ጥልቅነቱን ማስተዋል ይቻልበታል። ኢትዮዽያዊነት ካልሸነገሉት ብቻ ዬዕድምታ ሊቃውንት ያደርጋል። አቨው ሊቃውንት ዘመናትን ሲቀምሩ ከሺህ ዓመት በኋላ መስከረም ፩ መቼ ቀን ሊሆን እንደሚችል በሰማያዊ ጥበባቸው – ይቃኙበታል። ዛሬ ዓለም ደርሰናል ላለው ዬህዋ ስልጣኔ ቀደምቶቹ የእኛዎቹ ቀመሩን ተጠብበወበታል።
ዬኢትዮዽያዊነት ረቂቅ መንፈስ ገኃዱን ዓለምን እና መንፈሳዊ ዓለም በመስተጋብር ዬተደመመ ዬአመክንዮ አናት ነው። ጣዕሙን ለማጣጣም እስካልፈቀዱ ድረስ ዬሚላስ ዬሚቀመስ ቃናዊ ግንዛቤ አይኖርም። አንዲት እናት ጽንስ በሆዷ ማደሩን ቀድማ ዬምታውቀው እሷ ብቻ ናት። ቋንቋ አልቦሽ ስሜቱ ዬምሥራቹን ከማንም ቀድሞ ያበሥራታል። ዬእርግዝና ወራቷን ልዩ ዬሚያደርገውም ዬጽንሱ እና ዬእሷ ግንኙነት ውስጣዊ ዕውነትነቱ ዬትውስት፤ ወይንም ዬቅጂ ሳይሆን እሷ ዬበላችውን፤ ዬጠጣችውን፤ ዬተነፈሰችውን – ያለችበትን ህይወት በረቀቀ ሰማያዊ ታምር ዬግንኙነቱን መስመር ዘርግቶ ወጥ ስሜት ዬፈጠረላት – ያ ሃዲዱ ነው ዕውቅና ዬሰጠችበትን አመክንዮ ርቁቅ ሚስጢርነቱ ዬሚገልጥላት።
ዬሁለቱ ግንኙነት በእትብት ተያይዞ ዬቴሌፎን መስመሩ፤ ዬሃዲድ መንገዱ፤ ወስጣዊነት ውስጥን ከውስጥ በቃና ዘጉባኤ ይቃኘዋል – ዬተገባው የስሜት ዕውቅናው። ይህ ጥልቅ የስሜት አህዳዊነት ዬቆይታውን ጊዜ ውበት ያጣጥመዋል፣ ያዋህደዋል፣ አካል ተአምሳል ያደርገዋል። ስለሆነም ዬስሜቱ ሙቀትና መተላለፊያ መንገዱ ከፍጽምና ረቂቅነቱ ዬተነሳ በፊደላት ቅምረት በቋንቋ ለመግለጽ ይከብዳል። በጋራ ኑሮው ውስጥ ለከተሙት ለእናትና ለጽንሱ ግን ሁነቱ ረቂቅ ዕውነትነቱ ዬሚጨበጥና ዬሚዳሰስ ያደርግላቸዋል። ኢትዮዽያዊነትም እንደዚህ ነው።
ውስጥ ሲፈቀድ ዬሚገኘው ሌላው ትርፍ ዬበታችነት ስሜት ይቀበራል። ስለዚህም በራስ ዬመተማመን፣ እርግጠኛ ዬመሆን ደጎስ ያለ ባለቃና ስሜት ይፈጠራል። በራስ ዬመተማመን ስሜት እራስን አክብሮ ይነሳል። ዬራስ ዬሆኑ ነገሮች ይጠመዋል። ድንበር ዘለል ሸቀጦች ተገዢ ወይንም አምላኪ መሆንን ይጸዬፋል። ስለምን? ዬራሱ፤ ዬእኔ ዬሚለው ዬሚጨበጥ – ዬሚዳሰስ ዘመን ጠገብ ብልህ መንፈስ በእጁ ስላለው።
እንደ ኢትዮዽያ ዓይነት ዬሰው ልጆች መፈጠሪያ ሀገር ልጅነቱ በራሱ ለህልውና ዓራት ዓይናማ መንገድ ነው። በራስ የመተማመን መንፈስ ዬህይወት ሹፌር ነውና። ውድ ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ ዬአቅመዎት ምንጩ ሚስጢሩ ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይሄው ነው። ዋቢ ያደረጓቸው ሊቀ – ሊቃውንትም ለርስዎ ዬዕውቀት አባት ዘውድ ስለመሆናቸው ከልበዎት ዕውቅና በመስጠት ተቀብለዋቸዋል። ስለምን? ለምንጭዎት አስተርጓሚ ስለማይሹ። ዬበታችነት ስሜትም ስለማዬንጥወትም። ይህ ታላቅነትና ቅንነት በእርሰዎ እንዲህ ለምልሞና ዳብሮ፤ እንዲሁም አስብሎ ማዬት ለእኔ ዬሁለመና ዬአብነት ተቋምነትም ነው። ምቀኝነት ባለበት ቦታ ሁሉ በጎ ዕሳቤ ቀብር – ይውላል። ፈጣሪ አምላክ ከዚህ ስላደነዎት ከሁሉም ዬላቀውን ዬሞራል ሥጦታ ስላልነሳዎት – ዕድለኛ ነዎት።
- ቃና።
ዬማከብራችሁ ዬሀገሬ ዬልዕልት ኢትዮዽያ ልጆች … ቃናንም ሆነ ማዕዶትን በትምህርተ ጥቅስ አላስገባኋቸውም። እንዲያውም ኢትዮዽያ ቃና ዬሚባል አዲስ ዬቴሊቪዥን ፕሮግራም እንዳለ ዬሰማሁ ይመስለኛል። እ.አ.አ በ2008 በወርሃ ሐምሌ ላይ ዬጸጋዬን ድህረ ገጽ ሳደራጅ ቃና፤ ማዕዶት፤ ተስፋ፤ መክሊት፤ ዕድምታ፤ „አብረንታት“፤ ዬሎሬት ተስፋ (ለልጆች) በመምሪያ ደረጃ ዬሠራሁባቸው በመሆኑ ከ“አብረንታት“ ውጪ ሌሎችን ካለ ትምህርተ ጥቅስ መጠቀም ስለሚያስችለኝ ነው። ቀድሜ ሚዲያ ላይ ተጠቅሜበታለሁ እና ኃብትነቱን አል ሰረቅኩኝም። ተስፋን ለአዋቂዎች ለህትም ዬበቃ ዬግጥም መጸሐፌ ዕርዕስም አድርጌዋለሁ። በምድር ላይም እንደ ተስፋ የምወደው ሥምም ዬለም።
አሁን ወደ ቀደመው እንደ አቨው። ዬኢትዮዽያዊነት ቃናው „ረቂቅ መንፈስ“ ቢባል አይበዛበትም ባይ ነኝ – እኔ። ኢትዮጵያዊነት መሰረቱ ኢትዮዽያ ናት። ኢትዮዽያ አምላክ አለ፤ አምላኬን አመልከዋለሁ ብሎ ዬሚያምን ህዝብ ዬሚኖበት ሀገር ናት። ሃይማኖታዊ ዕምነት ደግሞ ረቂቅ ዬሆነ ዬመንፈስ ጸጋ ነው። መጸሐፍ ቅዱስም „ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዐን“ ናቸው በማለት አጽህኖታዊ ዕውቅና ይሰጠዋል። ረቂቅነቱን ልጨብጠው፤ ልዳስሰው ኤክስፐርመት ልስራበት፤ በላብራቶሪ ወይንም በውስጥ አንባቢ መሳሪያ ይፈተሽ፥ ይደመር፤ ይቀነስ፤ ይካፈል … ይባዛ ዬማይባልበትን ሃይማኖታዊ ዶግማ አምኖ መቀበል ማለት ነው።
በዚህ ህይወት ውስጥ መኖሩ „ፈርኃ እግዚአብሄር“ ያደረበት ህዝብ ዬሚኖርባት በዕት በመሆኗ በዓለም ዙሪያ ዬክርስትና ዕምነትና፤ ዬዕስልምና ዕምነት በሃይማኖታቸው ምክንያት ዬሚደርስባቸውን ዬማሳደድ ቀንበር ዬሚያስታግሱበት ጥላ – ከለላ፤ ዬቅዱስ መንፈሳቸው ዋሻ፤ እንደ እናት እቅፍ ድግፍ አድርጋ በክብር ሸሽጋና አቆላምጣ ዬምትይዝ እመ – ብዙኃን ናት ቅድስት ሀገር ኢትዮዽያ። ስለዚህም ስደት አቨው ሲገጥማቸው በነብያት መሪነት ለከፋቸው አማንያን ቀን ዬምታሳልፍ የራህብ መዳህኒት – ዬእናት ጓዳ ናት እመቤት ኢትዮዽያ። ለሥጋቸው ሳይሆን ለመንፈሳቸው ማደሪያ ዬተመረጠች ሃገር መሆኗ ዬረቂቅ መንፈስ ባለድርሻ ለመሆን ዬሚያግታት ምንም ምድራዊ ኃይል ዬለም። ይህ በሰውኛው ስሌት፤ በጋህዱ ዓለም ትንተና ሳይሆን፤ ውስጧን በመንፈሳዊ – በሰላማዊ ህይወት ማስተዋል – ከተቻለ። ለማገናዘቢያነት ብቻ ጥቂት ነገር ስለ „ፈርኃ እግዚአብሄር“ እና ስለ „ይሉኝታ“ ልበል። ሁለቱም ዬመንፈስ ረቂቅ ብቸኛ ዬህሊና ዬችሎት አደባባይ ስለሆኑ።
አንድ ኢትዮዽያዊ ወይንም ኢትዮዽያዊት ሰው በሌለበት፤ ማንም በማያያቸው፤ በማይታዘባቸው ቦታና ሁኔታ ሁነው እንኳን ስህተት ለመፈጸም ዬሚያስገድዳቸው ሁኔታ ቢፈጠር „እግዚአብሄር ያዬኛል“ ይላሉ፤ ይህም „ፈርኃ እግዚአብሄርነት“ ዬህሊና ዬችሎት አደባባይ ነው። ኢትዮዽያውያን ወደውም ይሁን ተገደው ህግ ተላላፊነትን ቢፈጽሙት እንኳን፤ በመንፈሳቸው ላይ ጫና ጥለው ነው። በገኃዱ ዓለምም ስንመጣ „ይሉኝታ“ አለ። ዬአረብ ዬጥበብ ሥራ በጣም ተደናቂ ሆኖ ዬሚጎድለው ነገር ስላለ ወዘና ያንሰዋል። ደረቅ ጠፍር ነገር ነው። ስለምን? የ“ይሉኝታ“ እንጥፍጣፊ ስሌለው።
„ይሉኝታ“ በህሊናችን ውስጥ ያለ ዬገሃዱ ዓለም መዳኛ ዬችሎት አደባባይ ነው። ኢትዮዽያዊነት በአልባሌ መንገድ አይኬድበትም። ዬኢትዮዽውያን ህይወት ለዛ አለው። „ምን ይሉኝ“ እንላለን። ዬጥፋተኝነት ስሜት እንዳይጠጋን እንድንሸሽ የሚያደርገን ረቂቁ ዬኢትዮዽያዊነት ንዑድ መንፈስ ነው – ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ። „ይሉኝታ“ ለዬትኛውም ዬገኃዱ ዓለም ዬህይወት ዘርፍ ህልውናችን ዬሚያጣፍጠው ዬህላዊነት ቅመም ነው። ስለዚህም ኢትዮዽውያን ለመንፈሳዊ ህይወታችን „ፈረኃ እግዚአብሄር“፤ ለጋህዱ ዓለም ህይወታችን ደግሞ „ይሉኝታ“ ሁለቱም በአዕምሯችን ላይ ዬፈረሹ፤ ዬፈቀድናቸው ዬፍርድ አደባባይ ናቸው። ኮርስ ዬማይወሰድባቸው፤ ሰሚናር ዬማናሰናዳባቸው፤ ጠበቃ ዬማንቀጥርባቸው፤ በዳኛ ፊት ዬማንቀጠቀጥባቸው፤ በሰዋዊ አቃቢ ህግ ዬማንዋከብባቸው፤ በታጠቀ ሃይል ዬማንጨፈለቅባቸው ዬራስ ዬሆነ ዬውስጣዊነትፍርድ ቤት ያለን ህዝቦች ነን። ይህ ረቂቅነት በእኩልነት በሁላችንም ዘንድ አለ። ከአፈሯ፤ ከአዬሯ፤ ከተፈጥሯ ያለ ተቀናቃኝ ዬተቸረን ብቸኛ ዬሃብት ሃብት። ይህ ዬሚስጢርን ውሎ ነው በውል ያዋዋሉልን፤ በኪዳን ያሰተሰሩልን፤ በጸና ዬፍቅር ብሄራዊነት ስሜት ያበለጸጉልን ፕሮፌሰር ዶር ፍቅሬ ቶሎሳ። እንዲሁም ሌሎች ሊቀ – ሊቃውንታ ስለ ጥልቅ ዬእናታቸው ፍቅር ዬገለጹበት ስንኝ፤ በመሆን ዬከበረ መሆኑ ጠላቶቿ ዬማይክዱት ዬወርቅ እንክብል ነው።
ለወላጅ እናትንም ቢሆን እናቴ ለእኔ „ረቂቅ መንፈሴ“ ናት እንላለን። እናትን ሊተረጉም፤ ሊያብራራልን ዬሚችል ቃለ ምህዳን ስናጣ። እንኳንስ ሀገር። ሀገርማ ዬደም ሥር ነው። ዬመኖር ጭንቅላት። ስለሆነም „ኢትዮዽያዊነት ረቂቅ መንፈስ“ መባሉ፤ አይጎረብጥም። እንደ እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ግንዛቤ በኢትዮዽያዊነት ዓውደ ምህረት ላይ ይህ አገላላጽ ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳም ዬሚጋሩት ይመስለኛል። „ኢትዮዽያዊነት ረቂቅ መንፈስ“ በዚህ አገላለጽ ውስጥ ኢትዮዽያዊነት በጠላትነት እስካልተፈረጀ ድረስ። ወይንም ዬኢትዮዽያዊነት አውንታዊነትና ቀደምትነት በቅናት ድብን አድርጎ ውስጣችን በምቀኝነት ካላጋየው – በስተቀር።
ኢትዮዽያዊነታችን ያሳጣን አንዳችም ነገር ዬለም። በዓለም አደባባይ አንገታችን ቀና አድርገን እኩልነታችን ከእኛ ቀድሞ ያወጀ የዕውቅና እና ዬክብር ተክሊላችን ነው። በተዛብ ሥርዓታት በዬዘመኑ ለደረሱ ዬጋራ ሆነ የግል በደሎች ሁሉ ተጠያቂው ሥርዓታትና ዘመኑ ቢሆኑ እንጂ፤ ዬማንነታችን አውራ ዬሆነው ኢትዮዽያዊ ዜግነታችን ወይንም እናት ምድራችን ኢትዮዽያ ተወቃሽና ተነቃሽ ሊሆኑ አይገባም። በምድር ላይ በዳይም ተበዳይም ህዝብ እኛ ብቻ አይደለነም። መሪዎች እንደ እኛ የሰው ልጆች እንጂ፤ ረቂቅ መናፍስታት ወይንም መላዕክታን አይደሉምና። አይደለም ትናንትት ዛሬ ያለውን የዓለም ምስቅልቅል እየኖርንበት ነው። እኛ ተለይተን የሹም ዶሮ እንሁን ካላልን በስተቀር።
ይልቅ ውስጥን ያከበረ መፍትሄ አመንጭነት ቢያንስ ለነገ ህፃናት ኢትዮዽያ ዬተስፋ ሀገር እንድትሆን ዬጠራ መስመር፤ ግልጽና ቀጥተኛ ፍላጎት፤ታማኝነትንና ሆደ ሰፊነትን ቀለቡ ያደረገ ዩመደማመጥ ትግል ትውልድን ያተርፋል። ለዚህ ደግሞ ዬጥበብ ሥነ – ህይወትነት እንደ መክሊታቸው በጥበብ ዬተቀመረው የዶር. ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ድካምና ጥረት፤ አዎንታዊነትን ቀለቡ ያደረገው ብርታታቸውን ውስጥ ማድረጉ ይጠቅማል። ትውልድን እናተርፍበታለን።
በሌላ በኩል ደግሞ ከዛሬ ላይ ቁመን መተከዙን ተግ አድርገን – ስለ ነገ እኛ ስለማንኖርበት ዘመን – ዬተተኪ ህጻናትን ዬፍቅርነት አብሮነት መከብከቡ፤ ለማውረስ መጣሩ ብልህነትም ነው፤ ዬማስተዋል ልቅናም ነው፤ ዬፈተናችን መግቻ መሳሪያችንም ነው። መማርም፤ ማውቅም፤ ሊቅነትም ከቅዱሳን ህፃናት ዬነገ ብሩህ ተስፋ ላይ ሊነሳ ይገባዋል። ዕውቀት ብርኃንነቱን ለነገ መንፈግ አይኖርበትም።
- ርቱዑ።
ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ በውስጣቸው ዬሚንቀለቀለው ዬኢትዮዽያኒዝም ሐዋሪያዊነት በእያንዳንዱ ዬሥንኝ ዘለላ በጥልቀትና በውስጥነት ቅዱስ መንፈስ ተቀምሞ ይገኛል። ይህን ክብረት፤ ይህን ቸርነት፤ ይህን ረድኤት አላዬሁህም አልሰማሁህም ማለት አይቻልም። ኢትዮዽያዊነትን አንዱን ካንዱ በመነጥል፤ ወይንም አንዱን ከአንዱ ከፍና ዝቅ በማድረግ፤ ወይንም አንዱን ከአንዱ በማፈራረቅ፤ ወይንም አንዱን በአንዱ በአለና በዬለም በማፈተግ፤ ወይንም አንዱን በማቅረብ ሌላውን በማራቅ ሳይሆን፤ ውስጣዊ ራዕይን፤ እንደ የሰው ልጅ ዬውስጥ ሴል ተፈጥሯዊ አወቃቀርና አደረጃጀት፤ ዬነርብ መስመር ሂደትና ክንዋኔ መስተጋብራዊ አምክንዮ ውስጥን መግራት ይጠይቃል።
„አክሱም ለወላይታው ምኑ ነው¡ ወልቃይት ለመሃል ሃገር ሰው ጉዳዩ ወይንም አጀንዳው አይደለም¡ ኢትዮዽያ ገና ያልተሰራች ሀገር ናት¡“ ጉራጌ ማህበረሰብ ጉራጌኛ ቋንቋ፤ የኦሮሞ ማህበረሰብ ኦሮምኛ ቋንቋ፤ የሐደሬ ማህበሰብ ሃደሬኛ ቋንቋ፤ የአፋር ማህበረሰብ አፋርኛ ቋንቋ፤ የትግሬ ማህበረሰብ ትግረኛ ቋንቋ፤ ወዘተ እንዳላቸው ሁሉ አማራ ማህበረሰብ አማርኛ ቋንቋ እንዳለው መቀበል ለሚሳናቸው ወገኖች ዬፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ ዬምርምር ተግባር ሊጠጥር መቻሉ ዬሚገርም አይሆንም። ኢትዮዽያዊነትን ተቀበልኩ ዬሚለው ዬሚስጢራቱን ዘለበት ከሊቅ እስከ ደቂቅ መርምሮ ዬራስ ማድረግን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ዬሀቅ አርበኝነትን – ዬተግባር ጌትነትን ይጠይቃል፤ ልክ እንደ ዬፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ።
ቀረጣጥፎ፤ ወይንም ጨልፎ፤ ወይንም ቀናንሶ በኢትዮዽያዊነት ውስጥ ነው ያለሁት ማለት ዬሚያስችል አንድምታ ዬለም። ኢትዮዽያዊነትን ሲሹወርችና ጎን ተገነጣጥሎ መሆን አይገባውም። መለኪያውም ለህልውናው እኩል ዕውቅና፤ እኩል አክብሮት፤ እኩል አትኩሮት፤ አኩል ፍቅርን በንጹህ ልብ በመለገስ ሊሆን ይገባል። መሆንና መስሎ መቅረብ ጊዜ ዬሚጠብቅ X -ray ነው። ቅንነት አብዝቶ ይጎድለናል። ቅኖች እንሁን!
ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ ክብር ከሰጡበት ዬሊቃናት መንደር ከቁጥር በላይ የሆኑ አደባባይ ያልወጡ፤ ተዝቀው ዬማያልቁ ዬመንፈስ ሃብታት ያሉበት ቀዬ ማህበረሰብ ነው። ተወደደም – ተጠላም። ተፈቀደም – አልተፈቀደም። ለዚህ አንድ ምሳሌ ላንሳ — ዬድንግሉ፤ የሐዋርያው፤ ዬወንጌላዊው ዬቅዱስ ዻውሎስ መልዕክታት ትርጓሜ ዬሚስጥራቱ ዕድምታ በመጸሐፍ መልክ ወጥቷል። ለተዋህዶ ልጆች ህይወት ነው፤ ንባቡ፥ ትርጉሙ፥ ሚስጢራቱ በአማርኛ ቋንቋ አለ፤ ያለሰባኪ ዬሆነ በረከት ነው። ዬአንድምታ አመሳጣሪው ሥም ግን ዬለውም። ሥምና ዝና ለእግዚአብሄር ቃል ላደሩ ሊቀ – ሊቃውንታት ከቁጥር ዬሚገባ አይደለም። ህይወታቸው እንዲያስተምር ዬፈቀዱት ንዑዳን ፈርጣማ አብሪ ሥራቸውን ብቻ ትተውልን ያለፉም – በህይወት ያሉም አሉ። ዕሴታቸው ዘመን አሻጋሪ ነው። ቁሞ አስተማሪ ነው። ስለሆነም ውድ ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ ጥረተዎት ህያው መሆኑን እግረ መንገዴን ላስገነዝበዎት እሻለሁ። እግዚአብሄር ይስጥልን፤ ያኑርልን!
ቋንቋን በሚመለከትም ቢሆን ይዛመዳል፤ ይወራረሳል፤ በዚህ ዬውርርስ ሂደት ሀገር በቀል ብቻ ሳይሆን ዓለም ዓቀፋዊም ነው። ዘመናዊነቱ በዘመናዊ ሥልጣኔ ዬሚያምን ብቃትም አለው … ለምሳሌ አማርኛ ፊደላት ውስጥ ፊደል „ፐ“ ከሀገርኛ ቋንቋ ዬበቀሉ ዬፊደላት ቅምር ትርጉም የሚሰጥ ቃል የለውም። ስለዚህ የቋንቋው ፈላስፎች ዓለም ዓቀፍ እውነታንም ያገናዘብ ብልጹግ ብቃት ያላቸው እንደ ነበሩ መልዕክት አለው። ምሳሌ … ፖርሳ፤ ፖፖ፤ ፖሊሲ፤ ፓስታ፤ ፖስታ፥ ፓኬት፥ ፓርቲ፥ ፖለቲካ፤ ፖሊሲ ወዘተ …
… ከዚህ ጋር „ሽ“ ብዙ ዬጀርመን ቃላት „ሽ“ ይበዛባቸዋል። በጎንደር በስሜን አውራጃ አመዛኙ ቃላት በ „ሽ“ ዬተንጠቆጠ ነው። በአማርኛ ቋንቋ ፊደላት ቅለቱም ስንሄድ ጀርመንኛ ለ“ቸ“ አራት tsch ሆኼያትን ይጠቀማሉ። አማርኛ ግን በአንድ ፊደል ድምጸቱ ይገለጣል። ለ „ሽ“ ሶስት ወይንም አራት ፊደላት ያስፈልገዋል … “ich or isch“ – ይህ ለፊደል ግድፈት መጋለጥ ዬሚዳርግ ብቻ ሳይሆን፤ ጊዜን ይፈጃል፤ ወረቀት ያጣብባል፤ ቀለምም ለህትምት ይጨርሳል። ዬአማርኛ ቋንቋ ቀደምት ፈላስፋ ሊቀ – ሊቃውንት ግን አማርኛን ጓዘ ቀለላ አድርገው መፍጠራቸው ብቻ ሳይሆን – ዬቃናው ምት ድምጸቱ እጅግ ሳቢ፤ መሳጭ፤ ትጉህ አገልጋይና ተደማጭ አድርገው ነው ዬቀመሩት፤ ይህ ዬሊቅነታቸው ደረጃ ያመሳጥርልናል። በዚህም ዘርፍ ቢሆን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ያላቸው አቋም አሳማኝ ነው። ቀላሉን መንገድ መምረጥ ለሁሉም ቆጣቢ መሆኑን ነው አበክረው ሲገልጹ ነው ዬኖሩት። ስለሆነም ዬፈጠራ ጠበብትነታቸው ውስጠቱ ፋክትን ዬተንተራሰ ነው – ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ።
ዬአማርኛ ፊደል አርቱ ከእነ ሙሉ ግራማው ዬተለዬ መሸቢያ ቁመና ዘይቤ style እና ዛላ አለው – mode። በተለይ እያነበቡ ግጥም ሲጽፋ በቀጥታ ወደ ጥልቅ ዬተፈጥሮ ሚስጢራቱ – ይወስዳል። ለዚህም ነው እኔ በተለዬ ንድፍ ዲዛይን ግጥሞችን እንድሰራ በራሱ መንገድ ዬመራኝ። ዬፊደላቱ ዬአቀማመጥ ውበት በራሱ መስህቡ ጸደይ ነው፤ „ፏ“ ይህችን ፊደል በትልቅ ሰርታችሁ በፍሬም ውስጥ አድርጋችሁ እዮት። አንድ ግጥም አለኝ ስለእሷ። በሥነ – ጥበባት ዘርፍ ሁሉ በረጅሙ በጠላትነት ተፈርጆ ቢዘመትበትም ሁሉም ከልኩና ከመጠኑ ሊያልፍ አልቻለም። ሁሉም ተመልሶ እሱን ፍለጋ ወረፋ ላይ ቆመ። ስለሆነም ፕሮፌሰር ዶር. ፍቅሬ በውስጣችን ኃብታት መመሰጣቸው ሊያስከብራቸው፤ ሊያሸልማቸው፤ ዬብሄራዊ ጀግንናነት ግርማ ሊያሰጣቸው ይገባል ባይ ነኝ እኔ። ማህደረ ዕውነት ናቸውና። ጠርዝ ለጠርዝ አይደለም ዬሚሄዱት። ተጨባጩን በእውነነት ጀሮ ነው ዬሚያደምጡት። ዬጸሐይ ቦታ።
ዬሌላ ሀገር ዜጋ ቢሆኑ ኖሮ – ዬምንሳለማቸው በሆኑ ነበር። ከብክበን – መስከርን ፊት ለፊት አድርገን በዓለምዓቀፋ ማህበረሰብ ሽልማት – በሽልማት ባስደረግናቸው ነበር። ግን እኛ ሳንክና እንቅፋት በመፍጠር፥ ሊጎላ ዬሚገባውን ሀገራዊ ፋይዳ ዬዳመና ግርዶሽ በጥርጣሪ በማማረት፥ ዬሚሰበስብን ህሊና ጣውንት ማድረግ – ለምዶብናል። ያልታደልን።
ይህ ሁሉ ዬመከራ በረድ በ100,000,000 ሚሊዮን ወገኖቻችን እዬፈሰሰ አድማጮቻችን ዬተዛነፍ ግንዛቤ ቤተኛ ዬሆኑት በዓለምዓቀፋ ማህበረሰብ መስክረን ወድቀን ተነሰትን፤ ዬጸሎትም አጥር ቅጥር ሰርተን ለአንቱነት ያበቃነው ዬውስጣችን ሁነኛ ስሌለን ነው። እንዴት ተብሎ? አብሮ መውደቅ ነው ምርጫችን።
- ውስጥነት።
„ህጻን ሆነን ጂዎግራፊ ስንማር ‹‹ደሴት‹‹ የሚለው ቃል በውሀ የተከበበ መሬት ነው፣ ተብለን ነበር፡፡ ይህ ቃል ከየት እንደመጣ ያወቅኩት ስለደሸት ወይም ደሴት ከሰማሁ በሁዋላ ነበር፡፡ ጠቢቡ ደሸት/ደሴት በጣና መሬቶች ላይ ስለተፈጠረና ስለኖረ ከሱ ስም የተነሳ በውህ የተከበበ መሬት ሁሉ ደሴት ተባለ ብዬ፣ አስባለሁ“
ዬተከበሩ ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ እኔም አንድ እምነት አለኝ። እምነቴ አድዮ አበባ ናት። አድዮ አበባ ብሄራዊ አበባችን ናት። በዓመት አንድ ጊዜ ሳታዳላ በዬደጃችን፤ በየአጥቢያው ተገኝታ የዓዲሱን ዓመት ብሥራት አስቀድማ ዬምታበስረን ወሬ ነጋሪያችን ወይንም ዬወርሃ መስከረም ጥቢ ጋዜጠኛችን ናት። አድዮ ለእኔ ዬውስጣችን ሃዲድ ናት link። አገናኝ ናት፤ ጋራ – ሸንተረር – ወንዝ – መስክ – ጓሮ – ዬሚቀራት ዬለም ፈካ ብላ ታንቆጠቁጠናለች። „እንዴት ባጃችሁት?“ በማለት ሁሉመናችነን ተስፋን ትቀልበዋለች። አድዮ አበባ „ሀገርስ አማን ነው?“ በማለት በዬደጃችን ቢጫማ ዬፈካ ገፆን ይዛ ብቅ ዬምትለው ከስሜን እስከ ደቡብ፤ ከደቡብ እስከ ምስራቅ፤ ከምሥራቅ አስከ ስሜን በሁሉም ቦታ ኢትዮዽዬዊ ደንበሩን አካልላ ዬምታገናኘን አኃታዊ መንፈሷኢትዮዽያዊነትን ነው – ለእኔ የሚተረጉምልኝ። ሊቃውነተ – ኢትዮዽያ፤ ዬኢትዮዽያን ብሄራዊ ዓርማ ከቀስተ-ደመና ሲነሱ ዬአድዮን ዬሁሉዮሽ ተፈጥሮም አመሳጥረውበታል ባይ ነኝ። አገናኝነቷ መሃል ላይ ነው አድዮ ናት link። ጀግንነቱን እና ልምላሜውን በተስፋ ዝማሬ በዜማ ዬቃኘች መገናኛ! ስለሆነም አባቶቻችን ብሄራዊ ሰንደቅ – ዓላማችን ቀለማት፤ ይዘት፤ ትርጓሜና ዬህልውናው ዬዝልቅ አሸናፊነት አስኳልን ሲጠበቡበት፤ ለብሄራዊ ዓርማነት ሲወስኑ አድዮ አባበባ ከነመንፈሷ ዬጉባኤው ታዳሚ ነበረች ብዬ አስባለሁ፤ አምናለሁም።
ሌላው ኢትዮዽያ ዬታምራት ሀገር ስለሆነች በመስቀል ብቻ ዬሚታይ ዬመስቀል ወፍም በመስቀል ሰሞናት ከአድዮ ትንሽ ዘግዬት ብሎ ይመጣል። ብርቅም ነው። ቀደምቶች እንደ እኛ ውስጣቸውን እዬዘለሉ ስለማይራመዱ፤ ውስጣቸውን ዬመተርጎም አቅማቸውም ፍልቅ በመሆኑ፤ ለእያንዳንዱ ዬህይወት መስተጋብር ደረጃው ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጡታል። ለዚህም ነው በዓመት አንድ ጊዜ ለሚጎበኛቸው እንግዳ „ዬመስቀል ወፍ“ እኮ ሆንክ /ሽ/ ዬሚሉት።
በተጨማሪ ጥንት በድሮ ጊዜ ራዲዮ፤ ቴሌቪዥን፤ ሥልክ፤ ቴሌግራም፤ ከመፈጠሩ በፊት ዜና አብሳሪ፤ ሲያስፈልግም ትራፊክ፤ ሲያሰኝም የጦር መሪ ወይንም መሃንዲስ ወፍ ነበረች። ዛሬም በገጠሩ አለ። ታዲያ ዬወፍ ጋዜጠኛ ዬድምጹን ወይንም ዬዜማውን ቅኝት ይተረጉመዋል። በቤት መሰናዶ ዬሚያስፈልግ ከሆነም ለሴቶች ይነገራል። አሰሳም ሆነ፤ ውጊያም ሆነ፤ ዬጉዞ ፍጥነት ዬሚወሰነው በወፍ ጋዜጠኝነት ነው። ወፍ ሠራዊቱ እንዳይንቀሳቀስ ካዘዘ ቅስቅስ ዬለም። አፈናም ከኖረ ዬቦታ ለውጥ እንዲኖር ወፍ ቀጭን ትእዛዝ ካስተላለፈ – ይተገበራል። ጠብ ዬሚል ነገር ዬለውም። ከሰራዊት ጋር አብሬ ተንቀሳቅሼ በዓይኔ ስላዬሁት አትራፊነቱን – አይቼበታለሁ። ዛሬም ቢሆን ዬወፍ ዜና መሪነት ትውፊቱ አለ።
ሌላ አንድ ጊዜ ጉዞ ላይ እያለን – አንድ ዬኖረ ዛፍ ወድቆ ስላገኘነው ለማረፍ ተቀመጥንበት። አንድ አባት ጎንበስ ብለው ዬሚቆጥሩት ነገር እንዳለ ሳይ – ገርሞኝ ምን አግኝተው እንደሆን ስጠጋቸው፤ ጸጥ ብለው ቁጥራቸውን ቀጠሉ፤ ሲጨርሱ ቀና አሉና ልክ „እንደ እኔ ስልሳ ፈሪ ነው“ (59 ዓመቱ ነው ማለታቸው ነው ስልሣ ፈሪ ሲሉ።) ከአጠገባቸው እኔ ስለነበርኩ „በምን አወቁ ስላቸው?“ በቀለበቱ አሉና ዬዛፍ እድገት አንድ አመት ሲሞላው አንድ ቀለበት ይሰራል፤ ሁለት ሲሞላውም ሁለተኛውን ይሰራል ልክ በዚህ ዘመኑን ይመዘግባል በማለት ደግመው አስቆጠሩኝ። ሰፈር ስንደርስ ፋሳቸውን ይዘው ወጡና ነይ አብረሽኝ አሉና ሳተና ኮበሌ ልጃቸውንም ለርዳታ ጨምረው „ሊቆርጡት ያሰቡት ዬዛፋ ዕድሜ አስር አመቱ መሆኑን ቀድመው ነገሩኝ“ ከዛ በፉስ ተያያዙት – ሲቆረጥ እንዳሉት 10 ቀለበት ሰርቷል። ያላመንኳቸው ስለመሰላቸው ይመስለኛል ወዛችን ሳያርፍ ወደ ማስረጃቸው ዬተግባር ዶሴ ዬወሰዱኝ።
አሁን ይህንን ዬተፈጥሮ ጥበብ እዚህ ሲዊዘርላንድ ቤተ መጸሐፍት እሠራ በነበረበት ጊዜ – መጸሐፍቱ በዬዕውቀት ዘርፋ ይደራጃሉ። አንዱ ጥናትና ምርምር ነበር። ከዛ ውስጥ አንድ ቀን ስለ ዛፎች ዬዕድሜ ቆጠራ ቀመር ዬተፃፈበትን መጸሐፍ አገኘሁ፤ ግርም ነው ያለኝ። ሌሎች ሳይንቲስት – ጸሐፍት ተብለው ዬሚመረቁበት፤ ዬሚደነቁበት ለኢትዮዽውያን ግን በነፍስ ወከፍ ዬተሰጠ በረከት ስለመሆኑ አመሳከርኩበት፤ ሌላም ከዚህው መምሪያ በትንሽ እጣታችን እና በአውራ እጣታችን መከካል በክር ዲዛይን እዬሰራን ዬምንጫወተው ነበር በልጅነታችን – ያም ከቁጥር ገብቶ በመጸሐፍ ታትሞ አግኝቼዋለሁ። እኛ ዬሌለን፤ ያልነካነው፤ ያልኖርንበት ፍልስፍና ሆነ ዬጥበብ ዘርፍ ዬለም። ዬእስያ ገብያ አውሮፓ ላይ ተውዳጅ ገብያ ነው። ሁሉም ምርት ዬኢትዮዽያ ነው። አሁን አሁንማ ጤፍ እንደ መዳህኒት እዬታዘዘ ነው እኮ። ከጥራጥሬ ምርቶች ለውስጥ አካላት ምቹነቱ ጤፍ እዬተመሰከረለት ነው።
- እርገት ይሁን።
ውስጥን ለመተርጎም በውስጥ መኖርን – ይጠይቃል። ውስጥን ለማዬትም ውስጥን መሆንን – ይጠይቃል። ውስጥን ለማድመጥ ውስጥን ዕውቅና መስጠት – ይጠይቃል። ከውስጥ ጋር ለመኖር ውስጥን ማፍቀርን -ይጠይቃል። ውስጥ ዬሚናገረውን ለማድመጥ ጥሩ አድማጭ መሆንን ይጠይቃል። ዬህዝብን ታሪካዊ ሃላፊነት ድርሻ ለመወጣትም ዬህዝብን ውስጡን መሰነቅ ይሻል።
„በኢትዮዽያ ወንዞች ማዶ ላለች፥ ክንፍ ያሏቸው መርከቦች ላሉባት፥ መልዕክተኞችን በባህር ላይዬደንገል መርከቦችንም በውኃ ላይ ለምትልክ ምድርወዮላት! (ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፲፰ ከቁጥር፩ እስከ ፪)
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ ዬተፈጠረ ሚስጢር።
እልፍ ነን እና እልፍነታችን በተግባር እልፍ እናድርገው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ