„ጋዜጠኝነትን እንደ መንገድ እንጂ እንደ ግብ አላዬውም።“ (ጋዜጠኛ ሙኒራ አብደልመናን አውል)
„አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል፤
በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?
በቅንነት የሚሄድ ጽድቅንም የሚያደርግ
በልቡም ዕውነት የሚናገር“
(መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 14 ቁጥር 1 )
ዕለተ ሰኞ ዕለተ
ጠባቂ
በከበቡሽ
የቁራሽ እንጀራ ብራና
የሰብለ ህይወት
አዝመራ
ለራህብ የሚራራ።
„ጋዜጠኝነትን እንደ መንገድ እንጂ እንደ ግብ አላዬውም።“
(ጋዜጠኛ ሙኒራ አብደልመናን አውል)
· መነሻ ምርኩዜ።
https://www.youtube.com/watch?v=mm3mFckIO_8&t=68s
Ethiopia: EthioTube አፈርሳታ - Lidetu Ayalew : ልደቱ አያሌው | February, 2021
104,436 views
•Premiered
Feb 13, 2021
· ምክሬ።
እናት የመጀመሪያዋ ትምህርት ቤት ናት እላለሁኝ።
እናትም የመኖር መቅድመ የፊደል ገበታ ናት እላለሁም።
እናት የመጀመሪያዋ ዬህይወት ጎዳና ናት እላለሁኝ።
እናት የመጀመሪያዋ ሉዓላዊ መምህር ናት የሚል ፍልስፍናም አለኝ።
ትክክለኝነቱን ሁሉም ከእናት ማህጸን ስለተፈጠረ መመዘን እና መወሰን የእያንዳንዱ
የሥርጉትሻ ብራና ቅን ታዳሚ መብት ይሆናል።
እናቴ እብዬ ሆዴ በማህበራዊ ግንኙነቴ ውስጥ ከምትለግሰኝ ምክር አንዱን ላጋራ።
„መጀመሪያ ስታይው የምትደነግጭለት፤ ከራስ ጸጉርሽ እስከ እግር ጥፍርሽ ውርር ካደረገሽ ያ ሰው፤ ያቺ ሴት የአንቺ የውስጥሽ የምትሆን
ናት እና አትለፊው፤ አትለፊያት“ ትለኝ ነበር። ይህም በሰው ብቻ አይደለም በቁስም፤ ገብያ ላይም ይህ ስሜት ከተፈጠረ ግዢው ትለኛለች።
ቤትም ከሆነ ተከራዬው። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነውና እንዳትተላለፊው ትለኛለች።
ስዕልም ቢሆን፤ ፎቶም ቢሆን አካባቢም ቢሆን ብቻ እንዲህ ያልተለመደ ነገር
ከሰውነቴ ግብረ ምላሽ ከመጣ፤ ማድመጥ እንዳለብኝ፤ መፍቀድ እንዳለብኝ፤ በፍጥነት መውሰን እንዳለብኝ፤ ሥጦታውን እንዳልጠቀጥቀው
አበክራ ትነግረኝ ነበር።
በልጅነት አንዳንድ ነገር ሳማክራት „ልብሽ ደነገጠብሽ? ውርር አደረገሽ ሰውነትሽን“
ስትለኝ። እእ ስላት „ተይው የአንቺ አይደለም። ፈቃዱ ያልሆነ አጋጣሚ ነው ትለኝ“ ነበር።
ይህ ዝክረ ምክር በህይወቴ ሙሉ የተጠቀምኩበት ነው። ዛሬም። ሳያቸው ልቤ
የሚደነግጥብኝ ፕሮ ፋይሎች፤ ትጋትም ቢሆን ሳይቀር ጠንከር አድርጌ እይዛቸዋለሁኝ ከውስጤ። የእናቴ ምክርም ወድቆ አያውቅም።
ጋዜጠኘ ሙኒራ አብደልመናን አውልን መጀመሪያ ያዬኋት ከአቶ ልደቱ አያሌው
ጋር በነበራት መሳጭ ውይይት ነበር። ገና ሳያት ውይይቱን ሳላዳምጥ ነበር አስተያዬት የጻፍኩት። እናም ቀጠሮ ለዛሬ ተያዘ። በእሷ
ዙሪያ ስሜቴን ልገልጽ።
አቅመ ቢሶች ስለምመሰክራላት ቅንነትን ሄደው እንደሚያጠቋቁሩ ስለማውቅ ለዛ
ቦታ የለኝም እኔ። በቅድሚያ ለሥራ ፈቶች ልግለጽ ብዬ ነው። እኔ እምሰክራላቸውም ሰዎች ከ እኔ ጋር እንደማይሰነብቱም አውቃለሁኝ።
ዕውነቱ ከውስጤ ስለሆነ በዚህም ግድ አይሰጠኝም። ትርፍ ላገኝበት አይደለም እኔ እምጽፈው የትውልዱ ብክነት ህሊናዬ ስለሆነ እንጂ።
በራሴ አቅም እና ጊዜ ነው እምደክመው። አገር ትውልድ አደራ ለ እኔ ሦስቱ ሥላሴዎቼ ናቸው።፡
እኔ ፈጣሪ እንደሰራኝ በፈቀደልኝ ልክ መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ። ነገ
ጋዜጠኛ ሙኒራ የሚሰጣትን ምስክርነት ቸል ብላ ባልሆነ አቅጣጫ ብትራመድም
ያ የእኔ ጉዳይ አይሆንም። እኔ ነገ ይህ ይህ ይሆናል ብዬ ለተሰጠኝ የቅንነት ጸጋ ስንጥር አላበጅለትም። ምንም እንኳን የወ/ት
ብርቱካን ሚዲቅሳን ክህደት ያዬሁ፤ ብበሌኔ የተመለከትኩ የቆስልኩበትም ያፈርኩበትም ቢሆነም። ዛሬ አዲስ ቀን ነው። ዛሬ አዲስ ቀለም
ነው።
ወላድ ብድባብ ትሂድ አንዱ ቢስት ሌላውን ቸሩ መዳህኒዓለም አልነሳነም። ካሳ
ከፈጣሪ ነው። ተመስገን። ስለሆነም ዘመን የሚገልጣቸውን የቅንነት ሥጦታዎች ከማበረታት አልታቀበም። ጥሪዬ ነው። ይህን ካልፈጸምኩኝ
የተፈጠርኩበት ምርቃት ይነሳል፤ ሚስጢርም ይሰወርብኛል። ጥበብም።
ቅን ሆኖ ነገሮችን፤ ሂደቶችን በመጀመሪያ ደረጃ መቀበል እራሱ የቅንነት ጸጋ
እና በረከት ነው። ገና ዲያቢሎስ ምን ታመጣ ይሆን ብዬ አቤቱታ ለጨለማው ንጉስ አላስገባም። ይልቁንም አምላኬ እና ጌታዬ እዬሱስ
ክርስቶስ ሆይ! ተስፋዬን ለሰብል አብቃልኝ። የትውልድ አድርግልኝ ይሆናል ጽኑ ዘወትራዊ ጸሎቴ። ትውልድ የሚድነው እንደ ሙኒራ ዓይነት
በስኩን ቅን ሰብዕናዎች ነውና።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ እናላችሁ ለዛሬ ቀጠሮ ይዤ አርብ ፎቶዋን ሳሰባስብ
ዋልኩኝ። ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን ፎቶ የማንበብ ልማድ ስላለብኝ ፎቶዋን ደርድሬ ውስጧን ፍለጋ ስባትልላችሁ ትናንት ማምሻ ላይ እራሷ
ስለ እራሷ የተግባሯን ሩብ ዓመት መቋጫ ግምምገማ መስራቷን አዬሁኝ። የበለጠ መረጃ አገኜሁኝ።
ሰኞና ሰኞ ተገጣጠመ ማለት ለካንስ እንዲህ ነው ብዬ ትናንት „ማን ናት ጋዜጠኛ
ሙኒራ አብደልመናን አውልን“ ዝግጅት በጨመተ ሁኔታ አዳመጥኳት። ዛሬ
ደግሜም አዳመጥኳት። ትመስጣለች። ከዚህም በላይ አገራዊ ኃላፊነት ቢሰጣትም ትመጥናለች። ሚዲያ ያው ግዙፉ አቅም ቢሆንም። ሲዊዞች
ሚዲያ ሚዲያን ይሠራል ይላሉ። (Media Macht media)
· መገለጥ።
በሸኜነው ዓመት ኢትዮጵያን ውስጣቸው ያደረጉ ግን በደነገለ ሰብዕና ውስጥ
የኖሩ እማናውቃቸውን ተከደኑ የትውልድ ሲሳዮችን የእኛዎች እጬጌዎችን ዘመን ገለጠልን። የሆነ አጭር ጹሑፍም ጽፌ ነበር። አንድ ብቻ
ነው የቀረኝ እንጂ።
በዚህ አዲስ ዓመት ደግሞ ጋዜጠኛ ሙኒራ አብዱልመናን አመጣ ፈጣሪ። እሷ
11 ዝግጅት ሠራሁ ትበል እንጂ እኔ ፈቅጄ ያዬሁት 11ኛውን ብቻ ነበር። እግዚአብሔር በፈቀደልኝ ቀን። አያታለሁኝ። ግን አዳምጫት
አላውቅም ነበር። እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ አለውና …
በዚህ ዘመን የካቲት ወር ላይ ነበር ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር ያደረገችውን
መሳጭ ውይይት በተደሞ ያዳመጥኩት። እናም ቀኑ ለቀኑ ቀን ሰጥቶት በመንፈስ ተዋወቅኳት። ከውስጤም ተቀበልኳት። እንደ እኔ ዕይታ
መማሯ ብቻ ሳይሆን አስተዳደጓም ረድቷታል ብዬ እሰባለሁኝ። በተጨማሪም ጸጋም አላት የፈጣሪ የአላህ።
እንደዚህ ወጣቶች አዲስ የአሰራር ፈር ቀይሰው ብቅ ሲሉ ተስፋ ይፋፋል። በራሳቸው ማንነት ውስጥ የበቀሉ ሰብሎች እና እሸታዊ ጎዳናቸው ለእኔ መንፈስም ቅርብ ናቸው። ነገ ምን ይመጣል? ነገ እንደዛ ቢሆን ባይሆን ብዬ ጊዜ አላቃጥልም። ለነገ ነገ ይጨነቅ።
ለዛሬ ግን እኔ የትውልዱ ነገር የቤት ሥራዬ ስለሆነ ለማግሥት የሚሆኑ የራሳቸውን
አሻራ ለማስቀመጥ በቅንነት የሚቀበሉ እንዲህ ያሉ ሰብዕናዎች በቅለው፤ አስብለው ማዬት በራሱ ተስፋን ያስናፍቃል። እለዛሬ የዕለተ
ሰኞ፤ የዕለተ ጠባቂ ቤተኛ እንሆ አደረግኳት።
ይህቺ ወጣት ጋዜጠኛ
በፍልስፍና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን፤ በቱርኪ ኢስታንቡልም ሁለተኛ ዲግሪዋን ወስዳለች። ከዚህም
ሌላ በዓለም ዓቀፍ ሚዲያ መቀመጫውን ቱርክ አንካራ ያደረገ አናዶል ኤጀንሲ የዜና አውታር ውስጥ እንደ ሠራች ገልጻልናለች።
መጀመሪያ ሪፖርተር ሆኜ ነበር የገባሁት። ከዛ የአፍሪካ ንዑስ ዴስክ ሃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁኝ በማለትም የሚዲያ ቆይታዋን
ስትገለጥ አዳምጫለሁኝ። ከሪፖርተርነት የአፍሪካ ዴስክ ኃላፊ እስከመሆን ደርሳለች
ማለት ነው። በውነቱ እኔ ይህ ሁሉ በዕውቅት የሰከነ አቅም አላት ብዬ አልነበረም ውስጤ በመጀመሪያው ቅጽበት የተቀባለት። ሳያቸው
ልቤ ውስጥ ከሚታተሙት የአገሬ ልጆች አንዷ በመሆኗ እንጂ። ሳያት የሆነ ስሜት ተሰማኝ። ስሜቱ የኛዊነት ነበር።
እኔ የተንከለከለ ነገር አልወድም። ቦጅቧጃ ስብዕና ግጥሜ አይደለም። የሰከኑ
ሰዎች እጅግ በጣም ይመስጡኛል። ለማድመጥ የፈቀዱ። ለመደመጥም ይፈቀዳሉና። ፍሬ ነገር ባይኖራቸውም እንኳን ስክነታቸው የውስጥ ሰላሜን
ይጠብቅልኛል ርጋ ያሉ ሰብዕናወች። በስክነታቸው ውስጥ የሚፈጠረው የትውልድ ሞራል ያጓጓኛል።
እኔ በግሌ ቅዳሜ ቀን እና አርብ ቀን ገብያ ሄጄ አላውቅም። ፈጽሞ። ብዙ ሰው ስለሚኖር። በአዘቦቱም አልባሌ ሰዓት ላይ ነው ወጥቼ ነው እምገበዬው።
አዬሩም፤ ጸሐዩም፤ ነፋሱም አውዱም ስክን ሲል የሄድኩበትን በአግባቡ ከውኜ
እመለሳለሁኝ። ልገዛ የምሻውን ነገር ከገዛሁ በኋላ እግረ መንገዴን ሌላ ሱቅም ጎራ የለም። ቀጥ ብዬ ወደ ቤቴ ነው። የትም ቦታ
ልሂድ የሄድኩበትን ከውኜ ወደ ቤቴ ነው።
ምክንያቱም የተጨናነቀው የፕላኔታችን ሁካታ ግጥሜ ስላልሆነ። ለዛውም በገዳማዊት
ሲዊዝ ተቀምጬ ማለት ነው። ጭምቷ ሲዊዝና ለእኔ የተፈጠረች ልኬ ናት። በተለይ እኔ እምኖርበት ቪንቲ ገዳም ሠፈር ነው።
እዚህ ፌስቡክ እራሱ ጋል ጋል ያለ ነገር ሲሆን እስኪሰክን ዞር ብዬ እቆያለሁኝ። በዚህች ወጣት ያዬሁት ስክነት ሳያት የሳበኝም እርጋታዋ ይመስለኛል። ለሴቶች እርጋታ ውበታችን ነው። ሴት ልጅ ደልዳላ መሆን አለባት። ወንድ ልጅ ከልካላ ይሁን እያልኩ አይደለም። አልወጣኝም። ሴት እናትነት ጸጋው እዮራዊ ነው። ሴት እኮ ቤት ናት። ቤት ደግሞ ነፃነት።
በእህት ሙኒራ ውስጥ አዲስ ጎዳና ሃሳብ አለ። እናት አገራችን ኢትዮጵያ የጎዳላት ብዙ ነው። ቀዳዳዋ ወዘተረፈ ነው። አብሶ ሚዲያ ላይ ብዙ በጣም ብዙ ያልተገሩ ስንክሳሮች አሉ። ይህን በእሷ ጸጋ ልክ፤ በእሷ የእውቀት ደረጃ ልክ፤ በእሷ ቅብዕ መጠን፤ በራሷ ቀለም ልክ የትውልድ ጥሪት ይሆን ዘንድ ሃሳብ አላት። የእህት ሙኒራ አሻራ? ይናፍቃል አይደል?
· የዕውነት ናፍቆተኝነት።
ሃሳቧ የህዝብ ለማድረግ ዕውነትን ፍለጋ እንደምትመሳን አጫውታናለች። ምኞቷ ትውልዱን ባልባለቀ ገንቢ
ጎዳና መንፈሱን በዕውነት ዙሪያ መግራት ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት አለው ብዬ አምናለሁኝ። ችግሩ መክሊቱን ወደ ገቢር
ለመለወጥ መድረክ ማጣት ነው። አሁን ተመስገን ነው።
ማህበራዊው ሚዲያው እራሱ ፏ ያለ በር ነው። ሁሉም የዓለም ዜጋ የእኔ የሚለው የነፃነት ቤት አለው። ህግ መተላለፍን ከገታን ማለት ነው። ስለዚህ የሥልጣኔውን ዘመን ተጠቃሚ ለመሆን እያንዳንዱ ባለጸጋ፤ እያንዳንዱ ባለመክሊት የራሱን ጎዳና መጀመር ይበል የሚያሰኝ ቅን ጥረት ነው።
· እራስን የመገምገም ሥራን
የማጠቃለል ስልታዊ ጥበብ።፡
እኔ በፍቅራዊነት ፕሮጀክቴ ላይ ምዕራፎችን በውህደት እና በመደምደሚያ ሁልጊዜ
አጠቃልላለሁኝ።
https://www.youtube.com/channel/UCb4Maqp24liAGdbPE553WGA
የአማራ ተጋድሎ እና የኦሮሞ ንቅናቂ ትሩፋት በፎቶ ማጠቃለያ ሰርቸለታለሁኝ።
„የድምጻችን ይሰማ“ ተገድሎ ድንቅ አፍሪካዊ ተጋድሎ ስለነበር ለእሱም ምን ተማርን የሚል አንድ ጠንከር ያለ ጹሑፍ ጽፌም በድምጽ
ሠርቸለታለሁኝ።
በተጫሪም የጎንደር የ45 ቀኑ ድንቅ የምህላ ሱባኤንም እንዲሁ የፎቶግራፍ
ማጠቃለያ ሰርቸለታለሁኝ። የህዝብን ተሳትፎ እራሴ ኃላፊነት ውስጄ አጠቃልላለሁኝ። ባለቤት ለሌላቸው ድንቅ ተግባራት በእራሴ አነሳሽነት
ወይ የፎቶ ወይ የሥንኛት መዘክር እሰራለሁኝ።
ለዛሬ አይደለም እኔ እምሠራው ለዛሬ 20/30 ዓመት ነው። ከእኛ የተሻለ
ትውልድ ትናንትን ሊከብር ይችላል ብዬም አስባለሁኝ። እኛ ዛሬ ዕውቅና ያልሰጠናቸውን ትጋቶች ማግሥት ባለቤት ይሰጣቸዋል ብዬም አስባለሁኝ።፡
https://www.youtube.com/channel/UCJEQXw86u_NG4A1FVC1j2qg?view_as=subscriber
· ልዩዋው ውዴም ሙኒ፣
የሩብ ዓመት ተግባሮቿን ገምግማለች። ምን ሠራን? ምን ቀረን? ምን ገጠመን?
ምንስ ይቀረናል? በቀጣዩ ጊዜ ጎዳናችን በምን ላይ ያተኩራል? ይህንንም በእያንዳንዳችን የህሊና ሰሌዳችን ውስጥ ጽፋልናለች። ድንቅ
ብቃት ነው።
ልዕልት ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የስክነት ክህሎት ሙሴ ይጠሰጣት ዘንድም እጸልያለሁኝ። በተፈጥሮዋ የአደራጅነት መክሊት እንዳላት አይቻለሁኝ።
እንደዚህ ዓይነት ክውን ተግባርት የሚከውኑ አደረጆች ብቻ ናቸው። ለአገር ብሄራዊ መሪነት ቢሮ እንኳን ማስተዳደር፤ ፋይሉን ማደራጀት የማይችል ሰብዕና ነው በእጩነት ህልም ዘመኑን ሲሸኝ እና ሲቀበል እምናዬው። ከዚህች ቀንበጥ የፖለቲካ ሊቃናት ሁሉ ቁጭ ብለው ሊማሩ ይገባል። ይህ የሩብ ዓመት ዘገባዋ በራሱ አንድ የትውልድ አሻራ ነው። እኛ እኮ ወጀብ ነው አለቃችን፤ ወይንም ሰበር …
ይህ በራሱ ለኢትዮጵያ ሚዲያ አዲስ ቅይስ ይመስለኛል። አበጀህ! የሚባልም ተመክሮ ነው። አዲስም ጎዳናም ነው። የናፈቀኝን እሸት ጎዳና ሳገኝ ፈካ ፈታ እላለሁኝ።
በተጨማሪም አንድ ዓለም አቀፍ አንጋፋ ጋዜጠኛ የሙያ አባቴ የሚለው ነገር ነበረው። ነፍሱን ይማረው በህይወት የለም። ጋዜጠኛ እስኪመጣለት አይጠብቅ። እሱ ይሂድና እንዲመጣለት ከፈለገውን ነገር ጉዳይ ጋር ይገናኘው ይለኝ ነበር። እሷም ይህን መስመር ለመከተል ትልም እንዳላት አዳምጫለሁኝ። ማለፊያ ትልም።
· አመክንዮዊ ጉዞ ….
ከሁሉ በላይ በሰርክል የተደራጀውን የሚዲያ አጥር ጥሳ ለመውጣት አዲስ ጎዳና ቀይሳለች። ይህ ገዢዎችም ከፈቀዱላት የሚከውን ነው የሚሆነው። ፈተናውም ከባድ ነው። አይደለም ኢትዮጵያ ውጭ አገር የሚቻል አይመስለኝም። ይቅናት! አሜን!
ይህ በኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ያልተለመደ አዲስ ጎዳና ነው። የተለመዱት ሰዎች ናቸው በአንድም በሌላም በዛው መድረክ ሲዘዋወሩ ዬምታዩት። በፖለቲካ ድርጅት አባልነት፤ ወይ በጋብቻ፤ ወይ በማህበራዊ ኑሮ ትስስር፤ ወይንም በዝምድና ቁርኝት ወይ በሰፈር ልጅነት ወዘተ …
የሚዲያውን ዓውደ ምህረት ወይንም ዕልፍኝ አስልቺ ችኮ አድካሚም ያደረገውም ይኸው ነው። እኔ ከማዳምጠው እማላዳምጠው
ይበልጥብኛል። ለምን ብትሉኝ?
(1) አንደኛ ይሰለቻል።
(2) ሁለተኛ አንድ ሰው ሁሉን ሊውቅ አይችልም። እይንዳንዱ የዕወቀት ዘርፍ የራሱ ዲስፕሊን፤ ማንነት እና ባለቤት አለውና። መቀመጥ
ካለብኝ ለመማር መሆን አለበት። ላለተርፍ መክሰር የለብኝም። የፌስቡክ ዜና ከሆነ አብሬው ነው የምውለው።
(3) ሦስተኛ ሙሽራ አቅሞች አደባባይ እንዲወጡ ለማድረግ በሩ የተቀረቀረ ነው። ብቅ ቢሉም ጠለፋውን ተቋቁመው በራሳቸው መክሊታዊ ቀለም የመዝለቁ ዕድሉም ያን ያህል
ነው። አንዱን ካልተጠጉ ደግሞ ይረሳሉ ወይ ይገለላሉ።
በዚህ ማህል አውራው አገራዊ ትንሳኤ ይስተጓጎላል። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ
ከሚፈርሱት አገሮች ተርታ ጉብ ያለችው። እያላት በሁሉም ዘርፍ የድርቅ እና የድርቀት ቤተኛ የሆነችው። ጸጋው እብዝቶ የሰጣቸው ይገለላሉ።
ዕውቀቱን አብዝቶ የሰጣቸው ሙሽራ አንገተ ደፋታ ናቸው። ዓይን አፋር ናቸው። ብቅ ሲሉም እኛም ፋሳችን ይዘን እንከተክታቸዋለን። ይህ ክብር ነው ብላችሁ እንደማትሞግቱኝ ነው።
ከሁሉ በላይ የዕውቅት፤ የሳይንስ፤ የፍልስፍና፤ የጥበብ ድርቀት ነው በተረ ነገር ጊዜም፤ መዋዕለ መንፈስም እዬባከነ ያለው። ስድብ ቁምነገር ሆኖ፤ አሉባልታ ጠሐይ ሆኖ ምራን የሚባለው። ይህ ለትውልዱ ኪሳራ ነው። ኪሳራን እዬደመርን መሮጥ የትም አላደረሰነም። ሩጫ …. ሩጫ …. ሩጫ ….. የከንቱነት ምርትን ለማፈስ።
ኢትዮጵያ አገራችን ባላት ሙሉ አቅም ልክ ትጠቀም ዘንድ በሩ ዝግ ነው። የተከረቸመ። ኢጎ ነው የኢትዮጵያ ገዢ ፒላር። ወይንም አሉታዊ ፉክክር። አዲስ ሰው፤ አዲስ ሰብዕና፤ ብቃት ያለው አቅም ሲወጣ ፉክክሩ ይጦፋል። ትውልዱ በዚህ ማህል ይሾልካል። ዕውቀቱም አፍ ባለው መቃብር ለግዞት ይላካል። ያ ድንቅ ሰው ያሰበለው ሰብልም በአረም ድንግዝግዝ እንዲል ይደረጋል።
ይህን ጥሶ ለመውጣት አብዝቶ የጥሞና ጊዜ ይጠይቃል። አብዝቶ ፈቃደ እግዚአብሄርን ይጠይቃል። መሰናክሉም፤ ፈቃደኝነቱም መደዴ አይደለም እና። ያልተለመዱ ጋሬጣዎች አሉበት እና። አንድ ነፍስ በራሱ ወጪ፤ በራሱ ጊዜ፤ በራሱ ገንዘብ ለሚደክምበት እንኳን ዕውቅናው ቀርቶ ሰላሙ አስቀንቶ ጦር ይታዝዝበታል። ይህ እኔ የኖርኩበት ዝክረ ታሪኬ ነው። ስለዚህ ለ እህት ሙኒራ ውጥን የፈጣሪ እርዳታን ከልብ መጠዬቅ ያስፈልጋል። ብረት መዝጊያ ቤተሰብ ትዳር ያስፈልጋታል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እፉኝት ነውና።፡
· ጥሞናዊ ሙያዎች።
በነገራችን ላይ የፍልስፍና፤ የህግ፤ የሥነ - ልቦና፤ የሳይንስ ሰዎች ጭምቶች ናቸው። ሙያዎቹም ጥሞናዊ ናቸው። እንደኛ ቃላትን አይደፍሩም። ቃሎች እና መልዕክታቸው ተመዝነው ሳይፈተሹ ይለፍ አይሰጣቸውም። ለዚህ ነው በዚህ ሙያ ዘርፍ ያሉ ሰብዕናወች እጅግ ቁጥብ፤ ለስላሳም የሚሆኑት።
እንግዲህ ሙኒሻ የዚህ ቤተኛ ናት የፍልስፍና ሊቅ ናት። በጭምቱ ሰብዕናዋ ፍልስፍና ታክሎ፤ ሥነ - ኃይማኖቱም ላይ ጠንካራ ትመስለኛለች ሳያት ቁልፉን የኢትዮጵ ቸግር አግኝታዋለች ብዬ አስባለሁኝ። የጎዳናውን ትልም ውስጠቱን ስፈትሸው።
አንድ የፊልም ፕሮዳክሽን ከእነ ሙሉ ስክሪፕቱ፤ ከእነ ሙሉ የአገልግሎት ሰጪ እና አቅራቢ ፕሮጀክት ተደራጅቶ እንደ ቀረበ ዓይነት ነው ሥዕላዊ በሆነ መልኩ ትልሟን በጭምትንት ያስተዋወቀችን።
ወጣቷ ጋዜጠኛ እና የፍልስፍና ሙሁር አሻራዋን በተደራጀ በሥልጡን እሳቤያዊ መንፈስ ጀምራዋለች። ማደራጀት መጀመሪያ መቅደም ያለብት መንፈስን በራስነት ውስጥነት ከማደራጀት መነሳት አለበት። የቸገራት ነገር የኦረሞሙማ ፕሮጀክት የሰበሮች መደራረብ ስለመሆኑም ተረድቻለሁኝ። አቅልም ትልም አልባ ነው ያደረገው አገራዊ ጉዳዮችን ሁሉ።
ከዛ ወጥቶ ቋሚ ሥራን መጀመር ነው። እኔ በጸጋዬ ራዲዮ 4 ፕሮግራሞችን ለሁለት ወር ልሰራ እችላለሁኝ። የቀኑ መርዘም፤ መጣር አያውከውም። በጊዜያዊ ተግባራት፤ ዘገባ ላይ ስለማላተኩር። በቋሚ ዕውነት፤ በቋሚ መርህ፤ በቋሚ የ አደራ፤ በቋሚ የትውፊት ተግባር ላይ እሰራለሁኝ። ለዚህ ዓመት የካቲት የሠራሁት ለሚቀጥለው ዓመት የካቲት ባቀረበው አያረጅም፤ አይሸብትም፤ ሽውራር አይበላውም፤ አይገረጅፍም። በዚህ ውስጥ ሃሳብሽን ለማደራጀት ካሰብሽ ከድንገቴው የሱናሜ ማዕበል የለፋችሁበት ተግባር ይድናል ብዬ አስባለሁኝ።
የሆነ ሆኖ የ60ዎቹ የገነቡትን ሁሉን ውጦ እራስን ማውጣት የቀበር ጉዞን ጥሶ ሰርክሉን መበጣጠስ ቀላል አይደለም። በ አቶ ልደቱ አያሌው የደረሰውን የ15 ዓመት መከራ፤ ዛሬም የሞት ፍርድ ማስተዋል በቂ ነው።
ስለሆነም ለዚህ የማህበራዊ ንቃተ ህሊና ድጋፍ ስለሚያስፈልጋትም ነው ይህን ጹሑፍ ለመጻፍ የተገደድኩት። ። እንርዳት ነው ጥሪዬ። ታዋቂዋ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች አርጅንቲናዋ ፖለቲከኛ አርቲስት ኢቢታ ፔሮን በምድሯ ውስጥ ሥርዓት ቢቀያየር ንቅንቅ የማይል ማህበራዊ ለውጥ አርጀንቲና ላይ ፈጥራለች። ሥር ነቀል ለውጥ ነበር ያመጣቸው። ለጀርመኖች ንግሥታቸው ናት፤ ለእንግሊዞችም።
አርጅንቲና ላይ አንድ ተብዕት ጠንክሮ ከወጣ እናቱ፤ እህቱ፤ ጓደኛው፤ የትዳር አጋሩ አቅም ያበጀው ልቅናውን ተብሎ እንደ ሃይማኖት እንዲወሰድ አድርጋለች ጀግናዋ ኢቪታ። ኢቢታ ህግ ድንጋጌ ብቻ አልነበረም ያሰወጀችው ማህበራዊ ለውጥ ነው ያሰፈነችው።
አሁን አርምን ለሴቶች የህግ ሙሉ ጥበቃ ታደርጋለች። የኢቢታ ግን ለሴቶች
ጥበቃ የሚያደረገው የማህበረሰቡ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ነው የቀረጸችው። ይህችን ወጣት ካገዝናት፤ ከደገፍናት፤ አይዞሽ ካልናት የእኛይቱ
ኢትዮጵያዊቷ ኢቢታ የማትሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ሃሳቧ ሩቅ ነው። የሚናፈቅ። የሚያጓጓም።
· „ኢትዮጵያ የኢሊቶች አገር ብቻ አይደለችም“
የችግሩን አስኳል አግኝታዋለች። „ኢትዮጵያ የኢሊቶች አገር ብቻ አይደለችም“ ሌላም ያነሳቸው የርትህ ጎዳና ነው። ኢትዮጵያ የኢሊቶች ብቻ አገር አይደለችም ብላናለች። ይህም ሌላ ፍጽምና ያለው ውስጥን አናገረ የሚገራም፤ የሚፈትንም የተጋድሎ መስመር ነው። ያልተደፈረም አምክንዮም ነው።
ሚዲያ ለተወሰኑ ዜጎች ብቻ ገጸ በረከት የተሰጠ ሆኖ ምልዕቱ ግን የበይ ተመልካች ሆኖ ዘመኑ ያልፋል። እያንዳንዱ ዜጋ የእኔ የሚለው ታሪክ እና መክሊት አለው። ግን ተዳፍኖ ዘመን ሲሸኝ እም! ብሎ እንዳመጠ ያልፋል።
ታስታውሳላችሁ አይደል። ነፍሱን ይማረውና ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛው አቶ ደምስ በለጠ 1% ዜጋ ነህ አልተባለም። አገር ሲጋብም አልተደመጠም። ሲያልፍም አልተደመጠም። ለምን? ሚዲያው የታቆረ ወይ (stagnant) ስለሆነ። እሱ ቀድሞ ለታገለለት ዓላማ አዲሶቹ ጭብጨባ በሽብሸባ አቀባበል ሲደረግላቸው እሱ ባይተዋር ነበር። ያን ሁሉ የደከመለት ተጋድሎ በምንም ነበር የተወራረደው። ግን እሱም አሻራ ነበረው።
· ጋዜጠኛ ሙኒራ ለትክክለኛው ወቅት የተሰጠች ሥጦታ ናት።
ጠቅላላ ሁኔታዋን ሳይ ለትውልዱ በትክከለኛው ወቅት የተሰጠች ሥጦታ ናት።
እርጋታዋ ብቻ ይበቃል። የጥያቄ አቀራረብ ገጸ ባህሬ አጭር፤ ግልጽ እና የተብራራ ነው። ጅረት እዬፈጠረ ተጠያቂንም አንደማጭንም
አያሰለችም። እንደ ገናም ተጠያቂው ስውር ዲስክርምኔሽን አይፈጸምበትም። ሃሳቡን እንዳሻው ማቀረብ ይችላል። ጊዜውን አትቀራመተውም።
እሷ እኔ ካልተናገርኩ ብላ ሜዳውም ፈረሱም አይብቃኝ አትልም። ጫሪ ሃሳቦችን አቅርባ ጸጥ ብላ በእርጋታ ታዳምጣለች። ከመታደል በላይ ነው።
· ሌላው አጋጣሚው ከተነሳ ቁስል የምልበትን ሌላ ነገር ላንሳ።
አወያዮች ይሁኑ ተወያዮች ምን ያህል አድማጭ እንደሚታወክ አያስቡትም። ሲዘጉ፤ ድምጹን ሲያጠፉት ሲከፍቱ፤ አንዱን ሲይዙ ወይንም ሲጥሉ፤ ካሜራ ላይ ያልተለመዱ ነገሮችን ሲያደርጉ ያ ጊዜውንም መንፈሱንም ሰጥቶ ቁጭ ብሎ ለሚያዳማጣቸው ክብር መናገራቸው ብቻ ይመስላቸዋል።
ርብሽብሽ ያለ፤ የተቆራረጠ አትኩሮታቸው ምን ያህል እንደሚበጠብጠን ፈጽሞ አያውቁትም። ፈጽሞ። አንድ ከዚህ የዳነ መንፈስ ሰሞኑን እያዬሁኝ ነው። በዚህ ውስጥ ያለው ልቅና ሳይጓጉል መከታተል በመቻሌ ፈጣሪዬን አመስግኛለሁኝ። ቁጭ ብዬ ማስተወሻዬን ገዝቼ በሰዓት በቀናት ለይቼ እዬያደመጥኩኝ እማራለሁኝ። ፕሮፖጋንዳ ስልችት ብሎኛል። ለእኔ ሰብዕና አያስፈልገኝም።
ከዚህ ድናለች ልዕልቷ። ኢትዮጵያ አንዲህ ውድ ተናፋቂ ደልዳላ እቴጌ እንዳገኜች አስባለሁኝ። መስጣኛለች። አክብሮቴ ከውስጤ ነው። ፍቅሬም ከህሊናዬ።
· እሸታዊቷን ተደሞ አይዞሽ ከጎንሽ ነን እንበላት።
ይህቺ ሸበላ ቀንበጥ ልትደመጥ፤ ልትደገፍ፤ አይዞሽ ልትባል ይገባል ነው የከበበቡሽ ቁራሽ እንጀራ ብራና የማዕልተ ሰኞ ብሄራዊ ትሪ። ትሁታዊው ማሳሰቢያው።
ይህች ውብ እና ውድ ፌስቡክ ወይንም ሌላ የማህበራዊ ሚዲያ ተስትፎ ካላት ዋናውን ስቴዲዮ ጨምሮ ሊንክ፤ ፎሎው በማድረግ ህልሟ ይሳካ ዘንድ እረዱልኝ ልል ነው ዛሬ ለእኔ ቅን ታዳሚዎች በአክብሮት እማሳስባችሁ። እሸት ተስፋ አይቻለሁኝ። ትውልድን የሚያበረክት። እኛ ምን እናድርግ? እኛ ምን አደረገን ብሎ ሰርክ ለሚያፋጥጠን ህሊና መስል አላት ይህቺ ውብ።
ሌላ በሥራ ለሚገጥም ውጣ ውረድ፤ ፈተና ፈጣሪ በሰጣት ልክ ታማኝ ከሆነችለት
እራሱ ጎዳናዋን ያሳምርላታል።
· ሰላም ወዳድነት በሳቂነት፤
· ፍቅርን በጦርነት አለመሻት፤
· አብሮነትን በመደመማጥ
ከጭቅጭቅ እና ከንትርክ በጸዳ መንፈስ ለመከወን መቀነቷን ጠበቅ አድርጋ ተነስታለች።
እርግጥ ነው የቅንድብ ጸጉር ማህበር የወደቁበትን፤ የመከኑበትን መንገድ ትከተል ዘንድ ደውለው እንዳናገሯት ገልጻለች። ከዚህም በላይ መናኮር ይመጣል። ክብሬ የሆንው ወጣት የሚሏትን ድሪቶ ሃሳብ ያን ቆሻሻ ውስጥ ጥላ እሷ በምትኖርበት ዘመን ባለ ዕውነት ውስጥ ፈልቃ እንድትተይ ነው ምኞቴ። እነሱ የፈለጉትን ይበሉ አንቺ ግን ውዴ ለአንቺ በተሰጠው መክሊት ልክ በአቀድሸው ዓላማ ጎዳና ቀጥይ ነው ሃሳቤ።
እነሱ ማገቻ አድርገው ባሰናዱት ሚዲያ ይዳክሩ፤ አንቺ ደግሞ በቀለምሽ ልክ
ባገኜሸው ሚዲያ በጀመርሽው የቅንነት ትውልድን በአዲስ ገንቢ ሃሳብ የማፍለቅ ህልምሽን ቀጥይበት። በርቺ አይዞሽ። ሌላ ባናደርግልሽ
በጸሎት እናግዝሻለን።
አጫጨር ከ30 ደቂቃ ያነሱ ዝግጅቶች ሲኖርሽም እኔ በጸጋዬ ራዲዮ ድምጹን
አርሜ አቀርበዋለሁኝ። እናንተ ብታርሙት ራዲዮ ፕሮግራም ላይ ጥራት የኤቲክሱ ግዴታ ስለሆነ ደግሞ ፈቅደን እንታሽበታለን ማለት ነው።፡
ወጣቷ እጅግ በርካታ ህልሞች ነው ያላት። ፈጣሪ አላህ ከፍላጎትሽ ጋር አገናኝቶሻል እና ለፍፃሜ እንደምትደርሺ፤ እንደምታሰብዬም እርግጠኛ ነኝ። ቅንነትሽ ታይቶኛል። ፍቅራዊነትሽ መልዕክት ልኮልኛል። የትውልድነትሽም በርቶልኛልና። አንችነትሽን ስትገልጪው በውስጤ በጽኑ እንደ ላስታው አለት ታተምሽ።
· ሳቅ ፍቅራዊነት ነው። ሳቅ አርበኛም ነው።
ሳቂታ መሆንሽን ነግረሽኛል። እናቴ እብዬ ሆዴ እምትታወቀው በሳቂተኝነት ነው። ሳቅን ታስተምረንም ነበር። እሷ በህይወት በኖረችበት ዘመን ሁሉ ሰው ሳታስከፋ ባጋጣሚ ያኮረፋት ቢኖር እንኳን በሳቋ አሸንፋ ውስጧ አድርጋ ነበር የኖረቸው በአርበኛው ሳቋ ነው። ለእኛም ያወረሰችው ይህ ነው።
ኢትዮጵያ አንድ ጋዜጠኛ እና የህግ ባለሙያ ጠበቃ፤ አንድ ፈላስፋ፤ ሳይንቲስት፤
የህግ፤ የሃይማኖት ሰብዕና፤ አንድ ሌላ የጤና ባለሙያ፤ አንድ ሌላ ደግሞ ሞጋች ፖለቲከኛ ፈገግ ውሽክ እያሉ የሚወያዩም አሉ። እነዚህ
ሊቀ - ሊቃውንታት የአገሬ ውዶች ይወቁት አይወቁት ጸጋቸውን አላውቅም። እንደምን የአድማጭ ፈውስ እንደሆነ።
· ውዴ ሆይ!
ከላይ የገለጽኩልሽ ሰብዕናዎች ምን ያህል ለንግግር ጥበብ፤ ምን ያህል ለሚዲያ አድባር ጸጋ እንደሆኑ ልነግርሽ አልችልም። በማልስማማበት አጀንዳ ሁሉ እታደማለሁኝ። ይንፍቁኛል። ሳቅ ፍቅራዊነት፤ ሳቅ ተፈጥሯዊነት፤ ሳቅ የልብ ንጽህና መግለጫ ነው። ስለዚህ መታደልሽን አክብሪው፤ አፍልቂው ይናፍቅኛልና። ፈጣሪንም አላህንም አመስግኝበት። አደራ!
ይልቁንም ፏ ፍንተው ያለው አፍርሳታ ቅዳሜን በፈገግታሽ ፍካት እና ፏፏቴ አስውቢልኝ እኔ ደግሞ ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ ሁኜ ሳቅሽን በእቅፌ ፍልቅልቅ ብዬ በድንግልና እቀበለዋለሁኝ።
… ዘወትር ቅዳሜ በአፍርሳታ የልብ አድርስ ጭምት ውይይት በቀጣይነት እንደማገኝሽ ተስፋ አደረጋለሁኝ። ሊንክም ስላደረግኩት። ተባረኪ።
· አፍርሳታ ትውፊት ነው። አፍርሳታ ኢትዮጵያዊነት ነው።
አፈርሳታ በኢትዮቱብ የቆዬ ዝግጅት ነው። እከታተለው ሁሉ ነበር። ማህል ላይ ተቋርጦ ነበር። መቀጠሉ ትንሳኤው ነው። እራሱ አፈርሳታ የአገር ጥሪት፤ ትውፊት፤ የሰለጠነ ተደሟዊ የተፈጥሮ ማህበረሰባዊ ህግ አስከባሪ ፍርድ ቤት ነው። በአፍርሳታ ማንነታዊ ተፈጥሮ ልክ በቀጣዩ የሥራ ጊዜ እንዳማገኝሽ ተስፋ አደርጋለሁኝ። በርችልኝ የእኔ ደልዳላ ከብርት እምቤቴ!
· እርማት።
የአንቺ ብቻ አይደለም የሁሉም ችግር ነው። ሚዲያ ላይ እማያቸው ሴት ሊቃናት እንግለዚኛ አብዝተው ይጠቀማሉ። በዬአረፍተ ነገሩ ከሚጠቀሙት አንቺ በበዛ ሁኔታ ትሻያለሽ። ትርጉም ከሌለው በስተቀር እንግሊዘኛውን መጠቀሙ አድማጭን ያለማወቅ ችግር ይመስለኛል። አድማጩ ኢትዮጵያዊ ነው እኮ።፡
ለምሳሌ ጉግል፤ ፌስቡክ ግድ ነው። ወይንም አንዳንድ ጉልበታም ቃሎች በእንግሊዘኛው ቢሆነ እንኳን ኮንፊደንስ፤ አናርኪዝም መጠቀም ቢያስፈልግ በጎኑ ፍቹን ማስቀመጥ ግድ ይላል። ንግግር ነው ያመልጣል። አንድ ቃል ከተሳተ ጠቅላላ ጭብጦ ይናዳል። ቅይጥ ቋንቋ በጣም የሚፈቀደው ለሥነ - ግጥም ጥበብ ነው።
በሌላ በኩል በ „ፐ“ የሚነገሩ አማርኛ ቃላት ወይንም ሥሞች የሉም። ሁሎችም የትውስት ናቸው። … ፖስታ፤ ፖሊስ፤ ፓስታ፤ ፖፖ፤ ፖሊሲ፤ ፓርቲ፤ ፖለቲካ፤ ፕሮጀክት፤ ወዘተ እንኝህን ህዝቡ ለምዷቸዋል። ፍቺ አያስፈልጋቸውም።
በጣም አበክሬ፤ አጠንክሬ እምናገረው ግን አማርኛ ቋንቋ ዲታ መሆኑን ነው። በጣም ጉልበታም ነው። እንዲያውም አማርኛ ቋንቋ ቅኔም ነው። የልብ አውቃ፤ አድርስም ልበ ሙሉ ቋንቋ ነው። ስለዚህ በራሱ አማርኛ ቋንቋ መጠቀሙ ያተርፋል። ውበቱንም ይጠብቃል።
ከላይ እንደገለጽኩት አፈርሳት ትውፊት ነው፤ ትሩፋት ነው፤ ታሪክ ነው፤ እንደራሴ ነው። ስለዚህ እራሱ አፈርሳት ሥሙ ይሞግታል ከራሱ ውጪ የሚያደርጉ ገጠመኝ ሲፈጠሩ። ለመወያዬው ዕልፍኙ ሌላ ቋንቋ ካልቸገረ በቀር መጨመሩ የአፍርሳታን ክብርም ያጫጫዋል። ተፈጥሮውን ይጫነዋል። ይውጠዋል። ቀለሙን ያበልቀዋል።፡
አማርኛውን በአማርኛ ቋንቋ አደርጅቶ፤ አፋፍቶ ማውጣትም ማስተዳደርም ይቻላል። አማርኛ ቋንቋ የራሱ እኔነት ያለው የዳበረ፤ ሥልጡን ግሎባል ቋንቋ ነው።
ቃናው፤ ምቱ ልዩ ነው። አይጠገብም። ለዚህም ነው አብረሻቸው የተማርሻቸው ጓዶችሽ ዝግጅትሽን ለማድመጥ የፈለጉት።
ለዬትኛውም መስክ ለትረካ፤ ለዘገባ፤ ለመዝናኛ፤ ለጥበብ ተግባር፤ ለቲያትር፤ ለፊልም የድምጽ ምቱ፤ ለዛው፤ ላሂው አንቱ ነው። የእስያ ሰዎች ሜዲቴሽን ነው የሚሉት። ልዩ ነው። ፍጽምና የተሰጠው። ስለዚህ በዬአረፍተ ነገሩ ዝንቅ፤ ቅይጥይጥ ለምታደርጉትም ሁሉ እንዲሁ ይህን እርማት ትጠቀሙበት ዘንድ አሳስባለሁኝ። አዚፋ በዶሮ ወጥ ወይንም ቅራሪ በበትኃ ጠጅ እንዳይሆን።
· መውጫ።
እህቴ ሆይ!
አንቺ ከጥሪሽ ጋር ተገናኝተሻል። አንቺ በጥሪሽ ልክ ተግባርሽን ቀጥይ። ስለትርትር እሳቤዎች አቅም አታዋጪ። እነሱን ካዳመጥሽ እምትሰሪው የእነሱን ጥሪ እንጂ የአንችን አይደለም። አትኩሮትሽ ለጥሪሽ ብቻ ይሁን። አደራ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
01.02.2021
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ ከዳማዊቷ ቪንተርቱር።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ፍቅራዊነት ብቻ ያስቀናኛል።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ረጋ ያለችው ደልዳላዋ ጋዜተኛ „ሙኒራ አብደልመናን አውል ማን ናት“
https://www.youtube.com/watch?v=XCRZnbRLr18&t=141s
#Afersata #EthioTube #Ethiopia
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ