ዬዘመኑ ማገዶዎች።

 

እንኳን ወደ ከበቡሽ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

 

ዕለተ ማክሰኞ ማዕዶተ ይግቡ

በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና

በቢሆነኝ የተብራራ ብራ

በሰብለ ሕይወት አዝመራ

ለራህብ የሚራራ።

„ዝም ብዬ የመከራን ቀን እጠብቃለሁ።“

(ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ 3 ቁጥር 17)






 

ማዕዶተ ይግቡ ባለቤት የሌላቸው ሰብዕናዎች፤ ተቋማት፤ ባህርያት፤ ትውፊትወትሩፋት፤ ተቋማት የሚቃኙበት ዕለት ነው።


ባለቤት የሌላቸው ቁምነገሮች አሉ። ሲፈጠሩ ሰብዕናቸው ለቁምነገር የተፈጠሩም ግን ባለቤት የሌላቸው። ማገዶዎች። ትናንትም ዛሬም አቶ እስክንድር ነጋ ካቴና ላይ ነው።

ትናንትም ዛሬም አቶ ስንታዬሁ ቸኮል ካቴና ላይ ነው። ትናንትም ዛሬም ወ/ሮ ቀለብ ስዩም ካቴና ላይ ናት። የሚገርመው ካሳዶጃቸው ጋር አብረው ነው የታሠሩት። የእስኬው ህሊና አንፖል ይመስላቸዋል። የሆነ ሆኖ እንዲህ እንሱ ይመጋዳሉ የሌሎች ሰብዕና ካቴና ያልነካቸው ሰብዕናዎች መወድስ ይሆናሉ።

 በእነሱ አቅም መጤ ሰብዕናዎች ይከብሩበታል፤ ይነግሡበታል፤ ይጵጵሱበታል። ግፉን ማዬት እንዲህ ከውስጥ ይገባል። እልፍኝ ሰርትህ እልፍኝህ ሲዘረፍ። ለዛውም በስልት እና በጥበብ ሳታስጠጣ። ውስጥን ይከረክራል። ሌላውን ማታለል ይችል ይሆናል። እኔን ግን አይታሰብም። ሂደቶችን ሁሉ ከውስጤ ነው እምከታተላቸውና።   


እነሱ ዘመናቸውን፤ ወጣትነታቸውን፤ ትዳር ጎጇቸውን ገብረው ዕድሜያቸው በካቴና እንዲህ ያርጋል። አሁን ደግሞ ወ/ት አስካለ ደምሌ ተጨምራለች። ውስጥን ይመረምራል። ስለሆነም ዛሬ የገጣሚ የባለቅኔ ክቡር ደበበ ሰይፉን ግጥም እነሱን ስለገለጠልኝ አቅርቤዋለሁኝ። በትክክል ይህ ቅኔ ይገልጸዋል።

ደጉ እጬጌው ሂደት የሚገርሙ፤ እራስን የሚፈታትሽ ስርንቅ ዝለቶች እና ዝበቶች፤ ሸፍጦች እና በቀሎች ወደ አደባባይም ብቅ እያደረገልን ነው። በቀን አንድ እኔ አቶ እስክንድር ነጋ እና ቲሙ ሲታሰር የገለጽኳቸው ዕውነቶችም እየፈለቁ ናቸው። ገና ከውጥኑ ጠረኑን በማጥናት የጻፍኳቸው ዕውነቶች ዓይናቸውን አፍጠው እያዬኋቸው ነው።

ትውልዱ ከአቶ እስክንድር ነጋ እና ከቲሙ በጥሞና ሊማረው የሚገባ ቁምነገረን በአስተውሎት ሊመረመረው ይገባል። በዬዘመኑ እንዲህ የላቀ ሰብዕና ተሳትፎ የሰው ሰው ሰብዕና አናፂ ሆኖ ከማዬት ባላይ ማህጸንን እንደ ዱባ የሚቀረድድ የለምና። ዝረፍ ቁስን ህሊና ቢስ ከሆንክ ግን እንደምን መስዋዕትነትን ትዘርፋለህ? ማህከነ!

 

„የክረምት ማገዶች

-----------------------

(በገጣሚ ባለቅኔ ከክበሩ ደበበ ሰይፉ)

 

እንዲህ ተጫጭሰን

እንዲህ ተጨናብሰን፣

ውሃ እንዳለዘዘን

ከውሃ ተዋግተንተዋግተንተዋግተን

ውሃን አሸንፈን፣

እሳትን ፀንሰን

እሳትን አምጠንአምጠንአምጠን

እሳትንም ወልደን፣

እሳትንም ሁነን፤

(የክረምት ማገዶች)

ካጨለጨልንለት የድሃውን ጎጆ፣ ቀሣከል ጭራሮ

ካበሰልንለት ዘንድ፣ የአርሶ አደሩን ንፍሮ

የሠርቶ አደሩን ሕዝብ ለሰስ ያለ ሽሮ፤

ታሪክ ይዘምረው የኛን እንጉርጉሮ።

ዘመን ይመስክረው፤ የኛን ውጣ ውረድ፣

የእንግልት ኑሮ።

---------

1981


ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

05.04.2021

ጎዳናዬ ዕውነት እና መርህ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማዬት ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።