የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ ሃያሲን ሊደፍር ይገባል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ ሃያሲን ሊደፍር ይገባል።
"ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፦
ለወለደችውም ምሬት ነው"
እንዴናችሁ ማህበረ ቅንነት? ልዕልት ኢትዮጵያስ እንዴት አለሽልኝ?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲኮኞቹ ሃያሲን ይፈራሉ፤ ያሳዳሉ፤ ያሳድማሉ፤ ሲቻላቸውም ያጠፋሉ። ይህ የጋራ ባህሪያቸው ነው። ለምን? ሁሉም የግራ ዘመም ርዕዮት ተጠማቂ ስለሆነ። አንድ ፖለቲከኛ ሲሞግት ይቆይ እና እሱ ሞጋች ሲገጥመው ያብዳል። ሁልጊዜ እሱ ከሰማዬ ሰማያት የወረደ ቅዱስ እና ብፁዑ አድርጎ ስለሚወስን።
የሚገርመው ሃያሲ የሚሳደደው፤ የሚወገረው በደቦ ወይንም በወበራ ነው። ይህም ሬድሜድ ነው። በፖለቲካ ህይወት ውስጥ ሃያሲ ተፈርቶ ተስፋ ጥግ ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም። ሃያሲያን ሲሳደዱ የመተንፈሻ ቧንቧ ሲፈልጉ አንድ ቀን በለስ ከቀናቸው አሳዳጃቸውን የሚጎዳ ተግባር ሊፈጽሙ ያችላሉ። ለትውልድ፤ ለአገር የሚታሰብ ቢሆን ደፍረው ወጥተው ሳይከፈላቸው የሚሰማቸውን ግልጽ እና ቀጥተኛ ሆነው ሳያሽሞነሙኑ የሚያሄሱ ወገኖች ሊከበሩ ይገባል ባይ ነኝ።
መዳኛው መንገድ ያ ብቻ ስለሆነ። ኢትዮጵያ ተፈጥሯዋ ለግራ ፖለቲካ የተመቸ አይደለም። "ዕውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር "የሚለው ብህሊ እንቅጭ እንቅጩን ተነጋግረን ዕውነትን እናፍልቅ ነው። ሌላም አለ እከሌ አቶ ሀ የግንባር ሥጋ ነው ይባላል። ያ ማለት ዕውነት ይደፍራል፤ ለዓላማው ሟች ነው ማለት ነው።
#አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ……
ሀ) ደጋፊ አለ።
ለ) ተጠማኝ አለ።
ሐ) ተደማሪ አለ።
መ) ተዋህጂ አለ።
ሠ) ተቀናቃኝ አለ።
ረ) ተፎካካሪ አለ።
ሰ) ተቃዋሚ አለ።
#የተሳትፎ ደረጃ
1) ቀጥተኛ ተሳታፊ።
2) ተዘዋሪ ተሳታፊ።
3) ተመልካች።
4) ተቀማጭ።
5) ታዛቢ።
6) አያገባኝም ባይ።
1) ሰላማዊ።
2) ትጥቅ።
3) መሃል ሰፋሪ።
4) የአደባ።
5) ገለልተኛ።
6) ቅይጥ።
#መብት።
በኢትዮጵያ መብት ልሙጥ ነው። አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን ሥርዓት መደገፍ እንደ መብት አይታይም። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለውን ሥርዓት በዬትኛውም መንገድ መሞገት መብት አይደለም። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲካ ዲሞክራሲ ሰማይ ቤት ያለ ክስተት ነው።
#ግዴታ።
መብት ካለ ግዴታ ይኖራል። ግዴታ ከመጣም መብት ይጠዬቃል። የሁለቱ መስተጋብር ተፈጥሯቸው በሚፈቅደው ልክ ዕውቅና አይሰጣቸውም በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዘንድ። ስለዚህ በመብት እና ግዴታ ውስጥ ተመስጥሮ የሚገኙት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት አዬር ላይ ተንሳፈው ስደተኛ ይሆናሉ ማለት ነው።
በዚህ ውስጥ ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን በቅጡ አውቆ አዳራን ሊወጣ የሚችል ማህበረሰብ እንዴት ይፈጠራል? አጀንዳ ሆኖ የማያውቅ በኽረ ጉዳይ ነው። ዲስኩር ሳይሆን እያዬ የሚማርበት፤ እያደመጠ የሚያስተውልበትዕድል ትውልዱ አልተሰጠውም።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወረርሽኝ በሽታው ደራሽነት ነው። ሞቅ ያለ ህዝባዊ ንቅናቄ ከኖረ የሚዲያ ምስረታ፤ የፖለቲካ ድርጅት ፈጠራው ይጦፋል። ይህም ብቻ አይደለም ዜናወች፤ መረጃወችም በደራሽ ጎርፍ ይጥለቀለቃሉ። ደራሽነት ለሰከነ አዕምሮ ግንባታ ፀር ነው። አንዱን ይዞ አንዱን አንጠልጥሎ ይሆናልና።
#ጥሞና።
በኢትዮጵያፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ጥሞና ተፈሪው አመክንዮ ሲሆን ደፋሪ የለውም። በጥሩ ሁኔታ ጥሞናን ተግባር ላይ አዋለ ብዬ እማስበው ለምልክት አቶ ጃዋር መሐመድ ነው። ያም በመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በክፍል ፩ እና በክፍል ፪ አርተስ ጋር በነበረው ቆይታ ወደ ፫ ሚሊዮን አድማጭ ነበረው። ሪከርድም ሰብሯል። ከእሱ በፊትም በውል አልተስተዋለም እንጂ አርበኛ ዘመነ ካሴም እራሱን ከሁሉም ነገር ገለል አድርጎ የቆዬበት ሁኔታ ነበር። የቀደመም ነበር። ይህ ስክነት፤ ይህ ዕርጋታዊ ውሳኔ ጠቃሚ ጎዳና ነው። የተርገበገበ፤ የተጣደፈ የተርገበገበ ሂደት ክንውኑን ተንዘፍዛፊ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲካ ፈንጣጣዊ ድዌደግሞ አምልኮ ነው። አንድ ሰው በህሊና ይኮፈሳል። ያ ሰው ስድስት ክንፍ አለው። ፃድቅ ነው። ከእሱ ድርሽ የሚል ከኖሮ አገር ምድሩ ይታወካል። ወጀብ ይነሳል። ሃሳቦች ጥግ አጥተው ባክነው ከስለው ይቀራሉ። ጠቃሚ፤ ገንቢ፤ አዳሽ፤ ተንከባካቢ፤ አዳኝ ቢሆን ያ ሃሳብ ልዑሉ ባለ ገበርዲን ከተነካሹግ ሆነው የሚነሱ ተከላካዮች ሃያሲውንም አዳኙን ሃሳብንም አሳደው ድብዛውን ያስጠፋታል፤ ሃሳብ አቅራቢው እስከ ቤተሰብ የዘለቀ ጨንገር ሆነ ጦሮ ይታዘዝበታል። በዚህ ምክንያት ሃያሲያን የነበሩ ሁሉንም እርግፍ አድርገው ወደ ሳይለንት ማጆሪቲ ሊጠቃለሉ ይችላሉ።
#ነገን በዕሳቤ አልቦሽ።
ተስተውሎ የማያውቀው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እና ፖለቲካው ነገ ምን ሊመጣ፤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አለማሰብ ነው። ተንባይ አይደለም የኢትዮጵያ ፖለቲካ። በደራሽ አመክንዮ ሲተራመስ ነገ ምን እና ምን ተስተጋብረው እንደሚመጡ ተስተውሎ አያውቅም። አሁን ጋዜጠኛ መሳይ "ህወሃት እና የአማራ ፋኖ አንድ ላይ ቢሰሩስ?" የሚል አጀንዳው ይሆናል ብሎ ማን ያስብ ነበር? ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ህወሃት ይሻለናል የሚል መንፈስ ያላቸው ስለመገጥሙ ዘግቦ ለእስር፤ ለውግዘት ተዳርጎ ነበር። ዛሬስ? ዛሬ ሌላ ዘፈን መጥቷል። የአማራ መደራጀትን ውግዝተአርዮስ ያሉ ዛሬ ፋና ወጊ ሆነዋል።
እና እናማ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተግትን በትጋት፤ እርጋታን በጥሞና ይጠይቃል እንደማለት። መቀያዬሙ፤ መጠራረቡ፤ መፋለጡም በብልህነት ቢስተዳደር እንላለን። ፍላጎትን አውቆ፤ ፍላጎትን ለማሳካት የደጉን ዘመን አስተውሎት መቃኜት ይበጃል። እንደ አባት አደሩ።
በቻይነት ለናሙና ፕ/ ብርሃኑ ነጋን መውሰድ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ተምሳሌት ይመስለኛል። ለአገር እና ለአህጉር መሪነት የታጩት ፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ በተመክሯቸው መሪነት የደረሱበት ውሳኔና የሚወርደው ወጀብ ተቋቁመው ዝቅ ብለው ህዝብን ለማግኜት በአስተዳደር ዘርፍ፤ በፖለቲካ ድርጅታቸው ያላገኙትን የመንፈስ ፍላጎት በስሱ ለማስፈፀም ዕዱሉን መጠቀማቸው የመቻል አቅማቸውን ያሳያል። በሂደቱ እንደ ሰውግድፈት መፈጠሩም፤ እሳቸውን የበለጠ እናውቅ ዘንድ ረድቶናል። ከሁሉ የገዘፈው ዕውነት ለእኔ ግን የቀደሙ ዕድልን የማሹለክ ሂደት ሳይደግሙ በአገኙት አጋጣሚ መጠቀማቸው አዲስ የልምድ ተመክሮ ከፍ ባለ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ቦታ መስራት መቻል የመቻል ሸማ ይመስለኛል።
ፓርቲያቸው ኢዜማ ሲደራጅ መንግሥት እና ፓርቲ ሆኖ የአደረጃጀት መርህን ተከትሎ ስለነበር ጥምረት ቢፈጥርም፤ እራሱን ችሎ ቢቀጥልም የተሻለ ዕድል ያለው ይመስለኛል። ከ97ቱ ግድፈትም እራሱን አርሞ እራስን በመቻል ፈተና ውስጥ ማሳለፍ መቻል የሰከነ ጉዞ ይመስለኛል። በዚህ ውስጥ የትግሉን ሙቀት እና ቅዝቃዜም እያስተዋለ እራሱን ሳያሰምጥ ለተሻለ ዕድል የሚተጋም ይመስለኛል። በባህሉ የእኔ የሚላቸውን በጥንቃቄ የመያዝ ጥበብ ስላለው። በሁሉም ቦታ መንፈሱን የማብቀል አቅሙም ይህ ባህሉ ይመስለኛል።
ይህ ሃሴቤ አብን በዚህ መልክ አዬዋለሁ ማለት አይደለም። ፈጽሞ። አውዱ ሌላ ቃና አለውና። የሆኖ ሆኖ ፕ/ ብርኃኑ ነጋ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሰጡትን ተከታታይ መግለጫወችንም ከልቤ ሆኜ አዳምጨዋለሁኝ። መሬት ላይ በአገኙትዕድል ተጠቅመው የህዝብ አገልግሎት እዬሰጡ ከፖለቲካ ፓርቲያቸው ጋር ልምዱን እንደምን እንዳዋህዱት መመዘን እሻ ስለነበር አጋጣሚውን ተጠቅሜበታለሁ።
ከሁሉ የሚደንቀኝ የሚገርመኝ የጠሚር አብይ ስሜት ቅጽበታዊ፤ ተለዋዋጭ እና ስኩን ስላልሆነ በሲቃ ሰብዕና ሥር ሆኖ መሥራት ምን ያህል ጋዳ እንደሚሆን አስባለሁኝ። በቤተሰብ ሲቃ ሰብዕና ካለው የቤተሰብ አባል ጋር መኖርን ማኖር እንደምን የገዘፈ ፈተና መሆኑን ስለማውቅው።
#ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና የፖለቲካ ድርጅት መሪነት።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያልተመደው ሁነት ይህ ይመስለኛል። ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማለት ለመሪነት ብቁ ያደርጋል ማለት አይደለም። ለመሪነት ብቁ የሚያደርገው የአንድ ቀበሌ መሪ ሆኖ ህዝብን በህይወቱ ውስጥ ሆኖ ኑሮውን ኑሮ ማገልገል ሲቻል ይመስለኛል። ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚኮነው በዬትኛው ዘርፍ ነው ብሎ ማጥናትም ይገባል። ለዚህ ግሎባላይዜሽን ዘመን ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ታላቅ ትምህርት ቤት ናቸው ብዬ አስባለሁኝ። ትርፍ እና ኪሳራውን መዝኑት።
#ቅብዓ።
መሪነት ቅባዕም ነው። ይህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቦታ ተሰጥቶት የማያውቅ ክስተት ነው። ይህንንም እንደ አጀንዳ በብልህነት መመርመር ያስፈልጋል። መሪነት ቅብዓ ብቻሳይሆን አቅል፤ አደብ፤ ጀምሮ መጨረስን፤ እራስ ላፀደቁት ደንብ እና ህግ ፈቅዶ መገዛትን፤ አናርኪዝምን መጠዬፍን። የሥራ ደንበርን፤ ወሰንን ጠንቅቆ ማወቅን። ቃል መጠበቅን። በራስ አቅም ልክ መመኜትን። በራስ ጥረት ላይ የተገኙ ውጤቶች ላይ አትኩሮት በበቂ መስጠትን። ሞቅ ካለው ሁነት ላይ አለመዶልን። አትኩሮትን በራስ ትትርና ውስጥ ማስከንን። ለጥፋት ምክንያትነት እንዳይመጣ መጠንቀቅን። አዛኝነት እና አይዟችሁ ባይነትን ማስቀደምን ይጠይቃል።
መሪነት መወጠን ሳይሆን የወጠኑትን ለግብ ማብቃትን ይጠይቃል። በፈተና ውስጥ ሆነው መሪነቱን ተቀብለው የተጉትን ዕውቅና ሰጥቶ ማመስገን፤ ማክበር እና ማዝለቅን እንጂ በትኖ መሄድን አያካትም። ወደሌላ ኃላፊነት እና ጥሪ ሲከድ መጀመሪያ በተደራጀው ውስጥ ያሉ አባላት፤ አካላት፤ ደጋፊ፤ ተባባሪ ደጋፊ ተቋማትን ሁሉ ማመስገን የመሪነት ጥራት እና ብቃት ነው። በኢትዮጵያ ደግሞ ያልተለመደ መከራ ነው።
የኢትዮጵያ ወላጆች ለአንድ ፔና፤ ለአንድ ከፈን ያላበቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ልጆቻቸው ሲመለመሉ ፈቃድ አይጠዬቁም። ሲሰውም ዋጋቸው መና ይሆናል። ይህም ሆኖ ዛሬም ይገበራሉ፤ ይገብራሉም። ይህን ግምት የሚሰጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ የለም። ሁልጊዜ አንጋቼ፤ የምንጊዜም ተማጋጅ ሁንልኝ በውነቱ ግፍ ነው። ብልህ መሪወች ግን ውለታ አይረሱም። መስዋዕትነቱንም ይቀንሳሉ በኢትዮጵያ ባይለመድም።
#ክውና።
ሃያሲያን ስጦታወቻችን ናቸው። ዕውቅና ይሰጣቸው። ይከበሩም። ይሞገቱም። ሥልጣን ላይ ያለው የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ አገዛዝ፤ ተጠማኝ፤ ተደማሪ፤ ተቀላች፤ ተዋህጂ፤ ተፎካካሪ፤ ተቃዋሚም ለመደገፍም ለመቃወምም ሙሉ መብት ሁሉም አለው። የዜግነት እሮቦ እና ሲሶ የለውምና። ሁሉም የህሊና ነፃነት አለው። ሁሉም የራሱ ጌታ እና እንደራሴ ነው።
ሰክኖ ማሰብ እራስን በደራሽ ኩነቶች አለማስዋጥ። ትውልዱ እና ተስፋው እንዲገናኝ ጥሞናን ምራኝ ማለት ያስፈልጋል።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/04/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ