በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ወደ ግጭት ያመራ ይሆን? ድርድሮችስ ውጤታማ ይሆናሉ? bbc
https://www.bbc.com/amharic/articles/c7498yd93e7o
በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ወደ ግጭት ያመራ ይሆን? ድርድሮችስ ውጤታማ ይሆናሉ?
19 መስከረም 2024
በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ እየመጣ ነው። አንደኛው ውጥረት በኢትዮጵያ በሶማሊያ መካከል ያለው ነው። ሁለተኛው ደግሞ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል።
በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል እየተካሄደ ያለው የቃላት ጦርነት በተለይ ካለፉት ቅርብ ሳምንታት ወዲህ እየተባባሰ መጥቷል። ይህ ደግሞ ወደ ቀጥተኛ አሊያም የእጅ አዙር ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ጭሯል።
ከሁሉም የላቀ አስጊ የሆነው ሶማሊያ በከተሙት የግብፅ እና የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች መካከል ግጭት እንዳይነሳ ነው።
ሶማሊያ በአውሮፓውያኑ መስከረም 16/2024 ለምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በላከችው ደብዳቤ ድርጅቱ ጉዳዩን እንዲያሸማግል ጠይቃለች። ይህ ምናልባቱ ውጥረቱ ሊበርድ ይችላል የሚል ፍንጭ ሰጥቷል።
እዚህ እንዴት ደረስን?
በአውሮፓውያኑ ነሃሴ 26 2024 ምሽት ሁለት አውሮፕላኖች የጦር ሠራዊት እና ወታደራዊ ቄሳቀሶች ጭነው የሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ አረፉ። በተመሳሳይ ሳምንት አንድ ገለልተኛ የሶማሊያ ድረ-ገፅ 1 ሺህ የግብፅ ወታደሮች ሶማሊያ መግባታቸውን እና ሁለቱ አገራት መስከረም ወር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ማቀዳቸውን አስነበበ።
መስከረም 12/2024 የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንግሥታቸው መቼ እና እንዴት የግብፅ ወታደሮች በሶማሊያ ይሰማራሉ ስለሚለው ጉዳይ ውሳኔ ላይ አለመድረሱን አሳወቁ። ነገር ግን ይህ የሁለቱ አገራት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ላይ ስጋት መጫሩ አልቀረም።
ግብፅ በበኩሏ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች ትገኛለች። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ደግሞ በተቃራኒው እየቀዘቀዘ ይገኛል።
ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ሌላ የውጥረት ምንጭ የሆነ ጉዳይ ውሉ ባልታወቀበት ወቅት ነው።
ባለፈው ዓመት ጥር ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር አንድ የመግባቢያ ስምምነት ላይ ትደርሳለች። ይህ ሰነድ ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ-ሰላጤ የባሕር ኃይል እንድትገነባ እና የባሕር በር እንዲኖራት የሚያትት ሲሆን በምትኩ ኢትዮጵያ የሶማሊላንድን አገርነት በይፋ እውቅና ትሰጣለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ አገራቸው የባሕር በር ማግኘት እንዳለባት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 2018 ወደ ስልጣን የመጡት ዐቢይ፣ መንበሩን ከተቆናጠጡ ከአንድ ዓመት በኋላ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የባሕር ኃይል አቋቋሙ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እርቅ በማውረድ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለውን “ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታ” አሻሻሉ።
ከሶማሊያ እና ኤርትራ ጋር “ቀጣናዊ የምጣኔ ሀብት ትብብር” ቢመሰርቱም ለንግድም ሆነ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚሆን የባሕር በር ማግኘት አልቻሉም።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 11/2023 ዐቢይ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ቀይ ባሕር “ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ብለው አገራቸው የባሕር በር ከማግኘት ውጭ “ምንም አማራጭ” እንደሌላት አስታወቁ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቴሌቪዠን ጣቢያ ይህን ጉዳይ ሲያራግበው የቆየ ሲሆን በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ከስምምነት ደረሱ።
ነገር ግን ሶማሊላንድ የራሷ ግዛት አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ በዚህ ስምምነት ደስተኛ አለመሆኗን በተደጋጋሚ ከገለፀች በኋላ ከግብፅ ጋር ስምምነት ፈረመች። ግብፅ ደግሞ አባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት የሻከረ ነው።
ሶማሊያ ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በሀገሪቱ የአል-ሸባብ ታጣቂዎችን ሲዋጉ የነበሩ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላትን ለማስወጣት እና በምትካቸው በአፍሪካ ሕብረት የፀጥታ ሚሽን መሠረት የግብፅ ወታደሮችን ለማሰማራት ቃል ገባች።
ግብፅ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ልትልክ ትችላለች የሚል ስጋት አለ። ይህ ደግሞ በአባይ ግድብ ላይ ጫና ለማሳደር ነው የሚሉ ትንታኔዎች ይደመጣሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ የግብፅ ወታደሮች ወደ ሞቃዲሾ የሚመጡ ከሆነ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ከሶማሊያ እንደማታስወጣ አስጠንቅቃለች።
የሶማሊያ መንግሥት ከግብፅ ጋር በደረሰው ስምምነት ምክንያት በውስጣዊ ፖለቲካ እየታመሰ ይገኛል።
አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ወታደሮች የተሰማሩት ጌዶ፣ ባይ እና ባኩል በተሰኙ የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ሥፍራዎች ሲሆን እነዚህ ቦታዎች ከሶማሊያ ጦር ቁጥጥር ውጭ ናቸው። የደቡብ ምዕራብ ክልል በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር መቀጠል እንደሚፈልግ ይገልፃል።
ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ፑንትላንድ ነባር ፖለቲከኛ የሆኑ ግለሰብ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግጭት “ሶማሊያን መጠቀሚያ እያደረገች ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
ማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥት ይህን ውስጣዊ ችግር ለመግታት እየጣረ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል መዲና ባይዶዋ መጥተው ከክልሉ ፕሬዝደንት ጋር መክረዋል።
ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል?
ኢትዮጵያ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ክልሎች ከ8000 እስከ 10000 የሚገመቱ ወታደሮች አሏት። 3 ሺህ የሚሆኑት ወታደሮች በአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ሚሽን በሶማሊያ (አቲምስ) ሥር የሚንቀሳቀሱ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ አሁን ከተፈጠረው ውጥረት በፊት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ባደረጓቸው ስምምነቶች የመጡ ናቸው።
በሶማሊያም ሆነ በኢትዮጵያ በኩል የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በ1977 የተከሰተውን ጦርነት እያነሱ ፕሮፖጋንዳ ሲያስደምጡ ተስተውለዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በጉዳዩ ደስተኛ አለመሆኗን በንግግርና በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
የግብፅ አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ገብተው ማረፋቸውን ተከትሎ ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ኃይሎችን እያስጠለለች ነው በማለት አስጠንቅቃለች።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በፈረንጆቹ ነሃሴ ወር መጨረሻ እንደዘገቡት ከሆነ የአገሪቱ ጦር ከሶማሊያ ጋር ድንበር ወደ ምትዋሰነው ምስራቃዊቷ ሶማሊ ክልል አድርጎ አዲስ የአየር ኃይል መቀመጫ ሊያቋቁም ነው። በሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጌዶ ክልል የሚገኙ ሁሉንም አየር ማረፊያዎች መቆጣጠራቸውም ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ የግብፅ ወታደሮች በሶማሊያ የሚሰማሩ ከሆነ ሶማሊያም ሆነች የአፍሪካ ሕብረት ቢፈቅዱም ባይፈቅዱም ወታደሮቼን አላስወጣም ማለቷ ለሞቃዲሾ ስጋት ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚሞክር “አስር ጊዜ ቢያስብበት ይሻላል” ማለታቸው ይታወሳል።
በፈረንጆቹ መስከረም ወር መባቻ ለምስራቅ ዕዝ ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ጦር ሠራዊታቸው ማንኛውንም “ተስፋፊ ኃይል” ለመመከት ዝግጁ ነው ብለዋል።
አንድ የኢትዮጵያ የበይነ-መረብ ቴሌቪዥን ጣቢያ በለቀቀው በድብቅ የተቀዳ ድምፅ መሠረት፣ የጦሩ መሪ ብርሀኑ ጁላ ግብፅ የኢትዮጵያ “ታሪካዊ ጠላት ናት” በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ታጣቂ ኃይሎችን ትደግፋለች ሲሉ ወቅሰዋል።
የድርድር ሙከራዎች እየተሳኩ ነው?
በያዝነው ሳምንት ሶማሊያ ለኢጋድ በላከችው ደብዳቤ ድርጅቱ እንዲያሸማግል ጠይቃለች። ይህ ምናልባት ሞቃዲሹ ሁኔታውን ለማለሰላስ ማሰቧን ይጠቁም ይሆናል።
ቱርክ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። ይህ ድርድር በከሸፈ ማግስት ነው ሶማሊያ ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የፈፀመችው።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በመካከላቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡ ጠይቀዋል። ሶማሊያ ከግብፅ ጋር የገባችው ስምምነት ኢትዮጵያ በእጅጉ ያስቆጣ ነው። በአውሮፓውያኑ መስከረም 17 ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ውይይት እንዲራዘም ተደርጓል።
ሶማሊያ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር ያለመስማማት ውስጥ ስትገባ የምትማትረው ወደ ቱርክ ነበር። ነገር ግን ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ቱርክ ሁለቱ አገራት ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ እየጠየቀች ነው።
ሶማሊያ፤ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን የስምምነት ሰነድ ካልቀደደች በቀር ውጥረቱ አይረግብም ትላለች። ይህ ከሆነ በኋላ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት በውይይት የባሕር በር ታገኛለች የሚል አቋም አላት። ኢትዮጵያ ደግሞ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ዓይነት ስምምነት ካልሆነ እምቢኝ ብላለች።
ትንሿ የአፍሪካ ቀንድ አገር ጁቡቲ ደግሞ ሁኔታውን ለማርገብ “በጋራ የሚተዳደር” የባሕር ባር ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል ገብታለች። ኢትዮጵያ ለ95 በመቶ የወጪና ገቢ ንግዷ የጂቡቲን ወደብ ነው የምትጠቀመው። ይህ ማለት ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በስምምነታቸው ከገፉበት የገቢ ምንጯ ይንጠፈጠፋል ማለት ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ