"በኮማንድ ፖስት ሥር ያሉ ክልሎች በፌዴራል እስረኞች መጨናነቃቸውን አስታወቁ" BBC
https://www.ethiopianreporter.com/136872/
በኮማንድ ፖስት ሥር ያሉ ክልሎች በፌዴራል እስረኞች መጨናነቃቸውን አስታወቁ
"በአሁኑ ወቅት በኮማንድ ፖስት ሥር ካሉት ክልሎች መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች በፌዴራል እስረኞች ተጨናንቀው መፍትሔ አጥቻለሁ ሲል፣ የጋምቤላ ክልል በበኩሉ የክልሉ ፖሊስ አፋጣኝ ምላሽ እንዳይሰጥ የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ሀብቱን እየተሻሙት መቸገሩን ገለጸ።
የክልሎቹ ተወካዮች ይህንን የገለጹት በወንጀል ተጠርጥረው ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶች አተገባበርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው፣ ብሔራዊ ምርመራ ሒደት፣ ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች አተገባበር ላይ ከተለያዩ ክልሎች ከተሰባሰቡ የፍትሕ አካላት ተወካዮች ጋር ባለፈው ሳምንት ባደረገው ውይይት ነው።
በውይይቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተወካይ በማረሚያ ቤቶችና በፍርድ ቤቶች መካከል ሰፊ ርቀት መኖሩን ገልጸው፣ ከማረሚያ ቤት ለፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮዎች በፍጥነት ለመውሰድና ለመመለስ ፖሊስ እየተቸገረ መሆኑንና ጉዳዩም መፍትሔ አለማግኘቱን ተናግረዋል።
ከክልሉ ቢሮ ጋር በመጻጻፍ በእስር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎች መብታቸው እንዳይጣስ እየሠራን ነው ያሉት ተወካዩ፣ የቦታ ጥበት በመኖሩ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር በመተከልና በአሶሳ ዞኖች የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ላይ የማስፋፊያ ግንባታ እያከናወኑ መሆኑን አሳውቀዋል። ይሁንና ከምንም በላይ በፌዴራል መንግሥት እስረኞች መቸገራቸውን ገልጸዋል።
‹‹በክልሉ እያጨናነቀን ያለው የፌዴራል እስረኞች ጉዳይ ነው። በርካታ የፌዴራል እስረኞች ነው ያሉት። 250 የፌዴራል እስረኞች አሉን። እነዚህን የፌዴራል እስረኞች በተመለከተ በተደጋጋሚ ጊዜ ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ጋርም እንጻጻፋለን። ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይጣስ በጊዜ መፍትሔ ማግኘት አለባቸው ብንልም፣ ምንም መፍትሔ አላገኘንም፡፡ ችግሩን መጥተው እንኳን የማያዩበት ሁኔታ አለ፤›› ብለዋል።
ስለፌዴራል እስረኞች ሁኔታ ሌላው የክልሉ ተወካይም ዝርዝር ጉዳዮችን አቅርበዋል። ‹‹ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተለያዩ ክልሎች ጋር አዋሳኝ እንደመሆኑ መጠን እንደ ቅርበታችን ከኦሮሚያ የሚመጡ ተጠርጣሪዎች ይኖራሉ። በክልላችን ከተያዙ በኋላ ምርመራው የሚጣራው አንደኛ በፌዴራል ነው፣ ሁለተኛ ደግሞ መረጃውና ማስረጃው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው፣ ሰውየው የሚታሰረው ደግሞ እኛ ክልል ውስጥ ነው። በዚህ ሒደት በየጊዜው ተጠርጣሪው ላይ የሰባትና የ14 ቀናት ቀጠሮ ይጠየቃል። እየተጠየቀ ነው ገና ማስረጃው እየመጣ ነው እየተባለ፣ ተጠርጣሪዎች እስከ ስድስት ወራት ድረስ ያለ ምንም ምክንያት የሚታሰሩበትና ከዚያ በኋላ የሚፈቱበት ሁኔታ አለ፤›› ሲሉ አብራርተዋል። በአማራ ክልል በኩልም እንዲሁ ከፋኖ ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ሰዎች እንደሚታሰሩ ጠቅሰዋል።
‹‹ከፋኖ ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥረው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ከተያዙ በኋላ ከዚያኛው ወገን መረጃዎችን አምጡ አታምጡ ወደ ፍርድ ቤት ለማምጣት ችግር እየተፈጠረ የዜጎች መብት እየተጣሰ ነው፤›› ብለዋል።
ክልሉ በአሁን ወቅት በኮማንድ ፖስት ሥር እንደሚገኝ የገለጹት ተወካዩ፣ ከኮማንድ ፖስት ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ የራሱን መብትና ግዴታውን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ተናግረው፣ ለዚህም ምክንያቱ ስለጉዳዩ በቂ መረጃ ማለትም ኮማንድ ፖስቱ ምን ይገድባል የሚለውን ባለማወቁ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሰዎች ሲንቀሳቀሱ ወይም ደግሞ አንድ ክስተት ሲገጥም ለእስር እንደሚዳረጉ ገልጸው፣ ተጠርጣሪዎችን የማሰር ሒደቱ በኮማንድ ፖስት ሥር አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል።
‹‹በኮማንድ ፖስት ሥር ያለው የፍትሕ አካላት የተጠያቂነት ሥርዓት ትስስር ስለሌለው ተጠያቂነት የለም። ይህንን በጥልቀት ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ የተጠያቂነት ሥርዓቱ መዘርጋት አለበት። ሰው በግንዛቤ እጥረት ምክንያት መታሰር የለበትም፤›› ብለዋል።
በኢሰመኮ ውይይት ላይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካይ በበኩላቸው፣ ከጎረቤት አገር በሚነሱ ታጣቂዎች ጥቃቶች ሲደርሱም ሆነ በክልሉ ውስጥ ችግሮች ሲፈጠሩ፣ የክልሉ ፖሊስ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት መቸገሩን ገልጸዋል።
‹‹ለእኛ አሁን በጣም ከባድ ችግር ከሙርሌ ጋር የተያያዘው ነው፣ ጥቃት አለ። መንገዶች አስቸጋሪ ናቸው። የሙርሌ ታጣቂዎች የሚመጡት በሦስትና በአራት አቅጣጫ ነው። ምላሽ ለመስጠት መንገድ የለም። አንዳንዴ ጥቃቶች ሲከሰቱ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ፖሊስ እየተቸገረ ሕዝቡ ችግር ላይ እየወደቀ ነው፤›› ብለዋል።
በጋምቤላ ክልል ተቋማዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በእነዚህ ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ አለመሆኑን፣ እስከ ክልላዊ ከፍተኛ የመንግሥት መዋቅር ደረጃዎች ድረስ እንደሚገኝም ተወካዩ ገልጸዋል።
ፖሊስ ለጥቃቶችና ለሚፈጠሩ ክስተቶች ፈጥኖ መድረስ አለመቻሉን በተመለከተ ሲያስረዱ፣ ‹‹እንደ ጋምቤላ ፖሊስ ፈጣን ምላሽ እንዳይሰጥ የሚያደርጉ ከፍተኛ ጫናዎች አሉብን። የፖሊስ ፓትሮል መኪናዎች በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ለመከላከያና ለፌዴራል ፖሊስ ይሰጣሉ። ፖሊስ በምላሹ ችግሮች በሚፈጠሩበት አካባቢ በጊዜ መድረስ እንዳይችል ሆኗል። መከላከያና ፌዴራል የራሳቸው ፓትሮሎችና መገልገያዎች አላቸው። ይህ ጉዳይ ክልላዊ ዕርምጃ እንዲወሰድበት ነው ጥያቄያችን። ፖሊስ እንዲህ ዓይነት ክፍተት ካለበት ሥራውን እንዴት በስኬት ይሠራል?፤›› ሲሉ ጠይቀዋል።
የሁለቱ ክልሎች ተወካዮቻቸው ኢሰመኮ በወንጀል ተጠርጥረው ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶች አተገባበርን በተመለከተ ያደረገው ብሔራዊ ምርመራ፣ በቀጣይ በክልሎቻቸው እንዲካሄድ የጠየቁ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር በተካተተው አሁን ራሱን የቻለ ክልል የሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር በበኩላቸው፣ በኮንሶ ካለው ችግር ውጪ አሁን ችግሮች በሰፊው ተቀርፈዋል ብለዋል።
ሪፖርቱ የቆየ ነው ያሉት ኃላፊው፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በላይ ማሳለፉን ጠቅሰው፣ በምርመራው የተገለጸው ግኝት የቆየውን ክልል የነበረበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው፣ አሁን ችግሮቹ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፈዋል ባይባልም በጣም ቀንሰዋል በማለት በሰነዱ በተቀመጠው ልክ ነው ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል። ይሁንና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ከጋምቤላ ክልል ጋር በተመሳሳይ በመከላከያ በኩል ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሆነም አሳውቀዋል።
‹‹በእኛ ክልል ከፍተኛ የሆኑ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች አሉ። አንዳንዴ ኮማንድ ፖስት ይሆንና የሚታሰሩ ሰዎች አሉ። ኮማንድ ፖስቱን በአብዛኛው የሚመራው መከላከያው ነው። መከላከያው ለክልሉ ፖሊስ አሳልፎ ካልሰጠ በስተቀር አንዳንዴ ምርመራ የማይጀመርባቸው ሁኔታዎች አሉ። አንዳንዴም ኮማንድ ፖስቱ አሠልፎ ለክልሉ ፖሊስ ካልሰጠ በስተቀር፣ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚታሰሩ ሰዎች አሉ። አንዳንዴ በጣም ነው የምንቸገረው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ገፍተን ሄደን ከእነሱ ጋር በመነጋገር ተጠርጣሪዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ገብተው ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶ በእንዲህ ዓይነት ሒደቶች ውስጥ እንዲያልፉ የማድረግ ሥራዎችን ግን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል።
ክልሉ በ24 ሰዓት ውስጥ በየፖሊስ ጣቢያው በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎችን ጉዳይ ሪፖርት የሚያቀርብበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቅሰው፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ተጠርጣሪዎች የሚታሰርባቸው ዞኖችም መለየታቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ለአብነት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጌዴኦና የጎፋ ዞኖችን አንስተዋል። በሌላ በኩል በዋስ ዕጦት በእስር የሚቆዩ ሰዎች መኖራቸውን፣ እንዲሁም ማረሚያ ቤት የሌላቸው ዞኖች እንዳሉም ገልጸዋል።
‹‹በዋስ ዕጦት የሚታሰሩ ሰዎች አሉ። አንዳንዴ ጉዳያቸው በጣም ቀላል ሆኖ ፖሊስ በራሱ ጊዜ በራሱ ዋስትና መልቀቅ እየቻለ፣ ሰዎች ታስረው የሚቆዩባቸውን ፖሊስ ጣቢያዎች ለይተናል። ኮሬና ኮንሶን መጥቀስ እንችላለን፤›› ብለዋል። ‹‹ኮንሶ፣ ጉጂና ኮሬ ማረሚያዎች የሉንም። ከእነዚህ ቦታዎች መጥተው ተጠርጣሪዎች አርባ ምንጭ ያሉባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከዚህ አንፃር ለዓቃቤ ሕግ ቶሎ ውሳኔ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር ግብረ መልስ ሰጥተናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በኮንሶ ዞን ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል። በቅርቡ በመሬት ምክንያት በተቀሰቀሰ ግጭት 11 ሰዎች መገደላቸውን፣ በሰዎቹ ግድያ ምክንያት የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማረጋጋት ወደ አካባቢው ከተንቀሳቀሰው ፖሊስ ሠራዊት መካከል ተጨማሪ ስምንት የፖሊስ አባላትና የሌሎች አምስት ንፁኃን ዜጎች ሕይወት ማለፉንም አሳውቀዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ጉዳዩን በእኛ በኩል አጣርተን፣ ከእኛ ብቻ ሳይሆን ከፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ዘርፍ መጥተው ምርመራ ተካሂዷል። የምርመራው ውጤት ለፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ተላልፎ ተሰጥቷል። ወደ 90 ሰዎች አካባቢ ነው የነበሩት፡፡ ከእነዚያ ውስጥ በድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩት 13 ሰዎች ተለይተዋል። ከዚያ ውጪ ሌሎቹ አልተያዙም። ምርመራ ቀጥሏል፣ ግን ጉዳዩ ለፌዴራል ፖሊስ የማስተላለፍ ሥራ ተሠርቷል፣ ምርመራ ላይ ነው ያለው፤›› ብለዋል።
በደቡብ ምዕራብ ስለሚነሱ የዞንነት፣ የልዩ ወረዳነትና የክልልነት ጥያቄዎች በተመለከተም የጋሉላ ዞንነት ጥያቄ ተመልሷል ብለው በሒደቱ ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ከ80 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ምርመራውን ፖሊስ በሚፈለገው ልክ አጣርቶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ቀርቦ ውሳኔ ማግኘቱን ተናግረዋል። የወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተደራጀ በኋላ ይህ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ችግር ወይም በዘፈቀደ የታሰረ የለም ብለዋል።
በኢሰመኮ ውይይት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ተወካይ አቶ ተስፋዬ ገመቹ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ዓውደ ጥናት ያስፈለገበት ምክንያት ግኝቶቹን እንድንክድ ሳይሆን ክፍተቶችን ዓይተን ማስተካከያ እንድናደርግ ነው። ስለዚህ በአዎንታዊነት ብንቀበልና ምንድነው እኛ ዘንድ ያሉት ችግሮች የሚለውን ማየት ነው የሚበጀው። እኛ በግልጽ ሕዝብ ውይይት በተሳተፍንባቸው አንዳንድ ቦታዎች ባቀረብናቸው እውነቶች ምክንያት ማስፈራራት ሁሉ ደርሶብናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ምላሽ ለአብነት የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹ምንም እንኳን መጨረሻ ላይ ሁሉ ነገር ሙሉ ነው ለማለት አይደለም የሚል ሐሳብ ቢነሳም፣ እኛ ባየናቸው አንዳንዶቹ አካባቢዎች ያለው እውነታ ከተባለው የተለየ ነው ለማለት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል።
ለዚህ ገለጻቸው ማሳያነት ያነሱትም በክልሉ የሚገኘውን በጉማይሌ ልዩ ወረዳ ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ላይ እየደረሰ ነው ያሉት የዘፈቀደ እስር ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነው ብለው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓይነት በሰፊው እየታየ መሆኑን፣ እዚህም ማሰቃየትና ኢሰብዓዊ መብት አያያዝ በሚለው ሥር የሚጠቀሱት፣ አንዳንዶቹ በግልጽ ከዚህ ቀደም ተሰብሳቢዎች የተወያዩባቸውና ሊያርሟቸው ቃል የገቡባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹አንዳንድ ፖሊሶች ዛሬም ለማሳመን በድብደባ ምርመራ ለማድረግ የሚሞክሩባቸው ቦታዎች አሉ። ይህ ሁሉንም ይወክላል ማለት አይደለም። ነገር ግን እነዚህ ማሳያዎች መስተካከል የማይችሉ ከሆነ በሒደት የቀደመው፣ የጠላነው፣ ማኅበረሰቡ የተማረረበት፣ መንግሥትም እለውጠዋለሁ ብሎ ቃል የገባበት ነገር ተመልሶ እንደማይመጣ እርግጠኛ አይደለንም፤›› ብለዋል።"https://www.ethiopianreporter.com/
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ