"መንግሥት የርዕደ መሬት በታየባቸው አካባቢዎች የጉዳቱን መጠን አሠሳ የሚያደርግ ቡድን ማሰማራቱን ገለፀ" BBC

 https://www.bbc.com/amharic/articles/c623m1566m9o

 

"መንግሥት የርዕደ መሬት በታየባቸው አካባቢዎች የጉዳቱን መጠን አሠሳ የሚያደርግ ቡድን ማሰማራቱን ገለፀ"

 አዋሽ እና በአካባቢው ያሉ ሥፍራዎችን የሚያሳይ ካርታ

"መንግሥት የርዕደ መሬት በታየባቸው አካባቢዎች ከተለያየ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ ባለሙያዎች ማሰማራቱን ገለፀ።

የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙኒኬሽን ቅዳሜ፣ ታህሳስ 26/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ርዕደ መሬቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማሥፈር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

መግለጫው አክሎም ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ርዕደ መሬቱ በታየባቸው አካባቢዎች ተሰማርተው የጉዳቱን መጠን አሠሣ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከ2017 አዲስ ዓመት ጀምሮ በአፋር፣ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች እየተደጋገሙ እና ንዝረታቸውም እስከ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ ድረስ እየተሰማ ይገኛል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ክሥተቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠን እና በድግግሞሽ እያደጉ መሆናቸውን አስታውቋል።"

በተለይም በዚህ ሳምንት በርዕደ መሬት መለኪያ እስከ 5 ነጥብ 8 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ መንቀጥቀጥ መከሠቱን መረጃዎች ያሳያሉ ሲልም ገልጿል።

በአዋሽ ፈንታሌ እና አካባቢው ትናንት ለሊት 9:52 ሰዓት ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍ ያለ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ትናንት ሌሊት የነበረው የመሬት መንቀጥቀጡም በሬክተር ስኬል 5.8 ሆኖ መመዝገቡን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ አስታውቋል።

በአጠቃላይ ባለፉት 24 ሰዓታ ውስጥ በኢትዮጵያ ከ5 በላይ የመሬት መንቀጥቀጦች የተከሰቱ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ በሬከተር ስኬል ከ5 በላይ ሆነው ተመዝግበዋል።

መንግሥት ክሥተቶቹን በዘርፉ ባለሙያዎች በቅርብ እየተከታተለ ይገኛል ያለው መግለጫው፤ በተለይ የርዕደ መሬቱ ማዕከል የሆኑት አካባቢዎችን በመለየት በ12 ቀበሌዎች ላይ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቦታው በማሰማራት የጉዳቱን መጠን አሠሣ እያደረገ ይገኛል ሲል ገልጿል።

በእነዚህ ቀበሌዎች ከሚኖሩ 80 ሺህ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ ለማሥፈር ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው በማለትም አስታውቋል።

በማኅበራዊ አግልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በኢኮኖሚ ተቋማት እና በመሠረተ ልማት ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

ርዕደ መሬቱ እስካሁን ባለው ሁኔታ በዋና ዋና ከተሞች የጎላ ተጽዕኖ አላደረሰም ያለው መግለጫው፣ ቢሆንም ዜጎች በባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መልእክቶችን እንዲከታተሉና በጥብቅ እንዲተገብሩ አሳስቧል።

የዘርፉ ባለሞያዎች በተለይም ወርሃ መስከረም እና ጥቅምት ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች የነበሩባቸው ወራቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

በኅዳር ወር ጋብ ብሎ የነበረው ርዕደ መሬት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ሲሆን፤ ከእስካሁኑ በሬክተር ስኬል ከፍተኛው ርዕደ መሬት የታየውም ባለፉት ቀናት ነው።

የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል?

መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንብርብሮች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል 'ኮር' ይባላል። ቀጥሎ የሚገኘው 'ማንትል' ነው። በመቀጠል 'ክረስት' ይመጣል። ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው።

ክረስት እና የማንትል የላይኛው አካል ቴክቶኒክ ፕሌትስ ከተባለው ድንጋይ የተሠሩ ናቸው።

'ቴክቶኒክ ፕሌትስ' ዝግ ባለ መልኩ ሁሌም ይጓዛሉ። በዚህ መካከል ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ ሆኖ በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን የሚነቀንቀው እና የሚያፈራርሰው።

በቀላል አገላለጽ በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ መሬት ትንቀጠቀጣለች ማለት ነው።

'ቴክቶኒክ ፕሌትስ' በየዓመቱ በጥቂት ሴንቲ ሜትሮች እንቀስቃሴ ያደርጋሉ። እነዚህ መሬት የተዋቀረችባቸው አለቶች በተለያየ አቅጣጫ ነው የሚንቀሳቀሱት። ፍጥነታቸውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ አለቶች እርስ በርስ ተፋፍገው ሊያልፉ ይችላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ክፍል ከሌላኛው እየራቀ ሊሄድ ይችላል። እርስ በርስም የሚጋጩ አሉ።

በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ድንጋዮች ሲተፋፈጉ ርዕደ መሬት ያስከትላሉ። በመተፋፈጉ መካከል የሚከሰተው ኃይል ከፍተኛ ስለሆነ የመሬት ማዕበል ይፈጥራል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የባሕር ጠለል ላይ ሲከሰት ደግሞ ከፍተኛ ማዕበል ይፈጠራል። ሱናሚ የሚባለውም ይህ ነው።

በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በተለየ ቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው።

ይህ የመሬት ውስጥ ንቅናቄ እና መንቀጥቀጥ ጥንካሬ የሚለካበት መሳሪያ ሬክተር ስኬል ይባላል። ይህ መለኪያ ርዕደ መሬቱ የፈጠረውን ማግኒቲዩድ ይመዝናል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።