ርህርህና ተሰደደ። እግዚአብሄርም አለቀሰ።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።
እርህርህና ተሰደደ።
እግዚአብሄርም አለቀሰ
„በምድር ላይ የሰው ህይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?“
(መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 7 ቁጥር 1)

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ©ሲዊዘርላንድ
10.01.2020




እንዴት ናችሁ ቅኔዎቹ የአገሬ ልጆች? ደህና ናችሁ ወይ?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የከረባት እና የገበርዲን ብቻ በመሆኑ ስሞግት ኖርኩኝ። ደጉ ዘሃበሻም፤ ደጉ ሳተናውም ፈቃዳቸውን አልነሱኝም። በራሴ ግራቀኝ ሚዲያም በጸጋዬ ድህረ ገጽ እና ጸጋዬ ራዲዮም በኽረ አጀንዳ ነበር።

በሌላ በኩልም በአገረ ኢትዮጵያ ዕንባ ሲበረታ፤ የዕንባ ቅልቅል ሲን የድምጽ አልባዎችን የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ አድምጡልን፤ እባካችሁ እርዱን እያልኩ በዬደጁ ስባትልም ምክንያት አድርጌ አቀረብ የነበረው የሴቶች አቅም ዕውቅና አለመሰጠቱ ነው የኢትዮጵያን ችግሩን ያበራከተው፤ ሴቶችም ባለቤት ያጡበት መሰረታዊ አመክንዮ ሴት ወሳኝ ሊሂቃን ወደፊት ባለመምጣቸው ነው እል ነበር። ሴቶች በክህሎታቸው ብቃት ሥርዓቱን የመራት፣ የመለወጥ አቅም አላቸው፤ ዕድሉን ካገኙ ሴቶች በጸጋቸው ጸጋ አትራፊ የርህርህና ማህንዲስ የመሆን ተስፋ ይኖራዋል ነበር ሙግቴ።

ጠሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሴቶችን ወደፊት አመጡ ብዬ ደስ አለኝ። ከቀደመው ሰብዕናቸው ተነስቼም ተስፋ ነበረኝ። ብዙም ጽፌበት ነበር። ያን ስለምን እንዳደረጉት አሁን አሁን የራሱ ዕድምታ እንዳለው እዬገባኝም ነው፤ ያው የወደቀውን ኢህዴግ የግንባራቸውን ሥም ለማደስ ነው የተጠቀሙበት። አሁን ሙሽራው ኢህዲግ ነው ያለው።

የሆነ ሆኖ በዛን ጊዜ እኔ ብቻ ሳልሆን ዓለም አደነቀ። ህልም ይመስል ነበር። በራዲዮ ሎራ እራሱን ችሎ በአጀንዳ ሴት የራዲዮን ጋዜጠኞች ተዋያዩበት። ራዲዮ ሎራ የኮሚኒቲ ራዲዮን ነው። በኮሚሽን ነው የሚተዳደረው። እኔ ከ2008 እ.አ.አ ጀምሮ የጸጋዬ ራዲዮ በአማርኛ ቋንቋ በወር ሁለት ጊዜ የማስተላልፍበት ፕሮግራም ነው። ወደ 20 ቋንቋወችን ያስተናግዳል - ራዲዮኑ። 

ወደ ቀደመወ ምልሰት ሳደርግ የዛን ጊዜ ሙግቴ ሴት መሆንእራሱ የሚፈታቸው ችግሮች ስላለው፤ የሴቶች በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል ሙሉ እምነት ነበረኝ የዛሬን አያድርገው እና። እናትነት እራሱ መድህንነት ነበር - ላወቀበት። እናትነት ጥበብ ነበር - ለተጋበት። እናትነት ህይወትነት ነበር - ዕውቅና ለሰጠው። ሴትነትም መፍትሄ አስገኝ ማንነት ነው - ሚስጢሩ ለገባው። ሴትነት ብዙ ነገር አለው - አጀንዳው ለሆነው።

ነገር ግን በኦሮምያ ባዬነው የሴት ከንቲባዋች ፍጹም ጭካኔ ማልቀሳችን ላይበቃ፤ ይህ ሁሉ ማአት እዬፈሰሰ በብሄራዊ ደረጃ የሴት የፖለቲካ ሊሂቃን ልብ እርህራሄ ሊጠጋው አልቻም። ሴት ሊሂቃን በኃላፊነታቸው ውስጥ ያሳዩት የሰው ልጅን የማግለል፤ የመጫን ገመና እራሱ ውስጥን ያቆስላል። እጅግ ተስፋ አጥቼ በድምጽ የሠራሁት ሊንክ እንሆ። ለታሪክ እንዲቀመጥ። ልፋት ከንቱ ሲሆን ከማዬት በላይ
 ምን የትውልድ ዕዳ አለና? ለዚህ ነበርን ወጣትነቴን የገበርኩት -ን?!

የእናትነት መክሊት ግማዱ በአብይወለማ ሌጋሲ።( ከሥርጉተ ሥላሴ 08.05.2019)

ይህ ሁሉ የሴት ሊሂቅ፤ ይህን ያህል ቦንዳ ኃላፊነት ተሸክመው አንድም ቀን ስለ ሰብዕዊ መብት እረገጣ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሴቶች ዕንባ በአጀንዳ ተወያይተውበት አያውቁም። በመኖር ውስጥ ያሉ አለመኖሮችያሳፍራል። አንገትም ያስደፋል። 

መንግሥትንም ደፍረው አይጠይቁም፤ ድርጊቱን በአደባባይ ወጥተው አያወግዙም። እርግጥ ነው „በጃዋርውያን ንቅናቄ“ ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ድምጻቸውን አሰምተው ነበር። ውጤቱ እና ስኬቱ ግን ብዙም አላዬሁም። ቢያንስ ደፍረው መውጣቸው ግን የተገባ እርምጃ ነበር። እንደ ሰብዕዊ መብት ሉላዊ አቅምነት ግን ቀጣይ እርምጃቸው የጠበቅኩትን ያህል አልሆነም። ዕድላቸውን ያሳለፉ ይመስለኛል።

ሁሎችም እንለቃለን ኃላፊነቱን ቢሉ እና ቢያድሙ መንግሥት ይደነግጣል። ግን ርህርህና ሲኖር፤ ተፈጥሯዊ ሴትነት ካለመከነ ነው። እናትነት ጸጋው ካልተነነ ነው። እንዴት እንቅልፍ ወስዷቸው ያድራል? እንዴት?! ኢትዮጵያ ከአፍጋኒስታን፤ ከኢራን ተርታ በሦስተኛ ደረጃ በቀውስ ስጋት ስትወጣ 50/100 ሴት ካቢኔ ባለበት አገር። ያስደነግጣል። እኔ አልቅሻለሁኝ። ይህንን ሚዛን ማስጠበቅ ካልቻሉ ለምኑ ሊሆኑ ነው? ለዚህ ግራጫማ ዘመን ዋቢ ካልሆኑለት ምንድን ይሆን ክብራቸውስ - ሹመታቸውስ?
  
የሴቶች፣ የወጣቶች እና የህፃናት ሚኒስተርም ያለ ይመስለኛል። ምን ይሆን የሚሠራው?! ምስል። አይታፈርም መጋቢት 29 ቀን 2012 ደግሞ እንደ ተለመወደው ጠሚር አብይ አህመድን ይዘው እዬከበከቡ፤ ያው በፍቅር ቁልምጫ ዕንባቸውን ዱብ ዱብ እያደረጉ ዲስኩር እንሰማ ይሆናል አለባበሳቸውን አሳምረው። ለ2012 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ለዕለቱ ጥቁር ልብስ ቢያሰፉ ይሻላቸዋል። የሰውም ግፍ አለውና። ዕለቱ የወግ ገበታ ነው የሚሆነው። መቼም የወሬ ቋት ሆኗል የተያዘ የተረዘዘው ሁሉ።

የመንግሥት ሚና የጠፋበት ዘመን። የመንግሥት ሥራ ማለት የወግ ቋትነት ነው። በቃ! ዲስኩር ብቻ። ቢያውቁት እዬፈረስን ነው። ኢትዮጵያዊነት የተያያዘበት ሙጫ እየለቀቀ ነው 50/100 የሴት ካቢኔ ባለበት አገር። በመኖር ውስጥ ያሉ አለመኖሮች።

የሆነ ሆኖ እርህራሄ ከሴት አንጀት የጠፋ ዕለት ቀዩን የዲያቢሎስ አውሎ እዬናጠው ስለመሆኑ ያመለክታል። የሚገርመኝ የሴት የጥበብ ሰዎች ጉዳይ ነው። በደንቢ ደሎ ታግተው ያሉ 17 ልጆች የኢትዮጵያ አይደሉንም? ከእንጨት፤ ከእሳር ከቶ ከምን ይሆን እነኝህ ልጆቻችን የተፈጠሩት?

በፈጣሪ አምሳል የተፈጠሩ አይደሉምን? ሞት እኮ ጥሩ ነገር ነው። በአረመኔዎች እጅ ወድቆ መሰቃዬት ግን አይጣል ነው። ይህን የኦነግ ጦር እኮ መንግሥት እራሱ በሎጅስቲክ ደግፎ ነው ከዚህ ደረጃ ያደረሰው። ተው እያልን። ካቢኔው ታጣፊ አልጋ ተገዝቶለት ለሽ ብሏል። የተወካዮች ምክር ቤቴም ስሊፒንግ ባግ ተሸምቶለት እንቅልፉን ይለሸልሻል።

በኢህዴግ በግንባሩ ላይ ጫና በመፍጠር የኦሮሞ ፓለቲካ የበላይነት ለመጫን፤ ፖለቲካዊ ትርፍ ለኦሮሙማ ለማስገኜት ታልሞ ይሰራበታል። ሌላ ቦታ ሚዛን እንዳያስጠብቅ ጠንከር ብሎ የሚወጣ ኃይል ካለ በተለይ በአማራ ክልል በአደማ ሥርዕዎ መንግሥት ይደቆሳል። ሊሂቃኑም ሰኔል እና ቹቻ ይታዘዝላቸዋል። እናቶችም ገመድ እንታጠቁ ያልፋ። 

የኦነግ ጦር ደግሞ በሙላት በሁሉም ዘርፍ ይታገዛል፤ ይቆላመጣል። እንክህ እንክህ ይባልለታል። ተጨማሪ ደጀን አጋዢ ጦርም ይሰናዳለታል። በዬጊዜው ይመረቅለታል፤ አሁን 30 ፈሪ ሁኗል የሥልጠና ዙሩ። ለውጊያም ይመቻችልታል። ቅዱሳንን ለማገተም ይሳናዳለታል። አልጋ ባልጋ ነው፤ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ ለኦሮሞ ፖለቲካ። ሁሉም የኦሮሞ ሊሂቅ በነፍስ ወከፍ የሚያዘው ሠራዊት አለው ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ።

ለምርጫ ውድድርም አንቱ ተብሎ ለጦረኛው ኦነግ ሁለመናው ብሎ ይቀርብለታል። በዚህ ኢትዮጵያን ይወጋል፤ በዚህ ኢትዮጵያን ለመረከብ ለሥልጣን ምቹ ሁኔታ ለፉክክር ይፈጠርለታል። በዚህ በኤኮኖሚ አቅም እንዲደረጅ ለባንክ ዘረፋ መንገድ ይጠረግለታል። በዚህ ደግሞ ቢሮክራሲው ሙሉ በዛው መንፈስ ይሞላል። የቤት ልጅ። በዬትኛውም ዓለም ሆኖ አያውቅም። ቀሪው ሰራዊቱ ደግሞ በመንግሥት ተቀጥሮ መደበኛ ማህያ እያገኜ ተዘባኖ ይኖራል። የኢትዮጵያ መከራ! ባለቤት የሌላት አገር።

የሆነ ሆኖ የተከበራችሁ የጥበብ ህሊናዎች የት ናችሁ ያላችሁት? የት ሄደች መቅዲ? የት ሄደች መሲ? የት ሄደች ቲጂ? የት ሄደች ሸዊት? የት ሄዱ ሩህሩኃን? ቦኮ ኃራም ልጃገረዶችን ሲያግት ደልዳላዋ ቀዳማይ እመቤት / ሮ ሚሺያል ኦባማ ፊት ለፊት ወጥተውልጃገረዶቻችን መልሱን“ አሉ። እንዲህ ዓይነት ሚዛን ሴቶችን አለማችንም አፍርታለች።


እኔ መቼም እማልደክምበት መሰመር የለም። አንዲት ብርቱ ሴት ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ለማፍራት እረጅም ጊዜ ይወስድባታል ቢያንስ 50 ዓመት፤ ያሉን ደግሞ ታሰሩብን። ቀጣዮች ሴት ልጃገረዶች ከማን ምን ይማሩ? ብዬ ለክብርትነታቸው ሴት ጋዜጠኛ እና ብሎገር ሲታሰሩብኝ በግል አመልክቼ በፍጥነት መልስ አሰጥተውበት ነበር። ብርክት!

በሌላ በኩልም ከእኛ በኋላ ወጣት ሴት ፖለቲከኛ ለማዬት ባለመቻሌ ሳዝን ቆይቼ ወ/ት ትዕግሥት ይርጋ በስንት ዘመን አንስት የፖለቲካ ታጋይ በቀዬው ለግለግ ብላ ስትወጣም፤ ስትታሰርብኝ እንዲሁ ለሩኽሩኋ ሉላዊ የመቻቻል እናት ለአገረ ጀርመን መራሂተ እናት አንጌላ ሜርክልም እንዲሁ አመልክቼ ሰፊ ጊዜ፤ ሙሉ ዕውቅና ሰጥተው ብዙ በጣም ብዙ አግዘውናል። ለኢትዮጵያ ሴቶች ሊሂቃን ወደፊት መምጣትም ሰፊ አስተዋፆ አበርክተዋል ብዬ አስባለሁኝ። የጠሚር አብይ አህመድ በጀርመን ያን ያህል ክብር የተቸረው ፍላጎታችን ያስፈጽማሉ በሚል ዕድምታም ነበር።

እሬቻ ጭፍጨፋም እንደዛ በዓል ለማክበር የሄዱ ወጣቶች ወጥተው ሲቀሩ ለተባበሩት መንግሥትታ ለቀድሞው፤ ለደጉ ዋና ጸሐፊ ወጣቶቻችን መኖራቸው ተቀማ ብዬ አቤት ስል፤ ወጥተው ሶልዳሪቲ አሳይተው ነበር። የጭንቀቴ አመክንዮው በወስጣቸው የበቀለ ነበር።

የችግሩ ምንጭ ከሥርዓቱ ቢሆንም ግን ፖለቲካው ላይ የሴቶች ሊሂቃን ተሳትፎ ጎልቶ አለመወጣት የርህርህና ድርቀት ስለመሆኑ አበክሬም እጽፍ አመለክትም ነበር። ይህን ሁሉ አልፈን አሁን የራሳችን የሴት ካቢኔ ሲኖረን እርህርህና መነነ። አያሳዝንም?! እኛስ አናሳዝንም? እግዚአብሄርስ አያለቅስምን? አሁንስ እኔ ምን ብዬ ላመልክት? ምንስ ብዬ አቤት ልበል? የኢትዮጵያ አንስት ሊሂቃን ጨካኝ ሆኑ ብዬ - እርህርህናቸው ተሰደደ ብዬ? እንዴት? ከባድ ፈተና - ከራሴ ጋር እዬተሟገትኩኝ ነው።

ዘማሪ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ለመሆኑ የት ናቸው? „እኔ የሁሉም ኢትዮጵውያን ልጆች እናት ነኝ“ ብለው በዓለም አደባባይ ቃል ገብተው አልነበረምን? ቃል ማለት እንደዚህ ነውን? ለእነዚህ ልጆች ስለምን እናት መሆን ተሳናቸው?

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችም ተነጥለው ባለፈው ዓመትም ዘንድሮም ተፈናቅለው መንገድ አዳሪ ሆነዋል። ተስፋ ቢስም ሆነዋል። የተሰዉት ተሰውተው። አሁን ደግሞ ወደ 17 የሚጠጉ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ታግተዋል። ለእነዚህ እናት መሆን ስለምን አልተቻላቸውም? „ለተባረከች አገር የተበረከ ትውልድ“ ከዬት ይጠጋ ይህ ቀልብ ሳቢ ሞቷቸው? በቃ - በቃል ብቻ? ላይተገብሩት ስለምን ይናገሩታል?! በማን ተስፋ እናድርግ? ጥግ አጣን።  


የዶ/ር አብይ አህመድ ሚስት ዝናሽ ታያቸው በአለም መድረክ ላይ ያደረገችው አስገራሚ ንግግር |
Abey Ahmed Wife Zinash Tayachew speech
„Accelerating the End of Hunger and Malnutrition Event »

ግማሽ እጁ ካቢኔ ሴት? ምንድን ይሆን ጥቅሙ? ሴት ፕሬዚዳንት ምን ይሆን ፋይዳው? ሴት የፍትህ አናት መሆንስ ምን ማለት ይሆን? መኖራቸውን ባለመኖር እንሰበው ይሆን? ግርባው ብአዴንስ ምን ይሆን ተልዕኮው? በቃ ጭጭ? ዝም?! ይቀዘቅዛል።

ቀለጤዎቹ፤ ዘመናዮቹ ሴት የካቢኔ አባላት በተለይ ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚል እና ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ „ለተራበ ትቼ ለጠገበ አዝናለሁ“ እንዲሉ፤ „የደላው ገንፎ ያላምጣል“ እንደሚባለውም ለተመቻቸው ለጠሚር አብይ አህመድ ባቄላ ባቄላ የሚያክለውን ዕንባቸውን ሲያንዠከዥኩት አስተውላለሁኝ።

ለእነዚህ ምንዱባንስ ማን ዕንባ ያዋጣላቸው? አሁን ኢትዮጵያ ምድር አዛኝ ሴት አለን ማለት እንችላለን? ወይንስ እርህርህና ተሰደደ እንበል? በስንቱ ይለቀስ? በስንቱስ ይታዘን? ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ሲሾሙ ኢትዮጵያ እናት አገኜች ብዬ ነበር። ግን በግን ገነገነ ገነነ እንጂ።

ሴቶች በአስ ቤታቸው ታረዱ፤ ሴቶች በአስ ቤታቸው መኖራያቸው በግሪድር ታረሰ፤ ሴቶች በድንጋይ ተወግረው ተገደሉ። ሴቶች ጡታቸው ተቆርጦ ተገደሉ፤ ሴቶች በቆርቆሮ ተገዝግዘው ታረዱ፤ እናትነት አለቀስ! እግዚአብሄርም አለቀሰ! ከእንግዲህስ እኔ ፖለቲካውን ወንዶች ብቻ ያዙት ብዬ የመጠዬቅ፤ የመሞገት፤ የማመልከት ሞራሉስ ይኖረኛልን?! ፈጽሞ።

የመንግሥት ሚደያዎችስ ምን ይሠራሉ? ምንድን ይሆን ውሏቸው? ከ12ሺህ እስከ 40 ሺህ የሚገመቱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በዚህ ዓመት ብቻ ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል ነው የሚባለው። የተወሰኑት ዩንቨርስቲዎች ሥራ አቁመዋል፤፡ የተወሰኑትም በግማሽ ልብ ይንቀሳቀሳሉ።

ለመሆኑ ትምህርት ልቦና ካልተሰበሰበ፤ ህሊና ካልረጋ እንዴት መማር ይቻላል? ይህ እኮ ህውከት ላለበት ብቻ ሳይሆን በአንደኛ፤ በመለስተኛ እና በሁለተኛ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎችም ጭምር የውስጥ ሰለማቸውን ያውካል፤ ሩቅ ተስፋቸውን ያቀጭጨዋል።

ይህ ለሚዲያ ሰዎች፤ ለሴት የፖለቲካ ሊሂቃን፤ ለሴት የጥበብ ሰዎች ውስጥ ያልሆነ የትኛው ጉዳይ ይሆን ውስጣቸው የሚሆነው። ?! የሰላም የኖቤል ሽልማት?! ለዛ የወርቅ ሽልማት በዓይነት ማዘጋጀት ይሆን ትውልድ ማለት? ወይንስ ፌስታ ላይ ማውካካት ማግስትን ያሳምረው ይሆን?

የትምህርት ውጤት እኮ በሩቅ ጊዜ ሊታይ የሚችል ነው። ትውልድ እዬመከነ ነው። ይህ አጀንዳ ካልሆነ አገር እንዴት ትታሰብ? አደራስ እንዴት ይታሰብ? ማግስትስ እንዴት ይታሰብ? ኃላፊነት በምን ይገለጽ? በምንስ ይተርጎም? ተጠያቂነት እንዴትስ ይመሳጠር? ምክነት - በከንቱነት። 




























ባለፈው ሰሞን በጠገዴ የታገቱ ህጻናት ተረሸኑ። ወደዬት ነው ጉዟችን? ምን እዬሆን ነው? 


ለድምጽ አልባው ትውልድ ድምጽ እንሁን!
አብረን እናልቅስ! ለራሳችንም እናልቅስ!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።