የፈረንጆች 2025 አዲስ ዓመት ሲመጣ አንድ አመት የሚሞላው ስምምነት ጨነገፈ። እኔ በዚህ ዙሪያ ምንም አላልኩም ነበር። ዝም ብዬ ነበር የባጀሁት። ምክንያቴ አስተማማኝ የፖለቲካ አቅም፤ አቋምም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መሪ ስለለ። የሆነ ሆኖ በዚህ የአንካራ ስምምነት ሰላም በኢትዮጵያ እና በሱማሌ ሉዓላዊ አገራት #መታጨቱ ግን ያስደስተኛል። ይህ እርምጃ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅም፤ ለቱርኪ ለአንከራ፤ ለሱማሌ መንግሥት ምን አትርፎ ምን ሊያከስር እንደሚችል የዘርፋ ባለሙያወች ይተንትኑት። ለእኔ የሰላም #ቃጭሏ ናት ወሳኝ ጉዳይ። ዓለምዓቀፍ ማህበረሰቡም የስምምነቱን ይዘት እንደምን እንደሚመለከተው እንጠብቃለን። ባለ ተስፋ ጠባቂው የሱማሌ ላንድ መንግሥት እና ህዝብስ ከአዲሱ መሪው ጋር ይህን መርዶ እንደምን ያስተናግዱት ይሆን? አማፂው የሱማሌው አልሸባብስ???? በቅድሚያ ከBBC አማርኛ ዜና ያገኘሁትን የስምምነቱን ነጥብ አንስቼ የራሴን ዕይታ አቀርባለሁ። የአብይዝም ሚዲያወች ደግሞ አሁን ምን ለማለት ይጣደፋ ይሆን??? ወዘተረፈ ጋራጅ ስላላቸው። ጥገናክፍላችው በርካታ ነውና።
"ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከስምምነት የደረሱበት ሰነድ ምን ይዟል?"
https://www.bbc.com/amharic/articles/cly25z39pdpo
ከ 4 ሰአት በፊት
"ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን አለመግባባት በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ ደረሱ።
ከሁለቱ አገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከፈረመች በኋላ ነበር።
ቱርክ በአገራቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ፕሬዝዳንቷን ጨምሮ በከፍተኛ ባለሥልጣናቷ አማካይነት ለወራት ስትጥር ቆይታ ከስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አስታውቀዋል።
ኤርዶዋን ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ" እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አንካራ ላይ ተገኝተው በተደረገው ለስምንት ሰዓታት ከቆየ ንግግር በኋላ ነው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጸው።
የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊ በር እንደታገኝ የሚያደርግ ነው ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
"በነበረን ስብሰባ በተለይ ኢትዮጵያ ካላት የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ፍላጎት አንጻር፣ ወንድሜ ሼክ ሐሰን ኢትዮጵያ ወደ ባሕር መተላላፊያ በር እንድታገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል ኤርዶዋን።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ስር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ" እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።
ለዚህም ሁለቱ አገራት ንግግሮችን በማካሄድ በወራት ውስጥ አጠናቀው ለስምምነት ለመቅርብ ተስማምተዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተናገሩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት መቻሉን አመልከተዋል።
"የኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ የማግኘት ፍላጎት ጎረቤቶቻችንን ጭምር የሚጠቅም ሰላማዊ ጥረት ነው፣ ይህ ፍላጎት በትብብር መንፈስ እንጂ በጥርጣሬ ሊታይ አይገባውም" ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ገንቢ ውይይት" ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን "በትብብር፣ በወዳጅነት እና በጠላትነት ሳይሆን በጋራ ለመሥራት ከሚኖር ፈቃደኝነት ጋር ወደ ቀጣዩ ዓመት ያሸጋግራል" ብለዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው አንካራ ላይ የተደረሰው ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን "ልዩነት የበቃ" ነው በማለት አገራቸው "ከኢትዮጵያ መሪዎች እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ" መሆኗን አመልክተዋል።
የአንካራው ስምምነት ነጥቦች
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ፕሬዝዳንት አማካይነት ውዝግቡ ከጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ አንካራ ላይ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ከስምምነት የደረሱባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች የሚያመለክት 'የአንካራ ውሳኔ' የሚል ሰነድ ይፋ ሆኗል።
ይህ በቱርክ መንግሥት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኩል የወጣው የአንካራ ስምነት ሰነድ በዋናነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል አወዛጋቢ የሆነውን የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ጉዳይን ያነሳል።
በተጨማሪም ሶማሊያ ከመጪው ጥር ወር በኋላ ከግዛቷ እንዲወጣ የምትፈልገውን በአፍሪካ ሕብረት ስር የተሰማራውን የኢትዮጵያ ሠራዊትን በሚመለከትም ከዚህ በፊት የተሠረጨውን የሶማሊያን ወቀሳ የሚያነሳ ነጥብም ተካቶበታል።
የአንካራ ስምምነት ዋነኛ ነጥቦች
- የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።
- በወዳጅነት የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት ተስማምተዋል።
- ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።
- የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ።
- ሁለቱ አገራት በቱርክ አመቻቻነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ድርድር ማድረግ የሚጀምሩ ሲሆን፣ ይህም በአራት ወራት ውስጥ የሚቋጭ ይሆናል።
- በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም አገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ፣ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋር በመሆን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።
- ሁለቱ አገራት የቱርክን ድጋፍ በመቀበል በስምምነቱ አተረጓጎም እና አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በቱርክ አማካይነት በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተዋል።
^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^^
መልካም ዜና ነው። ውጥረቱን ያረግባል። ለሰላም #ቅርብ የሆነ መንፈስ ያለው አውራ ተግባር የቱርኪ መንግስት ፈጽሟል። ሰላምን የሚያስንቅ #ዕንቁ ጉዳይ ምድራችን የላትም። መጨረሻውን ያሳምረው። አሜን። በዚህ አንኳር ጉዳይ ውስጥ የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን #አሳቻ ሰብእና መመርመር ይችላል። መጀመሪያ ይገሽሩታል። ከዛ ሲቀጣጠል ፀጥ ብለው ቁጭ ይላሉ። መጨረሻ የመፍትሄው ቁንጮ ጉልላት ሆነው ብቅ ይላሉ። የሚገርመኝ ግን የፕሮፖጋንዳ ባንዶቻቸው የጠቅላይ ሚኒስተራቸውን ሩቅ ፍላጎት ሰንሰለት እና ምልሰቱን ሳያጠኑ ይዘፈቁበታል። ትልልቅ የፖለቲካ ኤክስፐርቶች ሳይቀሩ ነው እንደ አለ ተቀብለው የሚተነትኑት። አንድ ምሳሌ ላንሳ የአገር እና የውጩ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይ በበሰለ ገብተው ሰላም #አማጭነትን ማዕረግ ተጎናፀፋ። ያን ጊዜ የኦሮምያ ኦርቶዶክስ ይጠነሰሳል ብለን ስላላሰብን አደነቅን። ሐሤቴ እኔ እራሴ ወደር አልነበረውም። ከዛስ? በአውሮፕላን ከብክበው አገር ያስገዟቸውን ትጉህ ጳጳስ አገር አትገባም ብለው #አገዱ። ያን ጊዜ ይህን አስበን ነበርን??? በሌላ በኩል የኦሮምያ ቅዱስ ሲኖዶስም ተጠንስሶ አሁን በቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ አለ አስኳሉ። #ልምምድ እያደረገ ነው። በመጨረሻም ከዛ የምጣት ቀናት በኋላ አስታራቂው እሳቸው ዶር አብይ አህመድ አሊ ነበሩ። ክብሩ፤ ማእረጉ ለሳቸው ተሰጠ። የተሰውት ሰማእታት፤ የነደዱት አብያተ ቤተክርስትያናት ግን ባለቤት አልባ ሆኑ። በዬበዓላቱ ያለው ጭንቅ እና መሰዋትም እንደ ቀጠለ ነው። ወጀቡም ወጨፈውም አለ። ለካቴና የተሰጡትም አስተዋሽ የላቸውም። ሌላም በህወሃት እና በፌድራሉ ጦርነት ቅድስቷ ሚና እንዲኖራት ተደረገ። የትግራይ አባቶች ተከፋ። ሦስተኛ ሲኖዶስ ተጠነሰሰ። በዚህ ከሱማሌ ላንድ ጋር በነበረው ስምምነት ጥር ቢመጣ አመቱ ነው። ብዙ ሰው ቅራኔው ውስጥ እራሱን ማገደ። በዛ ምክንያትም በግብጽ መሪነት ብዙ መናኮር ተከሰተ። ደም የሚያንተከትክ ጉዳይ ተፈፀመ። በመጨረሻ በቱርክ አገናኝነት የኢትዮጵያ እና የሱማሌ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮች ቱርኪ ላይ ተገናኙ።
ጠቅላይ ሚር አብይ ለዚህ #ዕድል #ካወጣው የመቋጫ ስብሰባ እንደሚገኙ ቀድመው ወስነዋል። የታሪኩ ባለቤት መሆን ይሻሉ። ከዚህ በፊት የቀደሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አንባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ የዛሬው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት፤ ከስልጣኑ ዘወር እንዲሉ አደረጉ። በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ የወደብ ረሃብን ለማስታገስ የአሻራው ቁንጮ እራሳቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ብቻ እና ብቻ እንዲሆኑ የሚያስችል ክስተት ፈፀሙ። የነገው አይታወቅም። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚር አብይ አንድ አዲስ ሁነት ሲከውኑ አርቆ የሚተነብይም፤ ያን የሚመክት ስክነታዊ ጉዞ የሚያደርግ ከሊቅ እስከ ደቂቅ አላዬሁም። ይህን እምጽፈው የስርዓት ለውጥ ለማምጣት ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እሳቤ የቀደመ፤ ያስተዋለ፤ አቅምን በቅጡ ማኔጅ የሚያደርግ ዕውቀት እንደሚያስፈልግ መሆኑን ለማጠዬቅ ነው። የሚፈላሉ ብዙ ፍላጎቶች ስለማደምጥ።
የቱርኩ መሪ በዚህ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ያላቸው ተሳትፎ እኔ ሳስተውለው #ጥበብ አለበት። መንፈሱ የኡቱማን ቱርክ ሆኖ ግን መሪው ሃሳቡን ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ጋር #አዘምነውታል። የሆነ ሆኖ የስምምነቱ ነጥብ የኢትዮጵያ መንግስት ቢማርበት ባይ ነኝ። ስምምነቶች እንዲህ ግልጽ እና አጭር በቀላል አገላለጽ ለሁሉም በሚገባው ሁኔታ ሊቀመር ይገባል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያደረጉት ስምምነት አይታወቅም ነበር። ከአረብ ኢምሬት ጋር ያላቸውን ስምምነትም አናውቅም። ከህወሃት ጋር በኬኒያ ያደረጉት ስምምነት አይታወቅም። ከኦነግ ጋር በኤርትራ ያደረጉት ስምምነት አይታወቅም። #አይታወቅም + #አይታወቅም= #አይታወቅም። እንግዲህ የአብይዝም ሚዲያወች " ወደብ ተገኜ " የሚለው የዛሬ ዓመት ጥድፊያቸው ዛሬ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ይደመጣሉ። ሁልጊዜ በዶር አብይ አህመድ የውሳኔ ተለዋዋጭነት ሲያዳልጣቸው ነው እምመለከተው።
ሆነም አልሆነም ኢትዮጵያ ከጭንቀት የምትገላገልበትን #የሰላም ዘመን በጽኑ እመኛለሁኝ። በሰበር ስትናጥ፤ በጦርነት ደወል ስትናጥ በመፈናቀል፤ በሃዘን ኩርምትምት ብላ ስለሰነባበተች። ነገረ ግብጽስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኝ ይሆን? ነገረ አረብ ኢምሬትስ? የመግባቢያ ሰነዱስ አድራሻ ወደዬት ተላከ??? ስንት ያህል የአዬር ጊዜ ተሰጥቶት ነበር? ያ አተረፈ ወይንስ አከሰረ? ይሄኛውስ ምን ጋራንቲ አለው? ተፈፃሚ ከሆነ ለቀንዱም፤ ለአህጉሩም፤ በስሱ ለዓለምም እፎይታ ነው። ተፈፃሚ መሆን ከተቻለ። በዚህ ዙሪያ ብዙ አቅም ፈሷል መቋጫው ይህ ሊሆን። ሱማሌም ይሉኝታ ቢስ ሆነው እንጂ ደም የተገበረላቸው ህልውናቸው በኢትዮጵያ የማህፀን እና የአብራክ ማገዶነት ነበር። ዝምታው ጠቅላይ ሚር አብይን ያመነ ጉም የዘገነ ስለሆነ ነው። የወጣላቸው አክተር ናቸው። ለዚህ ነበር እኔ ከኖቤል ኦስከር ይሻል ነበር ያልኩት። ገና ዓለምም አላወቃቸውም ለክፋውም ለደጉም ክስተት።
በሌላ በኩል ለሱማሌላንድ ግን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ሰፊ #የለማ ተግባር ፈጽመውለታል። በብዙ ሚዲያወች የነበረው እውቅና #አነቃቅተውላቸዋል። #ባለውለታቸውም ናቸው። ስምምነቱ "#ቢሰረዝ እንኳን" ተጠቃሚነታቸው በብዙ ሁኔታ እነሱ ናቸው። ሱማሌንም አራውጠዋል። ጁቡቲ እራሷ ስጋት ላይ ነበረች። የሱማሌ፤ የኤርትራ እና የግብጽ የሦስትዮሽ ምክክርም ዓላማ እና ግብ የነበረው ነበር። #የፈላ - #የሚንተከተክ - #የታመቀም ሁነት ነበር። የቱርኪ መንግስት ይህን ተግ አድርጎታል። ለዛውም ሶርያ ላይ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ቱርኮች እያዳመጥ ነው። ነገስ??? የአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለውጥም ለብዙግሎባላዊ ሁነት ተጽዕኖ ይኖረዋል። ከሁሉም ነገን እግዚአብሄር አላህ ያውቃል። ሰላም #ትርታ ነው። ንፁህ ኦክስጅን። በመጨረሻ ምንም ክስተት፤ የትኛውም ሰብዕና፤ የትኛውንም አቅም #አቃሎ ማዬት አይገባም። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ይህን በኽረ ጉዳይ ቸል ልትሉት አይገባም። ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
12/12/2024
^
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ