ኃላፊነት የሁሉም ኃላፊነት ነው።

ኃላፊነት የሁሉም ኃላፊነት ነው።
"የአምላክ ልጆች ሆይ ለእግዚአብሄር አምጡ፤
ክብርና ምስጋናን ለ እግዚአብሄር አምጡ።"
መዝሙር ፳፰ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 08.11.2018
 ከጭምቷ ሲወዘርላንድ።

ጤና ይስጥልኝ የኔዎቹ እንዴት ናችሁ? ደህና ናችሁ ወይ? አቅምን፤ ብልህነትን፤ ታማኝነትን፤ መልካም ነገርን ማዋጣት ማግስትን ያሳምራል። ባለፈው ዓመት ይህ የጥገናዊ ለውጥ አዬር መደገፍ አስፈለጊነት አስመልክቶ ብዙ ነገሮችን ብያለሁኝ። መልካሞቹ ሰዎች ጥረትን አህዱ ሲሉ የተጋሁበት ምክንያት ሁሉም የአቅሙን ማድረግ ከቻለ ዛሬን ማግኘት ስለሚቻል፤ ዛሬን ማግኘት ከተቻለ ነገ እና ከዚያም ወዲያን ማግኘት ስለሚቻል ነበር።

እኔ ዛሬ ማንሳት የፈልግኩት ስለ ኃላፊነት ጽንሰ ሃሳብ ትንተና ልሰጥ አይደለም። ግን ነገር ግን ኃላፊነትን ወደ ሌላ ከማሻገር በፊት እራስ ላይ ያለውን ኃላፊነት በቅድሚያ መወጣት ይገባል ለማለት ነው። ሁሉንም ነገር መንግሥት ሊከውን አይችልም። በሰለጠነው አገርም ብዙውን ሃላፊነት የሚሸከመው ህዝብ፤ የሃይማኖት ተቋማት እና የሲቢክስ ድርጅቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ ላይ ለዛውም የ50 ዓመት ቁልል ችግር አልበቃ ብሎ በተደራጁ ሃይሎችም የተሰሩ ሰው ሰራሽ ችግሮችም አሉበት። የሆነ ሆኖ ችግርን በማውራት ችግር አይቃለልም። የሰው ልጅ የአኔ ኃላፊነት ይህ ነው ብሎ መቀበል መቻል አለበት። ግዴታን እዬተወጡ መብትን መጠዬቅ ልንከተለው የሚጋባ መርህም ነው። ጥገናዊ ለወጡን መተቸት እችላለሁ ግዴታዬን ግን አልወጣም ማለት ሥርዓለበኝት ነው። ካለ ግዴታ መብት ካለመብት ግዴታ ኑረውም አያውቁም። 

ለምሳሌ ልጆችን በሞራላዊ ዕሴት ማነጽ የወላጆች ንጥር ግዴታ ነው። ልጆች የሰውን ልጅ እንዲያከብሩ፤ እንዲያፈቅሩ፤ እንዲወዱ ለሰው ልጅ እና ለተፈጥሮ እንዲሳሱ፤ የሰውን ልጅ ሁሉ ወገኔ ነው ብለው እንዲያቅፉ፤ በታማኝነት እንዲስማሙ፤ የሰው ልጆች የሚናገሩትን መልካም ነገር የእኔ ነው፤ ይጠቅመኛል ብለው እንዲያዳምጡ አድርጎ ማሳደግ የወላጆች ግዴታ ነው።

ልጆች ምቀኘነትን፤ ሌብነትን፤ ዝርፊያን፤ ወረራን፤ ጥላቻን፤ ቂምን፤ በቀልን ሴረኝነትን አደመኝነትን እንዲተው አድርጎ ማሳደግ የወላጆች ግዴታ ነው። ልጆች ስድብን፤ ክፉ ነገርን፤ መጠራጠርን፤ ማግለልን፤ ማደመን፤ ሃሜትን እንዲጠዬፉት አርድርጎ ማሳደግም የወላጆች ግዴታ ነው።

ወላጅነት እኮ ከመንግሥት በላይ ሃላፊነት አለው አንድን ማህበረስብ በመቅረጽ እረገድ። አንድ ልጅ ከቤቱ ነው በመልካም ሥነ - ምግባር እና ሞራል ተገንብቶ ተኮትኩቶ ማደግ ያለበት።

ልጁን ልቅ የሰደደ ወላጅ አገር እዬናደ፤ አገር እያፈረስ፤ ሥርዓት እንዲጣስ መንገድ እዬጠረገ ስለመሆኑ ሊረዳ፤ ሊገነዘብ ይገባል። አንድ ልጅ ሥርዓት እስካለው ድረስ ትውልድን በመገንባት፤ አገርን በጥሩ ነገር በመገንባት እረገድ ሰፊ ድርሻ ይኖረዋል።

ልጆችን ት/ቤቶች ብቻ ሊገሯቸው አይችሉም። ልጆች አብዛኛውን ጊዚያቸውን የሚያሳልፉት ከወላጆቻቸው ጋር ነው። ስለዚህም ወላጆች በቤታቸው ውስጥ አንድ አንሰተኛ የመወያዬ መድረክ ከፍተው ልጆችን ስለሰው ተፈጥሮ ታላቅነት፤ ስለሰው ክብሩነት ድንቅነት፤ ስለሰው ታምራዊ ፍጡርነት፤ ስለሰው ውብነት ለፕላኔታችን አስፈለጊነት ሊነግሩ፤ ሊያስተምሩ ሊመክሩ ይገባል። 

ማቀጣል ምን ትርፍ አለው? መናድስ ምን ያሰገኛል? አሁን የሚታዬው በድሃ አገር ማቀጣል እንደ ባህል እዬተወሰደ ነው። አንድ ነገር በተቃጠለ ቁጥር ትውልድ የሠራው ትውፊቱ እዬነደደ ስለመሆኑ ለልጆች ሊነገራቸው ይገባል። 

ልጆች ከትውፊታቸው ባፈነገጡ፤ ሥርዓት በጣሱ ቁጥር ትውልድ ይባክናል። ትውልድ ከባከነ ደግሞ ነገን ማሰብ እጅግ ይከብዳል። ዛሬ ላይ ሆነን ነገን ስናስብ ሁሉንም ነገር መንግሥት እንዲወጣው የምናስብ ከሆነ፤ እያንዳንዳችን ድርሻችን ለመወጣት ዝግጁ አለመሆናችን ብቻ ሳይሆን ስለ ትውልዱ ብክንት አደጋ ገና ፊደል አልቆጠርንም ማለት ነው።

ዛሬ ባለው የጥገናዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ጥፋቶች ጎልተው የሚታዩት ወላጆች ልጆቻቸውን ለመቅጣት፤ ለመምከር፤ ለማረቅ፤ ለማስተካከል ካላቸው ቁርጠኝነት ስስነት የመነጬ ነው። 

ዛሬ ሁሉም ሃላፊነት አለበት ነፃነትን በአግባቡ ለመተረጎም እና የተገኘውን ነፃነት ሥርዓትን ጠብቆ ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመምራት። ለዚህ ደግሞ ወላጆች መልካም ያልሆነውን ነገር ለይተው ለልጆቻቸው በመንገር እና ልጆችን በተከታታይ በመምከር ልጆች ነጋቸውን እንዳያጠቁሩ፤ ነጋቸውን እንዳያበልዙ፤ ነጋቸውን እንዳያጠወልጉ ሳይደክሙ፤ ሳይታክቱ ማስተማር ይኖርባቸዋል።
ሚዲያዎችም በዚህ ዙሪያ መስራት አላባቸው። 

ሚደያዎች ብሶትን፤ መርዶን፤ የሚያባስሱ የፍርሻ አዋጆችን ከማወጅ ተቆጥበው ልጆች የአገር ተራኪቢነታቸውን በተሟላ ሞራል ታንጸው እንዲከውኑት ማበረታት አብነት ያላቸውን ወጣቶች ወደ ፊት በማውጣት አርያነታቸውን እንዲከተሉ በማደረግ ተግባር ላይ አትኩሮት ማድረግ ይገባቸዋል።

ልጆች ከማናቸውም አፍራሽ ተልኮ ካላቸው ቡድኖች፤ ግለሰቦች አመለካካት እና ዝንባሌ ተቆጥበው መልካምነትን፤ ደግነት፤ ቸርነትን፤ አክብሮትን፤ ሥራ ወዳድነትን፤ ታታሪነት አጠንከረው እንዲገፉበት ወላጆች ሰፊውን ድርሻ ሊወስዱ ይገባል።

አሁን ያለው ቁልፉ ጉዳይ ወላጆች ላይ ነው። እርግጥ ነው ጎዳና ላይ የወጡ ልጆች በብዛት አሉን። እነሱንም ዬዬከተማው አስተዳደር የወጣት የመልካምነት እሳካዎቶችን በማዘጋጀት በተወሰነ ጊዜ በሃላፊነት ስሜት ተኮትኮተው የሚያድጉበትን መንገድ መፈልግ ይኖርባቸዋል። 

አብሶ ወደ ፈለጉት የሃይማኖታዊ ተቋማት እንዚህ ታዳጊዎች እንዲያዘንብሉ ከሆኑ ሞራላዊ ልዕናቸው ከፍ ወደ አለ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል።

ነገን ከአስፈሪነት ወደ ተስፋነት ለማስቀጥል ልጆች ላይ ሊሰራ የሚገባው ተግባር ባሊህ ባይ ሊያገኝ ይገባል። ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ስለሚያምኑ በዬትምህርት ቤቶች የመልካምነትን አብነት የሆኑትን ወጣቶች ለጥቂት ደቂቃ ልምዳቸውን ተመክሯቸውን እንዲያስተላልፉ ማድረግ ይገባል። በዚህ ላይ ከተቋማዊ ተልዕኮዎች በላይ ባህላዊ ሂደቶች እጅግ ውጤታማ እና አበረታች ስኬትን ያጎናጽፋሉ እና በዛ ላይ መትጋት ይገባል።

ምን አለ እያንዳንዱ ከተማ በሳምንት አንድ እሁድ ለሁለት ሦስት ሰዓት አካባቢውን ቢያጸዳ። ለዚህ ደግሞ የዕድሜ ባለጸጎች አብነቱን እራሳቸው ቢጀምሩት ወጣቶች ይከተሉታል።

የከተማ አስተዳደሮች የዓመት ሰንጠረዥ አውጥተው በከተሞች ያሉ የመሥሪያ ቤት ሰራተኞችን በነጻ አገልግሎት ከወጣቶች ጋር እዬመዱቡ ቢያሰሩ ለጤናም ለማህበራዊ ህይወትም ሰፊ ድርሻ አለው።

ይህን ለወረት ሳይሆን ቋሚ በሆነ ሁኔታ ሁሉም አካባቢውን የሚያጸዳበት ባህል ቢጀመር የመንግሥትን ወጪም ኃላፊነትንም ይቀንሳል። በማህበራዊ ህይወት ዘርፍ ከሚጠፋው ጊዜ አንዱን ክፍል በኃላፊነት ተርክቦ አብነት ያለው ተግባር መከወን መጀመር ዛሬ ተግባር ይሆናል ይህ ተከታታይ ተግባር ሲቀጥል ደግሞ ዕድሜ ጠገብ ሲሆን ባህልም ታሪክም ይሆናል።

ሁሉንም ኃላፊነት መንግሥት ይወጣው ነው እኔ እያዬሁት ያለው። መለዬት አልቻልንም የህዝብን ኃላፊነት እና የመንግሥትን። መለዬት አልቻልነም  የእኔ እና የእኛን።

አሁን ስለ ሰላም ጉዳይ ስናነሳ ሰላም የራስ ነው። ሁሉም ለአካባቢው ዘብ ለመቆም መጣር አለበት። አፍራሾች የሚሉትን በመናቅ ገንቢዎች የሚሉትን በማደመጥ ሁሉም ለራሱ ለአካባቢው፤ ለጎረቤቱ ዘብ ቢቆም ኃላፊነትን በመከፋፈል ኃላፊነትን ያቀላል።

መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የ50 ዓመት የገነገነ ችግር ሃላፊነት ተከምሮበታል። በዛ ላይ አዲሱ የጥገናዊ ለውጥ ባዶ ካዝና እና ዕዳ ነው የተረከበው። ይህም ብቻ አይደለም የሴረኞች ሴራ ሳቦታጁም እጅግ የከፋ ነው። 

ስለሆነም ሰው ተግባሩን ተግቶ አይከውንም። ከሚከፈለው በታች ነው ሰራተኛው የሚሰራው። አንድ ሰው ከሚከፈለው በላይ መስራት ሲኖርበት የሚከፈለውን የሚመጥን ተግባር ለመከወን አለመተጋት ሸክምነት ነው። ራሱ የመንግሥት ሠራተኛው የአገር ሸክም ነው የሆነው። 

የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ይህ ጥገናዊ ለውጥ ቢጨናገፍ የመንግሥት ሠራተኛው፤ ባለማህያው ሁሉ ለማኝ ይሆናል። ይህ ደግሞ በዘመነ ደርግ ጊዜ ታይቷል።
ወደ ቀደመው ምልስት ሳደረግ በዚህም የኢኮኖሚ ድቀቱ አለ። የለም የሚባሉ ነገሮች እያሉ ሁሉ ታሽገው ቀናቸው እንዲያልፍ እዬሆነ ነው። 

ከብዙ ድካም መዳን የቻለው ተፎካካሪ በሉት ተቃቀዋሚ ተቃዋሚ በሉት ተቀናቃኝ ሁሉ ራሱ ችግር ፈጣሪ ነው። ነፃነት ያገኘው ሁሉ ችግር አምራች ነው። ይህን ሁሉ መከራ የኢትዮጵያ መንግሥት ተሸክሞ ቢያንስ የነፍስ ወከፍ ግዴታን አለመወጣት ራሱ አገር አፈርሽነት ነው። የትውልድም አባካኝነት ነው።

የኢትዮጵያ መኖር ለሁሉም የሚበጅ ነው። አገር ከሌለ ሁሉም የለም። ይህን የኢትዮጵያ ህዝብ እብሶ ሊሂቃን የሚባሉት የተረዱት አይመስልም። ዝናም፤ ክብርም፤ ሞገስም፤ ማማርም መኖርም ብቻ ሳይሆን ሞትም የሚያምረው አገር ስትኖር ብቻ ነው። አሁን የሚታዬው ግን እጅግ የዘመነ የቅልጣን ጉዳይ ነው። „ቂጥ ገልቦ ራስ ተከናኒቦ“ አይነት ነው።

ነፃነት ዋጋ ተከፍሎበት እንጂ ከሰማይ የተገኜ መና አይደለም። ግን የተከፈለውን ያህል ሃላፊነት ለመውሰድ ያለው ተነሳሽነት ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነው። አገር የሚገናበው በትብብር፤ በመደማመጥ፤ በመቻቻል፤ በመከባባር አንቺ አንተ ትብስ በመባባል እንጂ በፉክክር አይደለም።

የእኛው ግን ፉክክር ነው፤ አሉታዊ እልህ ነው፤ መታበይ ነው፤ ሴራ ነው፤ ሸር ነው፤ ቱማታ ነው፤ ጥድፊያ ነው። ገና ነፃነትን አላውቅናትም። ያሰለፈነው የ27 የጨለማ ጊዜ ተመክሮ ምንም አላስተማረንም። 

ይህ የጥገናዊ ለወጥ አመራር ሆነ ቅልጥፍና ሳናስበው የተገኜ ትሩፋት ሆኖ ሳለ አሁን በመጎርጎር መንፈሱን ሰርቀን ቀፎውን ለማስቀረት ስንታክት እንገኛለን። ልብ ይስጠን ፈጣሪ። አሜን!

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

የኔዎቹ ደጎቹ ቅኖቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።