(ለመንግስትና ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች)

ከአቶ ጀንበሩ አረጋ ፔጅ ነው ያገኜሁት። አላነበብኩትም።
እንዳያመልጠኝ ነው ፖስት ያደረግኩት።
ይድረስ ለመሪዎቻችን !!
(ለመንግስትና ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች)
ስለአገሬ ሰላምና ደህንነት አሁንም እጮሀለሁ !!
በጀምበሩ አረጋ (ረ/ፕሮፌሰር)
ጎንደር ዩኒቨርስቲ ስነ-ትምህርት ኮሌጅ
ሀ) ታሳቢዎች (Assumptions)
አገሬ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ውስጣዊ ፈተና በፍጥነት ትወጣ ዘንድ ይህንን የአጭር ጊዜ የመፍትሔ ሀሳብ በራሴ ተነሳሽነት ሳቀርብ የሚከተሉትን ጉዳዮች ታሳቢ አድርጌ ነው፡፡
 የአገሬና ሕዝቧ ሰላምና ደህንነት እንደሚያስጨንቀው አንድ ተራ ዜጋ ለሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ያለኝን ከመወርወርና ከቅንንነት በስተቀር ምንም አይነት ሌላ ፖለቲካል ፍላጎት (Other Political Interest) የሌለኝ መሆኑን ትረዱኛላችሁ በሚል
 የመንግስትና የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ከተስተካከለ የአገራችን ችግር በወሳኝ መልኩ መፍታት እንችላለን የሚል ጠንካራ ዕምነት ስላለኝ
 ከመንግስትና ከገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካከልየችግሩ አሳሳቢነት የሚያስጨንቃቸው አንዳንድ አመራሮች ይኖራሉና ለመፍትሔውም ይተጋሉ የሚል ግምት ስላለኝ
 ከታሪካችን እንደምንረዳው መላ የአገራችን ሕዝብ መንግስት የሚለውን በቀላሉ የሚያምንና በጠንካራ መንግስት አስፋላጊነት የሚያምን እንደሆነ ስለምረዳ
 መሰሪ ፖለቲከኞቻችን በየመድረኩ እንደሚያስጮሁት የጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት ሳይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትን የሚፈልግ ነው የሚል ጠንካራ እምነት ስላለኝ ነው፡: ለሕዝብ እብሮነትና የጋራ ተጠቃሚነት የሚተጉ ቅንና ቆራጥ መሪዎችን ወደፊት ካመጣናቸው የሕዝቧ ሰላምና ደህንነት የተረጋገጠማት ውጫዊ ጠላቶቻችን በርቀት የሚያከብሯትና በቀላሉ የማትደፈር ጠንካራ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ዕውን እናደርጋለን የሚል ውስጣዊ ምኞትና እምነት ስላለኝ ነው፡፡
ለ) የት ላይ ነን ? ዋነኛው ችግራችንን የቱ ነው?
ባለፉት ሁለት አመታት የገባንበት የእርስበርስ ጦርነት ጥሎብን ካለፈው ጠባሳ በአግባቡ ሳናገግምና የጦርነቱ መሰራተዊ መንስኤም በአግባቡ ዕልባት ሳያገኝ አገራችን በችግር ላይ ችግር እየተደራረበባት ይገኛል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በአገራችን የተፈጠሩ ችግሮችን መዘርዘር ጊዜ ማጥፋት ነው፡፡ የሚታዩ ችግሮች ተደምረውና ተቀንሰው ሲጠቃለሉ የዜጎች መፈናቀልና ሞት የዘወትር ተግባር የሆነባት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ለርሀብና ቸነፈር የተጋለጡባት፣ የባለስልጣናት ሌብነትና መጠቃቀም የተንሰራፋባት፣ በኑሮ ውድነት አብዛኛው የከተማ ሕዝብ እየተሰቃዬ ያለባት፣ ዘግቶበልነት የተለመደ የኑሮ ዘይቤ የሆነባት፣ የብዙሐኑ ሞራልና ትውፊቶች በጥቂቶች ስግብግብ ፍላጎት የሚጨፈለቅባት፣ የማይደፈሩና የማይነኩ ሐይማኖታዊ ቀኖናዎችና ትውፊቶች ጊዜ ባገነናቸው ጋጠወጦች ያለከልካይ በአደባባይ የሚጨፈለቁባት፣ምዕመናን በእምነታቸው ምክንያት በመንግስት ኃይሎች በአምልኮ ስፍራዎች በጠራራ ጸኃይ በጥይት የሚደበደብባትና የሚረሸኑባት፣ዜጎች በራሳቸው አገር የመንቀሳቀስና የመኖር መብታቸው የተነፈገባት፣ ሕግ ይከበር ብሎ የሚጠይቅን ሕዝብን (ለምሳሌ ከአገራችን ጠቅላላ ሕዝብ ግማሽ የሚሆነውን መላ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይን) በመንግስት ሜዲያ ቀርቦ ”ቆሞ ቀር” ብሎ በአደባባይ በጅምላ የሚዘረጥጥ ክልላዊ መንግስትና ጋጠወጥ መሪ በነጻነት የሚንደላቀቅባት፣ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ሃላፊነት በጎደለው መንግስታዊ ቡድን በጅምላ የሚሰቃዩባት፣ዜጎች በሰላም ወጥተው የመግባት መብታቸውና የመኖር ሰብአዊ መብታቸው የተነፈገባት በአጠቃላይም ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነት የሌለባትና የተረጋጋ መንግስታዊ ስርዓት የሌለባት አገር ከሆነች ሰነባበተች፡፡
ለዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ የዳረገን ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶችን መዘርዘር ቢቻልም ዋነኛው ምክንያት ግን ላለፉት 50 ዓመታት በአገራችን የተዘራው መርዘኛ የዘውግ ፖለቲካ የወለደው የጥላቻና መጠፋፋት የውሸት ትርክት፣ ድርጊትና የዚሁ ትርክት ውጤት የሆነው አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ልፍስፍስነት ነው፡፡ በአጭሩ አገራችን የአመራር ቀውስ ውስጥ በመግባቷ ለህልቆ መሳፍርት አደጋዎች ተጋልጣለች፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው አብዛኞቹ የአሁኖቹ “መሪዎቻችን” በዚህ አደገኛ ትርክት ተኮትኩተው የጥላቻ መርዙን እየተጋቱ ያደጉ ፍጡራን በመሆናቸው የዘውግ አባቶቻቸውን ባህሪ ወራሾች ቢሆኑ ሊደንቀን አይገባም፡፡ “ለውጡ” እየተባለ ጆሯችን እስኪደነቁር የሚነገረን “ሪፎርም” ከቅዠት ያለፈ ካለመሆኑም በላይ አገራችን ወደከፋ አዘቅት እየወሰዳት እንዳለ በየእለቱ እየሰማን፣እየተመለከትንና እየኖርነውም ነው፡፡ ራሳቸውን የሁሉም መልካም ነገር ምንጭ አድርገው የሚቆጥሩት የ”ለውጡ” አጋፋሪዎች የአገራችን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊትና አሁናዊ የሕዝብ ፍላጎትን በሚመጥን ደረጃ የሚገኙ ባለመሆናቸው ችግሮችን በጥበብና በብልሀት ከመፍታት ይልቅ በቅዠት፣በሴራ፣ በድንፋታና በነውጥ የደመነብስ ጉዞ መምረጣቸው አገራችን ከድጡ ወደማጡ እየወሰዷት ይገኛሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በአገራችን ውስጥ በየዕለቱ ለምናያቸው ችግሮቻችን የሚታወቁ ውጫዊ ምክንያቶች ቢኖራቸውምና ከሕብረተሰቡ የስልጣኔና ዘመናዊነት ጉደለት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በእኔ አተያይ አገራችን ወደአዘቅት እየወሰዳት ያለው መሰረታዊው ችግር ግን የመሪዎቻችን በአግባቡ መምራት አለመቻል፣ስግብግብነትና ቅንነት መጓደል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ ያለበትና መጠዬቅ ያለበት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አሊ መንግስትና የፕሬዚደንት አብይ ፓርቲ (ብልጽግና) ነው፡፡ በእርግጥ በዚች አገር ውስጥ የፓርቲና የመንግስት ስራ የተደበላቀና ከኢህአደግ አሰራር እንዳለ የተወረሰ በመሆኑ ፓርቲውን ተጠያቂ አደረክ ማለት መንግስትንም ተጠያቂ አደረክ ማለት ነው፡፡ ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡
የችግሩ ባለቤት እስከቀበሌ ድረስ ያለውን ሁሉንም የመንግስት አመራርና የፓርቲ መዋቅር (እኔንም ጨምሮ) የሚመለከት ቢሆንም የሁሉም ነገር ፈጣሪ (ስልጣን ሰጪና ነጣቂ) የሆነው የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ትልቁን ድርሻ ይስዳል፡፡ በእኔ ትዝብት የአመራር ክፍተቶቹ መገለጫዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
 ከሁሉም በላይ ገዥዎ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮቹ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ድርጃታዊና መንግስታዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ስለመሆናቸው/ አለመሆናቸው የሚከታተልበት የኦዲትና ኢንስፔክስሽን አሰራር ስራ ላይ እየዋለ ባለመሆኑ በየፊናው የሚፏልለው ባለስልጣን ተበራክቷል፡፡ የፓርቲ ዲስፕሊን የሚባል ነገር በአባላቱም ይሁን በአመራሩ ዘንድ አይታወቅም፡፡ሁሉም ያለተጠያቂነት ስሜቱ በነዳው ልክ የሚዘባርቅበት አሰራር የተለመደ ሆኗል፡
 ሙገሳን እንጂ ትችትንና ድክመትን ለመቀበልና ለማስተካከል የማይፈልግ አመራር በከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከተ መምጣቱ
 አሁን ካለንበት አካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎች ተነስቶ መጪውን ጊዜ ቀድሞ ተንብዮና አስቀድሞ ተዘጋጅቶ ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን በድል ለመወጣት የተዘጋጀ (proactive) ሳይሆን በየጊዜው የሚነሳውን አሳት ለማጥፋት መሯሯጥን (reactive) መደበኛ ስራው አድርጎ የሚመራ አመራር መበራከቱ
 ለመናገር እንጂ ለማዳመጥ ጊዜ የሌለውና ጆሮውንም በስሚንቶ የደፈነ አመራር መበራከቱ
 መንግስት ነኝ የሚል አካል ባለበት አገር ዜጎች የሆነ ብሔር አባል በመሆናቸው ብቻ በአገራቸው ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተደጋጋሚ መንግስታዊ እገዳና ክልከላ በማድረግ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እያደረገ ያለ መንግስት መሆኑ
 ለአለቃው በማጨብጨብና በማደር ስልጣኑን ለማቆዬት የሚተጋው አመራር እየተበራከተ መምጣቱ
 ስልጣንን የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት የምንጠቀምበት መሳሪያ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ እንደሐብት ምንጭነት የሚመለከተው አመራር እየተበራከተ መምጣቱ፡፡ በዚህም ምክንያት ስልጣንን በምልጃና በእጅ መንሻ ከስልጣን አከፋፋይ የፖለቲካ ነጋዴዎች (በዬደረጃው ያለ የፓርቲው አስተባባሪ ኮሚቴ) የሚገዛው አመራር እየተበራከተ መምጣቱን የአደባባይ ሐቅ እዬሆነ መምጣቱ
 የፓርቲውና የአገሪቱ መሪ የሆኑት ዶ/ር አብይ በምድር ላይ ያለ የሁሉም ነገር ባለቤትን ምንጭ (የበቁ) አድርገው መቁጠራቸውና አለማወቃቸውንም ለማወቅ ሙከራ አለማድረግ
 በፌደራልና በክልል የሚገኙ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች በተለይም ጠቅላይ ሚንስትሩና አንዳንድ የክልል መሪዎች በተለያዩ ሁነቶች ተገኝተው የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች የሕዝቡን ሞራልና እሴቶች የማይጠብቁ ከመሆናቸውም በላይ በግል ፍላጎትና ጊዚያዊ ስሜት (Emotion) የተጫናቸው መሆንና ለግጭት መንስኤዎች መሆናቸው፡፡ ማይክ ሲጨብጡና ስብሰባ ሲመሩ የማይጠበቅና ጥንቃቄ የጎዳላቸው መልዕክቶችን እንደመጣላቸው መልቀቃቸው የተለመደ ሁነት መሆኑ
 ሞጋች የሆኑ አመራሮችን ወደፊት ከማምጣት ይልቅ ከስርዓቱ ገፍቶ ማስወጣት ወይም አንገት ማስደፋት እየተለመደ መምጣቱ
 የአመራር ምልመላውና ምደባው ብቃትንና ብቃትን (ልምድን፣እውቅትን፣ ክህሎትን፣ አመለካከትን፣ ለሕዝብ አሳቢነትንና (selflessness) ቁርጠኝነትን... ወዘተ) መሰረት ያደረገ ከመሆን ይልቅ በእምነት፣ በጓደኝነት፣ በሰፈር ልጅነት፣ በአበልጅነት፣ በታዛዥነትና የመሳሰሉትን ደካማ መስፈርቶችን ተጠቅሞ ለአድርባይ አመራር ቅድሚያ የመስጠት አሰራር መደበኛ አሰራር መሆኑ፣
 አግላይ የሆነ የአመራር ምደባ አይን አውጥቶ መምጣቱ፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው በርከት ያሉ የአንድ እምነት ተከታዮች ቁልፍ የፌደራል አመራር ቦታዎችን እንዲይዙ በማድረግ ሌላ አደጋ እያስከተለ መሆኑ (ውስጥ ውስጡን እየተብላላ ያለና በአንድ ወቅት ሊፈነዳ የሚችል አውዳሚ ምልክቶች የአደባባይ ሚስጥር እየሆኑ ነው)
 በከፍተኛ አመራሩ መካከል ያለው ግንኙነት እከከኝ ልከክልህ በመሆኑና ከመተራረም ይልቅ ችግሮችን
ማድበስበስና መሞጋገስ የበዛበት መሆን
 የአመራር ስኬትና ውድቀት የሚለካበት ይህ ነው የሚባል ስርዓት ካለመኖሩም በላይ የተጠያቂነትና የግልጽነት ስርዓት አለመዘርጋቱ
 አመራሩ የችግር አፈታት ስልቱ ለችግሮች ባለቤት ከመስጠትና የችግሩን ባለቤት ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የጋራ ባለቤት (ባለቤት አልባ ጥፋቶች) መሆንና አለባብሶ ማለፍን መደበኛ አሰራር አድርጎ መቀጠል
 በየወቅቱ ስራን በግምገማ የመምራት አሰራር ፈጽሞ አለመኖር (በተለይም የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር)
 የፓርቲው አደረጃጀት ከፌደራል መንግስቱ አወቃቀር ጋር አብሮ የማይሔድ በመሆኑና ለስልጣን ሞኖፖሊ የተጋለጠ መሆኑ
 በሕዝብ ላይ የፈለጉትን ደባ የሚፈጽሙ አመራሮች አገር እያፈረሱ እንደሆነ እየታወቀ ከማረም ይልቅ ሽፋን መስጠት የተለመደ አሰራር ሆኖ መቀጠሉ፡፡ ለምሳሌ የአቶ ሽመልስ ድንፋታና የአዳነች ማናለብኝነት ግልጽና ሕቡዕ ክስተቶችን አጋልጧል
 በተወሰኑ ክልሎች ላይ ጠንካራና ሞጋች አመራር እንዳይኖር አልሞ መስራትና የተረጋጋ አመራር እንዳይኖር በቀጥታና በእጅአዙር ጫና ማድረግ (በአሁኑ ስዓት በአማራ ክልል በስራ ላይ ያለው በራሱ የማይተማመንና ደካማ የመንግስትና የፓርቲ ከፍተኛ አመራር ጥሩ ማሳያ ነው)
 ተስፋ የተጣለባቸውና በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ተመርጠው ወደ ተወካዮች ም/ቤትና ክልል ም/ቤት እንዲገቡ የተደረጉ የሕዝብ ወኪሎች ሚናቸውን በአግባቡ እንዳይጫዎቱ ከማድረግ አንጻር ኢሕአደግ ይከተለው የነበረው አፋኝ ስርዓት በሚያስንቅ ሁኔታ ም/ቤቶቹን ማፈን መደበኛ አሰራር እንዲሆን መደረጉ (ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የፌደራሉ የህ/ተ/ም/ቤትና የአዲስ አበባ ም/ቤት )
 ኢህአደግ በመውደቂያው ዋዜማ ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የአብይ መንግስት የህዝብን ቅሬታ በጠመንጃና በወታደራዊ ኃይል ለማፈንና ዝም-ጭጭ ለማስባል በአዳባባይ መደተግባር እየገባ ያለ መሆኑ
 ኢሕአደግ ሲያደርገው ከነበረው ባልተለዬ ሁኔታ መንግስትን በአደባባይ የሚሞግቱና የመንግስትን ድክመት የሚያጋልጡ ግለሰቦች፣ጋዜጠኞችና የማህበረሰብ አንቂዎችን የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈበረኩ ማሳደድና ለአስር መዳረግ የተለመደ ማፈኛ አሰራር ሆኗል
 በመንግሰትና በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ያሉት ሚዲያዎች የሕዝብ አይንና ጆሮ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ ኢሕአደግ ይከተለው ከነበረው አፋኝ ስርዓት በባሰ ሁኔታ ሚዲያዎቹን ማፈንና የመንግስትና የገዥው ፓርቲ ልሳኖች ሆነው እንዲያገለገሉ በማደረግ መደበኛ አሰራር እንዲሆን መደረጉ
 አብዛኞቹ የፓርቲና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮቻችን የአገራችን ታሪክና የሕዝቡና ስነልቦና በውል ያልተረዱና የሚያውቁትም ቢሆኑ ቅንነት የጎደላቸው በመሆናቸው በየመድረኩ ግልብና ጥራዝ ነጠቅ ቅንጭጫቢ ድስኮሮችን የሚያድርጉ በመሆናቸው ለግጭት እየዳረጉ መሆናቸው
 አብዛኞቹ የገዥው ፓርቲ አመራሮች ብዙሀኑን የአገሪቱ ሕዝብ የሚከተለውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥላቻ የታወሩ በመሆናቸው በቅድስት ቤተክርስቲያኗና በአማኞቿ ላይ ታሪኳንና መልካም ስሟን ማጥፋትና ተራ አሉባልታ የሚዘሩ አንዳንድ የሌላ እምነት ነብይ ነን ለሚሉ ግለሰቦች (ዮናታን አክሊሉ፣ አዩ ጩፋና ሌሎች) ከማረም ይልቅ በቀጥታና በእጅ አዙር “አይዟችሁ” በመባላቸው ለግጭት መንስኤ እየሆኑ መምጣታቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ተጠያቂው የፓርውና የመንግስቱ መሪ የሆኑት ጠ/ሚንስትር አብይ ናቸው፡፡ በኢት/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ላይ በሰሞኑ የተስተዋለው መንግስት መራሹ ጣልቃገብነት ያስከተለው ቁጣና አገራዊ አደጋ የመነጨው በጥላቻ ከታወሩት አድሏዊ መሪዎቻችን ያልበሰለና መካሪ አልባ እይታና ድርጊት የመነጨ ነው፡፡
 የእኔነት አስተሳሰብና ድርጊት እየጎላ መምጣትና የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ጠባብ ፍላጎትን (ምንአልባትም አገር የመሆን ፍላጎትን) ለማሳካት የማይነኩ ነገሮችን ሁሉ በማናለብንነት መነካካትና አለመረጋጋት መፍጠር (የአዲሰ አበባዋን የአዳነችና የሽመልስን የተናበበ ሕቡዕ ፍላጎት ቆም ብሎ መፈተሸ በቂ ነው)፡፡ የሚገርመው ነገር ያ-ሁሉ አይን ያወጣ ጥፋት ሲፈጸም የአገሪቱ መሪ አንድም ቀን ሲገጽጹ አለመሰማታቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጥርጣሬ ያለፈ እየሆነ ያለ እውነታ መሆኑ፡፡
 የአገሪቱ ቁንጮ የሆኑት ሰው በማወቅም ባለማወቅም አራችንና መላ ሕዝቧን የሚጎዳ ሀሳብ ሲሰነዝሩና ወደተግባር ሲለውጡ በዳር ተመልካችነት የተሰለፉትና አጤሬራ ለመያዝ ተቸክለው የምናያቸው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣የአገራዊ ሰላምና ደህንነት ም/ቤት አባላት፣ የሚኒስትሮች ም/ቤት አባላትና ሌሎች በዙሪያቸው በአማካሪነት ስም የተኮለኮሉ አካላት የችግሩ አካል ናቸው፡፡
ሐ) ከዚህ ችግር እንዴት እንውጣ?
አንድ አባባል አለ-The Elephant in the room!! አባባሉ በአጭሩ ሲጠቃለል “ክፍሏን ለማጽዳት መጀመሪያ ዝሆኑን ከክፍሏ አስወጣው” እንደማለት ነው፡፡ No more Business as Usual. It is a high time to think and act out of the Box!! ከመሸግንበት ሳጥን እንውጣና የማይቻል የሚመስለውን እንጋፈጠው፤ ለትልቁ ችግር ቅድሚያ እንስጥ ለማለት ነው!!
አገራችን አሁን ከገጠማት ውስብስብ ችግር ለመውጣት ብዙ ማሰብና ማንሰላሰል የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ቅንና በሩህ ልቦችንም ይፈልጋል፡፡ ከተለመደው አሰራር ወጣ ብሎ ማዬትና ወደስራ መግባትም የግድ ነው፡፡ መፍትሔዎቹን ከረጅምና ከአጭር ጊዜ አኳያ መቃኘት ያስፈልግ ነበር፡፡ የምርጫ ዘመኑ ሲቃረብ የአገርን ጥቅም የሚያስከብሩና የህዝቡንም ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ስትራቴጅክ ጉዳዮች እንደ አገርም ሆነ እንደክልል ከወዲሁ መታሰብ ይኖርባቸዋል ፡፡ በዚህ አጭር ጹህፍ የእኔ ትኩረት የአጭር ጊዜ በስልጣን ላይ ያለው መንግስትና ገዢው ፓርቲ አገራችን ከገጠማት አሁናዊ ፈተና በፍጥነት ትወጣ ዘንድ (በተለይም ከአመራር አንጻር) ምን መሠረታዊ ርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ መጠቆሙና ማመላከቱ ላይ ትኩረት ማድረግ መርጫለሁ፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የችግሮቻችን ስረመሰረቶች ውጫዊና ውስጣዊ ተብለው የሚከፈሉ ቢሆንም የእኔ ትኩረት ውስጣዊ ችግራችን በተለይም ከመንግስትና ከገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የጥንታዊት ወድ አገራችን ታሪክና ባህል በሚመጥን ደረጃ መምራት አለመቻልና የአገሪቱ መሪ ግልጽነት የጎደለውና የተወናበደ አካሄድ (Sorry to say this but I have to say it) ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የመፍትሄ ሀሳቦቸም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት አሁን ካለንበት አሳሳቢ አገራዊ ሁኔታ በፍጥነት እንወጣ ዘንድ፡-
 በመጀመሪያ ደረጃ በብዙ የስጋት አመላካቾች አሁን አገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን መቀበል ይገባል፡፡ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች አሁን ባሉት ተጨባጭ ችግሮች ላይ የጋራ መግባባት መድረስ ይጠበቅበታል
 በየቦታው በአመራሩ ድክመትና ስውር ፍላጎት የተፈጠሩ ችግሮች የአገራችን ሕልውና አደጋ ላይ እየጣሉና በፍጥነት ካልተሰተካከሉም አገራችን የባሰ አደጋ ውስጥ የመግባት እድሏ ሰፊ መሆኑን ከልብ መቀበል ይገባል
 ከዚህ የአገር አደጋ በፍጥነት ለመውጣት የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አጭር እቅድ አውጥቶ አሁን ለደረስንበት አስከፊ ደረጃ ለምን ልንደርስ ቻልን እንዴትስ ማስተካከል እንችላለን በሚል ቁጭት በሩን ዘግቶ የግለሰብና የአካል ግምገማ ማድረግ አለበት
 በዚህ ግምገማ በመላ አገራችን በ4ቱም አቅጣጫዎች ለተፈጠሩ የሕዝብ ሰቆቃዎችና በደሎች ማን ምን ድርሻ ነበረው የሚለውን መለዬት ያስፈልጋል
 ከሰቆቃዎቹ በስተጀርባ አገርን ሊያጠፉ የሚጭሉ ድብቅ ፍላጎቶችስ ምን ምን እንደሆኑ በአግባቡ መለዬት የግድ ይሀናል ማለት ነው
 በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነት የሚወስድ አካልንና ግለሰብን መለየየት መረሳት የሌለበት ተግባር ነው
 በችግሩ ምንነት፣ በችግሩ መሰረታዊ መንስኤና በችገሩ ባለቤት በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ በጥብቅ ድስፕሊን በሚመራ ግምገማ የጋራ መግባባት ከተደረሰ በኋላ አውዱን የሚመጥን የማስተካከያ መንገዶችን መቀየስ ይገባል
 በፓርቲው ሕገ ደንብ መሰረት የገዥውን ፓርቲ አስቸኳይ ወይም ልዩ ጉባኤ በመጥራት የከፍተኛ አመራሩን የግምገማ ሪፖርት በጉባኤው መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይገባል
 አሁን ከገጠመን ፈተና በፍጥነት እንወጣ ዘንድ በአንጻራዊነት መሰረታዊ የአመራር ብቃቶችብ የሚያሟሉ፣ቅን፣አድሏዊነትን የሚጸዬፉ፣ቆራጥና የሕዝብን ጥቅም በተግባር የሚያስቀድሙ አመራሮችን ወደፊት በማምጣት የፓርቲውን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደገና ማደራጀትና እንደአስፈላጊነቱ የፓርቲውን ፕሬዚደንትና ም/ፕሬዚደንቶች እስከመቀዬር ድረስ ሊታሰብ ይገባል፡፡ በዚህም መሰረት የፌደራልና የክልል የመንግስትና የፓርቲ ከፍተኛ አመራሩን እንደገና የማደራጀት ስራ ይከናወናል
 ለአገር ሕልውና አደጋ የሆኑትን አመራሮች እንደጥፋታቸው አይነትና ልክ የማስተካከያ (አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ) ርምጃ መውሰድ
 ቀጥሎም በዬደረጃው ያለ የፓርቲውንም ሆነ የመንግስት አመራር ምደባውን እንደገና መፈተሸና ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል
 የፓርቲውን አደረጃጀትም እንደገና መፈተሸ ትኩርት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ አሁን ያለው የፓርቲው አደረጃጀት ለአንዳንዶቹ ክልሎች ፍጹም ማናለብኝነትን ያጎናጸፈ ሲሆን በአንዳንዶቹ ክልሎች ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደፈለጉ እንዲሾሙና እንዲሽሩ በር የከፈተ ስለሆነ ለጣልቃገብነት ተጋልጠዋል፡፡
 የረጅም ጊዜ ስትራቴጅክ የለውጥ እቅዶችን የሚነድፍና የሚመራ ግብረ ኃይል በክልልና በፌደራል ደረጃ ማደራጀትና ወደስራ ማስገባት ያስፈልጋል
 ከፌደራል መንግስቱ (ከጠቅላይ ሚንስትሩ በስተጀርባ) በስተጀርባ መሽገው የፌደራል መንግስቱን በፈለጉት ካርታ የሚያጫውቱ የያ-ትውልድ ቅሪቶችና አክራሪ የተንኮል አባቶች ከጣልቃገብነትና እጃቸውን ከሚያስረዝሙበት የአሰራር ክፍተት የሚገለሉበትና ስርዓት የሚይዙበት መንግስታዊ አቋምና ተግባራዊ ርምጃ መወሰድ አለበት
 በመጨረሻም የሕግ ማሻሻያዎችም ካስፈለጉ ከሁኔታው ጋር የተጣጣሙ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች የሚዘረጉበትና ስራ ላይ የሚውሉበት ሁኔታ መታሰብ አለበት፡፡
መ) ከሳጥኑ ወጥተን ማሰብ ካልቻልንስ?
የአመራር ማስተካከያ ለማድረግ ካልታሰበበትና በተለመደው አግባብ (Business as Usual) እውነታዎችን በአዳራሽ ውስጥ ድስኩር፣ በመሞጋገስ፣ በጭብጨባና በማይጨበጡ ቅዥቶች (fantasy) ውስጥ እወነታውን ሸውደን ለማለፍ የምንቀጥል ከሆነ ምን ሊከስት ይችላል? የሚለው ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ It is a high time to think and act out of the Box. If not, the worst will be in place!! ከተደብቅንበት ሳጥን ወጥተን ለመስራት ቁርጠኝነት ካላሳዬንና በይሉኝታ ታውረን አገራችን መምራት አንቸገርም ብለን የምናሰብ ከሆነ በእኔ ግምት የሚከተሉት ክስተቶች ተጠባቂዎች ናቸው፡፡
 የሕዝብ ሰቆቃ ወደከፋ ሁኔታ ይሸጋገራል ከዚያም ስርዓት አልበኝነት በመላ አገራችን ሊፈነዳ ይችላል፣የእርስ በርስ ግጭት ከስጋትነት ወደ እውን መሆን ሊሸጋገር ይችላል
 የአገራችን ሕልውና ለታሪካዊ የውጪ ጠላቶቻችን ጥቃት የበለጠ ይጋለጣል፤ የአገራችን ሕልውናም በቀላሉ ሊመለስ ወደማይችል አደጋ (unprecedented Danger) ውስጥ ሊገባ ይችላል
 አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የግጭቶችን መፋፋም በአይነ ቁራኛ እየጠበቀ ያለው የሕወኃት ወራሪ መንጋ በመላ አገራችን በተለይም በአማራና በአፋር ክልል 4ኛውን ዙር ወረራ ሊጀምርና አስካሁን ያለታዬ ቀውስ ሊያስትል ይችላል
 አገርን የመበተን ሙከራዎች በየአቅጣጫው ሊከሰቱ ይችላሉ በአጋጣሚውም የዘውግን ካባ የለበሱ ጥቃቅን ነገስታት በየጥጉ ሊፈለፈሉ ይችላሉ (ዘመነ-ዘውጋዊያን)
ሁኔታው ሲከፋና በገዢዎቹ በደል የተንገፈገፈና ተስፋ የቆረጠ ሕዝብ መሪዎቹን የሚበላበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል የአንዳንድ አገሮችን ታሪክ ማስታወስ ይገባል እላለሁ፡፡
የመጨረሻ ቃሌ
ስልጣንም ሆነ ዕድሜ በጊዜና በአጋጣሚዎች የተወሰኑ ናቸውና አገራችን ከገባችበት አዘቅት ለማውጣትና ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ እንችል ዘንድ ራስ ወዳድ ባለመሆንና በቅን ልቦና በመትጋት የየድርሻችን በጎ አሻራ እናስቀምጥ እላለሁ!!
አስተውሎትን ይስጠን !!
የካቲት 7፣2015 ዓም
ጎንደር፣ኢትዮጵያ

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።