ከአባ ጌዴዎን ዘደብረሊባኖስ ለሶፍያ ሽባባውና መሰል ምልከታ ላላቸው ሁሉ ተጻፈ 29/07/2015 ዓም

 

ከአቶ ብርኃኑ ደርብ ያገኜሁት ነው። ጠቃሚ ስለሆነ ሼር አድርጌዋለሁኝ። የተከባበር መልስ ነው።
ይድረስ ለሶፍያ ሽባባው...እና መሰሎቿ ከገዳም አባት የተላለፈ መልዕክት
ከአባ ጌዴዎን ዘደብረ ሊባኖስ
©
ከሁለት ቀናት በፊት "ይድረስ ለኦርቶዶክስ ጳጳሳትና መምህራን!!" በሚል በገጽሽ የለጠፍሽውን ልጥፍ ከነተሰጠው አስተያየት ጭምር አነበብኩት። በዋናነት ሐሳብሽ "እንደዚህ ናችሁና እንደዛ ብትሆኑ" የሚል ከፍረጃ ተነስቶ በጣም በጥንቃቄና በጥበብ የተጻፈ መሆኑን ጽሑፉ በራሱ ይናገራል። የመልእክትሽ ዋና ዓላማም "ይህንን አድርጉና ወደ ኦርቶዶክስ መልሱን!!" በሚል በመግቢያው ተገልጿል። በአጠቃላይ ጥንቃቄ ለተሞላው በጨዋ ደንብ ለቀረበ ሐሳብሽ አድናቆትና ምስጋና አለኝ።
ሰዎች ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚርቁበት ያልሽው ምክንያት ዘርዝረሻል። በስተመጨረሻም ይሁንልኝ ያልሽውን እርማት እንዲህ በማለት" የአለም ሁሉ መድሀኒት ለሆነው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ክብርና ምስጋና እውቅና ትስጥ ያኔ ወደ ኦርቶዶክስ ከሚመለሱት ቀዳሚዋ እኔ እሆናለሁ!" ሐሳብሽን ቋጭተሻል።
ይህን ምላሽ የምጽፍልሽ አንድ ታናሽ አገልጋይ የደብረሊባኖስ ገዳም መነኩሴ ስሆን የማገለግለውም በነገረመለኮት ዩኒቨርስቲ የአንጻራዊ ነገረመለኮትና የሥነ ልቡና መምህር ሆኜ ነው።
በቅድሚያ ጽሑፍሽ "ጉድለት" ወይም "ደካማ ጎን" ብሎ በፈረጀው እሳቤ ላይ የሚያጠነጥንና እንደመፍትሒ ጠቁሞ የሚቋጭነው። በዚህም የቤተክርስቲያኒቱን ጠናካራ ጎን ማንሳት አልተፈለገም አሊያም ዕውቅና መስጠትን ሳይሻ በአሉታዊ ጀምሮ በአሉታዊ ይጨርሳል። ከዚህም በመነሳት ለቤተክርስቲያኒቱ ያለው ምልከታ አንድ ጎን ብቻ መሆኑ ነው።
በቅድሚያ ግለሰቦች ፈጠሩት ላልሽው ችግር ቤተክርስቲያኒቱን ተጠያቂ አድርገሽ መፈረጅሽ አግባብ አይደለም። እንዳልሽው ችግሩ ካለ ግለሰቦች በየትኛው ሥፍራ ተመሳሳይ አካሔዶችን ሊከተሉ ይችላሉ። ነገር ግን እንደቤተክርስቲያን ከኃላፊነት አንጻር ተጠያቂ ለማድረግ በቅዱስ ሲኖዶስ ወስና የተቀበለችው ሐሳብ መሆን አለበት።
ለዛሬ በዋናነት መልስ የሚያስፈልገው የተዛባ ምልከታሽን ሰፋ አድርጌ በማየት ልቋጭ። በሐሳብስ በስተመጨረሻ በሰፈርሽው ሐሳብ " የአለም ሁሉ መድሀኒት ለሆነው ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ክብርና ምስጋና እውቅና ትስጥ ያኔ ወደ ኦርቶዶክስ ከሚመለሱት ቀዳሚዋ እኔ እሆናለሁ!" ብለሻል። በዚህም ቤተክርስቲያኒቱን ከውጪና በጠላት አፍ ከሚነዛባት ሱሑት እሳቤ ተነስተሽ የግምትሽን ሐሳብ ከመሠንዘር በቀር ጠጋ ብለሽ ከውስጥ እንዳላወቅሻት ማሳያ ነው። ሐሳብሽን አንድ በአንድ ማየትና ለተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያለሽን የተዛባ ምልከታ የሚያረጋግ ጠውን እሳቤ ላንቺም ስለምትናፍቂያት ቤተክርስቲያን ለማወቅና የተዛባውን ምልከታሽን ለማስተካከል የሚረዳሽን እውነት ባጭሩ ልግለጽ።
ስለኢየሱስ "የሚገባውን ክብርና እውቅና ትስጥ" ብለሻል። ይኽ አስተያየት ለተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አይገባትም። ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ክብር በዓለም ላይ ከተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀር ሌላ የሰጠና የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም። እስኪ ከመጠሪያዋ ጀምሮ እንይ። መጠሪያዋ ተዋሕዶ ነው። ይህ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመሆን ለዓለም ቤዛ መሆኑን የዓለም መድኃኒት መሆኑን የሚገልጽ ነው። የተመሠረተችው በእርሱ ነው። ዛሬም ሁለንተናዊ ሕይወቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስሙንም ዘወትር ከዓመት እስከ ዓመት በኪዳን በመስዋት በቅዳሴ በሰዓታትና በማኅሌት እንዲህ እያለች ታመሰግነዋለች፦
“ኢየሱስ ክርስቶስ ጥዑመ ስም ለዘይጼውዖ
ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብስተ ሕይወት ለዘይበልዖ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዋዐ መድኀኒት ለዘይሰትዮ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ በግዐ መድኀኒት ለዘይሠውዖ ፤
ከመ ይባርኩነ ይፈኑ አርዳኦ፤
ለጸባኢነ ይጽብኦ ወልታሁ ነሢኦ”
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠራው ስሙ ጣፋጭ ነው፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚበላው የሕይወት እንጀራ ነው፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠጣው የመድኃኒት ጽዋ ነው፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚሠዋው የድኅነት በግ ነው፤
ይባርኩን ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን ይላክ፤
ጋሻውን አንሥቶ የሚጣላንን ይጣላው።"
እያለች በየእለቱ ቤተ ክርቲያን ስሙ መብል መጠጥዋ ፣ክብሯ ፣ መድመቂያውዋ ፣ማንነትዋ እና ሁሉ ነገርዋ እርሱ እንደሆነ ትመሰክራለች። የትኛውም ቅዱስ ቢታሠብ የትኛውም ሰማእት ቢዘከር ኢየሱስ ክርስቶስን አክብሮ በመክበሩ ስለአርኣያነቱና በክርስቶስ ኢየሱስ ስላገኘው ሰማያዊ በረከት እንጂ ከክርስቶስ ተነጻጽሮ አይደለም።
ኢየሱስ ክርስቶስ ስትጠራው እንኳ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብላ ነው። በዚህም ጌትነቱን አዳኝነቱን አምላክነቱንና ክርስቶስነቱን ሳትመሰክር ስሙን አትጠራም። ይህም በዚህ ልክ ከብሮ የሚጠራ ሌላ የለምና ክብሩ ከፍ ያለ አቻም ሆነ ተመሳሳይ የሌለው መሆኑን ያሳያል። ካነሳሽውአክይቀር ርስቶስ ኢየሱስን እንዴት እንደምታከብር በደንብ ማየት ከፈለግሽ ውሳጣዊ ዓይንሽን መክፈት ይኖርብሻል።
በዓመት የሚከበሩ በዋናነት የሚታወቁ ዘጠኝ ዐበይትና ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አሉ። ከዘጠኙ ዐመታዊ ዐበይት ወይም ዋና በዓላት መካከል 8 በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ተግባር መዘከሪያ ሲሆኑ አንዱ ብቻ ርደተ መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ በስሙ የተሰየመ መታሰቢያ ዕለት ነው። በዘጠኙ ትይዩ ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት ሲኖሩ ዘጠኙም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ጉዞ መታሠቢያ ዕለታት ናቸው።
በዓመት ውስጥ 7 አጽዋማት ሲኖሩ 6 ቱ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ከአማኞች የሚሰጡ የምላሽ መንፈሳዊ ተግባራት ሲሆኑ አንዱ ስለእመቤታችን ክብር ለበረከት የሚጾም ነው።
በወር ውስጥ ረቡዕ በጌታየ በኢየሱስ ላይ ምክረ አይሁድ ስለተፈጸመበት አርብ ስለተሰቀለ እሑድ ሞትና መቃብርን ድል ነስቶ የተነሳባት የጌታ ቀን ሆና ስትታሠብ ወር በገባ በ06 ስሙ ኢየሱስ ተብሎ የተጠራበት በ10 ነገረ መስቀሉ የሚታሠብበት 27 እርጥብ መስቀል ተሸክሞ መንገላታቱ ና ስቃዩ የሚታሰብበት በ28 እግዚአብሔር ሰውን መታረቁ ክርስቶስ ወይም አማኑኤል በሚለው ስሙ የሚታሰብበት ሲሆን ወር በገባ በ29 ደግሞ ሰው ወደ አምላክነቱ ዙፉን ለመውጣት በመፈለግ የሠራውን ስሕተት፤ እግዚአብሔር ወደ ሰውነት በመውረድ ለማረም በከብት በረት ስለኛ ድህነት የሰው ሥጋ ተዋሕዶ በቤተልሄም በግዕዘ ሕጻናት ያለቀሰበት የልደቱ መታሠቢያ ዕለታት ናቸው። በዐጠቃላይ በወር ውስጥ ለ 17 ቀናት በዋናነት የሚታሠብ ሲሆን ከወር እስከወር ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ በኪዳንና በመስዋት ይታሠባል።
በእርግጠኝነት በዚህ ልክ ክርስቶስን የሚያከብር የእምነት ተቋም ቢኖር ብቸኛዋ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት። ለመገመት ያህል አንቺ በምትሳተፊበት እምነት ቢታሠብ በወር ከ4 ቀናት እንደማይበልጥና እሱም በትርፍ ቀን ተብሎ እንጂ እንደተዋሕዶ የጌታ ቀን ተብሎ የተሰየመ ሰንበት ኖሮኣችሁ አይመስለኝም።
በሳምንት እንደዚሁ 3 ቀን ረቡዕ አርብና እሑድ ከላይ እንደገለጽኩት በተለየ የሥርዓተ አምልኮ ክንዋኔ ሲታሰብ ከሳምንት እስከሳምንት ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ በኪዳን ቀስብሐተ ነግህ እና በመስዋእት ይታሠባል።
እነዚህ ሁሉ ተግባራት በስሙ መከናወናቸው ለአምልኮና ከነገረ ድህነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሠረት ስላላቸው ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል። “ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤”
— ፊልጵስዩስ 2፥12
እነዚህ ሁሉ ከክርስቶስ የማዳን ተግባራት ጋር የተቆራኙት መንፈሳዊ መጋቤ ምላሾች ወይም አምልኮኣዊ መንፈሳዊ ግብረ መልሶች ዓላማቸው ነገረ ድህነት ወይም መዳን ላይ የተመሠረቱ ናቸው።
የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የመጨረሻ ግብቡ ክርስቶስን መልበስ ወይም በክርስቶስ መኖር ወይም በባዕድ ቋንቋ ቴዎሲስ (Thosis) ለባሴ እግዚአብሔር ወይም ለባሴ ክርስቶስ መሆን ነው። ይህም ማለት ("መለኮትነት_deification ሱታፌ አምላክ") ወይም ከእግዚአብሔር ጋር በምስጢራዊ አንድነት መተባበር ነው። (mystical union with God) or (conformity to and intimate union with God)ማለት ነው።
እነደ ቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ኦርቶዶክሳዊ መዳን (Orthodox salvation) የሰው ልጅ የተፈጠረበትን መልክ ባለመታዘዝ ምክንያት በመጣሉ ያጣውን መልክ በክርስቶስ ኢየሱስ አግኝቶ ያገኘውን ሰማያዊ መልክ ጠብቆ መኖር ነው። ሰው እንዴት እንደተፈጠረና የነበረውን መልክ ሲያስረዳ ኦሪት ዘፍጥረት እንዲህ ይላል፦
ዘፍ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁶ እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ²⁷ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
ባለመታዘዝ ምክንያት ሰማያዊ መልኩ ስለተገፈፈለሚያፍር ማንነት ተላልፎ ከልጅነት ወደባርነት ተሰጠ። ያጣነውን እግዚአብሔርን መምሰል በክርስቶስ መስቀል እንደተመለሠልን ሲያስረዳ “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።” — 2ኛ ጴጥሮስ 1፥2-3 ይላል።
ባለመታዘዝ ከጸጋው ልብስ የተራቆተውን የሰውን ልጅ “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” — ኤፌሶን 4፥24 በማለት ያዘዋል።
ይህም በጥምቀት እንደሚከናወን ሲያስረዳ ፦“ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።”— ገላትያ 3፥27 ይላል።
በዚህ የተጀመረው ሕይወት ተጠብቆና አድጎ ከክርስቶስ ጋር አንድ ሆኖ ለመኖር ጥረት ያደርጋል። ይህም የለበስንውን የጸጋ ልብስ የተመለሠልን የጠፋ ሰማያዊ መልክ መልሶ እንዳይጠፋ ሐዋርያው እንዲህ እያለ ያሳስባል፦
ኤፌሶን 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ²⁶ ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ ²⁷ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።
²⁸ የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። … ³⁰ ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ።
³¹ መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። ³² እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።
ምክንያቱም ድህነት በአንድ ቀን ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በኑሮ ሁሉ የሚጠበቅ መሆኑን ሲያስረዳ ዳግም፦ “ስለዚህ፥ ወዳጆቼ ሆይ፥ ሁልጊዜ እንደ ታዘዛችሁ፥ በእናንተ ዘንድ በመኖሬ ብቻ ሳይሆን ይልቁን አሁን ስርቅ፥ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤” — ፊልጵስዩስ 2፥12 ይላል። ድህነት የሚጠበቅ መሆኑን ካልጠበቅነው ተመልሰን በባርነት ቀንበር የምንወድቅ መሆኑን ሲያስረዳ ጌታችን በወንጌል ይህን ምሳሌ መስሎ አስተምሯል፦
ማቴዎስ 18
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²³ ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። ²⁴ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።
²⁵ የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ²⁶ ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና፦ ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው። ²⁷ የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት።
²⁸ ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና፦ ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው። ²⁹ ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ፦ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው።³⁰ እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው።
³¹ ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ።
³² ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ ³³ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ³⁴ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ³⁵ ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።
ከዚህ የምንረዳው መክፈል የማንችለው በአዳም ምክንያት ተላልፎ የመጣዊ የቀዳማዊ በደል ውጤት በእርሱ በክርስቶስ የተከፈለ ሲሆን ከእኛ የሚጠበቀውን መንፈሳዊ ተግባር የማንወጣ ከሆነ የተከፈለው ዕዳ ድጋሜ ተሰርዞ በበደሉ ውጤት ተጠያቂ እንደምንሆን ነው።
ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊው ነገረ ድህነት ከስሜታዊነት ይልቅ መንፈሳዊነትን ያገናዘበ በመሆኑ እንደዚህ በመሆን ውስጥ የሚገለጥ ነው። እንጅ ""መዳን በእምነት ብቻ ነው"" ብሎ ከሕይወት የሚፋታና የሚጠበቀውን ኃላፊነት እንዳይወጣ በሚያግድ ንድፈ ሐሳብ የታጠረ አይደለም።
ቴኦሎጃዊያን አባቶች ይህንን “God became man so that Man might become god.ሰው አምላክ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ሆነ” በማለት የነገረ ድኅነትን መንገድ ተዋሕዶ መሆኑን ያስረዳሉ።
እግዚአብሔር ሰው በመሆኑ ምክንያት ያገኘነውን ሰማያዊነት ወይም ከእርሱ ጋር የምንኖርበት ምስጢራዊ አንድነት የተጠበቀለት ሰው መዳን ከዘላለማዊ የሞት እስራት ማምለጥ ብቻ ሳይሆን እዚህ እና አሁን በክርስቶስ ወደ ሕይወት መግቢያ በር ሆኖሎት በዚያም ማደግንና መጠበቅን ማእከል አድርጎ በእድሜው ሙሉ የሚጓዘው መንፈሳዊ ሕይወት ነው።
የኖቲክ መታደስ በመንፈሳዊ ሕክምና በምስራቃዊ ክርስትና ውስጥ ያለው ማዕከላዊ ንድፈ ሐሳብ ኑስ Nous በተለምዶ "አእምሮ" ወይም "ማወቅ ወይም መገንዘብ"mind" ወይም "understanding ተብሎ ይተረጎማል)፣ የግንዛቤው ማዕከል ይህም የአማኙ ወይም የግለሰቡ መሃል፣ ልብ (heart), ወይም መንፈስ (spirit) ነው።
ኑስ (nous) የሰው ውሳጣዊ ዓይን ወይም ነፍስ (soul) ነው። ይህም ማለት አመክንዮአዊ እና ሊታወቅ የሚችል ግንዛቤ ማለት ነው። ኦርቶዶክሳዊ መዳን የሚሰራው በዚህ ክፍል ነው። ምክንያቱም በአዳም ኃጢአት እና ውድቀት የተጎዳው በጭለማ አእምሮ የተገለጠው የሰው ልጅ ነፍስ ነበር። ለዚህ ነው ዮሐንስ ክርስቶስን ለዓለም የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን ያለው።
አሁን በክርስቶስ ልትድን የምትችለው ነፍስ ክርስቶስን ከማመን በላይ ከፍ ብላ በማደግ ክርስቶስን መምሰል አለባት። ይህም ሦስት ነገሮችን አጠቃሎ ማለትም፦ ሥጋን ፣ነፍስንና መንፈስን በመጠበቅና በመቀደስ ቅዱስ የሆነ ኑሮ ስንኖር እግዚአብሔርን ስንመስል መዳናችን ተጠብቆ እውን ይሆናል። ይህም በሀይማኖት ጸንቶ መኖር በሚል ተገልጧል።
"የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ(ሐዋ 14:21-22) ተብሎ ተጽፏል።
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቶስ የመሠረታት ሐዋርያት ያስፋፏት ናትና ቅዱሳን ሐዋርያት በመልእክታቸው እንዲህ ብለውናል።
"ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል" እያሉ የእውነትን ወንጌል ሰበኩ። ከዚህ መልእክት አንጻር፦
የሐዋርያት ቃል ሲብራራ "ድኛለሁ ተፈውሻለሁ ዘና በል" የሚል ወንጌል አለመኖሩ ነው።The Lord Jesus opened heaven, not closed hell (ጌታ ኢየሱስ ገነትን ከፈተ እንጂ ሲኦልን አልዘጋም)። ከአዳም የኃጢአት ውጤት ያዳነን ብቸኛው አዳኝ እርሱ ቢሆንም ክርስቶስ መስቀሌን ተሸከመልኝ ብለን የምንተወው መስቀል የለም።
"የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ_ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።" ብሎናል። (1ኛ ጴጥ 2:21) የተወልን ፍለጋው Living in struggle and carrying the cross(መስቀሉን መሸከም በተጋድሎ መኖር) ነው። ስለዚህ "በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፥ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም" ብሎ እውነቱን ነግሮናል።(ሉቃ 13:24) ባለው ቃል መሠረት ድህነትን መጠበቅ ማሳደግና መጋደል መስቀሉንም መሸከም ግድ ነው።
ስለዚህ ለመዳን አራት ነገሮችን መያዝ ግድ ይልሃል
በሥርዓተ አምልኮ መጽናትና መሳተፍ ይህም
✔ምስጢራትን መፈጸም(መጠመቅ ሜሮን
ቁርባን መቀበል)
✔መንፈሳዊ ተጋድሎ(ጾም ጸሎት ስግደት)።
✔መልካም ስራ (ትህትና ፍቅር ምጽዋት)
ያስፈልግሃል።
በአጠቃላይ ያለ ክርስቶስ ኦርቶዶክስን ማሰብ መኪና ያለነዳጅ ያለምንም ኃይል መብረሩን ያቁም እንደማለት ነው። ክርስቶስን “እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለንና” (ዮሐ 4፥42) እንደተባለ እኛም እንዲሁ እንላለን።
እምነታችን በሐዋርያው እንደተገለጸው ይህ ነው። “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” — ሐዋርያት 4፥12 ጌታችንን አምላካችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበልንው መዳን በእርሱ የሆነ አዳኝ መድኃኒት ስለሆነ ነው። እኛስ ኢየሱስ በተባለ በ ክርስቶስ ስም አምነናል አውቀናል በእርሱ እንኖራለን ደግሞም እንድናለን ድነንማል።
በተረፈ ጠቀለል አድርጌ ስመልስ ስለመጽሐፍ ቅዱስ ላነሳሽው።፦ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የእምነት አስተምህሮ መሠረቶች 3 ናቸው።
1, 👉ዶግማ= (የማይሻር የማይሻሻል የመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ መልእክት ሲሆን ለድርድር የማይቀርብ ጽኑ መሠረት ነው)
2, 🙏ቀኖና = (ቤተክርስቲያን እየተጠበቀች እዚህ የደረሠችበት የአባቶች ሲኖዶሳዊ ውሳኔዎች)
3, 🙏ትውፊት = (በቅብብሎሽ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ የዶግማ መጠበቂያ አጥር)
✍️የትውፊት ትክክለኛነት 3 መመዘኛዎች
👑1️⃣, ማንኛውም ትውፊት የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ተጻርሮ ወይም ተቃርኖ ከተገኘ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም።
👑2️⃣, ማንኛውም ትውፊት እርስ በእርሱ ተጣርሶ ከተገኘ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም።
👑3️⃣, ማንኛውም ትውፊት የሌሎች አኃት አብያተ
ክርስቲያናትን አስተምህሮ ተቃርኖ ከተገኘ
ተቀባይነት የለውም።
⛪️ትውፊት እነደየ ሁኔታው ሊሻሻል ይችላል። ትውፊትን የማሻሻል ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ሲሆን የሕዝብ አስተያየትን መነሻ በማድረግ የሊቃውንት ጉባኤ መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ ሲያቀርብለት ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ሊያሻሽለው ይችላል።✝️✝️✝️
💒ትውፊት እንዲሻሻል የሚያደርጉ 3 ገፊ ምክንያቶች
⏰1️⃣, ከሕዝብ ንቃተ ኅሊና ጋር መጣጣም ካልቻለ
🔴2️⃣ የአካባቢ ሁኔታ ቢቀየር (enviromental change) ለምሳሌ ለመጾም የማያስችል የአየር ሁኔታ ቢፈጠር
🔕3️⃣ የፖለቲካ ሁኔታ በተቃራኒዎች በብልጫ ሲመራና እንደ ቀድሞው ለመገልገል አስቸጋሪ ሲሆን
በዝርዝር ለማሳየት ያህል እስኪ ዶግማ ምንድን ነው? ቀኖና ትውፊትስ?
ዶግማ በዓለም አቀፍ ጉባኤያት (ecumenical councils) የጸደቀ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን ከአበው የተቀበለችውን እምነት የምትገልጥባቸው አስተምህሮዎች ደግሞ doctrines ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው” ይህ ዶግማ ነው፤ “ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት” ይህም እንደዚሁ፡፡ የክርስቶስን አምላክነት ለማይቀበሉ አርዮሳውያን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያን አስተምህሮ (doctrine) ተከትላ መልስ ሰጥታለች፤ ስትሰጥም ትኖራለች፡፡ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ (Theotokos) ብለው ለመቀበል ለሚቸገሩ ንስጥሮሳውያን ደግሞ፣ እንዴት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም “ወላዲተ አምላክ” እንደምትባል የምንገልጥበት ወይም የምናስተምርበት ዶክትሪን፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡
እነዚህ አስተምህሮዎች በዓለም አቀፍ ጉባኤያት የተወሰኑ ሲሆን፣ ውሳኔያቱን ከተጨማሪ ጉዳዮች ጋር የቤተ ክርስቲያን አበው በቀኖናት (canons) አጽድቀዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር በ325 ዓመተ እግዚእ (AD) የተጠራው ጉባኤ ኒቅያ 20 ቀኖናት አሉት፡፡ እነዚህንና ሌሎቹን ዓለም አቀፋዊና ብሔራዊ ውሳኔያት፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ከርስቲያን Holy Canons (ቅዱሳት ቀኖናት) በማለት ትጠራቸዋለች፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳት ቀኖናት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በዓለም አቀፍ ጉባኤያተ አበው የጸደቁና የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ የሚያንጸባርቁ (ከዶግማዋ ጋር የሚስማሙ እንጂ፣ የማይጋጩ) ናቸው፡፡
“ቀኖናት ይሻሻላሉ/ ይለወጣሉ” ሲባል “እንደ ቀኖናው ዓይነት ይወሰናል፤ የሚለወጥና የማይለወጥ አለ”፡፡ ለምሳሌ የክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ወይም የመለኮትና ትስብእትን ተዋሕዶ አስመልክቶ ቅዱሳን አባቶቻችን የወሰኗቸው ቀኖናት Dogmatic Canons ስለሆኑ ማንም ተነሥቶ ሊለውጣቸው አይችልም፡፡ Practical የሆኑ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ቀኖናት ላይ ግን፣ በሐዋርያት መናብርት የተሾሙ አበው ወይም የእነርሱ ተከታዮች (ተላውያነ አበው) የሆኑ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባዔ (ቅዱስ ሲኖዶስ) ማሻሻያ ማድረግ ይችላል፡፡ ማሻሻያ ከተደረገባቸው practical canons መካከል አንዱን ልጥቀስ፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፡- ቅስና መሾም የሚገባው ሰው 30 ዓመት የሞላው እነደሆነና ኤጲስቆጶስ ደግሞ በ50 ዓመቱ መሾም እንዳለበት የሚደነግግ ቀኖና ነበር፡፡ በሂደት ግን ቤተ ክርስቲያን ተምረውና በቅተው ለተገኙ ልጆቿ 30 ወይም 50 ዓመት ባይሞላቸውም የቅስና እና ጵጵስና መዓርግ ሰጥታለች፡፡
ወገኖች! Apostolic Succession (ሐዋርያዊ ሰንሰለትን) በመጠበቅ ተወዳዳሪ የሌላት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት በተቀደሰው ትውፊት (Holy Tradition) አማካኝነት ቅዱሳት መጻሕፍትንና ከእነርሱ የሚመነጨውን ርቱዕ (የቀና) አስተምህሮ ያስረከበችን፣ ማንም የመሰለውን መላምት እያመጣ ከቀጥተኛው (ኦርቶዶክሳዊ) መንገድ እንዳይወጣ አጥር ሆነው የሚጠብቁ Holy Canons (ቅዱሳት ቀኖናት) ስላሏት ነው፡፡ ይህን ለመረዳት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የአምልኮ ውበት እና ሥርዓት፣ Protestantism ውስጥ ካለው ቀውስ (chaos/anarchy) ጋር በማነጻጸር መረዳት ይቻላል፡፡ ኢየሱስ ስላልን ተወገዝን ተባረርን የሚሉ አካላት ይህንን በመናድ ቤተክርስቲያኒቱን ማተረማመስ የሚሹ አካላት ናቸው።
በጥራዝ ነጠቅ አካሔድና አነጋገር፣ በዘመናት ተፈትኖ ያለፈውንና በምድር ላይ ሆነን ሰማያዊ ሐሴትን እንድንለማመድ የሚያደርገንን ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓተ አምልኮ ሸርሽረን እንደ አንዳንድ ሥርዓት እንደሌላቸው ቤተእምነቶች ወደ ሥርዓት አልበኝነት እንዳንገባ የሚያደርጉ ስሑት አስተምህሮዎችንና አካሔዶችን ታርማለች ትመክራለች ትገስጻለች አልሰማም ካለ ሌላውን እንዳይበክልና መለያየት እንዳይፈጠር አውግዛ ትለያለች። በዚህ ስህተታቸው ሲወገዙ ኢየሱስ ስላልን ተወገዝን ብለው መሸሸጊያ ፍለጋ ሊያሳብቡ ይችላሉ። ኢየሱስ ስላለ የሚባረርና የሚወገዝ ቢኖር ኖሮ አንድም ቀዳሽም ሆነ ኪዳን አድራሽ ካህን ባልተገኘ ነበር። ውሸት ነውና ዝም ብለው ለሚዋሹ ዋሾዎች ስንሰማ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡
©
ከአባ ጌዴዎን ዘደብረሊባኖስ ለሶፍያ ሽባባውና መሰል ምልከታ ላላቸው ሁሉ ተጻፈ 29/07/2015 ዓም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።