መደራጀት ሊፈራ አይገባውም።

 

ይህ ግርባው ብአዴን ዬወጣቱን መንፈስ ሲያደነዝዝ በነበረበት በ2011 ዬጻፍኩት ነው።
መደራጀት ሊፈራ አይገባውም።

 
• እፍታ።
መደራጀት ኃይል ነው። መደራጀት አቅም ነው። መደራጀት ስንዱነት ነው። መደራጀት ፍቅር ነው። መደራጀት አብነት ነው። መደራጀት የታማኝነት ማስፈጸሚያ ነው። መደራጀት የህሊና መቅኖ ነው። መደራጀት ዓላማና ግብ ያለው ሰብዕና ማለት ነው።መደራጀት የአብሮነትም አንባ ነው። መደራጀት የሥን - ልቦና ቅዬሳ ተቋም ነው ለአዎንታዊ ከተጠቀምንበት። ይህችን ለመግቢያ ከከሽንኳት በኋላ እምጠቅሰው በመደራጀት ዙሪያ ያሉ ጥቂት ነገሮችን ነው። በጽንሰ ሃሳቡ ዙሪያ ሌላ ጊዜ ብመለስበትም ትንሽ የአማራ ወጣቶች በገጠማው አንኳር ችግር የምለው ይኖረኛል።
ወግ።
የአማራ ወጣቶች እዬተደራጁ ነው። ማህበራቸው ነፃ እና ገለልተኛ ነው። ማህበራቸው ዓላማ እና ግብ አለው። ዓለማ እና ግብ ደግሞ የአንድ ድርጅት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የአማራ ወጣቶች መደራጀት የአዳማን ሥርዕዎ መንግሥት አላስደሰተም። ስለሆነም እውቅና እንዲነፈገው ተደርጓል። ከሰኔ 15 በፊት በነበረው ሰንበት የደብረታቦር ወጣቶች ኢንጂነር ይልቃልን ጌትነትን ጋብዘው ነበር ነገር ግን ታግደዋል። ይህ መቼም እኔ እብደት ነው የምለው። ሰው ያበደ ዕለት ጋብቻን ያግዳል። ልክ እንደ ባቢሎን ግንብ ቀያሹ እንደ አቶ በቀለ ገርባ ማለት ነው።
ነፍሳቸውን ይማረውና ዶር አንባቸው መኮነን በመሩት ጉባኤ ደብረታቦር ላይ የወጣቶች ጉባኤ ነበር። አቶ ዮኋንስ ቧያለውም ተገኘተው ነበር። ሁለተኛ የወጣት ድርጅት አስፈላጊ አለመሆኑ በአጽህኖት ሲገልጹ ሰምቻለሁኝ። በፖለቲካ በሳል ከሆኑ አንድ የፖለቲካ ሊሂቅ የማልጠብቀው ገለጻ ነበር። በተፎካካሪያቸው በአብን ላይም የነበራቸው ምልከታ ጤናማ አልነበረም። ፖለቲካ በድንበር የተከለለ የኩሬ ውሃ አይደለም። የሰው ልጅ አንድ ምርጫ ብቻ አይደለም ያለው። የሰው ልጅ የወንዝ ውሃ አይደለምና።
ስለሆነም የሰው ልጅ ምርጫው ሊገደብ አይገባም። የሰው ልጅ ምርጫም የቅንድብ ጸጉርም አይደለም። ፍርስርስ ይበል ብአዴን ባልልም፤ ከእነቁም እንቅልፉ አገልጋይነቱን ይዞ ይቀጥል። ማንነቱ ግን የአማራን ህዝብ መንፈስ የመሸከም አቅም የለውም። ይህም ከአማሰራረቱ ጫጩትነት የመነጨ ነው። የማንነት ቀውሱ እንዳለፈ ጊዜ አሁንም ቀጥሏል።
ለዛውም አምስት ሊሂቃኑን ገብሮ። እነዛ አምስት ሊሂቃን ጋር ትግል የጀመሩት ከተፈጥሯዊ ህልፈት በስተቀር እንዲህ በጥይት አልተደበደቡም አሁንም አሉ። እንዲያውም ዘለግ ያለ መብት የተሰጣቸው በሲነሪቲያው እጅግ ዝቅተኛ የሆኑ ሁሉ ነው አሁን ቀንድ ሆነው የሚታዩት። አልፈው ተርፈው የፈጠራቸውን ወደ ሽቅብ ለመገሰጽም ይንጠራራሉ፤ „ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ“ እንዲሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ስብሰባ መቀመጥ ስሌቱ እጅግ ይጎመዝዛል?! የሆነ ሆኖ ለእኔ ብአዴን የተቃጠለ ካርቦን ነው።
ወጣቶች በዕድሜያቸው፤ በሙያቸው፤ በሆቢያቸው ዙሪያ የመደራጀት ሙሉ ዓለም አቀፍ መብት አላቸው። ይህን ብአዴን ወይንም የአዳማ ሥርዕዎ መንግሥት የሚገድበው አይደለም። እኔ የህዝባዊና የሙያ ማህበራት አደራጅ በነበርኩበት ጊዜ ሴቶችን፤ ወጣቶችን፤ መምህራንን፤ ሠራተኞች ማህበራትን በሚመለከት በመደራጀት ዙሪያ ያለው ጥቅምና ጉዳት አንድ ጥናታዊ ተግባር በተደራጀ ቡድን አስጠንቼ ነበር። እኔም ያን ጊዜ ወጣት ነበርኩኝ።
በተለይ ከመምህራን እና ከወጣቶች የጥናት ማጠቃለያ ጭብጥ የመጣው በነፃነት እንድንደራጅ ይፈቀድልን የሚል ነበር። ከአኢወማ፤ {የኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር} ከኢመማ {ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበርም።} በጣም ሞጋች ነበር በዚህ ዙሪያ ድምጻቸውን የሰጡት አባልተኞች ቁጥር። ያሰፈሩት አሰተያዬት የህሊና ካቴና አንሻም የሚል ሁሉ ነበረው። ራሱ የኢሠፓ አባል የሆኑት ሳይቀር ይህ እንዲሆን ይሹ ነበር። ጥናቱ የተካሄደው ጎንደር ከተማ ነበር። አሁንም የአማራ የወጣቶች ማህበር የተመሰረተው ጎንደር ከተማ ላይ ነው። ስሜቱ አለ። ነፃ ሆኖ የመደራጀት። መንፈሱ እራሱ ጤናማ ነው።
አቶ የኋንስ ቧያለው አለ የሚሉት የኢህዴግን የወጣት ሊግ ነው። ያ የድርጅታቸው መሳሪያ፤ የድርጅታው ወታደር፤ የድርጅታቸው ካድሬ፤ የድርጅታቸው ፕሮፖጋንድስት ነው። ለቦይ ውኃነት የተሰናዳ። እንኳንስ ለአማራ ባለቤት ሆኖ የማያውቀው ብአዴን ቀርቶ ባለቤት ሆኖ ቢያውቅ እንኳን ገለልተኛ የሆነ ዕሳቤ ያላቸው ዜጎች መፍጠር ለአንድ አገር ህልውና የኦክስጅን ያህል ያስፈልጋል። ከፖለቲካ ድርጅቶች በላይ። ይህን እዬፈራው ነው ዓለም ያሸበሸበለት የአብይወለማ መንፈስ።
እነዚህ የአማራ ወጣት ማህበራት መሰናዶ ነው የሚያደርጉት። መሰናዶው የህሊና የሞራል ነው። ይህ የህሊና እና የሞራል መሰናዶ ደግሞ መንግሥት በባጀትም፤ በጽ/ቤት ሰጥቶ ሊደግፈው የሚገባ ቁም ነገር ነው። የቤት ሥራውን እዬሰሩለት ስለሆነ። ትውልድ እዬተሰቃዬ ነው። ሥነ - ልቦናው ታውኳል። ሥነ - ልቦናው የታወከ ትወልድ እንዴት አደራ ሊረከብ ይችላል? ይህን ኃላፊነት ነው የአማራ ወጣቶች እዬተወጡ የሚገኙት። ልክ በሰለጠነው ዓለም እንዳለው ማለት ነው።
ሥነ - ልቦናው የተሰናዳ ወጣት ቢፈልግ ብአዴን፤ ቢፈልግ አብን፤ ቢፈልግ መኢህድ፤ ቢፈልግ አዴፓ፤ ቢፈልግ ኢዜማ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ቢሄድ የሚያኮራ ተግባር ነው የሚፈጽመው። በሃሳብ ልዕልና ተኮትኩቶ ስላደገ። በሞራል ስለታነጸ ለአደራ የበቃ ይሆናል። እራሱ የሥብሰባ ሥርዓትን መማር በራሱ አንድ የትምህርት ሌሰን ነው።
እኔ በ2014 ይመሰለኛል እንዲህ ዓይንት „ቁራሽ እንጀራ“ የሚል በ8 ክለቦች አንድ አሰባሳቢ ማህበር የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ፤ ግን ብሄራዊ ድርሻን ለመወጣት የፈቀዱ በገለልተኛ ያሉ ሰባዕዊነት የሚሰማቸው ወገኖችን በፆታ፤ በሙያ፤ በዕድሜ ለማደራጀት እና የህሊና መሰናዶ ተግባር ለመከወን አቅጄ ስራ ጀመርኩኝ። የሥነ -ጹሑፍ ምሽት ሁሉ ነበረው፤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፤ የመንግሥት ድጋፍ፤ የህግ አገልግሎት በነጻ፤ የፕሬስ አገልግሎት በነፃ አገኜሁ። ነገር ግን በግንቦት 7 ምክንያት ጨንግፎ ቀረ። ስበስቡም ተበትኖ ቀረ። ምንም ዓይነት የሲቢልም የፖለቲካ ድርጅትም አስኳል ከግንቦት 7 ውጪ የሆነ ድርጅት እዚህ ማደራጀት አይቻልም። ሆም ቤጅ ሳይቀር። ግዞት። ለዚህም ነው እኔ የግንቦት 7 መንፈስ ተስፋ እማልጠብቀው። በግለሰቦች ሰብዕና ሳይሆን ተስፋ እውን የሚሆነው በደርጅት አደረጃጃት አወቃቀር ዓላማና ግብ ጥራት ስኬቱ ሚዘናን ላይ ተቀምጦ ነው። ብራዊነት ከወገብ በላይ እና ከወገብ በታችነት ንድፍ የለውምና።
ከቀደመው ጋር ሳያይዘው የቁራሽ እንጀራ ደንባችን አንድ ሰው የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ሲቀብል ድርጅታችን በክብር ይለቀዋል። የአባልነት ግዴታውም ሆነ መብቱም አብሮ ይቆማል። ሙሉ የህሊና ብሄራዊ መሰናዶውን እኛ ጨርሰን ግን ለሚጠቅምበት ቦታ፤ በማህበር አባልተኛችን ምርጫውን ለማሳካት ሲሄድ ትውልዳዊ ድርሻን ከመወጣት አንጻር ኩሩ ተግባር ነበር። ለራሱ ለግንቦት 7 ጠቃሚ ነገር ነበር። አሁን የአማራ ወጣቶች ማህበር ሆነ የአማራ የተማሪዎችን ማህበር እማዬው እኔ እንደዛ ነው።
ራሱ ብአዴን ወጣቱን መሰብሰብ ቢፈልግ ከድርጅቱ ጋር ተገናኝቶ በቀላሉ ወጣቶችን ማግኘት ይችላል። በነፍስ ወከፍ ከሆነ ግን እጅግ ከባድ ነው። ለምሳሌ ደርግ የቀበሌ፤ የገበሬ ማህበራትን ባያደራጅ ኑሮ ከጫካ የመጣ ጉልበተኛ ቡድን እንዴት አቅም ፈጥሮ አገር 27 ዓመት ሊመራ ይቻለው ነበር?
• ክወና።
በሌላ በኩል ምርጫ ቢኖር ታዛቢ ችግር አይኖርም ወጣቶች በተደራጁባቸው ቦታዎች ሁሉ። ምክንያቱም ከፖለቲካ ነጻ ከሆኑ ገለልተኛ ነው የሚሆኑት። ለጸጥታም ቢሆን በእያንዳንዱ ቤት ወታደር ማስቀምጥ አይቻልም። ወጣቶች ግን ይህን ኃላፊነትም ሊወስዱ ይችላሉ። ስሜታዊ የሆኑ ወጣቶች ይገራሉ። ከማቃጣል፤ ከማፍረስ ተጠቃሚ ማህበረሰብም፤ ተጠቃሚ አገርም ስሌለ። ስለዚህ አቤቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደ ጎባኑ፤ እንደ አንጡራ ጠላቱ የሚያውን የአማራ ወጣቶች ማህበር ጊዜ ሳያጠፋ ዕውቅናውን መስጠት ይገባዋል። ህጋዊ ሰርትፊኬትም ሊሰጣቸው ይገባል፤ ጠቃሚና አትራፊ መንገድ ነው።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
10/04/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ኑሩልኝ ቅኔዎቹ።
መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።