በተስፋ ማጣት ውስጥ ተስፋ አይገኝም።
በተስፋ ማጣት ውስጥ ተስፋ አይገኝም።
ተስፋ የእዮር ስጦታ ነው።
ተስፋ የአቅም መክሊት ነው።
ተስፋ የማግስት የችሎት አደባባይ ነው።
ተስፋ መፈጠራችን ነው።
ተስፋ ትናንት፤ ዛሬ እና ነገም ነው።
ሰከንዳት፤ ደቂቃት፤ ሰዓታት፤ ወራት፤ ዓመታት፤ ዘመናት ሁሉ በተስፋ ይኖራሉ ይተማሉ ይፀድቃሉ።
ፍጥረታት በተስፋ ተፈጥረው ተስፋ ይሆናሉ።
ዓላማ በተስፋ ተፀንሰው የግብ ሠራዊት ይሆናሉ።
ተስፋ እና ተስፈኛው ሰክነው መነጋገር፤ መወያዬት መምከር ከቻሉ ተስፋ ለድል ይበቃል። ተስፋ ፈንታዚ አይደለም። ይልቁንም ከእግዚአብሄር ተስፋ ይሰጥ፤ ተስፋውን እሱ ይመራው ዘንድ መፍቀድ። መፍቀዱ በትህትና እና በአክብሮት በጥሞና እና በመታመን ከሆነ ተስፋን የፈጠረ አምላክ ለሰጠው ስጦታ ተፈፃሚነት ይቆማል።
አብሶ ቅን ሆኖ፤ ግልጽ ሆኖ፤ ደግ ሆኖ ሰዋዊ እና ተፈጥሯዊ የሆነ ጉዞ ተስፋውን ያገኛል። የሚያገኜው ተስፋም የፀና ይሆናል። ተስፋን ለሰው ሲሰጥ ወጣ ገባ ነው። ተስፋን ለፈጣሪ ከሰጡት ግን ባለቤቱ ይከውነዋል።
አሁንም በአባ እዮብ አማራዬ ላይ ተስፋዬን ለተስፋ ፈጣሪ ለአምላኬ ነው እምተወው። ተስፋዬ በፍጡራን አቅም፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዘንድ አላደርግም። አብሮ መዛል፤ አብሮ መበተን መሆኑን አስተውያለሁኝ። ዬሚገርመው ትግል አቆምኩ ሲል አንድ ነፍስ ያ ሁሉ ተስፈኛ ለበሽታ፤ ለመከራ ሸልሞ መሆኑ አይታዬወም። ምንጊዜም ጥገኝነታችን ለፈጣሪ እንዲሆን እመኛለሁኝ።
ህዝባችን ተሰቃይቷል። ዛሬም እንደ ትናንቱ ለጫማ እንኳን አልበቃም። ሊቃናቱ ሊሂቃኑ ከፍም ዝቅም ቢሉ እንብዛም አይጎዱም። ህዝባችን ግን ተጎሳቁሏል። ይህን እናስተካክላለን ብለው ዬሚታትሩትም ይንገላታሉ። እንግልታቸው ቤተሰብን ይጨምራል። ተስፋን ለማግኜት ሰማዕትነቱ ከባድ ነው። ስለሆነም በጥንቃቄ፤ በእርጋታ ቢሆን መልካም ነው።
ጨካኞች ለተስፈኛ ርህራሄ ዬላቸውም። ይህ ሊታወቅ ይገባል። በሌላ በኩል ግን ጨካኞች ከፈጣሪ በታች ስለመሆናቸው ሊያውቁት ይገባል። ያ እንደተናደው ሁሉ ይህም ያከትማል። በዚህ ውስጥ አማራ ጉዳዬ ያላችሁ ሚዲያወች፤ ዬፖለቲካ ሰወች፤ አደራጆች እና መሪወች እርእስ ስትመርጡ፤ ስትጽፋ ስትናገሩ እራሳችሁን ማዳን እንዳለባችሁ አጀንዳችሁ ብታደርጉ ጥሩ ነው። ከሰማችሁኝ። እኔ እርእሱን፤ ዬተፃፈበትን ቀለም፦ ዬጭብጡን ሁነት አጠናለሁ። አገር ቤት ያላችሁ እንደ አናንያ አዛርያ እና ሚሳኤል ቋያ ውስጥ ናችሁ። ህይወታችሁ መኖራችሁ ተስፋ ነውና እሰቡበት።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
11/04/2023
ተስፋችን አምላካችን።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ