«አማራ ክልል እየተፈጸመ ያለው የመብት ጥሰት እንዲመረመር የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጠየቀ»
«አማራ ክልል እየተፈጸመ ያለው የመብት ጥሰት እንዲመረመር የዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጠየቀ»
ሲሳይ ሳህሉ
ቀን:
October 20, 2024
https://www.ethiopianreporter.com/134542/
«ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረውና በአማራ ክልል በሁለት ተፋላሚ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት እየደረሰ ያለውን የከፋ የመብት ጥሰት፣ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ምርመራ እንዲያደርጉበት በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ጠየቀ፡፡
ፎረሙ በጦርነት እየታመሰ ባለው የአማራ ክልል የጤና ተቋማትና አገልግሎት ላይ እየደረሰ ነው ላለው ቀውስ ምላሽ መስጫ ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል፡፡ ይፋ በተደረገው ባለ 45 ገጽ ስትራቴጂ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ዩኒሴፍ፣ የአለም ጤና ድርጅት፣ የተመድ የሥነ ሕዝብ ድርጅት፣ የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል፡፡
በስትራቴጂክ ሰነዱ እንደተብራራው፣ የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ አደጋ እንደተደቀነበትና በጦርነት ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት ሥራ ማቆማቸውን፣ ከ1,100 በላይ ሠራተኞች መፈናቀላቸውን እና መገደላቸው ተመላክቷል፡፡
በሰነዱ ከ5,000 በላይ ሰዎች ለፆታዊ ጥቃት መጋለጣቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ውስጥ ወደ ጤና ተቋም የመጡትና የተመዘገቡትን ብቻ የሚይዝ ስለመሆኑ የፎረሙ ዋና ጸሀፊ ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በቀጠለው የደኅንነትና የፀጥታ ሥጋት የተነሳ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትና የልማት አጋሮች በክልሉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴና ድጋፍ በጊዜያነት ለማቆም እየተገደዱ ስለመሆኑም አመላክቷል፡፡
በበረታው ጦርነት በመንገድ መዘጋት ምክንያት ወደ ክልሉ የሚላኩ መድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎች እንዳይገቡ ከመገደቡ ባሻገር፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ወደ ዞንና ወረዳዎች ለመላክ አስቸጋሪ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በርካታ የጤና ተቋማት በክልሉ ዝቅተኛውን የጤና አገልግሎት እንኳ ለህዝቡ ማቅረብ እንደተሰናቸው ፎረሙ አስታውቋል፡፡
በሱዳን የሚካሄደውን ጦርነት ፈርተው ወደ አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር መተማ የገቡ ሱዳናውያን ቁጥር ከ140 ሺሕ በላይ መድረሱን የሚገልጸው ይህ ስትራቴጂክ ሰነድ፣ የስደተኞች ቁጥር የጤና አገልግሎት ችግሩን እንዳባባሰው አስታውቋል፡፡
የኮሌራ በሽታ በክልሉ በ12 ዞኖችና በአራት የከተማ አስተዳደሮች መከሰቱ በሰነዱ የተገለጸ ሲሆን፣ የኮሌራን በሽታ ለመቆጣጠር አለመቻሉንም ተገልጿል፡፡
ፎረሙ የአማራ ክልል ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ውድመት ካለማገገሙ ባሻገር የሱዳን ጦርነት አማራ ክልል የቀጠለው ጦርነት፣ ድርቅ፣ ወባና ኩፍኝ ክልሉን አደጋ ውስጥ ጥለውታል ብሏል፡፡
ይህ ስትራቴጅክ ሰነድ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ጨምሮ ሁሉም የብሰዓዊ ድጋፎች ያለምንም መስተጓጎልና ክልከላ ለሕዝቡ ተደራሽ እንደሆነ በጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉ ወገኖች ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪ የሚያደርግ ስለመሆኑ የፎረሙ ጸሀፊ ተፈሪ መላኩ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ጸሀፊው ‹‹ንፁኃንን ያለ አበሳቸው የማይገባቸውን ሰቆቃና ፍዳ እየከፈሉ በመሆኑ፣ ሁለቱም ውጊያ ላይ ያሉ ወገኖች ያለምንም መስተጓጎል የጤና እና ሌሎች የሰብዓዊ አገልግሎትና አቅርቦቶችን ለሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲደርሱ መፍቀድ አለባቸው›› ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በውጊያ ላይ ያሉ ሃይሎች ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን እያከበሩ ባለመሆኑ ይህን እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ስመሆኑ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹የሴቶች መደፈር ትልቅ የሆነ ልብ የሚሰብር የመብት ጥሰት በመሆኑ ይህን ጉዳይ የመብት ተቆርቋሪዎች ሊመረምሩት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ደኅንነታቸው ሊከበር ይገባል ያሉት ሰብሳቢው የጤና ተቋማት በጦነቱ ምክንያት በገጠማቸው የግብዓት አቅርቦት የደኅንነት ችግር የትራንስፖርት ችግርና የሰው ኃይል ችግር የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡
ታፈረ (ዶ/ር) ‹‹የጤና ተቋማት አምቡላንስ በጣም በሚያሳዝን መንገድ ከተፈለገው ዓላማ ውጭ እየዋለ በመሆኑ ይህ ሊታረም ይገባል›› ብለዋል፡፡
በስትራቴጂክ ሰነዱ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ተብሎ የቀረበው ሰነድ በጤና ተቋማት የመጣውን ብቻ የያዘ ስለመሆኑ የሚገልጹት የፎረሙ ሰብሳቢ፣ የሰብዓዊ ቀውሱን መሉ መረጃ የማያሳይ ቁንጽል መረጃ በመሆኑ የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች የመብት ጥሰቱን እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጸሀፊው አክለውም ስትራቴጂክ ሰነዱ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩን ተረድቶ ጫና እንዲያደርግና ሕጎች እንዲከበሩ በሚል ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ስትራቴጂውን በሚዲያ የማስተዋወቅ፣ የመንግሥት አካላትን የማናገርና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ከፎረሙ ጋር አብሮ የሚሠራው የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በክልሉ ያለውን የጤና ተቋማት ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ጥናት ለማካሄድ የኢንተርኔት፣ የስልክ መቋረጥና የመንገድ መዘጋት ከፍተኛ ማነቆ እንደፈጠረበትና ጥናቱን በልኩ ማካሄድ እንዳልተቻለ ተገልፅዋል፡፡
ጸሀፊው በየትኛውም ዓለም ላይ ያለው ልምድና የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት፣ የቀይ መስቀል መኪና ለሌላ ዓላማ መዋል እንደማይቻል ጠቅሰው፣ የጤና አገልግሎቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ገደብ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች እንዲሰሩ የሚደረግበት አሰራር እንደሚፈጠር ጠይቋል፡፡»
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ