እውን ብልጽግና #የአማራ እና #የኦሮሞ ነውን??

 

እውን ብልጽግና #የአማራ እና #የኦሮሞ ነውን??
ግልፁ አመክንዮ ብልጽግና የአማራ ህዝብን በመደበኛ ሁለመና የሚነቅል #ጦሮ ነው - ለእኔ።
 
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
 
አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሉዓላዊ ሚዲያ እና የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ በክፍል አንድ ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በኢህአዴግ አደረጃጀት እና በብልጽግና አደረጃጀት ያለውን መዋቅራዊ ልዩነት አብራርቷል። ያው አቶ ኤርምያስ የህወሃት መራሹ የኢህዴግ ዬግንባሩ መደበኛ ፖለቲከኛ ስለነበር የአደረጃጀቶችን ውስጥ የማወቅ አቅም አለው። ትንታኔው በፓለቲካ ፓርቲ የአደረጃጀት መርህ አይደለም። ቢሆን ብዙ የማነሳቸው ጥያቄወች ነበረኝ። የአወቃቀሩን ዘይቤ ባህሪውን ብቻ ነው የገለፀው። እርዕሱ እኔ እማተኩርበትን ብቻ ነው የወሰድኩት። እንዲህ አይነት ግንዛቤን የሚያሳድጉ ማብራሪያወች ለጨመቱ ፖለቲከኞች መልካም ይመስለኛል። ለመሞገትም ምቹ ሩም ይሰጣል።
 
አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሲገልጥ "#ብልፅግና #የአማራ እና #የኦሮሞ ጥምረት ነው።" ይህም የሆነው ውክልናቸው በቁጥር ስለሆነ ነው የሚል ዕድምታን ነው ያስቀመጠው። በዚህ ዕሳቤው ለናሙና እስኬ ዶር ለገሰ ቱሉ ያገኙትን ቁልፍ እድል በኦሮምያ፤ ወይንም በሱማሌ አንድ የአማራ ልጅ ዕድሉን ካገኜ ያስረዳኝ።
 
“የአማራ ብልጽግና የሚባል የለም” አቶ አረጋ ከበደ።
 
ለመሆኑ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ፌድራሊዝም በኢትዮጵያ አለ ብሎ ያምን ይሆን??? የእኔን ስነግረው ፌድራሊዝም በኢትዮጵያ ያለው አማራ ክልል ብቻ ተንጠልጥሎ የቀረ ጥውልግ ፍልስፍና ነው ኢትዮጵያ መሬት ላይ። "መልከ ጥፋን በሥም ይደግፋ" እንደሆነ እገልጽለታለሁኝ። ምዕራባውያኑን፤ አውሮፓውያንን ለማጭበርበር የተሠራ ቅብ #የድንጋይ ሃውልት ነው። 
 
የብልጽግና አደረጃጀት ቅጁም ከዚህ ይመነጫል። ጠቅላይ ሚር አብይ "እኛ ዝሆን ነን፤ እንሰብራለን፤ እንቀረጥፋለን፤ እንበላለን" ባሉበት ወቅት አላፈሩም "ብልጽግና የማነው ብለው ሰወች ይጠይቁናል፤ እኛም #ብልጽግና የኦሮሞ ነው እንላቸዋለን" ብለውናል። ዕውነቱም ይህ ነው።
 
እኔም እማምነው ይኽውን ነው። ብልጽግና የኦነግ መንፈስ በገዳ አስተምህሮ የተጫነው፤ የመሥራቹን ሃይማኖታዊ ቀመሩንም አስልቶ የተደራጀ ነው። እኔ ፓርቲ ለማለት በጣም ነው የሚቸግረኝ። ዛሬ ተሽሞንሙኖ ቢቀርብም ምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት መርሆችን ያልተከተለ አፈንጋጭ ተቋም ነው ብዬ ነው እማምነው።
 
 በወቅቱም የጨነገፈ ብዬ ጽፌበታለሁ። ምርጫ ቦርድንም ሞግቼበታለሁኝ። ብልጽግና ክልላዊ እንጂ ብሄራዊ ተቋም ነው ብዬ አላምን። ምክንያቱም ብዙ ነገሩ ቅብ እና በብልጠት ዲስኩርን ሰንቆ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት መርሆ የማይከተል በአሰኜው ሰዓት በተመሰጠረ የራሱ ህግ #ህግን #ጥሶ ያሻውን የሚፈጽም ሞገደኛ ተቋም ነው። 
 
የኢትዮጵያን ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌወች፤ ዓለም ዓቀፍ የሰባዕዊ መብት ድንጋጌወችን፤ ዓለም ዓቀፍ የፓርቲ የአደረጃጀት መርሆችን ሁሉ ጠቃጥቆ የተፈጠረ ነው። እራሳቸውን ጠቅላይ ሚር አብይን የሚመስል ነው። ለዚህም ነው ዶር አብይ እራሳቸው አሰመራጭ ኮሜቴ ሰብሳቢ ሆነው እሳቸውን እራሳቸውን #በፕሬዚዳንትነት አቅርበው ብቻቸውን ተወዳድረው ያስመረጡት።
 
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል ይላሉ ጎንደሮች ……… አቶ እስክንድር ነጋ ይህን ፈጽሟል ሲባል ሰምቻለሁ በሌላ የውይይት መድረክ። #አልፈፀመም። የባልደራስ ምስረታ ለማካሄድ የከፈለበትን አዳራሽ ተከለከለ። ግፍ በገፍ። ተሰብሳቢው መንገድ ዳር ሆነ ዕጣው። እዛ ላይ ሆኖ ትክከለኛውን ፕሮሲጀር መከተል አላስቻለውም። አሳዛኝ ክስተት ነው የነበረው። የነበረውን ወከባ አንርሳ። መንቀሳቀሻ፤ መፈናፈኛ ነበር የተነሳው። በኋላም በመኢህድ ግቢ ድንኳን ጥሎ ነው የከወነው። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እኮ ሁሉ እያላቸው፦ የዓለሙ የሰላም ሎሬት ተሸላሚ፤ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች አዛዥ ሆነ ነው በስጋት ተወጥረው እዬተረባበሹ በሳቸው ሰብሳቢነት የብቻ እጩ፤ የብቻ ተመራጭ የሆኑት። ስለሆነም ከዚህ ጋር ተያይዞ በአቶ እስክንድር ላይ የሚነሳው የማመሳስያ አቅርቦት ትክክል አይደለም። 
 
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ስመለስ የአማራ ህዝብ በህወሃት ዘመን በነበረው የተጽዕኖ መስመር ነው ብልጽግናም የተጓዘው። በብልጽግናም፤ በኦሮማራም መኖሩን ከመገበር በስተቀር የአማራ ህዝብ አተረፈ የሚባለው ቅንጣት የፖለቲካ፤ የማህበራዊ፤ የሃይማኖታዊ የተስፋ ትርፍ አላገኜም። የአማራ ህዝብ አተረፈ ከተባላ በኦሮማራ ማገዶነት፤ ብክነት፤ ሰላም ማጣት፤ መሰዋት፤ ውድመት እና ስጋትብቻ ነው።
 
ወደ ውክልናጉዳይ ስንመጣ ኦሮሞወች፤ አርጎባወች፤ ቅማንቶች፤ አገወች በአማራ ክልል የፖለቲካ ውክልና ሙሉ ለሙሉ ሲኖራቸው በዬትኛውም ክልል ግን ይህ ፈጽሞ አልተሞከረም። ከክልሉ ውጪ የሚኖረው የአማራ ህዝብ ብዙ ነው።
 
 ይህ ለ33 ዓመታት የዘለቀ መርግ አመክንዮ ነው። ያልተደፈረ የማይደፈር። ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ ለ33 ዓመታት 50+ የሆነው የአማራ ህዝብ ለሳዕታት ያህል የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ አያውቅም። ኢትዮጵያ የአማራን የተፈጥሮ ፀጋ ባጣች ቁጥር ትጎዳለችም። 
 
የሆነ ሆኖ በመላ ኢትዮጵ ውስጥ የአማራ ፖለቲከኛ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውክልና በሌለበት "ብልጽግና የአማራ እና የኦሮሞ ነው" ብሎ ደፍሮ የሚያናግር ምንም አይነት የፋክት አመክንዮ የለም። 
 
በአማራ ክልል የአማራ ህዝብ በልጆቹ ውክልናው ሙሉ ሆኖ እንዳይከናወን፤ አማራ በፖለቲካ ውክልናው ከፍ ብሎ እንዳይወዳደር አማራ ክልል ተሸንሽኖ ውክልናው ለሌሎችም ተሰጥቷል። የአማራ የፖለቲካዊ መብት ቅርጫ ላይ ነው። ግዴታው ደግሞ ጫን ተደል። የአማራ ክልል እንደ ኦሮሞ ክልል ቢሆን #ዶር ለገሰ ቱሉ ውክልናቸው በአማራ ክልል ሆኖ የፖለቲካ ጠቃሚነታቸው ግን ለኦሮምያ ክልል ባልሆነ ነበር። 
 
ይህ ቀልድ እንዲቆም ነው መሠራት ያለበት። ይህ ነው ህወሃትን ከመንበሩ ያወረደው። ግሎባሉም አምኖበት ነበር ያ ታሪካዊ ሂደት የተከናወነው። ብልጽግናም ለቀኑ ቀን የሰጠው ዕለት አይቀርለትም መራራ ስንብት። እርግጥ ነው የሰከነ፤ የጠሞነ ትጉህ ፖለቲከኛ ይሻል። ከውስጥ ችግሩን አይቶ መመከት የሚያስችል አመክንዮ ካለ ይህን መሰል ፈጣጣ ዝበትን መግራት ይቻላል።
 
ሌላው ሌሎች ክልሎች በቁጥራቸው ልክ ውክልና ያገኙበት #የስልጣን ተዋረድ ስጦታም የሚወራረደው በዘመነ ኢህአዴግ የአማራ ቁልፍ የውክልና መሰረቶች ተከፋፍለው ለሌሎች ክልሎች ስለታደለ ነው። ባለውለታው የአማራ ህዝብ ሆኖ ተወዳሹ ጠሚር አብይ አህመድ ናቸው። 
 
ይህን አመክንዮ ደፍሮ የሚያነሳውም የለም። በዚህም ሂደት ተጎጂው የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና ይሆናል። የነበረውንም ሙሉ ለሙሉ ነው ያጣው የአማራ ህዝብ። 
 
አሁንም የብልጽግና ሌሎች ክልሎችን ውክልና ሰጠ ቀልድ የአማራ የፖለቲካ ውክልና #ተሸንሽኖ ስለተሰጣቸው ነው። ለክልሎች ብቻ ሳይሆን ለተደማሪወች የታደለው የፖለቲካ ውክልናም የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና #እንዲጫጫ ተደርጎ ነው። ይህ ፋክት ስለሆነ ለድርድር ፈጽሞ ሊቀርብ አይችልም።
 
ሌላው ቀርቶ በዘመነ ኦሮማራ ፍቅር በፍቅር በነበረበት ጊዜ የለውጥ መንፈስ ተሸካሚ አማራ ክልል ነበር። ከውጭ የገቡት ፖለቲከኞች ካባው፤ መብቱ፤ ሽልማቱ የፖለቲካ መድረኩ የነበረው አማራ ክልል ብቻ ነበር። እንዲያውም ግርባው ብአዴን ለእኔ የካባ አምራች የኢቤንት ሠርገኛ እንደነበር ነው የሚረዳኝ። ዛሬ እንዲህ በሁሉም ዘርፍ ስደተኛ ሊሆን። በወቅቱም ጽፌበታለሁኝ። 
 
ብናገላብጠው፤ ብንደምረው፦ ብንቀንሰው፤ ብናባዛው፤ ብናካፍለው የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና በዘመነ ህወሃት መራሽም ይሁን በዘመነ ብልጽግና #ታንቆ የተያዘ ነው። የፋመው የአማራ ህዝብ ግልጥ እና ስውር፦ የግል እና የወል ተጋድሎውም ይኽው ነው።
 
 የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ አማንያን ሊሂቃንን ጨምሮ ዕጣ ፈንታቸው በብልጽግና #ረመጥ ነው። ካለ ሙሉ ሥር - ነቀል ለውጥ ትክክለኛውን ዕውነታዊ የፖለቲካ ውክልና ማምጣት አይቻልም። 
 
ከዚህ ጋር ተያይዞ ብቅ ያሉት ቀንበጦች ወይ በሞት፤ ወይ ደግሞ ዕድሚያቸው በካቴና እንዲወራረድ ይደረጋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ህዝብ በመቀነስ ፕሮጀክትም መከራውን ተሸካም የአማራ ህዝብ እና የኦርቶዶክስ አማንያን ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም የማድህዬትም ተግባር በስፋት እዬተሰራበት ነው። 
 
አጣዬ ከ9 ጊዜ በላይ ስትነድ እሷን መልሶ ለመገንባት ያላቸው በተደጋጋሚ ዋጋ ሲከፍሉ አብሮ መደህዬት ግድ ይሆናል። ይህም ታቅዶ እዬተሠራበት ያለ ጉዳይ ነው። የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና በትክክለኛው መንፈስ ቢሆን ምጣተ አማራ አይመጣም ነበር። 
 
የአማራ መንፈስ መነቀል ብቻ ሳይሆን መሳደዱም ልክ ሊወጣለት አይችልም። እዬተማገደ፤ እዬተገበረ ነው። የትኛው ቁልፍ ቦታ ይሆን አማራ ያለው? ገንዘብ ሚር? ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር? ፍትህ ሚር? በፀጥታው ተቋማት? ልሙጥ ነው። ምክትል አፈ ጉባኤ አማራ ነበሩ? ዛሬ ኦሮሞ ነው። 
 
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ለክልሎች አደልኩ፤ ዕድል ከፈትኩ ብለው የሚደሰኩሩት ሁነት በረደኑን የሳቸው ማህበራዊ መሠረት የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ፖለቲካ ሳይሆን የተሸከመው አሁንም የአማራ ህዝብ ፖለቲካ ህዝብ ላይ ነው የተጫነው። ይህ ብልጠት ለእኔ ማጭበርበር ነው። በማጭበርበር ዘላቂ ፍላጎትን ማስፈፀም አይቻልም።
 
ሌላው #ብሄራዊነት ተነስቷል። ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ፕሮጀክት ውስጥ አንድም ኢትዮጵያኒዝምን የሚያበረታታ፤ የሚያፋፋ መንፈስ የለውም። ድርቅ የመታው ነው። ይህ ደግሞ ዶር አብይ አህመድ የመንፈስ #ነቀላ እና #ተከላ ላይ ስላሉ አቅደው የሚፈጽሙት ነው። ሚዲያወችን እዮቸው። 
 
ወጣቶች የሚወዳደሩባቸውን መስኮች የፋና ላምሮትን ሎጎ በአስተውሎት እዩት፤ የሳቸው የግል ፕሮጀክቶችንም እዩ። በማስተዋል መርምሩት። ከትውፊታችን ጋር ምንም ቀረቤታ የለም። ዝርግ ነው፤ ለዛውም መዛግ ሽው የሚለው። ምክንያቱም ሳይለንት ማጆሪቲው የተከደነ ሲሳይነቱ አለና። ለቀኑ ቀን ሲሰጠው የቀን ተስፋ ይበራል።
 
በተጨማሪም ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን መመኜት በሚመለከትም ገና የሚጠብቁት ሳይሆን ሆነውበታል እኮ። ብልጽግና ተቋማቸው ፕሬዚዳንታዊ ነው። ፓርላሜንታዊ ህገ መንግስቱ በሳቸው በአብይዝም ድንጋጌወች ተተክቷል። 
 
ኢንጂነር ታከለ ኡማን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሲያደርጉ ህግ አውጥተው ነው። የአስቸኳይ ጊዜ ሲያውጁ፤ የፓርላማ አባላትን ሲያስሩ፦ ሚኒስተሮችን ሲሾሙ በሳቸው ፊርማ ነው። እጅግ ዘርፈ ብዙ አመክንያችን ማንሳት ይቻላል። ለመሆኑ ህግ እና ህገ መንግሥት ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ምናቸው ናቸው? እንደልቡ እኮ ናቸው። ከአነጋገር ዘይቤያቸው ጨምሮ "#ሸለፈታም።" 
 
ለብዙ ሰው ላይታዬው ይችላል ለእኔ ግን ኦነግ ወደ አዲስ አበባ ከተጋበዘበት ጊዜ ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ አዲስ አበባ #በኦሮምያ ክልል ጠቅልለዋታል። እንደ እኔ እምነት አዲስ አበባ የምተዳደረው በኦሮምያ ህግ እንደሆነ ነው። 
 
ህዝባዊ ስብሰባ ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ አዲስ አበባ ላይ የማይፈቀደውም ለዚህ ነው። ይህ ተመስጥሮ የተያዘ ስውር ገመና ነው። አሁን ያለው የአዲስ አበባ እድሳትም ታሪካዊ፤ ትውፊታዊ ሁነቶችን ምንጠራ ነው። ይህን ሂደት የዛሬ 50 ዓመት በምናባችሁ እሰቡት።
 
 እኛ የተረከብናት አዲስ አበባ አትኖርም። ይህን የሚፈጽሙት ደግሞ በልባቸው ፕሬዚዳንት ነኝ ብለው ስለተቀበሉት ነው። እሳቸው ያቀዱትን ሲፈጽሙ ለእኛ ግን ደራሽ ዜና ነው። ለዚህ ነው የሚዲያ ተቋማት ከሰበር ዜና ሊወጡ የማይችሉት።
 
እንደ እኔ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ #ተጠባቂ ሳይሆን መሬት ላይ በህግ #ጥሰት እዬተከወነ ነው። ደገፋዊቻቸው ይህን የአናርኪዝም ጉዞ የተረዱት ላይሆን ይችላል። ዕውነቱ ግን ይሄው ነው።
 
ሌላው ያ ጠንካራው ደቡብም ፍርስርሱን ነው ያወጡት። በዚህ ውስጥ ብዙ ማህበራዊ ተቋማት ትስስር ተበጣጥሷል። በጥድፊያ ላይ ናቸው። በአንድ እሬቻ ዋዜማ ላይ አቶ ሽመልስ ሲናገሩ የ5 ዓመት ዕድል ተሰጥቶናል። ይህን በ5 አባዝተን እንሰራበታልን ነበር ያሉት። እምናዬውም ይኽውን ነው። 
 
ከዚህ ልቆ የሚወጣ የሃሳብ ልዕልና ነው ያቀተው። እንጂ ብልጽግና የተፈጠረበትን ተልዕኮ በጥድፊያ እዬከወነ ነው። ህልሙ ኢትዮጵያን አፍርሶ በሚፈቅደው ልክ መፍጠር። ታሪክ ከእሱ እንዲጀምር ማድረግ፤ ማስደረግም። ይህን በግድም ፦ በውድም ከህወሃት ጋር ሆነ ከፋኖጋር ያለው ውጊያም ዕውነቱ ይሄ ነው። ስድስት ፕሬዚዳንት በ6 ዓመት ...
 
ሲጠቃለል ብልጽግና የአማራ ክልልን የሲዳማን ክልል ያህል የዕውነት ዕድል ካገኜ እንደ እድል ይቆጠራል። እንኳንስ ከኦሮምያ እኩል የፖለቲካ ውክልና ሊኖረው። አይታሰብም። የአማራ ህዝብ ለሌሎች #ጌጥነት እሱ ሙሉ ግማዱን እንዲሸከም የተገደደ ህዝብ ነው።
 
 ይህም ብቻ አይደለም በመላ ኢትዮጵያ ያሉ የአማራ ተቋማት ሁሉ አመድ መልበሳቸው ላይበቃ ተቆርምጣ በተሰጠችው በክልሉም ተመሳሳይ ዕጣ እያስተናገደ ነው። አፈር ልበሱ ሬሳ ታቀፋ ነው ሂደቱ። 
 
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ከጥዋቱ ጀምሮ ያደረገው ተጋድሎ ትክክለኛ እና መርኃዊ ነው። እኔ እነ ቲም ገዱ አይደለሁም እንጂ በጥዋቱ ላደርግ የምችለው ማንኛውም ዜጋ በዬክልሉ እኩል የፖለቲካ ውክልና በብቃቱ እንዲያገኝ ማድረግ ዋነኛ መደራደሪዬ ይሆን ነበር። 
 
ያ ባይሆን ደግሞ በዬክልሉ ለአማራ ህዝብ ልዩ የአስተዳደር ዞን እንዲኖር አስደርግ ነበር፤ ይህ ካልሆነ ግን አማራ ክልል ብቻ ተንጥሎ ያለውን የውክልና ሁኔታ #እለሙጠዋለሁኝ። 
 
የአማራ ህዝብ በዬዘመኑ ለሚነሱ ፖለቲከኞች ፍላጎት 90% ሊሸከም የሚገደድበት ምንም ሁኔት የለም እና። ቲም ገዱ ጥረቱ በእነሱ ብቻ የተከናወነ ሊመስላቸው ይችላል። ሳይለንት ማጆሪቲ ውስጥ ያሉ የአማራ ልጆች በተከታታይነት እና በትጋት በሠሩት ነፍስ ያለው ተግባር ነበር ህወሃት ፈቅዶ እና ወዶ ስልጣኑን #በሰላም ለኦሮማራ ያስረከበው።
 
ወደፊትም የአማራ ህዝብ ማገዶነቱን ትርፍ በማያገኝበት ሁኔታ ከዬትኛውም አካል ጋር ህብረት ሊፈጥር አይገባም። የአማራ ህዝብ ብልህነትን እንጂ ብልጠትን ተግባራዊ ስለማያደርግ በብዙ ተጎድቷል። ይህ #መሰለስ የለበትም። 
 
በቃ ያለው የፋኖ ንቅናቄም ግድፈቶችን አርሞ በጠንካራ ሞጋች አመክንዮዊ ሃሳብ ሊፋፋ ይገባል። በራሱ በብልጽግና ሎጎ ውስጥ ብናኝ የኢትዮጵንይዝም መንፈስ የለውም። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በኢትዮጵያኒዝም ላይ ይቀናሉ። ፋክክሩም የደራ ነው።
 
ቸር አስበን #ቸር እንሁን።
ቅን አስበን #ቀና እንሁን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
21/10/2024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።