#እራህብ። " የሞት አፋፍ ላይ።" #ዛሬን ማኖር #በዛሬ ድርጊት #ፍሬ ነገን ማስቀጠል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሳቢያ ሳያስፈልገው ለሰባዕዊነት የሚደረገውን ተግባር መደገፍ ይገባዋል። ሰው የጀንበር ሥራ አይደለምና። የክልሉም አስተዳደር ይህን ጉዳይ ባሊህ ሊለው ይገባል። ለፋኖም ይህ ጉዳይ ጉልላቱ ሊሆን ይገባል።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
እንዴት አደራችሁ ማህበረ ቅንነት? ትናንት የምችልበት ሁኔታ ላይ ስላልሆንኩ ነበር ሼር አድርጌ አስተያዬት ያልፃፍኩት። የሆነ ሆኖ በዋርካው ምሬ ጉዳይ እኔ እንደታዘብኩት የተረጋጋ መንፈስ እንዳለ ነው። ስለሆነም ይህን የሰባዕዊ ጉዳይ አፈፃፀም ዕውን ይሆን ዘንድ የሚተጋበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
በራህቡ ምክንያት መቋቋም የተሳናቸው የትውልድ ዕንቡጥ ህፃናት ማለፋቸውን ሰምቻለሁኝ። እጅግ አዝናለሁ። ጣር ላይ ያሉም ይኖራሉ። ጉዳዩ ከአቅም በላይ፤ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት #ፈጣን የሆነ የፋኖ ውሳኔ ያስፈልጋል።
በህይወታቸው ወስነው እርዳታውን ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፦ ሹፌሮቻቸው፤ የሥራ ባልደረቦቻቸው ከመነሻ ቀጠናቸው እስከ መዳረሻው ድረስ በግራ ቀኙ ተፋላሚ ወገኖች በፋኖ እና በመንግሥት ሰራዊት፤ በአስተዳደሩ በኩልም ( አድማ በታኝ፤ ሚሊሻ) #አፈሙዝ #ፀጥ ሊልላቸው ይገባል። ሳይጨነቁ፤ ሳይፈሩ፤ በሙሉ የሰላም ሁኔታ ሰብዕውያን ተግባራቸውን ይፈጽሙ ዘንድ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል። ይህ ሰባዕዊነት #ቅዱስ እና #ንፁህ ተግባር ነው። በረከትም ምርቃትም ያስገኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ቸር አስበን፦ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፦ ቀና እንሁን። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
19/12/2024
ረሃብን የሚያውቀው #የተራበው ብቻ ነው።
"በሰሜን ወሎ ህጻናትን ጨምሮ 10 ሺህ ገደማ ሰዎች በከፍተኛ የምግብ እጥረት መጎዳታቸው ተገለጸ በሰሜን ወሎ በምግብ እጥረት ምክንያት የተጎዳ ሕፃን። "
የፎቶው ባለመብት, BUGNA HEALTH BUREAU
17 ታህሳስ 2024
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተከሰተ ድርቅ እና የምግብ እጥረት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ጨምሮ 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መጎዳታቸውን ወረዳው አስታወቀ።
በክልሉ ባለው ግጭት እና ተፈጥሯዊ ተፅዕኖ ምክንያት ወረዳው ለድርቅ እና የምግብ እጥረት መጋለጡን የቡግና ወረዳ ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ዓለሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የተነሳው ግጭት አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያለፈው ሲሆን ከግጭቱ ባለፈ ወረዳው "ዝናብ አጠር እና በተፈጥሮ የተጎዳ ነው" ያሉት ኃላፊው በተደራራቢ ችግሮች ምክንያት የምግብ እጥረት መከሰቱን አስታውቀዋል።
"ማኅበረሰቡ ምርት ባለማግኘቱ እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ መግበው የተሻለ የጤና እድገት እንዳይኖራቸው [አድርጓል]" ሲሉ ተፈጥሯዊውን ተጽዕኖ የገለጹት አቶ ገ/መስቀል፤ "ረድኤት ድርጅቶችም ለማኅበረሰቡ አልደረሱለትም" ብለዋል።
በወረዳው ብርኮ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ የካባ የአንድ ዓመት ከሦስት ወር መንታ ወንድና ሴት ልጆቻቸው በምግብ እጥረት "ስቃይ" ውስጥ እንደሆኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ምን አግኝተን እንርዳቸው? እስካሁን ድረስ በተቻለን ይዘናቸው ነበር። ከአዲስ ዓመት ወዲህ ግን ምንም ነገር የለም። ተያይዞ ቁልጭልጭ ሆነ እኮ?" ሲሉ ስላሉበት ሁኔታ አስረድተዋል።
"ጡጦ የምልበት ጎን [አቅም] የለኝም። ጡቴን ብቻ ነው ሳጠባቸው የከረምኩት። የጡት ወተት አሁን አነሳቸው፤ እንዴት ይድረሳቸው?. . . የተገኘው ምግብም አልሆናቸው አለ፤ አልስማማቸው አለ።"
ጠላ በመሸጥ ይተዳደሩ ነበሩት ወ/ሮ የካባ ልጆቻቸው ሲታመሙ ስራ እንዳቆሙ ይናገራሉ። ከቤተሰቦቻቸው ያገኙት የነበረውን የምግብ ድጋፍ በማጣታቸው መቸገራቸውንም ያስረዳሉ።
"ሐኪሞቹ «መግቧቸው፤ የምግብ እጥረት ነው» ይላሉ። እኛ ደግሞ ከየት እናመጣዋለን? ጊዜው ከፋብን። መሬቱ [ደረቀ]፤ እናት አባት አንድ ሁለት ኬሻ [እህል] ይሰጡን ነበር። ከዛ ብሶም ዘመኑ አጠፋው" ሲሉ እርሳቸውም በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ሕፃናት ልጆቻቸው እየተጎዱ እንደሆነ ገልፀዋል።
አንድ የአካባቢው የጤና ባለሞያ "ጤና ጣቢያ የሚመጡት እናቶች ከሚያጠቡት ልጅ ይልቅ እነርሱ ራሱ የከሱ ናቸው" ይላሉ።
እርሻቸውን በረዶ እንደመታባቸው የሚናገሩት የወረዳው ነዋሪ አቶ ደሳለው አለባቸውም፤ ባለቤታቸው እና የ10 ወር መንታ ልጆቻቸው በምግብ እጥረት ተጎድተው ጤና ጣቢያ መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባቄላ፣ ገብስ እና ጤፍ ያመርቱ እንደነበር የተናገሩት አቶ ደሳለው፤ "እናት የምትበላው የላትም፤ ልጆቹም የሚጠቡት የለም" ሲሉ ዘንድሮ "የተለየ" ችግር ገጥሞናል ብለዋል።
"በጣም ሲብስብን፤ ሲጨንቀን [ወደ ጤና ጣቢያ] አመጣናቸው። ሁለተኛ ቀናችን ነው። . . . [የምግብ] እጥረት ስላለባቸው ተዳክመዋል፤ ከስተዋል" ሲሉ ልጆቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
ቡግና ወረዳ ከአንድ ዓመት በላይ በፋኖ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን፤ ቡድኑ መንግሥት ለወረዳው መድረስ የሚገባውን መድኃኒት እና ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት አስተጓጉሏል ሲል ወቅሷል።
በወረዳው ዋና ከተማ አይና ቡግና የሚገኘው አይና ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ መኮንን አሻግሬ አካባቢው ካለበት ተፈጥሯዊ ችግር በተጨማሪ ከአዲሱ በጀት ዓመት በኋላ የተመጣጠነ የምግብ ላይ የሚሰሩ ረድኤት ድርጅቶች ግብዓት ማቆማቸውን ያሳያውቃሉ።
አንድ የጤና ባለሞያም ወረዳው የምግብ እጥረት ችግር ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ችግሩ ጎልቶ መታየቱን ለቢቢሲ ይናገራሉ።
በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የአልሚ ምግቦች እና መድኃኒቶች አቅርቦት በመስተጓጎሉ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሕፃናት "ለተወሳሰበ ምግብ እጥረት" እንደተዳረጉ ይገልፃሉ።
በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ የጤና ባለሞያዎች ለክትባት ዘመቻ ሲወጡ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሕፃናት 'በሥርዓተ ምግብ ልየታ' "የከፋ" የምግብ እጥረት ላይ እንደሆኑ መታዘብ ችለዋል።
ቢቢሲ የደረሰው እና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተለቀቁ ምስሎች የችግሩን ጥልቀት የሚያሳዩ እና ለእይታ የሚረብሹ ናቸው።
በቡግና ወረዳ ካሉ 16 ቀበሌዎች በተለይም ላይድባ፣ ብርኮ፣ ጉልሃ፣ በርኳኳ እና ፈልፈሊቅ በተባሉ ቀበሌዎች ከስድስት ወር እስከ አምስት ዓመት ያሉ ሕፃናት "አሳሳቢ" የምግብ እጥረት ላይ እንደሚገኙ የተተደረገው ጥናት አሳይቷል።
በዓለም አቀፍ 'አጣዳፊ የምግብ እጥረት' መለኪያ መሰረት 65 በመቶ የወረዳው ህፃናት በምግብ እጥረት መጎዳታቸውን የጤና ጥበቃ ፅ/ቤቱ መረጃ ያሳያል።
በዚሁ መለኪያ መሠረት 84 በመቶ የወረዳው እናቶችም "በከፋ ደረጃ" የምግብ እጥረት ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የፅ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ዓለሙ በቡግና ወረዳ ሰባት ሺህ የሚሆኑ ህፃናት በምግብ እጥረት መጎዳታቸውን እና ከሦስት ሺህ በላይ ነፍሰ ጡር እናቶችም መጎታዳቸውን አስታውቀዋል።
ለሦስት ቀበሌዎች አገልግሎት የሚሰጠው ብርኮ ጤና ጣቢያ ብቻ በኅዳር ወር አራት ሕፃናት በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ማለፉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጤና ጣቢያ ባለሞያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወረዳው በከፍተኛ የምግብ እጥረት የሕፃናት ሕይወት ማለፉን ማረጋገጥ እንዳልቻሉ የተናገሩት አቶ ገ/መስቀል፤ ነገር ግን ሕፃናት "የሞት አፋፍ ላይ" ናቸው ብለዋል።
"የሕክምና [ሥርዓቱ] ስለፈረሰ ከዚህ በላይ ልየታ ብናደርግ [ተጎጂዎች] እናገኛለን። . . . እያንዳንዱን [ቤት] አንኳኩተን አላየነውም" ሲሉ በወረዳው ያለው የጤና ቀውስ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል የአይና ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ መኮንን ገልፀዋል።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል "ለጋሽ ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደ ወረዳው ገብተው ማገዝ ካልተቻሉ የሰው ሕይወት እንደሚያልፍ ግልጽ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ማክሰኞ ታኅሳስ 08/2017 ዓ.ም. ሁለት ተሽከርካሪዎች አልሚ ምግብ እና መድኃኒት ጭነው ቡግና ወረዳ መደረሳቸውን ባለሞያዎች ተናግረዋል።
"ብዙ ሰዎችን እንታደጋለን" ሲሉ በአቅርቦቱ ተስፋቸውን የገለጹት አቶ መኮንን፤ እስከ ሦስት ወር ድረስ የሚበቃ ግብዓት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር የአልሚ ምግብ እና መድኃኒት አቅርቦቱ የማይቀጥል ከሆነ የጤና ቀውሱ "ተባብሶ" ይቀጥላል የሚል ስጋት አላቸው።
"ከዚህ የተባባሰ ነገር ሊኖር ይችላል። መድኃኒት ካልተገኘ ባለሞያው ኖረም አልኖረም ትርጉም የለውም" ሲሉ ከወዲሁ ስጋታቸውን ገልፀዋል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ