"የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰት የፈጸሙ ኃላፊዎችን ከስልጣን እንዲያነሳ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ መከሩ BBC" በማስተዋል ይደመጥ።

 https://www.bbc.com/amharic/articles/cvg69094qgeo

 

"የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰት የፈጸሙ ኃላፊዎችን ከስልጣን እንዲያነሳ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ መከሩ"

 

"የኢትዮጵያ መንግሥት፤ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚከሰሱ ባለስልጣናትን፤ "በተለይም የሠራዊት አባላትን በአስተዳደራዊ ፈቃድ" ከስልጣን እንዲያነሳ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አምባሳደር ቤዝ ቫን ስካክ መከሩ።

በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች "የሚፈጸሙ ያሉ ጥሰቶች" በቀጠሉበት ሁኔታ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህን መተግበር "አስቸጋሪ" ካልሆነም "የማይቻል" እንደሆነ ተናግረዋል።

እንደ የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ያሉ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በተመለከተ የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን የሚያማክረውን ቢሮ የሚመሩት አምባሳደር ቤዝ ይህንን የተናገሩት ረቡዕ ታሕሳስ 9፤ 2017 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ነው።

የትናንቱ መግለጫ፤ አምባሳደር ቤዝ ከሕዳር 29 እስከ ታህሳስ 2፤ 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የነበራቸው ቆይታ ላይ ያተኮረ ነው።

"በኢትዮጵያ እና በመላው አፍሪካ የተጀመሩ የሽግግር ፍትህ እና ተጠያቂነት ሂደቶችን ለማጠናከር" ወደ ምስራቅ አፍሪካ ተጓዙት አምባሳደሯ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸውን እና የፍትህ ሚኒስቴር ባዘጋጀው የሽግግር ፍትህን የተመለከተ ውይይት ላይ መካፈላቸውን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍትህ ቢሮ ኃላፊዋ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን የሽግግር ፍትህ ሂደት ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው የገለጹ ሲሆን "እስካሁን ባለው ሂደት ላይ ተስፋ እንደጣሉም" ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን "የሲቪክ ምህዳር መዘጋት እና በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ የቀጠሉትን ጥሰቶች" እንደሚያውቁ ጠቅሰዋል። እነዚህ ሁኔታዎች መንግሥት ሊተገብር እየተዘጋጀ ያለውን ሁሉን አቀፍ ሽግግር ፍትህ "አስቸጋሪ ካልሆነም የማይቻል" እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

"ሰዎች ሀሳባቸውን ለመግለጽ፣ እውነታውን ለመናገር ነጻነት ካልተሰማቸው የፍትህ ሂደት ላይ እንደማይሳተፉ እናውቃለን። በእነዚህ ሌሎች ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶችም በፖለቲካዊ ንግግር መፈታት አለባቸው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አምባሳደር ቤዝ፤ በኢትዮጵያ "ረጅም ታሪካዊ ጥሰቶችን እና አሁን የሚታዩ ግጭቶችን" ለመፍታት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ምን አይነት እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሆነ እንዲገልጽ የአሜሪካ መንግሥት እየተጠባበቀ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ የአሜሪካ መንግሥት "መወሰድ አለባቸው" በሚል በምክረ ሀሳብነት ከሚያቀርባቸው ጉዳዮች መካከል ጥሰቶችን የፈጸሙ የመንግስት ባለስልጣናትን የሚመለከተው ይገኝበታል።

"ሊታሰብበት የሚገባው አንድ ትርጉም ያለው እርምጃ ጥሰት በመፈጸም የተነሱ [ሰዎችን] ከስልጣን ማንሳት ነው። በተለይም የሠራዊት አባላትን፤ ለምሳሌ በወንጀል የተከሰሱን ሙሉ ምርመራ እስከሚደረግ ድረስ በአስተዳደራዊ ፈቃድ [ከስልጣን] ማንሳት" ተገቢ እንደሆነ ምክረ ሀሳባቸውን አቅርበዋል። የፌደራል መንግሥት ለተፈጸሙ በደሎች "ይፋዊ እውቅና" እንዲሰጥም አምባሳደሯ መክረዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ "ግልጽ፣ አካታች እና ተጎጂዎችን ማዕከል ያደረገ" የሚሆን ከሆነ የአሜሪካ መንግሥት "አጋር" ለመሆን ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ስላለፈው [ጉዳይ] ታማኝ መሆን እና በስልጣን ላይ [ባሉ ግለሰቦች] ላይ እውነተኛ እርምጃዎችን በመውሰድ ተጠያቂ ማድረግ ለመንግሥት በጣም አስፈላጊ [እርምጃ] ነው" ያሉት አምሳደር ቤዝ፤ የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የተካሄዱ የክስ እና የዲሲፕሊን ሂደቶች "ግልፅ እንዳልሆኑ" ተናግረዋል።

"ማን በምን ወንጀል እንደተከሰሰ፣ ቅጣቱ ምን እንደነበረ ምንም መረጃ የለንም። የሁሉን አቀፍ ሂደት አካል እንዲሆን ይህ [የክስ] ሂደት እንዴት እንደተካሄደ እይታው ሊኖር ይገባል" ብለዋል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።