ኧረ ድንግል ሆይ ድረሺ።" በሰሜን ወሎ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ህፃናትን ጨምሮ ሰዎች መሞታቸውን የዳሰሳ ጥናት አመለከተ" BBC
https://www.bbc.com/amharic/articles/c2exeywdz1do
" በሰሜን ወሎ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ህፃናትን ጨምሮ ሰዎች መሞታቸውን የዳሰሳ ጥናት አመለከተ"
"በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተከሰተ ከፍተኛ ምግብ እጥረት የእናቶች እና የህጻናት ሕይወት ማለፉ በዳሰሳ ጥናት ተረጋገጠ።
ካለፈው ወር ጀምሮ በወረዳው ከፍተኛ የምግብ እጥረት መከሰቱን ቢቢሲን ጨምሮ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን፤ ለዕይታ የሚረብሹ ምሥሎችም ይፋ ሆነዋል።
የአካባቢውን የምግብ እጥረት ለማረጋገጥ አጭር ዳሰሳ ያደረገው ወልዲያ ዩኒቨርስቲ ቀውሱ ከተነገረው በላይ "ከባድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ብሏል።
ስድስት ባለሞያዎችን ያካተተ ቡድን በቡግና ወረዳ አራት "ቁልፍ" ቀበሌዎች ላይ ባደረገው ምልከታ ከፍተኛ የምግብ እጥረት፣ የህክምና አገልግሎት እጦት እና የውሃ ችግር ማኅበረሰቡ መጎዳቱን አመልክቷል።
ቡግና ወረዳ በድርቅ የሚታወቅ አካባቢ ከመሆኑ ባለፈ የሰሜኑ ጦርነት ጠባሳ ያረፈበት እና ባለፈው ዓመት የጎርፍ እና የበረዶ አደጋዎችን በማስተናገዱ ማኅበረሰቡ "ፍሬ" እንዳላገኘ አርሶ አደሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ወረዳው ከአንድ ዓመት በላይ በፋኖ ኃይሎች መያዙን ተከትሎ፤ ወደ አካባቢው ማደባሪያን ጨምሮ የመድኃኒት እና የህክምና ግብዓቶች፣ የአንቡላንስ አገልግሎት፣ የባንክ አገልግሎት እንዲሁም የሴፍቲ ኔት እገዛዎች መቋረጣቸው ታውቋል።
"ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ተዳምረው ነው [ማኅበረሰቡን] ለእንዲዚህ ዓይነት ችግር የተዳረገው" ሲሉ የወረዳውን የቀውስ ምክንያት የተናገሩት አንድ የጥናት ቡድኑ አባል፤ የሰው ሕይወት ማለፉንም ተናግረዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ባለሙያው ምልከታ ባደረጉባቸው እና ጤና ጣቢያ ባላቸው አራት ቀበሌዎች እናቶች እና ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናት በምግብ እጥረት መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
ቢቢሲ የተመለከተው እና የወረዳውን የምግብ እጥረት እና የጤና ሁኔታን የሚዳስሰው ጥናት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከተመዘገቡ ሞቶች ውጪ አምስት ህፃናት እና ሁለት እናቶች በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ማለፉን ይገልጻል።
ሦስት ህፃናት በቆብ ቀበሌ (ክላስተር) ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ብርቆ እና ቅዱስ ሀርቤ በተባሉ ቀበሌዎች ደግሞ ሁለት የህፃናት ሕይወት አልፏል።
በወረዳው ዋና ከተማ አይና ደግሞ ሁለት እናቶች በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ማለፉን ባለሙያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአይና ከተማ በጎረቤቶቿ ቤት ለቡና በሚቀርብላት 'የቡና ቁርስ' ልጆቿን ትመግብ የነበረች አንዲት እናት "መቸገሯ ሳይታወቅ" ሕይወቷ አልፎ እንደተገኘች ማወቃቸውን ባለሙያው ተናግረዋል።
"ሰው በረሃብ እየሞተ ነው" ያሉት ባለሞያው፤ "በዚህ ዘመን ሰው በረሃብ መሞት የለበትም ብለን እናምናለን። ቡግና ላይ ግን ይሄ ተፈጥሯል" ብለዋል።
"እነዚህ [በአሃዝ የተገለፁት] በጣም ከአቅም በላይ ሆኖባቸው ተቸግረናል ብለው የሚመጡ ናቸው። ጤና ጣቢያ ሳይደርሱ የሚሞቱ በጣም ብዙ ናቸው" በማለት የተጎጂዎች አሃዝ ከዚህ ከፍ እንደሚል ይገምታሉ።"
ሌላ በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉ ባለሙያም በተለይም የቡድኑ የቆይታ ጊዜ ሰፊ ቢሆን እና ያልተረደሰባቸው አካባቢዎች ላይ መድረስ ቢቻል "ከዚህ የከፋ ነገር እንደሚኖር ጥርጥር የለውም" ብለዋል።
የቡግና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታዬ ካሳው በወረዳው የሰዎች ሕይወት ማለፉን በወሬ ከመስማታቸው ውጪ "የተረጋገጠ ነገር የለም" ሲሉ በከፋ የምግብ እጥረት የሰው ሕይወት ማለፉን አለማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አስተዳዳሪው ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ወረዳው ላይ በተከሰተው ከፍተኛ ምግብ እጥረት የሰዎች ሕይወት ማለፉን ለማረጋገጥ ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የጤና ባለሙያዎች በተደራጀ አግባብ ህፃንም ይሁን እናትም ትሁን ለሌላም [ሰው] ይሁን በተለይ ከረሃብ ጋር ተያይዞ ችግር ያለባቸው ቀበሌዎችን፤ በጣም የተጎዱ የምንላቸውን [ላይ] ጥናት እያካሄድን ነው" ብለዋል።
በወረዳው "ረሀብ ነው ተከስቶ የነበረው" የሚሉት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጌታዬ ካሳው፤ ወባ እና እከክን የመሰሉ ተዛማች በሽታዎች መከሰታቸውንም ጠቁመዋል።
የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ባለሙያው ወረዳው ላይ ያለው ተደራራቢ ችግር እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች እንደዲስፋፋ ማድረጉን የተናገሩ ሲሆን፤ "ከረሃብ ጋር ተያይዘው" የሚመጡ ሌሎች በሽታዎችም መከሰታቸውንም አክለው ገልፀዋል።
በወረዳው በተለይም ተጋላጭ የሆኑት ህፃናት፣ እናቶች እና አረጋዊያን ላይ "ትልቅ ተፅዕኖ" ማሳረፉን አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጌታዬ ካሳው 110 ሺህ ከሚሆነው የወረዳው ሕዝብ 79 ሺህ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው፤ "ተስፋ ሰጪ ሥራዎች" እተከናወኑ ነው ብለዋል።
መንግሥት፣ ዩኒሴፍ እና የዓለም የጤና ድርጅት የመሳሰሉ ረድኤት ድርጅቶች ምግብ እና መድኃኒቶችን ለተጎጂዎች እያቀረቡ ነው ያሉት አቶ ጌታዬ፤ ከላሊበላ ሆስፒታል ስምንት የጤና ባለሙያዎች ወደ ወረዳው አቅንተው አገልግሎት እየሰጡ ነውም ብለዋል።
አስተዳዳሪው በወረዳው ውስጥ ባሉት አራቱም ጤና ጣቢያዎች "በጣም የተጎዱ" ህፃናት እና እናቶች ተኝተው ህክምና እና ምግብ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአካባቢው ያሉ የሁለት ጤና ጣቢያ ባለሙያች ጅማሮው የተሻለ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉ በሚፈለገው ልክ ተደራሽ እየሆነ አይደለም ብለዋል።
ባለሞያዎቹ ወደ ጤና ጣቢያ ከሚመጡት ግማሽ ያህሉ ተጎጂዎች ያለ ምግብ እና መድኃኒት እርዳታ ወደ ቤታቸው እተመለሱ መሆኑንም ተናግረዋል።
የወረዳው አስረዳዳሪም እየቀረበ ያለው እርዳታ "በቂ ነው ማለት አይቻልም" በማለት፤ ገና ተደራሽ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የእህል መሰብሰቢያ ወቅት ላይ የምግብ እጥረት መከሰቱ የሚያሳስባቸው የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ባለሙያ፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ "ሙሉ ለሙሉ ወደ ረሃብ ይሸጋገራል" የሚል ስጋት አላቸው።
ወረዳው ዘላቂ የሆነ ትኩረት ያሻዋል የሚሉት ባለሙያው፤ ይህም አስቸኳይ ከሆነው የዕለት ደራሽ የምግብ እርዳታ ባሻገር ነው ብለዋል።
በዚህ ሀሳብ የሚስማሙት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጌታዬ፣ ማኅበረሰቡን በዘላቂነት ማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተተነጋገርን ነው ብለዋል።
የቡግና ወረዳ በተለያዩ ጊዜያት በድርቅ የሚጠቃ አካባቢ መሆኑን ነዋሪዎች የሚናገሩ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት ከትግራይ ተነስቶ ወደ አማራ ክልል ተስፋፍቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት የእርሻ ሥራ ከመስተጓጎሉ በተጨማሪ በወረዳው የነበሩት ውስን መሠረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በተጨማሪ ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ግጭት ምክንያት አካባቢው መሠረታዊዎቹ የጤና፣ የግብርና እና የእርዳታ አቅርቦቶች ተቋርጠውበት በመቆየቱ ችግሩ መባባሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ