የኛ ነገር። "አብዛኛዎቹ እርቃናቸውን የታገቱ 26 'ኢትዮጵያውያን' ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በፖሊስ ተገኙ" BBC
https://www.bbc.com/amharic/articles/cwyw3e2d2x5o
"አብዛኛዎቹ እርቃናቸውን የታገቱ 26 'ኢትዮጵያውያን' ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በፖሊስ ተገኙ" BBC
"የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በአንድ ቤት ውስጥ ታግተው የቆዩ እና ኢትዮጵያዊ ናቸው ተብሎ የሚታመኑ 26 ሰዎችን ጆሃንስበርግ ውስጥ ማግኘቱን አስታወቀ።
በቤቱ ውስጥ ከተገኙት ስደተኞች መካከል 15ቱ እርቃናቸውን የነበሩ ሲሆን፣ በቤቱ አቅራቢያ የተገኙት ቀሪዎቹ አስራ አንዱ ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸው ተነግሯል።
ሃያ ስድስቱ ሰዎች የተገኙት ሐሙስ አመሻሽ ላይ በጆሃንስበርግ ከተማ ሰሜን ምሥራቅ ዳርቻ ላይ ባለ ሰፈር ውስጥ ከጎረቤቶች በተገኘ ጥቆማ አማካይንት መሆኑን ፖሊስ ገልጿል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም ሦስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉት ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዴት እንደገቡ ግልጽ ባይሆንም ባለሥልጣናት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ መሆናቸውን ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ ነው።
ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ "የሕገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ቡድን" መዋቅርን ማፍረሱን አመልክቷል።
የተወሰኑት ስደተኞች ከተያዙበት ቤት ለማምለጥ ሲሞክሩ የሰበሩት መስኮት
ባለሥልጣናት የተገኙት ስደተኞቹ ታግተው ስለቆዩበት ሁኔታ እና አንዳንዶቹም ለምን እርቃናቸውን እንደነበሩ ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ከቤቱ አቅራቢያ የተገኙት ስደተኞች "መስኮት ሰብረው ያመለጡ ናቸው" በማለት የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ የከባድ ወንጀሎች ክትትል ቡድን ቃል አቀባይ ኮሎኔል ፊላኒ ንኳላሴ ተናግረዋል።
ከቤቱ ለማምለጥ የመስኮት መስታወት ሲሰብሩ እና ብረቱን ለመገነጥል ሲሞክሩ ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች ህክምና እንዲያገኙ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጿል።
ከስደተኞቹ መገኘት ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ይዘው የተገኙ ሲሆን፣ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተሳትፈዋል ተብለው ተከሰዋል።
ኮሎኔል ንኳላሴ "ለተጨማሪ ምርመራ ጉዳዩ ወደሚመለከተው አካል ተመርቷል. . . 26ቱ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ግለሰቦችም በአሁኑ ወቅት የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ሰለመሆናቸው ለማረጋገጥ ጉዳያቸው እየታየ ላይ ነው" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከጆሃንስበርግ በስተምሥራቅ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ 90 የሚሆኑ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ያለፍላጎታቸው እና ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ተይዘው መገኛታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ሊገኙ የቻሉት የአካባቢው ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር አንድ የታገተ ግለሰብን ለማግኘት ፍለጋ ባደረገበት ጊዜ ነበር። በፖሊስ ሲፈለግ የነበረውም ታጋች ኢትዮጵያውያኑ በነበሩበት ቤት ውስጥ ተገኝቷል።"
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ