ጉድ በል ጎንደርስ አሁን። እምም። ህምም። "በአማራ ክልል ዳኞች የሚፈጸምባቸው አካላዊ ጥቃት እንዳሳሰበው ኢሰመኮ አስታወቀ" ሪፖርተር።

 https://www.ethiopianreporter.com/137175/

 

"በአማራ ክልል ዳኞች የሚፈጸምባቸው አካላዊ ጥቃት እንዳሳሰበው ኢሰመኮ አስታወቀ"


"በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው አዋጅ ቁጥር 6/2015 ዓ.ም. መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ በአማራ ክልል በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች፣ ዳኞች ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የሚፈጸምባቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በተጨማሪም አሰባሰብኩት ባለው መረጃ በዳኞች እስራት፣ ዛቻና ያልተገባ ተፅዕኖ እንደሚፈጸም በመግለጽ የግኝቱን ውጤት መሠረት በማድረግ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና በኢሰማኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ተጽፎ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፕሬዚዳንትና ለክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያስረዳው፣ ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ድረስ በዳኞች ላይ ድብደባ፣ እስርና ወከባ ደርሶባቸዋል የሚሉ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት ተፈላጊውን የሰነድ መረጃ በመሰብሰብ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በዳኞች ላይ የሚፈጸም አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት በኢሰመኮ ግኝት ከቀረቡ ጉዳዮች አንደኛው ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ባሰባሰበው የሰነድና የቃል ማስረጃ ለአብነትም ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በአስቸኳይ አዋጁ ወቅት በአዊ ዞን በወረዳ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ በችሎት ላይ እንዳሉ የወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የጦር መሣሪያ ከታጠቁ ሦስት አጃቢዎች ጋር ወደ ችሎት በመግባት ዳኛውን ከችሎት በኃይል ወደ ውጭ በማስወጣት በፍርድ ቤቱ ደንበኞችና ሠራተኞች ፊት ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመው የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት ማድረሳቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በተጨማሪም ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2017 ዓ.ም. ድረስ በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ 35 ዳኞች በፀጥታ አካላት ተይዘው እንደነበር ኢሰመኮ ገልጿል፡፡ አክሎም 35 ከሚደርሱት ዳኞች 22ቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ታስረው መፈታታቸውን 13 ዳኞች ደግሞ አዋጁ ካበቃ በኋላ የታሰሩ መሆኑና አብዛኞቹ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን እስካጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በየደረጃው የሚገኙ የተወሰኑ አስፈጻሚ አካላትና የኮማንድ ፖስት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጊዜ ወሰን ካበቃ በኋላም ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻውን›› እንደ ሽፋን በመጠቀም በዳኞች አስተዳደር ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት ሕገ መንግሥትን በሚፃረር መልኩ የፍርድ ቤቶችን ተቋማዊና የአሠራር ነፃነት የጣሱ መሆናቸው ኮሚሽኑ አብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሲሰጥ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ለመፍታት ፍቃደኛ ካለመሆን ባሻገር የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባላከበሩ ፖሊሶች ላይ የሚሰጡ የቅጣት ውሳኔዎችን አለመፈጸም በስፋት የሚታይ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን በኮሚሽኑ ሪፖርት ቀርቧል፡፡

ኢሰመኮ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ የክልሉ ምክር ቤት የክልሉን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅን በማሻሻል ዳኞች ከስራቸው ጋር በተያያዘ ያለመያዝ፣ ያለመታሰርና ያለመከሰስ የሕግ ከለላ እንዲሰጣቸው እንዲያደርግ የጠየቀ ሲሆን፣ የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ፍትሕ ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ታስረው የሚገኙ ዳኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ፣ በፍርድ ቤቶች አሠራር ጣልቃ እንዳይገቡ እንዲሁም በዳኞች ላይ ከሚፈጸም ማንኛውም ጣልቃ ገብነት፣ ጥቃትና ትንኮሳ እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።