J 6/ 2019 ትናንት ከመሼ። እንዴት ናችሁ ውዶቼ? በውነት ውስጥ ያሉ ሞጋች ሃሳቦች።

 J 6/ 2019

ትናንት ከመሼ።
እንዴት ናችሁ ውዶቼ? በውነት ውስጥ ያሉ ሞጋች ሃሳቦች።
 
ትናንት ከመሼ አንድ ዜና አዳመጥኩኝ የባልደራስ ህልውን ስጋት ላይ ስለሆነ፤ የውጩን መንፈስ የሚያሰተባብር አንድ ተጨማሪ ጠቃሚ እርምጃ ባልደራስ ወስዷል። ጋዜጠኛ አቶ ኤርምያስ ለገሰን ምክትል ሰብሳቢ አድርጓል። አቶ ኤርምያስ ዛሬ ሳይሆን እሱን ድምጹን ከሰማሁበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ አባባ ውስጡ ናት፤ አጀንዳውም ናት። አቅምም አለው።
ስለዚህ ውሳኔው የተገባ ቦታ ለተገባ አቅም መሰጠቱ መልካም ነው። እንግዲህ በህይወቱ የተቃጣ ነገር ስለነበረ ከሰነበተ ብዙ የማድረግ አቅም አለው ብዬ አምናለሁኝ። የቀን ግብዣ ደግሞ የሚያመጣው ባይታወቅም። በገለጣው ለቀረለበለት ጥያቄም አገር መግባትን አንስቷል። 
 
በፖለቲካ ብስለቱ ልክ አላገኘሁትም መልሱን፤ በቀደመው የሐሴት ስካር ቢሆን ይቻል የሁናል ለወቅት ብቻ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ካቴና ናፍቆት ከሆነ ይሞክረው፤ "አይጥ ለሞቷ የድመት አነፍንጫ ታሸታለች" እንደሚባለው ነው። አሁን ፈጦ የወጣው የፖለቲካ ሙቀት "ሥልጣን አንለቅም" ነው። ለዛሬ አይደለም ለነገም። ይህ መቼም ተንባይ የሚሻው ጉዳይ አልነበረም። አዬሩ ራሱ እኮ አግሬሲብ ያደረገው "ሥልጣን" ተቀናቃኝ አቅም ብቅ አለ እኮ ነው። እንዲያውም ከቀደመው የከፋ ነው የሚሆነው።
 
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ሳዳምጠው ምክትል ስለመሆኑ እንጂ „ሾምነው“ አይልም። ሚዲያዎች ደግሞ ባልደራስ አቶ ኤርምያስ ለገሰን ምክትል አድርጎ „ሾመ“ እያሉን ነው። የቃል አጠቃቀሙ ያቃሉን ነፃነት የነፈገ ይመሰለኛል።
በመሾም፤ በመመረጥ፤ በመመደብ፤ በመተካት፤ በመሰዬም፣ በመወከል መካከል ሰፊ የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ልዩነት አለ። መመረጥ ከቦታው አብረህ አባል ሆነህ ስትገኝ ነው። መሾም የመንግሥታዊ አካል ሥልጣን ብቻ ነው። መተካት ከፊት ለፊት የነበረው በሆነ መንገድ ሥፍራውን በጊዚያዊነት ወይንም በዘላቂነት ሲለቅ የሚከወን ነው። አሁን እኔ የ አቶ ኤርምያስ ለገሰን ምክትል ሰብሳቢ እንዲሆኑ ውክልና ሰጠ ቢል ባልደራስ ብዙም የጽንሰ ሃሳብ ህጋዊ መጠይቅ አያስነሳም ... ሌሎችም እንዲሁ ...
 
ምደባ ግን ልክ አቶ ሙስጡፊ ኡመርን አዬነት አጋጣሚ ሲፈጠር በፖለቲካ ውሳኔ የሚከወን ነው። የዳኛ ወ/ሪት ብርቱካን ሜዴቅሳ ሹመትንም እንደ ፖለቲካ ምደባ በተወሰነ ደረጃ ማዬት ይቻላል። ስለዚህ ባልደራስ ባልወሰደው እርምጃ „ሹመት“ የሚለውን ቃል የጨመሩ ወገኖች ግድፈት ፈጽማዋል ብዬ ነው እማስበው። ጽንሰ ሃሳቡ በፍጹም መቀራረብ የማይችል ነውና ማረም አለባቸው ብዬም አስባለሁኝ። ቅራኔን በሚያደርጉ፤ ስንጥቅን በሚጠግኑ፤ መጦፍን በሚያስታግሱ ሥነኛ ኃይላት አጠቃቀም ላይ ሚዲያዎቹ ብርቱ ጥንቃቄ ቢያደርጉ ምርጫዬ ነው። 
 
በተጨማሪም ይሄ ለባልደራስ ላለበት ቀንበርም ተጨማሪ ወጀብ ይሆናል። ባልደራስ መንግሥት አይደለም፤ መንግሥት ለመሆን እዬሠራ ያለም አይደለም። ስለሆነም ይህ ውክልና በምን ስሌት „ሹመት“ ሊባል ይችላል? መጪው ችግር ሰለታዬው የበቀለው የተስፋ ችግኝ እንዳይጫጫ፤ ወይንም እንዳይከሰም የ አቅም ውርርስ ነው የተደረገው። ብልህ እርምጃም ነው። እኔ እንደ ኑዛዜ ያህል ነው ያዬሁት።
እግረ መንገዴን ማንሳት እምሻው ደግሞ አንዳንድ ወገኖቼ ባልደረስ እኮ ለሥልጣን አይደለም የሚሉ አሉ። ዜጋ በአገሩ እኩል ቢሆን ባልደራስ ለሥልጣንም ራሱን አደራጀቶ መንቀሳቀስ መብቱ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁኝ። ከሲቢክስ ወደ ፖለቲካ ድርጅት ራሱን መቀዬርም ይችላል በሂደት።
 
„ሹመት“ የምትለዋ ነገር ኢዜማ ሲፈጠር መንግሥትና ፓርቲ ሆኖ ነው። እንደ መንግሥት ቃለ ምህላ ሲፈጽም እና ሲያስፈጽምም አይተናል። ሁለት አካላትን ነው የያዘው። ከእህት ድርጅትም ድጋፉን አይተናል ከኢህዴግ ሳይቀር። በመልካምነቱ ባዬውም።
ኢዜማ አዲስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አህድዮሽ መንግሥታዊ አወቃር ነው ያለው 100% የአንድ ግንባር ሁነት። ስለሆነም ከምርጫ በኋላ ቢሆን አይገርምም ምን አልባት ምርጫና እርግጫ፤ ምርጫና ፍጥጫ እንደለመደበት ካልመጣ፤ በዚህም ራሱ አዬሩ ራሱ የሚናገረው ነገር አለ።በታዕምር ኦዴፓ መሪነቱን ለማንም አሳልፎ ይሰጣል ተብሎ አይታሰብም። ገና አስቀድሞ የመንገድ ጥርጊያው ይህው ነው።
የሆነ ሆኖ ገና በስም አብ ላይ እያለ ኢዜማ ከምርጫ በፊት ነው ይህን መንገድ የተከተለው። አዲስ ፓርቲ ሲፈጠር መንግሥት እና ፓርቲ ሆኖ መቼም ለእኔ እንቆቅልሽ ነው። ያው አባላቱን በተስፋ ስንቅ ለመቆዘር ካልሆነ ብዙም እንዲህ ያለ ውስብስብ መንገድ አስፈላጊነቱ አይታዬኝም። መዘምን የልዩነት ሃሳብን በማስተናገድ አቅም እንጂ በመዋቅር፤ በሥያሜ፤ በቃላት ውበት ለአላዛሯ ኢትዮጵያ የሚፈይደው የለም። 
 
ዓመቱን ሙሉ እኮ ዘመን ያሉ ውይይቶች፤ ዘመን ያሉ ኮሚሽኖች ተሰምተው በማይታወቁ ውብ ቃላት ሲተውኑ ተመልክተናል ግን የዴሞክራሲ ተስፋ በጠበንጃ እንደሚቀጥል እዬሰማን እያዬንም ነው። ስለዚህ እውነት ከሆነው፤ በ እጅ ከሚጨበጠው ከሚዳሰሰው ኮንክሪት ነገር መነሳቱ ከሁሉም በላይ ትውልድን አያባክንም። እኔ ጉዳዬ የትውልዱ ብክነት ነው። ለማይዘልቅ ዓላማና ፍላጎት የትውልድ ግብር ዘመን ሳይታክተው ስለሚያስተናግድ። 
 
የሆነ ሆኖ እሱ የክት ስለሆነ ኢዜማን ማለቴ ነው ፍቅሩ አልቆ የሚሆነው ሆኖ እስክናዬው ድረስ ለአሁኑ ተናገሪ የለውም መንግሥትም ፓርቲም ነኝ ቢል መንግሥቴን ልትፈትን መጣህ ተብሎ „ጦርነት“ እንገጥማለን አልተባለም።። ባልደራስ ግን በፋመ ወጀብ ላይ ስለሚገኝ „የሹመት“ ቅጥያ የሰጡት ሚዲያዎች፤ ግለሰቦች፤ አክቲቢስቶች ይህን ቢያሰተካክሉት መልካም ይመሰለኛል። „እንኳንም ዘንቦብሽ“ እንዲያውም ነው። 
 
"ሹመት" የሚለው ኃይለ ቃል ቅራኔውን ያሰፋዋል ግጭቱንም ያፋፍመዋል። „ሹመት“ በሚለው ላይ ግጭት ቢነሳ ባልደራስ ብሎት ኖሮ ቢሆን እኔ እራሴ እጅግ እምሞግትበት ነበር። እንኳን ዘመነኛው መንግሥት። የጽንሰ ኃሳብ አጠቃቀም ላይ የባለቤቱን ኮፒ ራይት መብት መጠበቅ ግድ ይላል። መጋፋትም የተገባ አይደለም። „ሹመት“ የሚል እኔ አላደመጥኩኝም። 
 
ሌላው አዲስ አበባ ጥሩ ሰው ማግኘቷ በመልካም ጎኑ ሳዬው። ከኢትዮ 360 ውጥን ጋር ሳዬው ደግሞ ሁለቱም ጀማሪ ተቋማት፤ ሁለቱም በፈተና ውስጥ ያሉ ተቋማት፤ ሁለቱም ፈተና የፈጠራቸው ተቋማት፤ ሁለቱም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በደጋፊዎቻቸው የማይፈቀዱ ሲሆኑ አንዱ በአንዱ ላይ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት፤ የትጋት እና የዳኝነት የልዩነታቸው እና የግንኙነታቸው መስመር እንዴት መስተናገድ እንደሚችሉም እጬጌው ሂደት የሚመልሰው ይሆናል። 
 
በመርኽ ደረጃ ግን ሲቢክስ ድርጅት ቢሆንም ባልደራስ ምን አልባት ነገ ወደ ፖለቲካ ድርጅት ቢቀዬርም ባይቀዬርም አሁን ባለው ሁኔታ ራሱን የቻለ ዓላማ እና ግብ ይዞ የተነሳ ስለሆነ በምን ሰንሰለት ኢትዮ 360 አማራጭ ሚዲያ አድርጎ ማዝለቅ እንደሚቻል ይህንም ለእጬጌው ሂደት ይተው።
 
ምክንያቱም „ባልደራስ ባለአደራ“ መባሉ ያለውን መከራ እያዬነው ነው። „የድምጻችን ይሰማ የችግር መፍቻ መንገዱ „ባለአደራ“ ሲባል ግን ከልካይ የለበትም። ከዚህ ላይ አንድ እምናገረው ነገር አቶ ኤርምያስ ለገሰ እንዴት እንደተቀበለው፤ እንድምን ሁለቱን አጣምሮ ለመስራት እንደ ተሰናዳ አዳምጨዋለሁኝ። 
 
ብቻ ድርጅቶች ሆኑ ተቋማት ሲመሰረቱ የዓላማ እና የግብ ግልጽነት ለቀጣይ ህልውናቸው ወሳኝ ነው። የመንፈስ ብክነትን የመቆጣጠሪያ አንዱ መሰረታዊ ጉዳይም ይመስለኛል፤ እኛ አጀንዳችን ሆኖ ባይታወቅም።
 
አቅማችን እዬበላ ተሰበሰበ ሲባል የሚበተን፤ በቀለ ሲባል የሚያረው የተቋማት፤ የድርጅቶች አመሰራረት ታስቦባቸው ሳይሆን ፍጥረተ ነገራቸው የችግሮች ገፊነት ስለሚሆንም ዝልቀታችን ያው ታቱ ነው። በየግል ህሊና ያለውን መታመንን እንኳን ማዝለቅ አንችልም እንኳንስ በወል የሚሰሩ ነገሮች። ባዕድን ለማብቀል። 
 
የግልጸኝነት ጥገኛ ያለመሆን አፈጣጠር በሌላ በኩል ለተጠሪነት እና ለተጠያቂነትም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ቀላቅለን ወይንም አዋህደን ወይንም አዋደን፤ ወይንም አስተዛዝለን ሁለት ዓላማዎችን ከጀመር ግን ዝልቀቱ፤ የመታመኑ ነገር፤ የጠላት ብዛቱ ወዘተረፈ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ያለበት ወቅታዊ ችግርም ይሔው ነው። ኢትዮጵያ ትቅድም እና ኦሮሞ ይቅደም።
 
የዚህ የዓላማ እሰጣ ገባ ነው የቀወሶቹ ሁሉ መናህሪያ። „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው፤ ኦሮምያ ከኢትዮጵያ ውጪ“ ሁለቱን አስተሳሰቦች እና የትግል ጭንቅላቶች በአንድ ዘንግ ለመስፈጸም አንዱ አንዱን እዬዘለለ፤ እዬደፈጠጠ በሄደ ቁጥር መንገዱ ሰጠመ።
ኢትዮጵያዊነት በዚህ ውስጥ ለአዲስ መከራ ተዳረገ፤ ከቃል ያለፈ ባለቤትም አላገኝም። ኢትዮጵያን የመሰጠሩ ዜጎች ናቸው ከ27 ዓመት ፍዳ በኋላ ለአዲስ ትኩስ የበቀል መፈጸሚያ ሆነው አሁን ግፍ እዬተቀበሉ የሚገኙት። ዜግነትም ማዕከላዊ አጀንዳ አለመሆኑን አስተውያለሁኝ። 
 
ይህን ስል ግን የባልደራስ ንቅናቄ እና የኢትዮ 360 ሚዲያ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላቸው ጽናት ከኦዴፓ ከገጠመው ኢትዮጵያን የመምራት ችግር ጋር የሚነጻጸር አለመሆኑን አበክሬ መግለጽ እሻለሁኝ አሁን ባላቸው አቋም እና አቅጣጫ የሁለቱም መርህ ይመሰለኛል።
በመጨረሻ የአዲስ አበባ ቅን መንፈሰ ተጋድሎ አቶ ኤርምያስ ለገሰን እንዳታጣ የምሻውን ያህል ኢትዮ 360 እሱን ቢያጣ ጭንቅላት አልቦሽ ህልም ይሆናል። እስኪ ሁለቱንም የስጋት መሰኮቼን ለእጬጌው አሸክሜ ቀኑን ይባርክ በማለት ልሰናበት።
ኑሩልኝ መሸቢያ ሰንበት፡፤

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።