በራስ አቅም ውስጥ ስለመስከን።

 

በራስ አቅም ውስጥ ስለመስከን።
 

 
እንዴት ናችሁ ውዶቼ? ደህና ናችሁ ወይ ክብረቶቼ የኔታዎቼ ለአላዛሯ ኢትዮጵያም ቅኔዎቼም?
አንድ ሰው መጀመሪያ እኔም አቅም አለኝ ብሎ ራሱን ማሳመን ይኖርበታል። ሁለተኛው አቅሜ ከሌላው ነፍስ አያንስም አይበዛም በማለት ተመጣጣኝ ሙቀት ለህሊናው መቀለብ ይኖረብታል በራስ አቅም መስከን። ሦስተኛው ዕድሉን ባገኝ የበለጠኝ ነፍስ ከደረሰበት ለመድረስ አንጎሌ የጎደለው ወይን ከህሊናዬ የወለቀ አንዳችም ብሎን የለም ብሎ ማሰብ ይኖርበታል።
ሌላው እንደ አስተዳደጉ ምቹ ሁኔታ ይለያይ፤ እንደ ፈጣሪ አላህ ፈቃድ ይለያይ እንጂ እኔም ፈጣሪዬ የሰጠኝ ልዩ ሥጦታ ወይንም የተለዬ መክሊት አለኝ በማለት መክሊቱን ፈልጎ ማግኘት ይኖርበታል።
መክሊት በራሱ ጊዜ፤ በሁኔታዎች አጋጣሚ ሊታወቅ ይችላል። ግን ባለቤቱ ራሱም ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ለዚህ ዘመን መቼም ትልቁ ናሙናችን የማለዳ ኮከቧ እጩ ተዋናይት እመቤት ካሳ ትልቅ ምሳሌ ናት።
ከዛ እልም ካለ ገጠር ወጥታ ዛሬ ያለችበትን የሞራል ልዕልና እና ለየተቀባይነት ደረጃ ስናስተወል ለአቅሟ የሰጠቸው ዕውቅና እና ክብር ምን ያህል ብጡል እንደሆን በማስተዋል ልንማርበት ይገባል። በዚህ አጋጣሚ የፈጠራ ባለቤቱን አባ ቅንዬን ገጣሚ፤ ጸሐፊ አቶ ፍጹም አሰፋን ላመስግነው። የእሱ ነገር ብዙ ሚስጥር አምድነት አለበት።
ወደ ቀደመው ስመለስ አንድ ሰው ስለራሱ ያልተጋነና ወይንም ያልከሳ፤ ልኩን የጠበቀ፤ ለአቅሙ ዕውቅና መስጠት መቻሉ መኖሩን በመኖር ቀለም ያሰክንለታል። ከሁሉ በላይ በራስ የመተማመን ማገሩን ያጠብቅለታል።
እያንዳንዱ የሰው ልጅ ለዓለማችን ውበት የራሱ የሆነ ድርሻ እንደሚበረክትም ራሱን ለራሱ ማሳመን ይኖርበታል አንድ ነፍስ። አንድ ክስተት ብቻው አድጎ ጎልምሶ አይታይም። የአንድ ክስተት አድጎ መጎልመስ የብዙ ህብር አቅሞች ስብስብ አቅም ሰጪነት ነው የህልውናው መሰረት።
አንድ ሰው ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል ባልኩት ርዕስ ላይ እንደገልጽኩት አንድ ታዊቂ ነፍስ ታዋቂነቱን ያደመቁለት፤ የሚገነቡለት የብዙኃን ህብራዊነት ያቅም መዋጮ ስለመሆኑ አንስቻለሁኝ። በዚህ ህብራዊነት አንድ አቅም መጋቢ ባጀገነው ነፍስ ውስጥ የእኔም ድርሻ አለበት ብሎ በድፍረት ማሰብ ይኖርበታል።
አቅም መጋቢው የራሱንም አቅም ዕውቅና ከሰጠ በተስፋ ጥንዝለት ላይ ችግር አይገጥመውም ያጀገነው ቢንሸራተት። አንድ ነፍስ ለራሱ አቅም ዕውቅና በሰጠ ቁጥር ሌላ ቦታ መዋለ አቅሙን ባውልኩት ልክ ተስፋዬን አገኘዋለሁኝ የማለት ሞራሉም ሙሉዑ ይሆናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የኢትዮ 360 ሚዲያ መስራቾች ለመክሊታቸው የሰጡት የዕውቅና እና ድፍረት ነው ተስፋቸውን ማዋል፤ ማሳደር ብቻ ሳይሆን ቋሚ ጥግ እንዲያገኝ ያደረገው።
በሌላ በኩል አቅም ሲጪው አቅም መግቦ አቅም የተበረከተለት ተሰፋ ሲወድቅ አብሮ የሚወድቀው ለዛ ተስፋ የእሱም ባረኮት እንዳለበት ልብ ስለማይለው ነው። ለራሱም አቅም ዕውቅና ስለማይሰጠው ነው።
በዚህ ውስጥ የምናዬው ትልቅ ብልህነት ደግሞ አለ። አቅም ተመጋቢው ብዙም ዕውቅና የማይሰጠው፤ በቅጡም አክብሮ የማይዘው፤ እንዳሻው የተከማቸን አቅም እንደ አልባሌ የሚያፈሰው አቅሙ የእሱ ብቻ ሆኖ ከዛ ዘውድ ደረጃ እንዳደረሰው የሚያውቀው አቅም መጋቢው የሰጠውን አቅም የሸበሸበው ዕለት ይሆናል። እስከዛ ምንም ግምት አይሰጠውም - በነፃ የተገኜ ፏፏቴ አድርጎ ስለሚያው አስቀድሞ በአሰተዳደር ድህነት ይሾልከዋለው።
በዚህ ውስጥ ሁለት ነገሮችን አዋደን እንይ።
አቅም መጋቢና
አቅም ተመጋቢ
አቅም ሰጪው አቅም መግቦ ጀግና ያደረገው ነፍስ ሲወድቅ ቀድሞ የራሱን አቅም ዕውቅና ካልሰጠ ጀግናው ባንዳለጠው ቁጥር እሱም አብሮ ያንዘላልጠዋል ተስፋ ቢስም ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ለማጀገን ያበቃውን አቅም ከዬት እንዳገኘው በቂ ትኩረት፤ በቂ ዕውቅና ሰጥቶት በቅጡ ያላስተዳደረውም አቅም ተመጋቢው ጀግንነቱ መውደቁን የሚውቀው ከወደቀ በኋላ ይሆናል።
ስለዚህ አቅም ሰጪውም አቅም ተመጋቢዊም በውስጣቸው ያለውን አቅም በመስጠትና በመቀበል ያለውን ድልድይ በቅጡ ዕውቅና ሰጥተው ማስተዳደር ቀዳሚ የትልማቸው መስመር ሊሆን ይገባል እላለሁኝ።
አቅም ዝም ብሎ ከሜዳ የሚታፈስ ጠጠር አይደለም። አቅም ዝምብሎም እንዳሻው በርካሽ ግብይት የሚገኝ አይደለም። አቅም ነፍስ ሆኖ፤ ነፍስ ዘርቶ ነፍስ የሚያደረግ የክህሎት ጥረት መንበር ነው።
እንበርታ!
መሸቢያ ሰንበት።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።