ፍትኃት እንዴት? ፍትኃት በማን? ፍትኃት ለማን? ዕለተ ሰኞ ማዕዶተ ጠባቂ

ፍትኃት እንዴት? ፍትኃት በማን? ፍትኃት ለማን?
 

 
ዕለተ ሰኞ ማዕዶተ ጠባቂ
በከበቡሽ የቁራሽ እንጀራ ብራና
በቢሆነኝ የተብራራ ብራ
በሰብለ ሕይወት አዝመራ
ለራህብ የሚራራ።
„የሰው ልብ መንግድ ያዘጋጃል፤
እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቃናለታል“
(ምሳሌ 16 ቁጥር 9)
• መቅድም።
ውድ ቤተሰቦቼ እንዴት ሰነበታችሁልኝ? ደህና ናችሁ ወይ? ናፍቃችሁኛል!!! እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። አሁን ደግሞ በጋ ነው። በጋ ነፍሴ ነው። ይቀለኛል። መንፈሴ ፏ ፍንትው ይላል። ይፈታታል ሁለመናው።
በጋ ቢለብሱትም፤ ቢመገቡትም አይዋ በጋን እቅፍ እድርገው ቢሞጨሙጩትም፤ አሽኮኮ ቢያደርጉትም በጋ ጠሐይ ነው። ብርኃን። እና ሥርጉትሻ እና በጋዋ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው። ደህና ነኝ።
„አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁ“
• ምስጋና።
(1) ጹሑፌን ያነበባችሁ፤ የተቻችሁ፤ ሼር ያደረጋችሁ የኔወቹ የእኛነት ውስጦቹ ልስልስ ያለ፤ ዘንጠፍጠፈ ያለ ሞንሟና ምስገናዬ በያላችሁበት ይድረስልኝ። አሜን። ኑሩልኝ ለእኔም ለቅኒትም ኢትዮጵያም።
(2) የት ጠፋሽ? ደህና ነሽ ወይ ብላችሁ አክብራችሁ ከህሊናችሁ ሆናችሁ ስለደህንነቴ አበክራችሁ የጠዬቃችሁኝ ቤተሰቦቼ ውስጤን የምገልጽበት ቃል የለኝም። እናንተ ሰው ወዳጆች ወገኖቼ ሆይ! የእኔ ድንግል በያላችሁበት ጥላ ከለላ ትሁንልኝ።
አጤ ፌስቡክ እናንተን የመሰለ አሳቢ፤ አዛኝ፤ ጠያቂ፤ አጽናኝ፤ አይዞሽ ባይ ስለሰጠኝም አክብሮታዊ ምስጋናዬን አቀርብለታለሁኝ። ፌስቡኬኛ ሳልሆን ያቃጣልኩት፤ ያባካንኩት ጊዜ እጅግ ይቆረቁረኛል። እንዲህ አይነት ወገን የሚገኝበት የአብሮነት አውድነት ፍጽምናው የልዕልና ነውና። ተመስገን።
• ለምን ጠፋሁኝ?
የጠፋሁት ምክንያታዊ ነበር። ከመጋቢት 18/2010 ጀምሮ እሰከ ሐምሌ 19/2010 ድርስ ምዕራፍ አንድ ነበር። በ100 ቀኑ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የተግባር ትትርና ተመስጬ ነበር።
እርግጥ ነው በግንቦት 5/2010 ላይ „አብይ ሆይ!“ የሚል ዘለግ ያለ አንድ ሞጋች አቤቱታ አቅርቤ ከምርጫ በፊት አቤቱታ ላላቀርብ ቃል ገብቼ ነበር። ጹሑፍ ሰፊ ነበር። ደጋፊ ተሟጋች ሆኖ የወጣ ነበር።
አብሶ የካቢኔ አውቃቀሩን ሰውኛ እና ተፈጥሮኛ ስለማድረግ፤ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ላይ ገና በማለዳው ዕውቅና ለመስጠት የታዬው ማረግረግ አሳስቦኝ፤ አማራ ልጁን ዒላማ ማስተማር ትውፊቱ መሆኑ ለአገር ብሄራዊ አንድነት ጠቃሚ መሆኑን፤ መልካም ማህበረበስብ ለመፍጠር ሊወሰዱ የሚገቡ በኽረ ጉዳዮች የያዝ ነበር።
ነገር ግን ሐምሌ19/ 2010 የኢንጂነር ስመኜው በቀለ አገዳደለ ብቻ ሳይሆን የአገዳደሉ ሂደት ትራጀዲነት ይህ ሥርዓት ተስፋ ሊሆን ከመቻሉ ጋር ግብግብ በህሊናዬ ፈጥሮ ጥርጣሬ ያሰደረብኝ ወቅት ነበር። ከዛ በኋላ ዕምነቴ ተሟጠጠ።
ጊዜያቶችን በተለያዩ ምዕራፎች ከፋፍዬ ከወንኩኝ። በድምሩ 4 ምዕራፍ ነበር። 2/3/4 ረጃጅም ነበሩ። ምዕራፍ አንድ ግን በጣም አጭር ነበር። አሁን ዛሬ 5ኛው ምዕራፌ ተጀመረ።
• ጥሞና።
ጥሞና በህይወቴ ውስጥ አንዱ መርሄ ነው። ወጀብ ሲበዛብኝ፤ ፍሰኃ ሳገኝም፤ ዕድል ሲቀናኝም፤ ዕድል ሲወጣ እና ሲወርድም ምንግዜም የጥሞና ጊዜ እውስዳለሁኝ። የጥሞና ጊዜዬ አጭር ረጅም ሊሆን ይችላል። ለተወሰነ ሰዓትም ሊሆን ይችላል።
ጥሞና ስወስድ ቤተሰቦቼም ሳይቀሩ ማዕቀብ ይጣልባቸዋል። የቅርብ ሰወቼም እንዲሁ። ጥሞና እንደ ኦክስጅን ለሰው ልጅ የሚያስፈልግ የህሊናዊነት ቁምነገር ነው። የግል ውይይት ጠረጴዛ።፡መጠሞን ራስን ያስገዛል። ራስን ይበረብራል። ራስን ይቦርሻል። ራስን ያጸዳል። እራስን ይገራል።
ስለዚህ የማድመጥ፤ የማተኮር፤ ሃሳብን የመሰብሰብ፤ ክለሳ // ሪባይዝ የማድረግ፤ የጥሞና የስክነት ጊዜ ስለሚያስፈልገኝ ከብርቱካን 14 በኋላ የተሰጠኝ ወቅት ስለሆነ ፌስቡክ ለመግባት ፈቃደኛ አልነበርኩም።
ይህ በዚህ እንዳለ በጣም የተጨናነቀ ምዕራፍ ነበር ምዕራፍ 4። ስለዚህ ከብርቱካን 14 በኋላ ደግሞ ምዕራፍ 5 ለመጀመረ የስክነት፤ የመረጋጋት፤ እራስን የመግራት፤ እራስን የማረቅ፤ ከራስ ጋር የመወየያት፤ ሁኔታዎችን ሰክኖ የማድመጥ ጊዜ አስፈለገኝ።
• ማድመጥ የጥሞና የልብ ጆሮ ነው።
ማድመጥ በንግግር ጥበብ ውስጥ ሁለተኛው ፒላር ነው። እኔ ሦስት ስለማደርገው ግብረ መልስም አለ በእኔ ፍልስፍና ሦስተኛ። የሆነ ሆኖ ከንግግር ጥበብ ወጣ ያለው እራስን፤ አካባቢን፤ የተሳትፎ ዓውድን፤ የህሊና አቅምን፤ መኖርን፤ የመኖር አኗኗሪ ሁነቶችን ለማነጋገር፤ ለማዋያዬት የጥሞና ጊዜ ትልቅ የልብ ጆሮ የሚያስፈልግበት የማድመጥ ጊዜ ይሆናል።
ሌላው እያደመጣችሁ የምትሰሩበት እና እራሱን አስችሎ ለጥሞና ጊዜ የሚኖራችሁ የማድመጥ ክፈለ ጊዜ በፍጹም ልዩ ናቸው። አደቡ ጣዕሙ፤ የማስተዋል ለዛው፤ ተፈጥሮን ጥበቧን ለማንበብ ያለው ፈቃደኝነት የማይለቅ ቀለም ነው።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ዜጋ በአገሬ ጉዳይ በሙሉ አቅም እና ጊዜ በነፃ ካለምንም ክፍያ እንደሚያገለግል፤ እንደሚሳተፍ ሰብዕና ሁሉንም ነገር አቻችሎ፤ አሳታርቆ ለመጓዝ ይህን መሰል እራስን የመግዛት፤ እራስን የመግራት፤ እራስን የመመርመር፤ ስህተትን የማረምም ወቅት በእጅጉ ያስፈልጋል።
• ተመስገን ነው።
የእኔ የሚዲያ ተሳታፊወች ቀደም ባለው ጊዜ በራሴ በጸጋዬ ድህረ ገጽ፤ በደጉ ዘሃበሻ፤ በደጉ ሳተናው አምደኝነት፤ አሁንም ባሉት በከበቡሽ ብሎግ፤ በፌስቡኬ፤ በቁጥር አንድ እና በቁጥር ሁለት የሥርጉተ ሥላሴ ዩቱብ ቻናሌ የተሳትፎ ማሳዬ ሁልጊዜ ጥፍት እምልበት ጊዜ አለ። በሌላ በኩል በሚስጢረ ጥሞናዊ ወቅቴ አበክሬ እሰራለሁኝ። እምሠራው ግን በግድፈቶቼ፤ በቸኮልኩባቸው፤ በተገጨሁባቸው ዘርፎች ላይ ነው። በ አመዛኙ በጥፋቶቼ ላይ ነው እማተኩረው።
የሆነ ሆነ አሁን ተመስገን ነው በማዕከላዊ አብይዝም መንፈስ ውስጥ ጥሞና ቃሉ እራሱ ዕውቅና አግኝቷል። የተከበረው አቶ እስክንድር ነጋ ከስሜን አሜሪካ እና ከአውሮፓ ሲመለስ የጥሞና ጊዜ እንዲወስድ እራሱን አስችዬ ተጠሞን ብዬ ጽፌያለሁኝ። እንዲህ ሁሉን ትቶ ካቴና ሊሆን ቤቱ ለጊዜው ስስታም ሆነ እና ሳይጠሞን ሥራ ጀመረ። ባልደራስን ከሲቢክስ ድርጅት ወደ ፖለቲካ ድርጅት ለመለወጥ የሰከነ የጥሞና ጊዜ በእጅጉ ያስፈልግ ነበር። ወዝን ለማሳረፍም።
የአብን እና የባልደራስ መሪዎች ታስረው ሲፈቱም እራሱን አስችዬ በተለይም ለአቶ ክርስቲያን ታደለ ተጠሞን ብዬ ጽፌ ነበር። በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የግድያ ሁነት ተከትሎ የታሠሩት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሲፈቱም እባከወት ይጠሞኑ ብዬ ጽፌ ነበር።
አቶ ልደቱ አያሌው ከእስር ሲፈቱም እባከወት ይጠሞኑ ብዬ ጽፌያለሁኝ። ሰሚ አልነበረም። ከእስርም ሲፈቱ ሆኖ ከአንዱ ትጋት ወደሌላው ሲዘዋወሩ ጥሞና ብሎ ነገር ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች አይታወቅም። ፈጽሞ። አድርጉ ተብሎ እንኳን አይሆንም።
አስተዋሽ ሰጥቶቸው እንኳን አክብረው አይተረጉሙትም። ምክንያቱም ስላልከፈሉበት። ከዚህ ለአንድ ጊዜ የምክር አገልግሎት ስንት ፍራንክ ያስከፍላል።
ሌላው ቀርቶ አሁን በብርቱካን 14 ሲሳተፉም ሲያጠናቅቁም ፖለቲከኞች ሊጠሞኑ ይገባ ነበር። እማዬው ግብግብ ሚዲያ ላይ ነው። ወይንም ፎቶ ሾፕ ላይ። አያችሁ እግዚአብሔር ለእሱ የሚሰጠው ጊዜ ይፈልጋል። ላደረገው ነገር ሁሉ ክብር ሞገስ ሊሰጠው ይገባል። ለተመስገን አቅልም፤ አደብም ያስፈልጋል። ዓለም ሰፊ ናት። ጊዚያዋም እንዲሁ።
መኖርን ለሰጠ አምላክ ብታሸንፍም፤ ባታሸንፍም „አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁ“ መባል አለበት። ይኖርበታልም። እኔ አንድ ቅን ኢትዮጵያዊ ጋር ስተዋወቅ ፈጣሪዬን በርከክ ብዬ አመሰግናለሁኝ። በዚህ በክፋት በተሞላች፤ በከርዳዳዋ ዓለም ውስጥ ከኢንትሪግ የጸዳ ሰው ማግኜት ለእኔ ከላይኛው ነው ብዬ አምናለሁኝ።
• አቅም።
የህዝብ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የወንዝ ዳር አሽዋ ነው። በቃ ዝም ብለው ያገኙት። ለዛም ነው ሲያባክኑት የሚታዬው። በልገሳ የሰጣችሁትን ሳያከብሩ ያነን ሲያጡ ሠራዊት አሰለፍው ከፍለውም ሌላ ዘመቻ ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሚሊዮኖች በነፃ አገለገልናቸው። ሳናውቃቸው፤ ሳያውቁን። ያ ቅንጦት ነበር። ለእኔ አሁን ላይ ማለቅለቅም ነበር ማለት ይቻለኛል።
ያን ክብር፤ ያን ሞገስ፤ ያን ተስፋዬ መባል በአፍጢሙ ደፍተው 3 ሰኔወችን፤ 3 ጥቅምቶችን ለቀውስ አሰናዱ ረሸኑ፤ አሰሩ፤ አሰደዱ፤ አፈናቀሉ የእኔ ሥልጣን በአፍሙዝ የተገኜ ነው ለማለት ብዙ ደከሙ። ኢትዮጵያን ጫካ አደረጓት። ይህ የዕብደት ጉዞ ከምን ሳንክ መጣ ቢባል የጥሞና ጊዜ ብሎ ነገር ካለማወቅ የመጣ ነው። ጥሞና ላፒስ፤ ላውንደሪ፤ ቡርሽም ነው።
የሰው ልጅ ለፈጣሪው ጊዜ ከኖረው ብዙ በጣም ብዙ ጎዳና ይጠረግለታል። ህልም ያያል። መንፈሱ የሚግሩት ረቀቅ ጸጋወች ይታደላል። አይደለም አገር ለመምራት ትዳር ለመምራት፤ እሱም ቢቀር ከአንድ ሰው ጋር የቀረበ ግንኙትን ለመፍጠር ጥሞና መድህን ነው።
ጥሞና ስክነት ነው። ጥሞና መርጋጋት ነው። ጥሞና ተፈጥሯዊ ላፒስ ነው። ጥሞና ዕውቀት ነው። ጥሞና ብልህነት ነው። ጥሞና ነብይም ነው። ጥሞና ማህንዲስም ነው። ማግሥትን ይቀይሳል።
ተመስገን እምለው የምርጫ ሰሞናት የጥሞና ቀናት ተብለው ተሰዬሙ በብሄራዊ ደረጃ። እልል አለች ሥርጉትሻ። አሁን ደግሞ ለእቴጌ ትግራይ የጥሞና ጊዜ ሰጥቻለሁ ብለዋል ዶር አብይ አህመድ። ይህን ፈቅደውት ወይንስ በአስገዳጅ ሁኔታ?
ይህም ሆኖ ጥሞና የሚለውን ቃል መጠቀማቸው እራሱ መልካም ነው። እሳቸው ከራሳቸው አፍልቀው እንዳተገበሩት ማድረግ ግን የተለመደ ነው። እሳቸው የማንኛው ሰው ሃስብ ዘራፊ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ሳይቀር ዘርፈው የራሳቸው አድርገው ያቀርቡታል ትንሽ ቃላት ቀያይረው። ከዘረፉ በኋላ በሳቸው ፍልስፍና ይታቀፋል። አሁን አሁን ነጮችም እዬሞገታቸው ነው የዘረፏቸውን የሰውን ፍልስፍና።
ጥሞና እዬፈረሷት፤ እያቀጠሏት፤ እዬተደፈሯት ያለችው የቅድስት ኦርቶዶክስ ትወፊቷ ነው። ንብረቷም ነው። ከቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በማውጣት ፖለቲከኞች እንደ እምነታቸው ጥሞና ይወስዱ ዘንድ ግን የገዳ የድንገቴ ሱናሜ ሲያጥለቀልቀኝ ከራሴ የግል የጥሞና መርህነት አውጥቼ ኢትዮጵያን ለማዳን ተራጋጩ፤ ገረጭራጫው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይሰክን ዘንድ ሊቃናቱ፤ ሊሂቃኑ ጥሞና ይወስዱ ዘንድ ስማጸን ነበር።
አሁንም እማጸናለሁኝ። ይህን ቋሚ ቅን ታዳሚወቼ ያውቃሉ እንደ ሊቀ ትጉኃን አቶ ሰለሞን ኃይሌ ያሉ። ርዕስ ሰጥቼ ብዙ በጣም ብዙ ጽፌበታለሁኝ። ለጎሸው ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የመልካምነት ቅራሪ ለነሳው ሰብዕናችን። ሰውነታችን እራሳችን ለምንፈትነው ቀራኒዮ ለላክነው ግብታዊነታችንም ጭምር ጥሞና ያስፈልገናል። የጥሞና ክትባት ለእያንዳንዳችን። እሳቸው ከተጠቀሙበት በኋላ ከዚህም ከዚያም ጥሞና ሲሉ ተንታኞች አድምጫለሁኝ።
• ለመሆኑ?
የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ማይክ፤ ካሜራ፤ አንደበት፤ ማምታትት፤ መዘባረቅ፤ መንጨባረቅ፤ መበጥበጥ፤ ማደፍረስ፤ መናድ፤ መደበላለቅ፤ መጨፈላለቅ፤ ልቅነት መቼ ነው የሚጠሞነው? ጥያቄ ያ ነው።
ሹፌር ሆኜ አሳዬሁ ለካቢኔወቼ ተከታይ አጣሁ ብለውናል፤ እስኪ ጥሞና ይውሰዱ እና ከአስልቺነት ራስወትን ይታደጉት? የሚገርመው የጥሞና ጊዜ ብለው በምርጫው አሳውጀው እሳቸው ጅማ ላይ አጤ ሆነው ቤተ - መንግሥት ሰርተው ነበር። አዲስ አበባ ላይም እንዲሁ። አይችሉማ። ቁንጥንጥነት፤ ቅብጥብጥ፤ ሙልጭልጭ ያለ ሰብዕና ነውና ያላቸው። ለጥሞና የሚመቹ አይመስለኝም።
አሁንም እቴጌ ትግራይ ትጠሞን ብለው አማራ ይዞታህን ከተነጠቅክ ሰነፍ ነህ ብለው ክተት አውጀዋል። ለትግራይ የእራሻ ወቅት ጥሞና ሰጠን ሲሉ፤ ለአማራ ሠራዊት ደግሞ ቀዝቃዛ የክተት ጥሪ ታውጆለታል። ገበሬው እኮ ነው ፋኖም ሚኒሻም።
የጥሞና ጊዜ „ገድሎ እግዚአብሔር ይማርህ“ አይደለም። የገደሉትን ህዝብ ምህረት ባይጠዬቅ የገደሉትን ህዝብ የፈጠረ አምላክ ስላለው ተጸጽቶ አመድ ነስንሶ፤ ትቢያ ለብሶ ምህረት መጠዬቅ ነው እዮርን ይገባ የነበረው።
በነገራችን ላይ አቶ እስክንድር ነጋ ስብሰባ በአዲስ አበባ ጠራ ሲባል በግንቦት 01/2011 ነፍሳቸውን የማያውቁት ጠቅላዩ በቤተ መንግሥት ልደታ ዕለት የፖለቲካ ሰዎችን የሚዲያ ሰወችን በድንገቴ ጉባኤ ቤተ - መንግሥት ጠሩ። አትኩሮት ለመሻማት። ነገር ግን እዬር ሌላ ነገር ፈጸመ። ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን አደጋ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከሰተ።
ያን ጊዜ ከበቡሽ ብሎጌ ላይ ይገኛል ዶር ለማ መገርሳ እና ዶር አብይ አህመድ አመድ ነስንሰው ፈጣሪን ይቅርታ ይጠይቁ ዘንድ፤ የጥሞና ጊዜ ሊኖራቸው እንደሚገባ ጽፌም ነበር።
ከዛ በኋላም ያን ያህል የደም ጅረት ሲፈስ በዬጊዜው እባከወትን ጥሞና ይውሰዱ ብዬ ተማጽኜ ነበር። ለዚህም ነው የማድመጫ ጊዜ ስሌላቸው በዓለም አቅፍ ደረጃ እንዲህ የወደቀ ዕቃ የሆኑት። ሌላው ቀርቶ አንባገነን መሆን አልተቻላቸውም።
አንባገነንነቱን እንኳን አላወቁትም። የራሺያን መሪ ፑቲንን የሚያድንቁ አንድ ሊቀ - ሊቃውንት የዶር አብይ አህመድን እውር ድንብሱን የአንባገነንነት ሩጫ ማቅረብ አይሻም። ይህ ምን ለማለት ነው? አንባገነን መሪ ለመሆን እንኳን አቅሙ የሌላቸው ስለሆኑ።
አሁን ፕሬዚዳንት የሚለው ሥም ቀርቶባቸው ነበር እሱንም ይዘዋል። የሚገርመው ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ፕሬዚዳንት፤ አንድ ጠቅላይ ሚኒስተር፤ አንድ ም/ ጠቅላይ ሚኒስተር እና አንባሳደር ነው ያለው። አይገርምም? ፍርክርክ።
(1) ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ።
(2) ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ።
(3) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ደመቀ መኮነን።
(4) „የብልጽግና“ ፕሬዚዳንት አብይ አህመድ
(5) የውጭ ጉዳይ ሚር አቶ ደመቀ መኮነን። የባይወሎጂ ሙሁር።
ለዚህ የሥራ ድልድል እራሱ ጥሞና ያስፈልገዋል። 100ሚሊዮን ህዝብ ላላት አገር ሰው ጠፍቶ አንድ ሰው ፕሬዚዳንትም/ጠቅላይ ሚኒስተርም ለዛውም ፕሬዚዳንት እያለ/ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ያው አንድ ነፍስ?
አሁን በትናንቱ የፓርላማ ውሎ ከ60 አንባሳደር/ ወደ 30 ዝቅ እናደርገዋለን፤ በነፃ አገልግሎት ውጭ ጉዳያችን እናከናውናለን የሚል አዲስ ትልምም አዳምጫለሁኝ። በተመላላሽም ይሰራሉ ብለዋል። ውጤቱ ሳይገለጽ የምርጫው ማለት ነው። ከዛ በኋላ መንደፋደፍ ሆነ። የሆነ ሆኖ ዲፕሎማሲ በትርፍ ጊዜ ከተሠራ ሙያው ባለሙያ ስላለው እነሱ ይሂዱበት። ይሄ ቀርቷቸው ነበር ይህንም ለመበተን ተሰናድተዋል።
ማስታወቂያ ሚኒስተር ኢትዮጵያ የላትም። የውድቀቱ የውሃ ልክ ያሳያል። አሏት የሚባሉ የሚኒስተር መ/ቤቶችም እሳቸው ናቸው ሚኒስተሩ። የጤና፤ ከንቲባነት፤ የዲኮሬሽን፤ የቀለም፤ የፓርክ፤ የጽዳት፤ የህንፃ ግንባታ፤ የቅርሳቅርስ፤ የደን ልማት፤ የልመና፤ የዘይት አከፋፋይነት፤
የመጋዝን ሠራተኝነት፤ አንባሳደርነት፤ ተጽዕኖ ፈጣሪም - ካድሬም - ፕሮፖጋንዲስት - አክቲቢስትም - ሞደሬተርም - አስተዋዋቂም - ገላጭም - አክተርም - ሞደኛም - ፓስተርም፤ ቆመስም - ሃጅም - ዳኛም - ፈራጅም - ኢኮኖሚስትም - ፕሮጀክት ማናጀርም- ምን ያልሆኑበት ቦታ አለና? ሁሉም ቦታ እሳቸው አሉ ግን የሰነፍ ብሆዕቃ ወይንም የሰከራም ልብስ ነው የሆነው ሁለመናው። ኢትዮጵያን ከልባችሁ እዘኑላት እባካችሁ ቅኖቹ።
• ቅደም ተከተል።
ባለፈው ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢንፍሌሽን ግሸፈት እና መፍትሄወችን ስጠቋቁም የጻፍኩት ነበር። ቅደምተከተል አንዱ አድርጌ። እሳቸው በምናባቸው የሠሩት ቅደምተከተል አለ። አሁን ጦርነቱን በሚመለከት እዬነገሩን ነው።
ሌላውንም አጀንዳወች ያቆዩና ለዛ እሳቸው ህሊና ውስጥ ላለው የሸፍጥ ድንኳን ማሟያ፤ ማቀዝቀዣ ያውሉታል። እዬቆጠቡ ነው የሚያወጡት። ምንዛሬ በሉት … ምንዛሬው ከፍ የሚልበትን ወቅት ያውቁታል … የሚያስጨበጭብበትን ... ጭብጨባ ከሌላ አልተደመጥኩም ብለው ይጠይቃሉ ... የ ሻሻው የፒኮኩ ልዑል ...
እንደ አገር ግን ብሄራዊ ህዝባዊ የሆነ የተግባር ቅደምተከተል የለም። ምን አልባት በሳቸው ህሊና ያለው የገዳ ወረራ፤ የገዳ መስፋፋት፤ የገዳን አስምሌሽን ለማስፈጸም ከያዙት የህሊና ኢማጅኔሽን ዳንቴል በስተቀር። አንዱ ቅርፊት „ብልጽግና መደመር“ ሲሆን ሳይሆን ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ነው እምንሰማው። ወይ በሳቸው// ወይ በማንቆርቆሪያወቻቸው።
ለመሆኑ ከተሞችን ኢሪሊበንት ለማድረግ ከሠሩት ፕሮጀክት ውስጥ የትኛውን አሳኩ ለሚለው በአጣዬ፤ የሽዋ ሮቢት፤ በዝዋይ፤ በሻሸመኔ የፈጸሙት ውድመት ትግራይ ላይ ባለው፤ በነበረው ጦርነት „ጀግኖች ከሆኑ ለምን ከተማዋን ለቀው ወጡ?“ ሲሉ አዳምጬ ነበር።
አሁን ላይ በሚገልጹት ውስጥ ነው ይህ ከቀደመው ጋር አያይዤ አንዱ የቅደም ተከተል ሲናሪዮ እንደ ነበር የምረዳው። ያውቁኛል። አንጀት ጉበታቸውን አውጥቼ እንደምከታተላቸው።
ባህርዳርን በተመኙት ጊዜ ማውደም አልቻሉም። ሰማዕቱ ባህርዳር በሰኔ 15/2011 አልፎት ነበር። ወደፊትስ? ጎንደር ፋሲል እና ሌሎች ቅርሶቹ? ላሊበላ እና ቅርሶቹ ጣና ላይ ያለው የእንቦጭ አረም ትኩረት ማነስ እና የገዳማት ሁነት፤ የአዕውፋተ ፍልሰት መቼ እና መቼ ይሆን በሳቸው ህሊና የታቀደው ጨርሶ ለመደመርመስ?
ሌላው በጥሞና ሊመረመር የሚገባው ጉዳይ ይህ ይመስለኛል የሱዳን 500 ኪሎሜትር ዘልቃ መግባትም እጮኛነቱ ከዚህ ጋር ይመስላል። አሳቻ ናቸውና። የሚገርመው የሠራዊታችን ትልቁ የጦር መሣሪያ "ልቡ" ነው ብለውናል። ወኔ ቢስ መሪ ያለው ሠራዊት ልቡ ይሰለባል።
እንደ አገር አርቲፊሻል አረባዊ ትውፊትን ልቅና ሰጥቶ ፒኮክን አንግሦ እፍግብ የሚያደርጋቸው የፓርክ ውሎ፤ የደብረዳሞ፤ የአክሱም፤ የዓድዋ፤ የማይጨው፤ የጉንዳ ጉዳይ አጅንዳቸው አይደለም። እሳቸው የሚያስቧት ኢትዮጵያ አርቲፌሻል ፌካዊ ዕለታዊ የ21ኛው ምዕተ ዓመት በአብይ የተሠራች አርባዊ የእጅ ሥራ ውጤት እንድትሆን ነው።
ይህ መራራ ሃቅ ዛሬ አይታይሁም ነገ ነው የሚታያችሁ። ስለጦርነቱ ስሞግት ብዙ ወዳጆቼ ተከፍተውብኝ ስለነበር መራራ ስንብት አድርገናል። በምጽፋቸው ላይ ተጽዕኖ እዬፈጠሩ በጓዳ ሲያባትሉኝ በክብር መለያዬቱን ወደድኩኝ። አሁን ይገባቸዋል።
እሳቸው አንድ ቤተ - መጽሐፍት ሠራሁ ብለው ፕሮፖጋንዲስት ሆነው ሲደልቁ ግን ዘመናትን የሚያናግሩ ቅርስ እና ውርስ ወድመውም፤ ከኢትዮጵያዊነት ውጪም ሆነው ተገንጥለው ሆነ ተከትረው፤ ተከትረው ሆነ ተበጥርቀው፤ ተበጥርቀው ሆነ ተቀዳዳደው ማዬት ይናፍቃቸዋል። አያደረጉትም ነው ካለ አንዳች ባሊህ ባይ ... ለዚህ ነው አቶ ዮናስ ደስታ የተባረሩት።
አሁን „ለድመቷ በሬ አይታረደም“ ድውይ ፍልስፍና ከዚህ አንጻር ነው ሊታይ የሚገባው። ቀደም ባለው ጊዜም „ጸጉረ ልውጥ“ ከዚህ ጋር ሊታይ ይገባም። ጅሎቹ ሰሜነኞች ዛሬም በአፈሙዝ ሊዳኙ እያኮበኮቡ ይገኛሉ። የሚገርመኝ ትርፍ ነገሩ ነው።
ስሜን ኢትዮጵያ ተወደደም ተጠላም የኢትዮጵያንዚም የደም ቧንቧ ነው። ለነገሩ ልበ ቢሶቹ ስሜነኞችን እያቧከሱ እሳቸው እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ታጥበው ቁጭ ብለዋል። ስሜነኞች ስል ትግራይ፤ አፍራ፤ እና የአማራን ክልልን ሙሉውን ያካትታል።
በጌምድር የሚለው ሥም በሌለበት ለሳቸው የዕብለት ሸማ ደግሞ በጌምድር ይባላል። ዕውነቱን አይደፍሩም። አማራ ክልል ማለት ተስኗቸው ጎጃም ጎንደር እያሉ ሲያምሱት ይገኛሉ። ጎጥ ላይ እንዲወረድ። ግን ማህል ላይ ዘንዶ ይለቃሉ።
„ወልቃይት አንችን ብረሳሽ ቀኜ ትርሳሽ“ ግሎባል ነው። ለነገሩ ሲያሹት ሲያፍተለትሉት ባጅተው ይህችን ታህል መተንፈሳቸውም ጥሩ ነው። በተጨማሪም አማራ አለ ብለው ማመናቸውን ሰሞናቱ እንደ አንድ ባጀት ቋጥረው ይዘው ለሰሞናቱ የትርክት ሰሌዳ ጠመኔያቸው ሆኖ አይቻለሁኝ። ተመስገን ነው።
ምን ጊዜም የአማራ ልጅ „አብይን ያመነ ጉም የዘገነ“ መሆኑን ዶግማው ሊሆን ይገባል። ከማህበረ ኦነግ የምህረት መሰላል አይሰበው። ይልቅ ሳይዘናጋ ወይንም ሳይንጠራራ በመክሊቱ ልክ ሆኖ ሁሉንም በማስተዋል ሊመረምረው ይገባል። ለራሱ ዘቡ ራሱ መሆኑንም!
• ቀደም ባለው ጊዜ።
ኦሮማራ ዒላማው ስሜን ፖለቲካ መበተን ነበር። ለዚህም አማራ እና ትግራይን ማዋጋት። አባ አዋጉ ይህን ሞክረው ሳይሳካ ሲቀር ነው ከትግራይ ጋር ጦርነት የገጠሙት። ማን ያስነሳው ማን። እሱም እራሱን ያቻለ የበሰለ ዕድምታ አለውና።
ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊት ብዙ ጽፌበታለሁኝ። ለገዳ ወራራ በገብር እና በአልገብርም እንደሆነም አበክሬ ገልጫለሁኝ። በትናንቱ ውሎ ይህን ነገረውናል። „ብልጽግና“ ቢሆኑ ይህ አይሆንም ነበር ብለዋል። አያችሁ እሳቸው ለሞገዳዊ የሽብር ፕሮጀክታቸው ቅደምተከተል አላቸው። ሰውረው የያዙት። ተልዕኳቸው ሲሳካ ደግሞ አያገባኝ በሉ እንደ ፍጥርጥራችሁ ብለው ትተው ወጥተዋል። አጋግመው።
የሚገርመው በመሸንፍ ወስጥ ያለ ማሸነፍ፤ በማሸንፍ ውስጥ ያለ መሸነፍ ሁለቱንም በጥምረት አይቻለሁኝ። መሸነፍ ሜካፕ አያስፈልገውም። ማሸንፍም ሜካፕ አያስፈልገውም። አይደለም ዛሬ በመካከለኛው ዘመንም መሸነፍም መሸነፍም ዘጋቢ አጥቶ አያውቁም እና። መሸንፍን ላለመቀበል መግደርደር መላላጥ ነው። ተፈቅዶ የሆነ ነገር የለምና።
የአማራር ውድቀት መሠረቱ ቅምጥ ፍላጎት ይዞ መንቀሳቀስ ነው። ኢትዮጵያ ታሸንፍለች ለማለት በዕውነት ቋት ውስጥ ሆኖ እንጂ በዚህ መልክ አይደለም። በሸፍጥ፤ በሴራ፤ በፉክክር በእልህ እና በማን አለብኝነትም አይደለም። በኮንፊዩዝድን እና በኮንቢንስም ድንብስ ቲወሪም አይደለም። ኢትዮጵያ አጋድመው እያረዷት ስለመሆኑ እናስተውላለን። ከጠቀማቸው።
17ሺህ ልጅህን በትነህ፤ ለአንተ ያደሩ ነፍሶችን ጥለህ ፈርጥጠህ፤ አንተን አምነው የሄዱ የመንግሥት ሠራተኞችን፤ እነዛ እንቦቅቅላ ሸበላ እና ሳተና ተማሪዎችን አላውቃችሁም ብለህ ከወር በፊት ፕሮሰሱ ተጀምሮ ነበር መቦጫረቅ ነው። መጫደርም።
በሲቢሉም፤ በሚሊተሪውም፤ በታሪክም፤ በትውፊትም፤ በፖለቲካም ሁሉን የነሳው መሪ ኢትዮጵያ እንዲህ አጋጥሟት አያውቅም። አጤ ልብነድንግል በብዙ ነገር ይታማሉ። ግን ከዶር አብይ አህመድ ጋር ማነጻጻር አልችልም። በፖለቲካ ስል ግር እንዳይላችሁ „ብልጽግና“ አንድ አባል የለውም። የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። አልተጸነሰም። ሞጋች ካለ ይምጣ እና ይሞግተኝ አለሁለት።
ከህዋህት መራሹ ኢህዴግ የተወረጀውን ውራጅ የትውስት አባል ተሸክሞ ነው እሚፏልለው። ዕድሜ ይንሳው እና በገዳ የምርጫ ቦርድ ቀዳዳ ዕወቅና አማካኝነት። በህወሃት ማንፌስቱ በተዘጋጀው ህገ - መንግሥት፤ ሰነድ መዋቅር፤ አስተዳደር ነው የሚዘባበነነው ሁሉም።
አንዲት የፓርቲ አደረጃጀት መርህን አያሟላም የገዳ ሞጋሳ „ብልጽግና“ ለዚህ ነው በዬሄደበት ወድቀት ቁርስ፤ ውርዴት ምሳው፤ ተቃላይነት ራቱ የሆነው። ዲስፕሊን የለውም። ምክንያቱም አንርኪዝም ነው የፈጠረውና።
በትናንቱ የፓርላማ ውሎ „ዓለምን አፍ ያዘጋ፤ ያስደመመ ምርጫ?“ መሳቅ ብቻ አይበቃውም። ቁስ ለማሟላት አቅም የሌለው፤ ምርጫ የቁጥር ጉዳይ ነው፤ የ7 ወይንም የ8 እዬተባለ በግምት መደዴ ሲዳክር አዲስ አበባ ላይ አንኳን የተሟላ የምርጫ ሂደት ለመከወን ያልቻለ፤ ምርጫ ተጀምሮ ቁስ በኢልኮፍትር ያጓጓዝ፤ በቀጣይ ቀናቶች ምርጫ ሲካሄድ የነበረበት፤ ሦስት ሙሉ ክልሎች፤ 6 ኮማንድ ፖስቶች ምርጫ ያልተከናወነበት ዝርክርክ ብቻ ሳይሆን ዝልግል ሁነት የታዬተበት አብጋኝ ሂደት ነው ያዬሁት እኔ።
ትግራይ ምረጫ ቦርድ ፈጥራ በአጭር ጊዜ በታቀደው ሁኔታ ከውናለች። ይህ አሊ አይባልም። ለዛውም ሚዲያ ታግዶ። ይህ ስለቃጠለ፤ በቅናት ስላደበን አንድ ሳምንት ሳይሞላ ስለምርጫ ተደሰኮረ ሲዳከር ተባጀ፤ ከምርጫ ማግሥት ትግራይን ለቀን ወጣን ተባለ። ይህን እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ፍልስፍና የፌንጣ ፖለቲካ እለዋለሁኝ።
• የፌንጣ ፖለቲካ።
"ከጸጉረ ልውጥ ከቀን ጅቦች ከውስኪ ከፌስታል ፖለቲካ፤ ከወራጅ የለም ፖለቲካ በሰበሩን ቦታ፤ ከሰበሩን ፖለቲካ የቁማር ፖለቲካ፤ ከቁማር ፖለቲካ እንበላለን እንሰብራልን እንቀረጥፋለን ፖለቲካ፤ ከዛ ተወጥቶ የሻሸመኔወዝዋይ ጭፍጫፋ እና ውድምት፤ ከዛ ወደ ግሊንሶ፤ ከግሊንሶ የትግራይ ጦርነት መራራው መከራ በማይካድራም፤ ከትግራይ ቤንሻንጉል፤ ከቤንሻንጉል ወደ አጣዬ፤ ካራኮሬ ውድመት፤ ከዚህ ፍርሰት ወደ ምርጫ ፖለቲካ ከምርጫ ፖለቲካ የተናጠል ስምምነት፤ ከዛ የበሻሻ ፖለቲካ፤ ከበሻሻ ፖለቲካ ወደ ጊዜያዊ ሽግግር መንግሥት በኦሮምያ ከዛ ወደ ለድምት በሬ አለመታረድ።" መላ ቅጥ የለሽ ዝብርቅርቅ ....
ከዚህች ላይ በተናጠል ስምንነት የለም። መስማማት፤ መደራራደር ተስማሚ አካል ሰብ ተቋም ሲኖር ነው። ያ ሁሉ ፍዝ የመንግሥት ጋዜጠኛ በለው የእንቅልፎሽ ሸንጎው አንድ ነፍስ ሊሞግት ቀርቶ ቀና ብሎ ለማዬት አይደፍርም። ውሸት አገር ገዝቶ እንዲህ ሲወራኝ ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል ድንኳን ጥሎ ሃዘን ይቀመጥ?
ፌንጣን እሰቡት። የኦነግ የፖለቲካ አመራር ሁሉም አይቀርበትም። ድንገቴው፤ ሱናሜው፤ ትዕቢቱ፤ ለህግ አለመገዛቱ፤ ውሸቱም፤ ልቅነቱ፤ አናሪኪዝምነቱ፤ ትዕቢቱ፤ ጥጋቡ ዝላዩ ከላይ እስከታች በኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች የጸጥታ አካሉ ተደራጀ። እናም ውጤቱ ታዬ። ፉከራው የሳሙና አረፋ ሆኖ አረፈው።
አንድ ክፍለ አገር ያሰማራው ህዝባዊ ኃይልን ግን መመከት አልተቻለም። መዝለል እና መፍረጥ። ድል ሲሆን ሚዲያ ላይ እነሱ ያጥለቀልቁታል። ሲሸነፉ ደግሞ አማራ ወጥቶ ዲስኩር እንዲያሰማ ያደርጋሉ። ጨዋታው ይህ ነው።
ሌላው ልብአልቦሹ ህወሃት አሁንም እዬፎገላ ነው። ተከዜን እሻገራለሁ እያለ። እዛ አማራ መክቶ ከመለሰ ሚዲያ ላይ ተኮልኩለው ይመጣሉ በመደዳ ማህበረ ኦነግ። የመቀሌው ጊዜያዊ ድል ላይ የተገኜው የአማራ ማስ ሚዲያ አልነበረም። የተገኜው የኦርምያው OBN ነበር። ራያ ላይም እንዲሁ። አፍሪካዊ ሆኖ የተደራጀው። በዚህ ቀልድ ውስጥ ነፍሳቸውን የሳቱ የአማራ ሊቃናት ጉዝጓዝ ይሆናሉ። የት ላይ አንደ ተቆመ ከልባቸው ሆነው መመርምር አይችሉም። ተጋሩም እንዲሁ።
ለተጋሩ ትናንትም ዛሬም አማራ እንጂ የኦነግ ኃይል አይደለም የከተከተው። የከዳው ኦነጋዊው ኦህዴድ ነው። የተቀጠቀጠው ሥነ - ልቦና ግንባታው በአነሰ ግምት 10 ዓመት ይፈጃል። አሸንፍን የሚሉት ከማህበረ ኦነግ በተገኜ መረጃ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው የነጩ ቤተ - መንግሥት ቤተኞች እና የግሎባል ቁልፍ ቦታ ነፍሶች ነው።
እንጂ ህወሃት ከሥሩ እንዲነቅል በተሠራበት ጊዜ ሁሉንም መመከት ተችሎ ነበር። ሥልጣን ላይ እያለ። ሌላው እነሱ ጫካ ላይ ሆነው ዲያስፖራው ስልታዊ ነበር ህወሃት ወደ ስልጣን ይመለስ ብለው አልታገሉም።
በሰባዕዊ መብት ረጋጣ ላይ ነበር ያተኮሩት። ብዙ በሰባዕዊነት ለምንተጋ ሰብዕናወች ቅርባችን ስለነበር አጀንዳው አግዘናል። አነሱ ግን ውላቸውን አይረሱም። በሠራዊቱ ውስጥ ባሉ የኦነግ መኮንነኖች ባገኙት መረጃ መሪነት ለድል ሲበቁ እንደተለመደው በክህደት ጎዳናቸው ቀጥለዋል። ዳኛ ግን አለ። የዕውነት አምላክ ፈጣሪ። ወልቃይትን ጠገዴን አያውቁትም። የሚያውቁት ለመኖር በጋብቻ፤ ለሥራ ሲሄዱ ብቻ ነው።
ይህን በስማ በለው ሳይሆን ቤተሰቦቼ ህይወቱን የሚኖሩበትም ስለሆነ ነው። ስክን ያለ ሥራ ሚዲያ ላይ እምሠራው ኢትዮጵያዊነት እንዳይጎዳብኝ ስለመሳሳ፤ የትውልዱ ብክነት ስለሚያሳስበኝ እንጂ በራሴ ጉዳይ ፕሮፖጋንዲስት አስፈልጎኝ አልነበረም።፡
ይህ በእኔ ዕድሜ እንኳን የነበረ ሃቅ ነው ወልቃይት ጠገዴ የወገራ እና የስሜን አውራጃ ናቸው። ዕውነቱ ቢነገር ጎንደር ለትግራይ ጉሮሮው ነው። እንደምን ብለው ደካክመው በወጋራ በር እንደሚመመጡ በእኛ ዕድሜ የምናዬው ሁኔታ ነበር። የራስ አካል አድርጎ አቅፎ እና ደግፎ አብሮነትን ማብራት የጎንደር ደሙ ነው። ጎንደር ለተጋሩ ህይወቱ ነው። ፍቅሩ ነው። ትዳር ጎጆው ነው። መከታው ነው። ሌላው ሲነሳ የሰማሁት ስለ ቅዱስ ያሬድ ነው። እሱን አሳደው እኮ አክብሮ የተቀበለው የጎንደር ህዝብ ነው። አጤ በካፋን አባታቸው ሲያልፉ ጎጃም ድረስ ሄዶ እናታቸውን እቴጌ ማርማዊትን ጨምሮ አምጥቶ ያከበረ ብልህ ህዝብ ነው ጎንደር።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሳደርግ ውለታ ቢሱ ህወሃት የቀደመው ሳይጸጽተው ደግሞ ለማስገበር ቅራቅርን ተዳፈረ። እናም ምሱን አገኜ። ወደፊትም የእውነት አምላክ ስላለ ፉከራውን ቀረርቶውን ጥሶ የሚወጣው ዕውነት ብቻ ይሆናል። መዝረፍ በፈጣሪ ዘንድም ጸያፍ ነውና። ኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኝ የተጋሩ ሰወችም ከሃቅ ጋር ሊገናኙ ይገባል። ዕውነት የሆነውን አምክንዮ ከሚሸሹት። ከሚፈሩትም። በዝህች ሃቅ ትውር ሲሉ አላያቸውም። ከአቶ ገብረ ምድህን አርያ በስተቀር።
• ማንነት ቆላ እና ደጋ የለውም።
በዚህ አጋጣሚ ፖለቲካኛው አቶ ያሬድ ጥበቡ ደጋው ለአማራ፤ ቆላው ለትግራይ ይሰጥ የሚል የመፍትሄ ፕሮፖዛል በርዮት ሚዲያ አቅርበው ሰምቻለሁኝ። በሙግት ነው እሳቸውን እማውቀው። ስሞግታቸው ግን አክብሬ ነው። እናም አሁንም ቀደምቷ ሞጋቻቻው በዚህ አጋጣሚ እምትለው ነገር አላት። ካደመጡኝ።
የተከበሩ ማንነት ቆላ እና ደጋ የለውም። ፔሬድ! ማንነት በገብያ ህግ አይተዳደርም። ማንነት በድርድር ሥርዓትም አይዳኝም። ማንነት ሸቀጥ አይደለም። በቦንዳ ወይንም በሜትር የሚቸበቸብ። ማንነት መጋረጃም ክልልም የለውም። ግሎባል ነው።
እኔ ሲዊዝ ነው የምኖረው። ደጋ በሚጫነው ወይና ደጋው ቪንተርቱር ግን አማራነቴ አይገደብም። ትናንትም አማራ፤ ዛሬም አማራ ነኝ። ትናንትም ሴት ዛሬም ሴት ነኝ። ትናንትም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጅ ዛሬም እንዲሁ። ትናንትም ኢትዮጵያዊ ዛሬም ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ማንነት ቦታ አይወስነውም። ከማንም ችሮታ የሚለምንም አይደለም።
ቢያንስ የማይካድራን ሰማዕታት እንደምን ዘለሏቸው አቶ ያሬድ ጥበቡ? ቆላውን ለህወሃት መስጠት ማለት ግፍ ፈጽሙ ይሆን? ብዙ ጊዜ በርህርህና መስክ አስባቸው ነበር። ይህ ጭካኔያቸው ግን አንገሸገሸኝ። እዘናለሁ አቶ ያሬድ በጣም። ያሳዘነኝ የሞገታቸው አለመኖሩ ጭምር ነው።
የማከብረወት አቶ ያሬድ ጥበቡ ደጋ እና ቆላ እያሉ ባይሸንሽኑን ጥሩ ነው። ያ ህዝብ ለርስወም ባለወልታወት ነው። ትናንትን አይርገጡት። ቆላውም ደጋውም አማራ ነው። አብሮ ለመኖር ግን ከልካይ የለባቸውም ተጋሩወች። እነሱም ኢትዮጵያዊ፤ አማራም ኢትዮጵያዊ።
በሌላ በኩል አቶ ያሬድ ያነሱት ነገር በርህርህና ይመስለኛል አሁን የሃሳብ ፖለቲካ ሳይሆን የዞግ ስለሆነ ለሰራዊቱ የተሰጠው ስልጠናም አጭር ስለሆነ በጠገዴ፤ በወልቃይት ህዝብ ላይ ጭካኔ እንዳይፈጸም ተማጽነዋል። ህም።
እነሱ የያዙት መሳሪያን ቃታ መክፈት እና መዝጋት አማራ ሳይችልበት ይቀር ይሆን? እኔ እራሴ አልሞ ተኮሽም ነኝ። ጎንደር ሱዳን ግብጽ ጠላት አገር እንደሆኑ እዬተነገረን ነው ያደግነው። ስለዚህ አነሰም በዛም መቀነቷን የፈታች ሴት፤ ቀበቶውን የፈታ አማራ አይኖርም። ጦርነቱን ከሞገቱ ሰብዕናዎች አንዷ ነኝ አያስፈልግነም በሚል። ግን ከዚህ ከተደረሰ ወኔን ሱቅበደረቴ ለመሸመት ገብያ አይወጣም - አማራ።
ስለዚህ ወኔ ቅኝት ትግራይ መሄድ አያስፈልገንም። አማራ የወኔ ተጠማኝም አይደለም። እንተዋወቃለን። አንድ ህዝብም ነው። ሰርገኛ ማለት አልችልም በትግራይ እና በጎንደር ያለውን ሁኔታ። ከዛም በላይ ነውና። ስለዚህ እነሱ ያላቸው ጥንካሬ እኛም አለን። እነሱ ያላቸው ድክመትም በእኛም ውስጥ ይኖራል። ባይሆን እመርጣለሁኝ። ጦርነት የበቀል ምርት ነውና። የጥላቻ ውቅያኖስ ነውና። ከሆነ ግን ፈጣሪ ከዕውነት ጎን ይቆማል።
ከሆነ ደግሞ ሙሉው ትግራይ ቢሰለፍ ያን የሚመከት ኃይል አማራ አያጣም። ዕውነቱ ይህ ነው። ከጨከኑ እስከ አሁን የታገሰው አማራ ጭካኔ ማድረጉ አይቀሬ ይሆናል። ይህ ይልቅ ያስፈራኛል። ጭካኔ ናፋቂ አይደለሁምና።
ጠቅላዩ ደግሞ ከ4ኪሎ ተራራቸው ሆነው የማን ደም ፈሰሰ እያሉ ያጫርሳሉ። በነገራችን ላይ ዶር አብይ አህመድ አሊ የዓለም የህዝብ መቀነስ ፕሮጀክት አባልም የሆኑ ይመስሉኛል። እንዲቀነስ የሚፈልጉትም ሙለው ስሜን ኢትዮጵያ እና በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ደሃወችን ነው። እሳቸው ደሃ ጠል ናቸውና። ፕሮጀክታቸው ለቱጃሮች ብቻ ነው።
እኔ ይልቅ ከአቶ ያሬድ ጥበቡ ከእሳቸው ሌላ እማስበው በመላ ኢትዮጵያ ባሉ ዩንቨርስቲዎች ያሉ የተጋሩ ልጆች ምን ይሆኑ እያልኩኝ ነው። በመላ ኢትዮጵያ ተበትነው የሚኖሩት ተጋሩ ምን ይገጥማቸው ይሆን እያልኩኝ ነው እምብሰለሰለው።
ታስታውሱ ከሆነ አቶ ያሬድ ጥበቡ ከአማሪካው ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ሁለት ተከታታይ ክፍለ ጊዜ ቆይታ "የእርስበርስ ጦርነት አያሰጋኝም" ሲሉ እርስወ ዕድለኛ ነውት እኔ ግን ዕንቅልፍ የለኝም ብዬ የዛሬ 4/5 ዓመት በደጉ ሳተናው ድህረ ገጽ ሞግቻቸው ነበር። ይሕው እያዬት ነው። ዓለምን ያናጋ መከራ … ዛሬስ ምን ሊሉት ይሆን ያን ግድፈታቸውን? እና የፖለቲካ ተንታኝነታቸው ብቻ ሳይሆን ተንባይነታቸውን?
የሆነ ሆኖ ህወሃት የፈጸመው ግፉ ሰማይም ምድርም አይችለውም። የትናንቱ ግፍ በደል በዓለም አደባባይ ለፍትህ ስላልቀረበ ነው እነሱ በ7 ወር የደረሰባቸው በደል እና ግፍ ጎልቶ የሚቀርበው። የፕሬዚዳንት ጆባይደን ወደ ስልጣን መምጣት አግዟቸው አንድ ትልቅ ሰው አላቸው የጆባይደን ካቢኔ ውስጥ። ያ ነው ሚስጢሩ።
እኛም እራሳችን በሰባዕዊ መብት ረገጣው በውጭ አገር የ ኤርትራ ወታደር በመፈጸሙ ውርዴት በመሆኑ ሞግተናል። ሉዓላዊነታችን ነፍሳችን ትንፋሻችን ነውና። ሱዳን በጎንደር ላይ ለፈጸመቸው ወራራ ግን የእነሱን ፈንድሻ አይተናል፤ አማራ በዬትኛውም ሁኔታ ሲጨፈጨፈም አስተውለናል ፈንጠዝያውን፤ ተዋህዶ ስትዋረድ እንኳን ከጎኗ ለመቆም አቅሙም አቅሉም የለም።
የሆነ ሆኖ በአማራ ህዝብ የተፈጸመው ጭካኔ ለዓለም ፍርድ ቢቀርብ የሚተርፍ አንድም ነፍስ አይኖርም። ሚዲያ ላይ ጸያፍ ነገሮችን ለሚጽፉ ሁሉ ቅጣታውን እያገኙ መሆኑን አድምጫለሁኝ በርዮት ሚዲያ። ይህ መናበብ፤ ይህ ጥንካሬ ይደነቃል። አማራ ይህን ልስራ ቢል የሚተርፍ ይኖር ይሆን የህወሃት እና የኦነግ ሰወችን?
አማራ ንጹህ፤ ቻይ ድንግል ህዝብ ነው። ነገር ግን በልኩ ዕውቅና ያልተሰጠው ባተሌ። ግን ፈጣሪ አይረሳውም። መልካምነት የባለቤቱ ነውና። ጥላቻን ጥላቻ አያክመውም። ከመልካምነትም ኪሳራ የለም። አሁንም ወደፊትም መልካምነት ይለማ ዘንድ በዛ እንተጋለን።
የስሜን ኢትዮጵያ እናቶች ተበድለዋል።
ዘመን ከዘመን አማጽያኑን ያስጠጋሉ። መንግሥት ሲሄድ አማጽያን አስጠጋችሁ ተብለው በ በመንግሥት ይደበደባሉ። መንግሥቱ ሲሄድ ደግሞ ሸማቂን መንግሥትን ደገፋችሁ ተብለው ይቀጠቀጣሉ። አሁን ሰባዕዊነት እያሉ ሲጮሑ የነበሩት ህወሃት „ብልጽግናን“ ደገፋችሁ ብሎ ተጋሩን ሲጨፈጭፍ ድምጻቸው አይሰማም፤ በተጋሩ ጉዳይ ዓለም ሲመክር ያን ይዘግባሉ፤ በወልቃይት ጉዳይ ዓለም ሲመከር ያን ይዘሉታል። ተጋሩ በሚስጢር መገንጠልን ሲወያይበት ያን እንኳን ሽፋን አይሰጡትም። ኢትዮጵያኒዝም ፍዳውን በዚህ መልክ ያያል።
ድምጽ አልባወቹ የስሜን እናቶችም እንዲሁ አሳራቸውን ያያሉ። ለጥቂት አክተሮች ሁልጊዜ መንደድ። የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የራያ ተጋድሎ የህልውና ተጋድሎ ነው። ካልጎሼ አይጠራም። ሲከር ይበጠሳል፤ ሲሞላም ይፈሳል። ፍቅር ነው ከባዱ ጥላቻ ምን ሲያደክም? እናስተውል።
ጥጋቡ አላስችል ብሎ አቶ አባይ ወልዱ ጎንደር ድረስ ሄደው ጀግና ኮነሬል ደመቀ ዘውዴን እስከ ቤተሰባቸው ለመደመምሰስ ሲዳፈሩ እራሳቸውን ነቀሉ። አሁንም ነገረ ቅራቅር ነው ይህን ሁሉ ማት ያመጣው። ጥጋብ በሰማይም በምድርም መርዝ ነው። እራስን የሚያጠፋ ማላታይን። ፉከራ ሳይሆን ከዕውነት ጋር መታረቅ።
ህወሃት ለድል መብቃቱ ደስ ያሰኛቸው ነፍሶችም አበከረው በአስተውሎት ይራመድ ዘንድ ህወሃትን መመከር ያስፈልጋቸዋል። በሦስት ነፍሶች ነው የሉላዊ ድጋፍ የተገኜው። እነኝህ ነፍሶች ቢያሸልቡ ሁሉም ያከትማል። ዕውነት የሆነ ነገር እጬጌው ሂደት እዬነገረን ነው። ማድመጥ ያስፈልጋል።
አሁን ሲያሸንፍ ጀግና፤ ሲሸነፍ የሰባዕዊ መብት ረገጣ ጊዜው ያከተመ ይመሰለኛል። ያከተመ ስል በሰዋዊነት፤ በተፈጥራዊነት ስንሰራ ለነበርን ሰብዕናወች ሁኔታዎች ዕውነትን እንደግፍ ዘንድ ግድ ይለናል እና። ትናንትም የወገንኩት ዕውነትን፤ መርህን ነው። ወደፊትም።
• አሁናዊነት።
„ጁንታ“ የተባለ ድርጅት አሁን ቲፒኤልኤፍ ሲሉ በራሳቸው አንደበት በዶር አብይ አህመድ አዳመጥኩኝ። እኔ አንድም ቀን ተጠቅሜበት አላውቅም። እሳቸውን የሞረደ፤ የሳለ፤ የፈጠረ ድርጅት ነው ይህ ድርጅት አንጋፋም ነው።
ቲፒኤልኤፍ ከአድዋ ሥርዕወ መንግሥት ወርዶ ወደ ጫካ ሲገባ በጎበዝ አለቃነት ነው ጦርነቱን የመራው። ድል አድርጎ ሲገባ ደግሞ ወደ ነበረበት መንበሩ ተመለሰ። እሱም ህግ ጥሶ ተመርጧል፤ እሳቸውም ህግ ጥሰው የንግሥና ጊዜያቸውን አራዝመው ምርጫ 3/4 በማይሆን የአገሪቱ ህዝብ ምርጫ አካሂደው ተመርጠዋል። እኩል ለኩል ስለሆኑ ነው ጦርነቱን ፈጸምኩኝ ብለውናል። ይህ ነው ሚስጢሩ።
ጠቅላዩ ተቃጥለው ነበር ኮረና ሳይበግራቸው ህወሃቶች ምርጫ አካሂደው በዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ መኮፈሳቸው። ህግ ጥሰቱን በሚመለከት ሁለቱም ያው ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ናቸው። ህወሃት ሆነ ኦህዴድ።
• እኔ።
እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ተሸናፊ መሪ እንዲህ ልቡን ሞልቶ፤ ከረባት ለብሶ፤ ቂቅ ብሎ ሪፎርም አደረኩት ባለው፤ የጀግና ውሎ ብሎ ሲደነፋ ውሎ ያደረ ነፍስ እንደዛ ተኮፍሶ በበኽርነት ሳያነሳ መሸነፉን፤ በኢኮኖሚ ጉዳይ ሻታ ሲዘዋውር ቆይቶ ሽንፈቱን ይሉኝታን በቦንብ ደብድቦ ዲስኩር ማሰማት ውርዴቱ እና ውርዴው ለዛ ለለሽ ይበሉም ፓርላምም ነው።
በሽንፈት የሥራ ዘመን መጠናቀቅ ለዛ እንቅልፋም ፓርላማ ዕዳ ነው። የታሪክ፤ የትውፊት፤ የአደራ። ህወሃት ኤርትራን አስገነጠለ „ብልጽግና“ ትግራይን አልቦሽ መንግሥት መሰረትኩኝ ይለናል። ቀጣዩ ዕቅድ ተነግሮናል። ኢንባሲዎች እንደሚቀነሱ፤ ለካቢኔ ቱባዎች ሹፌር እንዳማይቀጠርላቸውም። ሌላም ፍርሰት ይኖራል። ገዳ ትውፊቱ ይኽው ነው።
የሆነ ሆኖ በውጭ አገር ወታደር ታግዘህ፤ ተደገፍህ ፎክረህ አሁን ያ ሲሟሽሽ ልዕልና ክብር በዚህ ልክ ሲፈጠፈጥ ማዬት ስለምን የትውልዱ አባል ሆንኩኝ ያሰኛል? የሚገርመኝ ደግሞ የህወሃት ድንፋት ነው። ያው ሠራዊት ነው። አለቃ ነው የተቀዬረው። ሽንፈቱ የራስም ነው።
40 ዓመት ሙሉ አንድ ብቁ ሰው መሪ ሊሆን የሚችል ሰብዕና እንዳልገነቡ እራሳቸው ሊያፍሩበት ሲገባ ድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ይሸማቀቁ ዘንድ የሠሩት ተግባር እጅግ አሳፋሪ ነው። ከተጋሩ መኮንን መሪነት፤ ወደ ኦነጋዊ መኮነን መሪነት ነው የተዛወረው ሠራዊቱ።
ትናንተ ኤርትራን በባድም ያረገፈ፤ ዛሬ ደግሞ ከኤርትራ ተመጽውቶም ያን ለድል ያለበቃ የመከነ ጉድ። ለዚህ ነበር እኔ አትራፊ ጦርነት አይደለም። አትጀምሩት ስል የነበረው። ራያ፤ ወልቃይት፤ ጠገዴ ግን ነፃነታቸውን አግኝተዋል። ለነፃነት ደግሞ ሁሉም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው አሁን ላይ። ህወሃት ጥጋቡ አላስችለው ካለ። የያዘውን ይዞ ቢቀመጥ ነው የሚበጀው። ማት ከሰማይ ሊወርድም ይችላል። እሱም አስፈሪ ነው። የህዝቡን ሰላም አወኩት ሁለቱም።
በጦርነት አሸናፊም ተሸናፊም የለም። አተረፍን ከተባለ በቀል እና ቂም ነው ብዬ ስሞግት ነበር። እርግጥ ነው የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የአዳርቃይ፤ የማይመጸምሪ፤ የራያ ወገኖቼ ለ7 ወርም ቢሆን መተንፈስ መቻላቸው ታላቅ እፎይታ ነው። ነገ ሲታሰብ ግን ይጎመዝዛል። በጣም። ብዙ የደም ጅረት ይኖራል። ተናግሬዬም ነበር ሰላም ለማግኘት ጎንደር እንደማይችል። „ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል“ እንዲሉ።
ደጋግሜ እንደምገልጸው ህወሃትን አግንኖም፤ አንኳሶም ማዬት አይገባም። ከሁሉ የሚከፋው ጦርነቱ የእርስበ እርስም ነው። ድል ሚስጢር ነው። ሚስጢር ከወጣ በአንድ ሰው ጦርነቱ ሊያበቃ ይቻላል። ዶር አብይ አህመድን አምኖ ጦርነት ውስጥ መግባት መርጉ ጉዳይ ነበር፤ ለወደፊትም። ቂመኛም። በቀለኛም ናቸውና። የሆነውም ይህው ነው። ወኔም የላቸውም። አንድ ቀን ድንግል የሆነ ወኔ አይቸባቸው አላውቅም።
ያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ምርኮኛ የትግራይም ነው። ውርዴቱም የጋራ ነው። የሚያስፎክር አይደለም። ብልሹነቱ የጋራ ነው። ለማኝ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት ዛሬን ሲይ ምን ይል ይሆን?
ሌላ ጀኒራል ካሳዬ ጨመዳ እና ጄ ጻድቃን በማነጻጻር አንድ ዲስኩርም ሰምቻለሁኝ። ዶር አብይ አህመድ ለጄ ካሳዬ ጨመዳ ዕድሉን አልሰጧቸውም። በሰጣቸው እና በተለካኩ። አይደለም ለሳቸው ጄ / አሳምነው ጽጌ አስቀድመው የተወገዱበት ሚስጢር ለዚህም ነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲያሸንፍ ዶር አብይ አህመድ አይፍቅዱም።
ኢትዮጵያ ምራቅ ላይ ብቻ ነው ያለችው። እሳቸው የሚተጉት የአብይዝምን ኦሮሞይዜሽን ለድል ማብቃት ነው። ይህ የምርኮ ጉዞ ሲዳሰስ በዶር አብይ አህመድ ጀርባ ያሉት አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው። እሳቸው ምርኮኛ የነበሩ ናቸው።
ሌላ ሁለቱም መኮንኖቻቸው ጄ / ብርሃኑ ጁላ ጄ/ ባጫ ደበሌም ምርኮኛ ናቸው። እሳቸውም ዶር አብይ አህመድ የራዲዮ ኦፕሬተር ናቸው። በምን አቅም ጦርነት ማሸነፍ ይቻላል? ለዛውም የእርስበርስ። አማካሪወቾቻቸው ግንቦት 7 ናቸው። በ200 ሰው ኢህዴግን እናሸንፋለን ብለው ሞገድ ላይ ሲፎክሩ የነበሩ። ባዶ እጃቸውን ገብተውም ወና የቀሩ። ማህበረ ሌንጮም አንዲት መንደር ተቆጣጥሮ የማያውቅ ከንቱ ድርጅት ነው።
• ወጠ፤
የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ ሲነሳ አቶ አስራት አብርኃም የጻፉት ነገር ነበር። በ2008 ማለት ነው። የገብያ ውሎ ነው ብለው። እዛው የሚቀር፤ የአማራ ሊቃናት እንኳን የማያዳምጡት ነው በማለት አቃለው፤ አሳንሰው ተሳልቀው አቅረቡት።
እኔ ደግሞ ሞግቻቸው ነበር። ጹሑፉን ፈልጌ እለጥፈዋለሁኝ። ማንነት ሸቀጥ አይደለም በገብያ ህግ አይገዛም! በእኔ ውስጥ ያለውን ቋያ አያውቁትም ብዬም ብዬ ከውስጤ ነበር የሞገትኳቸው። የወልቃይት እና የጠገዴን ጣዕም አውቀዋለሁና። የፍቅር ቤት ነው።
አሁን ነገረ ወልቃይትወጠገዴ የጸጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ሆነ። ዛሬ ላይ ምን ሊሉ እንደሚችሉ አቶ አስራት አብርሃን ባያቸው ደስ ይለኝ ነበር። የህወሃት መነሳትም፤ መውደቅም መሠረቱ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ነው።
መውረር፤ መስፋፋት፤ መዝረፍ አልበቃ ብሎ ያን ያህል ቀጥቅጦ፤ ጨፍልቆ፤ ድጦ አርዶ ግን ፋሺዝም ሆኖ አለመርካት። ፋሺዝምን በቃኝ ያለ ህዝብ እስከ ልጅልጅ ይህን ይፋለማል። ለዚህ ነው እኔ የምሠራው ለዛሬ አይደለም ከ20/30 ዓመትም ነው የምለው።
የአማራ ህዝብ መከራ በቁንጣ ቁንጢ ፖለቲካ አይቀረፍም። እእ። ይህ ሂደት እንደ ቅልጣን ለሚያደርገው የአማራ ሊቃናት እና ተቋም ቆራጥ መድህንኑ ይመስለኛል። ዲስፕሊኑን ለመሸከም ያስወስነዋል።
ይልቅ ገዳ ከዚህ መማር ይኖርበታል። የአማራ ህዝብ የቀደመ ርስቶችን ለማስመለስ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ከጀመረ ብዙ ነገር እንዳልነበር ይሆናል። ዓለም ህግ አላት። አማራ የስፔኖችን ጎዳና ከተከተለ ህልውናዊ መኖሩ በዓለም ህግጋት ይደነገግለታል። ስለዚህ አሁንም ለገዳ መሳፍንታት ጥሞና ያስፈልጋቸዋል ባይ ነኝ። ተክለፍልፈዋል። ጥጋቡም አላስችላቸው ብሏል።
አማራ ከተማን ማበጀት ስለሚችልበት ገዳ እዬተከታተተለ ቢያወድመውም መልሶ ይገነባዋል አማራ ርስቱን። አንድ ነገር ቢፈጠር አዲስ አበባን አውድሞ ገዳ እንደሚወጣ አሁን ካለው የዶር አብይ አህመድ አገላለጽ መረዳት ይቻላል።
ትግራይን ከበሻሻ ጋር አነጻጽረው የስበት ማዕከሏ መጠናቀቁን ነገረውናል። የነገሩን ነገ ደግሞ አዲስ አበባን ከማን ጋር ሊያስተካክሉ እንደሚችሉ አይታወቅም። ለነገሩ ቡችላቸው ኢሪሌባንት ከተማ እናደርጋታለን ብለው ነገረውናል።
የቲም እስክንድር ነጋ እስርም ለዚህ ፕሮጀክትል ልዕልና ነው። የሆነ ሆኖ እሳቸው ገዢ ከሆኑ ብቻ ነው አሁን አዲስዬም እምትቀጥለው። ምክንያቱም ማድህዬትም፤ ማውደም ፕሮጀክታቸው እንደሆነ የሰሞናቱ ተከታታይ ያልተገራው ንግግራቸው ይገልጽዋል። ቀደም ብዬም ጽፌበታለሁኝ። ነገረ አብይን ለመረዳት ስክንት ይጠይቃል።
• ወረተኝነት።
የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህምድ ትልቁ ባህሪያቸው ወረተኝነት ነው። በወረተኝነት ውስጥ ስልቹነትም አለ። ይህንንም ቀደም ብዬ የአሳቸው መሪ ባህሪያትን ስዘረዝር ጽፌወላሁኝ። ጦርነቱ ሰልችቷቸዋል። እና እንዲቆም ፈለጉ።
እንደ ሥርጉተ ሥላሴ መረጃ አሸልከው ሠራዊቱን ያስማረኩ እሳቸው ይሆናሉ የሚል ዕድምታ ነው ያለኝ። አላምናቸውም። ለምን ጥላችሁ ወጣችሁ ለሚለው ምክንያታዊ ጥያቄ ጉዝጓዝ ስለሚያስፈልጋቸው ነው ይህን ያደረጉት ብዬ አስባለሁኝ።
አሁንም ወደፊትም እሳቸውን አምናችሁ የሙጥኝ ብላችሁ የምትኖሩ ነፍሶች እባካችሁ እሰቡበት። ሰብሰብም በሉ። አንድ ቃል በሳቸው ውሎ አያድርም። ፈጽሞ። እሳቸው የማን ናቸው? የሚያውቅ ሰው የለም። ለዚህ ነው እኔ አሳቻ ያልኳቸው።
አይደለም ለእኛ ለውጭው አለም የበሰሉ ፖለቲከኞችም፤ ፈላስፎች፤ ሳይንቲስቶች፤ ኤክሰፐርቶች ሊፈቷቸው የማይችሉ ሰው ናቸው። ለዚህ ነው ድንግቴው ዱብዕዳ ሆኖ ሦስት ዓመት ሙሉ ዓለም ኢትዮጵያ ላይ ተቸንክራ የምትገኜው።
• እኛ ምን // እናድርግ።
(1) አንጉረፍ /// አናጎፍር።
(2) አንኩረፈረፍ /// አናኩርፍ።
(3) አንልዘዝ /// አንደንዝዝ።
(4) አንበልዝ /// አንፍዘዝ።
(5) አንደነቅ // አናሟሙቅ።
(6) አንሸብሸብ /// አንሟሽሽ
(7) ከዕለታዊነት ወጥተን ዘላቂነት ላይ እንሥራ!
(😎 ሰዋዊነት እና ተፈጥሯዊነት ይምራን።
(9) በማናቸውም ሁኔታ ከፈጣሪያችን ፈቃድ ጋር እንተሳሰር፤ የቃል ነን እና በቃላችን ውስጥ እንስከን።
ክወና።
• ፍትኃት ለማን?
ለተራጋጩ፤ ለብስጩው፤ ለገረጭራጫው የኢትዮጵያ ፖለቲካ።
• ፍትኃት ለምን?
ሰው ለመሆን!
• ፍትኃት ለማን?
ለሁላችንም።
• ፍትኃት ለመቼ?
ለትናንት፤ ለነገ፤ ለነገ ወዲያ፤ ለዚያም ወዲያ። ማግሥት አጀንዳችን ይሆን። ከላይ ከላይ እንፍላ። ብዙው ሰው ቤተሰብ ይመራል። ተመክሮው አለ። እኛም ለመምራት ክህሎቱ ይሁነኝ ይባል ነው ዕይታዬ። ከዚህ ጋር አትደንግጡ። አትረባበሹ። ፈጥኖ ከንፎ ከሚሾፍረው ረግቶ ሰክኖ የሚሾፍረው የሃሳብ አቅም ይበልጥ ባለድል ነው። ለዛውም ጤናው ተጠብቆ።
• ፍትኃት የት?
በያለንበት።
• ፍትኃት እንዴት?
በጥሞና።
• ፍትኃት በማን?
በፈጣሪ። ድንግልናን ይጠይቃል። በችኮላ - በጥድፊያ - በሩጫ ፍኃት የለም። አይገኝም። ፍትኃት ወርቅ ነው። ከፈሰሰ አይታፈሰም።
• መደምደሚያ
ደስታን በልክ ያዙት በትህትና። ሃዘንንም እንዲሁ በመጽናናት። ሁለቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ ናቸውና። ስለሆንም በልክ መሆን የፈጣሪን ምርቃት ጥበቃ ያገኛል። ኢትዮጵያን ስትረዷት ምጥን ትሆናላችሁ። ኢትዮጵያ ከብዳናለች። ልኳ መሆን አልተቻለነም። ሁሌ መፍረከረክ። የዲስኩር ምርኮኛ መሆን።
• በመንግሥት ጋዜጠኞች የግብረ ሰላም ምሽት፤ በእንቅልፋሙ ፓርላማ ውሎ ዲስኩር ምርኮኛው በመደዳ ይሰለፋል። የምራቅ ክምር ስንቅ እና ትጥቅ ለነፍስም ለስጋም ይሆን ይመስል። በቃኝ የምራቅ መኮረፍረፍም ሊባል ይገባል። ከሁሉ በላይ ካህዲና ክህደትን መጠዬፍ ይገባል።
ክብረቶቼ ዛሬን በዚህ ልከውነው። ኑሩልኝ ለእኔም ለቅኒት ኢትዮጵያ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06/07/2021
„ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል።“ የጎንደሬዎች ቅኔ ነው።
የቃል ነን እና ስለቃሉ በህጉ ለመኖር እንፍቀድለት።


 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።