ጎንደር የአፍሪካ የአጤወች ፓላስ፤ የጥቁሮህዝብ የመናጋሻ ርዕሰ ጉልላት የባህል አውራ ናት።

 

ከአቶ አዳነ ጌትነት ፔጅ ከጎንደር ቱዩብ የተወሰደ።
 No photo description available.
 
ጎንደር የአፍሪካ የአጤወች ፓላስ፤ የጥቁሮህዝብ የመናጋሻ ርዕሰ ጉልላት የባህል አውራ ናት።
ስለተፈጠርኩባት ሳይሆን ከምድር በላይ ብቻ ሳይሆን ከምድር በታች ታሪኳ ምስክር ነው። ለዚህ ነው
ህወኃት በጥርሱ ነክሶ የያዛት። ግን ዓይነታው ጎጃም ቅኔ ሆነላት። ተመስገን።
"ጎንደር - ታሪካዊ የመናገሻ ከተማ፤ 💚💛❤
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
ጎንደር ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር 175ኪ.ሜ፣ ከአዲስ አበባ 738ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ታሪካዊ የመናገሻ ከተማ ናት፡፡ ከተማዋ በውስጧ በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ በርካታ ታሪካዊ የመስህብ ሀብቶችን ይዛ በመገኘቷ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ ናት፡፡ በታሪካዊቷ ከተማ እና አካባቢ የሚገኙ የመስህብ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ግብዣችን እያቀረብን ሰለ ጐንደር ያዘጋጀነውን ጹሑፍ አንብበው ለወዳጅዎ ያጋሩት ዘንድ አቅርበንልዎታል፡፡
የጎንደር ስያሜ እና አመሰራረት፤
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
ጎንደር የሚለውን ቃል ለስያሜ እንዴት መጠቀም እንደተጀመረ ብዙ አፈ-ታሪኮች ይነገራሉ፡፡ በርካታ ሰዎች የጐንደር ስያሜ ምንጭ ነው ብለው የሚያምኑት የሚከተለውን አፈ-ታሪክ ነው፡፡ አፈ ታሪኩ በከተማዋ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሁለት ወንድማማቾች በመካከላቸው የተፈጠረውን የድንበር ጠብ ለመፍታት ወደ ሽማግሌ እንደሄዱ ይተርካል፡፡ ሽማግሌዎችም የወንድማማቾችን ክርክር ከሰሙ በኋላ ለታላቅየው “አንተ በዚህ ተቀመጥ” ብለው ታናሽ ወንድሙን ደግሞ “አንተም ከወንድምህ ጎን እደር” ብለው አስማሟቸው ይላል፡፡ ከዚህ ጀምሮ “ጎን እደር” የሚለው ጐንደር በመባል መጠራት እንደጀመረ አፈ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ በሌላ በኩል የጎንደር ስያሜ “ጉንደ ሀገር” ማለት ነው የሚሉም አሉ፡፡ ጉንደ ሀገር ማለት ታላቅ ሀገር ማለት ነው፡፡ ይህ ስያሜ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ባዘጋጁት መዝገበ ቃላት ላይም ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ጐንደር በአፄ ፋሲለደስ የተቆረቆረች ከተማ እንደሆነች ብዙ ሰዎች ያምናሉ፡፡ ታሪካዊ ማስረጃዎች ግን ጐንደር ከአፄ ፋሲለደስ በፊትም ሰው የሚኖርበት ቦታ እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡ በአፄ አምደ ፅዮን(1307-1337ዓም) ዜና መዋዕል “ጐንደር” የሚለው ስም መጠቀሱ ቀዳሚው ማስረጃ ሲሆን አፄ ፋሲለደስ ከመንገሳቸው በፊት “ጎንደሮች ማርያም፣ ጎንደሮች ጊዮርጊስ እና አበራ ጊዮርጊስ የሚባሉ ቤተ ክርስቲያኖች በከተማዋ የነበሩ መሆኑ ሲታሰብ ጐንደር ከአፄ ፋሲለደስ ዘመን በፊት ረጅም ዕድሜ የነበራት ከተማ መሆኗን መረዳት ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ጐንደር የከተማ ቅርጽ እንድትይዝ፣ ዘመናዊ ሁና እንድትደራጅ፣ ብዝሃነትን እንድታስተናግድ፣ በንግድ ማዕከልነት እንድትቀጥል፣ በትምህርት እና ኪነ - ህንፃ ጥበብ እንድታሸበርቅ፣ የኢትዮጵያ መዲና እንድትሆን ያደረጓት አፄ ፋሲለደስ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አፄ ፋሲለደስ ሲነሱ ጐንደር፤ ጐንደር ስትነሳም አፄ ፋሲለደስ መነሳታቸው የማይቀር ሀቅ ነው፡፡
ጎንደር በዋና መዲናነት እንድትመረጥ ያደረጓት ምክንያቶች፤
▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔▔
አፄ ፋሲለደስ የንጉሥነት ስልጣኑን “ዓለም ሰገድ” በሚል የንግሥና ስም ከአባታቸው አፄ ሱስንዮስ(1596-1624ዓ.ም) ከተረከቡ በኋላ “ፋሲል ይንገስ፣ ተዋህዶ ይመለስ፣ የሮም ሀይማኖት ይፍለስ፡፡” የሚለውን የአባታቸውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ዙፋናቸውን አደላድለዋል፡፡
አፄ ፋሲለደስ በ1624ዓ.ም እንደነገሡ ለአራት ዓመታት ቀደም ብለው እንደነበሩ ነገሥታት በጣና ዙሪያ፣ በጎጃም-አዴት፣ በደንቀዝ፣ በጎርጎራ፣ በደብሳን፣ በጎመንጌ፣ በአዘዞ እና አካባቢው መቀመጫቸውን እያዘዋወሩ ኢትዮጵያን አስተዳድረዋል፡፡ በ1628ዓ/ም ደግሞ መዲናቸውን ጐንደር በማድረግ “የጎንደር ወርቃማ” ዘመን እንዲጀምር አድርገዋል፡፡
አፄ ፋሲለደስ መዲናቸውን በጐንደር ለመስራታቸው በርካታ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን በዋናነት የጐንደር መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እራስን ከጠላት ለመጠበቅ የተመቸ መሆኑ፣ በረሃው እና ደጋውን ለመቆጣጠር የሚያስችል አማካኝ ቦታ መገኘቷ፣ተስማሚ የአየር ጠባይ የታደለች መሆኗ፣ ለመጠጥ እና ለንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ወንዞች እና ምንጮች በብዛት መኖራቸው፣ ንጉሡ ላሰቡት ግንባታ የሚሆኑ ግብዓቶች በቅርብ መገኘታቸው፣ ወባን ከመሱ በሽታዎች ነጻ መሆኗ፣ የደመቀ ንግድ እንቅስቃሴ መኖሩ ወዘተ ንጉሡ ጐንደርን ለመምረጣቸው ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡
በአፈ ታሪክ ደግሞ አፄ ፋሲለደስ ጐንደርን በመዲናነት የመረጡበት ምክንያት ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአፈ ታሪኩ መሰረት ከአፄ ልብነ ድንግል(1500-1532ዓ/ም) ዘመነ መንግስት ጀምሮ “ጐ” ትነግስ ወይም በ”ጐ” በሚጀምር ፊደል በምትጠራ ስፍራ ቤተ መንግስቱን የተከለ ንጉሥ የረጋ ዘመነ ንግሥና ይኖረዋል የሚል ራዕይ ይታያቸው ነበር ይላል፡፡ ይሄን ራዕይ ለመፈፀምም በ”ጐ” ፊደል የሚጀምር መዲና ለማግኘት በጎጃም፣ በጎርጎራ፣ በጎመንጌ መቀመጫቸው በማዟዟር ነገሥታቱ ኢትዮጵያን ቢያስተዳድሩም “ጐ” ትነግስ የሚለው ራዕይ እስከ አፄ ፋሲለደስ ዘመነ መንግስት ድረስ መታየቱን አላቋረጠም ነበር፡፡ አፄ ፋሲለደስ በጐንደር መዲናቸውን ሲሰሩ አባቶች ሲያዩት የነበረው ራዕይ እንደተፈጸመ ይተርካል፡፡
አፈ ታሪኩ ከአፄ ፋሲለደስ ጀምሮ የነበረው የተረጋጋ የሰላምና ሥልጣኔ ዘመን ንጉሡ ለአባቶች በራዕይ የታየችው ትክክለኛዋ “ጐ ትነግስ” ጐንደርን ከማግኘታቸው ጋር ያገኛኙታል፡፡
ጐንደር በአፄ ፋሲለደስ የኢትዮጵያ መዲና ከሆነች በኋላ የከተማ እና ከተሜነት መመዘኛዎች ፈጥና በማሟላቷም “ጐንደር - የከተሞች እናት” ተብላለች፡፡ ጐንደር ቀድመዋት ከተመሰረቱት ከተሞች በንግድ፣ በዕደ ጥበብ፣ በግንባታ፣ በዘመናዊ አኗኗር፣ በትምህርት፣ ብዝሃነትን በማስተናገድ ወዘተ የተለየ አካሄድ በመሄዷ እና ከጐንደር በኋላ በኢትዮጵያ ለተመሰረቱ ከተሞች ሁሉ ምሳሌ መሆን በመቻሏ ነው የከተሞች እናት የተባለችው፡፡ ለአብነት ጐንደር ብዝሃነትን እንዴት እንዳስተናገደች የከተማዋ ሁለት መንደሮችን ማየቱ በቂ ነው፡፡
የመጀመሪያው የወለቃ የቤተ እስራኤላውያን መንደር ነው፡፡ በዚህ መንደር የሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን በእጅ ጥበብ ሙያ ጎበዞች ሰለነበሩ አፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግስታቸውን ሲያሰሩ እንደተሳተፉ ይወሳል፡፡ ቤተ እስራኤላውያን ለጐንደር ስልጣኔ ያበረከቱት አስተዋጹኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ሁለተኛው የብዝሃነት ማሳያ አዲስ ዓለም ናት፡፡
ጐንደር የሲራራ ንግድ ማዕከል በነበረችበት ጊዜ በርካታ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች በከተማዋ አዲስ ዓለም በሚባለው መንደር ይኖሩ ነበር፡፡ አዲስ ዓለም በዘመኑ “ነጋድራስ” የሚባለው ማዕረግ የሚሰጣቸው ሰዎች መገኛ እና በጣም የተዋበ ሰፈር እንደነበረ በታሪክ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ጐንደር ቀድማ ለተከተሏት ከተሞች የሀይማኖት ብዝሃነትን አስተምራለች፡፡ (Yihune Dagnew)"
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20/12/2021
እቴጌ ጎንደር ኑሪልን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።