ጤናችን።

 

ጤናችን።
ተርኋሚ መላኩ ብርኃኑ እንዳጋሩት
ስትሮክ እየጨረሰን ነው
(መላኩ ብርሃኑ)
……………………………………
"ይህንን መረጃ ሳነብ ያገኘሁት ነው። ለሁላችንም እንዲጠቅም ወደአማርኛ መልሼዋለሁ። ስትሮክ የዕለት ከዕለት ችግራችን እየሆነና የሁላችንንም ጓዳ እያንኳኳ በመሆኑ መረጃው ይጠቅመናል ብዬ አስባለሁ። እባካችሁ ሼር በማድረግ እውቀት አሸጋግሩ። ምናልባት በዚህ መረጃ የአንድ ሰው ህይወት ታተርፉ ይሆናል።
እኔ በበኩሌ ከ8 አመት በፊት ይህ መረጃ ቢኖረኝ ኖሮ ምናልባት ወንድሜን ከሞት የማትረፍ እድል ይኖረኝ ነበር። እሁድ ቀን ጠዋት ነው። ወደጓደኛዬ ኒካ ስነስርአት ለመሄድ ስነሳ ወንድሜ ቀድሞኝ ከቤት ወጥቶ ስለነበር ከቤታችን ደጃፍ የሚገኝ አስፋልት መንገድ ዳር ላይ ተቀምጦ አይቼው ነበር። ከአይኑ እስክጠፋ ቁጭ ባለበት ቦታ ሆኖ ያየኝ እንደነበር ያወቅኩት ርቄ ሄጄ ዘወር ስል ወደኔ አቅጣጫ ያይ እንደነበር በመታዘቤ ነው።
ከሁለት ሰአታት በኋላ ፑል በመጫወት ላይ እንዳለ ተዝለፍልፎ ወደቀ ተብሎ ተደወለልኝ። ስደርስ ቤተዛታ ሆስፒታል ገብቶ ስትሬቸር ላይ ተኝቶ አገኘሁት። ሃኪሞች ከሻይ እስኪመለሱ እርዳታ አላገኘም። ቀስ በቀስ ራሱን ሙሉ በሙሉ ሳተ። ችግሩ ምን እንደሆነ አላወቅንም የነገረንም ሃኪም የለም። በመጨረሻ ቤተዛታ ከአቅሜ በላይ ነው አልችልም አለ ……ጥቁር አንበሳ በበኩሉ አልጋ የለኝም ሲል…እኛም ለጭንቅላት ምርመራ የታዘዘልንን ኤምአርአይ ፍለጋ ስንንከራተት ሰአቱ ገፋ። መጨረሻ ላይ ሀያት ሆስፒታል አልጋ ተገኝቶ የፅኑ ህሙማን ጥብቅ ክትትል ክፍል (ICU) ገባ። በዚያው ሁኔታ ሳለ በሶስተኛው ቀን ህይወቱ አለፈ።ገና በ22 አመቱ። ለቤታችን ታላቅ ሃዘን ሆነ። ዛሬ ድረስ ሁኔታውን ሳስበው እንባዬን ማቆም አልችልም። እጅግ የምወደውን ወንድሜን የነጠቀኝ ስትሮክ ነው።
ከዚያ ጊዜ በኋላ የቅርብ ዘመዶቼን ጨምሮ የማውቃቸው ብዙ ሰዎች በስትሮክ ተጠቅተው አይቻለሁ። ብዙዎቹ ሞተዋል።ብዙዎቹ ፓራላይዝ ሆነዋል። በዚህ ሁለት ወር ብቻ የማውቃቸው ሶስት ሰዎች በስትሮክ ሞተዋል።
በስእሉ ላይ እንደምትመለከቱት ስትሮክ ወደአንጎል የሚሄደው ደምስር በረጋ ደም በሚዘጋበት ጊዜ የደም ዝውውር ሲቋረጥ የሚከሰት የደም ወደአንጎል መፍሰስ የሚያስከትለው ከባድ የጤና አደጋ ነው። ከባድ የደም ግፊት፣ የልብና ኩላሊት በሽታ ለስትሮክ መከሰት ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ሃኪሞች ይናገራሉ።
ብዙዎቻችን ስለማናስተውለው እንጂ የምንሰማው የዘመድ ወዳጆቻችን ድንገተኛ ሞትና ራስ መሳት ከስትሮክ ጋር ቁርኝት አለው። ይህ አደጋ ድንገት ባልታሰበ ሰአት ይከሰታል። ተኝተን፣ እየሰራን፣ እየበላን፣ እየተጫወትን፣ መንገድ ላይ ሆነን ሊከሰትብን ይችላል።
በስትሮክ የተመታ ሰው ለብዙ ጉዳቶች ሊዳረግ ይችላል። አንዳንዶችን በሙሉ ወይም በከፊል ፓራላይዝ ያደርጋል። አንዳንዶቹን የአእምሮ ማስታወስ ችሎታቸውን በሙሉ ወይም በከፊል ይነጥቃቸውና ሚስትና ልጆቻቸውን ጭምር እንዲረሱ ያደርጋቸዋል። የከፋ ጊዜ ልክ ኮምፒውተር ፎርማት እንደሚደረገው ሁሉ ስትሮክ ያጠቃቸውን ሰዎችም አዕምሯቸው ምንም ሳያስቀር ሙሉ በሙሉ የመርሳት ችግር ይጋርጥባቸዋል። አንዳንዶቹ ላይ ደሞ ራስን ስቶ ሽንትና ሰገራ ለመቆጣጠር እስካለመቻል ምግብ እስካለመቀበልና በመጨረሻም እስከሞት ያደርሳቸዋል።
የስትሮክ የከፋው ጠባይ የያዘውን ሰው አንዳንዴ ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች አድርጎ ማስቀረቱ ነው። እናት ለታመመ ልጇ ሞትን እስክትመኝ የታመመ ሰው በጠያቂ "አሁንስ በገላገለው " እስከሚባል ድረስ ተስፋ ያስቆርጣል።
የጭንቅላት ቀዶ ሃኪሞች አንዳንዴ ከተሳካላቸው በአንጎል ውስጥ የፈሰሰ ደምን በመጥረግ ህይወት ያተርፋሉ ወይም ጉዳት ይቀንሳሉ። በኛ አገር ደረጃ በከባድ ስትሮክ ተመትቶ ሙሉ በሙሉ የመዳን ብቻ ሳይሆን ከሞት የመትረፍ እድል ራሱ አናሳ ነው። እግዚአብሄር ተጨማሪ የመኖር እድል የሰጠው ሰው ከሳምንታት ወይም ወራት ራስን መሳት በኋላ ሙሉ በሙሉ ተርፎ በተአምር ከሞት ወደህይወት ይመለሳል። የአንዳንዱን ህይወት ደግሞ እስከእድሜ መጨረሻው ድረስ አበላሽቶ ያስቀረዋል። በአጠቃላይ ስትሮክ መቼና እንዴት እንደሚከሰት ስለማይታወቅ ሰይጣን በሽታ በሉት። ሹክክ ብሎ መጥቶ ውድ ህይወታችንን ይነጥቀናል።ወይም ከነበርንበት ሙሉነት ወደከባድ ጎዶሎነት ይቀይረናል።
ስትሮክን በተመለከተ ያለው መልካም ዜና አንድ ብቻ ነው። ምልክቱን አውቀን ከቀደምነው የሞት በትሩን የማስጣል እድል አለን ። በጣም ቀላል በሆኑ ዘዴዎች አንድ ሰው በስትሮክ ስለመመታቱ ማረጋገጥና በፍጥነት ወደሀኪም ወስደን ህይወቱን ማትረፍ እንችላለን። በርግጥ እግዜር ይጠብቅ ነው እንጂ በኛ ሃገር ሃኪሞችና ሆስፒታል ሁኔታ ብዙ ተስፋ ማድረግ አይቻል ይሆናል። ( በወንድሜ ሞት ያረጋገጥኩት ይህንኑ ነው)። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚያረጋግጡት የስትሮክ ምልክት የታየበት ሰው በ3ሰአታት ጊዜ ውስጥ ሃኪም ጋር ከደረሰ ሙሉ በሙሉ ለመዳን እድል አለው። ዋናው ጥያቄ አንድ ሰው በስትሮክ ሲመታ የሚያሳያቸው ምልክቶች ምንድናቸው? እንዴትስ ማወቅ ይቻላል? የሚለው ነው።
አንዳንድ ጊዜ ምልክቶቹን ለመለየት ከባድ ቢሆንም STROKE አንድን ሰው እንዳጠቃው ለማወቅ የምንረዳባቸውን ቀላል ዘዴዎች አሉ። ቀዳሚው ዘዴ የ STROKE ን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ፊደላት በቃል ይዞ በአዕምሮ መመዝገብ ነው። STR
S= smile. በትሮክ የተመታ ሰው ፈገግ ማለት ያዳግተዋል። ፊቱ ስሜት አልባ ይሆናል። አንድ ጊዜ ፈገግ እንዲል መጠየቅና ውጤቱን ማየት
T =talk ስትሮክ አንደበት ስለሚይዝ የሚወጡ ቃላት እንዲንተባተቡና ትርጉመቢስ እንዲሆኑ ያደርጋል። ቀላል አረፍተነገርን ሳያቆራርጥ እንዲናገር መጠየቅ (ምሳሌ ቴሌቪዥኑን ስንት ትሸጠዋለህ? እንዲል )
ውጤቱንም ማጤን
R=raise hands ስትሮክ እጅና እግር እንዳይታዘዝ ያደርጋል። ሁለት እጆቹን ወደላይ እንዲያነሳ መጠየቅና ውጤቱን ማየት
ከነዚህ አንዱን በትክክል መወጣት ከተሳነው የስትሮክ ምልክት ነውና ሃኪም ጋር በፍጥነት መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል። በተጨማሪም ምላሱን ቀጥ አድርጎ እንዲያወጣ መጠየቅ ማውጣት ከተሳነው ወይም አጥፎና አጣሞ ካወጣው በስትሮክ የመመታት ምልክት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል ።
በቃ ይኸው ነው። ለሁሉም ሼር አድርገን ህይወት እናድን"
እግዚአብሔር ይስጥልን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20/12/2021

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።