"ሙያ በልብ"

     „ሙያ በልብ“
                                    ከሥርጉተ ሥላሴ 13.06.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)

         „እውቀትን ለማን ያሰተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተወ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? 
             ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ሥርዓት በሥርዓት፣ ሥርዓት በሥርዓት ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። 
            በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ህዝብ ይናገራል፣ እርሱም ፣--- እረፍት ይህቺ ናት የደከመውን አሳርፉ ይህችም 
                                      ማረፊያ ናት አላቸው፤ እነርሱም ግን መስማትን እንቢ አሉ።“ 

                                          (ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፳፰ ቁጥር ፱ እሰከ ቁጥር ፲፪)


እኔ እንደሚገባኝ እና እንደምረዳው ከሆነ ከእንግዲህ አማራ ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት፤ ከዬትኛውም የፖለቲካ ሊሂቅ፤ ከዬትኛውም ጋዜጠኛ፤ ከዬትኛውም አክቲቢስት፤ ከዬትኛውም ዘመን አመጣሽ የፖለቲካ ተንታኝ ጋር እስጣ ገባ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። እርግጥ ነው በዚህ በአዲሱ የአብን መንፈስ የማይመቹትን እዬፈለፈሉ ጥንካሬን ለማትጋት ለማውጫነት ያለፉትን አምክንዮች በማንሳት ከውድቀት እንዲድን መታታር ግን የተገባ ይሆናል። የእኔም ጹሁፍ ዓላማ ይሄው ነው። 

አዲሱ አብንም ከልብ ሆኖ ሊያዳምጠን ይገባል። ገና ከመፈጠሩ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ተራራ ያሰኜኛል ካለ እራሱን አንድ አድርጎ ለመምራት ደግሞ ከተሳነው ጣፊያ ልመና መሄድ ራሱን ያሳጠዋል፤ የዛሬ ድምቀት ነገን ያከስማል። ስለምን? በፈለገ ቅብ ድርጅት ከእንግዲህ የጎንደር መሬት እንዲታረሥ አንሻም። ጎንደር በዙር የሰው ብርንዶ ማቅረቢያነቱ ይህ ዘመን የመጨረሻው ሊሆንም ስለሚገባም። ለጎንደር ህዝብ ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ በላይም መሪ አይጠበቅም። ለዚህ ነው እንደ ሰማሁት ከተመረጡ በኋዋላ በተደሞ ነፍሳቸውን እንዲያሰነብትላቸው ጸሎትን በወል ተያይዞት ያለው። ከእንግዲህ ከፋኛ የሚል ባለ መሳሪያ በተፈጠረበት ባባዕቱ በጫካው እንጂ ጎንደር እየተማጣ የሽፍትነት ምሽግ እግዲህ መሆን አይገባውም። 

ከፋኝ የሚል በራሱ ዱር እና ገደል እንደ ቀደምት አባቶቻችን የራሱን ልጆች አስከትሎ መሸፈት መብቱ ነው። ወደ ጎንደር መተመም ግን ከዘመነ አብይ በኋዋላ መቋጫ ያገኛል። ጦርነቱ ባድመ ላይ አልነበረም፤ ወይንም አፋር ላይ የኤርትራን ቁንጫን መወጣጫ ጎንደር ነው የነበረው። የዘመነ ኢህአፓም፤ የዘመነ ኦህዴድም ቢሆን ጎንደር ነበር ለእርድ የቀረበው። እሰከ ቅርሱ፤ እሰከ ውርሱ እስከ ቅርሱ። ስለዚህ መሸፈት መብት ሲሆን ግን የራስን ልጅ ይዞ በራስ ጫካ እና ዱር … ጎንደር የድርብበርብ ቂም ማወራረጃ አይሆንም ከእንግዲህ። የጎንደር ህዝብ ተሰብስቦ በጋራ እና በውል ይህን ብይን መስጠት አለበት። 

አንድም ከፋኝ የሚል ሽፍታ በቀዬው ማሳደር፤ ማዋል አይኖርበትም። አካባቢውን እሱ እራሱ መጠበቅ አለበት። ከሌሎች ብሀር እና ብሄረሰቦችም ጋር ምንም ግጭት አያስፈልገውም። መሠረታዊው ጥያቄ አቅርቧል። መልሱን እዮባዊነትን አስልቶ መጠበቅ አለበት። ለዛውም ገዳይ ተብሎ ከነቅርሱ እኮ የተወነጀለው ማህብራዊ መሠረቱ የነተናጋው እሱ እራሱ ነው። ጎንደር ስንቅ ብቻ ሳይሆን መንፈስ ሲያቀብል የመንፈስ ልእልናዊ ሞራሉን ተገድሎ በሞቱ ውስጥ ዳግም ለሞቱ ነበር ወስኖ የኖረው። ከእንግዲህ በሩን መዘጋት ነው። የጎንደር ልጆችም እዬሄዱ ጥልቅ የሚሉትን ነገር ማቆም አለባቸው በምህላ። ለነሱ ካለ ጎጃም ህዝብ ማንም የላቸውም። ጎንደር የጎጃም የምስጋና ቀን ማዘጋጀት ይኖርበታለኝ። የፈለገ ልጁ በፈለገው የፖለቲካ ሥም ይምጣ ጎንደር ራሱን የማድመጫ ጊዜው ነው። የዘር ማፍሪያ ከማጣት፤ አንስት ልጆቹ መርዝ ከመወጋት፤ ጥፍር ከመውለቅ፤ ደም ከመሽናት እንደዚህ የሁሉ ነገር መሞከሪያ ወዲያ ምን ይጠብቃል?

እስከ አሁን የተከፋበትን የሚገልጽበት አገር ቤት የአማራ ድርጀት አልነበረም። ከመአህድ በስተቀር። እሱን በሽታሽቶሽ የአማራ ሊሂቃን ተጨምረውበት ከከሰመ በኋዋላ ደግሞ ውሹን ያዋሳ ሆኖ ቆይቷል። አድማጭ አልባ፤ ችግርን ተጋሪ አልባ? 
ስለምን? በሁሉ ክልል ላይ አነሰም በዛ በርከት ያሉ ድርጅቶች አሉ። አማራ መሬት ላይ ግን አንድም አልነበረም። ስለዚህም ጥቃቱ ዋቢ ጠያቂ አልባ ቀጣይነቱም አጣያያቂ አልነበረም። ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ የሚሆኑት የ66ቱ የማርክሲስት ሌኒኒስት ኢትዮጵያዊ ሊሂቃን እንጂ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ብቻ ሊሆን እንደማይችልም ይታወቃል። ኢህአፓ ያውቅ ነበር የወያኔ ሃርነት ሆነ የአቻዎቹን አቋም ግን አማራ መደራጀት የለበትን ባዩ እሱ ነበር። ስለምን ማን ጠበንጃ ያነግታል? ማን ስንቅና ትጥቅ ይሆናል? ማን አንጣፊ እና ጎዝጓዥ ይሆናል? ዛሬም አማራ መደራጀት የለበትም ብለው የሚሞግቱተም እናሱ ናቸው የማሌ አባ እና እማ ወራዎች። አንጋቻቸው ባርነት በቃኝ በማለቱ። ሎሌያቸው አማራ አሻም ስላላቸው፤ መንገድ ጠራጊያቸው የኮዳ ኑሮ ሰለቸኝ ስላላቸው። ድልድያቸው የታንኳ ኑሮ መረረኝ ስላላቸው።

ወያኔ ሃርነት ትግራይ ጠላቴ አማራ ነው ብሎ ሲነሳ እነሱም ዓላወጁትም እንጂ በስውር ጠላቴ አማራ ነው ብለው ነው አማራ በጎሳው ሳይሆን በህብረ ብሄር ብቻ ነው መደራጀት ያለበት ብለው አማራውን ተጭነው፤ ተጨቁነው ለጥቃት፣ ለስደት፣ ለእርዛት ለዘር ጥፋት እንዲዳረግ በስትራቴጂ ህብረ ብሄር በሚል ሽፋን ብቻ ሸብበው ሲያሳንቁት የኖሩት። በህሊናቸው መስጥረው አማራ በተገኘበት ሲያሰገልሉ፤ ሲያሳድዱ ጠረኑን ሲጸዬፉት ነው የኖሮሩት። እከሌ ተከሌ ሳይባል ዕድሉን ቢያገኙት የሚፈጽሙት በደል ከዚህ የተሻለ አይሆንም፤

ሁሉም የ66ቱ የፖለቲካ ሊሂቃን ከወያኔ ሃርነት ማንፌሰቶ የሚለዩት አገራዊ ምልከታ ያላቸው ግን አማራን በማጥቃት፤ በማግለል ሥነ - ልቦናዊ አቅሙን ተረግጦ በመያዝ ደረጃ በስትራቴጂ ይዘው በታክቲክ ሸብበው እና መስጥረው የያዙት ገመናቸው ነበር። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዕድሉን ባያገኝ አሁን ያለውን ጫጫታ በተደሞ ሲገመገም እነሱም አማራን በሚመለከት በስትራቴጂ ደረጃ ከማንኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ የማግለል በስልት፤ የመመንጠር ተልዕኮ ነበራቸው። ይህ ዕውነት ነው። ወጥተው ለማውግዝ እንኳን አቅም የላቸውም። ዕልቂቱን ሲጽፉ የሥልጣን ምኞታቸውን ሲገልጹ፤ ድርደር ሲያደርጉ አማራን ሰርዘው ነው የሚፈጽሙት።
ሚዲያ ላይ የሚታዩ አማራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱ መናጆ ሲሆኑ አብዛኞቹ ከሌላም ዘር ደም ያለባቸው ናቸው። እነዚህ ከሌላ ዘር ያለባቸው ሙልጭ አድርገው አማራነታቸውን ክደው በጠላትነት መሰለፋቸውን ሲያረጋግጡ ነው የአዬር ላይ ጭብጨባው እና እልልታው የሚጎርፍላቸው። ይህ ነው ጨዋታው 43 ዓመት የተኖረው።

አሁን በተፎካካሪ ፓርቲዎች ታሪክ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ መመሥረት ዛሬ ቢፈሩት፤ ራድ፤ ቢይዛቸው ግድ ይላል። ተለጣፊዎችን ለማደረጃት ባለቀ ሰዓት ነበር „አንድ ለአማራ“ „የአማራ የወጣቶች ክንፍ“ የሚል አዘጋጅተው የነበረው። ይሄ የሳጥናኤል መልዕክት ነበር ለአማራው። የለማ እና የገዱ መንፈስ የበላይነቱን ይዞ ባይወጣው ኖረ ይህ ሲዖላዊ መንፈስ አብሮ በአማራ ሥም ተደራድሮ የተለመደው የሸብጥ ዕዳውን ለዘለዓለም ይለብስ ነበር ቅኑ አማራ።

ትውልድ ከቶውንም የማይተካቸው እኒያ ግልጽ እና ቀጥተኛ ፕ/ አስራት ወልደዬስ ድከምም በአረም ተውጦ ይቀር ነበር። ሃምሌ 5ም የሙጃ እራት ሆኖ ይቀር ነበር። ባለፈው ዓመት የሙት ዓመታቸው ተከበረ ተብሎ ሁሉ እኮ ትችት ነበር። ቢያንስ በስብዕዊ መብት ተሟጋችነታቸው እሱም ቢቀር በሙያቸው ስላበረከቱት ታላቅ ኢትዮጵያዊ ተጋድሎ ቢነሱ፤ ቢወሱ፤ ቢወደሱ የጎረበጣቸው ብዕራቸውን ስለው ወጥተው ነበር። ዛሬ ሌላ ቀን ስለሆነ እጅግም የተደራጀ፤ እጅግም የተዋበ፤ ውስጣቸን የሚያውጅ አማራዊ ቃናችንን አጉልቶ የዘከረ „አማራ ነን“ መዝሙርን በአንድ ድምጽ ያጸደቀ፤ መሪዎቹን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ የመረጠ ሳተና ወጣቶችን የያዘ አካል መሬት ላይ ተፈጥሯል። እርግጥ ነው ከጉድፍ ነፃ ነው ማለትም አይቻልም፤ ለቀረመትም ዝርግ ሆኖ ቀርቧል። ጥንቃቄ ከጎደለው የቅንጅት ዕጣ ፈንታ ይገጥመዋል። ይህን ዛሬ መናገር ግድ ይላል። 

አንድም አማራ ከእንግዲህ ድምጹን አቅሙን ሁለመናውን ከዚህ ውጪ ማድረግ አይችልም። በፍጹም። አማራ የነበረበትን የግፍ ዘመን አሸንቅጥሮ እሱነቱን፣ ብቃቱን፣ ችሎታውን፣ ቅኔነቱን አቅሙን በልኩ እና በቁመናው ከአያት ቅደመ ቅኔው ተነስቶ እራሱን እንዲያበራ መንገዱን በጠራ መስምር ማዬት ግድ ይለዋል። ይህ ከሆነ ይህ መፈራቱ፤ ይህ ራድ ማስያዙ የተገባ ነው። ይፈሩናል። ይገባልም።

ስለዚህ ጊዜ ማባከን አያገባም። የፈለገ የፈለገውን ይጻፍ፤ የፈለገ የፈለገውን ይበል፤ የፈለገ የፈለገውን ይለጥፍ የብራና፤ የቀለም፤ የማይክ ጉጉስ መቆም አለበት። ያሸነፈ ሰው ብዙ አይጮኽም። በዝምታው ውስጥ „ሙያ በልብ“ ብሎ ሥራውን ይሠራል። ኦህዴድን ተመልከቱት፤ በልቡ ውስጥ የልቡን ይከውናል። በቃ ዘመን እራሱ ከኦህዴድ ተቀንቶም፤ ታፍሶም ተዝቆም ከማያልቀው ችሎታው ጋር መማር የስፈልገዋል። አሁን እኔ እንደ ሥርጉተ ስናገር የከረምኩትም ማንም ድርጀት ለዚህ አሁን ለተመሠረተው ድርጅት ቀናዊ ምልከታ አለው ቢባል ኦህዴድ ብቻ እና ብቻ ነው። ይልቅ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ምልከታ አብን ከኦህዴድ ጋር የቀረበ ግንኙነት ቢኖረው ምርጫዬ ነው። ስለምን? ኦህዲድ ፈርሃ እግዚአብሄር ያለው ድርጅት ነው። የ66ቱ ግርፍ እኮ የለም በዚህ ውስጥ። ከዚያ በላይ የተመክሮው ማሳ እና የእርምጃ አወሳሰዱ ቅደም ተከተል ሁለት ትውልድ ይገነባል - የኦህዴድ። ለዚህም ነው ሥርጉተ ሥላሴ ለማውያን የሆነችው፤ ኦህዴድም ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን አእምሮ አለው የመትለውም።

እንዲያው እንደ እኔ አመሠራረቱ በዚህ መልክ የሆነው አብን ደረጃውን የጠበቀ ተግባር እንዲከውን ነው የማስበው። አብን የራሱን አክቲቢስቶች፤ ጋዜጠኞች፤ የሚዲያ ሰዎች ማፍራት አለበት። ኦህዴድ ሥልጣን አንድ ላይ እንዲከማች፤ ዕውቅና አንድ ቦታ ላይ እንዲከማች፤ ብቃት አንድ ቦታ ብቻ እንዲከማች ሳይሆን የሚያደርገው ከተለመወደው ውጪ „ማብቃት“ ነው መርሁ። ስለዚህ ይህን መንገድ ነው መከተል ያለበት አብን። ይህ መንገድ አንዱ እክል ቢገጥመው ሌላው ይተካዋል። አሁን ብዙም ያልተባለላቸው አቶ ካሳሁን ኮፌ ከሌሎች ያልተናነሰ አቅም፣ ብልህነትን ችሎታ ቁጥብነት ነው ያላቸው። እኔ እንዲያውም ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር ይሁን ዶር ነገሬ ሌንጮ ይዘውት የነበረው ቦታ ሁሉ ለእሳቸው ቢሰጥ ምርጫዬ ነበር። ስለምን የተከደነ የ አቅም ዴታ ስለሆኑ። ኦህዴድ ልቅም ያሉ ተተኪዎች አሉት። ኦህዴድ የሥልጣን ሽግሽግ ሲያደርግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የምክር ቤቱ አባል ነበሩ። ዴሚክራሲን ፈጸምነው ሳይሆን ጀመርነው ነበር ያሉት። ይሄው ዛሬ የአንድ አገር ብሄራዊ ጠ/ ሚር ቦታን ተረከበዋል - ዛሬ።  የኦህዴድ የጽ/ ቤት ሃላፊ ናቸው። እኔ እራሴ ያወቅኩቸው ዕድሉን ይሰጣል ኦህዴድ። ዕውቅናውን መወደሱን መቀደሱን እኔ ብቻ ጠቅልዬ ልያዝ አይልም የለማ መንፈስ። ይህ ልቅና ዴሞክራሲ የተፈጠረበት ዘመን በአዲስ ተሃድሶ ኢትዮጵያ ላይ እንደ ገና እንደ ተፈጠረ ያሳያናል። ኦህዴድ ልዩ የሚያደርገው ከሚስጢሩ ጋር ስለተገናኜ ነው ከዴሞክራሲ ጥልቅ የሰብል መርህ ጋር። በዬትኛውም ድርጅት ቢሆን ዶር አብይ አህመድን አናገኛቸውም ነበር። ቅደስናቸውን ተጠቃሚ የሆነው በ =ኦህዴድ አቅም ያላቸውን ወደፊት በማምጣት ጥበቡ ነው።

አቅም ያለውን ወደፊት ለማውጣት ስስታም አይደለም ኦህዴድ። ለሥልጣን እና ለ እውቅና ስግብግብ አይደለም ኦህዴድ። ለሥም እና ለዝና አጋባሽ አይደለም ኦህዴድ። መሬትን በረገጠ አቅም የሚለውን በመሆን ውስጥ ሃሌ ማለት የጀመረ የመጀመሪያው አውነተኛ የዴሚክራሲን መንገድ እህዱ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ለዚህም ነው እኔ ብሄራዊ አደራን ለመቀበል ሙሉ አቅም አለው የምለው። ኦህዴድ አቅም ሲይ ተጠድፎ ሄዶ ጠልፎ አይጥልም። ወይንም ስሙን በክሎ ማህበራዊ መሠረቱን አያናጋም ይህ ነው የለማ አስተምህሮት። ለማ ልናጠናው ልንማረው ይገባል የምለውም እኔ ለዚህ ነው። ለማ ጥልቅ መንፈስ ነው። ለማ ረቂቅ መንፈስ ነው። ለማ የ66ቱ የሴራ ዲሪቶ እንጦርጦስ የላከ የጀግኖች ቁንጮ ነው፤ የመሆን አንባ አናባቢም ነው። ለማ ቋሚ ሌሰን ነው!
እኔ ለአብን የምመክረው ሚዲያ ላይም ብዙም መታዬት ሥራ አይደለም። ሥራ አቀብት ቁልቁለቱን ወጥቶ ወርዶ ደሙን፤ ዘሩን የገበረውን ህዝብ ድምጽ ዝቅ ብሎ ማድመጥ ነው። በራስ አቅም ላይ የተመሰረተ ተግባር መኖር፤ በራስ ሃሳብ ላይ የተነሳ ስልት እና ስተራቴጂ መንደፍ አንጂ አቅም ለቀማ እና አንጋጦ ማዬት ከሆነ ብዙም ዕድሜ አይኖረም የተፈራውን ያህል የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አፈር ግጦ ትቢያ ይሆናል።

ሌላው ጉባኤውን ምክር ቤቱን ሲያስብም ሀምሌ 5 ቀን ጋር ማወዳጀት ግድ ይለዋል አማራ። ልዩ ልዩ ዝግጅቶቹን ሲያካሄድም የፕ/ አስራት ወልደዬስን የሙት፤ የልደት ቀን እያሰበ መሆን አለበት። ትውፊቱ ይሄው ነው። አማራ ሁን ተብሎ አልሆን ብሎ፤ አማራ አይደለህም ሲባል የተወለደው አማራነቱ ከዚህ ቅኔያዊ ወተት መቀዳት አለበት። እራሱን ሳያሾልኩ ታሪኩን ጠብቆ መጓዝ አለበት አብን። ስጋቴ በንጹህ ህሊና ቢጀመር ምኞቴ ነበር። ከሰማያዊ ፓርቲ የጨመራችሁት አመራር እና የሰጣችሁት ሃላፊነት ግን ይኮሰኩሳል። ይህ ድርጀት የመመስረቱ አመክንዮ የአማራ ተጋድሎ ነው። ለሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ አጀንዳው ያልነበረ ነው። አጀንዳው ያልነበረን መንፈስ አምጥቶ ከዚህ መሸጎጥ እኔ በግል ድርጅቱን በጥርጣሬ እንዳዬው አድርጎኛል። ሙሉ ዕምነቴን ለመስጠት ፈጽሞ አልችልም። የራስሽ ጉዳይ ትሉኝ ይሆናል። ግን እኔም አቅም ያለኝ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም። ስለምፈራ ነው በሁሉም ሚዲያ እምገለለው። መፈራቴ ደግሞ ከሁሉ በላይ ሐሤት የሚሰጠኝ ነው። ጹሁፌ ሲነሳ ሲለጠፍ ደስ ያለኝን ያህል ይሰማኛል። ስለበለጥኩኝ፤ ሰለ አሸነፍኩኝ መሆኑን ግብረ ምላሹ ስለሚያውጅልኝ። አማራነት ተፈሪ ነው። ሴታዊነት ሲታከልበት ደግሞ ነጎድጓዳማ ሞገድ ነው። ይፍሩን ደስ ይለናል። 

የአማራ ድርጅት ስለተባለም፤ የአማራ አክቲቢስት ስለተባለም፤ የአማራ ሚዲያም ስለተባለም፤ አሁን ዕውቅና በሚዲያ ስለተገኘም አይደለም ደጋፊ የሚኮነው። ከአማራ ተጋድሎ በኋዋላ አሁንም አማራ አጃጅላለሁ ብሎ አንድ ሰው አማራ መሬት ላይ ሌላ የፖለቲከ አጀንዳ ተሸክሞ እንግልት በህዝቤ እንዲደርስ አልሻም - አልፈቅድም። አብሶ ጎንደር ላይ ቀልዱ መቆም አለበት። ዬየዘመኑ ምሽግ እና የመሞከሪያ ጣቢያ ጎንደር እና የጎንደር አማራ መሆን የለበትም። ስለሆነም ይህን ስርክራኪ ነገር በተደሞ ማድመጥ ይገባል። የሰው ግብር አሁን የጎንደር ልጅ ነው። የትም የማያውቀውን ነው እንመሰግናለን የማይባል ህዝብ አሁን ለነ ራስ ተሰማ ናደው የአድማ ሌጋሲ ድርድር ውል ማወራረጃ እንዲሆን የተፈቀደው።

በተረፈ እነ አብን ወደ ሥራ ግቡ። ህዝባችሁን አዳምጡ። ዘብርሃነ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ግዞት ላይ ያዋሏቸው ራስ ተሰማ ናደው ነበሩ። በኢትዮጵያ ሥልጡን የፖለቲካ ታሪክም ሥልጡን የአድማ ጠንሳሽ እሳቸው ነበሩ። የቅንጅት ፍርሻም ይህ ጠንቅ ነው። አሁንም ይህን ለማስተናገድ እንዳትተጉ አበክሬ ላስገነዝባችሁ እሻለሁኝ። ይኮሰኩሰኛል ድሪተቶ ፍለጋ መሄዳችሁ። 20 ሺህ  የአማራ ወጣት እያለ ስንት ትንታግ እያለ ስለምን ሰማያዊ ፓርቲን ደጅ ጥናት እንዳስኬዳችሁ አልገባኝም። ከቻላችሁት ሞክሩት ሴራውን። አንድነትን ያህል ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ደረጃ በደራጀ አቅሙ እዬቀነሳ እሰከ መፍረስ ያደረሰው ይህን መሰል ቅንነት ነው። አንድነት አንጥፎ ጎዝጉዞ የተቀበላቸው አቶ አስራት አብርሃ የአማራ ተጋድሎን የገብያ ግርግር እዛው የሚቀር፤ የአማራ ሊሂቃን ዕውቅና የማይሰጡት አድርገው ነበር ዋጋ ቢስ፤ ዕሴተ ቢስ አድርገው አራክሰው፤ አጣጥለው የትሜና እንደ ማበሻ ጨርቅ የወረውሩት፤ አሁን ቁጭ ብለው ለለውጡ ሰፊውን የተጋድሎ ግንባሩን ያስገኘው ያ ገናና መንፈስ ስለመሆኑ እያስተዋሉት ነው። አንድነት ቀጥሎ ቢሆን ኖረ አብን ሌላ መከራ ነበረበት ቁልፉ ቦታ የተሰጠቸው ለእሳቸው ነበር እና። ሌላው ከዚህ ማዕቀፍ እንዲያውም የሰላ የስለላ ተግባር ባይረስ ተሸካሚ ሆኖ ነው ያረፈው። አሁን አብንም ይህን ጥራኝ ፍርሻ ብሎ ነው አጀንዳው ካልነበረው ከሰማያዊ ፓርቲ አቅም ተዋሽ የሆነው? ያገኛታል።

በአንድ ወቅት የሚመሠረት ፓርቲ በዛው አጀንዳ ውስጥ ግብር የከፈሉት አጀንዳቸው የሆኑትን እንጂ ለፖለቲካ ትርፍ የሚሰለፉትም መሆን አልነበረበትም። አሁን አርበኛ ንግሥት ይርጋ ተቀምጣ አቶ ጋሻው መርሻ ለዛውም ድርጅት ጉዳይን? በጸዳ እና በንጹህ መንፈስ መጀመር ነበረበት። ጉዟችሁን በትክክል እከታተለዋለሁኝ። ምክንያቱም እኔ ከእንግዲህ አንድም የጎንደር ልጅ ከአማራነቱ ውጪ እንዲታሰር አንዲገላታ ስለማልሻ። ጎንደር ግንባሩን የማያጥፈው ለጎጃም ህዝብ ብቻ እና ብቻ ነው። ለተጋድሎውን ለደማው ለሞተው፤ ትዳሩን ለበተነው፤  በመከራው ጊዜ ሺህ ልጆቹን ለግብር ላቀረበ ለአብራሃሙ በግ ለእምዬ ጎጃምዬ። ከዚህ ሌላውን ግን እእ ይብቃኝ።

ኦህዴድ ለሁሉም ክፍት የሆነው አቅም ስላለው ነው። እናንተ ምን ተመክሮ? ምን አቅም አላችሁ በራችሁን እንዳሻው ቧ ለማድረግ የፈቀዳችሁ። ገና እኮ ጀማሪዎች ናችሁ። በሴራ ከትሞ ለኖረ ኔት በዝግም አልቻልነውም እንኳንስ አንዲህ ያገኘህውን ሁሉ ዘመዴ ተብሎ ተቀላቅሎ። ይህም ሆኖ አህዴድ በኦቦ በቀለ ገርባ አቀበባል ላይ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዲገኙ አድርጎ ነበር። በሌላ ቃለ ምልለስ ከዶቼቬሌ ጋር በነበረው የኦህዲድ ውክል አካል እጅግ የምመሰጥባቸው አቶ ካሳሁን ኮፌ ሲጠዬቁ ህዝቡ የሁላችን ነው፤ ህዝቡ ደስ ሲለው ደስ ይለናል ነገር ግን ለተፎካካሪያችን መድረኩን ብቻቸውን ልንተውላቸው ስለማይገባ ነው ተወካያችን እዛው ተገኝተው የተልዕኳችን መልዕክት እንዲያስተላልፉ የተደረገው ያሉት። ይሄ አይደለም ገና ጮርቃውን አብን ቀርቶ ዘመንን ያስተምራል። ተፎካካሪ ፓርቲን መንፈስ ከውስጥ ሸጉጣችሁ ፓተንታችሁን እያስረከባችሁ ማሸነፍ? የማይሆን ነው። አባላት እጪዎች የሚመለመሉበት ቁልፍ ቦታ ነው ይሄ ቦታ። በግልጽ ቋንቋ ውሳኔው ዘልዛላ ነው። የአማራ ተጋድሎን አደራንም የሚፈታትን እርምጃ ነው።

ሰማያዊ ፓርቲ እኮ ተፎካካሪ ፓርቲ ነው ለአብን ስልቱን እዬቀደመ ለሰማያዊ ፓርቲ የሚገልጽ ሰው አስቀምጠህ ውድድሩን አሸንፋለሁ ማለት ዘበት ነው። አንድነት እኮ በራሱ ነው ራሱን ያጠፋው። ያገኘውን ሁሉ ከደንብ እና ከሥርዓት ውጪ ቀይ ምንጣፍ አንጥፎ ተቀበለ ይሄው ለሃቀኞችም ሳይሆን እንዲህ ባክኖ ቀረ። ሃቀኞች እራሳቸውን ገብረው መመለሻ ቤት አልባ ነው የቀሩት። ብልጦች ደግሞ ለቀጣዩ ሂደት ባለቀይ ምንጣፍ። አሁንም አብን የሠራው ያነን ተመሳሳይ ግደፈት ነው። በራሱ በተጋድሎው ደም ውስጥ የበቀሉ ታጋዮች እያሉ ሌላ መከራ አምጥቶ ለአማራ እንደጫነበት ነው እኔን የሚሰማኝ። የሆነ ሆኖ ለራሳችሁም ራሳችሁ ፈተና አምራች መሆን ከተፈቀደ ችግር የለውም። ችግሩ ጎንደር ከእንግዲህ ባልጠራ ጉዞ ደም ገብር ከተባለ ብቻ ነው ጠብ የሚኖረው። ቢያንስ የሥራ ሃላፊነቱ አዲስ ሽግሽግ ሊኖረው ይገባል። በግማሹ ትግሬ በግማሹ አማራ የሆነውን ደግሞ ገንዘብ ስለከፈለ ሰብስቡ እና ይህ ደም የተገበረበት ድርጅት እንኩቶ አድርጉት። የምጠብቀው ቀጣዩ ይሄው ነው። ድርጅቶችን አቅም ተፈታትኖ እንዲህ ዕውቅናቸውን ሸርሽሮ ባዶ ያስቀረው ይህን መሰል ሰላቢ ጉዞ ነው። በሸታ የሚድነው ከበሸታው መዳህኒት እንጂ በሽታን ከሸለመው ነፍስ አይደለም።

ጥንቃቄ በእጅጉ ያስፈልጋል። የጀምላ ጉዞ አያስፈልግም። ለሰማያዊ ፓርቲ የአማራ ተገድሎ መከረኞች ምኑ ናቸው? ምኑ? አንድነትን ለማዳከም ተመሠረተ፤ መሥራቾቹን አባረረ አሁን አባወራ ሆኖ አረፈው። ነገ ደግሞ ለሌላው ጥርጊያ መንገድ ከፍቶ እሱ ራሱን ያከስማል። ገና ብቅ ባለው ቡቃያም መንፈሱን በስልት አስገብቷል። ጎርጉሮ ተስጥቶታል ፈረሰኛም ሆኗል ከዛ ያከስመዋል። በመሃል ጅሉ ጎንደር ይረመጣል። ቲያትሩ ይሄው ነው የራስ ተመሰማ ናደው ሌጋሲ ….

አሁን „አንድ አማራ ፓርቲ“ ለ አማራ ተጋድሎ ምኑ ስለሆነ ነው ምስጋና የሚቸረው? ጎንደርን ለመስጨፍጨፍ አብሮ ስላደመ? በአውሮፓው ህብረት ሪፖርት ላይ የአማራ ተጋድሎ ስለተገለለ? በፕሮ ሚዲያዎቹ ላይ የአማራ ተጋድሎ „በነጻነት ሃይሉ“ ስለተሸበለለ? የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር መሥራቾች በባዕድ አገር ለእስር፤ ለስንበት፤ ለስደት ስለተዳረጉ? ምኑ ስለሆነ? ነገ ደግሞ አንጥፋችሁ ጎዝጉዛችሁ ቀይ መንጣፍ ዘርግታቸሁ ተዋህድን ትሉን ይሆናል። ጎንደር እስኪ ምንድነው ያተረፈው? ማን ነው የሚሞተው? የሚታሰረው? የሚፈረድበት? አካሉ የሚጎድልው? ይሄ ህሊና ቢስነት ብቻ ሳይሆን ከንቱ ውዳሴንም መሻት ነው። ሁሉን ወዶ አይሆንም። ከሁሉ ጋር አለመጣለት የተገባ ቢሆን ግን ወገንን አጥርቶ ማውቅ ያስፈልጋል።

ደግሞ በእናንተ ገና ከመፈጠራችሁ እሰጣ ገባ እንጀምርን? ከእነሱ ይልቅ የገዱ የለማ የአብይ የአንባቸው መንፈስ ብዙ አትርፏል - ለአማራ ተጋድሎ አንበሳችን በሙሉ ክብር ከእሰር ተለቋል ኮ/ ደመቀ ዘውዱ። መተንፈሻም የተገኘው አርበኞቻችንም የተፈቱት በእነሱ እንጂ ቃብቲያ ላይ ማሰልጠኛ ጣቢያ አቋቁመናል እንደተባለው በአውሮፕላን ያ መከረኛ ህዝብ ተጨፍጭፎ ቢሆን ምን ሊባል ነበር? የወያኔ ሃርነት ትግራይ ስልቱን ደርሶበትም ይሁን በሌላ ምክንያት ወገኖቹ ከዛ ስላሉ አላደረገውም እንጂ ቢያደርገው ኖሮ ሺዎች ደመ ከልብ ሆነው ነበር። ሪፖርትር ከሥፍራው አልነበረም እኮ። ያ በራሱ ታሪክን ያጠቁራል። ድራማውን ለጊዜው ከድኜ ልለፈው። እንደዛ አይደረገም። ከቦታው ከቀዬው ሪፖርትር ሳይኖር እንደዛ ዓይነት የገድያ የአዬር ላይ ውጊያ … ባልተወለደ አንጀት።
አንድም ቀን ዕውቅና ያለገኘው የአማራ ተጋድሎ አብን ወልዶ አሁን ለእነሱ ምስጋና እና ቃለ ምልልስ? የት የሚያውቋችሁን ነው? እንደ ገና የጎንደር ህዝብ በቁርሾ እና በቁስሉ ላይ ሚጢሚጣ ገና ከመፈጠራችሁ ነስንሱ። እናንተን ዕውቅና ያሰጣችሁ፤ ለዚህ ያበቃችሁ የአማራ ተጋድሎ እንጂ „የነፃነት ሃይል“ ሚዲያ አይደለም። አርበኞቻችን ሲፈቱ ደስታቸው አልነበረም ፕሮዎች በሙሉ። አሁንም ስለምን ተደራጃችሁ ብለው ኤርትራ ላይ ሆነው እያቀራሩ ነው እንደ ለመደባቸው። እዛው በዬተፈጠረበት ጫካው ላይ ተሁኑ ነው መፎከር የነበረበት …

በመኢህድ፣ በኢዴፓ፤ በኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ታይቷል። አሁን እዛ ረግረግ ገብተን እንቦጫረቃልን ብትሉ ዳጥ በዳጥ ነው የምትሆኑት። እፉኝት እፉኝት ነው። ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ ደግሞ እናቱን ገድሎ ነው የሚወለደው። የአማራ ህዝብ እራሱ በዛ ትሁት አንደበት አለስልሰው፤ አክብረው ዝቅ ብለው ለያዙት ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጉባኤም ምን ያህል ፈታኝ እንደ ነበር ታይቷል። ብትደራጁም ከተጋድሎ አንዲት ጋት ፈቅ ማለት ከመጣ ህዝባችን እንነግረዋለን። ኔት አለን ዕድሜ ለዘመነ አብይ። ሌላው ቀርቶ ከእነ አቦ ሌንጮ ለታ ስለምን ለመማር አትሞክሩም። አገራዊ ንቅናቃዌ እራሱ አንድ ሊ/መንበር መወስን ያላስቸዋለው ዋናው ምክንያት ብልጥ ለብልጥ ሆኖ ስለነበር ነው። አሁን ቀድመው የገቡት ምክንያቱ መዋጥን ስላልተቀበሉት እንጂ ለጊዜውማ ግዙን ንዱን ታማኝነት ከእናንት በላይ ላሳር ተብለው ነበር። ከዚህ ተመክሮ የአማራን ተጋድሎ እውክለዋለሁ የሚለው አዲስ ድርጀት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ከልቡ ሆኖ ሊመረምረው ይገባ ነበር። ብዙ ነገሩ መልካም ቢሆነም ዝንቅ አቋሙ ግን ጎንደር እና ጎጃም ለከፈለው መስዋትነት የሚመጥን አይደለም። ጮርቃ ከበሰለ፤ በውል ከተደራጀ ሸር እና ሴራ ጋር የሃሳብ እና የመንፈስ ሃዲድ መዘርጋት ትርፉ ለዛ መከረኛ አማራ ህዝብ ወልቆ መቅረትን ነው የሚያስከትለው። የመከራውን ገፍት የተጋፈጡ አካሎች ውጪም አሉ።

ከሁሉ ከፍ ባለ ሁኔታ ሊመሰገን የሚገባው እንደ ሲቢክስ ድርጀት የአስራትን ዓርማ ያነሳው ሞረሽ ወገኔ ነበር። „የአማራ ድምጽ“ ሚዲያው ግን የእኔም ምርጫ አይደለም የሌሎች ቂም መወጣጫ እና መለበጫ የተሰውረ ፍላጎት መረማማጃ ነው። የአቶ ሞላ አስገዶም ክርስትና ልጅ ነው። አዎንተዊም አይደለም ቂም ሲያመርት ነው ውሎ የሚያድረው። ለነገሩ አዳምጬውም አላውቅም። „ሞረሽ ወገኔ“ በፖለቲካ አደረጃጃቱም ቢሆን ፕሮፌሽናል ነወ አቶ ተክሌ የሻው። በመደበኛ ከፍተኛ አማራር አካልነት የሠራ ሰው ነው። አሁን ይህን „አማራ ድምጽ“ ከመሰረተ ወዲህ አቋም መግለጫው ባይመቸኝም በድርጅት ደረጃ አቅሙን ጠንቅቄ አውቀዋለሁኝ ተመክሮ በዕውቀት የተደገፈ በሳል ልምድ ያለው ሰው ነው።

 እርግጥ ያ ብቃቱን በፍቃዱ በፈቀደው መልክ ምን ያህል የመንፈስ ሃብታቱን እዬቀነሰ ወይንም እዬጨመረ እንደመጣ እራሱ ያውቀዋል። ሞረሽ መሪውም ጎርፍ የቆለለው ፖለቲከኛ አይደለም። ወጥ አማራ ነው መንፈሱም። በዛ ላይ በሳል አደራጅ እና የበቃ የታሪክ ሊቅ ነው። መአህድም እንደ ድርጅት ጥንካሬ ያለው ተግባር ከውኗል የሎቢ ተግባሩ አንቱ ነው። ዛሬ አብሮ የተመሰገነው „አንድ አማራ“ ድርጀት እነሱን ለማጥፋት ጥሮ አልሳካላት ሲል ከራሱ ድርጅት ወጥቶ የተመሰረተ ተለጣፊ የሲኦል ጥሪ ነው ለአማራው። እርግጥ አላዘንኩም። ስለምን? የቁርጡ ቀን ሲመጣ  ስለምሞግተው አብን እራሱን። እኔን ገትቶ ሸፍኖ የሚያሰቀረኝ ፈጣሪ ብቻ እና ብቻ ነው። የሰው ሴራ እና ውግዘት ሆነ አቋርጦ ለማስቀረት ማንም አቅም የለውም። ያማ ቢሆን ብቅ ብለው ካሊማቸውን ደርበው እንደ ተቀመጡት እሆን ነበር። በር ሲዘጋ በመስኮት፤ መስኮት ሲዛጋ በጣሪያ፤ ጣሪያ ሲዘጋ በምድር ውስጥ ለውስጥ መንገድ ተዘርግቶ የግድ ነው ጎንደርዬን ማዳን …

ለአማራው ከኦህዴድ የተሻለ ብሄራዊ የቀረበ ታማኝ ፍጹም ታማኝ የፖለቲካ ድርጅት፤ ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ በላይም መሪ ከቶውንም አያገኝም - አማራ። ተጠንቅቃችሁ ተራመዱ! የአዬር መና ናፋቂ አትሁኑ። ዝብርቅርቅ አታድርጉት ደስታውን። „አማራ ነኝ“ ብሄራዊ መዝሙር ተምጦ የተወለደ በዛ የሞት የሽረት ታገድሎ ነው። አሁንም አማራውን ለግብር ለማሰናዳት ለራስ ተሰማ ናደው ሌጋሲ ግብር እንዲከፍል አታሰናዱት … አቅም አያሸተቱ ጉብታ ተኖሮበታል። አቅሙ ሲከስም ደግሞ አስታዋሽ የለውም። አሁን አርበኛ ሊሊሳ ፈይሳን ማን የት አለህ ይለዋል። ለዛች ወቅት ግን „ሊሊሳን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ“ ተብሎለት ነበር። የአማራ ተጋድሎ እና አርበኞቹ በተገለሉበት ጉባኤም ተጋባዥ እንግዳ ነበር በግዙፉ አውሮፓ አገሮች ማህበር ላይ። „የወጋ ቢረሳ የተወጋ“ አይረሳም የሚሉት ጎንደሬዎች ለዚህ ነው … አሁን እነ አርበኛ ዘመነ ካሴን ማን ያስታውሳቸዋል? ማን? ለሰማያዊ ፓርቲ አርበኛ ዘመነ ካሴ ምኑ ነው? ስደት ለስደት ይንከራተታል? በድጋሚ በጥንቃቄ ተራመዱ። አትቀይጡት የደም ዋጋውን።

ከሊሂቃን እኮ አቶ የሱፍ ያሲን ብቻ ነበሩ የአማራን ተጋድሎ እናዳምጣቸው ብለው የጻፉት አንድ ለእናቱ። እኔ እንደ ጎንደሬ አማራነቴ እሳቸው በሥም ተጠቅሰው መመስገን ነበረባቸው ባይ ነኝ። እኔ እሳቸውን ያዬሁት ልክ እንደ ጎጃም ህዝብ ነው። የአፋር ህዝብ ከጎናችን እንደ ቆመ ነበር የተሰማኝ። ሻማም አብርቻለሁኝ። ወቀሳ በግልጽ ስለጻፍኩኝ በማግስቱ በጉራጌ ዞን አንድ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፤ ነገረ ቤተ - መንግሥት ሆኖ አገር ምድሩን አካሏ መሬት አትብቃኝ ብሎ ነበር፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታዎጅ አቁሙ ተብሎ ቆመ። በሌላ በኩል ግን ፋኖ ቄሮ ዝም አትበል ቀጠለ እየተባለ እንዲረመጥ አንዳንድ ልብ አንጠይጣይ ግፋ ባይ ጹሁፎች ተከታተሉ ከዛም አልፎ ጭልጋ ላይ በሠረገላ ተጎዘን ቅዱሳኑ ጥቃት ፈጽንም ተብልን ነበር። ምን ማለት ነው ይሄ? የራስህን ወገን አቁም ብለህ፤ ሌላ ቦታ አለን እዬተዋጋን ነው፤ ተገድለንም፤ ታርደንም፤ በጥርስ ተይዘንም ሊጠግቡ አልቻሉም። ስለሆነም አዲሱ አብን በደም ግብር ኤንም ቢንም ሲንም እንዳይከፋው አያስኬድም። ታዲያ እንዲህ ለምስጋና ቸር እና ለጋሽ ከሆናችሁ ወያኔ ሃርነት ትግራይን እንኳን ገደልከን ብላችሁ፤ እንደ ብአዴን የባህርዳር አውሮፕላን ጣቢያውን „ግንቦት 20“ እንዳለው እናንተም እንደዛው ስለምን አታደርጉም ነበር?  

ሌላው ቀርቶ አቶ መላኩ ፈንታ የጎንደር ህዝብ አቀባበል አደረገላቸው ብሎ አቤቱ የኢሳቱ ጋዜጠኛ ጭስ ብሎ አቶ ደረጀ ሃብተወልድ ጹሁፍ ጽፏል። ምን አገባህ ቢባል ምን ሊል እንደሚችል አይታወቅም? ራሱን ጨምሮ የተሸከማቸው ተንታኞቹ ጋዜጠኞቹ እኮ አብዛኞቹ እዛው ሲያደግድጉ የነበሩ ናቸው፤ መሪዎቹም ቢሆኑ።

ጎንደር የሚያከብረውንም ፊት የሚነሳውንም አሳምሮ ያውቃል። አስተርጓሚ ሚስጢር ተርጓሚ አያስፈልገውም። ሚስጢር የሆነ ህዝብ ነው። አቤቱ ደረጀ ሃብተወልድ አያፍርም ባህርዳር ላይ ስለተፈናቀሉት እና ከእነሱ ስለተሰጠው ምጽዋት ይነገረናል። አማራ ከብት አይደለም፤ አሞሌ ሲይ የሚስበገበግ፤ ጎንደሬ ግድርድሬ ሲባል አልሰማም እንዴ? ሠርግ በልተው ነው የሚሄዱት ቤተሰቦቻችን፤ እህል ብርቁ አይደለም ለአማራ ህዝብ ግብጽን በህይወት ያኖረው የአማራ መንፈስ ቅርስ እና ውርስ ነው።  ወልቃይት እና ጠገዴ „የነፃነት ሃይል“ እዬተባለ በአውሮፕላን ተጨፍጭፎ ቢሆን ኖሮ እኮ መፈናቀል አይደለም ሞት እኮ ሞት ሲታወጅ የት ነበር ያ መንፈስ። አማራነት አሞሌ ጨውነት አይደለም። አማራነት ማንነት ነው። ደም በአሞሌ አይደለም የሚፈጠረው በውርስ ነው የሚገኘው። የጠራ የአማራነት ደም ያለው አማራ ነኝ ብሎ ለመውጣት የሚያቀትው አንዳችም ነገር የለም። አማራነት ቢያኮራ እንጂ የሚያስፍር ሰብዕና አይደደለም እና። የሚያሸማቅቅም አይደለም። ምን አጥነተን ከማንስ አንሰን? ስለበዛ እኮ ነው የመንፈስ ሃብታች የበታችነት ያለበት ሁሉ ጦሩን በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲመዝ እና ሲያስመዝ የሚኖረው። ተፈሪው ግርማ ሞገሳችን አይሸመትም አይቀናም። ሁሉን ስላልነሳንም ደስ ይለናል። ሐሴትም እናደርጋለን!

የኦሮሞ ፕሮቴሰትን በእጅ ለማስገባት ምን እንርዳችሁ ብሎ ተንበርክኮ የለመነ መንፈስ አማራ ተጋድሎን ለመግደል ግን „ጎንደር ህብረትን“ አጉልቶ በማውጣት ነበር የተጋው። ፈጣሪ ግን እንደ ቤተ - እስራኤሎች ያልረሳው አምላክ በምድርም በሰማይም ቁጣውን እያከተታለ አማራን ደረጃውን አስጠብቆለታል። ወደፊትም ይቀጥላል። ምን አንዳለን? ምን እንደምንችል? ምን ማደረግ እንዳለብን? አሳምረን ፤ አበጥርን፤ አንተርትረን ጠንቅቅን እናውቃልን። የምንፈራውም ለዚህ ነው። „የፈሩት ይደርሳል“ ሆኖ እዬታዬ ነው በዬ አቅጣጫው ራድ እና እንቅጥቅጥ። የአማራ ተጋድሎ ይቀጥላል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ። መፈራታችን እዮራዊነት ነው። ለዚህ ፈጣሪ አምላካችን ተንበርክክን አዘውትረንም እንመሰግነዋለን። የእስራኤል ህዝብም የተፈራው በዚህ ሰማያዊ ጸጋው ነበር። ያን ሁሉ መከራ እና መገለልን የተቀበለው። ዛሬ ግን ቀን ወጥቶለታል፤ ለእኛም የአብርሃም እና የይሳህቅ አምላክ ቃል ኪዳኑን አይነፍገነም። ስላደረገልን መልካም ነገር ሁሉ ቸሩ አምላካችን እናመሰግናለን። ስለወደፊቱም ስለሚያደርግልን የተስፋችን እውንነት እናመሰግነዋለን። አብይን የሰጠን አማላክ ጥበቡ ረቂቅ ነው። ተመስገን!


የአማራ ተጋድሎ ይቀጥላል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ!
የጠራ መስመር ለጠራ ድል ያበቃል!
ቅይጥ ፍላጎት ግን ሾክሽኮ ይገድላል!

የኔዎቹ ለነበረን ቅናዊ አብሮነት ለጥ ብዬ ትሁታዊ ምስግናዬን አቅርባለሁኝ። መሸቢያ ጊዜ።  


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።