የኢትዮጵያ ሃኪሞች ጥያቄ የኢትዮጵያ እንደ #ቀይ #የደም #ሴል ጥያቄ ሊታይ ይገባል። #የፖሊሲ አዲስ ጥሪም አለበት።
ህክምና ሁልጊዜ #በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ነው።
(መጽሐፈ ጥበብ ምዕራፍ፯ ቁጥር ፳፩)

ብልህነት ቢኖር፤ ለህዝብ ርህርህና ያለው መንፈስ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር፤ ህዝቤ የእኔ #ውስጤ ነው የሚል ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ ቢኖር በውነቱ የሃኪሞች ጥያቄ የኢትዮጵያ የቀይ ሴል ጥያቄ ስለሆነ #መሪ አጀንዳ አድርጎ መውሰድ ይገባ ነበር። ህክምና ህንፃ ግንባታ አዬደለም። የሰው ልጅ የትርታ ፋክት እንጂ። የትኛውም የፖለቲካ አቋም፤ ወይንም የፖለቲካ ተቋም እስትንፋሱ የሰው ልጅ ጤንነት ነውና። ይህን በኽረ ጉዳይ #የካድሬ ማሳ ማድረግ አስፈላጊ አይመስለኝም።
ብዙወቹ የብልጽግና ዘመን ሰጥ ካድሬወች፤ በርካታ የግል የሚዲያ ሰራተኞች፤ አክቲቢስቶች እኮ ከአብይዝም ጋር የመጡ ናቸው። አብይዝምን መደገፍ መብት ቢሆንም ተመክሮ፤ ስክነት ሳይሆን እንደ ግል የተሻለ ዕድል ምቾት ላይ ያተኮሩ፤ ወይንም የተጽዕኖ ፈጣሪነት ረሃብተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም ሆኖ አብይዝምን ስለደገፋ ብቻ ጥልቅ እና ውስብስቡን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲተነትኑ የሚሰጣቸው ዕድል ይገርመኛል።
ፖለቲካ የዳማ፤ የካርታ ጨዋታ አይመስለኝም። ግጥግጦሽም አይመስለኝም። የፖለቲካ ሳይንስነቱ ሆነ ፍልስፍናነቱ እራሱ ያንሰዋል ባይ ነኝ። የመኖር 13ኛው #ፕላኔት ፖለቲካው ስለሆነ። ሌላው ቀርቶ በፖለቲካ ተምሮ የመጨረሻ የዕውቀት ዳር ደርሶ፤ መምህርም ሆኖ ካልሰራበት ይልቅ፤ ሳይማር ግን በመደበኛ በሥርዓቱ፤ በደንቡ፤ በዲስፕሊኑ ውስጥ የሠራ ፋንክሽነሪ በብዙ እጅ ይበልጣል። ለደራሽ ፖለቲከኝነት ወጀብ እንጂ የፖለቲካ ጥበብ ጋዳ ይመስለኛል። ሚሊዮን ተከታይ ይኑር፤ የመናገር ጸጋም ይኑር የፖለቲካ የተፈጥሮ ጸጋ በራሱ የመሪነት አቅም ጥራትን ይጠይቃል። በመሪነት ውስጥ ተተክሎ፤ በቅሎ፤ አሽቶ እና አስብሎ መገኜትን በአጽህኖት ይጠይቃል።
መድረክ ላይ ሙሉዘመን ስለተቆዬም ለሚዲያ ጌጥነት መሆን ይቻል ይሆናል። አንድ የፖለቲካ ሰብዕናን የሚሻ ሰው በመንግሥት አሰራር እና አመራር እና ዲስፕሊን ውስጥ መኖር ዕድል ካገኜ ሌላ ማንነት፤ ሌላ ቃና እና ሌላ ጣዕም አለውና። ሥራ ሲጀምር ፈርሞ ይገባል፤ ሲወጣም መውጫ ሰዓት አለው። ዲስፕሊን፤ መርህ ገብ ሁነት ከነፍሱ ጋር ተዳብለው ሳይሆን ተመስጥረው ይገኛሉ።
ለአንድ መደበኛ ሠራተኛ የግምገማ ነጥብ ይሰጣል። ሲቀር የሃኪም ወረቀት ይጠየቃል ወዘተ በዚህ ሁነት ማለፍ የመኖር #ሽልማት ነው። የመብትን ጣሪያ እና ግድግዳ ስለሚያሳውቅ። ፖለቲከኛ ከሆነ ቀድሞ መግባት፤ አምሽቶ ወይንም አድሮ መስራት፤ ዓውደ ዓመታትን ሆኑ ሰንበት ወደ ሥራ ቀንነት ፈቅዶ ማድረግ ሌላ ዓለም ነው። ልዩ የሆነ ማዕዛው ያማረ ጥሪ ነው።
ይህን ፈቅደው፤ ለመታዘዝ፤ ለዛውም በአብይዝም ሥር የበታች ሠራተኛ ለመሆን የወደዱት ፕሮፌሰር ዶር ብርኃኑ ነጋ ትናንት የተቃዋሚውን መንፈስ በዓውራነት ሲመሩ የነበሩበት ሰብዕና እና የዛሬው በተለያዬ ጊዜ ከሚሰጡት ቃለ ምልልስ ዕድገቱን፤ የማስተዋል አቅሙን መረዳት ይቻላል። ቀደምቱን የትግላቸው ምዕራፋትን "#የሞገድ" ፖለቲካ ነበር ያሉት ከሉዓላዊ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ። የፕሮፌሰሩ ውሳኔ እኔ ስመዝነው ከብሄራዊ የአገር መሪነት እራስን ዝቅ አድርጎ #ለመታዘዝ በመንግሥት አብሮ በውስጥነት የመሥራት ፋይዳን ለናሙና እሳቸውን እንደ አንድ የምርምር ማዕከል አድርጎ መውሰድ ይገባ ይመስለኛል። ዕድሉን አላስጨነቁትም።
ብልህነት፤ ማስተዋል፤ ጥበበብ ሚዛን ለራስ ነውና መዝኑት። ሰሞኑን ከዶር ምህረት ደበበ ጋር ያደረጉት እጅግ ረጅም ቃለ ምልልስ አሰልቺ አልነበረም። የኦሮማራ ገጠመኝ የከፈተላቸውን ዕድል አልደፋትም። በተደጋጋሚ ሲያነሱት የምሳማው በዘመነ ግንቦት ፯ ቀድመው ሊከሰቱ ይችላሉ ብለው የገመቷቸው ሦስት አመክንዮችም የምገረምባቸው ናቸው። ቀንም እንበለው ዘመን ሰጥ ዕድላቸውን በብልጠት ሳይሆን በብልህነት ተጠቅመውበታል ብዬ አስባለሁኝ።
በአንፃሩ ፕሮፌሰር ዶር. መራራ ጉዲና በአካልም በተደጋጋሚ አግኝቻቸው አውቃለሁኝ፤ ዛሬም እዛው ላይ #እንደተቸከሉ ናቸው። ለዛውም የፖለቲካ ሳይንስ ሊቅ ናቸው። ተረብ እና ፖለቲካ? አሽሙር እና ፖለቲካ ጋር በቤተኝነት ቀጥለዋል? ተጽዕኖ ፈጣሪን መጠጋታቸውም ትርፋማ ስኬትን አላስገኜላቸውም። አሁንም ሌላ ወጀብ፤ አሁንም ሌላ ሱናሜ፤ አሁንም ሌላ አውሎ ጠባቂ ናቸው።
ሁለቱን የኢትዮጵያ ሊቀ - ሊቃውንታት አንድ የተግባር መስክ ላይ በተመሳሳይ ጊዜ ብታስቀምጣቸው የበለጠ ስኬት በፕሮፌሰር ብርኃኑ ነጋ ታገኛለህ። ዝልቅ ተመክሮ ለ፭ ተከታታይ ዓመታት አግኝተዋል። አዲስ ኢትዮጵያን ጠንቅቆ የማወቅ በር ያገኙ ይመስለኛል። ይህ ዕውነት ነው።
በቅርብ ጊዜው ቃለ ምልልሱም ብዙ በጣም ብዙ ትውልድ ጠቀም ጉዳዮች ተነስተዋል። "ትምህርት ቤት እና #ተማሪ ቤት" ብቻውን ብዙ ይነግረናል። ይህ ውይይት ባይደረግ ሁለቱን አመክንዮወች የመመዘን ዕድል አይኖርም ነበር። ፕሮፌሰሩ የራሳቸውን #አሻራ አስቀምጠዋል በኢትዮጵያ የመንግሥት መዋቅር ሆነ፦ በካቢኔ አባልነታቸውም ሆነ በሚኒስተርነታቸው። ዕድሉን በስልት በመጠቀም አትርፈዋል።
የቅንጅት መራራ ስንብት የመማሪያ ተቋማቸው እንዳደረጉት አስባለሁኝ። እሳቸውን አምነው መሰል እርምጃ የወሰዱ ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ እነሱም አትርፈዋል ባይ ነኝ። ያው በዘመነ አብይዝም በተገደፈው ግድፈት ሁሉ በሚመለከታቸው ጉዳይ ሁሉ ተጠያቂነቱም እንዳለ ሆኖ። መብት ያለግዴት ህልውና የለውም እና።
የሆነ ሆኖ ፕሮፌሰር ዶር. ብርኃኑ ነጋ ያገኙት ተመክሮ ገብያ ውስጥ በጅምላም ይሁን በችርቻሮ የገብያ ህግ የማይተዳደር እናም እንደ ሸቀጥ የማይሸመት ነው። ህይወቱን ሲኖሩበት የሚያውቅ ያውቀዋል። ዕድልን በጊዜ፤ ዕድልን በቦታ፤ ዕድልን በሁኔታ ማስተዳደር መቻል ለእኔ ብልህነት ነው። ዕድሉ ታቅዶም ይሁን በገጠመኝ ይገኝ። ወደፊትም እንደ ጀርመኖች ወይንም እንደ እስራኤሎች የፖለቲካ ልምድ አዲሱ ፓርቲያቸው ኢዜማ ውህደት ሊፈጥር ይችላል #ከውስጣቸው ከተቀበሉት ብልጽግና ጋር። እናም የተሻለ የማድረግ አቅም፤ የበለጠ የመወሰን አቅም በብሄራዊ ፖለቲካዊ ሁለገብ ክስተቶች ላይ ሊያገኙ ይችላሉ።
"ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል" ይላሉ ባለ ቅኔወቹ ጎንደሮች፥ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የብልጽግና አቶ አዳም ፋራኽ ያገኙት ዕድልም ዕንቁ ነው። ፈጽሞ የማይገኝ ዕድል ነው። በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የብሄራዊ ቁንጮነት። ሦስት አራት ዩንቨርስቲ ገብቶ በማዕረግ የመመረቅ ስጦታ ያህል ነው። ብልጽግና አዲስ ነው። ተመክሮም ቢሆን የዛን ያህል ነው። የብልጽግና አፈጣጠሩም የአደረጃጀት መርኽ ጎደሎወች የነበሩበት ቢሆንም በተገኜው ወፍ ያወጣው ዕድል በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ በዲስፕሊን ራስን ገርቶ፦ እራስንም መርቶ መቀጠል እና ዓላማን ማስቀጠል የነፍስ ተቋምነት ነው። ላወቀበት። አዲስ የመሪነት ማንነትም ነው። ላይ ይሁን፤ ማዕከል ላይ ይሁን፤ ታችም ይሁን በፖለቲካ ሥነ - ሥርዓታዊ መዋቅር ውስጥ በመደበኛ መሥራት።
#ወደ ቀደመው ……
የሆነ ሆኖ የሃኪሞች ታጋሽ፤ ትሁታዊ ጥያቄ ቁልፍነትን እና የሳሙና አረፋ ጉዳዮችን በፈርጃቸው ነጥሎ ማዬት ይገባዋል የአብይዝም መንግሥት። ብልጽግና መራሹ የአብይዝም መንግሥት እሱ በእሱ በሆነው የሥልጣን ዘመኑ ኃላፊነትም ተጠያቂነትም ያለበት እሱ ስለሆነ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋታል የሚሉ አካላትም ቢሆኑ በሃኪሞች ጥያቄ ላይ #ሞፈር ዘመት ቢያሰኛቸው ለዕውነተኛ ግባቸው ፈጽሞ አይረዳቸውም።
የያትኛውም ማህበረሰባዊ ጥያቄ የፖለቲካ ጥገኝነት ወይንም ስደተኝነት አዋጭ ምርጫ ሊሆን አይገባም። አስተማማኙ የእራስ አቅምን በራስ ፍላጎት አንፆ መሠረት መጣል ነው የሚጠቅመው። በሌላ በኩል በዚህ ሰበብ የሃኪሞች ጥያቄ ነፃነትን ይጫናል ወከባው። ሊጨነግፍም ይችላል ዕውነተኛው ህሊናዊ ጥያቄ። ሌሎች ብሶቶችም #ታምቀው እንዲቀመጡ ያደርጋል። ለራስ ነፃነት ቀናይ የሆነ ሰብዕና ሁሉ ለሌላውም ሙሉ ነፃነት የመስጠት አቅሙ እኩል ሊሆን ይገባል።
ምክንያቱም የራስ አስተማማኝ አዲስ ሃሳብ፤ አዲስ ተቋም ብቻ ነው እና ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች መሻታቸው ዋስትና ሰጪ የሚሆነው። ይህን ከኦሮማራ ንቅናቄ ማዬት ይቻላል። ግጥምጥሙ አይደለም ዘላቂ እርካታ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊያስገኝ ቀርቶ #መሪው፤ ማዕከሉ ገዱይዝም ሆነ ለማይዝም ጭንቅላቶቹን እንኳን አላሰነበተም። በዛ ንቅናቄ የነበሩ ጉልሆች አሁን ማዬት አልተቻለም። ወይ የአፈር፤ ወይ የካቴና፤ ወይ ስደት ተቀብለዋቸዋል። ኦሮማራ የተንሳፈፈ ፍላጎት፤ መሠረቱ ያልጠነከረ የውስጥነት ተቋም ስላልነበረ። ጥገኝነት ሐረግ ነው። ወይንም #ላንቁሶ ተክል።
የሆነ ሆኖ ተቋም ብቻውን አይቆምም። ማንኛውም ተቋም የሰው ልጅ ያስፈልገዋል። ፖለቲካ ተፈጥሯዊ ነው። መነሻውም መድረሻው የሰው ለሰው ነው። የሰው ልጅ ደግሞ የተሟላ #ጤና ያስፈልገዋል። ለጤናው ደግሞ የጤና ተቋም ያስፈልገዋል። የጤናው ተቋም ደግሞ በሰው ነው ተግባሩ የሚከወነው። እራሱ ሃኪሙ ጤናው ተጠብቆ የሌላውን ጤና ለመጠበቅ #ጤነኛ ሊሆን ይገባል። ሃኪምም እንደ ሰው ያመዋል እና።
ህክምና ወይንም ሃኪምነት የኢትዮጵያ የተስፋ ማዕከል፤ የራዕይ መዳረሻ፤ የትውልድ ዓላማ እና ግብ ነው። ይህ ወሳኝ አካል ቸገረው፤ ከፋው፤ ደህዬ፤ ተጎሳቆለ፤ ተስፋ አጣ ማለት ኢትዮጵያ ቀይ የደም ሴል #አልቦሽ መኖርን አህዱ አለች ማለት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የመኖር የተስፋ ምስባክ በለው #ካስማ ጤና ነው። የጤናው አንበል ደግሞ ሃኪም ነው።
የሃኪሞች ጥያቄ ነጠላ ጥያቄ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። ፋታ የማይሰጡ የሚሊዮን ህዝብ አድን፤ ነፍስ አድን ትርታ፤ ትንፋሽ ጉዳዮች በሃኪሙ የማድረግ አቅም እና ብቃት አሉና። ህክምና ሁልጊዜ #የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሥር ያለ ነው። ድንገተኛ ለህክምና ሙያ መደበኛ ተግባሩ ነው፤ የትንፋሽ መቋረጥ፤ በሰው እጅ የሚከወኑ ቀዶ ጥገና፤ ምጥ ላይ ያሉ እናቶች፤ የልብ ምታቸው ባላንስ ያልሆኑ ዜጎች፤ ወይንም የሚወጣ የሚወርድ የደም ግፊት ያለባቸው ወገኖች፤ በመኪና አደጋ የሚመጡ ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ፤ በእግር ጉዞም ላይ በሚገጥሙ ድንገቴ ሁነቶች፤ በጦርነት ወይንም በግጭት የሚከሰቱ መጎዳቶች፤ በተፈጥሮ አደጋ በመሬት መንቀጥቀጥ ይሁን በውሃ ሙላት የሚከሰቱ ኩነቶች፤ ይህም ብቻ አይደለም ለጉብኝት ይሆን መደበኛ የሥራ ቦታቸው ኢትዮጵያ የሆኑ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የጤንነት ዋስትና ማዕከሉ የጤና ባለሙያው ነው።
ይህ ማለት ለእኔ መኖር በኢትዮጵያ ውስጥ በቀጥታ ከሃኪሞች መንፈስ ጋር በጥገኝነት ሳይሆን #በውህደት ያለ ክስተት ነው። ስለዚህ ብልህ አመራር፤ አዲስ ታክቲክ እና ስትራቴጂ ያስፈልገዋል ማለት ነው። ባለፈው ጹሁፌም አንስቸዋለሁኝ የኢትዮጵያ የካቢኔ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ በችግሩ ላይ ያስተዋለ የተግባር አቅጣጫ ሊነድፍለት ይገባል።
በቀጣይም ቀጣይ ጥያቄወችን እንደሚመጡ ታሳቢ ያደረገ ጥናት ሊደረግበት ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ የጤና ሚኒስተሯ፤ ዶር መቅደስ ዳባ በሰጡት ቃለ ምልልስ የሚሊዮኖች ትርታ ጋር የተወሃደው ጥያቄ የመፍትሄ አቅም ያለው ሆኖ አላገኜሁትም። ለጤና ሚኒስተሩ ተቋምም ከአቅሙ በላይ ይመስለኛል። ብሄራዊ አዲስ #ፖሊሲን የሚጠራ ወይንም የሚሻ አመክንዮዊ ክስተት ሆኖ ነው እማዬው። የሊቀ ሊቃውንት ጥያቄ በሙሉ አቅም ላይ ያለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አንዳንድ ጊዜ ራስመር ጥያቄወች ይፈጠራሉ። ለዚህ መሰል ራስመር ጥያቄ ሙሉ መንፈስን መፍቀድ ይገባል። የመዋለ መንፈስ ቁጠባ፤ መንቆጣቆጥ፤ ማቃለል፤ ማግለል፤ ወይን የሆነ ካልተገባ ጉዳይ ጋር አነካክቶ መለጣጠፍ አያስፈልግም። ፖለቲከኝነት እኮ የዘመኑን የፖለቲካ ባህሬ ከውስጡ መረዳት ነው። መጀመሪያ በቂ ግንዛቤ። ለግንዛቤው ጥሞናዊ ጥናት። ለጥሞናዊ ጥናት ብልህ እና የሰከነ አቅጣጫ። ለአቅጣጫው በራሱ የተማመነ የማድረግ አቅም ይጠይቃል። በተለይ ጥያቄው የወል ሆኖ ነጥሎ ቂም ቋጥሮ ስጋት፤ ቅጣት፤ በቀል በአብይዝም የአገዛዝ መዋቅር ሊኖር አይገባም። ይህም ዘርፍ ለእኔ ስጋቴ ስለሆነ።
ይህን መሰል ክስተት በተፎካካሪ ይሁን በተቃዋሚ ፖለቲከኞች መነሳቱ ሁሎችም መደበኛ ሥራቸው ነው። ሰውኛ ተቋማትም መደበኛ ሥራቸው ነው። ግዴታቸውን ለሚወጡ ሩህሩኃን ሚዲያወችም የአትኩሮታቸው አቅጣጫ ማድረጋቸው የተገባ ነው። ግራ ቀኙ ማሳውን ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ተፈጥሯዊ ነው። አንዳንዱ አግንኖ ሊያሟሙቅ፤ ሌላው በኮፒራይት ሊታመስ ይችላል። ሸማ በየፈርጁ ሊሆን ይገባል። ንጹህ ትሁት ጥያቄን የአብይዝም ሥርዓት የእኔ ግዴታ ብሎ ሊቀበለው ይገባል።
ወሳኙ ጉዳይ ጠቃሚው አገር በቀል የሆነው የመፍትሄ አማራጭ በዘለቄታ ረሃበን፤ የመኖር ዋስትና ይሰጠን የሚለው በትዕግሥት የለመለመ፤ በትህትና የተቃኜ፤ በሰላማዊ ውስጣዊነት ላይ ያተኮረውን ጥያቄ በተሻለ ያስተናገደው ለራህቡም፤ ሆነ ለቀጣይ የመኖር ዋስትናም ከቂም፤ ከጥላቻ ከበቀል በፀዳ ሁኔታ መልስ የመስጠት አቅም ያለው ማነው ከሚለው ይሆናል። ድርጊት እና ዊዝደም ለጥያቄው በቂ ምላሽ ይኖራቸዋል። ይህ ከማን፤ ከዬትኛው አካል አለ ነው ቀዳሚው መስመር።
ፋክክሩ ጤናን ጤናማ ሂደቱ ይቀጥል ዘንድ ብልጥነት ሳይሆን፤ ክስም ሳይሆን፤ ማጣጣልም ሳይሆን ዕውነት - ገብ፤ ፋክት - ገብ ጤነኛ ውሳኔ እና ገቢራዊ ግብረ ምላሽ መስጠት ይገባል። ጥያቄው በፆታ፤ በዞግ፤ በሃይማኖት፤ በፖለቲካ የአቋም ልዩነት፤ በዕድሜ፤ በትምህርት አቅም፤ በሙያ ወዘተ ልዩነት ሊመደብ አይችልም። ከሊቅ እስከ ደቂቅ 120 ሚሊዮን ህዝብን ይመለከታል። ጥያቄው ለኢትዮጵያ ቀይ የደም ሴል ነው። ስለዚህ የሰከነ አትኩረታዊ አቅም ይጠይቃል። ለጥያቄው ምላሽ እና ስኬት ገቢር ላይ ተሽሎ መገኜት ነው። "ላም አለኝ በሰማይ፤ ወተቷን የማላይ" መፍትሄ አይሆንም።
ማህበረ ቅንነት እንዴት አደራችሁ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/05/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ አያስፈልገውም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ