የሰኔ 16ቱ 2010 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ክሽፈት።

የሰኔ 16ቱ የ2010 መፈንቅለ 
መንግሥት ሙከራ ክሽፈት 
እና ቀጣይ ዕጣ።
ከሥርጉተ © ሥላሴ 27.06.2018 
(ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)
„እኔ በእድሜ ታናሽ ነኝ፤ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤
 ስለዚህም ሰጋሁ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁኝ።“
 (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ ፴፪ በቁጥር ፮)


  • ·       እፍታ።

ብዙ ሰው በጠ/ሚር አሜኑ አብይ አህመድ ላይ ብቻ የተቃጣ ጥቃት አድርጎ ነው የሚገምተው። አብረዋቸው የነበሩትን የካቢኔ አባላትን ሳይ እኔ በጣም የሚቀርቧቸው ከሳቸው ጋር ለመስራት ሙሉ ፈቃደኛ የሆኑትንም በአንድ ላይ ለመፍጀት እንደ ታሰበ ነው የሚገባኝ። መቼም ከጠ/ ሚር አሜኑ  አብይ አህምድ ጋር ለመሥራት ትልቁ መሥፈርት ሌት እና ቀን እንደብረት መትጋት የግድ ይላል። ይህን በቀደመው ጊዜ በሚገባ አብራርቼ ጽፌዋለሁኝ። ሰውዬው ሰርተው የሚደክሙ አይደሉም። የጸሐይ ጉልበት ያላቸው ጉደኛ ፍጥረት ናቸው። ይህን ፈቅደው በሚተጉት ላይም ወያኔ ሃርነት ትግራይ ከአቅሙ እና ከቁጥጥሩ ውጪ በላይ መሆኑ እረፍት አይሰጠውም። የትኞችንም አይፈልጋቸውም። 
  • ·       ራት ፍጥነት ብቃት በሙሉዑነት።

ገራሚው ነገር የሥራቸው ጥራት እና ብቃት ፍጥነት ስኬት በድምሩ ሲታይ ደግሞ Quality የሚባል ዓይነት ነው። የረገጡት ሁሉ ለምለም ነው። የነኩት ሁሉም የተሳካ ነው። የአሮን በትር እንደሚባለው። ይህ ደግሞ የዛሬ አይደለም። በተገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ የተሰካ ውጤትን የሚያስመዘግቡ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች አሉ፤ ተራራን ንደው ለጥ ያለ ምቹ አስፓልት ለማድረግ የተሰጣቸው። ሰዉ ሳይገባው የከረመው ይሄው ልዩ የጸጋ ሚስጢር ነው።

በኤርትራውያን ዘንድ ይጎዘጎዛሉ ብዬ ጽፌ ሁሉ ነበር። ያደረጉት ንግግር እጅግ የሚገርም ነበር። እንኳስ ለኤርተራ ህዝብ ለዓለም ህዝብ ታላቅ የተመክሮ ት/ ቤት ነው የከፈቱት። እኔ ደስ የሚለኝ ይህን አቅማቸውን  የዓለም አቀፉ ማህብረሰብም እንዲዩት ፈጣሪ ስለፈቀደልኝ ነው። በዚህ ሉላዊ ዓለም በዬደጁ ይህ መልካምነታቸው ቤተኛ ይሆናል። በዓለም ላይ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ለሰላም ልዩ ፍቅር ያላቸው። እውነት ለመናገር ወንዞች ተራሮች ሳይቀሩ በድጋፍ ነው የሚቆሙላቸው እንኳንስ የሰው ልጅ። 

ስለምን? በሰው ልጅ የሚደርሰው መከራ ሁሉ በወንዞች፤ በተራሮች፤   በእጽዋት፤ በእንሰሳትም ላይም ስለሆነ። መሬት አፈር ራሷ ተጠቂ ናት በጦርነት ትንዳለች፤ ደም እንድትጠጣ ትግደዳለች። እርግጥ ነው የዲያቢሎስ መንፈስ ያለቸው ያው ሸቀጥ ላይ ነው ትጋታቸው እና ስለሰው ሰውኛነት እንብዛም ስለሆኑ ይህ ንጹህ መንገድ ይመራቸዋል። ይጠዘጥዛቸዋል። ያንገሸግሻቸዋል። ያሳብዳቸዋል።
  • ·       የጥንካሬው ፈቃድ።

እኔ እንደማስበው ዘመናቸውን ሁሉ የተዛጋጁበት ነው የሚመስለኝ። ሲናሪዮም ቢጋርም አዘጋጅተውለት የቆዬ ነው ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱ እንዲዚህ ዓይነት አለቃ ገጥሞኝ ስላማውቅ። ጓድ ገብረመድህን በርጋ እንዲህ ነበር። የረጋ፤ የሰከነ፤ የማድመጥ ክህሎቱ የምድር የማይመስል። ሁሉም ነገር በመሰናዳት የሰከነ የከበረ ነበር። ይህን በንግድ ሚ/ር ቋሚ ተጠሪ በነበረበት ጊዜም፤ የጎንደር ክ/ሐገር የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ በነበረበት ጊዜም፤ በሚዛን ተፈሪም አንደኛ ጸሐፊ በነበረበት ጊዜ አብረውት የሠረቱ ይመስክሩታል። መቼም ሰው በህይወቱ እድለኛ ሲሆን በቻ ነው ከእንዲህ ዓይነት ሰው ጋር የመሥራት አጋጣሚ የሚኖረው። ራስ እግሩ ዩንቨርስቲ ነው። 

አሁን የሚደንቀው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የአገር መሪ ስለሆኑ ከሳቸው ጋር ዕድል አግኝቶ የሚሠራው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቀደም ብዬ በተለያዬ ሁኔታ በጹሁፌ እንደገለጽኩት ሰናፉ // ፋውሉ//  ስልቹው // ሌባው ሳይሆን ግን ሥራ ህይወቱ - አገሩ - ሰንደቁ ላደረገ ሁሉ ቀን ወጥቶለታል ብዬ አስባለሁኝ። አላዛሯም ኢትዮጵያ። „ማገልገል“ „ከመደመር“ ባለነሰ የህይወታቸው ዶግማ ነው።  መቼም በህይወት ምን ያስደስትሻል ብባል እኔ ከመጻፍ ባልተናነሳ የማይደክው አለቃ ነው የምለው።

ዛሬ ኢትዮጵያ እኮ ያለው አዳዲስ ነገር ውጦናል ማለት ይቻላል። ምኑን ይዘን ምኑን ማንሳት እንዳለብን ሁሉ እስኪቸግረን ድረስ። እጅግ የሚገርም እጅግ የሚደንቅ ዕውነትም የማይምስል ድርጊት ነው እዬተከወነ ያለው። እያንዳንዷ እስተዛሬ የባከነችው የማድርግ፤ የመሆን ደቂቃ ሁሉ ጥቃት አውጪ በጥበቡ ፈጥሮላታል ለ ልዕልት ኢትዮጵያ። አላዛር የምላትም ለዚህ ነው። እራስ እግሯ ቁም ነገር ናት ሰከንዷ ሁሉ። መደነቀ ከሚባለው ያለፈ ነው።

ስለዚህ ይህን አቅም ለመስበር አንድ ሰው ብቻ በማስወገድ ይሳካል ብሎ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አያልምም። በፍጹም፡፤ ካቢኒውን ማፍረስ ነው ዒላማው። ለዛውም አሁን እኮ በዝንቅ ነው ያለው። ማን ተማን መለያ ማንዘርዘሪያ የለም። ሆድ አደሩን ጨምሮ ሌባው ዘራፊው ሁሉ ማህብርተኛ ነው ኢትዮጵያን በቁም ለመግደል። 

በጠራ መንፈስ እና አቅም ሙሉ ለሙሉ በጠ/ ሚሩ መንፈስ ውስጥ የሚፈጠረው ካቢኔ  ራሱ እኮ ገና ነው። ይህም ቢሆን ባጠገባቸው ያሉት የቅርቦቹ ደግሞ ውስጥ ለውስጥ የተገናኘ የጥራት የመደማመጥ መስመር ያለ ይመስለኛል። አሁን አሁን እንዲያውም የበረከት ጋንታ በአቶ ደመቀ መኮነን ላይ ሰፊ የሆነ የስለላ ሥራ እንደሚሰራ ነው የሚሰማኝ። የሁለቱ ግንኙነት ያስፈራው ብቻ ሳይሆን ያራደውም ሁኖ እዬታዬኝ ነው።

አሁን ላይ እኔ ለአቶ ደመቀ መኮነን የተለዬ አዎንታዊ ዕይታ እዬኖረኝ ነው። ስለምን? ይህን ለውጥ እንዲቀጥል እስከተጉ ድረስ እና ለዶር. አብይ አህመድ የጀርባ አጥንት እስከ ሆኑ ድረስ ለምትናፍቀኝ ኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ናቸው ብዬ አምናለሁኝ። ከሁሉ በላይ እራሳቸውን ከጠ/ ሚር እጩነት አግለዋል። ይህ ድምጽ እንደይከፋፈል አድርጓል። በሰፊ የድምጽ ልዩነትም ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እንዲመረጡ አድርጓቸዋል። በሌላ በኩል እሳቸው ም/ ጠ/ ሚር ሆነው ከላይ ዶር አብይ አህመድ ደግሞ ከታች ሆነው ሠርታውል። በዚህ ዘመን የበታችህ አለቃህ ሆኖ አብረህ ለመሥራት መትጋት መፍቀድም ይህም ሌላ ጸጋ ነው። ሆኖም አያውቅም። ሳታኮርፍ፤ ሳትናኮል፤ ሳታድም፤ ሳቦታጅ ሳትሰራ፤ ሴራን ሳትተባበር ... የሚገርም ሰብዕና ነው። 

ስለዚህ ጥልቅ የሆነ ተመስጦ እንዲኖረኝ አድርጓል። እርግጥ ነው እሳቸውን በሚመለከት በአማራ ጉዳዮች ላይ ድፈረት እንደሚያነሳቸውም፤ የረባም የባለቤትነት ስሜትም፤ ተቆርቋሪነትም እንደማይሰማቸው ባውቅም ለአጠቃላይ ለለውጡ ያላቸው ቅናነት ግን ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲቀጥል ብቻ ሳይሆን ምንም ሳንክ እንዳይገጣመቸው እጸልይላቸዋለሁኝ።

በዛ ላይ የበታች ሲሆኑ ለሚያኮርፉትም ታላቅ ተቋም ከፍተዋል። እንዲሁም የበታችም፤ የባላይም መሆንን እንዲህ በጸጋ ማስተናገድም ሌለው የጠራ ሰብዕና ነው። ለኢትዮጵያውያን አዲስ ምዕራፍ ነው። በዚህ ላይ ለዚህ የመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላ ኤርትራ ህዝብም፤ እንዲሁም ለመላ ዓለም ሰላም ወዳድ ህዝብም ቢሆን ለደስታው እኩል የሚችሉትን ለመድረግ በመታተር ተጋድሎ አድርገዋል። ወሸኔ ነው። ማለፊያ አቅም ነው የሆኑት። ይህን መሰል ንጽህና እና የሊሂቃኑ ቅንነት በማጣችን ነው አቅም ብቅ ባለ ቁጥር በዘመቻ እያደቀቅን በታቱ ስንቆዝም የኖረንው … መከራችንም ያበራከትነው። 

ስለዚህ የቅዳሜው የጥቃት ሰለባ አንድ ነፍስ ብቻ ሳይሆን ለሙሉው፤ እዛ ለነበሩት የአብይ መንፈስ ካቢኔ የታቀደ ነበር ብዬ ነው የማስበው። እንደ ድርጅትም ለኦህዴድ እና ለገዱ መንፈስ። የካቢኔው እዛው ላይ መቅረት ብቻ ሳይሆን በታቀደው መልክ እቅዱ ሙሉ ለሙሉ ቢሳካ ኢትዮጵያ የሶርያ መሰል ዕድል ይገጥማት ነበር ያለጥረጥር። አዲስ አበባም መንግሥት አልባ ትሆን ነበር። በዚህ ማሃል የታጠቀው፤ በቅጡ የተደራጀው፤ ደህንነቱም የጸጥታው ሃይልም በእጁ ያለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሙሉ ለሙሉ ሁሉንም በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል አፍታ አይፈጅበትም ነበር። 

ከዛ ሁሉም እስር ቤት ቲፍ ብሎ በበቀል በሰከሩ ካድሬዎቹ ይጥለቀለቅ ነበር። ቀጣይ ተስፋ አይኖርም ነበር። 
   
ስለሆነም እኔ ጥቃቱ የመፈንቀል መንግሥት ሙከራ ነበር ነው የምለው። አንድ መሪ ብቻ ላይ ጥቃት ፈጽሞ የሚቆም በፍጹም አልነበረም። በፍጹም። አስቀድመው የነበሩ ቅደመ ሁኔታዎችን ላይ ስንነሳም ግብረ ምላሹ የሚያመልክተው ይሄው ነው። ይሄ በሃሳብ ደረጃ ቀድሞ የተጠና ቢሆንም፤ አጋጣሚው ምቹ ባለመሆኑ በተንጠባጠበ ሁኔታ በዬአካባቢው ይህን መሰል ጉዳይ እኮ ነበር ከጨለንቆ ጀምሮ ያሉትን ነገሮች ስትመለከቷቸው። ይህን የለውጥ መንፈስ ለመግታት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥርዕወ መንግሥት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።
  • ·       ጥድፊያ።

በመሃል ከደቡብ ህውከት በኋዋላ ደግሞ  ይህ የምስጋና ቀን ተሰረነቀ። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ተንቦላ ነበር። ደጋፊውን ሁሉ ተሰበባስቦ፤ ካቢኔውም እንዳለ በሙሉ አቅሙ ከነሙሴው የሚገኝበት ሁኔታ ተፈጠረ። ለዚህ ነበር እኔ ያለሰከነ ነው፤ እርጋታ ያንሰዋል፤ ጥድፊያ አያሰፍልግም፤ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ ይቻላሉ፤ ስለዚህም ቢቀር ምርጫዬ ነው ብዬ ጽፌ የነበርኩት።

አያድርገው እንጂ ሞት ብቻ እኮ አይደለም ሊገጥም የሚችለው። ጸሐፊ ምስባከ ወርቁን ማዬት ብቻ ይበቃል። እያለህ ቁመህ እዬሄድክ የማትኖር የማድረግ። እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ስከንት ብቻ ሳይሆን ጥበብ ያንሰዋል። የምሰማው ሁሉ ይመጣል ብሎ አንድም ሰው አስቦት አልነበረም። ይህም መቼም እጅግ አሳዛኙ ገጠመኝ ነው።

እንኳንስ ወያኔ ሃርነት ትግራይን የመሰለ አውሬ ድርጅት አስቀምጦ ቀርቶ በሰላም የሆነ ሁኔታ እንኳን ቢሆን ይሆናል ብሎ አስቀድሞ መተንበይ ግድ ይላል። የፖለቲካ ህይወት እኮ እንዲህ ነው። ሁለጊዜ ጠንቃቃ መሆንን ይጠይቃል። ወለም ዘለም ያለ በዛው ነው የሚቀረው። ያጣናቸው ሊሂቃን እኮ በዚህ መልክ ነው። ግዴለሾች ስለነበሩ። በዬደቂቃው በቅናት የሚያብዱ እርኩም መንፈሶችም ሳንክ ከመፈጠር አይተኙም። ምንም ቢሆን ምንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሴራ የጸዳ አዬር መጠበቅ ፖለቲካው የሰብዕና ብልህነት በእጅጉ እንደሚንጠው ያመላክታል። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። የግድ ወያኔ ሃርነት ብቻ አይደለም ... አቅም የለሹ ሁሉ አይተኛም። ከ እጁ ያመለጠው ዕድል ያባትተዋል። 

አንድ ተቋም አንድ ድርጅት ነገሮችን ሲያቅድ ጥቅም እና ጉዳቱን መመዘን ይገባል። ይህ አብዮት ተቀልብሶ ቢሆንስ ብሎ ማሰብ ይገባል። ሃሳቡ የተቀደስ ቅን ቢሆን ነገር ግን ፋታ ያስፈልገው ነበር። ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልገው ነበር። የተመረጠው ጊዜ ትክክለኛ አልነበረም። መረጋጋት የተሳነው ነበር። ችኩል እርምጃም ነበር። ደቡብ ላይ ያን የመሰለ የህዝብ ዕንባ በተደመጠበት ማግስት እሳቸውም ከብክንት ውስጥ እያሉ ተጨማሪ የቤት ሥራ መፍጠር መልካም አለነበረም። 

የጊዜ ምርጫው የጥንቃቄው ሁኔታ የተገባውን ያህል ስክንት አልነበረበትም። መሰናዶውም ያን ያህል ነው። ጸጥተውን እንኳን መምራት ያልተቻለበት። አሳዛኝ ነው። ዝግ ተብሎ በሰከነ ሁኔታ ቢዘጋጅ እኮ ካለመስዋዕትነት መፈጸም ይቻል ነበር። ቢያንስ መስዋዕቱን መቀነሰም ይቻል ነበር። ይህን ያህል በጥድፊያ ሠረገላ ከምንከንፍ …

ድል እኮ ለማግኘት ድሉን ለማቆዬት የሚያስችል አቅም፤ የእኔ የምትለው መተማማኛ በእጅህ መኖር አለበት። ሁሉም ነገር እኮ በወያኔ ሃርነት ትግራይ መዳፍ ውስጥ ነው ያለው። እኛ ያለን እስክሪቢቶ ወይንም ማይክ ነው፤ ለዛውም ይህ የለውጥ መንፈስ ልክ እንደ ወያኔ ሃርነት እንደ ጦር የፈራነው፤ በተገኘው ሁሉ መድረክ ያብጠለጠልነው ነው። „አስመሳይ ነው አብይ“ ብለን የለምን? „ሥርነቀል ለውጥ ነው የምንሻው“ „ጉልቻ ቢለዋወጥ“ ብለን አልነበርንም? ቀድሞ ነገር መቼ እረክተንበት ለመሆኑ? ሰባራ ሰንጠራ ስንለቃቅም አይደለምን የባጀነው? „አይዞህ“ ቃል መቼ ትንፍሽ ብለናት?
  • ·       የሚቀድሙ ነገሮች።

የሚቀድሙ ነገሮች ነበሩ። ራስን መግራት፤ ራስን ማወቅ፤ አቅምን መረዳት፤ አቅምን መሰብሰብ፤ ወዳጅ ጠላትን ማወቅ፤ የሃይል አሰላለፉን መመርምር፤ እኛ በዚህ ሁሉ የለንም፤ አልነበረንም Absence ። አሁንም በዬቦታው ሽሚያ ነው ባለሻንፕዮን ለመሆን። የድጋፍ ስልፍ ከማዘጋጀት ለእኔ የመንፈስ ስንቅ ቤተኛ መሆን ይቀድም ነበር። በሆነ ባልሆን ስትተረትር እዬዋልክ የድጋፍ ሰልፍ ዝግጅት። ብቻ ፈጣሪን እግዚአብሄር የሚወዳት በመሆኑ ሰማዕታትን ገብረን፤ ቁስለኞችን አሰቃይተን የሆነው ሆኗል። የሰው ብርንዶ አቅርበን። ለወደፊቱ ግን መስከን ያስፈልጋል። መርጋት ያሰፍልጋል። ይመጣል ሊሆን ይቻላል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።  
  • ·       አደጋ ቀጣይነት።

የአደጋ ቀጣይነት አይቀሬ ነው፤ ግን ትግራይ መሬትን አይነካም። ይህ አይሞከረም፤ በጅሉ በሌላው አካባቢ ነው እንደ ጥንቸል ሙከራ የሚደረገው። ይህን ነው ደቡብም፤ ሱማሌም፤ ጉምዝም፤ ጅማም ያልተረዳው። ስለምን? ባዕታቸውን የሰላም አንባ አድርገው ሌላውን ስለምን ያምሱታል የሚለው ከቁጥር የገባ ጉዳይ አይደለም። የሴራው ባለንባራሶች እንሱ ስለመሆናቸው ከዚህ በላይ ማረጋገጫም ፈጽሞ የለም። ሌላ ቦታ ነው ህዝብም የሚፈናቀለው፤ የሚሞተው፤ የሚጎዳው ... 

አሁንም ቀጣይ ጥቃት በተለያዬ መልክ ይቀጥላል። ወያኔ ሃርነት ትግራይ መርዝ ነው። ሌላው የሶሻሊዝም መርዝም አለ። እኛ አንችልም፤ ሌላው ችሎ የሚያደርገውን ደግሞ ጠላቱ እኛው ነን። እኛው እራሳቸን የራሳችን ራዕይ ጠላቶች ነን። የሚገርመው ነገር ስንታገለው የነበረው የርህርህርና መንፈስ አንድ ነገር ሆኖ ቢሆን ምን የቱ ላይ፤ ወይተኛው ጎራ ላይ ልንሰለፍ እንደምንችል ይተዋቃል። "አዛኝ ቅቤ አንጓች" ነበር የምንሆነው። ምክንያቱም በድጋፉ ውስጥ አልነበረንም ጭራሹኑ። ሸፍተንበት ነበር። በግብር ይውጣ ሠረጋላ ተለብጠን ነው … „እንዳያም ጥራው እንዳይበላም ግፋው“ ላይ ቸክለን የነበረንው። የተሰረዘ ተስፋ የሚያስቆረጥ ሁኔታ ነው የነበረው።

አንድ ጊዜ አንድ ቅን እጅግም የርጋታው ነገር የሚመስጠኝ፤ ባለጥሞና ወንድሜ „እኔ በዶር አብይ አህመድ ሥራ ደስተኛ ነኝ ግን ሥርጉተ ደጋፊዎች እያነሰን ነው“  ብሎኝ ነበር። እኔም አይዞህ አያስፍሩንም ብዬውም ነበር። አሁን ሊማሩ ቢችሎ የሟርት ዜና ወኪሎች የብዕሮችም የባለማይኮችም መሬት እዬደበደቡ ማዕት ናልን የሚሉት ሁሉ ሚሊዮን ህዝብ እንዴት ለዚህ ቅዱስ መንፈስ ፍቅር፤ እክብሮት እንዳለው ማዬትም፤ ማረጋገጥም ይቻላል። ዛሬ ሳይ ነበር አንዲት እናት እንዴት እንደሚመርቋቸው። እና ሚሊዮኖች እዬሞቱ፤ እዬደሙ፤ አካላቸውን እያጡ፤ ልጆቻቸውን እያጡ እንኳን አይዞህ  የእኔ አብይ ነው የሚሉት መቼም ሰይጣን መሆን አለበት ይህን የምልዕት መንፈስ ማድመጥ የተሳነው።
  • ·       ማጠቃለዬ

በመግደል ብቻ የሚቆም አልነበረም የነበረው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው። ለጊዜው ከሽፏል። ወደፊት አይኖርም ማለት ደግሞ አይቻልም። የአውሮፕላንም፤ የመኪናም ፤ የምግብ ብክለትም አደጋ ይኖራል። ስብሰባ ላይ የሰጧቸውን ነው የሚጠጡት ዶር አብይ አህመድ። ሰው የማመንም ልክ አለው። የሳቸው ግን ከልክ በላይ ነው። ትንሽ አይጠራጠሩም። ልብ ይስጣቸው ሌላማ እኔ ምን አቅም አለኝ እና ... 

ወደ ዋናው ጉዳዬ ምልሰት ሳደርግ ለመሆኑ 4ኪሎን ማን ያላሰላ ኖሮ ነውና? መጨረሻቸውን ያሳምርላቸው እንጂ በህይወቴ እኔ ያዬሁት ቀደመ ባለው ጊዜ ኮ/ ጎሹ ወልዴ ዛሬ ደግሞ ኦቦ ለማ መግርሳ ብቻ ናቸው፤ በዚህ በወንበር ጉግስ ላይ ቅድስናም፤ ንጽህናም፤ ሰምዕትነትም ያዬሁት …

ራትን ዝቅ ብለው የፈቀዱ እነዚህ ከነብይም ነብይ የሆኑ ንኡዳን ብቻ እና ብቻ ናቸው። ፈጣሪ ለትውልዱ ተቋም ከፈተ ቢባል እነኝህ ሁለት ሊሂቃን ቃለ ወንጌል / ቁራን ያህል ለትውልዱ ቅዱስ መንፈስን አውርሰዋል።

የቀድሞው ጠ/ ሚር አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝም የወሰዱት እርምጃ ቀላል አይደለም። ለዚህ ፍሰሃ እና ሰናይ ጉልላት ናቸው። ተተኪው ትውልድ ሥልጣናዊ በሸታ ተጠናውቶት እንዳያድግ ሰፊ መድረክ በዚህ ዘመን ተከፍቶለታል። የሚቀረው ቋሚ ሥርዓት መመሥረት ነው። ለዚህ ደግሞ በትረ ሙሴው ዓላማቸው ነው። አይደለም ለእኛ ለአፍሪካ የሚተርፍ ናሙናዊ ድርጊት ይከወናል።

እኛ ጋናን ደቡብ አፍሪካን አንጋጠን ስናይ ከዛም የተሻለ፤ ሥልጡን፤ ብቁ፤ ብልህ እና ጥበብ የሰፈነበት፤ የረጋ እና የሰከነ ሁኔታ ምድራችን ታገኛለች። ብቻ ህይወታቸውን እስከ ካቢያኒያቸው ይጠበቅልን። ጠላቶቻቸውን የዶግ አምድ ያደርግልን ፈጣሪ አምላክ። አሜን!

በተለይ አሁን ማን ምን እንደሆን አይታወቅም። ተቀላቅሏል። ስለዚህም አደጋው ሰፊ ነው። ልብ የሚያስጥልም አይደለም። የመጀመሪያው ደወል ተደውሏል። የሚገርሙኝ ለቀጣዩ የትግራይ ትውልድ ብጣቂ ልብ ያልራላቸው ግብዞች መሆናቸው ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የማፌስቶ ማህበርተኞች። ሲከር እንደሚበጠስ ሲሞላ እንደሚፈስ ልብ አላሉትም። ሰው ከሚችለው በላይ ከሆነ ትዕግስቱ ከባድ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እኮ ስለላፈው ይቅር ማለቱ እኮ የታምር ነው። ቅዱሳኑም፤ መላዕክታኑም አያደርጉትም። 

ሌላው ግን ... ብቻ የሰማይ ቁጣ ከመጣ ቦንብም፤ ፈንጅሚ አያስቀረውም … ያን ነው እኔ የምፈራው … መታበይ ጥሩ አይደለም። የሰውም ግፍ አለው። 43 ዓመት ሙሉ በሰው ስቃይ መፈረሸ። ያሳዝናል።

ታገድሎው ይቀጥላል። ጸሎቱን ስግደቱን ሱባኤውን ምህላውን ማድርግ ደግሞ አቅም ካላቸው ይጠበቃል። የኢትዮጵያ እናቶች የ43 ዓመት የእንባ ዘመን በውል ውል ይዞ ዘላቂ ሥርዓትን በቋሚነት መገንባት እንዲቻል።

እቅምን አውቆ አቅም እንደሚራ መፍቀድ ደግሞ የልቦና ጉዳይ ነው። የትውልዱ ብክነት ለሚያንገበግበን ይህ የዛሬው የአላዛሯ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ቀያሽ አዲስ መንገድ የሰማይ ታምር ነው … ገድል። 

ስለዚህም ሌላ ማድረግ ባይቻል ሳንኮችን፤ ተባይ ሃሳቦችን ከመሞገት ተግ አንልም፤ መረባችን ዘርግተንም የድጋፉን ሂደት እናጧጡፈዋለን። ጥላቻ፤ ቂም በቀል የዲያቢሎስ ስለሆነ በንጽህና ትወልዱ ከዘመናት የቁርሾ ዕዳ ነጻ የሆነ መንፈስ እንዲኖረው እንታትራለን። ያለን ሃብት ብዕር፤ ብራና እና ወንጌል ብቻ ነው …

በቀል ትውልድን ያቃጥላል!
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!
የኔወቹ ቅኖቹ ለስላሶቹ ለነበረን ጊዜ ኑሩልኝን በአክብሮት እንሆ ተቀበሉኝ!

መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።