ወይ የኢሳት እጬጌ ለአሜኑ ለአብይ መንፈስ ደረት ደቂ ሆነ!
ነገረ ጥበብ።
ከሥርጉተ© ሥላሴ 27.06.2018
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)
„አንጀቴ ፈላች አላረፈችም።“
(መጽሐፈ እዮብ ምእራፍ ፴ ቁጥር
፳፯)
- · እፍታ።
የሲዊዝዬ የኔታወች ያውቁታል „እፍታ - ጠብታ - የወግ ገበታ - ቃና - ማዕዶት ተስፋ - እድምታ
- የሎሬት ተስፋ“ የሥርጉትሻ የሚዲያዎቿ መክለፍት እንደሆኑ። ስለዚህ አንቺም በሌብነት ተጠዬቂ አለመባሌ ልብ ልክ ነው። ባይሆን
ዘራፊዎቹ ይጠዬቁ። መቼም ዘራፊ እና ዝርፊ ቀን ጨልሞባቸዋል በጠ/ ሚር አሜኑ አብዩ ዘመን።
መቼስ ደግፍን ስንጽፍ መከፋት እንደሌለው ሁሉ ተቃውመን ስንጽፍም ዘራፍ እንደማይባል ነው። ሳይደግፉ
ቅሬታ ማቅረብ ቀፋፊ ሰብዕና ነው። በመልካሙ ነገር ደግፎ ሲጓዳል ደግሞ ለዛውም ድንበር ተጥሶ ሲመጣ ሃይ ማለት የግድ ይላል።
ዛሬም መገረም እንደ ትናንቱ ሁሉ። ዲሲ በባለቅኔው ጠ/ ሚር የድጋፍ ሰልፍ ላይ ዕንባ በወረድ
ወረድ ተደመመ አሉ። ወይ መድህኒተ ዓለም አባቴ? ስንት ጉድ ነው የሚሰማው ተዛሬ ላይ። የዛሬ የምልከታዬ ጭብጡ ይሄው ነው። ጥበብን
ተጠዬቂ ልል። ስለመሆኑ ጥበብ ቀን ከሰጠው አምክንዮ ጋር ወይንስ
ቀንም ሰጠው አልሰጠውም ከእውነት ጋር ነው ቤተሰብነቷ? ጥበብ ደግሞ
ዘነብል ቀና? ኧረ አላመረብሽም በሏት። እንዴት ተቀለደ አሉ አይዋ እንቶኔ …
- · እንዴታ!
ለነገሩ ተዚህ ላይስ ለጥበብ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ከሞቀው መጣድ ያምርብሻል ወይ ልል ነው በዛሬው
ዕለት። .. ግን ያምርበታልን? ስንት ዕውነትን ስተረጋገጥ የከራረመችው የኢሳት የጥበብ አንባ አንበል … እሷ ትፈታተሽ፤ ትበርብርም
… „ሚዛን ለራስ“ ነው ይላሉ ጎንደሬዎች። እንዴታ!መቼስ ጉደኛው ኦህዴድ ስንቱን ሰው ነው የፈተነው፤ የፈተለውም። የተያዘ የተረዘዘው ሁሉ እዬወረደ ይፈጠፈጣል፤ እኔን እኔን ...እ
… ሲጎድልም ሲሞላም በሚዛን ቤት ዘንበል ቀና የለም። ዕውነት ኖሮ ተወጥቶ እንደ ተቆመሰው ሁሉ
ዕውነት እና ፍርድ ሲጓድል ዝም ቢባልም፤ እዬቆሰቆሱ ተናገሩ እያሉን ስለሆነ ያው ቤተመንግሥትነቱ ህልም መናው በትንት ስለተወራረደ፤
ተመስገን ለባላቤት አልባሾቹ ብለናል። ስለሆነም ትቢያችን ረገፍ … ረገፍ አድርገን እንደ ቀደመው ሁሉ ዘብ የለሽ ለሆነችው የኢትዮጵያ
እውነት የሙጥኝ የተባለውን ግርድፍድፍ ጉድ እስቲ ተጠዬቅ ማለት ያባት ነው፤ የዘራችን የነገረ አማራ።
- · ልዕልት ጥበቢት።
ጥብብ ዞግ የላትም። ጥብብ ሃይማኖት የላትም። ጥበብ ቀለሟ ዕውነት ብቻ ነው። ጥበብ ህይወቷ
ሃቅ ብቻ ነው። ጥበብ ነፍሷ ፋክት ብቻ ነው። ጥበብ እስትንፋሷ ተፈጥሮ ብቻ ነው። ጥበብ ወረቀት አምላኪ አይደለችም። ጥበብ የማንፌሰቶ
ባሪያም፤ ሎሌም፤ ገረድም፤ ምንጣፍ አንጣፊም፤ የኩሽና አደግዳጊም አይደለችም። የጥበብ ሰው ሆነው የፖለቲካ ድርጅት አባል የሆኑ
ፍጥረቶች ሊያፍሩ ይገባል ከወረቀት አምላኪዎች ተርታ ሲሰለፉ። የጥበብን ታላቅ የነፍስ ትንፋሽ ታዳፍረውታል እና። መክሊት እኮ ለሌላ
መንፈስ አይሸለመም። ሰው የመንፈስ ቅዱሱን ግርማ ሞገስ ለወረቀት? አበስ ገበርኩ!
ጥበብ ምንግዜም ዕውነትን ባላ እና ወጋግራዋ ማድረግ አለባት። ከእውነት የዘለለ፤ ዕውነትን የተዳፈረ
አመክንዮን ጥበብ መጸዬፍ አለባት። መኮነን አቅሟ ቢሳናት፤ ሁኔታው ባያመቻት፤ እንኳን ጥበብ ተፈጥሯዋ ልታይ ልታይ ስለማትል በእውነት
ዛቢያዋ ላይ ረግታ እና ሰክና ቀጥ ብላ እንደ ባንዴራው መቆም አለባት። ታዲያ እውነት ይህን ማድረግ ከተሳናት ስለምን ከጥበብ አውታርነት
አትሰናበትም?
ለጥበብ ሰው ፆታም፤ ደንበርም፤ የዕውቀት ደረጃም፤ አህጉርም፤ አገርም፤ ብሄርም፤ የቆዳ ቀለምም
ሳይገድበው ሁሉም ከነፍሱ በላይ ስፍስፍ የሚልላት ጥበብ የዕውነት ተሟጋች በመሆኗ ብቻ ነው። ጥበብ አታዳላም። ጥበብ የግል ቂምም፤ የግል ቁርሾም፤
የግል ጥላቻም የለባትም። እንደ ሰው ጥበብ ሃዲዷ በሰውኛ ስለሆነ ግደፈት ቢኖርም ግን ግድፈቱ ጥበብ ከተነሳችበት ሚዛናዊ እውነት
ጋር የሚጣረዝ ወይንም የሚፋለስ ሊሆን አይገባውም። ከዚህ ካለፈ ግን ክህሎቱ ተኗል፤ በኗል፤ ተሰዷልም። ቅባውም ከስሏል።
ዝም ማለት አክብሮት ቢሆንም፣ ይህን አክብሮትን ደፍሮ የሚጠቀጥቅ የጥበብ ሰው ካለ ግን የግድ
የተቀመጠበት አክብሮት ሊጣስ ግድ ይላል። ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል እና። ተዋናይ ሰራዊት ፍቅሬን በአንድ ድምጽ የኮነነው
ህዝበ -አዳም ፈጣሪ ከሰጠው መክሊቱ ወርዶ ኢ - ሰባዕዊ የሆነውን አረመኔያዊ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አምላኪ ሆነ በመውጣቱ
ነው። ሌሎቹም መሰሎቹ እንዲሁ፤ እንጂ ማንም ምንም ከእሱ ጋር የሚያገናኘው የለም። ሁሉም የሚያሳድረው አነሰም በዛም ቤቱ ነው።
- · ፖለቲካኞች እና የጥበብ ሰዎች።
ያው ሁላችን እንደምናውቀው ፖለቲከኞች የጥበብ ሰዎችን መጠቀማቸው የተገባ ቢሆንም የጥበብ ሰዎች
ግን የተቀበሉት ሃሳብ እንቅፋት ሲገጥመው፤ ሚዛኑን ሲስት፤ አርቀው፣ ገርተው ማስተካክል ግድ ይላቸዋል። ወይንም ደግሞ ግርዝዝ ከገጣማቸው
መሰናበት። ይህ ነው የጥበብ ተልዕኮ። መልካም ነው ተብሎ በሚታሰበው ጉዳይ ላይ ሳይንቅፉ መልካምነቱን ማጎልበት የተገባ ቢሆንም፤ መልካምነት አልጋ ላይ ሲውል ገና ጭብጨባ፤ ቻቻታ፤ ቲፎዞ እና ሁካታ ይቀርብኛል ብሎ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ለጥበብ ሰው ልኩ
አይደለም። አይመጥነውም። ለአድናቂወም የሚያቅለሸልሽ ትውኪያ ይሆናል።
- · ተጽዕኖን ፈጣሪ መልቅም የማይታክተው ግንቦት 7፤
ግንቦት 7 ከተጠጋቸው የጥበብ ሰዎች ቁንጮው አርቲስት አቶ ታማኝ በዬነ ነው። ጎንደርን ለመቀቀልም
የተገባ ምልመላ ነበር። አርቲስት ታማኝ በዬን መጀመሪያ ግንቦት 7 ይዞ ነበር ከሎንቦስ ኦህዩ የተጓዘው። በዛ ስብሰባ ላይ ቤተሰቦቼ
እንደ ነገሩኝ እንደ አንቺ ሚዛናዊ አቋም አለው ብለው አጫውተውኛል። አርቲስት አቶ ታማኝ በዬን ወደ እዛ የተወሰደበት ምክንያት አብሮም ባያድግም
ቤተሰቦቹ እዛ እንደሚኖሩ ስለተሰላ ነበር።
ግንቦት 7 ብዕር ብቻ ስላለውም ኤርትራን ስላሰላ፤ ኤርትራ ላይ ደግሞ ከወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ
ጋር በተያየዘ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ቀጥተኛ ደጋፊ የሆነውን የኦሃዩን ማህበረሰብ ልብ ለማግኘት ታስቦ እና ታቅዶ የተከወነ
ነበር።
ከዛ ቀጥሎ የመጣው ኢሳት ነው። ኢሳት ሲመጣ የተወሰኑ መልካም የሚያስቡ ባላሙያዎች የመሠረቱት
ነው ተባለ። ሃሳብ ጥንሰሳው እንዲያውም ከዛም የቀደመ ነው። በ2009 ላይ የተወሰኑ የሙያው ባለቤቶች የቴሌ ኮንፈረንስ ሁሉ ነበራቸው።
ፍራንክፈርት አማይን ላይ የጀማመሩት አንዳንድ ነገሮች እንደ ነበሩ እኔው ምስክር ነኝ። አነ አቶ ተፈሪ።
የሆነ ሆኖ በኢሳት መባቻ ላይ የትኛውም ድርጅትን ተልዕኮ አያራምድም የነፃነት ድምጽ ነው ተባለ።
ለኢትዮጵያውያን አኩል እንደሚያገለግል ነበር የተሰበከው። እኔ የተለያዩ ሰዎች ደውለው ሲነግሩኝ የግንቦት 7 ነው ነበር ያልኳቸው።
የግንቦት 7 መሆኑ አይደለም ጉዳዩ፤ እኔ የራሴ የጸጋዬ ድምጽ ራዲዮ እና የጸጋዬ ድህረ ገጽ ጣምራ ሚዲያም ስለላኝ፤ ለዛም ሰለሚከፈልበት
አቅሜም አይፈቅደም ተጨማሪ ወጪ በመደበኛ ውል ለማውጣት፤ በተጨማሪም በዋና አዘጋጅነት ስለምሰራም አጣምሮ መሥራት ፈተናው ከባድ
መሆኑን አቀወቃለሁኝ።
አንድ ሰው የሶሻሊዝም ፓርቲ ማህበርተኛ እንዲሆን ሲፈቅድ ልብ እንዲገጠምለት መፍቅድ ነው። ሰው
አይደለሁም ሮቦት ነኝ ብሎ መፈረም ነው። ቀይ ሲባል ቀይ፤ ነጭ ሲባል ነጭ። በቃ ህሊና የለሽነትን መፍቀድ። በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት
መርህ በልበ ልቦና ውስጥ መንቀሳቀስ አይፈቀደም። ታስሮ እና ተቀፍድዶ መቀመጥ ነው። ተሜ ይምጣልኝ እያለ የሚማጠነው ይህኑ እሰረኝ
መንፈስ ናፍቆት፤ ሽውታው አላስቆም አላስቀምጠው ብሎ ነው። እኛ ደግሞ አድገንበታል። ነፍስን ሸጦ ማደር ነው። በልብህ አታስብም፤
እንደልብህ አትራመድም ነው ጉዳዩ።
ስንት ሰው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ በፍቅር እብድ ብሎለት የውሽማ ሞት ሆኖ የኖረውም ለዚህ
ነው። የግንቦት 7 ቀንዶች ጋሬጣ ሆኖ ስለሚተለትለው፤ ማህበራዊ ኑሮን፤ ፖለቲካ ህይወትን ውልቅልቅ እንደሚያድርጉት ስለሚታወቅ።
አሁን እንዲህ እኔን መዝግቡኝ በወረፋ ሊሆን ቋጠሮ ድህረ በርጋታ በሰከነ ሁኔታ የነበረውን ዕይታ ከቴዲ የባህርዳር ኮንሰርት ጋር አያያዝከው ተብሎ „ወዴት
ወዴት“ ተብሎ ነበር። ለነገሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ የጠ/ ሚር አብይ አህመድ ፎቶ ሆነ የኦቦ ለማ ማግርሳ ፎቶ ትውር ያላሉበት
ድህረ ገጽ ነበር። ይቅርታም የሚመስል ነገር ጽፏል።
የሠራው እኮ ንጥር ያለ እውነት ነበር ቋጠሮ። ተልዕኮው ለዛ ነው። ኢትዮጵያን ወደ ክብሯ ለማስምለስ
ትውልዳዊ ድርሻን በሚችሉት ለመወጣት። የሚደያ ተግባር ይሄው ነው። ፖለቲካ ድርጅቶች፤ እምነቶች፤ አስተሳሰቦች እንዲኖሩ መጀመሪያ
አገር ትኑር ነው። ለዛ ክብር ነው የሰጠው ድህረ ገጹ። ግን አይቻልም፤ በሶሻሊዝም ፈጣሪ የሰጠህን ልቦና ሁሉ ሰብስበህ
በግንቦት 7 ሊቀመንበር ሥር ሰጊድ ለኪ ማለት አለበት ነው። አሁን ደግሞ ባል ስድስት ክንፉ መላዕክ ከሰማዬ ሰማዬት ወርደው አቋማችን
ቀዬርን ሲሉ ዕንባም አልቀረም አብሮ ተሰለፈ። ኡኡቴ ድንቄም ባለ ዕንባ ... ከትከት እንበል ...
- · ያጠረው ገመድ።
ግድ ነው መፎከሪያው ብራስልስም፤ ማቅራሪያው ኤርትራም ከእጅ ወጣች። ዕውነት ከሆነ ግን ዕውነቱን
ደግፈህ አቅም ሰጥተህ ከጊዜው ጋር እኩል ተራምደህ ከነከብርህ ብትውርድም ተከብርህ ነው። ብትመጣም ወደ አዲሱ ሃሳብ ትናንትም ስለነበርክብት
አያስተዛዝብም። አሁን እኮ ሩጫ እና ጥድፊያ ነው የተሆነው። እዚህ ውጪ አገር ያሉ ብቅ የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ድብዛቸውን አጥፍቶ፤ አገር ቤት ደግሞ የለማ የገዱ መንፈስ ማቆጥቆጥ ሲጀምር ፈንጁ ተጣለ። መንፈቅ ሆነው እኮ ጉዳዩ የታጋድሎ። የተከረመው ክራሞት ጉግሱ እኮ ይሄ ነው አይባልም። ለዛውም በሚታዬው ነው። በማይታዬው ሴራማ ፈጣሪ ይወቀው፤
ለነገሩ የጎንደር የአማራ የተጋድሎ አብዬት እኮ ዓለም አቀፍ ደረጃው ሥልጡን ነው የነበረው።
ያን መደገፍ በፍጹም ሁኔታ ሰው መሆነን የሚጠይቅ አምክንዮ ብቻ ነው የነበረው። ባልሠራው፤ ባልነበረበት አጀንዳው ባልሆነ መኮፈስ
ያማረው ግንቦት 7 አሻም ቢልም ህሊና ያለው የጥበብ ሰው ሚናውን ለይቶ ከሃቅ፤ ከእውነት ጋር መቆም ግድ ይል ነበር። ሃቅን ማንፌሰቶ
አለፈጠረውምና።
ስለሆነም ዕድሜው ሲቆጠር „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“
የአማራ ተጋድሎ ሲታከል ሦስት ዓመት ነው የሆነው። መቼም አሊ አይባልም ይህ የአሁኑ በዬሰዓቱ የሚደመጠው ሰበር ዜና
ገድል የአማራ ተጋድሎም ሙሉ አሻራ እንዳለበት። በዙ ሰብዕና ካለወጌሻ ነው የወላለቀው። ውዳሴ ከንቱነት የጊዜ ጉዳይ ነው። ሃቅን
የተጠለለ ግን ምንግዜም ያሸንፋል፤ ልበ ሙሉ ነው። ቋሚ ነው። ዝልቅም ነው። ሃቅ የመንገድ መሃንዲስ ነው እና … እሚያስዝነው ለግንባር
ሥጋዎች የጎንደር መንፈስ ይህ ዳገት ሆኖ መታየቱ ነው፤
- · ወደ ቀደመው የኢሳት እና የግንቦት 7 ጋብቻ …
እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ላላ ያፈነገጠ ተፈጥሮ ደግሞ ከዚህ ቅርቃር ውስጥ መግባት የማይታሰብ ነበር።
ለዛውም ራሱን ለመምራት ለተሰናው የአንቡላ ቅራሪ ውክል የበታች ሆኖ ማደግደግ ይቀፋል። ለዛውም እዚህ ግባ የሚባል ብናኝ የሰብዕና
አቅል ለነሳው … ፖለቲካ ቃሉ እራሱ ስለምን እንደምን ያለ መሆኑን ፊደል ላልተገዛለት፤ ባዬው አቅም ሁሉ ጌታ እንዳጣች በቅሎ ለሚበረግግ
የጉድ ቁንጮ፤ መታሰቡ እራሱ የልብ ውጋት ነው። ለደቂቃ እንኳን ቁሞ ላማነጋገር ፈቃድ ከእኔ ተገኝቶ አይታወቅም። በቋንቋ አንግባባም
…
ለእኔ የፖለቲካ ፍለስፍና ሃሳብ በጎርፍ የተከመረ የምንትሶ ቆጥ አይደለም። ይልቅ የአንድነት ልጆች እዚህ ሲዊዝ መሪዎቹ ጉበዞች፤
ታታሪዎች የሰብዕና ፖለቲካዊ ጠረን ነበራቸው … ሥም አጀንዳቸው አልነበረም። ይሄ በራሱ በቂ ነው። ድርጅት ከሥም፤ ከዝና ጋር መፋታት
አለበት ከሁሉ ቀድሞ። ቁጭ ብለው የመሥራትም አደብ ነበራቸው … ድርጅት ረጅም ጊዜ መቀመጥን ይሻል። ድርጅት የጤፍ ጠላ ስላልሆነ
…
ስለሆነም ለመጻፍ፤ ለማሰብም፤ ለመፍጠር ትውስት እና ቅልውጥ የሚያስኬድም አንዳችም ነገር የለም፤
ለታቆረ ሃሳብም አደግድጎ መገዛትም አልተፈጠረብኝም፤ እና ሳልለካከለክ፤ አልችልም አልኩኝ። አስቤ አቅጄ ወሰንኩኝ። ስልኩ ድንገተኛ
ቢሆነም ግን የማይሆነው እንደማይሆን ልቤ አትሞታል። ደቂቃ አልጠፋሁም ስወስን። እንዲያውም ከዚያ በኋዋላ ስልኬን አጥፍቼ ቁጭ አልኩኝ።
ከውስጥ ካለሁኝ መተቸት አልችልም። ያለኝ ምርጫ መደገፍ ብቻ ነው። ቅዱሳኑ የሚናገሩት ቃለምህዳን አደግድጌ መቀበል። ውጪ ከሆንኩኝ
ግን መደገፍም እችላለሁኝ መተቸትም እችላለሁኝ። ለሌላው ብርቅ ነው የፓርቲ አባልነት፤ እኔ እኮ በቅጡም 18 ዓመት አልሞላኝም የፓርቲ
አባል ስሆን። እንዲያውም ኢሠፓ እጩ አባል የሚባል የቆይታ ጊዜ አለው። እኔ በተለዬ ሁኔታ አካል ሳልሆን ነው የእጩ አባልነት ጊዜ
ተዘሎ ባልተለመደ ሁኔታ በቀጥታ ሙሉ አባል የሆንኩት። አዎና! ፓርቲዬ ኢሠፓ እንደ ዓይኑ ብሌን ከሚያያቸው እንዷ ነበርኩኝ።
- · መንገድ ጠራጊነት።
ኢሳት እንደ መጣ መንገድ አሳማሪው አርቲስት አቶ ታማኝ በዬነ ነበር። ማንም የማይደፍራትን ደቡብ
አፍሪካን ሳይቀር ደፍሮ ነበር የሄደው። በህይወቱ ወስኖ። ልባሞችማ በስካይፒ ነው ስብሰባውን የሚታደሙት። በዛን ጊዜ ከግንቦት
7 መሪ ጋር የአዲስ ዓመት ብሄራዊ ጥሪ አቅራቢ ሲሆንም እንደማይቀጥልም
እዛው ኦሃዩ ለሚኖሩ ለወል ቤተሰቦቻችን ነግሪያቸው ነበር። ቀስ እያለ ያልኩት አልቀርም፤ ገፋ እዬተደረገ የግንቦት 7 መሪ ድምጽ
ብቻን አስተናጋጅ ሆነ ኢሳት። ይሄው አላልኩም አልኩኝ ለቤተሰቦቻችን። እባክሽ እሱን ተይው ይሉኝል እነሱ። እኩል መያዝ ቢችል ግንቦት
7 ትናንትን የማስታውስ አቅም ቢኖረው፤ ውለታ ቢያውቅ፤ ይልኝታ ቢኖረው መንፈስን ማዝለቅ በቻለ ነበር። እንቅስቃሴው ተስፋ ስለሆነ
እያንዳንዷን ቅንጣት ነገር የሚከታታል ሰው ስለመኖሩም ልብ ብሎት አያውቅም። ይንቃል ሰውን ትልቁ ችግሩ ይሄው ነው።
ባለዲግሪዎችን፤ ፕሮፌስሮችን፤ ዓለም አቀፍ ተሸላሚዎችን ስለሰበሰበ ሌለውን እንደ ሥርጉተ ሥላሴ
ያለ ትቢያ ላይ ያለ "ሰው" አይደለም በግንቦት 7 ቤት። እሰቡት ኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች ያለች አገር ናት። ቁራሽም ራፊም
ያለው ከስንት አንድ ነው። ሊለምኑ ያፈሩ ቤት እንደተዘጋ የሚያልፉትም ቤት ይቁጠረው። ይህን ህዝብ የሚመራ ፓርቲ ነው ነጭ ለባሽ
እና የአደባባይ ሰው ሲቃርም ውሎ የሚያድረው። ከልባችሁ ሁናችሁ አጥኑት። በምቀኝትን፤ በክፋት፤ በተንኮል ሳይሆን የአቅሙን ዘነዘና
መሠረቱን የሆድ ዕቃውን ትንፋሽ … አስጠግታችሁ አጥኑት።
ከሞት እንኳን አንዱን ጓዴ ብሎ መግለጫ ሲያወጣለት ሌላው ጉዳዩ አይደለም። ከሰው ሰው በሰፋ
ሁኔታ የሚለይ እና የሚነጥል ድርጅት ነው። ለዛውም በሊሂቃኑ በሰሞናት ድንገተኛ ሞት እንኳን፤ እንኳንስ ደሃን ሊያስጠጋ ቀርቶ
… የሃብታም ድርጅት ነው። ዜግነት በገንዘብ ነው የሚያድለው። ጠረኑ ድሃን ባለቤት የሌላቸውን አያስጠጋም።
· የሆነው።
ኢሳት ሙሉ አቅም አግኝቶ እራሱን ሲችል ግንቦት 7 አርቲስት አቶ ታማኝ በዬነን ገፋ አደረገ
እና የራሱን መደበኛ ካድሬዎች አሰማራ ለኢሳት ፈንድ ራይዚንግ። አንሳፈፈው። ቤቱ ተዳርጅቷላ! ልክ የወያኔ ሃርነት ትግራይ በባዶ
እጁ ገብቶ አቅም ያላቸውን ሁሉ መጦ የራሱን ሰዎች እያስተማረ ቦታዎችን ሁሉ እንደተካው ማለት ነው።
ከ2015 ጀምሮ አርቲስት ታማኝ በዬነ ፊት ለፊት ለማማጣት አልተፈቀድም። የአማራ የማንነት የህልውና
ተጋድሎ ሲመጣ ጎንደሬ ደግሞ በድጋሚ ተፈለገ። ይሉኝታ የለም። ኢህአፓ ሲኮን ጎንደር፤ ቅንጅት ሲኮን ጎንደር፤ ግንቦት 7 ሲኮን
ጎንደር …
እንደ ለመደበት ግንቦት 7 አዲስ
ተልዕኮ ሰጠው፤ ሂድ እና ጎንደሬዎችህን አደራጅ እና የአማራ ድርጅቶችን የተጋድሎው ዓላማ አክሳ፤ ለእኛ አውል ተብሎ ወደ እዛ ተገፋ።
የቀረው ጥሪቱ የእኛ መንፈስ ብቻ ነበር፤ እሱንም አራቁቶ ግንቦት 7 ከእኛ መንፈስ ጋር ሙሉ ለሙሉ በስልት እና በጥበብ አፋታው፤
ነጠለው።
ለነገሩ በእኔ መንፈስ ውስጥ ከ2015 ጀምሮ ፈጽሞ የለም። ለዛ መስቃ ለተሰማበት የኢሳት ፈንድ
ራይዚንግ በርን ሄጄ የተፈጠረውን ድራማ ለቤተሰብም አልተናገርኩኝም። ከዛችን ቀን ጀምሮ አዳምጬው አላውቅም። ከአማራ የህልውና ተጋድሎ
በኋዋላ የእኔን መንፈስ የተከተሉ ሚሊዮን የአማራ ልጆች፤ የእውነትም አርበኞች አጀንዳቸው እንደማይሆን ይታወቃል። በዬደረሰበትም
እሱ የሚቀርባቸው፤ የሚጨነቅላቸው እነማን እንደሆኑ ይታወቃል። ለእሱ የበኽር ልጆቹ የግንቦት 7 የማንፌስቶ ማህበርተኞችን ብቻ ነው ሲንከባከብ የሚታዬው። ከዛ
የወጣነውን በሚመለከት ለሌላ ቀን ይቀጠር … ምህረት ቢደረግልን ምንኛ መልካም በሆነ ነበር። ለነገሩ እሱም ልቡ ያውቀዋል እኛም
ልባችን ያውቀዋል።
- · የአማራ የህልውና ተጋድሎ እና የሰብዕዊ መብት ተሟጋችነት መፈጥፈጥ።
በዛ የአማራ ተጋድሎ እውነተኛውን ነገር እያወቀ፤ ከቤተሰብም እዬሰማ፤ የአማራ የህልውና ተጋድሎ
ድብዛው ጠፍቶ እውቅና እናዲያጣ፤ የወልቃይት እና የጠገዴ መሰረታዊ ጥያቄ የውሽማ ሞት ሆኖ እንዲቀር ያን ያህል ዘመቻ ሲደረግ ለእሱ
ከመጤፍ የተቆጠረ አልነበረም „የነፃነት ሃይል“ ማህበርተኛ ሆነ። ይህም ይሁን መረጃው እያለ ግንቦት 7 ማሰልጠኛ ከፍትኩኝ ቃብቲያ
ላይ ሲል በአውሮፕላን ህዝቡ እንደ ሃውዚ ተጨፍጭፎ የፖለቲካ ሸቀጥ ስለመሆኑ እንኳን ወጥቶ ሊመሰክር፤ ሊሟገት አቅም አልነበረውም።
ከዚህም ያለፈ ሪፖርተሮች የት እንደሆነ ብዙ ነገር ያውቃል። የሰብዕዊ መብት ተሟጋችነቱ ለአማራ ህዝብ አልሆነም። አማራነት ከብት
አይደለም በአሞሌ ጨው የሚገዛ። አሁን እርዳታ ምንትሶ ቅብጥርሶ ሲባል ይደመጣል። መጀመሪያ አብሬህ ነኝ ለማለት ለመድፈር ደሜ ነህ
ማለት መቅደም አለበት።
ጥብብ ግን እንዲህ አልነበረችም። ሆናም አታውቅም። ጥበብ
የሰው ነፍስ ነው ጉዳዮዋ። አልፎ ተርፎ ስለሌለው ሲጨነቅ ቤቱ በእሳት እንዲነድ ጎንደር ሲፈረድበት አጀንዳው አልነበረም። ሚደያ የሌላት ከተማ ሲላት ዘጋርድያን ጎንደርን
አልቆጨውም፤ ጥቃቱ አልተሰማውም፤ አልጎረበጠውም። ታሪካችን በጠራራ ጸሐይ ሲዘረፍ አልነሸጠውም። እሱ ቀን ከሌት በደከመለት ሚዲያ
ያ ግፍ ሲሰራ የተጋድሎው ታታሪዎች ሲገለሉ ጉዳዩ አልነበረም። ለነገሩ ታዋቂነት እኮ የጥቂቶች ማልያ እንዲሆን ብቻ ነው የሚፈለገው።
የሰው ልጅ መጀመሪያ ከራሱ መጀመር አለበት። ጥበብም ከራሷ ነው የምትጀመረው። „የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሄርን መፍራት ነው“ ብላ።
አማራ ነኝ ማለትም አለማለትም መብት ነው። ቢለውም ባይለውም ምንም አያመጣም። የሰብዕዊ መብት
ተሟጋች ማለት እኮ ስለሰው ልጅ መትጋት ማለት ነው። አማራም ሰው ነው! አማራም ኢትዮጵያዊ
ዜጋ ነው! አማራም ሉላዊ ዜጋ ነው! ጎንደርም የኢትዮጵያ ናት! ጎንደርም የአፍረካ አካል ናት! ጎንደርም የሉላዊ አካል ናት!
የሰው ልጅ መብቱ ሲረገጥ፤ መንፈሱ ሲቀማ፤ ማንነቱ ሲዘረፍ፤ ጀግንነቱ ሲወረር አብሮ መንደድ
መቃጠል መጋዬት ነው። 20ሺህ አማራ በበረሃ ላይ ታስሮ ሌሊት ሌሊት በድብደባ ብዛት ቀብር የሚያድረው አማራ ነኝ ብሎ እንጂ „የነጻነት ሃይል ነኝ“ ብሎ አልነበረም። ባህርዳር ላይ 50 ንጹሃን
ሲጨፈጨፉ አማራ ነኝ ብለው ነው። አንባ ጊዮርጊስ ላይ 26 ህፃነት ሲጨፈጨፉ አማራ ነኝ ብለው ነው፤ አማራም ሰው ነው። ጎንደር ደብረታቦር ሲነዱ አማራ ነን ስላሉ ነው።
ሌላ ምን ሃጢያት ሰሃ የለባቸውም።
- · ትዝብት።
አቶ ጀዋር መሀመድ እውቅና እና ተቀባይነት እያገኜ ሲመጣ ሌላ መስናክል ተፈጥሮ ማህበራዊ መሠረቱ
ጋዬ። በዚህ ተለያዩ። የኦሮሞ ፕሮቴስት ሲመጣ ደግሞ ከእግሩ ሥር ተውድቆ „ምን እንደርዳህ“ ተባለ፤ ቅዱሳኑ ሂዱ ስላሉ አቅሙን
ለመውረር። እንደዛ ገፋፍተው አውጥተው የቁርሾ ማወራረጃ ያደረጉትን ወጣት ጀዋር መሀመድ ከደጁ ድረስ ተሄደ። የራስህ ወገነህ የሚከፍለውን
ገድል ለሌላ ምንም ላልከፈለ ባለገበርዲን ሸልመህ? ቢያንስ ተጋድሎውን ደግፈው አማራ ነኝ ያለው ስብሰባ በስያትል ሲያዘጋጅ እንደ
አንድ ተራ ዜጋ ባይጠራ እንኳን ስለምን ተገኝቶ አጋርነቱን መግለጽ ይሳነዋል አርቲስት አቶ ታማኝ በዬነ። የግድ መድረክ ላይ ለዝንትዓለም
መቀመጥ አለበትን? በዛ ወቅት አይህን ለመላ አማራ ህዝብ ነፈገው።
ከታች ከህዝብ ጋር ሆነ መሰብበስ እኮ ክብር ነው። ሁላችንም እኮ ስንት ታላላቅ ህዝባዊ ስብሰባዎችን
የከፈትን፤ ስንት ጉባኤዎችን የተሳተፍን ነበርን ዓለምዓቀፍ ሳይቀር። ግን ታችም ላይም ስንሆን እኩል ስሜት ነው ያለን። መሪው ብራስልስ
ላይ ኦሮሞን ብቻ ሰብሰብው እኔ ቢሸፍቱ ነው የተወለድኩት ኦርምኛ ቋንቋን በዚህም በዚያም ባልችለውም ግን ኦሮሞ ነኝ እያሉ። የትናንቱ
ጓድ ደበላ ዴንሳ እኔ ኩሩ የኦሮሞ ልጅ ነኝ እያሉን። ቢያንስ በመንፈስ እንኳን በሚያገናኝ የሃቅ መስመር ላይ ለመቆም እንዴት ይሳናል?
አንድ የጥበብ ሰው አቅምን ከሚለቅም ድርጅት ጋር ተጠግቶ ትናንትን እያዬ ዛሬም በዛው መንገድ
መጓዙ ግን ይገርማል። ስለምን ሰው ሁሉ ከጠቢቡ ቴወድሮስ ካሳሁን አይማርም። ቀጥ ባለችው በነጠረችው የጥበብ የእንቁ ጣዝማ ውስጥ
ነው ይህ የጥበብ ሰው የኖረው። ዝንፍ የለም። እሱንም ከእሱ የተጠጋቸውንም ጥበብ አክብሮ እና አስከብሮ የኖረ ታላቅ የኢትጵያዊነት የጥበብ እጬጌ። ተባረክ የእኔ ጌታ ሊቁ ቴዲሻ። የፖለቲካ ድርጅት መጠጋት ሲወድቅም አብሮ መውደቅ አለ። ዕውነትን ከሆነ ግን መቼውንም አይወደቀም።
- · አቅም እና ተቅማጥ።
ግንቦት 7 አቅም በመጣ ቁጥር ለዛ ሲያሰማራ በቃ ጥበብ እንደ ጋሬ መጎተት አለባትን? ፍርዱን
እና ዳኝነቱ ለአንባብያን። „ድምጻችን ይሰማ“ ግንቦት 7 አነጣጥሮ ጉብ ያለበት የተጋደሎ አድማስ ነበር። ያን ጊዜም ነው አክቲቢስቶችን
ዕውቅና በመስጠት መንበር ላይ ያወጣው። እናም አርቲስት አቶ ታማኝ በዬነም ያን ጊዜ በዚያው በተለመደው የውስጥ ለውስጥ የትእዛዝ
መስመር „አላህ አክቡር“ ብሎ ተነሳ። አሁን ደግሞ የፕሮቴስታንት አማንያን አቅም ሲያገኙ „እዬሱስ ጌታ ነው“ ምን ይባል ይሄ?
ስለምን እስከዛሬ ድረስ አልሆነም?
እሺ ይህም ይሁን ይባል „ከጣና ኬኛ!“ ጀምሮ ድርጅቱ ኢሳት ሰፊ መስክ ከፍቶ ኦህዴድን ሲዋጋው
ነው የከረመው እሰከ ትላንት ድረስ። … የት ነበር ዛሬ የአወርደው ዕንባ? አለቀሰ? … ወይ አለማፈር! „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ እኮ የዛሬ አይደለም የተፈጠረው። ለአንድ አማራም ሆነ ቅማንትም
አይደለሁኝም እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ላለ ብሄር አልቦሽ፤ ዞግ አልቦሽ፤ ሰፈር አልቦሽ የኢትዮጵያኒዝም አክቲበስት ቅድመ ሁኔታ እንደ
አቶ ኤርምያስ ለገስ ስለምን አስፈለገው? „ከኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ በላይ ምን አጀንዳ፤ ምን አምክንዮ፤ ምን የተደሞ የሚስጢራት
አንጎል ታምር እና ገድል ይሆን ከሰማይ እንዲወርድ የተፈለገው። የተጠበቀውስ። አሁን እኮ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ቀድሞ በተለያዬ ሁኔታ የሚያደርጉትን ንግግር ብሄራዊ ማድረጋቸው ካልሆነ በስተቀር አዲስ የተፈጠረ አንዳችም ነገር የለም። ቃሉ የሥንኙ መንፈስ እኮ ወጥ ነው።
ዶር አብይ አህመድ የዛሬ ሰው ናቸውን? ሌላው ይቅር አብረው የሠሩት ጋዜጠኞች፤ የሠራ ባልደረቦቻቸው፤
እኛም ቀደም ብለን ነፍሳቸውን በሌላ ጉዳይ የመረመርነውም ስንሞግት የትን ነበር የአርቲስት የአቶ ታማኝ በዬነ ዕንባ? ጥበብን የሚያኖራት ሃቅ እንጂ አንድ ቀንጣ ነፍስ የጫረው ወረቀት ወይንም ማንፌስቶ አይደለም።
ጥበብ ገበርዲንም፤ ሱፍም አይደለም ክፍሏ። ክፍሏ ፋክት ነው። ፋክት ሲዛባ፤ እውነት ሲያዝን፤ እውነት ሲከፋው፤ አውነት ሲሰደድ
ለእውነት ጠበቃ ያለሆነች ጥበብ በአፍንጫዬ ትውጣ … ባለው በቃሉ በተናገረው ላይ መቼ ነው ግንቦት 7 ተገኝቶ የሚያውቀው? ዛሬ ገነባሁት ያለው በማግስቱ
ሲናድ ሰደረመስ ነው የሚታዬው። ካድሬው እሺ አብሮ መነሳትም መውደቅም ግድ ነው ግን ጥበብ ምን ባደረገች አብራ ትልፈስፈስ?
ኦህዴድን አብረን ስናብጠለጥልን ከርምን፤ አብረን ለውጡ ከስሞ የብድር ዱቄት እንዲሆን ስናበረታታ ባጀን፤ ህውከት ስንከበከብ ስናናፈስ ኖርን አሁን ባለ ዕንባ ሆን፤ ወይ አለማፈር? ስንት ጊዜ አላማፈር ይጠራ ይሆን በሰፈረ የግንቦት 7 አልምኮተ
አህዱ ?
- · ምርጫ የለሽነት።
የሆነ ሆኖ ምርጫ የለም። የኤርትራ ባጀት እና ባዕት ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ቁምነገር ለማድረግ
ባለመው አሜኑ እጅ ነው። ስለዚህ ጓዝን ጠቀላሎ ንስሃ መግባት። ቀድሞ ነገር ግንቦት 7 የእኔ ቢል እኮ ከአቶ ታማኝ በዬነ በላይ
ለአውሮፓ ህብረት ተጋባዥ እንግዳ ባልኖረው ነበር። እኛ እማንታዘብ ይመስላችኋልን? ምን ቢሆንም ቢከፋንም፤ በረቀቀ ሁኔታ እራሱም ቢያስከፋንም፤ ቢያቆስለንም ግን የምናዬው
የጮሌዎች ብልጥነት ይገባናል። ልዩነቱ የሰፋ ነው ...
ስለምን ሁልጊዜ እሱ መንገድ ጠራጊ እንዲሆን እንደሚፈለግ አሳምረን እናውቃለን። ሰብዕናው በተናደ
መንፈስ ውስጥ ተለካልኮ እንዲህ መሆኑ ያሳዝነናል። ሃብትነቱ የኢትዮጵያ ስለነበር ሁሉም ልክ እንደ ዶር. አቦንግ ኢትዮጵያ ሜቶ
የሚስማማበት ሊሆን ይገባ ነበር። ዛሬ ግን እእ … ህሊና ያላቸው ሰዎች፤ ሰው ማዕከላቸው የሆነ ሰዎች አያደርጉትም። ሰው ሸቀጥ
አይደለም፤ ለግለሰቦች የፖለቲካ ሥም የችርቻሮ ንግድ መክፈቻ የሚሆን …
ለዚህም ነው በርቀት መቀመጥን የፈቀድነው። ሃቅ እውነት ነው ስንል ደግሞ ማንም ምንም ሰለከፈለን፤
ሆቴል ስለመረጠልን፤ በጀት ስለመደበልን፤ ጫን ያለ የውሎ አበል ስለቆረጠልን፤ ጠባቂ ዘበኛ ስላቆመልን፤ ስለሚያንጨበጭብልን ሳይሆን
በገንዘባችን ለዛውም ተገልምጠን፤ ተገፍትረን፤ ረጅም መንገድ ተጉዘን ሌሉትንም አክለን ደክምን ሳንል ዘግበናል፤ የምንችለውን ሁሉ ተሳትፈናል።
ግን ለተቃጠለ የካርቦን የማሌ ፍልስፍና ሳይሆን ኑሮን በቃኝ ብሎ በርሃን መምረጥ አንድ የጽድቅ መንገድ ነው ብለን ስለምናምን
…
- · አላማረበትም።
ጥበብ አስመሳይ፤ አድርባይ አይደለችም። የሆነ ሆኖ የአሁኑ ዕንባ ለአርቲስት አቶ ታማኝ በዬነ
አላመረበትም። ካለልኩ የተሰፋ ሽብሽቦ ነው የሆነው። ጥብቆ። ማልቀስ የነበረበት
የግንቦት 7 ካድሬዎች እና ፕሮ ሚዲያዎች „በኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ በወል ሲዘምቱ ነበር። በአማራ የህልውና ተጋድሎ አውቅና ላይ
ሲያድሙበት ነበር። ታስረው በተፈቱ ጀግኖች ላይ በነበረው የወል እቀባ ነበር። በአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ እውቅና እና ተቀባይነት
መገለል፤ ወጥቶ ማወገዝ ነበር ለሰብዕነት ተሟጋችነት ብቁነት ለመብቃት። ያን ጊዜ ይህ ዛሬ የተንዠረከከው ዕንባ የት ነበር አድራሻው?
የዕውነት ያስፍራል!
ዛሬ ቤተሰቦቼ በዚህ ጹሑፍ እንደሚያዝኑብኝ ባውቀውም ከራስ መጀመር ግድ ይላል … በእውነት ላይ ቆሞ ሲታትተር እሱ ባያምርበትም እኔ ግን ታግዬለታለሁኝ። ተግባሩ
እንጂ የአሱ ላይ መንጠልጠል ለእኔ ምንም ስላልሆነ … እሱ መድረክ አስተዋዋቂ በነበረበት ጊዜ ሥርጉተ እሱ ስለሚያስተዋውቀው የኪነጥበብ
ቡድን እርምት ዕውቅና የምትሰጥ ወጣት ነበረች።
አድገንበታል በጋሜ እና በቁንጮ ክብሩንም፤ ደረጃውንም፤ ዕውቅናውንም፤ ተቀባይነቱንም። ዛሬም
እርሾው አለ ካለበት። እኔን ሞግቶ የረታ አንድ ሰው እስኪ ይምጣ … በቃሉ አልገኝ ብሎ ግንቦት 7 እንድሸነፍ ካድረገው አመክንዮ
በስተቀር …
የጓድ ገብረመድህን በርጋ፤ የጓድ ወንደወስን ሃይሉ፤ የጓድ ዘርጋው አስፈራ፤ የጓድ አበበ ባዳዳ፤
የኮ/ አሰፋ ሞሲሳ፤ የጓድ ስለሺ መንገሻ፤ ነፍሳቸውን አርያመ ገነት ያግባልኝ እና የጓድ ገዛህኝ ወርቄ ልጅ እስኪበቃኝ ድርስ ሙሉ
ሰብዕናዬን በጥንቃቄ እና በስክነት ገንብተውታል። መደበኛ ሥራቸውም ነበርኩኝ። በዬትም ቦታ በት/ ቤት፤ በኮርሶች፤ በሰሚናሮች፤
በጉባኤዎች ስገኝ እንኳን የሚረዳኝ፤ የሚያግዘኝ ሰው የዘጋጁልኝ ነበር።
ሰው መፍጠር፤ ሰው ማብቀል መደበኛ ተግባራቸው ነበር። አንዳቸውም ጎንደሬዎች አልነበሩም። ግን
ለእነሱ ሥርጉተ ሥላሴ ከልጅም በላይ ነበረች። የተስፋቸው የማግሥታቸው የኪዳን ራዕይ። በዬትኛውም ሁኔታ በዬትኛውም ጊዜ ከህሊናቸውም
የማትፋቅ። ዛሬም አታሳፍረቸውም። በዛ በወጣትነቷ በነበራት ውበት እና ቀለም እንኳን ያልማረካትን ዓለም ተጽይፋው ነው የምትኖረው።
ክውን ሽክፍ ብላ በቁጥብነት፣ በንጽህና እና በቅድስና ነው የምትኖረው። እና መንገዳችን አንደ የነፃነት ፍለጋ ቢሆንም ያለፍንበት
የህይወት ተመክሮ ግን ፍጹም ልዩ ነው ስለዚህም አለተገጣጠምነም … ወደፊትም …
ጥበብ የማንፌስቶ ከራባት ጥብቅናን በቁሙ ተቃጥላለች!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ