በንቅንቁ መበላት እንዳይኖር ……

 

በንቅንቁ መበላት እንዳይኖር ……

"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"


 

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የጎሹ ነገሮች ጥራት አግኝተዋል። የኃይል አሰላለፋ ጥርት ብሎ ወጥቷል።

1) አብይዝምን ተስፋ ያደረጉ ሌላ ፈሰስ ቀይሰዋል፤

2) ህወሃትን የደገፋ በተንጠልጠል ላይ ናቸው፤

3) ዬኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን መደገፍ የቴራፒ ያህል ዬሚያዩት መተርተር ጀማምሯቸዋል፤

5) በነፃነት ትግሉ በአውራ ፓርቲደጋፊ ዬነበሩት ሙሉ አቅማቸውን ለአብይዝም አራግፈው ኤሉሄ ላይ ናቸው።

6) ተረስቶ የባጀው የአንድነት ኃይል ማፏሸኩን አስታግሶ በጉቶ ላይ እንደሚያጨበጭብ ቀንበጥ ምልስ ቅልስ ማለትን ታቱ እያለ ነው።

7) ፍንካቹ እና ጉራጁ ኢህአዴግ በጀሶ ተጠጋግኖ እዩኝ እዩኝ እያለ ነው።

••••••• ጠቅላዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ለአቅመ አዳም አልደረሳችሁም ሁሉ በእጄ ነው፤ ከአምስት ዓመት በፊት ዬነበረችው ኢትዮጵያ ዬለችም፤ ቆባ ላይ ናችሁ፤ ወይንም እጭ ላይ ናችሁ በስላችሁ ብቅ በሉ ሲሉ መራራ ስንብትን አዋሳ ላይ አስታጥቀዋቸዋል።

ነገረ ኤርትራ ተከድኖ ይንተክተክ፤ ግን አቅም አላት የእኔ የምትለው የፖለቲካ ድርጅት አላት። በነገራችን ላይ የፓርቲን የአደረጃጀት መርህ ሳያዛባ መንግሥትም፤ ፓርቲም ሆኖ የተደራጀው የግንቦቱ ኢዜማ ነው። ነባር // አልበተነም ብዬ ነው በጽኑ እማምነው። በጉልህ በአማካሪነት፤ በሎጅስቲክስ ይደግፋታል። ፖሊሲ በማመንጨትም የሊቃናት ስብስብ ነው። በአካሄድ ሆነ በአደረጃጀት እስከ አሁን አናርኪዝም በድርጅቱ አላዬሁም። ባልተወሰነለት የሥልጣን ጠገግ ገብቶ ሲዳክርም አላዬሁም። ሙሉ ድጋፍ በኦነጋዊ ኦህዴድ ቢደረግለትም የአሰራር ዝንፈት ከመርኽ አንፃር አላዬሁም።

በዚህ ልክ ሚዲያወችም ይመደባሉ። ሁሉም ሚዲያ አለው።

ነገረ አማራ ሁሉን ሰጪ በሁሉ ፊት ተነሽ ተበይም ሆኖ ይታያል። ዬሚነቃነቅ ነገር አለ። በስንጥቁ ይሁን በትርትሩ መለበጃው ቀለጦው የአማራ አቅም ነው። ሁሉም የሚነሳው በገፍ አቅሙን ዬሚለግሰውን አማራን ተንተርሶ ነው። ሁሉም ጎጆ እስኪወጣ ይፈልገዋል ለዛውም ሁለመናውን እርቃኑን እያስቀረ።

#ተንጠልጣዩ

ተንጠልጣዩ በሥመ አማራ ተሸጋግሮ ስኬቱ ግን ለህወሃት፤ ወይንም ለእሮ ኢህአዲግ የሙት መንፈስ፤ ወይንም ለኦነግወህወኃት ዬሆነውም ማቡካትም፤ መጋገርምካሰኜው አማራ ፖለቲካ ላይ ነው የሚትበሰበስ።

#ብቅታ ያለእርካታ።

ብቅታ ከአማራ ከታዬ እንደ ንብ ሄደው ይሠፍሩበታል። በማኒፌስቷቸው አንዲት ዘለላ አማራ የምትል ሐረግ፤ ፋኖ የምትል አመክንዮ፤ ዬጎበዝ አለቃ የምትል ይትብኃል የሌለው ግን እንደ ፌንጣ ደንበር አልቦሽሽሚያ በአማራ ሊቃናት ብቅታ ልቅና ይሆናል። ስለሆነምእራሱንችሎ መውጣት ዬሚገባው ዬአማራ ፖለቲካ ያገኜውን ይሁን እያለ የሁሉም የጥቃት ሰለባ ሆኖ ምክነት ተሆነ።

ተንጠላጣዩ ብዙ ነው። መሸጋገሪያ ድልድዩ፤ ዬነፍስ ማሳደሪያው አቅሙን በከንቱ ዬሚያፈሰው አማራ ነው። ይጠሉታል ተንጠፍጥፎ እስኪያልቅ ድረስ ግን ይምጉታል፤ ይመጠምጡታል። አንዳንዶቹ ያላዋቂ ሳሚ እንዲሉምከ2011 ጀምሮ አሳሩን አብልተውታል። ዬቁንጫን መወጣጫ እንዲሆን አድርገውታል። አስጠቅተውታልም። ዓይኔ የሚላቸውን ዕንቡጥተስፋወችንም አስደርቀዋል። ካለኃላፊነታቸው እዬተዝለገለጉ።

ምን ይደረግ?

ቅንጥብጣቢ ነገሮችን አያለሁኝ። 8/9 ዓመት ዬነበሩ ሙቶ ዬመነሳት። ውጭ ዬሚኖሩ የአማራ ሊቃናት ቀዳዳ ሲወትፋ፤ ለሰባራው ወገሻ ሲሆኑ፤ ዬጎደለ ሲሞሉ ኑረዋል። ይህ ዬአንድም የአማራ ነፍስ አልታደገም። አንድም ስለ አማራ ዋቢ የሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት፤ ዬውጭ አገር መንግሥት፤ ዬዲፕሎማሲ ትርፍ ዬለም።

ለምን? ዬአማራ ሳይንቲስት፤ ተመራማሪ የሰው ጎጆ ሲያደራጁ ስለኖሩ። አንድ የእኛ የሚሉት ጉልበታም ልሳነ አማራ፤ አንደበተ አማራ፤ ዬሁሉም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዬሚመክርበት፤ ሃሳብ የሚያዋጠበት ሚዲያ እንኳን ሊፈጥሩ አልቻሉም። ሁልጊዜ ጥገኛ ናቸው። ለዚህ ነው ተስፋው ሁሉ እዬተጠለፈ በምርኮኛ ተስፋ ሰኔል እና ቹቻ፤ ብሶት እና ዋይታ ብቻ ዬሚመረተው።

ይህን ሁሉ ትብትብ ጥሶ ዬሚወጣ ለፖለቲካ ሥልጣን ተዳብሎ ከተለያዩ ቅሪት አካላት ጋር ሳይሆን እራሱን የቻለ ጥርት ያለ፤ መረቅ ዬሆነ ሰላምን ያስቀደመ እልፍኝ ሊሠሩ ይገባል። አማራ መጣብህን ተጋፍጦ ለአገር መሪነት ኮንፒት የሚያደርግ የፖለቲካ ድርጅትን አምጦ መውለድ ይጠይቃል።

አቅም አለ። ፖቴይንሻሉ አለ። አደራጅ፤ ኮኦርድኔተር በእጁ ነው። ውራጅነትን ከማንም ሳይሻ ንፁህ አንቱ ዬተባለ ዲስፕሊንድ ዬሆነ ግልፅ ደንብ እና ማኒፌስቶ ያለው የአማራ የፖለቲካ ድርጅት ያስፈልጋል። ውህደቱ፤ ጥምረቱ፤ ለአማራ የፈዬደው የለም። ውልቁን ነው ያስቀረው። ማን ምን እንደሆነ ይታወቀላ። ፕሮፖጋንዲስት አያስፈልግም። ሁሉ ታይቷል። ሁሉ ተፈትሿል። ኢትዮጵያን እናድን ይደላል። ግን በማን ዬደም ግብር????

በዚህ አጋጣሚ በትህትና እማሳስበው ዬአንድነት ታጋዮች አማራወች ለአማራ ትግል ዬእርጎ ዝንብ አትሁኑበን። የወጠናችሁትን በመስመራችሁ ቀጥሉበት። ሁሉንም እዬበተኑ ለተጠቂው አማራ ማሸከም ግን ዕዳ ከሜዳ ነው። ሃግ ባይ ጠፍቶ ነው በልቅ ጉዞ እዚህ ዬተደረሰው። በአፍላ አፍላ እንጀራ፤ ጠላ ይሁን የአማራ ግብርነት ግንያንገሸግሻል።

ደጉ አማራዬ አቅምህን በቅጡ ቆጥበህ የምታስተዳድርበት የአንተ ዬሆነ የውስጥነት መሪ ይስጥህ። ሙሴ!!!!!

ዬአማራ ፖለቲካ ማህበራዊ መሠረቱን ያጣ ሁሉ ኮንቴይነር ሊሆን አይገባም። ዬአማራ ፖለቲካ ቁጡ እና ገረጭራጫ ሊሆን አይገባም። ዬአማራ ፖለቲካ ተበቃይ እና ቂመኛ ሊሆን አይገባም። እነኝህን ከሰነቀ ምርቃቱ ይነሳል ሳይበቅል ችግኙ ክው ይላል።

ትህትና፤ አክብሮት፤ አብሮነት፤ ቅንነት፤ ዕውነት፤ መርኽ፤ ግልጽነት ከተፈጥሮው ለተፈጥሮው ሊሆን ይገባል። ስክነት!

እግዚአብሔር ይስጥልኝ።

ዬኔወቹ መልካም ቀን።

ሥርጉተ©ሥላሴ

Sergute©Selassie

10/12/2022

ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።