ረዳት / ፕ ነብዩ ባዬ ሹመት የብዕር የነፃነት አዋጅ ነው - ለእኔ።
ለረዳት ፕ / ነብዩ ባዬ የሎሬቱ
ዓይን የትወፊት ዘብ አደር።
ከሥርጉተ - ሥላሴ 21.06.2018 (ከመንኩሲያዋ ሲዊዘርላንድ)
„ጽዮንም ሆይ ለአምላክሽ እልል በይ፤ የደጅሽን መወርወሪያ አፅንቷልና
ልጆችሽንም በውስጥሽ ባርኳልና መዝምሩ ዳዊት ምዕራፍ“ (፻፵፯ ቁጥር ፪)
- · እፍታ
ጥበብ አለፈላት። የእውነት ጥበብ አለፈላት። አብይ ኬኛ! ላይ ለሥነ - ጥበብ ሰዎች ዶር አብይ አህመድ የተለዬ ልዩ አቅም እንዳላቸው ገልጬ ጽፌ ነበር። ከሥነ ጥበብ ቤተኝነታቸው ከፖለቲካ ሊቃን የተለዬ ጸጋም እንዳላቸው ጽፌ ነበር። በዛን ጊዜ ጥሪዬ ይህን መንፈስ የሥነ ጥበብ ቤተኞች ድጋፍ ለማሰባሰብ ነበር ሃሳቡ። መቼም እግዚብሄር ይስጣው ሳተናውም ተባብሮኝ ሃሳቤን ለቅንች አድርሻለሁኝ። አንድ ሙሴ ሲመጣ ተጠቃሚው በሚገባ ሊውቀው ስለሚገባ ነበር ዘርዝር አድርጌ እስከ ክፍል ስድስት የሠራሁት። ባለቅኔው ጠ/ ሚር ለሥነ ጥበብ ቤተኛ ናቸው። ሚስጢሩን ያውቁታል። ሰው የሚታነጽበት ጥበብ ያለው ከዚህ ማህጸን ነውና።
ውዶቼ ከሥር ተጨማሪ ነገሮችን አክላለሁኝ እስከ ምርኩዙ። ዛሬ አንድ ዜና ስከታታል ታላቅ የምሥራች ሰማሁኝ። ዘመኑ የሎሬቱ ነው ብዬም በተለያዬ እርሰ ጉዳይም ጽፈያለሁኝ፤ ዛሬም እምለው ይህንኑ ነው። በጥበብ ውስጥ ሰው መኖር ሲፈቅድ ጥበብን ንጽህናዋን ተቀብሎ ነው። የዛሬው የነፃነት ቀን የብዕር እና የብራና፤ የመድረክ እና የድምፆዋ የነፃነት ቀን ነው።
- · ጥበብ እና ነፍሷ!
ጥበብ ምቀኞችን አትወድም። ከሁሉም በላይ ጥበብ ምቀኝነትን ትጠላለች ትጸዬፈውማለች። ከሁሉም በላይ ጥበብ „ምን ትጠያለሽ?“ብትባል ምቀኝነት ትላላች። ጥበብ ቅና እና ቀና ናት። ጥብብ አራስ ልጅ ናት። ግን ጥበብ አራስ ልጅ ትሁን እንጂ ርቱ አንደበት እና ብሩህ ጎልማሳ አዕምሮ ያላት ናት። ጥበብ እና ጥበበኛው ተገናኝተዋል ማለት የሚቻለው ጥበብ በራሷ ሞራላዊ አቅም ውስጥ ስትገኝ ብቻ ነው።
ርጋታው፤ ስከነቱ፤ ጥልቅነቱ፤ የውስጥ ጸጥታው እጅግ በጣም እጅግ ከሚመሰጠኝ የዘመን ዓውራ ጥበበኛ መካከል አንዱ መምህር፤ ተዋናይ፤ የቲያትር ጥበብ ሊሂቅ አንዱ ነው ረ/ ፕ/ ነብዩ ባዬ። እጅግም የምሳሳለት እጅግም የማልጠግበው፤ በቃለ ምልልሶቹ፤ በሚያነሳቸው ቁልፍ አመክንዮች፤ በሚሳጣቸው ትንታኔው የጥበብ አድበራ ከነታቡቱ ሎሬት ጋር የተደመመበት ታላቅ ወጣት የጥበብ ሰው ነው። የትወፊት ዘብ አደር።
ብዙ ነገሩ ከሚስጢሩ ስለሚነሳ ወደ ትሩፋቱ ያዘነበለ ስለሆነ፤ ትውፊቱን መጠበቅ፤ ማስጠበቅ ክህሎቱ ስለሆነ ህሊናዬ ነው። ሚስጢር ነው። ዛሬ ጥዋት እንዴት አደርክ ደግሞ ምን የምሥራች ይዘህልኛል ብዬ ሳንኳኳ ጌታው ዩቱብን ያን የልቤን መሠረት የሆነው የትወና ጠቢቡን የሎሬቱን ዓይን አገኘሁት።
የእኔ አብይ ሁሉንም አይረሳም። ዓይኑ የሠራ አካላቱ ሁሉም፤ በሁሉም ዓይናማ ነውና። አሁን ጥበብ ከዘር ቡና ተርቲመኝነት ወጥታ ወደ አውዷ እዬገሰገሰች ነው። ጥበብ መለኪያዋ መክሊት ብቻ ነው። መክሊት ነው ጥበብ መሥፈርያዋ። ጸጋ ነው መመዘኛዋ። ጥበብ ባትመተረም በውስጥ ምርመራዋ ተስጥዖ ነው ፍርድ እና ዳኝነቷ። ጥበብ የተፈጥሮ የምርምር ማዕከል ናት። ጥበብ ፈላስፋም ሳይንቲስትም ናት። ጥበብ አጅንዳዋ ሰው እና ተፈጥሮ ብቻ እና ብቻ ነው።
እኔ ገጣሚ ፍጹም አስፋውን የማለዳ ኮከቦችን ብርሃን የምወደው፤ የማክብረው ብቃትን አንጥሮ ለማውጣት ባለው ትጋት ነው። የኢትዮጵያ የጥበብ አድባር በሮቿ ለሁሉም ባለ መክሊት ክፍት ስለመሆኑ ስለሚያመሳጥርልኝ ነው። በዛ ላይ የሎሬቱ መንፈስም ያደረበት ስለሆነ ነው። ቤተሰቡ በሙሉ ይወደዋል - የእኔ ማለት ነው። እኔ ሎሬቱ ካልኩኝ በእነሱ መንፈስም ተጽዕኖ መፍጠሩ ግድ ስለሚል።
ዛሬ ለመላ የሥነ - ጥበብ ንጹህ ታዳሚም ታላቅ ቀን ነው - ለቅኖች። ለብዕር፤ ለመናገር ነፃነትም የመጀመሪያው የነጋሪት ደወል ተደውሏል።
አንጋፋው ብሄራዊ የኢትዮጵያ ቲያትር ቤት ዋና ዳይሬክትር ሆኖ በተሾመው በረዳት ፕ/ ነብዩ ባዬ ከሊቅ አስከ ደቂቅ ቅኖቹ ደስ እንደሚላቸው ነው። የሹመት ደብዳቤው በጠ/ ሚር አብይ አህመድ ቀጥተኛ ፊርማ የወጣ ነው። አያችሁ ሁለገብ እውቀት ያለው ሰው ሙሴ ከሆነ የሚጎድልበት የመኖር አውታር የለም። ሁሉም ተጠቃሚ ነው የሚሆነው - እኩል። ብልሃቱ የጠፋን ከዚህ ላይ ነው እኛ። አላዛሯ ኢትዮጵያ ባለቤት ካላቸው ልጆቿ ይልቅ የሌላቸው እንበልጣለን። አብሶ ወረቀት አምላኪ ለልሆኑት ፈተናው ቀራንዮ ነው።
- ጥበብን የሚያውቃት ከሴራ ጋር የተፈታ ብቻ ነው።
ጥበብን የቀረባት የሚቀርባት ሴራን የማያውቅ ሰብዕና ብቻ ነው። ጥበብ ገዳዮዋ ሴራ ስለመሆኑ ጠንቅቃ ታውቃለች። ጥበብ እኮ ጥበብ ናት። ጥበብ በጎ ናት። ጥበብ መልካም ናት። ጥበብ ርህርት ናት። ጥበብ ቂም የላትም። ጥበብ በቀል አታውቅም። ጥበብ ቁርሾን ትጸዬፋለች። ጥበብ ሩቅ ናት። ጥበብ ስለነገ ትውልድ ይጨንቃታል። ጥበብ ሰው ማነጽ ተገብሯ ነው። ጥበብ የህሊና መስኖ ናት። የሰው ልጅ በመጠጥ እና በውሃ ብቻ አይኖርም። የሰው ልጅ ህሊና የሚለማበት መስኖ ያስፈልገዋል። እሱም ጥበብ ነው። ጥበብ እኮ የሞራል ትምህርት ቤት ናት። ግን ጥበብ ሃይማኖት የላትም። የጥበብ ሃይማኖት ፍቅር ብቻ ነው። የጥበብ ታቦት ሰው እና ተፈጥሮ ብቻ ነው። ጥበብ የተፈጥሮ ያላተጻፈ ህግጋት፤ ድንጋጊያት አንቀጻት አሏት። ይህ የሚገለጥላቸው ከሴራ ጋር ንክኪ የሌላቸው ባለ ንጡሃን ብቻ ናቸው።
ጥብብ ቋንቋዋ ሰብዕዊነት ነው። ጥበብ ተቋምነቷ ለቸርነት ነው። የጥበብ መስመር አብሮነት ነው። ጥበብ ዘር የላትም። ጥበብ ሉላዊ ናት። ጥበብ መኖርም ናት። የሥነ - ጹሁፍ መምህሬ አቶ አበበ ኬሬ ጥበብ „በማህበረሰቡ ጓሮ ትታፈሳለች“ ይል ነበር። አዎን ጥበብ የጠራች፣ የነጠረች፣ ማህበራዊ ኑሮ መቀደስ ናት። ጥበብ ነፃነትም ናት። ጥበብ ዴሞክራሲም ናት። ጥበብ መናገርም ናት። ጥበብ መጻፍም ናት። ጥበብ ማንበብም ናት። ጥበብ መደራጀትም ናት።
ጥበብ ሃሳብን መግለጽም ናት። ጥበብ ልዑቅ ሃሳብ ናት። ጥበብ መጋረጃ የላትም። ጥበብ መረጃ ናት። ጥበብ ዜና ናት። ጥብብ የዓይን እርግብ የላትም። ጥበብ ዕውነት ናት። ጥበብ የጋራ የወል ሥራም ናት። ጥበብ አስተዳዳሪም ተዳዳሪም ናት። ጥበብ አዛዥም ታዛዥም ናት። ጥበብ ማድመጥም መደመጥም ናት። ጥበብ አድራጊም ተደራጊም ናት። ጥበብ አናባቢም ተነባባም ናት። ጥበብ ሁነኛ ዋቢም ናት። ጥበብ ጠበቃም ችሎትም ናት። ጥበብ ዓይንም ናት ፖስተኛ። የተፈጥሮ ፖስተኛ እኮ ዓይን ነው። ጥበብ መልክዕከተኛም ናት። ጥበብ ሐዋርያ ሰማዕትም ናት። ጥበብ ነብይም ናት። ጥበብ ተስፋ ናት። አዎን ጥበብ የተሰፋ ቀን ናት … ጥበብ ዕንባም ሳቅም ናት። ጥበብ ቤዛ ናት። ጥበብ ለዛሬ ቤዛው ለነገ ዋዜማው ናት።
- አብይ እና ጥበብ።
የእኛ አብይ የሥነ - ጥበባት ጧፍ። ክፍል አራት። ይህ እንግዲህ ታህሳስ 20. ቀን 2017 ነበር። ይህን ሥጽፍ የሥነ - ጥበብ ቤተሰብ ወደ መሪነት ሲመጣ የጥቅሙ ዲካን መለካት እንደማይችል ለማመሳጠር ነበር ይህን የጻፍኩት። ትውልድ ከቶውንም ከማይተካቸው ከተከበሩ የዓለሙ ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አንድ ጊዜ እሳቸው በአገር ባህል ልብስ ደምቀው መታዬነት ሲገልጹ „ጃንሆይ ግን እንብዛም ነበሩ“ ነበር ያሉት። በሥነ - ጥበብ ቤተኛ ሰው እረኛ ሙሴ ሲገኝ በንጽጽር ከሥነ - ጥበብ ሰው ውጪ የሆነ ኢትዮጵያዊ መሪ ጋር ማወዳደር አይቻልም። ፊደል ራሱ እኮ ጥበብ ነው። እያንዳንዱን የፊደልን ሆኽያት እዮዋቸው ልዩ ናቸው። የጥበብ ሰው ሙሴነት ሚስጢር በመመዴ መተርጎም አይቻልም በእዮራዊ ትርጉሙ ብቻ ነው ማመሳጠር የሚቻለው። የ አቅም ንጥርነት እና ትግንርት እኮ በጥበብ ውስጥ ለሰረጠው ሰብዕና ጥሞናው የምርምር ማዕከል ነው ለትውልድ።
- ልላዊነት በልቅና!
ይህ የአሁኑ ዋና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር ዳይሬክተርነት ለኢትዮጵያ ብቻ ይመስለንም ይሆናል። አይደለም። በፍጹም አይደለም። ስሜቱ እና ውስጡ ፓን አፍሪካኒዝም ብቻም ሳይሆን ሉላዊ ነው። አቅሙን በዛ ልክ አመጣጥኖ ለማምጣት ነው። ይህ እንግዲህ የዕምሮ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ አፍሪካን እንደ እናት ሰብበሰብ አድርጋ አልቃ ለማወጣት፤ አህጉሩን የዓለም ተወዳዳሪ አድርጋ ለማውጣት ካላት ህልም ጋር የሚተሳሰር ነው። ነገ የ አፍሪካ የቲያትር መዝከር ኢትዮጵያ ላይ ሊኖር እንደሚችል ማሰብ ይገባል፤ የሥነ -ጹሑፍ ማዕለም ሊኖር እንደሚችልም ማሰብ ይገባል። የፊደል ባለቤቶች እኮ ነን። ግዕዝን ያህል እጬጌ ያለን፤ አማርኛን ያህል ሉላዊ ዕውቅና ያለን። ነገ ኢትዮጵያ በሁለገብ የሥነ ጥበብ አቅም አስኳልነት ትጠበቅ ነው ይህ ዓዋጅ። እያንዳንዱ የአሁኑ ዘመን የአብይ መንፈስ ጉዞ ይሄው ነው። በነጠላ፤ በክፍልፋይ ዘነጣጥለን አንዬው። ለነገሩ የአቅም ጉዳይ ነው። የአብይ መንፈስ መንገዱም አዲስ ነው፤ ህሊናውም እዮራዊ ነው።
ለማንበብም፤ ለመተርጎም፤ ለማመሳጠርም የተቸገርነው ለዚህ ነው። የጎንደርን የአማራ የህልውና ተጋድሎ እኮ አመሳጣሪ አጥቶ በሳቢያ የትሜና ተጠቅልሎ እንደ ማበሻ ጨርቅ ወድቆ ነበር። ጊዜ ደጉ የለም የተባለ ማህበረሰብ ቁጭ እንዳሉ የለም ያሉት ሰብዕናቸው ዓይናቸው ጉድ እያዬ ነው። አሁንም እኔስ እላለሁኝ እያንዳንዱን የእርምጃ ቅንጣት ከተጠቀለልንበት የወረቀት ጣዎት ውጥተን ቅድስት አገር ኢትዮጵያ በቅዱሱ መጸሐፍ ከተሰጣት ደረጃ ህልም ራዕይ ፍጻሜ ጋር ለማዬት ልቦና ይስጠን። አሜን! አካል የሌለው የልዑል እግዚአብሄር አገልጋይ እንዲህ ይለናል።
„የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?“ ይሄ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ሆነ እንዲህ።
- · ልዩ ምስጋና ለባለቅኔው ጠ/ ሚር ለዶር አብይ አህመድ።
ክቡር ጠ/ ሚር አብይ አህምድ ሆይ! በዚህ እጅግ ፋታ በማይሰጥ የ100 ሚሊዮን ሺ ጥያቄዎች በግራ በቀኝ በሚያጣደፈዎት፤ ማህበረ ደራጎንም ያለ የሌለ ሃይሉን አሰባስቦ ውጋት በሆነበት ወቅት ዋናውን የኢትዮጵያን ሰቅ ሉላዊ አቅሙን በሚገባ ለመምራት የሚያስችል ውሳኔ በመወሰን ነፍሴን በእልልታ ስለዳበሷት በተለመደው የሻማ ጸሎት ውዳሴ ማርያሜን አድርሻለሁኝ። ይኑርልን የኛ ጠሐይ ዘአፍሪካ! አብይ ኬኛ! ቀሪው ዕድሜዬን አምላኬ ቢፈቅድልኝ ወደ እርስዎ ቢሸጋግርልኝ እልል እያልኩ ነው የምቀበለው። ይኑሩላት ለልልዕት ኢትዮጰያም ብቻ ሳይሆን ለእማማ አፍሪካ!
- የመልካም የሥራ ጊዜ ምኞት።
እጅግ የምሳሳልህ የትውፊት ዘብአደር ረ/ ፕሮፈሰር ነብዩ ባዬ መጪው ዘመን የሐሤት፤ የሰናይ፤ የብሥራት፤ የፍሬዘር፤ የልቅና፤ ልዕልት ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ደምቃ እና በርታ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ የልብ ውስጥ ማህተም ቀለበት ትሆን ዘንድ ተግተህ፤ በርትተህ ከፈጣሪ ጋር አንደምትሰራ አልጠራጠረም። ነፍስህን ስለማውቃት! አንተም እጅህ ዘርጋ አድርገህ እንደተቀብለከው ይህን ቅብዕ አኔ ደግሞ መንፈሴን አፍታትቼ ከልቤ ተቀብዬዋለሁኝ። ሐሤቴ ነው። የእኔ እናት እንኳን ደስ አለህ! ኑርልን። አክብሪህ።
- ተላከ
ከፍቅራዊነት ዩቱብ Sergute Selassie YouTube
ከKenebete ቀንበጥ የአዲስ ቀን ብሎግ ዋና አዘጋጅ።
የኔዎቹ የመልካም የምሥራች ቀን ስለ እናታችሁ ለሚጨንቃችሁ፤ ሁሉም ደስታው የጋራ እና የወል እንደ ሆነ ይገባኛል - ቅኖች ቀና ናቸው እና። ይህ ድል ኢትዮጵያን ቁምነገር ለማድረግ ካለመ ትልም የመነጬ ነው። ዛሬም አዲስ ቀን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰዓታት ሁሉ አዲስ እዬሆኑ ነው። ተመስገን ስለሁላችንም።
ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ